13

.

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው::" የማቴዎስ ወንጌል 7: 4

"እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅናወተት ግዙ።" ትንቢተ ኢሳይያስ 55 : 1

Friday, January 18, 2013

የ"ቃና ዘገሊላ" ትርጓሜ

በመምህር ፍቅረ ማርያም ባዘዘው

የቦ/መ/ብ/ቅ/እግዚአብሔር አብ ቤ/ክ የመጽሐፍ መምህር

ቃና ዘገሊላ

ይህ በዓል ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ከዘጠኙ ንዑሳን በዓላት መካከል አንዱ ሲሆን ይህም ጥር 12 ቀን ይውላል፡፡ በዓሉ መከበር የነበረበት የካቲት 23 ነበር፤ ነገር ግን የካቲት ላይ ጾም ስለሚሆን “የውሀን በዓል ከውሀ ጋር” ሲሉ ሊቃውንት ናቸው ጥር 12 ያደረጉት፡፡ 
የዮሐንስ ወንጌል ም.2፤1 “በሦስተኛው ቀን በገሊላ አውራጃ በቃና ሰርግ ነበር” ይላል፡፡ ከዚህ በኋላ በተራ ቀደም ያስቀድማሉ “የኢየሱስ እናት በዚያ ነበረች፤ ኢየሱስደቀመዛሙርቱ” ይላል፡፡ከዚህ ላይ የምንረዳው መጀመሪያ እመቤታችን ድንግል ማርያም አስቀድማ በሰርጉ ውስጥ መኖሯን ነው፡፡ እናት ከተጠራ በኋላ ነው ልጅ የሚጠራና ከዚያም ኢየሱስ ክርስቶስ፤ ከመምህር ጋር ደቀመዝሙር ይጠራልና ከእርሱም ጋር ደቀመዛሙርቱ ተጠሩ፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር በወቅቱ ወይን ባለቀ ጊዜ እመቤታችን ድንግል ማርያም ወይን የላቸውም ያለችው፡፡ እርሱም “ከአንቺ ጋር ምን አለኝ፤ ጊዜዬ ገና አልደረሰምና” አላት፡፡
ወደምሥጢሩ ስንገባ፤
              V  ሦስተኛ ቀን ምንድን ነው
1.  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀ ጥር 11 ቀን ነው፡፡ ወዲያውኑ እንደተጠመቀ ሳይውል ገዳመ ቆሮንቶስ ሄደ፤ 40 ቀንና 40 ሌሊት ጾመ፤ ጾሙ የካቲት 20 ቀን ይፈጸምና የካቲት 23 ቀን “በሦስተኛው ቀን ሰርግ ነበር” ይላል፡፡
2.  ሦስተኛ ቀን የሚለው
·         የመጀመሪያ ቀን የሚባለው ዘመነ አበው ፤ አዳም፤ እነአብርሃም፤ ይስሐቅ አበው የነበሩበት ዘመን ሲሆን፤
·         ሁለተኛ ቀን የሚባለው ዘመነ ኦሩት ነው፤ እነሙሴ የነበሩበት ዘመን ሲሆን
·         ሦስተኛ ቀን የተባለው ዘመነ ሐዲስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የሆነበት ዘመን ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር ሰርግ የሆነው፡፡
V  “እመቤታችን አስቀድማ ነበር” ሲል ደግሞ እመቤታችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በሥጋዊ እድገቱ እንደምትቀድመው ነው፡፡ እንኳን የእርሱ እናት ትቅርና ዮሐንስ መጥምቁም በ6 ወር ይቀድመው ነበር፡፡ እንግዲህ እናትን ሳያውቁ ልጅን ቢጠይቁ ያስቸግራል፡፡ አስቀድማ የነበረችውን ከኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ከመሆን በፊት አብራን የኖረችውን ድንግል ማርያምን ሳናውቅ ኢየሱስ ብንል ትርፉ ድካም ብቻ እንጂ አይሳካም፡፡ ዛሬም ቢሆን “ኢየሱስ” ከማለት በፊት አስቀድመን እርሷን አማልጅን እንበላት፡፡ ነገረ ድኅነትን ስናስብ በህሊናችን አስቀድመን እርሷን መሳል አለብን፤ ነገረ ማርያም የምሥጢረ ሥጋዌ መቅድም (መጀመሪያ)፤ የነገረ ድኅነት መሠረት ነውና፡፡ ጌታችን ተወለደ፤ ተሰደደ፤ አስተማረ፤ ተሰቀለ፤ ሞተ፤ ተነሳ፤ አረገ፤ ዳግም ይመጣል ሲባል በድንግል ማር ያም ሥጋ ነው፡፡ በነገራችን ሁሉ እርሷን ማስቀደም እንዳለብን ነው የምንረዳው፡፡
