13

.

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው::" የማቴዎስ ወንጌል 7: 4

"እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅናወተት ግዙ።" ትንቢተ ኢሳይያስ 55 : 1

Sunday, August 19, 2012

ጥቂት ስለ "ደብረ ታቦር"

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን!
ደብረ ታቦር ማለት ደብር ተራራ ማለት ሲሆን የታቦር ተራራ የሚል ትርጓሜ አለው፡፡ ከገሊላ ባህር በስተምዕራብ 17 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከናዝሬት ከተማ በስተምስራቅ ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምዕራብ አቅጣጫ ሲገኝ ከፍታው ከባህር ጠለል /ወለል/ 572 ሜትር ነው።
ደብረ ታቦር

  ይህን ተራራ ቅዱስ ማቴዎስና ቅዱስ ማርቆስ በፃፉት ወንጌል ላይ "ረጅሙ ተራራ" ሲሉት ቅዱስ ጴጥሮስ ደግሞ "ቅዱስ ተራራ" ብሎ ጠርቶታል። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን ክብረ መንግስቱን ለተመረጡት ሦስት ሐዋርያት ገልፆበታል። ምንም እንኳን ቅሉ 3ቱ የምሥጢር ሐዋርያት በተራራው ጫፍ ላይ ወጥተው ምሥጢረ መለኮትን ቢመለከቱም በግርጌ ከተዋቸው ከ9ኙ ሐዋርያት ውስጥ 8ቱ ምሥጢረ መለኮቱን ለማወቅ የልቡና መሻት ነበራቸውና ባሉበት ምሥጢሩ ተገልጾላቸዋል። የአስቆሮቱ ይሁዳ ግን በልቡናው ፍቅረ ንዋይ እንጂ ፍቅረ እግዚአብሔር ስላልሰረፀ ከዚህ ታላቅ ምስጢር አልተካፈለም። ምክንያት ያሳጣበት ዘንድ ግን 8ቱን ከእርሱ ጋር ትቶለት ወጥቷል። በተጨማሪም በልበ ሐዋርያት አድሮ የነበረውን የጥርጥር መንፈስ ድል ነስቶበታል።
 በደብረታቦር


v እስራኤል ዘስጋ አህዛብን ድል አድርገውበታል።

      መሳ4፡1-14 “…..የእስራኤል ልጆች በእግዚአብሄር ፊት እንደገና ክፉ ስራ ሰሩ። እግዚአብሄርም በአስር     በነገሰው በከነአን ንጉስ በኢያቢስ እጅ አሳልፎ ሰጣቸው የሠራዊቱም አለቃ በአህዛብ አሪሶት የተቀመጠው    ሲሣራ ነበረ። የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሄር ጨሁ…….”
እስራኤልም ላየ ሃያ ዓመት ያህል አገዛዝ ፀንቶባቸው ተጨንቀው ሲኖሩ እግዚአብሄር ለቅሶና ጨኸታቸውን ሰምቶ የእስራኤል አስር ሺህ ሰራዊት በነቢይት ዲቦራ አማካይነት በእግዚአብሄር ትዕዛዝ ወደ ደብረ ታቦር ለጦርነት ወጡ። እግዚአብሄርም ሞገስ ሆናቸው የአህዛብንም ሰራዊት በሰይፍ ስለት አስደነገጣቸው ሸሹም በምድረ በዳም አለቁ ሲሣራም ሸሽቶ ኢያኤል በተባለች ሴት እጅ ካስማ በጆሮ ግንዱ ተቸንክሮ ሞተ። በመሆኑም ታቦር ተራራ በእስራኤላውያን የሽሽት ሥፍራና የጦር ምሽግ ሆኖ በእግዚአብሄር ፈቃድ ለድላቸው ምክንያት ነው። ዕብ 11፡32-34

