13

.

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው::" የማቴዎስ ወንጌል 7: 4

"እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅናወተት ግዙ።" ትንቢተ ኢሳይያስ 55 : 1

Friday, September 9, 2011

ዕንቁጣጣሽ

ዕንቁጣጣሽ

እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላምና በጤና አደረሳችሁ፡

ዘመነ ማቴዎስም፣ ዘመነ ማርቆስም፣ ዘመነ ሉቃስም ሆነ ዘመነ ዮሐንስ፤ በአራቱም ዘመናት አስቀድሞ ርእሰ ዓውደ ዓመት ቅዱስ ዮሐንስ ይዘከራል፡፡ ዮሐንስ የስሙ ትርጉም «ጸጋ እግዚአብሔር» ማለት ነው፡፡ ዘመናት ዘመናትን እየወለዱ፣ ሰዓታት ደቂቃን ቅጽበትን /ሰኮንድን/ ሳይቀር እየሰፈሩ/እየቆጠሩ/ ዕለታት ሳምንታትን፣ ሳምንታት ወራትን፣ ወራት ዓመታትን አሁን ላለንበት ዘመን ደርሰናል፡፡ ዓውደ ዓመት በግእዝ ሲሆን በአማርኛ የዘመን መለወጫ/ ቅዱስ ዮሐንስ፣ ዕንቁጣጣሽ እየተባለም ይጠራል፡፡

ኃይማኖታዊ መሠረት


ቅዱስ ማርቆስ ወንጌሉን ሲጽፍ «የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ እነሆ መንገድህን የሚጠርግ መልእከተኛዬን በፊትህ እልካለሁ የጌታን መንገድ አዘጋጅ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ» ተብሎ በኢሳይያስ እንደ ተነገረ የነቢዩ ዘካርያስ ልጅ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በዘመነ ብሉይ መጨረሻና በዘመነ ሐዲስ መጀመሪያ ላይ ተነሥቶ «መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ» እያለ ስለ ክርስቶስ አዳኝነት እየመሰከረ በምድረ በዳ የንስሐን ጥምቀት እያጠመቀ ለኃጢአት ሥርየት እየሰበከ መጣ ብሎ በዘመነ ወንጌል የመጀመሪያ ምዕራፍ ገልጾታል፡፡
/የማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ ፩ ቁጥር ፵፤ [[ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕ ፵ ቁ ፫ - ፬/፡፡
የመጥምቁ ዮሐንስ ተግባር ለዘመነ ወንጌል በር ወይም መነሻ ሆኖ መገኘቱን በመረዳት የቤተክርስቲያን አበው የበዓላቱን ድንጋጌ በወሰኑበት ጊዜ የመጥምቁ ዮሐንስ መታሰቢያ በዓል የኢትዮጵያ ርዕሰ ዓውደ ዓመት በሚሆን መስከረም ፩ ቀን እንዲከበር በየዓመቱ የዘመኑ መጀመሪያ በእርሱ ስም እንዲጠራ አባቶች ደንግገዋል፡፡ / ድርሳነ ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ገጽ 1ጠ 3/ ይህንንም በዓል አባቶቻችን በርእሰ ዓውደ ዓመት ማክበር እንደሚገባ አስበው ያደረጉት ነው፡፡ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በሰማዕትነት ያረፈበት ቀን ሆኖ አይደለም፡፡ ለአዲሱ ዓመት መጀመሪያ ወይም ርእሰ ዓውደ ዓመት «ቅዱስ ዮሐንስ» ይባላል፡፡ መጽሐፈ ስንክሳር የዓመቱን መጀመሪያ /መስከረምን/ ሲያትት «ይህ የመስከረም ወር የተባረከ ነው እርሱም የግብጽና የኢትዮጵያ ዓመቶች መጀመሪያ ነው በማለት ያስረዳል፡፡ የዚህ ወር ቀኑና ሌሊቱ እኩል ፲፪ ሰዓት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ከመስከረም አንድ ቀን ጀምሮ ቀኑ እየጎደለ ይሔዳል፡፡
ከዚህ በመቀጠል በዓሉ በተለያየ ስያሜ ስለመጠራቱና ትርጓሜያቸውን እንመለከታለን፡፡

ዘመን መለወጫ


አስቀድመን ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ማንነትና የዘመን መለወጫ መግቢያው ላይ በስሙ ስለመጠራቱ ተመልክተናል፡፡ ዘመን መለወጫ ደግሞ ለምን እንደተባለና ለምን መስከረም ወር ላይ እንደሆነ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እንዲህ በማለት ያትታሉ፡፡ ሲያትቱም ብርሃናት/ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት/ የዓመት ዑደታቸውን በጳጉሜ ወር ጨርሰው በመስከረም ወር ስለሚጀምሩ ነው፡፡ ያን ጊዜ ሌሊቱም ከቀኑ ጋር ይተካከላል፡፡ ዓመቱንም ጠንቀቀው ቢቆጥሩት ፫፻፷፬ ቀናት ይሆናል፡፡ ለዘመን መታወቂያ ይሆን ዘንድ ፀሐይና ጨረቃ ከዋክብትን ፈጠረ ይላልና /መጽሐፈ ሔኖክ ምዕራፍ ፳፩ ቁጥር ፵፱፡፡ በሌላ በኩልም በዘመነ ኖኅ ዓለምን ውኃ አጥለቅልቋት ከቆየ በኋላ ዳግመኛ ከነበረው ውኃ የተገለጠችበት ወር «በመጀመሪያም ወር በምድር ታየች የንፍር ውኃው ከምድር ደረቀ» የሚለውን መሠረት አድረገው የአቡሻኽር ሊቃውንት የዘመን መለወጫን ታሪካዊ አመጣጥ ያስረዳሉ፡፡/መጽሐፈ ኩፋሌ፡ ምዕ ፯ ቁጥር ፩/
በመሠረቱ ዘመን ተለወጠ ሲባል የሚለወጡት ወራቱ ብቻ አይደሉም፡፡ በወቅቱ የሚከሰቱት/የተከሰቱት/ መልካምም ሆነ ክፉ ነገር /ገጠመኝ/ ሲሆን ወራቶቹ ግን ያው በየዓመቱ እየተፈራረቁ ይመጣሉ፡፡ ዘመን መለወጫ ላይ የሰው ልጆች ሕይወት ሊለወጥ ይገባል፡፡ ተማሪው ተምሮ ወደቀጣዩ ክፍል /ደረጃ/ የሚለወጥበት፣ ገበሬው የክረምትን ወራት በሚገባ ተጠቅሞ የሚቀጥለውን የበጋ ወራት የሚቀበልበት፣ ሠራተኛው የክረምቱን ዝናብ ታግሶ የፀሐይን ወራት የሚቀበልበት ሌላውም እንደዚያ ሆነው ወራቶቹ በዚያ ዘመን ያለው የተፈጥሮ ክስተቶች የሚለወጥበት ዘመን ተለወጠ እየተባለ ይነገራል፡፡

