13

.

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው::" የማቴዎስ ወንጌል 7: 4

"እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅናወተት ግዙ።" ትንቢተ ኢሳይያስ 55 : 1

Friday, November 25, 2011

ቅድስት አትናሲያ


ባለፈው የዮሐንስ ሐጺርን ታሪክ ስንመለከት የቅድስት አትናስያን ታሪክ እንደማቀርብ ቃል ገብቼ ነበር፡፡ ከዚህ እንደሚከተለው የቅድስት አትናስያ ታሪክ በጣም በአጭሩ የቀረበ ሲሆን ሰፊ የሆነውን የቅድስት አትናስያን ታሪክ በተለያዩ ክፍሎች በመከፋፈል በሌላ ጊዜ የምመለስበት ይሆናል ፡፡

“መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ፡ ዘጠና ዘጠኙን በበረሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሄድ ከእናንተ ማን ነው? ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ይሸከመዋል፣  ወደ ቤትም በመጣ ጊዜ ወዳጆቹንና ጎረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ፡- የጠፋውን በጌን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ ይላቸዋል፡፡ እላችኋለሁ እንዲሁም ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል በማለት ጌታችን ለፈሪሳውያንና ጻፎች የንስሐን  ታላቅነት ለማስተማር በምሳሌ ነግሯቸዋል፡፡" ሉቃ.  15፤4-7፡፡
የቅድስት አትናሲያ  ታሪክ የንስሐን ታላቅነት ልንማርበት የሚያስችለን ታሪክ ነው ፡፡ ቅድስት አትናሲያ ሚኑፎ /በአረፈችበት ቦታ ስም/ በመባል ትታወቃለች፡፡
የቅድስት አትናሲያ ወላጆች በግብጽ የሚኖሩ ባለጸጎች ነበሩ፡፡ እሷም በወላጆቿ ቤት በመልካም ምግባር ታንፃ አደገች፡፡ እናትና አባቷ ከሞቱ በኋላ በጎ ነገርን አያደረገች ለመኖር ቤቷን ለእንግዶች ማረፊያ፣ የተራቡ የተጠሙትን ለማስተናገጃ እንዲሆን ፈለገች፡፡ በተቻላት ሁሉ የተቸገሩትን እየረዳች ትኖር ዘንድ መልካም ነገርን አሰበች፡፡ ያሰበችውንም ትፈጽም ጀመር፡፡ ወደ እርሷ ቤት የሚመጡትን እንግዶች ሁሉ ተቀብላ አክብራ ታስተናግዳቸው ነበር፡፡ በቤቷ የደከማቸው ያርፋሉ፡፡ የተራቡ ይመገባ የተጠሙ ይጠጣሉ፡፡ የታረዙ ይለብሳሉ፡፡ የተቸገሩ ይረዳሉ፡፡

ይኽ መልካም ሥራዋ በቤቷ ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ በየቦታው የሚገኙ ገዳማትን ትረዳ ነበር፡፡ ለመነኮሳቱ የሚያስፈልጋቸውን ትልካለች፡፡ ከአንዱ ገዳም ወደ ሌላ ቦታ ለተልዕኮ የሚጓዙትን መነኮሳት በቤቷ ተቀብላ ታስተናግዳለች፡፡ ቤቷ ማረፊያቸው ነበር፡፡ በዚህ መልካም ምግባሯ የአካባቢዋ ሕዝብ ያከብራታል፡፡ በገዳም ያሉ መነኮሳትም ስለበጎ ሥራዋ ይወዷት ነበረ፡፡

አትናሲያ በዚህ ሁኔታ ስትኖር የመልካም ነገር ሁሉ ጠላት የሆነው ሰይጣን ታጥቆ ተነሳ፡፡ ግብራቸው በከፋ ሰዎች ልቡና አድሮ እርስዋ ዘንድ ቀረበ፡፡ እነዚያ ክፉዎች ሰዎች ወደ አትናሲያ እየሄዱ ተቀራረቡ፡፡ በጓደኝነት እየተጠጉ ተለማመዷት፡፡ የዓለምን የተመቸና የተደላደለ ኑሮ አስደሳችነቱን ይነግሯት ጀመር፡፡ በሀብቷ፣ በመልኳ፣ በቁመናዋ የዚችን ዓለም ደስታ የርስዋ ማድረግ እንደምትችል ያጫውቷታል፡፡

በየጊዜው በዙሪያዋ ተሰብስበው የሚነግሯትና የሚያባብሏት ሁሉ የልቡናዋን ሓሳብ እየከፈለው መጣ፡፡ ከመልካም ምግባሯ ይልቅ የዓለሙ ደስታ አጓጓት፡፡ በጎ ሥራዋን ዘነጋችው፡፡ ከዕለት ወደ ዕለት እየተለወጠች ከመልካም ነገር እየራቀች ወደ ኃጢአት ሥራ እየተሳበች መጣች፡፡

የተራቡ ይመገቡበት፣ የተቸገሩ ይረዱበት የነበረ ቤት፣ መነኮሳት ያርፉበትና ይስተናገዱበት የነበረ፣ ለመልካም ተግባር ያገለግል የነበረ ቤት ተለወጠ፡፡ የዝሙት ቤት አደረገችው፡፡ እርሷም በመልኳና በቁመናዋ ወንዶችን እያባበለች በዝሙት ተግባር ተሰማራች፡፡ ኃጢአትን አብዝታ ትፈጽም ጀመር፡፡

ይኽም ሥራዋ ከምትኖርበት አካባቢ አልፎ በሚያውቋት መነኮሳትም ዘንድ ተሰማ፡፡ ወሬው በአስቄጥስ ገዳም ደረሰ፡፡ ገዳመ አስቄጥስ ከዓባይ መጨረሻ ደቡባዊ ምዕራብ አቅጣጫ 65 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ አሁን ዋዲ አልናትሩን በሚባል፣ ከደቡም ምሥራቅ ወደ ሰሜን ምዕራብ 30 ኪሎ ሜትር ያህል በተዘረጋው ሸለቆ ውስጥ፣ በሊቢያ በረሃ አካባቢ የሚገኝ ገዳም ነው፡፡
የአትናሲያን ነገር በገዳሙ የሚኖሩት አረጋውያን ቅዱሳን እንደሰሙ ስለእርሷ እጅግ አዘኑ፡፡ መልካም ሥራዋን ያውቁ ስለነበረ ዝም ብለው ሊተዋት አልፈቀዱም፡፡ ተመካከሩ፡፡ ከአለችበት ድረስ መክሮና አስተምሮ የሚመልሳት እንደሚያስፈልግ ተገንዝበዋል፡፡ ሆኖም የአስቄጥስን ገዳም በረሃ አቋርጦ አትናሲያ ዘንድ መሄድ አለበት፡፡ ለዚህም የሚሆን ትሁትና ታዛዥ ሰው ያስፈልጋል፡፡ እናም በታዛዥነቱ የሚታወቀውን አባ ዮሐንስ ሐጺርን መረጡት፡፡
አባ ዮሐንስ ሐጺር ታሪኩን ባለፈው እንደተመለከትነው ወላጆቹ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያደረባቸው በእምነት የጸኑ በመልካም ምግባር የጠነከሩ ነበሩ፡፡ አባ ዮሐንስ ከወላጆቹና ከአንድ ወንድሙ ተለያይቶ ወደ ገዳም የገባውም ገና በልጅነቱ ነው፡፡ባለፈው እንደገለጽነው የገዳሙ አበምኔት ወድቆ ያገኘውን ደረቅ እንጨት አንስቶ   “ ይኽንን ደረቅ እንጨት ወስደህ ትከለው፡፡ ሳታቋርጥም ውሃ አጠጣው” ብሎ አዘዘው፡፡ አባ ዮሐንስ የደረቀ እንጨት አይጸድቅም ብሎ አልተናገረም፡፡    “እሺ” ብሎ በትህትና ታዘዘ፡፡ ደረቁን እንጨት ተክሎ ከ18 ኪሎ ሜትር ርቀት በቀን ሁለት ጊዜ ውሃ እያመላለሰ ያጠጣው ነበር፡፡ ሦስት ዓመት ያማቋረጥ ውሃ ሲያጠጣ ቆይቶ የደረቀው እንጨት ለመለመ፡፡ አድጎ ዛፍ ሆኖ ጣፋጭ ፍሬ አፈራ፡፡ አበምኔቱ ከዛፉ ፍሬ ወስዶ ወደ ታላላቆቹ መነኮሳት ዘንድ ይዞት ሄደ፤ “ እንካችሁ የታዛዥነትን ፍሬ ብሉ”  ብሎ ሰጣቸው፡፡ ይኸው በአባ ዮሐንስ ሐጺር ቅን ታዛዥነት ያደገ ዛፍ ዛሬም በገዳሙ ይገኛል፡፡