v የትርጓሜ ትምህርት ተሰጥቶበታል።

      ሐዋርያት የንባብ ብቻ ሳይሆን የትርጓሜና የሚስጢር ተማሪዎችም ነበሩ። ስለዚህም ነው በሐዋርያት አበው አስተምህሮ የምትመራው ቤተክርስቲያን በአብነት ትምህርት አሰጣጥ ሥርአቷ ንባብ ቤት ፣ትርጓሜ ቤት ፣ሚስጢር ቤት እያለች የምታስተምረው። ማቴ15፡15   በአንድ ወቅት ሊቀነቢያት ሙሴ እግዚአብሄርን  “ፊትህን አሳየኝ” ብሎ ለመነ እግዚአብሄርም “ጀርባይን ታያለህ እንጂ ፊቴን አታይም” ብሎት ነበርና የዚህ ቃል ትርጓሜ በደብረ ታቦር ተተረጎመ። ማለትም አምስት ሺህ ከአምስት መቶ ዘመን ሲፈፀም ሰው ሆኜ ስጋ ለብሼ ኋላ በደብረ ታቦር ታየኛለህ ማለቱ ነበር።ይህንን ቃል ለመፈፀም ነው ሙሴን ከብሄረ ሙታን አምጥቆ ያቆመው። ሌላው ነቢዩ ኤልያስን እግዚአብሄር “በኋለኛው ዘመን ምስክር ትሆነኛለህ” ብሎት ነበርና ይኸውም ሃይለቃል ኤልያስ ከብሄረ ህያዋን መጥቶ “የእኔን የኤልያስን ጌታ ማን ኤልያስ ነው ይልሃል እግዚአ ኤልያስ ይበሉህ እንጂ” ሲል በታቦር ተራራ ፍፃሜ አገኘ። ታያለህ የተባለውም አየ ትመሰክራለህ የተባለውም መሰከረ። ደብረ ታቦር የተባለውም ለዚህ ነው።

v ኑፋቄ/ጥርጥር ተወግዶበታል።

    ጌታችን በቂሳርያ ሃዋርያቱን ከባድ ጥያቄ ጠይቋቸው ነበር።ይኸውም፡- ማቴ16፡13-20 “ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደሆን ይሉታል” የሚል ነበር ይህ የሚስጥረ ስላሴ አብይ ጥያቄ በሌሎች ዘንድ ምላሹ ትክክል አልነበረም ስለዚህ ጌታችን በማንነቱ ላይ የተነገሩት አሉባልታዎች በሐዋርያቱ ዘንድ ምን አይነት አንድምታ እንዳለው ለማጠየቅ “እናንተስ እኔን ማን እንደሆንሁ ትላላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። ቅዱስ ጴጥሮስም በእግዚአብሄር መንፈስ ተቃኝቶ “አንተ ክርስቶስ የህያው የእግዚአብሄር ልጅ ነህ” ብሎ መለሰ ጌታም “በሰማያት ያለው  አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁህ ነው” አለው። ማቴ16፡13-20
      ዓለም በኑፋቄው (በጥርጥሩ) ሲገፉ ሐዋርያትም ያንኑ አሉባልታ እያንፀባረቁና በዓለሙ ወሬ እየተጠራጠሩ እንዳይኖሩ በደብረ ታቦር ላይ በቃል ትምህርት ሳይሆን በተግባር ትምህርት ማንነቱን፣ ግብሩን፣ የእነማን አምላክ መሆኑን ገልጦ አስተማራቸው። ሙሴ፣ ከነቢያት አንዱ ላሉት አምላከ ሙሴ ወነቢያት መሆኑን ፣ ኤልያስ ላሉት አምላከ ኤልያስ መሆኑን ለማስተማር ሙሴንም ኤልያስንም አምጥቶ አሳያቸው። በዚህ ጊዜ በሐዋርያት ልብ ያደረገው የጥርጥር መንፈስ በዚህ ቅዱስ ተራራ ተወግዷል።