የ"ዕንቁጣጣሽ" አመጣጥ


ዓመታት ተፈጽመው አዲስ ዓመት ስንጀምር ቅዱስ ዮሐንስ፣ ዓውደ ዓመት፣ አዲስ ዓመት ፣ ዕንቁጣጣሽ እየተባለ ይጠራል፡፡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እንደሚያስረዱት ዕንቁጣጣሽ የሚለው ስያሜው አመጣጥ ወይም ጥንተ ታሪክ በመጀመሪያ ኖኅ ለሦስቱ ልጆቹ አህጉራትን በዕጣ ሲያካፍላቸው አፍሪቃ ለካም ደረሰችው፡፡ በአፍሪቃ ምድርም ሲገባ በመጀመሪያ ያረፈው በኢትዮጵያ ነበር፡፡ ሀገሪቱም በአደይ አበባ አሸብርቃ ነበር፡፡ ወሩ ወርኃ መስከረም በመሆኑ ደስ ብሎት «ዕንቁ ዕጣ ወጣሽልኝ» ይህችን ወቅት እንቁጣጣሽ ብሏታል፡፡
ሁለተኛው የሀገራችን ንግሥት ንግሥተ ሳባ የንጉሥ ሰሎሞንን ዜና ጥበብ እየሰማች ስታደንቅ ትኖር ነበር፡፡ በጆሮዋ የሰማችውን በዓይኗ ዓይታ ለመረዳት ስለፈለገች በግመሎች ላይ ሽቱና እጅግ ብዙ ወርቅ እንዲሁም በኢትዮጵያ የሚገኝ በኢየሩሳሌም የማይገኝ ልዩ ልዩ ገጸ በረከት አስጭና ከብዙ ሠራዊት ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ገባች፡፡ ከንጉሡ ሰሎሞንም ጋር ተገናኝታ የያዘችውን ገጸ በረከት ከሰጠችው በኋላ ብዙ ነገሮችን ጠየቀችው፡፡ እርሱም አንድ ነገር ላይ ሰውሮ ሁሉንም ገለጸላት፡፡ ቤተ መንግሥቱንም፣ በቤተ መንግሥቱ የሚገኙ እጅግ በጣም የከበሩ ዕቃዎችን ሁሉ አስጎበኛት፡፡ ሲያበቃ «ዕንቁ ለጣትሽ ጌጥ ይሁንልሽ» ሲል እጅግ በጣም የከበረ ዕንቁ አበረከተላት/ሰጣት/፡፡ ወሩም ወረኃ መስከረም ነበር፡፡ ከዚህ በመነሣት እንቁጣጣሽ የሚለው መጥቷል፡፡ አሁን ከሚፈጸመው ሥነ ሥርዓት ደርሶ በመፈጸም ላይ ይገኛል፡፡ የሚከበረውም መስከረም አንድ ቀን ነው፡፡
አንድም «ዕንቁ ዕፅ አወጣሸ» ብሎ የአበባውን መፈንዳትን ያስረዳናል፡፡

ባህል ነክ ስርዓቶች


የኢትዮጵያ ሕዝብ በየዓመቱ በታላቅ ስሜት ከሚያከብራቸውና ከሚያዘክራቸው በዓላት አንዱና ተወዳጅ የዘመን መለወጫ በዓል ነው።
እንደ ዕፅዋት ሁሉ ሰው በመስከረም ላይ በተስፋ ስሜት ይለመልማል። ከቅዱስ ዮሐንስ ዋዜማ ጀምሮ በየቤቱ ጨፌና ቄጠማ ይጐዘጐዛል። አበባ በሥርዓት እየተዘጋጀ በየቦታው ይቀመጣል። በተለይም ልጆች አዳዲስ ልብሳቸውን ለብሰው በደስታ ይፈነድቃሉ። በአመሻሽ ላይ ችቦ አቀጣጥለው "እዮሐ አበባዬ መስከረም ጠባዬ፣ እዮሐ የበርበሬ ውኃ፣ በሸዋ በጐንደር በትግራይ በሐረር... ያላችሁ እንዴት ከረማችሁ፣ እንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገራችሁ። እንጉርጉሮ ገባሽ በያመቱ ያምጣሽ.." እያሉ ወጣት ወንዶችና ልጃገረዶች (በተለይ በገጠር) ሲዘፍኑና ሲጨፍሩ ያድራሉ።

የሚያበሩት ችቦና የሚያነዱት እሳት በግርማ ምሽት ሲንቀለቀል ውጋገኑ ካገር አገር ከሰፈር ሰፈር ከቦታ ቦታ... ይታያል። በዕንቁጣጣሽ መዓልት በተደመረው ሰፈርተኞች ከርቀትም ከቅርበትም ይሰበሰባሉ። አባቶች ይመርቃሉ። "ዝናሙን ዝናመ ምሕረት፣ እህሉን እህለ በረከት ያድርግልን፣ ሰላም ይስጠን፣ እህል ይታፈስ፣ ገበሬ ይረስ፣ አራሽ ገበሬውን፣ ሳቢ በሬውን ይባርክ፣ ቁንጫን፣ አንበጣን፣ ትልን... ያጥፋ፣ ምቀኛን ሸረኛን ያጥፋ፣ ወጡ ገቡ ሰቡ ረቡ የሚለውን ሁሉ እግሩን ቄጠማ ዓይኑን ጨለማ ያድርገው፣ ያርገው፣ ያርገው፣..." ይባባላሉ።
እናት አባት ዘመድ አዝማድ በልጆቻቸውና በወዳጅ ዘመዶቻቸው የተበረከተላቸውን የዕንግጫ ጉንጉን (የአበባ አክሊል) በራሳቸው፣ እንጀራ ማቡኪያቸው፣ በመሶባቸው፣ በወጋግራቸው... ላይ ያስራሉ። ከምሽት ጀምሮ እስከ ንጋት ድረስ በየቤቱ የተዘጋጀው ድግስ ይበላል፣ ይጠጣል።
በነጋታው የዕንቁጣጣሽ ዕለት ልጃገረዶች በሙሬ ወገባቸውን አስረው የሀገር ባህል ወይም ዘመናዊ ቀሚስ (ልብስ) ለብሰው አሽንክታብ ጨረቃ ጠልሰም፣ ብር ማርዳ (ዶቃ)፣ ድሪ፣ መስቀል፣ የአበባ ጉንጉን በአንገታቸው ላይ አጥልቀው ዓይናቸውን ተኳኩለው፣ ፀጉራቸውን ጋሜ ቅርፅ ተሰርተው፣ ራሳቸውን በአደስና በአሪቲ የተቀመመ ለጋ ቅቤ ተቀብተው በራስ ማሰሪያ ሸብ አድርገው፣ የብር መስቀላቸው ላይ አሪቲ (ሪያ) ሰክተው፣ እጅና እግራቸውን እንሶስላ ሞቀው በክንዳቸው አምባር አስረው፣ ብርአልቦ በእግራቸው፣ ብር ቀለበት በጣታቸው አድርገው፣ ሎሚ በጉንፋቸው ይዘው አሥር አሥር በመሆን ክብ ይሰሩና በእጆቻቸው ጭንና ጭናቸውን መሬቱን እየተመተሙ ተንበርክከውና ቁጢጥ ብለው ድሪያ ይጫወታሉ።በከተማው የእንቁጣጣሽ ባህል ደግሞ አበባዬ ሆይ ባልንጀሮቼ.. እያሉ ገንዘብ ይለምናሉ፣ ሲቀበሉም ከብረው ይቆዩን... ይላሉ። ገጠሬዎች ግን ይጫወታሉ እንጂ አይለምኑም።

 መጪው አዲስ ዓመት 2004 (ዘመነ  ዮሐንስ) የፍቅር፣  የሰላምና  የብልፅግና 
ዘመን  እንዲሆንልን የቅዱስ እግዚአብሔር
ፈቃድ ይሁን፡፡

Thursday, September 8, 2011

የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር

የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር

"በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ፥ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል።
የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ፥ ኮረብቶችም በደስታ ይታጠቃሉ።"
መዝሙረ ዳዊት 65 : 11 - 12
 ከውክፔዲያ
የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠርኢትዮጵያ (እንዲሁም በኤርትራ አብያተ ክርስትያናት) ዋና ካሌንደር ነው። አዲስ ዓመት በጁሊያን ካሌንደር አቆጣጠር በኦገስት 29 ወይም 30 የሚጀምር ሲሆን በግሪጎሪያን ካሌንደር ደግሞ ከ1901 እ.ኤ.አ. እስከ 2099 እ.ኤ.አ. ድረስ በሴፕቴምበር 11 ወይም 12 ይጀምራል። በየአራት ዓመቱ አንድ ቀን ይጨመራል። በአንድ ዓመት ውስጥ አስራ-ሁለት ባለሠላሣ ቀናት እና አንድ ባለ አምስት (ስድስት በአራት ዓመት) ቀናት ያሉባቸው ወራት አሉ።
የአመተ ምህረት ዘመናት ከጎርጎርዮስ 'አኖ ዶሚኒ' በ7 ወይም 8 አመታት የሚለይበት ምክንያት፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት 400 አመት ያህል በኋላ አኒያኖስ እስክንድራዊ ዘመኑን ሲቆጥረው ትስብዕቱ በመጋቢት 29 1 ዓ.ም. እንደ ሆነ ስለ ገመተ ይህ በትስብዕት ዘመን 1ኛ አመት ሆኗል። ይህ አቆጣጠር በምሥራቅ ክርስቲያን አገራት ከተቀበለ በኋላም በ443 ዓ.ም. ከሮማ ፓፓና ከምሥራቅ አቡናዎች መካከል ልዩነት ደርሶባቸው፤ በ517 ሌላ መነኩሴ ዲዮኒሲዮስ ኤክሲጉዎስ ሌላ አቆጣጠር (አኖ ዶሚኒ) አቀረበ። በሱ ግምት ትስብዕቱ የተከሠተበት ቀን ከአኒያኖስ ግምት በፊት በ8 አመታት አስቀደመው። የአኖ ዶሚኒ አቆጣጠር በምዕራብ አውሮፓ ላይኛነት በማግኘቱ የትስብእት ዘመን 1 አመተ ምህረት በአኖ ዶሚኒ 9 እ.ኤ.አ ሆነ።
የኢትዮጵያ ዘመን ኣቆጣጠር የጁልያን ዘመን ኣቆጣጠር ኣይደለም።