እነዚያም የገዳሙ አረጋውያን መነኮሳት አባ ዮሐንስ ሐጺርን ጠርተው ስለ አትናሲያ ነገሩት፡፡ ወደ እርሷ ሄዶ ነፍሷን ያድን ዘንደ ለመኑት፡፡ አባ ዮሐንስም ትእዛዛቸውን ተቀበለ፡፡ በጸሎታቸው እንዲረዱት አሳስቦ አስቸጋሪውን የበረሃ ጉዞ ሊያያዘው ተነሳ፡፡ ከረጅሙ የበረሃ ጉዞ በኋላ አትናሲያ ወዳለችበት ቦታ ደረሰ፡፡ ከቤቷም ሄዶ እንግዳ ተቀባይዋን  “ ለእመቤትሽ ስለ እኔ ንገሪ” በማለት እንድታገናኘው ጠየቃት፡፡ እንግዳ ተቀባይዋም ወደ እመቤቷ ሄዳ የእንግዳውን መልእክት ነገረች፡፡ አትናሲያ መልእክቱን በሰማች ጊዜ እንደ ለመዱት   “እንግዶቿ” ለረከሰ ሥራ ፈልገዋት የመጡ መሰላት፡፡ በመኝታ ክፍሏ ውስጥ እንደሆነች ተዘገጃጀች፡፡ ተኳኩላ አጊጣ በአልጋዋ ላይ ሆና እንግዳውን አስጠራችው፡፡

አባ ዮሐንስ እየጸለየ ይጠብቃል፡፡  “በሞት ጥላ ውስጥ ብሄድም እንኳን ክፉን አልፈራም አንተ ከእኔ ጋር ነህና” እያለም ይዘምር ነበር፡፡ የአትናሲያ ጥሪ ደርሶት እንግዳ ተቀባዩዋ እየመራችው ወደ መኝታ ቤቷ ገባ፡፡ አየችው፡፡ ጠበቀችው፡፡ የዛሬው እንግዳዋ ከዚህ በፊት እንደምታስተናግዳቸው የለመደቻቸው እንግዶች ዓይነት አይደለም፡፡ አስተያየቱም አኳኋኑም የተለየ ነው፡፡ አባበለችው፡፡ በአልጋዋ ላይ ከአጠገቧ እንዲቀመጥ ጋበዘችው፡፡ አባ ዮሐንስ ከጎኗ ተቀመጠ፡፡ ጠበቀች፡፡  እንግዳዋ በዝምታ ቆየ ከዚያም ራሱን ዘንበል አድርጎ ያለቅስ ጀመር፡፡ አትናሲያ በእንግዳዋ አኳኋን ተገርማ  “ለምን ታለቅሳለህ ? ” ስትል ጠየቀችው፡፡ ቀና አለና በአትኩሮት አያት፡፡ አስተያየቱ ንጹሕና የአባትነት አስተያየት ነው፡፡ ለተጎዳ ለተጨነቀ፣ በችግር ላይ ላለ ልጅ የሚያዝን፣ ከልብ የሚያስብ አባታዊ አስተያየት፡፡
“አትናሲያ ሰይጣናት በላይሽ ሲጫወቱ አየኋቸው” መልሷን አልጠበቀም   “ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስን ለምን አሳዘንሽው የቀድሞ በጎ ሥራሽን ትተሽ ወደ ጥፋት ሥራ ተመልሰሻልና አላት፡፡

አትናሲያ የተናገራትን ቃል ስትሰማ ደነገጠች፡፡ የቀደመ ስሜቷን አኳኋና ወዲያው ተለወጠ፡፡ ተንቀጠቀጠች፡፡ በዚያች አፍታ ራሷን ወደ ውስጧ አየች፡፡ መረመረች፡፡ በኃጢአት ያለፈ ሕይወቷ አንድ በአንድ ታያት በእጅጉ መበደሏ ጥፋቷ ታሰባት ባለፈ ውድቀትዋ ሁሉ ተጸጸተች፡፡ በሰራችው  ሥራ አዘነች እናም እያለቀሰች    “ምን ይሻለኛል?” በማለት ጠየቀችው፡፡ አባ ዮሐንስ ኀጺርም የእግዚአብሔርን መሐሪነትና ቸርነት ነገራት፡፡ በርጋታ እየመከረ ካስተማራት በኋላ “ንስሐ ግቢ” አላት፡፡ የኃጢአቷን ብዛት የበደሏን ታላቅነት ስታስበው   “እግዚአብሔር ይቀበለኛልን ? ” ስትል ጠየቀችው፡፡ እርሱም   “አዎን” በማለት የእግዚአብሔር ይቅር ባይነት አስረዳት፡፡

ከዚያ በኋላ አትናሲያ ተረጋጋች፡፡ በቃ ሕይወቷ በኃጢአት እንደአደፈ መቆየት የለበትም፡፡ ወሰነች፡፡ ከአለችበት ድረስ የመጣላትን የእግዚአብሔርን ቸርነት ማሳለፍና ማጣት የለባትም፡፡ ከአባ ዮሐንስ ምክር በኋላ ዓለም ኃላፊ መሆኑን ተገንዝባ ዘለዓለማዊውን ሕይወት መርጣለችና አላቅማማችም፡፡ ቤት ንብረቷን ለማሰብ ወደኋላ አላለችም፡፡  “ወደምትሔድበት ከአንተ ጋር ውሰደኝ” ስትል ለመነችው፡፡ እሱም   “ነይ ተከተይኝ”  አላት፡፡

ወርቅና አልማዝ ጌጦችን አልፈለገችም፡፡ ልብሶቿን አልመረጠችም፡፡ ከገንዘቧ ምንም ምን አልያዘችም፡፡ ያን ጊዜውኑ ፈጥና ተነስታ አባ ዮሐንስን ተከተለችው፡፡


ቀኑን ሙሉ ሲጓዙ ውለው በመሸ ጊዜ ለማደር ወደ ጫካ ውስጥ ገቡ፡፡ በዚያም ለእርሷ መኝታ የሚሆን ቦታ አዘጋጅቶ “እስኪነጋ በዚህ አረፍ ብለሽ ተኚ፡፡ እኔም ወደዚያ እሆናለሁ” አላት፡፡ ይህንንም ብሎ ከእርሷ ራቅ ብሎ ተገለለና እየጸለየ ብቻውን ተቀመጠ፡፡

አባ ዮሐንስ በሌሊቱ እኩሌታ ለጸሎት በተነሣ ጊዜ ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርስ የብርሃን ምሰሶ ተተክሎ አየ፡፡ የእግዚአብሔርም መላእክት የከበረች ነፍስዋን ተሸክመው ሲወጡ በአድናቆት ተመለከተ፡፡ በነጋም ጊዜ ወደ አትናሲያ ሄደ፤ ዐርፋም አገኛት፡፡ እጅግም አዘነ፡፡ ስለእርሷም ይገልጥለት ዘንድ እየሰገደ ወደ እግዚአብሔር ለመነ፡፡ ወደ እርሱም “ከቤቷ በወጣች ጊዜ እግዚአብሔር ንስሐዋን ተቀብሎ ኃጢአትሽ ተሠረየልሽ ብሏታል” የሚል ቃል መጣ፡፡ አባ ዮሐንስ ይኽን እንደሰማ የአትናሲያን ነፍስ መዳን ተረድቶና በሐሴት ተሞልቶ ወደ ገዳመ አስቄጥስ ሄዶ ለአረጋውያን የሆነውን ሁሉ ነገራቸው፡፡ ቅዱሳን አባቶች እርሱ እንዳያት ሁሉ እነርሱም ማየታቸውን ነገሩት፡፡ በአንድነት ሆነው የኃጢአተኛን ወደ ንስሐ መመለሱን እንጂ ሞቱን የማይሻ እግዚአብሔር አመሰኑት፡፡

የቅዱሳን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር የተመሰነ ይሁን፡፡
ለእኛም ዕድሜ ለንስሐ ዘመን ለፍስሐ ያድለን ፡፡

Source: http://www.melakuezezew.info/2011/11/blog-post_3342.html

የአባ ዮሐንስ ኀፂር ሕይወት -ክፍል 2


ዮሐንስ ኀፂር ቤተሰቦቹ ያወጡለት ስም ኮሎቦስ የሚል ነው፡፡ በሀገራቸው ቋንቋ አጭር፣ ድንክ ማለት ነው፡፡ በገዳመ አስቄጥስ በተጋድሎ ጸንተው ክብር ካገኙ ቅዱሳን መካከል አንዱና በግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ታላቅ ክብር ያለው አባት ነው፡፡ ቤተክርስቲያናችንም ከምትዘክራቸው ቅዱሳን መካከል አንዱ ነው፡፡ /ነሐሴ 29/ ፍልስተ አጽሙን ቤተክርስቲያን ታከብራለች፡፡ 
አባ ዮሐንስ ኀፂር በላይኛው ግብኝ “ቴባን” በምትባል መንደር በ339 ዓ.ም. ገደማ ተወለደ፡፡ ምንም እንኳን ቤተሰቦቹ የተትረፈረፈ ምድራዊ ሀብት ባይኖራቸውም ትዳራቸው በፍቅርና በፈሪሃ እግዚአብሔር ያጌጠ ነበር፡፡ ገና ለጋ ሕፃን  ሳለ የዘወትር ምኞቱ መንኩሶ መኖር ነበር፡፡ ውሎ ሲያድር በልቡና ያሰበውን እውን ያደርግ ዘንድ መንፈሰ እግዚአብሔር አነሣሣው፡፡ መላ ዘመኑን በሥርዓተ አበው በተጋድሎ ሊፈጽም ራቅ ወዳለ በረሃማ ገዳም ሄደ፡፡ ይህችውም ገዳመ አስቄጥስ ናት፡፡