V  ወይኑ ባለቀ ጊዜ “ወይን የላቸውም” አለች፡፡ የወይኑን ማለቅ ለእመቤታችን ማን ነገራትሙሽራው ወይስ ከሰርገኞቹ መካከል አንዱለዚህ ምንም አይነት መልስ እንደማይሰጥ ግልጽ ነው፡፡ ድንግል ማርያም ግን እራሷ ነበር ያወቀችው፤ ነቢይት ናትና፡፡ ስለሆነው እንዲሁም ስለሚሆነው ታውቃለች፤ ቅዱስ ዘካርያስና ቅድስት ኤልሳቤጥ ካመሰገኗት በኋላ “ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብጽዕት ይሉኛል” ማለቷ ወደፊት ስለሚመጣው ትውልድ ነበር የተናገረችው፤ ይህ  ነቢይነቷን የሚገልጽ ነው፡፡ (ሉቃ. 1፤48-49)  ኢሳይያስ በትንቢቱ በምዕራፍ 8፤1 “ወደ ነቢይቱ ሄድኩ ጸንሳም ነበር” የሚላት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ነው፡፡
በ2ኛ ነገ. 6፤8 በሶርያ የነበረው ንጉሥ በኢየሩሳሌም ያለውን ንጉሥ ሊወጋ (ሊገድል) በፈለገ ጊዜ በእልፍኝ ሆኖ የሚመክረውን ምክር ነቢዩ ኤልሳዕ ኢየሩሳሌም ሆኖ ይመለከትና ያውቅ ነበር፤ ኢየሩሳሌም ሆኖ በሶርያ የሚደረገውን እያየ ነበር፡፡ ስለዚህም የኢየሩሳሌሙን ንጉሥ “ከቤትህ እንዳትወጣ ሶርያውያን ሊገድሉህ ይፈልጋሉ” እያለ ይመክረው ነበር፡፡ ምን አይነት ጸጋ እንደሆነ አስቡት፤ ኢየሩሳሌም ሆኖ በሶርያ የሚደረገውን ነገር ማወቅ፡፡ ታዲያ በዘመነ ብሉይ የነበሩ ነቢያት እንዲህ የርቀቱን ነገር የሚያውቁ ከሆነ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የዶኪማስን የቤት ችግር፤ የወይን ማለቅ ብታውቅ ብትረዳ ምን ይደንቅየመለኮት እናትም እንዴት ጸጋው ይበዛላትእንደ እመቤታችንስ ጸጋው የበዛለት በዘመነ ብሉይ ማን ነበር “ጸጋን የተመላሽ ድንግል ሆይ ደስ ይበልሽ” የተባለች ድንግል ማርያም አይደለችምንእግዚአብሔር ዓይነ ልቡናችንን ያብራልን፡፡
V  “ከአንቺ ጋር ምን አለኝ” ያላትስ ምን ማለቱ ነበርወግጅልኝ፤ ሂጂልኝ ማለቱ ሳይሆን “ያልሽኝን እንዳልፈጽምልሽ ምን የሚከለክለኝ ነገር አለ” ሲል ነው፡፡ “እናትና አባትህን አክብር፤ ለእናትና ለአባትህ ታዘዝ” ያለ አምላክ እናቱን ሂጂልኝ፤ ወግጅልኝ አላት ሲባል አያሳፍርምይህማ እንዳይሆን ለእናቱ እየታዘዘ አደገ ወንጌል ይል የለምን፡፡ (ሉቃ. 2፤51) “ጊዜዬ ገና አልደረሰም” ያለው ወይኑ ከእንስራው በደንብ ካለቀ በኋላ ውሀ ሞልተው የጌታን ተአምር እዲታይ ለማድረግ ነው፡፡ ምክንያቱም ወይኑ በደንብ ሳያልቅ ከዚያው ላይ ቢሞላው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ተአምር አይታወቅም፤ ረድኤት አሳደረበት ይባላል አንጂ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወይኑ ሁሉ ካለቀ በኋላ ግን ውሀ ተሞልቶ ወይን ሲሆን ተአምሩ ይታወቃል፤ ይገለጻል፡፡ ለዚህም ነው “ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያውን ተአምር በቃና አደረገ” የሚል፡፡( ሌላም ሰፊ ምሥጢር ቢኖርም ለዚህ እትም ግን ይህን አቅርበናል፡፡)
የሰርገኛው ቤት ብቻ አይደለም፤ ወይን የጎደለበት ሁላችንም ወይን የለንም የሕይወት እንሥራችን ጎደሎ ነው፡፡ ይህ እንስራ (ጋን) የሚሞላው በእመብርሀን አማካኝነት ነው፡፡ እርሷ ከሌለችበት በፍጹም ሊሞላ አይችልም በመሆኑም ለሁሉም ሰው ለማስገንዘብ የምንወደው በቅድሚያ ጸጋ የበዛበት እመቤት መያዝ እንዳለብን፤ ለምን እግዚአብሔር ከእርሷ ጋር ነውና፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነውና ብሏታል እርሷን ከያዝን እግዚአብሔርን እንይዘዋለን፤ ያለእርሷ እንሥራችን አይሞላም ለዘመናት ደክመናል ነገር ግን እንስራችን ባዶ ነው፡፡ “እመቤቴ ከቤቴ ግቢ፤ ቤቴ ባዶ ነው” እንበላት፤ ትመጣለች ያን ጊዜ ቤታችን ይሞላል፡፡ የፍቅር ወይን፤ የቸርነት ወይን፤ የሰላም ወይን፤ የመተማመን ወይን በቤታችን ጎድሎብናል፡፡ ስለዚህ እመቤታችን በምልጃዋ ትሙላልን፤ ፍቅሯን ታሳድርብን፡፡ አሜን፡፡