ወራት

የወራት አቆጣጠር የተወረሰ ከቅብጢ ዘመን አቆጣጠር፣ ይህም የወጣ ከጥንታዊ ግብጽ ዘመን አቆጣጠር ነው። ሆኖም የወሮች ስሞች በግዕዝ ተለውጠዋል።
አማርኛ
ጎርጎርዮስ     በሰግር ዓመት
መስከረም
ሰፕቴምበር 11      ሰፕቴምበር 12
ጥቅምት
ኦክቶበር 11      ኦክቶበር 12
ኅዳር
ኖቨምበር 10        ኖቨምበር 11
ታኅሣሥ
ዲሰምበር 10      ዲሰምበር 11
ጥር
ጃንዋሪ 9      ጃንዋሪ 10
የካቲት
ፈብርዋሪ 8      ፈብርዋሪ 9
መጋቢት
ማርች 10      ማርች 10
ሚያዝያ
ኤፕሪል 9      ኤፕሪል 9
ግንቦት
ሜይ 9      ሜይ 9
ሰኔ
ጁን 8      ጁን 8
ሐምሌ
ጁላይ 8      ጁላይ 8
ነሐሴ
ኦገስት 7     ኦገስት 7
ጳጉሜ
ሰፕቴምበር 6     ሰፕቴምበር 6

የኢትዮጵያ ወራት
መስከረም - ጥቅምት - ኅዳር - ታኅሣሥ - ጥር - የካቲት - መጋቢት - ሚያዝያ - ግንቦት - ሰኔ - ሐምሌ - ነሐሴ - ጳጉሜ

በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ

ቤተ መቅደስህ ቅዱስ ነው በጽድቅም ድንቅ ነው። በምድር ዳርቻ ሁሉና በሩቅ ባሕር ውስጥ ላሉ ተስፋቸው የሆንህ፥ አምላካችንና መድኃኒታችን ሆይ፥ ስማን።
በጉልበትህ ተራሮችን አጸናሃቸው፥ በኃይልም ታጥቀሃል።
የባሕሩን ጥልቀት የሞገድንም ጩኸት ታናውጣለህ።
ከተአምራትህ የተነሣ አሕዛብ ይደነግጣሉ፥ በምድር ዳርቻም የሚኖሩ ይፈራሉ የጥዋትንና የማታን መውጫ ደስ ታሰኛቸዋለህ።
ምድርን ጐበኘሃት አጠጣሃትም፥ ብልጥግናዋንም እጅግ አበዛህ የእግዚአብሔርን ወንዝ ውኃን የተመላ ነው ምግባቸውን አዘጋጀህ እንዲሁ ታሰናዳለህና።
ትልምዋን ታረካለህ፥ ቦይዋንም ታስተካክላለህ በነጠብጣብ ታለሰልሳታለህ፥ ቡቃያዋንም ትባርካለህ።
በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ፥ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል።
የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ፥ ኮረብቶችም በደስታ ይታጠቃሉ።
ማሰማርያዎች መንጎችን ለበሱ፥ ሸለቆችም በእህል ተሸፈኑ በደስታ ይጮኻሉ ይዘምራሉም።"
(መዝሙረ ዳዊት  65 : 1 - 13

በጊዜውም አለጊዜውም ጽና

                                                      2ኛ ጢሞቴዎስ  4 

1  በእግዚአብሔር ፊት በሕያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ባለው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት፥ በመገለጡና በመንግሥቱም እመክርሃለሁ፤
ቃሉን ስበክ፥ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፥ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ፥ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም።
3  ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ ስለ ሆነ፥ እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ።
4  እውነትንም ከመስማት ጆሮቻቸውን ይመልሳሉ፥ ወደ ተረትም ፈቀቅ ይላሉ።
አንተ ግን ነገርን ሁሉ በልክ አድርግመከራን ተቀበል፥ የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ አድርግ፥ አገልግሎትህን ፈጽም።
6  በመሥዋዕት እንደሚደረግ፥ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና፥ የምሄድበትም ጊዜ ደርሶአል።
7  መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤
8  ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፥ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፥ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም።

ክርስቲያናዊ ሥነ - ምግባር

የመንፈሳዊ ትምህርት ማሰሪያው የምስጢራት መወሰኛው/የመጀመሪያው/ በጥሩ ሥነ ምግባር እራስንና ሌሎችን ቀርጾ መገኘት መሆኑን እምነታችንንና ምግባራችንን በጥሩ ሥራ መግለጽ አለብን ያዕ.2፡14
አንድ ሰው ጥሩ ወይም መጥፎ ሥነ ምግባር አለው ስንል ሥነ ምግባሩን በሁለት ነገሮች ማየት አለብን፡፡
1.  ውጫዊ ሥነ ምግባር
2.  ውስጣዊ ሥነ ምግባር
ነፍስና ስጋ እንደማይለያይ ሁሉ ሃይማኖትና ምግባር አይለያዩም፡፡ ያዕ. 2፡14

የሥነ ምግባር ሕግጋት

ሕግ ማለት ለማድረግ የሚያዝ ከማድረግ የሚከለክል ውሳኔና ሥርዓት ነው፡፡ ማንኛውም ክርስቲያን በእግዚአብሔር ዘንድ ቅድስናን አግኝቶ ይኖር ዘንድ የሥነ ምግባር ሕጎች የትኞቹ እንደሆኑ ግብራቸውና ስልታቸውን ለይቶ ማወቅ ይኖርበታል፡፡

                                  የሥነ ምግባር ሕጎች


- ክርስቲያን ሁሉ መንፈሳዊነትም ሥጋዊነትም ያለው ምድራዊ ፍጡር እንደመሆኑ እርሱንም የሚመለከተው ሕግ ሁለት ጠባይ ወይም በሁለት ክፍል ያለው ሕግ ይሆናል፡፡ ይኸውም
            - መንፈሳዊ/አምላካዊ/ ሕግ
            - ሥጋዊ ሕግ በመባል የሚታወቅ ነው፡፡

መንፈሳዊ /አምላካዊ/ ሕግ ለሰው ሁሉ ከልዑል እግዚአብሔር በተፈጥሮና በጽሑፍ የተሰጠው ሲሆን ዘለዓለማዊ በመሆኑ እና ከእግዚአብሔር በመገኘቱ መንፈሳዊ ሕግ ተብሏል፡፡

ኢ - ጽሑፋዊ ሕግ በሁለት ይከፈላል፡፡
-    ሕገ ልቡና
-    ሕገ ሕሊና

ሕገ ልቡና፡- ይህ ሕግ በሰው ልቦና አንድ ጊዜ ከተጻፈ በኋላ ሳያረጅ ሳያፈጅ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ ያለ የኖረ የተፈጥሮ ሕግ ነበር፡፡ ሮሜ. 1፡14 ሕገ ልቡና የተባለው ሰው በተባለው ሁሉ በልቦናው ተጽፎ የሚገኝ እያንዳንዱ ሰው ማንም ሳያስተምረው ክፉውንና ደጉን ለይቶ ሳይነግሩት እንዲያውቅ የሚያደርገው ስለሆነ ነው፡፡