ዮሐንስ በፍጹም  ትኅትና ወደ ገዳሙ አበምኔት ወደ አባ ባሞይ ቀርቦ የዘወትር ምኞቱን ነገራቸው፡፡ ልጅነቱን ተመልክተው /አሥራ ስምንት ዓመቱ ነበር/ በወቅቱ ከባድና አስቸጋሪ የሆነውን የምንኩስና ሕይወት ለዚያውም በገዳም አስቄጥስ ሊቋቋም እንደማይችል ፤ የገዳሙ መነኮሳት ሁሉ ብዙ ደክመው ራሳቸውን ከመመገባቸውም በላይ በጾምና በስግደት ብዙ ተጋድሎ እንደሚያደርጉ፣ /ለመኝታቸው/ የሰሌን ምንጣፍ እንኳን ስለሌላቸው ከበረሃው አሸዋ ላይ እንደሚተኙ ካስረዱት በኋላ ወደ አገሩ ተመልሶ ትዳር ይዞ በንጽሕና  በቅድስና ይኖር ዘንድ መከሩት፡፡ ከመጀመሪያውኑ በፈቃደ እግዚአብሔር መጥቷልና አባቴ ሆይ በትእዛዝህ ሁሉ እየተመራሁ ያዘዝከኝን እየፈጸምኩ እኖር ዘንድ መጥታቸለሁ፡፡ ልጅነቴን ዓይተህ እንዳትመልሰኝ በእግዚአብሔር ስም እለምንሃለሁ፡፡ ደግሞም አንተ ብትቀበለኝ እግዚአብሔር መልካሙን ሁሉ እንደሚያደርግልኝ አምናለሁ” ሲል አበምኔቱን ለመነው፡፡

አባ ባሞይ ነገሩ ቢከብደው ስለ ዮሐንስ የሚያደርገውን ይገልጥለት ዘንድ ወደ እግዚአብሔር አመለከተ፡፡ በዚያችም ሌሊተ ከእግዚአብሔር የተላከ መልአክ ተገልጦ “ዮሐንስ ለእግዚአብሔር የተመረጠ ዕቃ ነው፡፡ በመሆኑም እንድትቀበለው እግዚአብሔር አዝዞሃል” ሲል አስረዳው፡፡ በዚህ መሠረት ጊዜው ሲደርስ የገዳሙ መነኮሳት ተሰብስበው ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት ጾመው ጸልየው ሥርዓተ ምንኩስናውን ፈጸሙለት፡፡
ምንም እንኳን በዘመኑ በገዳሙ ያለው ሥርዓት የተጠናከረ ባይሆንም ዮሐንስ ብዙ ምግባር ትሩፋትን ያለሃኬት ይፈጽም ጀመር፡፡ ሃሳብን ከሚከፋፍል፣ ልቡናን ለምኞት ከሚጋብዝ ንግግርና ከሌሎች ጋር ጊዜን በጨዋታ ማባከንን ከራሱ አራቀ፡፡ እንደወጣኒ ሳይሆን በፍጹማን አምሳል ረሃብና ጥሙን እየታገሰ በትሕርምት፣ በጾም፣ በጸሎት፣ በሰጊድ ጸና ፡፡ ከመምህሩ ከአባ ባሞይ የተማራቸውን አጽንዖ በዓትን፣ ማስተዋልን፣ ጸጥታና መረጋጋትን፣ በመከራ መጽናትን፣ ትሕትናን፣ ታዛዥነትን ገንዘብ አደረገ፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ባሞይ ዮሐንስን ይመክረው ዘንድ ተነሣ፡፡ ብዙ ምክር ከሰጠውም በኋላ ከእርሱ ጋረ ማደር እንደሌለበት ነገረው፡፡ በዚህ መሠረት ዮሐንስ ለሰባት ቀናት ወደ መምህሩ በኣት ሳይገባ በውጪ ለዚያውም ከገዳሙ ክልል ውጭ ቆመ፡፡ ይህም ሳያንሰው አባ ባሞይ ዕለት ዕለት እየሄደ ትዕግሥትን እንዲማር በዱላ ይመታው ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆንበት ዮሐንስ እየሰገደ “አባቴ ሆይ ይቅር በለኝ” በማለት  ይለምነው ነበር፡፡ በሰባተኛው ቀን አባ ባሞይ ወደቤተክርስቲያን ሲሄድ ስድስት መላእክት ስድስት አክሊል ይዘው በዮሐንስ ራስ ሲያቀዳጁ አየ፡፡ በዚህ ተገርሞ ዮሐንስን ወደ በኣቱ መለሰው፡፡
ታዛዥነትና ተዘክሮተ እግዚአብሔር አባ ዮሐንስ ከሚታወቅባቸው መልካም ምግባራት መካከል የሚጠቀሱለት ናቸው፡፡ አንደ ቀን አባ ባሞይ ዮሐንስ ኀፂርን የደረቀ እንጨት ተክሎ ለምልማ እስክታፈራ ድርስ ውኃ እንዲያጠጣት አዘዘው፡፡ ያለማንጎራጎር በትኅትና ሆኖ አሥራ ሁለት ምዕራፍ ያህል ከሚርቅ ቦታ በቀን ሁለት ጊዜ ውኃ እያመላለሰ ያጠጣው ጀመር፡፡ በሦስተኛው ዓመት ያቺ በትር ለምልማ፣ አብባ ያማረ ፍሬ አፈራች፡፡ አባ ባሞይ በዮሐንስ ታዛዥነት እጅግ ተደሰተ፡፡ ፍሬውን ለቅሞ ለገዳሙ መነኮሳት እንካችሁ ይህ የታዛዥነት ፍሬ ነው እያለ ሰጣቸው፡፡ መነኮሳቱም ይህን ተአምር ባዩ ጊዜ አደነቁ፡፡ ለቅን ታዛዥ ሰው ይህ ጸጋ የሰጠ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡ በ402 ኛ.ም. በግብፅ ይኖር የነበረው ፓስቱሚያ /postumian/  በገዳሙ የአትክልተ ሥፍራ የአባ ዮሐንንስ እንጨት ለምልማና ብዙ ቅርንጫፎች አውጥታ ማየቱን መስክሯል፡፡
ዮሐንስ በልቡናው ዘወትር እግዚአብሔርን ያስብ ነበር፡፡ ከማሰብ ለአፍታ ያህል እንኳን አያቋርጥም፡፡ በዚህም በዙሪያው ያሉትን፣ በእጅ የሚሠራውን እስከመርሳት ደርሶ ነገረ እግዚአብሔርን በማሰብ ልቡናው ይመሰጥ ነበር ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም አርምሞን /ጸጥታን/ ገንዘብ በማድረግም ይታወቃል፡፡ የአርምሞን ጠቃሚነት አስመልክቶም ልጄ ሆይ መጥፎ ሃሳብ በአእምሮህ ተመላልሶ ልቡናህን መሳት ደረጃ ብትደርስም ዝም በል፣ አታጉረምርም በማለት ይመክር ነበር፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥ የበለጠ አፍአዊና ውሳጣዊ ዝምታ የሚገባ መሆኑን አስመልክቶም በቤተክርስቲያንም ውስጥ ቅዱሳት ምሥጢራት የሚፈጸሙበተ ቦታ መሆኑን ተገንዝበን ከምንጊዜውም በላይ ጸጥታንና አርምሞን እንያዝ ብሎ አስተምሯል፡፡
አባ ዮሐንስ ኀፂር ራስን የመግዛት ጥቅምን በሚመለከትም “አንድ መነኩሴ ከፍጹምነት ደረጃ መድረስ የሚችለው መላ ሕዋሳቱን ጠብቆ በልቡናው ተዘክሮተ እግዚአብሔርን ሲይዝ ነው” ብሏል፡፡ ከዚህ እምነቱ የተነሣም ስለጊዜያዊ ደስታ ማሰብና ማውራትን ይጠላ ነበር፡፡ በዚህም ፈንታ አፍአዊና ውሳጣዊ ሕዋሳትን የሚገባ መሆኑን በመግለጥ ያስተምር ነበር፡፡ የዚህም ምክንያት “ሰው አብዝቶ ሕዋሳቱን በገዛ ቁጥር በልቡናው የሚመላለሱ ምክንያቶች ከውስጡ እየጠፉ ይሄዳሉ፡፡ ይህም ልቡናን ሰላማዊና የተረጋጋ ያደርጋል” በማለት ያስረዳል፡፡
አባ ዮሐንስ ይህን በመሰለ መንፈሳዊ ተጋድሎ በርትቶ ሳለ አበምኔቱ አባ ባሞይ ለአሥራ ስምንት ዓመታት በደዌ ዘእሴት ክፉኛ ተይዘው ነበርና፡፡ እርሳቸውን ያስታምም ነበር፡፡ በስተመጨረሻም አባ ባሞይ ሊሞቱ ሲሉ የገዳሙን መነኮሳት አስጠርተው “አባ ዮሐንስን አክብሩት፣ ታዘዙለት፣ እርሱ በምድር የሚኖር መልአክ ነው እንጂ ሰው አይደለም” በማለት ክብሩ ከሰማያውያን መላእክት ደረጃ መድረሱን መሰከሩለት፡፡
በእንዲህ ዓይነት ተጋድሎ ጸንቶ ሳለ በአካባቢው የሚገኙ አረማውያን መነኮሳቱን ሊያርዱ፣ ሊያቃጥሉ መጡ፡፡ ዮሐንስም ወደ አባ እንጦንስ ገዳም ወደ ቁልዝም ሄደ፡፡ መሄዱም ሞትን ፈርቶ ለመሸሽ አልነበረም፡፡ ነገር ግን በአረማዊው ወንድሙ እጅ ሞቶ እርሱን በመግደላቸው ለዘላለም ሞት እንዳይዳረጉ በማዘን ነበር፡፡ በቁልዝም ገዳምም ዋሻ አዘጋጅቶ በብሕትውና ተጋድሎውን ተያያዘው፡፡
በአንድ ወቅትም የገዳሙ ምርት በመሰብሰብ ላይ ሳሉ አልታዘዝ ብሎ መነኮሳቱን ያስቸገረ አንድ መነኩሴ ይመክረው ዘንድ ለአባ ዮሐንስ አቀረቡለት፡፡ እርሱም አልታዘዝም ያለውን ይቅር በለኝ እያለ ጀመር፡፡ ላመት ሙሉ ጥቂት ጨው ብቻ ያላት ቁራሽ ደረቅ ዳቤ እየበላ አልታዘዝ ስላለው መነኩሴ አለቀሰ፡፡ ጌታ ሆይ ፍጥረትህን ሳላውቅ አናድጄዋለሁ፡፡ አሁንም አንተ ይቅር በለኝ በማለት ብዙ ጸለየ፡፡ በዚህ ጸሎቱም በደለኛውን ወደ ታዛዥነት መለሰው፡፡
አባ ዮሐንስ በጸሎቱ በለቅሶው ወደ እግዚአብሔር ከመለሳቸው ኃጥአን መካከል አትናስያ አንዷ ናት፡፡የአትናሲያን ታሪክ በሚቀጥለው እንመለከተዋለን ፡፡በዚህ ዓይነት ኃጥአንን ከእግዚአብሔር እያስታረቀ በአካባቢው ያትን ጎሳዎእ እያጠመቀ በቅድስና ዘመኑን ፈጸመ፡፡ በዘመኑ ፍጻሜም ደቀ መዛሙርቱ ቀርበው የመጨረሻ ምክሩን እንዲሰጣቸው ለመኑት፡፡ ብዙ ከመከራቸው በኋላ “. . .የራሴን ሥራዊ ፍላጎት በፍጹም አልከተልም፡፡ በራሴ ያልሠራሁትንም ሥራ ሌሎች ይሠሩ ዘንድ በፍጹም አልመክርም” በማለት አካፈላቸው፡፡ ብዙ ቃል ኪዳን ተቀብሎ በክብር ባረፈባት ዕለት ቅዱሳን መላእክት በመዝሙር በይባቤ ክብርት ነፍሱን ወደ ገነት አሳረጓት፡፡