ምሥጢረ ጥምቀት



በመምህር ፍቅረማርያም ባዘዘው
የቦሌ መ/ብ/ቅ/እግዚአብሔር አብ ቤ/ክ የመጽሐፍ መምህር
ጥምቀት
ጥምቀት ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ከዘጠኙ አበይት በዓላት መካከል ሲሆን፤ ይህ የጥምቀት ስርዓት የሚካሄደው በመዝፈቅ ነው፡፡ ይህም፤
V  ጥምቀት ዳግመኛ ተወልደን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የምንገባበት ምሥጢር ነው፡፡ ዮሐ.3፤5
V  በጥምቀት ኃጢአት ይሰረያል ሐዋ. 2፤8
V  መንጻትና መቀደስም በጥምቀት ነው፡፡ 1ኛ ጴጥ. 3፤21
የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት
ይህ ጥምቀት የሰው ልጆች የዕዳ ደብዳቤ የተደመሰሰበት ጥምቀት ነው፡፡ ይህ ማለት ሰይጣን በአዳምና በሔዋን አገዛዝ አጽንቶባቸው በነበረ ሰዓት እኛ የአንተ ባርያ ነን በማለት “አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ፤ ሔዋን አመቱ ለዲያብሎስ” የሚል የዕዳ ደብዳቤ አንዱ በዮርዳኖስ አንደኛው ደግሞ በሲዖል ጥሎት ነበር፤ በዮርዳኖስ ያለው በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ተደምሷል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል “ወደምሰሰ ለነ መጽሐፈ ዕዳነ በሥርያቱ እምዕደውነ” ቆላስይስ 2፤14 ይህም ማለት የዕዳ ደብዳቤያችንን ከባላንጋራችን ከዲያብሎስ አጠፋልን (ደመሰሰልን) ማለት ነው፡፡ ይህ  የዕዳ ደብዳቤ የባርነት ደብዳቤ ነበር፡፡ ጌታችን በዮርዳኖስ ሲጠመቅ እንደሰውነቱ ረግጦ፤ እንደአምላክነቱ አቅልጦ አጥፍቶልናል፡፡ ቅዱስ ኤፍሬምም “ወሰጠጠ መጽሐፈ ዕዳዎሙ ለአዳም ወለሔዋን፤ የአዳምንና የሔዋንን የዕዳ ደብዳቤ ደመሰሰላቸው”” ነው የሚለው የሰኞ ውዳሴ ማርያም፡፡ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ለእርሱ የሚጠቅመው ሆኖ ሳይሆን መጠመቁ ለእኛ ክብር ነው፡፡
ትንቢተ ሕዝቅኤል 36፤25 “ጥሩ ውሀንም እረጫችኋለሁ እናንተም ትጠራላችሁ፤ ከርኩሰታችሁም ሁሉ ከጣዖቶቻችሁም ሁሉ አጠራችኋለሁ፡፡” አለ፤ ይህም የሚያስተምረን በጥምቀት የነጻን የተቀደስን እኛ መሆናችንን ነው፡፡ የጌታችን ጥምቀትን ስናስብ የተቀደስንበትና የነጻንበት የዕዳ ደብዳቤያችን የተደመሰሰበት መሆኑን ነው፡፡
ጥምቀቱን በውሀ ያደረገበት ምክንያት
ውሀ ድሀ፤ ባለፀጋ ሳይል በሁሉም የሚገኝ በመሆኑ እንዲሁም ውሀ ብንጠጣው ሕይወት የሚሆን፤ ታጥበን የምንነጻበት …ወዘተ በመሆኑ ጌታም የመጣ ለሁሉም ሰው እንዲሁም ድሀ ባለጸጋ ሳይል ሁሉንም የሚያፈቅር አባት መሆኑን ለማስተማር ነው፡፡
ጥምቀቱን በዮርዳኖስ ስለምን አደረገው
1.  ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የአዳምና የሔዋን የዕዳ ደብዳቤ አንዱ በዮርዳኖስ ስለነበር ያን ለመደምሰስ ነው፡፡
2.  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ እንደሚጠመቅ ትንቢት ተነግሮ ነበር፡፡                                          መዝ. 113፤3-6
3.  በዮርዳኖስ ንህማን ከለምጹ የተፈወሰበት ነው፡፡ 2ኛ. ነገ.5፤8- ፍጻሜ
4.  አባታችን ኢዮብ የተፈወሰበት ነው፡፡