 ሕገ ልቦና ሕገ ተፈጥሮአዊ ወይም ሕገ ጠባያዊ እየተባለ የሚጠራ ሲሆን ሰው የሚመሰገነው በተፈጥሮ የተሰጠውን ይህንን ሕግ በንጽሕና በመያዙና በማዳበሩ ነው፡፡
የሰው ልጅ ክፉውን ለይቶ ያውቅበት ዘንድ የተሰጠው ሕግ ነው፡፡

ሕገ ሕሊና፡- ሕገ ሕሊና ወይም ሕሊናዊ ሕግ የእግዚአብሔር ድምጽ ለነፍስ የሚተላለፍበት በማናቸውም ክርስቲያን ሁሉ አድሮ የሚሠራ ሥነ ምግባራዊ ሕግን እንድንፈጽም የሚያነቃ አርፈን እንቀመጣለን ብንል እረፍት የሚነሳ ነው፡፡ አንድ ሰው ነፍስ አጥፍቶ እንደሆነ የሚከስ አልምቶም ከሆነ እንዲደሰት የሚያደርግ የሕሊና ዳኛ ነው፡፡

- ይኽ ሕግ አንድ ግብር እንዲፈጸም ወይም እንዳይፈጸም ማስጠንቀቂያና ምርጫን የሚያደርግ ሲሆን ከተደረግ በኋላ መጥፎ እንደሆነ መጸጸትን ሐዘንን ያመጣል መልካም ከሆነ ደግሞ ደስታን መጽናናትን ይሰጠናል፡፡ ማንኛውም የክርስትና ተከታይ የሆነ በስሙ የተጠራ ግን ሁሉ ፍለጋውን የሚከተሉ ሁሉ የራሱን ሕሊና ምርጫ ማክበር የእግዚአብሔርን ድምጽ መስማት ግዴታው ይሆናል፡፡ እየተጠራጠረ እያመነታም የሚሠራ ሰው ሁሉ ከሕሊናው ግምት ውጭ ይሠራል ማለት ነው፡፡ ይህም እርሱን መበደል ነው፡፡ ሮሜ. 14፡23 ስለዚህ ሳይሠራ ያመልጣል ከሁሉ አስቀድሞ በምንሠራው ሥራ እንደ ሃይማኖታችን ጽናት መጠራጠር አይገባንም፡፡ ይህንን ሁሉ ለማስወገድ ከሁሉ በፊት

1.  ጸሎት መጸለይ ማለት የሚሠሩትን ሁሉ ‹‹ ወይኩን ፈቃድከ ›› ብሎ መጠየቅ
2.  ዓለማዊ ማንኛውም ከእግዚአብሔር ፍቅር የተነሳ የእሱን አምልኮትና ፍቅር መግለጫ መሆን ይኖርበታል፡፡ አምላክ ሰውን አፍቅሮ አንድያ ልጁን ለእኛ አሳልፎ ቤዛ እንደሰጠ ሁሉ ዮሐ. 3፡16
3.  ስለ እግዚአብሔር ክብር ተብሎ የሚሰራ መሆን ይኖርበታል 1ቆሮ 10፡31
4.  ስለ ባልንጀራው ፍቅር መሆን ይገባዋል፡፡

አሥርቱ ትዕዛዛት

      ከእግዚአብሔር አምላክ በቀጥታ በሙሴ አማካኝነት ለእስራኤላውያን የተሰጠ ሕግ ነው፡፡ የተሰጡትም እስራኤላውያን ከግብጽ ከወጡ በ3ኛው ወር ፋሲካን ካከበሩ በ3ኛው ቀን በደብረ ሲና ሰፍረው ሳለ ነበር፡፡ ዘፀ. 19፡1-4 በዘዳ. 34፡28 ዘዳ. 4፡13 ላይ አሥሩ ትዕዛዛት አሥር መሆናቸውን እንረዳለን፡፡
በዝርዝር ተጽፈው የሚገኙት ግን በዘዳ. 20፡ 3 እና17 እና ዘዳ. 5፡5-21 ላይ ነው፡፡ አሥርቱ ቃላትና ስድስቱ ቃላተ ወንጌል ለእስራኤል ዘስጋና ለእስራኤል ዘነፍስ የተዘጋጁ ስለሆነ ሁላችንንም ይመለከታል፡፡ እነርሱም፡-

1.  ‹‹ እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ፡፡ ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ የማናቸውንም ምሳሌ የተቀረጸውን ምስል ለአንተ አታድርግ፤ አትስገድላቸው፤ አታምልካቸው ›› ዘፀ. 20፡2-6
2.  ‹‹ የእግዚአብሔር የአምላክን ስም በከንቱ አትጥራ፡፡ ›› ዘፀ. 20፡7
3.  ‹‹ የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ /አክብረውም/ ›› ዘፀ. 20፡ 8
4.  ‹‹ አባትህንና እናትህን አክብር ›› ዘዳ. 20፡12
5.  ‹‹ አትግደል ›› ዘፀ. 20፡13
6.  ‹‹ አታመንዝር ›› ዘፀ. 20፡14
7.  ‹‹ አትስረቅ ›› ዘፀ. 20፡15
8.  ‹‹ በሐሰት አትመስክር ›› ዘፀ. 20፡16
9.  ‹‹ አትመኝ ›› ዘፀ. 20፡17
10.  ‹‹ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ ›› ዘሌ. 19፡18


-    አሥርቱ ሕግጋት የብሉይ ኪዳን መሠረቶች ናቸው፡፡ የእግዚአብሔርን ሕግ ብትጠብቁ ብትፈጽሙትም ሕዝቤ ትሆናላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ ብሎ ቃልኪዳን ገባ፡፡ ሕዝቡም በአንድ አፍ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ‹‹እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን እንታዘዛለን›› ብለው ቃል ኪዳን ገቡ፡፡ ዘፀ. 19፡8፤ 24፡1-8 ቅዱስ ጳውሎስም እንደነገረን ይህ ፊተኛው ኪዳን ያለ ደም አልተመረቀምና ዕብ. 18፡ 22 ሙሴ ኪዳኑን ለማጽናት የደም መርጨትን ሥርዓት እንዳደረገ በሐዲስ ኪዳንም ቢሆን ሥነ ሥርዐቱ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ያላቸው ሕግጋት ናቸው፡፡ ማቴ 5፡17፣ 19፡15-22 ፣ዮሐ1፡12 እግዚአብሔር ሕዝቦቹና ልጆቹ ሊያረገን ይህን ታላቅ ተስፋ በመስጠት ቃል ከገባልን እኛ ደግሞ ትዕዛዙን ለመጠበቅ ምን ያህል ቃል ገብተንለታል? ጌታችን ብትወዱኝስ ትዕዛዜን ጠብቁ ዮሐ 14፡15 እንዲሁም ከሆነ እንደ እስራኤላውያን እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን እንታዘዛለን ብለን ከሁሉ በፊት ለእግዚአብሔር ቃል መግባት አለብን፡፡ ክርስትናውን ስንጀምር የመጀመርያ ሥራችን መሆን ያለበት ይህ ነው፡፡


                  የዐሥርቱ ትዕዛዛት ዓላማ

ዐሥርቱ ትዕዛዛት የተሰጡት በሚከተሉት ዓላማዎች ነው፡፡ ይኸውም፡-

1.  ከግብጽ ምድር ስላወጣቸው ውለታውን እንዲያስቡ
2.  ወደ ፊት በአረማዊያን መካከል ሲመላለሱ ከኃጢአት እንዲቆጠቡ
3.  መንፈሳዊ አካሄዳቸው ምን ምን አቅጣጫ መከተል እንዳለበት ለማሳየት ነው፡፡

የዐሥርቱ ትዕዛዛት አከፋፈል

የክርስቲያን ሕግ የፍቅር ሕግ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሌላውን የሚወድ ሕግን ፈጽሞበታል ካለ በኋላ ከዐሥርቱ ትዕዛዛት የተወሰኑትን በመጥቀስ ፍቅር የሕግ  ሁሉ ፍጻሜ መሆኑን በግልጽ ይነግራል፡፡ ሮሜ 13፡8-10 ታዲያ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረ ፍቅር በሁለት ይከፈላል፡፡ ማቴ 22፡34-41