የአባ ዮሐንስ ኀፂር ረድኤት በረከት አይለየን፡፡ 

ዮሐንስ ሐፂር 1


ዮሐንስ ሐፂር

ዮሐንስ ሐፂር በላይኛው ግብጽ ቴባን በምትባል መንደር በ339 ዓ.ም ተወለደ፡፡ ወደ ገዳም አስቄጥስ የገባው በልጅነቱ ሲሆን ያን ጊዜ አበምኔቱ አባ ባሞይ ይባል ነበር፡፡ አባ ዮሐንስ በተመሥጦው እና በታዛዥነቱ የታወቀ አባት ነበር፡፡ በመጀመርያው የአስቄጥስ ጥፋት ጊዜ ገዳሙን ትቶ ወደ ቁልዝም ተጓዘ፡፡ ያረፈውም በዚያ ነው፡፡
የዮሐንስ ሐጺርን ትምህርቶች ከዚህ እንደሚከተለው አቅርበነዋል ፡፡

1. የጠላቱን ከተማ ለመቆጣጠር የዘመተ ንጉሥ አስቀድሞ የውኃውን መንገድ ይዘጋል፣ የእህሉንም መግቢያ ይይዛል፡፡ ያን ጊዜ ጠላቶቹ ይራባሉ፣ ይጠማሉ፡፡ በመጨረሻም እጃቸውን ይሰጣሉ፡፡ የነፍስን ፆር ለማሸነፍም በተመሳሳይ መንገድ መጠቀም ይገባል፡፡ አንድ ሰው በጾምና በረኃብ ከጸና የነፍሱ ጠላቶች ይዳከማሉ፡፡

2. እኔ በትልቅ ዋርካ ሥር የተቀመጠንና አራዊት ሊጣሉት የመጣን ሰው እመስላለሁ፡፡ ሊቋቋማቸው እንደማይችል ከተረዳ ሸሽቶ ወደ ዛፉ በመውጣት ነፍሱን ያድናል፡፡ በእኔም የተፈጸመው ይኼው ነው፡፡ በበዓቴ ተቀምጬ ክፉ ሃሳቦች ሊቃወሙኝ ሲመጡ፣ ልቋቋማቸው እንደማልችል ባወቅኩ ጊዜ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ሸሽቼ እመሽጋለሁ፡፡ በዚያም ከጠላቶቼ ፍላፃ እድናለሁ፡፡

ዮሐንስ ሐፂር
3. መለወጥ የምትፈልግን ነፍስ በተመለከተ አባ ዮሐንስ እንዲህ አለ፡- በአንዲት ከተማ ውስጥ ብዙ ወዳጆች የነበሯት አንዲት አመንዝራ ሴት ነበረች፡፡ ከገዥዎቹ አንዱ ቀረባትና ‹መልካም ሴት ለመሆን ቃል ግቢልኝና አገባሻለሁ› አላት፡፡ እርሷም ቃል ገባችለትና ተጋቡ፡፡ ወደ ቤቱም ወሰዳት፡፡ የቀድሞ አፍቃሪዎቿ ያቺን ሴት ፈለጓት፣ እርስ በርሳቸውም ‹ያ ልዑል ወደ ቤቱ ወስዷታል፤ ወደ ቤቱ ብንሄድ ይቀጣናል፡፡ ነገር ግን በጓሮ በኩል እንሂድ፣ ለርሷም እናፏጭላት፣ የፉጨቱን ድምፅ ስትሰማ ከድርሱ ወርዳ ወደኛ ትመጣለች፣በዚህም ያለ ችግር እናገኛታለን› ተባባሉ፡፡ ወደ ቤቷም ጓሮ ተጉዘው ያፏጩ ጀመር፡፡ እርሷ ግን የፉጨቱን ድምፅ ስትሰማ ጆሮዎቿን ደፈነች፡፡ ወደ ውስጣዊው እልፍኝም ገባች፡፡ በሩንም ጥርቅም አድርጋ ዘጋች፡፡ ይህቺ ሴት የኛ ነፍስ ምሳሌ ናት፡፡ ወዳጆቿ የተባሉም ፈተናዎቿ ናቸው፤ ገዥ የተባለውም ክርስቶስ ነው፣ እልፍኝ የተባለውም ዘለዓለማዊው ቤት ነው፡፡ እነዚያ የሚያፏጩት ክፉዎች አጋንንት ናቸው፤ ነገር ግን ነፍስ ሁልጊዝም በክርስቶስ አምባነት ትሸሸጋዋለች፡፡

4. አባ ዮሐንስ ልቡናው ከእግዚአብሔር ጋር ስለነበረ ምድራዊ ነገሮችን ይዘነጋ ነበር፡፡ አንድ ቀን አንድ ወንድም ቅርጫት ሊወስድ ወደ አባ ዮሐንስ በኣት መጣ፡፡ አባ ዮሐንስም ምን ፈልጐ እንደሆነ ጠየቀው፡፡ ያም ወንድም ‹ቅርጫት ፈልጌ ነው› አለው፡፡ አባ ዮሐንስ ወደ በኣቱ ተመለሰና ዘንግቶት ወደ ሽመና ሥራው አመራ፡፡ ጥቂት ቆይቶ ያ ወንድም አንኳኳ፣ አባ ዮሐንስም ወጥቶ ‹ምን ፈልገህ ነው› አለው ‹ቅርጫት ስጠኝ ብየህ ነበር› ሲል መለሰለት፡፡ ተመልሶ ወደ በኣቱ ሲገባ ልቡናው በሰማያዊ ነገር ስለተመሰጠ ዘንግቶት ወደ ሽመናው ሥራ እንደገና ገባ፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ ያ ወንድም ሲያንኳኳ አባ ዮሐንስ ተመልሶ ወጣና ‹ምን ፈልገህ ነው?› አለው፡፡ ‹ቅርጫት ስጠኝ ብየህ ነበር› አለና መለሰለት፡፡ አባ ዮሐንስም እጁን ይዞ እየጐተተ ወደ በኣቱ አስገባውና ‹ቅርጫት ከፈለግህ ያዝና ሂድ፣ በእውነቱ እንዲህ ላሉት ነገሮች እኔ ጊዜ የለኝም› አለው፡፡

5. አንድ ቀን አንድ ሰው ወደ አባ ዮሐንስ ሐፂር በኣት መጣና ሥራውን እያየ ያመሰግነው ጀምር፡፡ አባ ዮሐንስ ዝም  አለውና ገመድ መሥራቱን ቀጠለ፡፡ እንግዳውም እንደገና ወሬውን ቀጠለ፣ አባ ዮሐንስም ጸጥ አለው፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ እንግዳው ወሬ ሲያበዛ፡፡ ‹አንተ ወደ በኣቴ በመግባትህ እግዚአብሔር ወጥቶ ሄደ› ብሎ ተናገረው፡፡