ጌታችን በ30 ዓመቱ ለምን ተጠመቀ
ብዙ ጊዜ ሰዎች የሚከራከሩበት በመሆኑ ነው፤ ይህም አንዳንዶቹ “ጌታ የተጠመቀ በ30 ዓመቱ ነውና እኛም እንደ እርሱ በ30 ዓመት መጠመቅ አለብን” ይላሉ፡፡ ይህ ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ  ጋር እኩል ነኝ እንደማለት ነውና አቅምን ማወቅ ጥሩ ነው፡፡ አዳምና ሔዋንም የወደቁት እንደ አምላካቸው እንሆናለን ብለው ነበር፡፡ “ጌታችን ለምን በሰላሳ ዓመቱ ተጠመቀ” ተብሎ ይጠየቃል እንጂ “እኔም እንደእርሱ በሰላሳ ዓመት መጠመቅ አለብኝ” ሊሆን አይችልም፤ ይህንን የምትሉ ወንድሞችና እህቶች ካላችሁ ስህተት ነውና ተመለሱ እንላለን፡፡ ጥቂት ቆይታችሁ ደግሞ እንደጌታ እንሰቀላለን እንደምትሉ ፍርሃቱ አለን፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰላሳ ዓመቱ መጠመቁ ምሥጢሩ ግን እንዲህ ነው፤ አዳም ሲፈጠር የ30 ዓመት ጎልማሳ ሆኖ ነበር፤ ይህ የ30 ዓመት ጎልማሳ አዳም ልጅነቱን አስወግዶ፤ ክብሩንም አጣ፡፡ ስለዚህ የአዳም ልጅነት የሚመለስለት ጌታችን በ30 ዓመቱ ሲጠመቅ በመሆኑ ነው፡፡ ክርስቶስን “ሁለተኛ አዳም” ያልነውም የመጀመሪያው አዳም ያጣውን በረከት በሁለተኛው አዳም በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወትን በማግኘቱ ነው፡፤ ስለአዳም ልጅነት ነው በ30 ዓመቱ የተጠመቀ እንጂ እናንተም በሰላሳ ዓመታችሁ ተጠመቁ እያለን አልነበረም፡፡
የእኛ ጥምቀት በ40 እና በ80 ቀን መሆኑ
1.  ሔዋን በተፈጠረች በ80 ቀን፤ አዳም ከተፈጠረ በ40 ቀን ነበር ገነት የገቡት፡፡ ይህም በተወለድን ወንዶች በ40 ቀን፤ ሴቶች በ80 ቀን ወደ ቤተመቅደስ መግባት እንዳለብን ነው የሚያስተምረን፡፡ (መ.ኩፋሌ 4፤9-11፤ መ.ዘሌዋውያን 12፤1-5፤ ሉቃ. 2፤21-24)
2.  ሕፃናት በብሉይ ኪዳን ሲገረዙ ክብርን ያገኙ ነበር፤ ፀጋውን ለይቷቸው አያውቅም፡፡ (ዘፍ.17፤11) ለምሳሌ
·         ነቢዩ ኤርምያስ የተቀደሰው በእናቱ ማኅጸን ነበር፡፡ (ት.ኤር. 1፤5)፤
·         መጥምቁ ዮሐንስ በእናቱ ማኅጸን በመንፈስቅዱስ ተመልቶ ነበር፡፡ (ሉቃ. 1፤15)
·         ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያስተምርበትም ሰዓት ሕፃናትን ባርኳቸዋል፤ ይህም ሕፃናት በዕድሜያቸው ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ የሚከለክላቸው አለመሆኑን ያሳያል፡፡ (ማቴ. 19፤13-15፤ ማር. 1፤13-15)
·         ቅዱስ ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 1፤16 ላይ የእስጢፋኖስን ቤተሰቦች በሙሉ እንዳጠመቀ ይናገራል፡፡ ቤተሰብ ሲል ደግሞ ከሕፃን እስከ ሽማግሌ ድረስ ያለው መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ስለዚህ “ሰላሳ ዓመት ሲሞላኝ ነው መጠመቅ ያለብኝ” የሚል ሰው ከመጽሐፍቅዱስ ጋር ገና ግንኙነት ያላደረገ ወይንም መጽሐፍቅዱስ ምን እንደሚል ያልተገነዘበ ሰው ነው፡፡
በማን ስም እንጠመቃለን
“በስመ ሥላሴ” በማቴዎስ ወንጌል ም.28፤19-20 “ወደ ዓለም ሂዱ ፍጥረትን ሁሉ አስተምሩ በአብ በወልድ በመንፈስቅዱስ ስም አጥምቋቸው” ይላል፡፡ አንድ አንድ ሰዎች በሐዋርያት ሥራ በምዕራፍ 2 ላይ ያለውን በመያዝ “ሐዋርያት ያጠምቁ የነበር በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው እንጂ በሥላሴ ስም አይደለም፤ ስለዚህ እኛም መጠመቅ ያለብን በኢየሱስ ስም ነው” ይላሉ፡፡ ይህ ግን ስህተት ነው፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ አጥምቁ ብሎ የላካቸው በአብ በወልድ በመንፈስቅዱስ ስም ነው፡፡ እነርሱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እያጠመቁ አብ እና መንፈስቅዱስን ዘንግተዋቸው አይደለም፡፡ ነገር ግን፤
1.  የዮሐንስ ወንጌል ም.14፤8 “እኔን ያየ አብን አይቷል፤…. እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን” ብሎ ተናግሮ ነበር፡፡ እነርሱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሲያጠምቁ አንድነታቸውንና ሦስትነታቸውን ጠንቅቀው ስለአወቁ እንጂ ጠፍቷቸው አይደለም፡፡