ፍቅረ እግዚአብሔር       2 ፍቅረ ቢጽ

1ፍቅረ እግዚአብሔር ከአንደኛ ትዕዛዝ እስከ ሦስተኛው ያሉት ሲሆኑ እግዚአብሔርን የሚመለከቱ ናቸው፡፡

2ፍቅረ ቢጽ ከአራተኛ ትዕዛዝ እስከ አሥረኛ ትዕዛዝ ያሉት ሲሆኑ በለእንጀራን የሚመለከቱ ናቸው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በአዎንታዊና በአሉታ ከመነገራቸው አንጻር በሁለት ይከፈላሉ ይኸውም፡-
      1. ሕግ በአሉታ የተነገሩ /አታድርግ/
      2. ትዕዛዝ በአዎንታ የተነገሩ /አድርግ/

ከዚህም ሌላ ከአፈጻጸማቸው አንጻር ሲታዩ በሦስት ይከፈላሉ፡፡

1.  በሐልዮ የሚፈጸሙ 1፣3፣4 እና 9 በሐሳብ
2.  በነቢብ የሚፈጸሙ 2፣ 8 በመናገር
3.  በገቢር የሚፈጸሙ 5፣6፣7 እና 10 በሥራ ናቸው፡፡


ምንጭ ፡- ሕግጋተ እግዚአብሔር መጽሐፈ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ 3ኛ የተወሰደ እንዲሁም የ/መ/ገ/ጽ/ቅ/ጊ/ቤ/ክ/ሰ/ት/ቤት

Wednesday, September 7, 2011

የ36ቱ ቅዱሳን አንዕስት
ስም ዝርዝርና የሚውሉበት ቀን
1. ኤልሳቤጥ የካቲት 16 ቀን
2. ሐና መስከረም 7 ቀን
3. ቤርዜዳን ወይም ቤርስት ታህሳስ 10 ቀን
4. መልቲዳን ወይም ማርና ጥር 4 ቀን
5. ሰሎሜ ግንቦት 25 ቀን
6. ማርያም መቅደላዊት ነሐሴ6 ቀን
7. ማርያም እንተ እፍረት እህተ አልአዛር የካቲት 6 ቀን
8. ሐና ነቢይት የካቲት 20 እና ጥቅምት 6 ቀን
9. ማርያም እሞሙ ለደቂቅ ዘብድዎስ ጥር 18 ቀን
10. ሶፍያ (በርበራ) ጥር 30 ቀን
11. ዮልያና (ዮና) ኅዳር 18 ቀን
12. ሶፍያ (መርኬዛ) ጥር 30 ቀን
13. አውጋንያን (ጲላግያ) ጥቅምት 11 ቀን
14. አርሴማ ግንቦት 11 ቀን
15. ዮስቲና ጥር 30 ቀን
16. ጤግላ ነሐሴ 6 ቀን
17. አርኒ (ሶፍያ) ኅዳር 10 ቀን
18. እሌኒ ጥር 29 ቀን
19. ኢዮጰራቅሊያ መጋቢት 26 እና ነሐሴ 2 ቀን
20. ቴዎክላ (ቴኦድራ) ጥር 4 ቀን
21. ክርስቲያና (አጥሩኒስ) ኅዳር 18
22. ጥቅሞላ (አሞና) ጥር 30 ቀን
23. ጲስ ጥር 30 ቀን
24. አላጲስ ጥር 30 ቀን
25. አጋጲስ ጥር 30 ቀን
26. እርሶንያ (አርኒ) ጥር 30 ቀን
27. ጲላግያ ጥር 30 እና ጥቅምት 11 ቀን
28. አንጦልያ (ሉክያ) የካቲት 25 ቀን
29. አሞን (ሶፍያ) ጥር 15 አና ነሐሴ 3 ቀን
30. ኢየሉጣ ነሐሴ 6 ቀን
31. መሪና ሐምሌ 27 ቀን
32. ማርታ እህተ አልአዛር ጥር 18 እና ግንቦት 27 ቀን
33. ማርያም የማርቆስ እናት ጥር 30 ቀን
34. ሣራ (ሶፍያ) የይሁዳ እናት ጥር 30 ቀን
35. ዮሐና (ዮላና) የኩዛ ሚስት ታህሳስ 26 ቀን
36. ሶስና ግንቦት 12 ቀን ናቸው፡፡
እነዚህ ጌታችንን ሲከተሉ ግማሾቹ በጉልበታቸው ግማሾቹ አብረው በማደርና አብረው በመዋል ከጌታችን ሳይለዩ አገልግለው በኋላም መንፈስ ቅዱስ በወረደበት ጊዜ አብረው ስለነበሩ ግማሾቹ ከሐዋርያት ጋር ተከፋፍለው ተሰማርተዋል፡፡

By: Esayas Habte-Mariam (Kidane-mihrt.org)

ጳጉሜ

ጳጉሜ ማለት ጭማሪ ማለት ነው፡፡ ይህም በዓመቱ መጨረሻ ላይ አምስት ወይም ስድስት ቀን በመሆን የምትመጣ ናት፡፡ በአራት ዓመት አንዴ ማለትም በዘመነ ዮሐንስ ጳጉሜ ስድስት ቀን ይሆናል፡፡ በዚህም ሐገራችን ኢትዮጵያ የአስራ ሦስት ወራት ጸጋ / Thirty months of sunshine / በመባ ትታወቃች ትለያለች፡፡ ጳጉሜ በዘመነ ዮሐንስ ስድስት በምትሆንበት ጊዜ ጾመ ነቢያት / የገና ጾም/ ህዳር 14 ቀን ይገባና ታህሳስ 28 ቀን ጾሙ ተፈቶ የልደት በዓል ይከበራል፡፡ በቅድስት ቤተክርስቲያን ካሉት ሁለት የፈቃድ አጽዋማት መካከል አንዱ በዚህ በጳጉሜ ወር የምንጾመው የፈቃድ ጾም ነው፡፡ ይህም ጾመ ዮዲት በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ ግን እንደ አንደኛው የፈቃድ ጾም /ጽጌ ጾም/ በብዙዋኑ ዘንድ የታወቀ አይደለም፡፡ የዮዲት ጾም የሚባለውም እርሷ ስለ ጾመችው ነው፡፡ እዚህ ላይ ዮዲት ተብላ የተጠቀሰችው በቤተክርስቲያን ታሪክ ትምህርት ላይ በጥፋት ሥራዋ በተደጋጋሚ የምትጠቀሰው ዮዲት ጉዲት እንዳልሆነች ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡ ወደ ታሪኩ ስንመለስ የፋርስ ንጉስ ናቡከደነጾር በሠራዊቱ ተመክቶ ሹም ጠላት አጥፋ ድንበር አስፋ ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበልህ ያላመነውን እያሳመንህ ና ብሎ ለጦር አበጋዙ ለሆሎፎርኒስ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ ዮዲ 2፡-2-7፡፡ እርሱም እንደታዘዘው በኃይላቸው የታመኑ 12ሺህ እግረኞችንና በፈረስ የተቀመጡ 12ሺህ ጦረኞችን እየመራ ዘምቶ ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበለ ያላመነውን እያሳመነ ብዙ ሀገሮችን እያጠፋ ሲሔድ ከአይሁድ ከተማ ደረሰ በዚህም ብዙ ጥፋ በመድረሱ የእስራኤል ልጆች አለቀሱ፡፡ ዮዲት ባሏ ሞቶባት ከወንድ ርቃ ንጽሕናዋን ጠብቃ በጾም በቀኖና በሀዘን ተወስና ትኖራለች በተፈጠረው ጥፋት ህዝቡ ላይ ለመጣው መከራ ማቅ ለብሳ በራስዋ ላይ ትብያ ነስንሳ ወደ እግዚአብሔር አለቀሰች፡፡ የፍጥረቱን ጥፋት የማይሻ እግዚአብሔር አምላክም ሕዝቡን የሚያድኑበትን መንገድ ለመጠየቅ ሱባኤ በገባች በሦስተኛው ቀን ገለፀላት፡፡ ዮዲ 8፡-2 ፡፡ ከዚህ በኋላ ጠላታቸውን በዮዲት ምክንያት እስራኤላውያን እስከ ዮርዳኖስ እየተከተሉ አጥፍተዋቸዋል፡፡
ዮዲት ጠላቷን ለማጥፋት የቻለችው በጾምና በጸሎት ከእግዚአብሔር አምላክ ኃይል አግኝታ ነው፡፡ ስለዚህ ምዕመናን ጥንተ ጠላታችን ሰይጣንን ፈቃደ ሥጋን ለማሸነፍ በጾም ከፈጣሪያችን ኃይልን መጎናጸፍ አለብን ብለው ጳጉሜን በፈቃድ ይጾማሉ፡፡
የጳጉሜ ወር ዕለተ ምጽአት የሚታሰብበትም ወር ነው፡፡ ይህም ጳጉሜ የዓመታት መሸጋገሪያ ጨለማው የክረምት ወቅት ወደ ማብቂያው የምናልፍባት እንደሆነች ሁሉ ምጽአትም ከጊዜያዊው ወደ ዘላለማዊ ከምድራዊ ወደ ሰማያዊ ከዚህ ዓለም ወደ ወዲያኛው መሸጋገሪያ ነውና ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Source: kidanemhret.org 