6. አባ ዮሐንስ እንዲህ አለ፡- ‹የብሕትውናን ኑሮ በከተማ ውስጥ የሚኖር አንድ ሽማግሌ ነበረ፡፡ ያ ሰው በከተማው ውስጥ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠውና ባለዝናም ነበር፡፡ አንድ አረጋዊ አባት ከማረፉ በፊት ያንን ሰው ሊያየው እንደሚፈልግ ለዚያ ሰው ጥሪ ደረሰው፡፡ ያም ሰው በቀን ከተጓዝኩ ሰዎች ስለሚከተሉኝ ለኔ የተለየ ክብር ይሰጡኛል ብሎ አሰበ፡፡ ስለዚህም በሌሊት ሰው ሳያየው ለመጓዝ ወሰነ፡፡ በመሸ ጊዜም አሁን ማንም አያየኝም ብሎ ተነሣና ጉዞ ጀመረ፡፡ ነገር ግን ሁለት መላእክት ታዝዘው መብራተ ይዘው መንገዱን ይመሩት ነበር፡፡ ይህንን የተመለከቱ የከተማው ሰዎች ወደ እርሱ ተሰባሰቡ፣ መላ ከተማው ያንን የመላእክት ብርሃን እያየ ከኋላ ተከተለው፡፡ ከክብር በሸሸ ቁጥር የበለጠ ክብርን አገኘ፡፡ በዚህም ‹ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፣ ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ከፍ ይላል› የሚለው የወንጌል ቃል ተፈጸመ፡፡ (ሉቃ. 14.11)

7. አባ ጴሜን አባ ዮሐንስ እንዲህ ብሎ መናገሩን ገልጧል ‹ቅዱሳን በአንድ ቦታ የበቀሉ ዛፎችን ይመስላሉ፡፡ ከአንድ ምንጭ ጠጥተው፣ ልዩ ልዩ ዓይነት ፍሬ ያፈራሉ፡፡ የአንድ ቅዱስ ሥራ ከሌላው ይለያል፣ ነገር ግን በሁሉም አድሮ የሚሠራው አንድ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡

ዋቢ   በበረሓው ጉያ ውስጥ


በረከተ ቅዱሳን ይደርብን
 
Source: http://www.melakuezezew.info/2011/11/blog-post.html

Thursday, November 24, 2011

ጾመ ነቢያት

እንኳን ለጾመ ነቢያት በሰላም እና በጤና አደረሳችሁ

 

ዘመኑ ጾመ ነቢያት የተባለበት ምክንያት ነቢያት የተናገሩት ትንቢት ስለ ተፈጸመበት እንዲሁም በየዘመናቱ የተነሡ ነቢያት እግዚአብሔር ወደፊት ሊያደርግ ያሰበውን በእምነት ዓይን እያዩ ምሥጢር ተገልጦላቸው የራቀው ቀርቦ የረቀቀው ገዝፎ እየተመለከቱ ያዩትም መልካም ነገር እንዲደርስላቸው ስለ ጾሙ ስለ ጸለዩ ነው፡፡ነቢያት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ፣ ወደ ግብፅ ስለ መሰደድ፣ በባሕረ ዮርዳኖስ ስለመጠመቅ፣ በትምህርተ ወንጌል ጨለማውን ዓለም ስለ ማብራቱ፣ ለሰው ልጆች ድኅነት ጸዋትወ መከራ ስለመቀበሉና ስለ መሰቀሉ፣ ስለ ትንሣኤው፣ ስለ ዕርገቱና ስለ ዳግም ምጽአቱ ትንቢት ተናግረው አላቆሙም፤ 

ለአዳም የተሰጠው ተስፋ ተገልጦላቸው ለተናገሩት ትንቢት ፍፃሜ እንዲያደርሳቸው ፈጣሪያቸውን ተማፀኑትም እንጂ፡፡ በየዘመናቸው «አንሥእ ኃይለከ፣ ፈኑ እዴከ፤ ኃይልህን አንሳ እጅህንም ላክ» እያሉ ጮኹ፡፡ በጾምና በጸሎት ተወስነውም ሰው የሚሆንበትን ጊዜ በቀናት፣ በሳምንታት፣ በወራትና በዓመታት ቆጠሩ፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ ኤርምያስ ስለ ሥጋዌው ትንቢት በተናገረ በ446 ዓመት ጌታችን ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው ሆኗል፡፡