2.  የኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አብ ልጅ እንደሆነ ራሱ ቅዱስ ጴጥሮስ መስክሮ ነበር፡፡ (ማቴ. 16፤17)
ስለዚህ በወቅቱ አወዛጋቢ እና መፍትሔ ጠፍቶለት የነበር ችግር የእግዚአብሔር ሰው የመሆኑ ምሥጢር ነበር፡፡ ታዲያ ሐዋርያት በሥራቸው ሁሉ ስለኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት እንዲሁም አዳኝነት መመስከር ስለነበረባቸው ብዙ ጊዜ የኢየሱስ ክርስቶስን ስም ይጠሩ ነበር፤ ዛሬ ሁሉ አማኝ ነው፤ በማን ስም መጠመቅ እንዳለበት ያውቃል፡፡ ስለኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት ያልገባው ሰው ብቻ ነው ስለእርሱ አምላክነት አስተምረህ የምታጠምቀው፡፡
የነገረ መለኮት ሊቃውንት “There is no baptism without Holy Spirit” ይላሉ ይህም ማለት በጥምቀት አብ ወልድ መንፈስቅዱስ ከሌሉበት፤ የእነርሱ ስም ካልተጠራ ያ ጥምቀት “ጥምቀት” አይባልም በውሀ ተነክሮ እንደመውጣት ያህል ነው ይላል፡፡ በዮርዳኖስ አብ በደመና “የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት” ሲል መንፈስቅዱስ በአምሳለ ርግብ ሲወርድ መታየቱ ሰው በሥላሴ ስም መጠመቅ እንዳለበት የተገለፀ ምሥጢር ነው፡፡ ለዚህ ነው የነገረ መለኮት ሊቃውንት “In the river Jordan is revealed the mysteries of Holy Trinity – that mean without Holy Trinity no baptism.” (The scholars of Theology) ያሉት፡፡
በኦሪት ዘፍጥረት ምዕ. 1፤2 “የእግዚአብሔር መንፈስ በውሀ ላይ ሰፍፎ ነበር” ይላል፡፡ ይህ ማለት ውሀን የሚያጠራ ለሰው ሁሉ ተስማሚ እንዲሆን የሚያደርግ መንፈስቅዱስ መሆኑን የሚገልጽ ሲሆን በተጨማሪ ግን ምሥጢራዊ ትርጉም ነው፡፡ ቅዱስ ጄሮም እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፤
“The symbol of Baptism. It is mystical meaning “the Spirit was stirring above the waters” already at that time baptism was being flourish ad owed. It caused not,  be true baptism, to be sure, without the Spirit.” (St. Jerom) “በውሀ ላይ ሰፍፎ የነበረው መንፈስ የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ ይህም ምሥጢራዊ ትርጉም ያለው ነው፤ ያለ መንፈስቅዱስ ጥምቀታችን እውነት አይሆንም” ነው የሚለው፡፡
የትርጓሜ መጻሕፍት መምህራንም የጥምቀት ምሳሌ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ “ውሀ በልብ የሚሳቡትን፤ በእግር የሚሽከረከሩትን ፤ በክንፍ የሚበሩትን አስገኝቶ ነበር፡፡ ይህም ማንኛውም ሰው በጥምቀት የሚወለደው ልደት ነው፤ ከሥጋ የተወለደው የሰው ልጅ በመንፈስ ሲወለድ ረቂቅ ምሥጢር ይገለጽለታል” ይላሉ፡፡ “በብዙ አቅጣጫ መንቀሳቀስ ይችላል፤ ሰማያዊ ፀጋ እንዲሁም ምድራዊ ፀጋ ይበዛለታል” ይላሉ፡፡ ስለዚህ ጥር 11 ቀንን ስናስብ ብሔራዊ ባህላችን ነው፤ ዓለም ሁሉ በጉጉት የሚጠብቀው በዓል ነው፡፡ በየዓመቱ ስናከብረው ሁልጊዜ በየዓመቱ እያጠመቅን አይደለም፤ አንዳንዶች “ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ በየዓመቱ ታጠምቃለች” ይላሉ፤ ጥምቀት አንዲት መሆኗን የምትመሰክር ሃይማኖት መሆኗን ሁሉም ያውቀዋል፡፡ (ኤፌ. 4፤4) ይህ ግን ክርስቶስ ለእኛ ሲል መጠመቁን ከገሊላ ወደ ይሁዳ (ዮርዳኖስ) ሄዶ መጠመቁን ለማመልከት አባቶቻችን ታቦታትን ከክብር መንበሩ ወደ ጥምቀተ ባሕር ይዘው በመሄድ የጌታን ትህትና እያስተማሩ እንጂ ሁልጊዜ ማጥመቃቸው አይደለም፡፡
ስለጥምቀት ያላችሁን ጥያቄ በሙሉ ለዝግጅት ክፍሉ በመላክ ለጥያቄዎቻችሁ ተገቢውን ሰፋ ባለ መልኩ ለመመለስ እንደሚቻል ለማሳወቅ እንወዳለን፡፤
የሰላም በዓል ያድርግልን፡፡
 ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ወርሐ ጥርን ስናስብ....

“ክቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅድመ እግዚአብሔር፤ የጻድቅ ሰው ሞት በእግዚአብሔር ፊት የተከበረ ነው፡፡”
በጥር 12 ቀን ዕረፍቱ ለቴዎድሮስ ሰማዕት
ሀገሩ አንጾኪያ (ከሮም ምስራቅ በኩል የሚገኝ) ሲሆን አባቱ ሲድራኮስ እናቱ በጥይቃ ይባላሉ፡፡ በዘመኑ ዲዮቅልጥያኖስ ለአጵሎንና ለአርዳሜስ ለተባሉት ጣዖታቱ ያልሰገደ ቤቱ ይበረበራል፤ በሠይፍ ይቀላል፤ ሥጋው ለእሳት ይሰጣል ብሎ አዋጅ ያወጀበት ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ ቡናብሴ በሚባል ወንዝ አካባቢ ሳለ በህልሙ  የወርቅ መሰላል ከምድር እስከ ሰማይ ተተክላ በላይዋ ዙፋን ተዘርግቶባት በዙፋኑ ላይ ንጉሥ ተቀምጦበት በግራ በቀኙ መላእክት ከበው ሲያመሰግኑት ወዲያውም ከመላእክቱ አንዱ ከወንዙ ቢነክረው እንደእርሱ እሳታዊ ሲሆን ጌታም ስለስሜ ትሞታለህ ከእኚህ እንደ አንዱ ትሆናለህ ሲለው ጓደኞቹ ለውድዮስና በኒቃሮስም መልአኩ ነክሯቸው እንደእርሱ ሲሆኑ አየ፡፡ በሰማዕትነት ሙቱ ሲለን ነው ብሎ ከሠራዊቱ የፈሩትን አሰናብቶ የተከተሉትን ከወንዙ አስጠም ለውድዮስንና በኒቃሮስን አስከትሎ ሄደ፡፡ ዲዮቅልጥያኖስም ለአጵሎም ስገድለት አለው፡፡ “አንተ አላዋቂ ጠበብቶችህ ደንጊያ ፀርበው እንጨት አለዝበው ለሠሩት ጣዖት ስገድ ትላለህን አልሰግድም” አለ፡፡ ተከታዮቹን በሰይፍ አስመታቸው፤እርሱን ግን አሰቀለው፡፡ ሥጋው እንደወንፉት ተበሳሳ፤ ደሙም እንደ ውኃ ፈሰሰ፡፡ ከሥቃዩ እንዲያጽናናው ቅዱስ ሚካኤልን ላከለት፤ ኋላ ግን ራሱ ጌታ ተገልጾለት “ስለምስፍናህ፤ ስለድንግልናህ፤ ስለተጋድሎህ ሦስት አክሊላት አቀዳጅሀለሁ፡፡ በስምህ ጥርኝ ውኃ እስከማጠጣት ድረስ መልካም ያደረገውን ሁሉ ምሬልሀለሁ፤ በጦር በእስር በመከራ በሥቃይ ሆኖ በስምህ የተማፀነውን ሁሉ ኃይል ጽንዕ እሆነዋለሁ” ብሎ ተስፋውን ነግሮት ነፍሱን ከሥጋው ለይቶ በስብሐተ መላእክት አሳርጎታል፡፡
የቴዎድሮስ ሰማዕት ረድዔትና በረከቱ ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡ አሜን፡፡
ጥር 15 ቀን ዕረፍቱ ለሰማዕቱ ቂርቆስ
ቅዱስ ቂርቆስና ቅድስት ኢየሉጣ በእግዚአብሔር ቸርነት በቅዱስ ገብርኤል ረዳትነት በእሳት ከመቃጠል፤ በንፍር ውሀ ከመለብለብ ከዳኑ በኋላ እለእስክንድሮስ መከራውን ፈርተው ይመለሳሉ ብሎ እያሰረ፤ በችንካር እየቸነከረ ሲያሰቃያቸው ቆየ፡፡ የማይሆንለት ቢሆን እጅ እግራቸውን አስሮ ከዝግ ቤት አስቀመጣቸው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የመከራቸውን ጽናት የትዕግሥታቸውን ብዛት አይቶ ከመከራው ሊያሳርፋቸው ሽቶ በመንፈቀ ሌሊት ተገልጾ “ሰላም ላንተ ይሁን፤ የመከራህን ጽናት የትዕግሥትህን ብዛት አይቼ ላሳርፍህ መጣሁ” አለው፡፡ “በሕፃንነቴ ይህን ያህል ተጋድዬ የምትሰጠኝ ምንድን ነው” አለው፡፡ “በልብህ ያለውን ሁሉ እሰጥሀለሁ” አለው፡፡ “እንኪያስ በስሜ ቤተክርስቲያን ከታነጸበት፤ ማየ ጸሎት ከተረጨበት ቦታ ሁሉ ረሀብ ቸነፈር የሰው በሽታ የከብት እልቂት፤ የእኅል የውሀ ጥፋት አይሁን” አለ፡፡ “ይሁንልህ” አለው፡፡ “ሥጋዬም በምድር አይቀበር” አለ፡፡ “እውነት እልሀለሁ ከመንበረ መንግሥቴ፤ ከማርያም እናቴ ከዮሐንስ መጥምቅም በቀር በመንግሥተ ሰማያት የሚበልጥህ የለም ሥጋህም እንዳይፈርስ በኤልያስ ሠረገላ አኖርልሀለሁ” ብሎ ተስፋውን ነግሮታል፡፡
ሲነጋ እለእስክንድሮስ ከመካነ ምኩናኑ ተቀምጦ ካለበት አስጠርቶ “የተመለስከው መመለስ አለን” አለው፡፡ ሰይፍ ጃግራውን ጠርቶ ንሳ ውደቅበት አለው፤ በሰይፍ መታው፤ ጌታም ነፍሱን በመካነ ዕረፍት ሥጋውንም ነጥቆ በሠረገላ ኤልያስ አኑሮታል፡፡ እናቱ ቅድስት ኢየሉጣንም በማግሥቱ በሰይፍ አስመትቷታት በሰማዕትነት አርፋለች፡፡
የሰማዕቱ ሕፃን ቂርቆስ እና የእናቱ ቅድስት ኢየሉጣ ረድዔትና በረከት ይደርብን፡፡ አሜን፡፡