Tuesday, September 6, 2011

ኢትዮጵያ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአሥራት አገር ናት፡፡

  
             ሊቃውንትም ነቢያት የተነበዩትን ትንቢት የቆጠሩትን ሱባዔ መሠረት በማድረግ ቅድስት ድንግል ማርያም በኪደተ እግሯ ኢትዮጵያን መባረኳን ያስተምራሉ፡፡ «ነቢዩ ዕንባቆም የኢትዮጵያ ድኳኖች ሲጨነቁ ዐየሁ፤» ዕንባ. 3፡7 ብሎ የተናገረው ቃለ ትንቢት እመቤታችን የኢትዮጵያን አውራጃዎች ለመባረኳ ማስረጃ መሆኑን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይተረጉማሉ፤ ያመሠጥራሉ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ኢትዮጵያን ለእናቱ አሥራት አድርጐ በመሥጠቱ በእርሷ በኩል ለሰው ልጆች ሁሉ የሚሆን የነገረ ድኅነት ምሥጢር በመከናወኑ ኢትዮጵያውያን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የተለየ ፍቅር አለን፡፡ የአብነት /የቆሎ/ ተማሪዎች በትምህርት ዓለም ከአንዱ ወደሌላው እየተዘዋወሩ /የአብነት/ ትምህርት ሲማሩ በእንተ ስማ ለማርያም፤ ስለማርያም እያሉ፡፡ የእመቤታችን ስም ስንቅ ምግብ ሆኗቸው ይጠቀሙበታል፡፡ ግሼን ደብረ ከርቤ የልጇ ግማደ መስቀል ከከተመበት አምባም የሚጓዙ ምእመናን «አንድ እፍኝ ሽምብራ አልያዝኩም ከቤቴ ስሟ ስንቅ ነው የእመቤቴ» እያሉ በፍቅሯ ተማርከው ግብር ሰፍረው ዕጣን ቋጥረው ሱባዔ እየገቡ ይማፀኗታል፡፡ እርሷም ከልጇ ዘንድ ባገኘችው የመወደድ ሞገስ ምልጃቸውን በመቀበል ጸሎታችውን በማሣረግ የእናትነት ሥራ ሥትሠራላቸው ኖራለች፡፡ ዛሬም እየሠራች ነው፡፡ እመቤታችን ከልጇ ያገኘችውን /የተቀበለችውን ቃል ኪዳን መሠረት በማድረግ በዐራቱ ማእዘን «ሰዓሊ ለነ ቅድስት፤ ቅድስት ሆይ ለምኝልን» የማይላት የለም፡፡ በፍቅሯ ተደስተው በአማላጅነቷ ተማምነው «የእመቤቴ ፍቅሯ እንደ ሰማይ ክዋክብት፣ እንደምድር አሸዋ በዝቶልኝ፣ እንደ ልብስ ለብሼው፣ እንደምግብ ተመግቤው» እያሉ ተማጽነው ልመናቸው ሠምሮ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊው፣ ቅዱስ ያሬድ ዘኢትዮጵያና አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ያዘጋጁላትን፣ አባ ጽጌ ድንግል የደረሱላትን የምስጋና መጻሕፍት በመድገም እመቤታችን ዘወትር መማጸን የቀደምት ኢትዮጵያውያንም የዛሬዎች ገዳማውያንና ምእመናን ዕለታዊ ግብር ነው፡፡

ጌታችን ለቀደሙት ቅዱሳን ሐዋርያት እመቤታችን አማላጅ እና እናት ሆኗ እንድታገለግል በገቢርም በነቢብም ከአደራ ቃል ጋር አስረክቧል፡፡ በገቢር በቃና ዘገሊላ የሰውን ችግር ፈጥና የምትረዳ ርኅርኅሪት እናት አማላጅ መሆኗን አሳይቷል፡፡ «ለዚሁም የወይን ጠጅ አልቆባቸዋል» ብላ ያቀረበችው ቃለ ምልጃ ምስክር ነው፡፡ እናት ሆኗ እንድታጽናናቸው በቅዱስ ዮሐንስ በኩል ከእግረ መስቀሉ ስር ሰባቱን አጽራሐ መስቀል ሲያስተጋባ ቅዱስ ዮሐንስን ጠርቶ «እኖኋት እናትህ፤ ድንግል ማርያምን ጠርቶ እነሆ ልጅሽ» ዮሐ. 19፡26፡፡ በማለት እመቤታችን የእናት ሥራ ለሁሉም ቅዱሳን ሐዋርያት እንድትሠራላቸው ምእመናንም ልጅ እንዲሆኗት በማያሻማ ቃሉ ተናግሯል፡፡
ቅዱሳን ሐዋርያት እመቤታችንን በእናትነት ከተረከቧት ጊዜ ጀምረው ልጇ በዕርገት በአካለ ሥጋ ሲለይ እንደ ልጅ አገልግለዋታል፡፡ በቤታቸው አኑረዋታል፤ ብትሠወርባቸው ፈልገዋታል፡፡ ብትርቃቸው ናፍቀዋታል፡፡ እርሷም ሲጠሯት ታደምጣቸዋለች፣ ሲፈልጓት ትገኝላቸዋለች፡፡ ይኸውም የሆነው ልጇ በአዳምና በልጆቿ ኃጢአት ምክንያት የፈረደውን ለራሱም ያላስቀረውን ሥጋዊ ሞት እናቱ ብትቀምስ በእናትነት የተረከቧት ቅዱሳን ሐዋርያት መካነ ዕረፍት ለይተው በንጹሕ በፍታ ከፍነው በጌቴ ሰማኒ እንደቀበሯት ስለ እመቤታችን የተጻፉ መጻሕፍት በዝርዝር ያስረዳሉ፡፡
የእመቤታችን ሥጋዊ ዕረፍት «ከመ ትንሣኤ ወልዳ» እንደ ልጇ ትንሣኤ ነውና ሙስና መቃብር ሳያገኛት ከሦስት ቀናት ሥጋዊ ዕረፍት በኋላ ከሞት ተነሥታ ወደ ሰማይ ስታርግ በዕለተ ቀብሯ ያልተገኘው ቅዱስ ቶማስ ደመና ጠቅሶ በደመና ሰረገላ ሲመጣ ዕርገቷን ይረዳል፡፡ እማኝ ደግሞ የተከፈነችበትን በፍታ /ጨርቅ/ ይቀበላታል፡፡ ለቅዱስ ቶማስ የተገለጠው የዕረፍቷ ምሥጢር ሌሎች ቅዱሳን ሐዋርያት እንዲገለጥላቸው ቢማጸኑ እመቤታችን ዳግም ተገልጻላቸው፡፡ ትንሣኤዋን ለማየት በቅተዋል፡፡
እነዚህ በቅድስናቸው የተመሠከረላቸው ቅዱሳን እመቤታችንን በሁለት ሱባዔ ማግኘታቸውን መሠረት በማድረግ በቤተ ክርስቲያናችን ከነሐሴ 1-16 በየዓመቱ አንደሚጾም ይታወቃል፡፡ ይህ እመቤታችንን የምንማጸንበት ጾመ ፍልሰታ ቤተ ክርስቲያናችን መፍትሄ የምትፈልግባቸውን ጉዳዮች ለእመቤታችን የምታቀርብበት ሰዓት ነው ብለን እናምናለን፡፡