ነቢያት ተስፋው በዘመናቸው ተፈጽሞ በዓይነ ሥጋ ለማየት ባይችሉም እግዚአብሔር«የማያደርገውን አይናገር
 የተናገረውን አያስቀር» ብለው አምነው ከወዲሁ ተደሰቱ፡፡ለዘመነ ሥጋዌ ቅርብ የነበሩት እነ ኢሳይያስ ጾሙ እንዴት 
መፈጸም እንዳለበትተናግረዋልም፡፡ ኢሳ 58-1፡፡በመሆኑም በጌታ ልደት ትንቢተ ነቢያት ስለ ተፈጸመበት
ይህ ጾም «የነቢያት ጾም» ይባላል፡፡ የወልደ እግዚአብሔርን ሰው መሆን ያስተማሩበትየሰው ልጆች ተስፋ የተመሰከረበት 
የምሥራቹ የተነገረበት ስለሆነም «ጾመ ስብከት»ይባላል፡፡
             ዘመነ ስብከት
ከታኅሣሥ 7 ቀን እስከ ታኅሣሥ 13 ቀን ድረስ ያሉት ዕለታት ናቸው፡፡ ምን ጊዜም ወደ ታኅሣሥ 6 አይወርድም ወደ 14ም አይወጣም፡፡ ስብከት ማለት ዐዋጅ ትምህርት ማለት ነው፡፡ ይህም ከልደተ አብርሃም እስከ ልደተ ዳዊት ያለው ትውልድ የሚታሰብበት ፤ ሙሴ በኦሪት፣ ነቢያት በትንቢት፣ ዳዊት በመዝሙሩ በብዙ ምሳሌ ይወርዳል ይወለዳል ሲሉ የተናገሩት የሚታሰብበት ወቅት ነው፡፡ መዝ.143-7 ፤ ኢሳ 64-1፡፡
የሚዘመረው መዝሙር «ወልደ መድኅነ ንሰብክ ዘእምቅድመ ዓለም ሀሎ፤ ከዓለም በፊት የነበረውንና መድኃኒት የሆነውን ወልድን እንሰብካለን» የሚል ነው ቅዱስ ያሬድ፡፡ ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል ብለው ትንቢት የተናገሩለትንና ሱባዔ የቆጠሩለትን ሐዋርያት ያላቸውን ትተው ተከተሉት ፈቃዱንም ፈጸሙ፡፡ ስለዚህ ምእመናን ክፉ ሐሳባቸውን አርቀው ርኩሰትን አስወግደው ፍጹም ለእግዚአብሔር እንዲገዙ ትምህርት ይሰጣል፣ ስብከት ይሰበካል፡፡ የሚነበበውም ምንባብ ይህንኑ የሚያመለክት ነው፡፡ ዮሐ.1-44-49 ፤ ዕብ.1-1-2፡፡
ብርሃን
ከስብከት ቀጥሎ ያለችው ሰንበት ስትሆን እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት አስተምህሮ ከልደተ ዳዊት እስከ ፍልሰተ ባቢሎን ያለው 14 ትውልድ ይታሰብበታል፡፡ ክቡር ዳዊት «አቤቱ ብርሃንህንና እውነትህን ላክ፤ እነርሱ ይምሩኝ ወደ ቅድስናህ ተራራና ወደ ማደሪያህ ይውሰዱኝ» /መዝ. 42-3/ እያለ ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስ ከርሱ ወገን እንዲወለድ ትንቢት ስለተናገረ ይህ የሚታሰብበት ነው፡፡ ነቢዩ ዓለም በጨለማ ስለሆነች ብርሃንህን ላክ፣ ሐሰትና የሐሰት አባት ነግሦባታልና እውነትህን ላክ አለ፡፡ ወልድን ላክልን ማለቱ ነው፡፡ ይህንም ቅዱስ ዮሐንስ «ብርሃን ዘመጽአ ውስተ ዓለም፤ ብርሃን ወደ ዓለም መጣ» ብሎ ሲመሰክር ጌታም ራሱ «እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም» ብሎ ተናግሯቸዋል፡፡ ዮሐ. 8-12 እንዲሁም ብርሃንን እውነት ማለቱ ኢየሱስ ክርስቶስን ነው፡፡ ላክልን ሲል ደግሞ መንፈስ ቅዱስን ስደድልን ማለቱ ነው፡፡
ከጨለማ ወደ ብርሃን አውጣን፣ ሥጋህንና ደምህን ስጠን ሲልም ነው፡፡ በዚህ ወቅት የሚዘመሩት መዝሙራት «ብርሃን ዘመጽአ ውስተ ዓለም አቅዲሙ ነገረ በኦሪት ከመ ይመጽእ ወልድ በስብሐት ወይዜንዎ ለጽዮን በቃለ ትፍሥሕት፤ ብርሃን ወደ ዓለም መጣ፣ የምስጋናን ቃል ለጽዮን የሚነግራት ወልድ በክብር፣ በጌትነት እንደሚመጣ አስቀድሞ በኦሪት ነገረ፤ አስታወቀ፡፡» የሚሉ ናቸው፡፡ ንስሐ ከመግባት ቸል እንዳይሉ ይነግራቸዋል፡፡ ነቢያት የጥል ግድግዳን ሰብሮ መለያየትን አጥፍቶ ከጨለማ ወደ ብርሃን የሚያወጣቸውን ሽተው ውረድ ተወለድ አድነንም እያሉ ጮኹ፣ እውነተኛ ብርሃን ጌታችን ጊዜው ሲደርስ ወደ ዓለም ወጣ፡፡ በመምጣቱም በጨለማ ያለው በብርሃን እንዲገለጥ ለሰው ልጆች እግዚአብሔርን የሚያውቁባት ዕውቀት ተሰጠች፡፡
ኖላዊ
ኖላዊ ተብሎ የሚጠራው ከብርሃን ቀጥሎ ያለው ሳምንት ነው፡፡ የቃሉ ፍች እረኛ ማለት ነው፡፡ እረኞች ለበጎቻቸው የሚያስፈልጋቸውን ሣር ውኃ ሳያጓድሉ እንዲጠብቁ እግዚአብሔርም ሕዝቡን በነፍስ በሥጋ የሚጠብቅ ቸር እረኛ ነው፡፡ ይኽንን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሲያብራሩ ከፍልሰተ ባቢሎን እስከ ልደተ ክርስቶስ ድረስ ያለው 14 ትውልድ ነው ይላሉ፡፡ በዚህ ዘመን እሥራኤላውያን ከሀገራቸው ተሰደው በባቢሎን 70 ዘመን ከኖሩ በኋላ ዘሩባቤልን አንግሦላቸው ይዟቸው እንዲመለስ ተደርጓል፡፡ ከዚያ በፊት እሥራኤል ጠባቂ እንደሌለው መንጋ ተበታትነው ሲኖሩ ነቢያት ከኪሩቤል ላይ የሚገለጥ እረኛቸው እንዲገለጥ የእሥራኤል ጠባቂያቸው ሆይ፣ አድምጥ እያሉ የጠየቁበት መታሰቢያ ነው፡፡ መዝ.79-1-3፡፡ 
መዝሙሩም «ኖላዊ ዘመጽአ ውስተ ዓለም ወልዱ ወቃለ እግዚአብሔር ዘወረደ እምላዕሉ፤ የእግዚአብሔር ልጅና ቃሉ የሆነ ክርስቶስ ከላይ የወረደ ወደ ዓለም የመጣ እረኛ» የሚል ሲሆን የሚነበበው ደግሞ አንቀጸ አባግዕ የተባለው የዮሐንስ ወንጌል ክፍል ነው፡፡ ዮሐ.10-1-22፡፡ እረኛ የሌለው በግ ተኩላ ነጣቂ እንዲበረታበት በበደሉ ከትጉኅ እረኛው የተለየው የሰው ልጅም በሲኦል አጋንንት በርትተውበት ሲጠቀጠቅ ኖሯል፡፡ እንዲሁም ከመንጋውና ከእረኛው የተለየ በግ እንዲቅበዘበዝ አምላኩን ዐውቆ አምልኮቱን ከመግለጽ የወጣው ሕዝብ በየተራራው መስገጃዎችን እየሠራ የሚታደገውን አምላክ በመፈለግ ሲንከራተት ኖሯል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ «እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበር» እንዳለ፡፡ 1ኛ ጴጥ.2-25፡፡ ነቢያት በዓለም ተበትነው የሚቅበዘበዙትን ሕዝቡን በቤቱ ሰብስቦ የሚጠብቃቸው እውነተኛ ቸር እረኛ እንዲወለድ ስለተናገሩ ያን ለማስታወስ ሳምንቱ ኖላዊ ተባለ፡፡ 
ገሃድ/ ጾመ ድራረ ጥምቀት
ይህ ጾም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ጥምቀት በማሰብ የጥምቀትን ዋዜማ መጾም ነው፡፡ ይህም ማለት በጥምቀት ዋዜማ ከምግብ መከልከል ነው፡፡ የሚቆርብ ሰው አክፍሎ የሚያድር ስለሆነም የጥምቀትን ድራር መጾም ነው፡፡ ሐዋርያት «ልደት ጥምቀት ዓርብ ረቡዕ ቢውል በሌሊት ቀድሰው ሥጋውን ደሙን ይቀበሉ፤ ከሌሊቱ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ጹሙ ብለው አይፍረዱ» ብለዋል /ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15/፡፡ የልደትና የጥምቀት በዓል በረቡዕ ወይም በዓርብ ቀን ቢሆን በበዓለ ሃምሳ የሚበላውን የጥሉላት ምግብ በጠዋት በመብላት ምእመናን በዓሉን እንዲያከብሩ ታዟል፡፡
ይህም እነዚህ ሁለቱ ታላላቅ የእግዚአብሔር በዓላት በመሆናቸው ነው፡፡ የጥምቀት በዓል በረቡዕና በዓርብ በሚውልበት ጊዜ በረቡዕና በዓርብ ፈንታ ማክሰኞንና ሐሙስን በመጾማችን ሁለት ሥራ ይፈጸምልናል፡፡ በዚህም የጾምና የበዓል ማክበር ሥራ ይከናወናል፡፡ የጥምቀትን ዋዜማ ጥሉላት መባልዕትን መተው ነው፡፡ ይህንንም እንደ ዘይቤው ገሀድ ይለዋል፣ መገለጫ፣ ግልጥ፣ ይፋ መሆን ማለት ነው፡፡ እንዲሁም ጋድ ይለዋል፣ ለውጥ፣ ልዋጭ ማለት ነው፡፡ ጥምቀት ረቡዕ ዓርብ ሲውል በዚያ ለውጥ ማክሰኞ ሐሙስ ይጾማልና ጋድ አለው፡፡ እንዲሁም አንድ ጊዜ ሲጾም አንድ ጊዜ ሲቀር እንዳይረሳና ቅዳሜ ወይም እሑድ በሰንበት ቀን ይጾሙ ዘንድ አይቻልም፣ ነገር ግን እህል ውኃ እንጂ ጥሉላት ከመብላት መጠበቅ ይገባል፡፡
ልደት የሚውልባቸው ረቡዕና ዓርብ ቢሆኑ የፍሥክ /የሚበላባቸው/ ቀናት ሆነው እንዲከበሩ ሐዋርያት ያዘዙ ቢሆንም በዋዜማው የሚገኙት ማክሰኞና ሐሙስ ከጾመ ነቢያት ጋር የተያያዙ ስለሆኑ መጾማቸው ግድ ነው፡፡ ሆኖም የነቢያትን ጾም የማይጾሙ ሰዎች በመላው የጾሙ ቀናት ሲበሉ ቆይተው በዋዜማው ብቻ ገሀድ ነው ብለው ይጾማሉ፡፡ ነገር ግን ለጾመ ነቢያት ገሀድ የለውም፡፡ ጾሙ የጥምቀት ብቻ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ለጾመ ነቢያት ገሀድ እንዳለው የሚናገሩም አሉ፡፡ ለዚህም የሚያቀርቡት ማስረጃ እስከ ምሽት መጾሙን ነው፡፡ ይህም «አድልው ለጾም፤ ለጾም አድሉ፡፡» እንዲሉ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ቢጾም የሚያከራክር ወይንም ስህተት ነው የሚያሰኝ አለመሆኑን መረዳት ይገባል፡፡
ነቢያት ይወርዳል፣ ይወለዳል ብለው የተናገሩት ቃል ይፈጸም ዘንድ የሰው ልጆችም ድኅነት ማረጋገጫ እውን ይሆን ዘንድ እንደ ጾሙ እንደ ጸለዩ በልደቱም እንስሳት፣ ሰዎች እንዲሁም መላእክት በአንድነት በደስታ እንደዘመሩ የእኛም ደስታ የተረጋገጠበት ነው፡፡ በመሆኑም በፍቅር፣ በጾም በጸሎት ዛሬም እናስበዋለን፡፡ ነቢያት በረከት እንዳገኙ እኛም ከእግዚአብሔር በረከት እናገኛለን፡፡ ለዚህም አምላካችን ይርዳን ፡፡
ጾሙን ጾመ ሥርየት ፤ ጾመ መድኃኒት ያድርግልን! 
ለብርሃነ ልደቱ በሰላም እና በጤና ያድርሰን !
ጾመን ለማበርከት ያብቃን - አሜን !!