ጥር 21 ቀን ዕረፍታ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ
ማርያም ማለት
·         ልዕልት ማለት ነው፡፡ሮም ራማ አርያም ማለት ልዑል ማለት እንደሆነ እሷም መትሕተ-ፈጣሪ መልዕልተ ፍጡራን ናትና፡፡
·         እግዝእተ ብዙኃን ማለት ነው፡፡
·         ጸጋ ወሀብት ማለት ነው፡፡ ለጊዜው ለአባትና ለእናቷ ፍጻሜው ግን ለሰው ሁሉ ጸጋ ሆና ተሰጥታለችና፡፡
·         ፍጽምት ማለት ነው፡፡ ለጊዜው መልክ ከደምግባት ፍጻሜው ግን ንጽሐ ሥጋ ከንጽሐ ነፍስ፤ ድንጋሌ ሥጋ ከድንጋሌ ነፍስ አስተባብራ ይዛ ተገኝታለችና፡፡
·         መርሕ ለመንግሥተ ሰማያት ማለት ነው፡፡ ምእመናንን መርታ መንግሥተ ሰማያት ታገባለችና፡፡
·         በዓለመ ሥጋ በዓለመ ነፍስ ካሉት ሁሉ የከበረች የገነነች ማለት ነው፡፡ ማር በምድር ካሉት መባልዕት (የሚበሉ ሁሉ) ያም በገነት ካሉ ዕፅዋዕት/ፍሬያት/ ሁሉ የከበሩ የጣፈጡ እንደሆኑ፡፡
·         ማ - ማኅደረ መለኮት
ር - ርግብየ ይቤላ
ያ - ያንቀዓዱ ኀቤኪ ኩሉ ፍጥረት
ም - ምስአል ወምስጋድ ማለት ነው፡፡