ኢትዮጵያ የእመቤታችን አሥራት አገር ስትሆን እመቤታችን ለኢትዮጵያውያን እናት መሆኗ እየተነገረ ለምን በፈተና ውስጥ አለፍን? ልጇ በአሥራት ኢትዮጵያን የሰጠባት ሀገር አባቶች ማስፈራሪያ ሲደርስባቸው መንፈሳዊነት /ኀይለ መንሳዊ/ ተዘንግቶ ሥጋዊ ጥበብ በቤተ ክርስቲያን መድረክ ሲታይ ምን ይባላል? «እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋት ርኩሰት በተቀደሰችው ሥፍራ ቆሞ ስታዩ አንባቢው ያስተውል በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራራዎች ይሽሹ» ማቴ. 24፡15፡፡ የተባለው ቀን ደርሶ ይሆንን?
ቤተ ክርስቲያን ለረጅም ዓመታት ለገጠማት ችግር መፍትሔ እመቤታችን እጅ ላይ አለ ብለን እናምናለን፡፡ እመቤታችን ብትሠወርባቸው አባቶች ሱባዔ ገብተው እንዳገኟት የፍቅር እናት ናትና ፍቅር አንድነት እንድትሰጠን እርሷን መማጸን፤ የዶኪማስን ጓዳ እንደሞላች የጐደለውን እንድትሞላ ውዳሴዋን እየደገሙ ድንግልን መማጸን ያስፈልጋል፡፡

በውዳሴ ማርያም፣ በጸሎተ ማርያም የሚመካ በጉልበቱ አይመካም፡፡ ጊዜ ረዳኝ ብሎ በወገኖቹ ላይ ግፍ አይፈጽምም፡፡ ስለዚህ በዚህ በወርኀ ጾም እመቤታችን ምልጃዋ ከአገራችን፣ ከቤተ ክርስቲያናችን ጋር እንዲሆን በሱባዔ እንማጸናት፡፡
በጾመ ፍልሰታ ከሊሂቅ እስከ ደቂቅ በማስቀደስ፣ በጾምና በጸሎት ሁለቱን ሳምንታት እንደሚያሳልፉት ይታወቃል፡፡ በሱባዔው የቤተ ክርስቲያናችን ችግሮች የሚወገድበት ምእመናን በበረከት የሚጐበኙበት ቅድስና የሚሰፍንበት መንፈሳዊነት ትልቅ ከበሬታ የሚገኝበት ጾም እንዲሆን ሁሉም ምእመን መትጋት አለበት፡፡

ሁለቱ ሳምንታት በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ዘወትር እየተገኘን ምሕላ የምናደርስበት፣ የተጣላነውን ይቅር ለእግዚአብሔር፣ የበደልነውን የምንክስበት ጾም መሆን አለበት፡፡ ቀናቱን እየቆጠርን እስከተወሰነው ሰዓት ብቻ መጾም ብቻ በሕይወታችን መሠረታዊ ለውጥ አያመጣም፡፡ እመቤታችን የአገራችን አሥራት የሁላችን እናት በመሆኗ የእናትነት ሥራ እንድትሠራልን በሚገባ ልንማጸናት ይገባል እንጂ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ሱባዔ ብለን ውዳሴ ማርያም በደገመ አፋችን ሰው የምናማ በሰው ሕይወት ገብተን የምንፈተፍት ከሆነ እመቤታችንን አናውቃትም፡ እመቤታችንም አታውቀንም፡፡ ስለዚህ ጾመ ፍልሰታን እስኪ ሁላችን ኢትዮጵያውያን የተዋሕዶ ልጆች ድንግልን በአንድ ድምፅ እንጥራት፡፡
የእመቤታችንን ጾመ ፍልሰታ፤ እንደ ብርሃን ተስፋ በማድረግ በተለይም ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚተጉ አባቶች እና ምእመናን ለተሰደዱ፣ ለተራቡ፣ በፈተና ውስጥ ለሚገኙ ይማጸኑ እንላለን፡፡ ውዳሴ ማርያሙ፤ ሰዓታቱ ጨለማን ተገን አድርጐ ከሚቃጣ ማስፈራሪያ እና ዛቻ ድርብ ኀይል አለው፤ እስኪ ለቅድስና፣ ለንጽሕና ለመንፈሳዊነት ቅድሚያ እንስጥና የእግዚአብሔርን ብድራት እንጠብቅ፡፡ ጾመ ፍልሰታ መንፈሳዊነት፣ እውነት፣ ቅድስና የጠራ አሠራር፣ በቤተ ክርስቲያን የሚሰፍንበት እንዲሆን እንመኛለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Source: Kidane-Mihrt.org by G/M

የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ነገር እንደምን ነው ቢሉ፦

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም
ነሐሴ 7 ቀን    ተፀነሰች፣
ግንቦት 1 ቀን ተወለደች፣
ታህሳስ 3 ቀን ወደ ቤተመቅደስ ገባች
መጋቢት 29 ቀን አምላክን በድንግልና ፀነሰች፣
ታህሳስ 29 ቀን አምላክን በድንግልና ወለደች፣
የካቲት 16 ቀን የምሕረት ቃል ኪዳን ከልጅዋ ከወዳጅዋ ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ተቀበለች፣
ጥር 21 ቀን በክብር አረፈች
ነሐሴ 14 ቀን በክብር ተቀበረች፣
ነሐሴ 16 ቀን እንደ ልጇ ትንሳኤ ተነስታ ዐረገች 
                        "አቤቱ ወደረፍትህ ተነስ አንተና የመቅደስህ ታቦት" መዝ.131፡8/
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከተወደደው ልጃ ታማልደን፣ በበረከት፣ በረድኤት አትለየን፡፡ አሜን!!!
Source: Kidane- Mihret.org

Monday, September 5, 2011

ቅዱስ ሩፋኤል ጦቢት እና ጦቢያ

"ስለዚህ እንግዶችን መቀበል አንርሳ፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳንዶች ሳያውቁ የመላእክትን እንግድነት ተቀብለዋልና፡፡"  ዕብ. 13.1-2 ፡፡
በየዓመቱ ጳጉሜ 3 የቅዱስ ሩፋኤል መልአክ መታሰቢያ ነው ፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል የጦቢትን ዓይን ያበራና ወለተ ራጉኤልን ተቆራኝቷት ከነበረው ጋኔን ያላቀቃት መሆኑ በመጽሐፈ ጦቢት በስፋት ተገልጿል፡፡
ጦቢት በፋርስ ንጉሥ በስልምናሶር ዘመን የተማረከ ከነገደ ንፍታሌም የተወለደ ጽኑዕ እሥራኤላዊ ነው፡፡ እግዚአብሔር በስልምናሶር ፊት የመወደድን ግርማና ባለሟልነትን ስለ ሰጠው አለቃ አድርጎ ሾሞት ነበር፡፡ ለወገኖቹ ምጽዋት በመስጠት ሕገ ርትዕን በመሥራት የተጋ ሰው ነበር፡፡ ሐና የምትባል ሚስት አግብቶ አንድ ልጅ ወልዷል፡፡ ስልምናሶር ሞቶ ሰናክሬም በነገሠ ጊዜ ከሹመቱ ስለሻረው ደግሞ ወደ ምድያም መሔድ አልቻለም፡፡
ሣራ ወለተ ራጉኤል ከፍተኛ ችግር ደርሶባት ነበር፡፡ ችግሯም ሕፃናት ወልጄ ቤት ንብረት ይዤ እኖራለሁ በማለት ባል አገባች ነገር ግን በዚች ሴት አስማንድዮስ የሚባል ጋኔን አድሮ ያገባችውን ሰው ገደለባት ሌላም ባል ብታገባ ሞተባት እንደዚህ እየሆነ በጠቅላላ ሰባት ድረስ ያሉትን ባሎችን ገደለባት፡፡