Source: http://www.melakuezezew.info/2011/11/blog-post_23.html

Monday, November 21, 2011

ውዳሴ ከንቱ

ውዳሴ ከንቱ የሚለው ቃል የማይረባ የማይጠቅም  ውዳሴ የሚል ትርጓሜ ያለውሲሆን  ውዳሴ  ብጡል (የተናቀ፤ተርታ) ውዳሴ ተብሎም ይጠራል፡፡የቃሉ ትርጉም  በዚህ መልኩ የሚፈታ  ይሁን እንጂየማይጠቅምከመሆን አልፎ  ሰውን ሊጎዳ የሚችል ነገር በመሆኑ  የቤተክርስቲያናችን መጻሕፍት  አጥብቀን   ልንሸሸው እንዲሚገባ ያስተምራሉ፡፡
         ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግሩ ስር   ተቀምጣ ቃላት ታዳምጥ የነበረችውን የማርታ እህት  ማርያምንማርያምስ የማይቀሟትን  በጎ ዕድል መረጠችሉቃ10÷42  ብሎ ያመሰገነበትን  ቃል አበው ሲተረጉሙመማር ውዳሴ ከንቱ  የለውም “  አላውቅም  ማለት ነውና፡፡  ስለዚህም  አጋንንት  የማይቀሟትን (ዋጋዋን ) የማያስቀሩባትን መማርን መረጠች ማለት ነው ብለው መተርጎማቸው ‹‹ውዳሴከንቱ›› የሰውን የልፋት ዋጋ  በምድራዊ  ክብር  የሚያስቀር  ከንቱ ነገር መሆኑን ያስረዳል፡፡  አበው ከውዳሴ ከንቱ  እንድንጠበቅ ማስተማራቸው  የመልካም ስራችን  ዋጋ  ሰዎች  በሚያቀርቡልን የምስጋና ስጦታ ምክንያት በምድር  እንዳይቀርብን በማሰብ ነው፡፡ በወንጌልም ጌታ  ከሰዎች ምስጋና  በመሻት መልካም  ሥራቸውን  በሰው  ፊት ስላደረጉ ፈሪሳውያን  ሲናገር  “እሙንቱሰ ነሥኡ እሴቶሙእነዚህስ  ዋጋቸውን  ተቀብለዋልማቴ6÷2  በማለት ከሰው የተቀበሉት ምስጋና  ሰማያዊ  ዋጋቸውን እንዳሳጣቸው አስተምሯል፡፡
     እንዲህ ስንል ግን በሰው የተመሰገነ ሁሉ ውዳሴ ከንቱ  ሆኖበታል   ያልተመሰገነ ደግሞ አልሆነበትም  ማለትም  አይደለም፡፡  በልቦናው   የመመስገን መሻት  ኖሮት  መልካም ሥራ  የሠራ  ነገር ግን   በለስ ያልቀናው  ያልተመሰገነ ሰው ሊሰርቅ ሄዶ አጥር ፀንቶበት፣  ውሻ ጮሆበት፣ጠባቂ ነቅቶበት  የተመለሰ ሰውን  ይመስላል፡፡   መሻቱ  በልቦናው  ስላለ ሰዎች  ባያመሰግኑትም  ቅሉ ለመመስገን  በመሻት አስቀድሞ  ወድቋልና  ከሰው ውዳሴ  ሳይፈልግ  የሠራ ሰውም  ሰው  ቢያመሰግነው  እንኳ አይሻውምና  በውዳሴ  ከንቱወደቀ አያሰኝም፡፡  ይህም ውዳሴ ከንቱ ኃይል አግኝቶ ሰውንየ ሚጥለው  የተዘጋጀ ልቦና ሲኖረው መሆኑን  እንገነዘባለን፡፡
    ውዳሴ ከንቱ  በሦስት ዓይነት  መንገድ ሲቀርብ እንደ  አቀራረቡና አቀባበሉም ሰዎችን ሊጎዳ ይችላል፡፡
.  ሰዎች ስለ እኛ
  ውዳሴ ከሰዎች ለእኛ በሚቀርብበት ወቅት  የሚያመሰግነን ሰው ማን ነው? ምስጋናውስ ለእኛ የሚገባን  ነውን? የሚሉትን ጥያቄዎች  ራሳችንን  መጠየቅ ከጉዳት  ይጠብቀናል፡፡ የሚያመሰግነን  ሰው ማነው? የሚለውን ማሰባችን  ተወዳጅነትን  ለማትረፍና በአፀፋ ለማመስገን  ከሚመጡ ሰዎች  ሲጠብቀን ምስጋናው ለእኔ ይገባልን? የሚለውን ማሰብ ደግሞ ምስጋናውን ይገባናል ብሎ ከመቀበል ይጠብቀናል፡፡ በወንጌል ጌታችንቸር መምህር ሆይብሎ የቀረበው ሰው  መመስገንንና  ተወዳጅነትን ለማትረፍ  ሲሉ ምስጋና   ከሚያቀርቡ ሰዎች የሚመደብ ነው፡፡ (ማር 10÷17) ምስጋናንለእኔ የሚገባ ነውን?” ብሎ መርምሮ መቀበልን የተማርነው ከቅዱሳን እናቶቻችንና ከቅዱሳን አባቶቻችን ነው፡፡
   ክብር ይግባትና በሚገባት ግብር የተመሰገነች እመቤታችንእፎኑ ከመ ዝኑ እንጋ አምኃ ይትአምኁ - እንዲህ ያለውን ሰላምታ እንዴት ይቀበሉታል?” ሉቃ 1÷29 ማለቷ ቅዱሳን በሚገባቸው ገንዘብ ቢመሰገኑ እንኳ (በትህትና) አይገባንም እንደሚሉ የሚያስረዳ ነው፡፡
     በትንሣኤ ዘጉባኤምተርቤ አብልታችሁኛልና፣ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና ….” ተብለው የሚመሰገኑ ቅዱሳንመቼ ተርበህ አበላንህ?መቼ ተጠምተህ አጠጣንህ?.....” ሲሉ ሠርተው እንዳልሰሩ ሆነው በትህትና እንዲመልሱ ተጽፏል፡፡ ማቴ 25÷44
አቡነ ተክለሃማኖትም ከብዙ ትሩፋትና ተጋድሎ በኋላአሌ ሊተ ወይ ሊተ ለዘኢገበርኩ ምንተ - ወዮ ለኔ ምንም ላልሠራሁትእያሉ ምርር ብለው ማልቀሳቸውን ገድላቸው ዘግቦታል፡፡
እኛም ምንም እንኳ ከእነርሱ መዐርገ ትህትና ደርሰን አይገባንም ማለት ባንችል በብሩህ ፊት ሆነን ውዳሴን እያጣጣሙ ከመቀበል መለየት ይገባናል፡፡ይልቁንም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ እንዳሉት በምንመሰገንበት ወቅት የከፉ ኃጢአቶቻችንን እያሰብን ራሳችንን መገሰፅ ይገባናል፡፡
. እኛ ስለ ሰዎች 
ምስጋና ከእኛ ስለ ሰዎች በሚቀርብበት ወቅትም ልናስተውላቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ፡፡በእርግጥ ሰዎችን ማመስገንና እንዲመሰገኑ መፈለግ ከክርስቲያኖች  የሚጠበቅ የበጎ ምግባር መገለጫ  ነው፡፡
እንደ ዲያቢሎስ መመስገን ብቻ እንጂ ሰውን ማመስገንና ማበረታታት የማይፈልጉ ሰዎች አሉና፡፡ ነገር ግን የምስጋናውን ልክ የምናልፍ ከሆነ ለተመስጋኙ ጥቅም ከመሆን ይልቅ ፈተና የምንሆንበት ዕድል የሰፋ ነው፡፡በውዳሴ ከንቱ የወደቀ ከሆነም መሰናክል የሆንነው እኛ በመሆናችን እንቀጣለን፡፡ ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ቢኖር የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ከጥልቅ ቢጣል ይሻለው ነበርተብሎ ተጽፏልና፡፡ ማቴ 18÷6 ስለዚህም መመስገን የሚገባውን ሰው መለየትና መመስገን በሚገባው ልክ ማመስገን ከእኛ የሚጠበቅ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ደግሞምከጠላት መሳም የወዳጅ ንክሻ ይሻላልተብሎ እንደ ተፃፈ ለሰዎች ከሚቀርብላቸው ምስጋና ይልቅ ወቀሳና ምክር ለመሻሻል ይጠቅማቸዋልና ማመስገን ብቻ ሣይሆን መውቀስና መምከር ተገቢ ነው፡፡ጌታችን የአይሁድ መምህር የሆነ ኒቆዲሞስንአንተ የአይሁድ መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን?” ብሎ አለማወቁን ገስፆ መምህርነቱን አመስግኖ እንደ ተናገረው ዮሐ. 3÷10 ፡፡
. እኛ ስለ እኛ