v የቅድስት ሥላሴ ምስጥር ተገልጦበታል

   አስቀድሞ በማቴ3፡16፣ ማር1፡9 ፣ሉቃ3፡26 እንደተጠቀሰ ጌታችን በዕደ ዮሐንስ በባህረ ዮርዳኖስ ሲጠመቅ የሥላሴ ምስጢር የሰው ልጅ ሊረዳው በሚችለው መጠን እንደተገለጠ እንደዚሁ ሁሉ በደብረ ታቦር አብ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት” ሲል መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ ደመና ተገለጠ። ይህ ሚስጠር በድጋሜ መገለጡ ሐዋርያት በልቡናቸው የቅድስት ሥላሴ ምስጢር እንዲጸና የጌታችንንም እውነተኛ ማንነቱን እንዲያውቁ ነው።
                       በአጠቃላይ በደብረ ታቦር፡-
·         የክርስቶስ የባህርይ አምላክነት የተመሠከረበት፡ ምሥጢረ ሥላሴ የተገለጠበት፡
·         የሦስቱ ሐዋርያት ባለሟልነት የተገለጠበት
·         የተግባር ትምህርት የተሰጠበት
·         አሉባልታና ተራ ወሬ የከሸፈበት
·         የቅዱሳንን ክብር የተገለጠበት፡ ተራራም እንኳን ‘ቅዱስ’ እንደሚባል የተማርንበት
·         የብሄረ ሕያዋን መኖር የተመሰከረበት
·         የትንሳኤ ሙታን ዋስትና የተገለጠበት ወዘተ….ነው።
 