የዕረፍቷ ነገር እንደምን ነው ቢሉ ስድሳ አራት ዓመት በዚህ ዓለም ኖራ ጥር 21 እሑድ ቀቀን ጌታ እልፍ አእላፍ መላእክቱን አስከትሎ መጥቶ “እናቴ ሆይ ከዚህ ዓለም ድካም ላሳርፍሽ መጣሁ” አላት፡፡”ልጄ ሰማይና ምድር የማይወስኑህን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማኅፀኔ ተሸክሜ፤ በድንግልና ወልጄህ እሞታለሁን አለችው፡፡ በሲኦል የሚሰቃዩ ነፍሳትን አሳይቶ “እናቴ ሆይ ሞትሽ ለኚህ ቤዛ ይሆናቸዋል” አላት፡፡ “እኚህን ከማርክልኝስ ይሁን” አለችው፡፡ ቅድስት ሥጋዋን ከክብርት ነፍሷ ለይቶ በቃለ አቅርንት በዝማሬ መላእክት አሳረጋት፡፡ ደቀ መዛሙርቱንም ከያሉበት በደመና ጠቅሶ ካለችበት አድርሶ “እመቤታችሁን ቅበሩ” አላቸው፡፡ ባጎበር አድርገው ይዘዋት ወደ ጌቴ ሴማኒ  ሲወስዷት አይሁድ አይተው “ልጅዋን ተነሣ፤ ዐረገ እያሉ ሲያውኩን ይኖራሉ፤ አሁን ደግሞ እሷን ተነሳች ዐረገች እያሉ ሊያውኩን አይደለምን ኑ ሥጋዋን እናቃጥለው፡፡” ብለው ተነሱ፡፡ ከመካከላቸው አንዱ ታውፋንያ ዘሎ ያልጋውን ሸንኮር ያዘ፤ የታዘዘ መልአክ መጥቶ ሁለት እጁን በሰይፍ ቀጣው፡፡ “በድያለሁ ማረኝ” ብሎ ቢማፀናት ራሷን ዘንበል አድርጋ ቅዱስ ጴጥሮስን “እንደነበረ አድርግለት” አለችው፤ ቢመልሰው ድኖለታል፡፡ ከዚህ በኋላ ዮሐንስን ጨምሮ ከመካከላቸው ነጥቆ ገነት በዕፀ ሕይወት ሥር አኑሯታል፡፡ ኋላም በሐዋርያት ሱባዔ በነሐሴ 14 ቀን ክቡር ሥጋዋ ተመልሶላቸው ቀብረዋት በነሐሴ 16 ቀን እንደ ልጇ ባለ ትንሣኤ አርጋለች፡፡ የእመቤታችን የወላዲተ አምላክ ቅድስት ደንግል ማርያም እናትነቷ፤ ፍቅሯ፤ በረከቷ እና ምልጇዋ ከሁላችን ጋር ለዘለዓለም ይኑር፡፡ አሜን፡፡


  ወስብሐት ለእግዚአብሔር