 ውዳሴ ከንቱ ሰዎች እኛን በሚያመሰግኑበት ወቅት ባለን አቀባበል ወይም እኛ ለሰዎች በምናቀርበው ምስጋና ልክ ብቻየ ሚመዘን አይደለም፡፡እኛ ስለ ራሳችን ባለን አስተያየትና በምናቀርበው ምስጋናም ጭምር እንጂ፡፡ በእርግጥ ለራስ ጥሩ አመለካከት መያዝና ራስን ማበረታታት ተገቢ ነው፡፡ይህ ሁኔታ ልክ ከሌለው ግን ለራሳችን ብቻ የምናዜም በውይይት መሃል እኛ ብቻ መነሳት የምንፈልግ ከእኛ ይልቅ ሌላ ሰው ቢነሣ ቅር የሚለን ገፍተንም ስለራሳችን ጥሩነት የምናወራ እንሆናለን፡፡ በቅዱስ መጽሐፍየሌላ ሰው አፍ ያመስግንህተብሎ መጻፉ ሰው በራሱ አንደበት መመስገን እንደሌለበት የሚያስረዳ ነው፡፡በወንጌልም የታዘዙትን ሁሉ በፈፀሙ ጊዜ አገልጋዮች ምን ማለት እንዳለባቸው የተቀመጠላቸው ትዕዛዝ  “የማንጠቅም ባሪያዎች ነን በሉ”  የሚል ነው ሉቃ. 1710 ፡፡ ይህም ሰው ከልክ አልፎ ለራሱ ቦታ እንዳይሰጥና በውዳሴ ከንቱ  እንዳይወድቅ ለመጠበቅ  የታዘዘ ነው፡፡ ርዕሳችን  ውዳሴ ከንቱ በመሆኑ  በማይጠቅም  ውዳሴ ላይ ብቻ አተኮርን  እንጂ የሚገቡና  የሚጠቀቅሙ የታዘዙም  ምስጋናዎች አሉ፡፡የማይጠቅም ውዳሴየሚለውን ርዕስ  በራሱ  የሚጠቅም ውዳሴ መኖሩን  የሚጠቁም  ነው፡፡
የሚጠቅም ውዳሴ (ውዳሴ ዘይረብሕ)
    ቅድስት ቤተክርስቲያናችን መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት በማድረግ ጎጂነቱን አውቃ የከለከለችው ከንቱ ምስጋና እንዳለ ሁሉ ተገቢ ነው ይጠቅማል ብላ የፈቀደችው ያዘዘችውም የምስጋና ዓይነት አለ፡፡ ይህ የምስጋና አይነት የተለየ ስያሜ  ባይኖረውም  ከውጤቱ በመነሳት ውዳሴ ዘይረብሕ (የሚረባ-ረብ ያለው ውዳሴ)፣ ውዳሴ ዘይበቊዕ (የሚጠቅም ውዳሴ) ልንለው እንችላለን፡፡
    ለአምላካችን እግዚአብሔር፤ለቅዱሳን፤ በሥራቸው ሊመሰገኑ ለሚገባቸው ቅን ሰዎች፤ አንዳንዴም በምስጋና ልናበረታቸው ለሚገቡ ድኩማን የሚደረጉ ምስጋናዎች ከዚህ ዓይነቱ ምስጋና ውስጥ የሚመደቡ ናቸው፡፡
     ለእግዚአብሔርና ለቅዱሳን የሚቀርቡ ምስጋናዎች አመስጋኙን ብቻ ሲጠቅሙ የቀሩት ደግሞ የሚጠቅሙበት ጎዳና ቢለያይም አመስጋኙንም ተመስጋኙንም የሚጠቅሙ ናቸው፡፡ ምስጋና አመስጋኙን ብቻ ሊጠቅም እንደሚችል የሚያሳይ በቅዳሴ ማርያም ላይ “ዘንተ ቅዳሴ ዘይቄድስ ካህን አኮ ማርያምሃ ዘይቄድስ አላ ውእቱ ይትቄደስ - ይህን ቅዳሴ የሚቀድስ ካህን ማርያምን የሚቀድሳት አይደለም ራሱ ይቀደሳል እንጂ” የሚል ንባብ ይገኛል፡፡ ከጥቅማቸው ከፍታ አንፃር ካየነው ደግሞ ለእግዚአብሔርና ለቅዱሳን የሚቀርብ ምሥጋና ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ራሱን የቻለ ሰፊ ሐሳብ በመሆኑም በዚህ ጽሑፍ የምንዳስሰው አይሆንም፡፡ ይልቁን ከሰዎች ጋር ባለን ማኅበራዊ ሕይወት ስለሚያጋጥሙንና ጥንቃቄ ስለሚፈልጉ ምስጋናዎች በጥቂቱ እንመለከታለን፡፡
       መልካም ለሚሠሩና ቅን ለሆኑ ሠዎች ምስጋና እንደሚገባቸው በቅዱስ ዳዊት የመዝሙር መጽሐፍ “ወለራትዓን ይደልዎሙ ክብር - ለቅኖችም ምስጋና ይገባቸዋል  መዝ 33:1 ተብሎ የተጻፈ ሲሆን ልጁ ሰሎሞን ደግሞ መልካም ስለምትሠራ ልባም ሴት በጻፈበት የምሳሌ ክፍል  ልጆችዋ ይነሣሉ ምስጋናዋንም ይናገራሉ ባልዋ ደግሞ እንዲህ ብሎ ያመሰግናታል።መልካም ያደረጉ ብዙ ሴቶች አሉ አንቺ ግን ከሁሉ ትበልጫለሽ። ውበት ሐሰት ነው ደም ግባትም ከንቱ ነው እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን እርስዋ ትመሰገናለች። ከእጅዋ ፍሬ ስጡአት ሥራዎችዋም በሸንጎ ያመስግኑአት።”  ምሳ 31:28 በማለት ጽፏል፡፡ ከእነዚህ ጥቅሶች መልካም ለሚሠሩ ሁሉ ምስጋና የሚገባ መሆኑን ብንረዳም ጎን ለጎን ልናደርጋቸው የሚገቡ በቂ ጥንቃቄዎችም አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል፡-
፩- በመጠንና በተገባ ነገር ማመስገን
ምስጋናው ያልተመጠነና የተጋነነ ከሆነ በአንድ በኩል ተመስጋኙ በደንብ አንዲሠራ ከማድረግ ይልቅ በምስጋናው እየተደሰተ ተዘናግቶ እንዲኖር የሚያደርገው ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ በውዳሴ ከንቱ እንዲወድቅ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ አመስጋኙም ለውድቀት ምክንያት በመሆኑ ከመቀጣት አይድንም፡፡
፪-ከጕሕሉት(ከሽንገላ) እና ከውሸት የፀዳ መሆን
ብዙ ሰዎች ዘመን የወለደውን ንጉስ የወደደውን ተከትለው በልባቸው ባያምኑበት እንኳ መስሎ ለማደር ብለው ሰዎችን ያመሰግናሉ፡፡ ተመስጋኙ ይህ ከልብ ነው፣ ይህ አይደለም ብሎ መለየት ባይችልም ልብና ኲላሊትን የሚመረምር አምላክ ይፈርድብኛል ብለን “በአፉሆሙ ይድህሩ ወበልቦሙ ይረግሙ - በአፋቸው ይመርቃሉ በልባቸውም ይረግማሉ፡፡” መዝ 62:4 ከተባሉት እንዳንቆጠር መጠንቀቅ ይገባናል፡፡
፫ ምስጋናን ሱስ እስኪሆን አለማስለመድ
      ምስጋና ከተለመደ እንደሌሎቹ ልማዶች ሱስ ሊሆን ይችላል፡፡ አበው “ኀዲገ ልማድ ፅኑዕ ውእቱ - ልማድን መተው ከባድ ነው” እንዳሉ በውዳሴ ሱስ የተጠመደ ሰውም ከዚህ ልማድ መውጣት ሊከብደው ሲቀር ቅር ሊሰኝ አልፎም ለምን አልተመሰገንኩም ብሎ ሊቆጣ ይችላል፡፡ ሰው እንዲህ ካለ ክፉና አስተቺ ልማድ ውስጥ እንዲገባ ምክንያት መሆን ከባድ ፍርድ ያለበት በመሆኑ ሱስ እስኪሆንበት በነጋ ጠባ ሰውን ከማመስገን መጠበቅ ተገቢ ነው፡፡
      በቅዱሳት መጻሕፍት መልካም ለሚሠሩና ቅን ለሆኑ ሰዎች ብቻ ሳይሆን ምስጋናው ለማይገባቸውና የእነርሱ ባልሆነ ነገር ሰዎችን ማመስገን ጠቃሚ ሆኖ የሚገኝበት ጊዜ እንዳለም ተጽፏል፡፡ በሥጋዊ ትምህርት ጎበዝ ያልሆነውን ተማሪ ጎበዝ በማለት ተነሳሽነቱ እንዲጨምርና እንዲሻሻል ማድረግ እንደሚቻል በመንፈሳዊ ሕይወቱ ያልበረታን ሰውንም በማመስገን ማበርታት እንዲሁ ይጠቅማል፡፡ ይህን በተመለከተ በመጽሐፈ መነኮሳት ላይ “ወድሶ ለሰብእ በዘኢኮነ ሎቱ ወድሶ ለሰብእ በዘኢኮነ ድልወቱ እስመ ወድሶ ለሰብእ ይወስክ ኃይለ - ሰውን የእርሱ ባልሆነና ባልተገባው ነገር አመስግነው ምስጋና ለሰው ኃይልን ይጨምራልና” ተብሎ ተጽፏል፡፡
     ከላይ ስለተገለጡት ተገቢ ምክንያቶች ማመስገን በዚህ ጽሑፍ ተነግረው የማያልቁ እጅግ ብዙ ጥቅሞች አሉት፡፡ “ብፁዕ ሕዝብ ዘየአምር የብቦ - እልልታን (ምስጋናን) የሚያውቅ ሕዝብ ምስጉን ነው፡፡” መዝ 89:15 ተብሎ እንደተጻፈ ሰዎችን ለማመስገን መነሳት በራሱ የሚያስመሰግን ደግ ተግባር ነው፡፡ ቁጣው የራቀ ምሕረቱ የበዛ አምላክ “በወንድሙላይየሚቆጣሁሉፍርድይገባዋል” ማቴ 5:22
       
      ብሎ ካስተማረን ወንድሙን ያመሰገነ ምን ይነት ሽልማት ይገባው ይሆን? “ዘይፀርፍ ላዕለ እኁኁ ዘረፈኬ ላዕለ እግዚአብሔር ልዑል - በወንድሙ ላይ የተሳደበ በእግዚአብሔር ላይ ተሳደበ” ተብሎ ከተጻፈ ወንድሙን ያመሰገነ ምን ይነት ክብር ይጠብቀው ይሆን?
Source: http://www.bahiran.org