  የደብረ ታቦር በዓል አከባበር

         ደብረ ታቦር ከዘጠኙ አበይት በአላት አንዱ ሲሆን በምዕመናን ዘንድ ቡሄ(ቡሔ) ተብሎ ይከበራል። ትርጉሙም ቤተክርስቲያናዊ ነው። ይሄም፡-
        ቡሄ ተብሎ በሃሌታው ‘ሀ’ ኀምስ ፊደል ሲፃፍ
        የደመቀ፣ የጎላ፣ ብርሃን፣ የብርሃን በዓል የሚል ትርጓሜ ይሰጣል።ይህም ከጌታችን በደብረ ታቦር ገጹ እንደ ብርሃን ከማብራቱና ልንሱም እጅግ ነጭ አንፀባራቂ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ነው። ማቴ17፡2፣ማር9፡3፤ ሉቃ9፡29
     ይህን በማስመልከትም በደብረ ታቦር በዓል ዋዜማ (ነሃሴ 12) ቀን ችቦ ይበራል። በልጆች ቸዋታም “ቡሄና፣ ቡሄ በሉ ልጆች ሁሉ፣ ቡሄ በሉ ዝም አትበሉ ፣ ቡሄ መጣ ያ መላጣ ቅቤ ቀቡት እንዳይነጣ….” ይባልለታል። በሌላ በኩል ‘ቦኸየ’ ማለት ተገለጠ፣ነጣ፣በራ ሆነ የሚል ትርጉም ሲኖረው የክረምቱ ወቅት መፈፀሙን ደመና መገፈፉን ብርሃን መገለጡን የምናበስርበት ስለሆነ ነው።   
       ቡሔ ተብሎ በሐመሩ’ሐ’ ኀምስ ፊደል ሲፃፍ
       ደስታ፣ፍስሃ ማለት ይሆናል። ይኸውም “ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል” መዝ 88፡12 ተብሎ የተነገረው የትንቢትን ቃል መሰረት ያደረገ ነው። በታቦር የተገለጠው መለኮታዊ ብርሃን እሥስ አርሞንኤም ተራራ ታይቷልና ነው። ለዚህም ነው ሌሊቱ እንደ መዓልት ስላበራ እረኞች ወደ ቤታቸው ያልገቡት።
        አንድም ‘ሐ’ የሰላምታና የቡራኬ ቃል ሲሆን ትርጉሙም “ፍስሃ፣ ሰላም” የሚል ነው። ይኸውም እረኞች በሚያት ብርሃን በደስታ ተሞልተው ስለቀሩ ወላጆቻቸው የሚበሉትን ይዘው ሄደው “በሓ” ብለዋቸዋል። “እንዴት ዋልክ ፣ ጤና ይስጥህ፣ ደስታ ሰላም ለእናንተ ይሁን፣ ጠላትህን ያውድቅ ፣ቢሰኛህን ያርክ” ማለት ነው። አንድም ቡሔ ወላጆች ልጆቻቸውን (እረኞችን) ብርሃናዊውን ክስተት “ምንድነው?” ብለው ቢጠይቋቸው “ብሔ” ብለዋል። ይኸውም በእብራይስጥ ቋንቋ “አምላክ” ማለት ነው።
      ሐዋርያት ብርሃነ መለኮቱ ስለተገለጠላቸው እረኞችም በብርሃኑ ሲቸዋወቱ በማምሸታቸው የደብረ ታቦር በዓል የደቀመዛሙርትና የእረኞች በዓል ይባላል። በሃገራችንም ልጆች (እረኞች) ከየዘመዶቻቸው፣ ከወላጆቻቸው የተሰጣቸውን ሙልሙል ዳቦ ወይም ህብስት በህብረት በመመገብና ከበዓሉ ቀድመው(ገምደው)  ያዘጋጁትን ጅራፍ በማጮህ የችቦ ማብራት በዓሉን ያከብሩታል። ይኸውም ቢሆን ሃይማኖታዊ ትርጓሜ ያለው እንጂ በዘልማድ የሚደረግ አይደለም።
  ሙልሙል ዳቦ(ህብስቱን) በታቦር ዙሪያ ስለነበሩ እረኞች ወላጆች ምግባቸውን ይዘው መሄዳቸውን ያመለክታል።
አንድም ህብስቱ ምሳሌነቱ ለክርስቶስ ነው። “አነ ውእቱ ህብስተ ህይወት ዘወረደ እምሰማያት፤ እኔ ከሰማይ የወረድኩ የህይወት እንጀራ ነኝ” እንዳለ ዮሃ6፡32
   የጅራፍ ጩኸትና ማስደንገጡ ሶስቱ አዕማደ ሐዋርያት(ጴጥሮስ፣ያዕቆብና ዮሃንስ) በድምፀ መለኮት መደንገጣቸውንና መውደቃቸውን ያመለክታል። የጅራፉም ድምፅ በየተራራውና በአፋፍ ላይ እንዲጮህ ይደረጋል እንጂ እንደዘመኑ በየመንደሩ ሰው ለማወክ በርችት ከትውፊታችን ውጪ በሆነ መልኩ በማከናወን የሚገለፅ አለመሆኑን ልብ ይሏል።
    ሌላው በዚህ በዓል የሚከናወነው በዜማ የታጀበ ጭፈራ ነው “ሆያ ሆዬ” እየተባለ ይጨፈራል። ይህ ቃል “ጌታይ ሆይ እመቤቴ ሆይ” እያሉ አባወራውንና እማወራዋን የሚያከብሩበትንና የሚያቆላምጡበት የፍቅር አጠራር ነው እንጂ ጥርጉም የለሽ ቃል አይደለም።ከዚህ ጋር ተያይዞ በዓሉን የሚያወሱ የግጥሞች ስብሰባም በአንድነት ይነገርበታል።

  ለምሳሌ፡-
           ሆያ ሆዬ ሆያ ሆዬ
          ሆይ የኛ ጌታ መድሃኔዓለም
         እባክህ ስጠን ፍቅርና ሰላም
              ሆያ ሆዬ ዝና
              በእምነት እንፅና
ለሐዋርያት ሆ የላከው መንፈስ
ዛሬም ለኢትዮጵያ ሆ ጸጋው ይዳረስ
በበጎ ምግባር ሆ እንድንታደስ
በቅን ልቡና ሆ በጥሩ መንፈስ
የአምላክ በረከት ሆ ለሁላችን ይዳረስ
እያለ ይቀጥላል።
           በረከተ ደብረ ታቦር በሁላችን ላይ ይደርብን መልካም በዓል።
                                   ወስብሃት ለእግዚአብሄር።      

የቦሌ መንበረ ብርሃን ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤ/ክ ሰ/ት/ቤት ትምህርት ክፍል
ነሐሴ 13 ቀን  2004 ዓ.ም