የራጉኤል ልጅ ሣራ በዚህ ሁኔታ በኀዘን ተውጣ ስትኖር በነበረበት ጊዜ ጦቢት ሸምግሎ ስለ ነበር ልጁ ጦብያን ጠርቶ በዚህ ዓለም እስካለ ድረስ ሊሠራው የሚገባውን መንፈሳዊ ሥራ እንዲሠራ በጥብቅ ከመከረው በኋላ በመጨረሻ ልጄ እኔ ሳልሞት የኑሮ ጓደኛህን ፈልግ፣ ስትፈልግም ዕወቅበት፣ እኛ የአብርሃም የይስሐቅና የያዕቆብ ዘሮች ነን ስለዚህ ከእነርሱ ወገን የሆነችውን እንድታገባ ከዚህም ሌላ ከገባኤል ዘንድ በአደራ ያስቀመጥኩት ገንዘብ አለና እኔ በሕይወት እያለሁ ብታመጣው የተሻለ ነው አለው፡፡
ጦብያም ያባቱን ምክር ሁሉ በጽሞና ካዳመጠ በኋላ ‹አባባ የነገርከኝን ነገር ሁሉ በተቻለኝ መጠን እፈጽማለሁ ግን ከገባኤል ጋር ስላለው ገንዘብ እንዴት ለማምጣት እችላለሁ? ሀገሩን አላውቀውም› አለው፡፡ በዚህ ጊዜ ነገሩ አሳሳቢ ሆኖ ስላገኘው ጦቢት ልጁ ጦብያን ‹አብሮህ የሚሄድ ሰው እስቲ ፈልግ ምናልባት አብሮ የሚሄድ ጓደኛ ታገኝ ይሆናል ደመወዝም ሰጥተን ቢሆን ካንተ ጋር የሚሄድ አንድ ሰው ግድ ያስፈልግሃልና ሂድ ሰው ፈልግ› አለው፡፡
ጦቢት ስንቃቸውን አስይዞ ጦብያንና ቅዱስ ሩፋኤልን ሸኛቸው
አብሮት የሚሄደው ሰው ለመፈለግም ቢሄድ አንድ መልካም ጐበዝ አገኘ ይኸውም መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ጦብያ ግን መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል መሆኑን ፈጽሞ አላወቀም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ጦብያ መልአኩን ሰው መስሎ እንዳገኘው ‹የሜዶን ክፍል ወደ ምትሆነውና ራጌስ ወደ ምትባለው ሀገር ከእኔ ጋር ለመሄድ ትችላለህን የድካምህን ዋጋ የጠየቅኸውን ያህል እሰጥሃለሁ› ሲል ጠየቀው ቅዱስ ሩፋኤልም ‹እሺ ካንተ ጋር ለመሄድ ፈቃኛ ነኝ መንገዱንም ሆነ ሀገሩን በሚገባ አውቀዋለሁ ከገባኤል ቤት ብዙ ጊዜ ኑሬአለሁና› አለው፡፡
ከዚህ በኋላ ጦብያ በል ከአባቴ ጋር ላስተዋውቅህ ብሎ ወደ አባቱ ወስዶ አስተዋወቀው ከእኔ ጋር የሚሄደው ሰው ይህ ነው በማለት ካስተዋወቀው በኋላ ጦቢትም ከወዴት እንደ መጣ ማን ተብሎ እንደሚጠራ ጠየቀው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤልም የታላቅ ወንድምህ ወገን ከመሆንም ሌላ ስሜም አዛርያስ ይባላል አለው፡፡ ጦቢ. 5.12 ፡፡ ጦቢትም የወንድሙ ዘመድ መሆኑን ከሰማ በኋላ ‹አንተስ ወንድሜ ነህ በል የልጄ የጦብያን ነገር አደራ ከሀገር ወጥቶ አያውቅምና እንዳይደነግጥ ደኅና አድርገህ እንድትይዝልኝ› ብሎ ስንቃቸውን አስይዞ ሸኛቸው፡፡
አዛርያስ /ቅዱስ ሩፋኤል/ በመንገድ ይመራው ነበር፡፡ በዚህም ቅዱስ ሩፋኤል ‹መራኄ ፍኖት› /መንገድ መሪ/ ይባላል፡፡ እነርሱ ሲሄዱ ውለው ማታ ጤግሮስ ከተባለው ታላቅ ወንዝ ደረሱና ከዚያም ለማደር ወሰኑ፡፡ በዚህ ጊዜ ከድካሙ ጽናት የተነሣ ጦብያ ሊታጠብ ወደ ወንዙ ወረደና ልብሱን አውልቆ መታጠብ ሲጀምር አንድ ዓሣ ሊውጠው  ከባሕር ወጣ፡፡ ወዲያውም መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ጦብያን ያዘው ፤ ዓሣውን እንዳትለቀው አለው ፤ ጦቢያም ከዓሳው ጋር ግብ ግብ ገጥሞ እየጐተተ ወደ የብስ አወጣው ፡፡ከዚህ በኋላ ቅዱስ ሩፋኤል ጦብያን እንዲህ ሲል አዘዘው፡፡  ዓሣውን እረደው ጉበቱንና ሐሞቱን ተጠንቅቀህ ያዘው ሌላውን ግን ጠብሰን እንበላዋለን አለው፡፡
ጦብያም መልአኩ እንዳዘዘው ዓሣውን አርዶ ሐሞቱንና ጉበቱን ያዘ
ጦብያም መልአኩ እንዳዘዘው ዓሣውን አርዶ ሐሞቱንና ጉበቱን ያዘ፣ ሌላውን ሥጋውን ግን ጠብሰው ራታቸው አደረጉት፡፡ ጦብያም ያንን የዓሣውን ጉበትና ሐሞት ለምን እንደሚያገለግል ለመረዳት ‹ይህን ያዘው ያልከኝ ለምንድን ነው?› ሲል ጠየቀው ቅዱስ ሩፋኤልም ጋኔን ያደረበት ሰው ሲገኝ ይህንን ከዕጣን ጋር ቢያጤሱበት ጋኔኑ ይለቃል ሲል መለሰለት፣፡
በዚህ ሁኔታ አንድ ባንድ ሲነጋገሩ ከቆዩ በኋላ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ጦብያን ‹ዛሬ ከራጉኤል ቤት እናድራለን፡፡ እርሱ ዘመድህ ነው፡፡ የእርሱም ልጅ ሣራ የምትባል ቆንጆ ልጅ አለችው፡፡ እሷን ለሚስትነት ይሰጥህ ዘንድ ለራጉኤል እነግርልሃለሁ› አለው፡፡
ጦብያም ‹ያች ልጅ ከዚህ በፊት ሰባት ሰዎች እንዳገቧትና ሰባቱም ባገቧት ሌሊት ደርቀው /ሞተው/ እንደሚያድሩ ሰምቻለሁ፡፡ ስለዚህ እኔ ላባቴና ለእናቴ አንድ ልጅ ነኝ እርስዋን አግብቼ ከዚህ በፊት እንዳገቧት ሰዎች እኔም የሞትኩ እንደሆነ አባቴንና እናቴን የሚረዳቸው የለም ቢሞቱም የሚቀብራቸው አያገኙምና እፈራለሁ› አለው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ግን  ‹አባትህ ከዘመዶችህ ወገን ካልሆኑ በስተቀር ሌላ ሴት እንዳታገባ ሲል የነገረህን ረሳኸውን? በል ሰባት ባሎቿ ሙተውባታል ስለምትለው እኔ መድኃኒቱን አሳይሃለሁ ፤ አይዞህ አትፍራ አትሞትም የዓሣውን ሐሞትና ጉበቱን ለምን መሰለህ ያዘው ያልኩህ ? እንግዲህ ሐሞቱንና ጉበቱን ከዕጣን ጋር  ጨምረህ ስታጤስበት በሣራ አድሮ የነበረው አስማንድዮስ የተባለው ጋኔን ወጥቶ ይሄዳል ፈጽሞም ወደ እርሷ በገባህም ጊዜ ሁለታችሁ ይቅር ባይ ወደ ሆነው እግዚአብሔር ጸልዩ እርሷም የተዘጋጀች ናት፡፡ ከእኛ ጋርም ወደ ሀገርህ ይዘናት እንሄዳለን› አለው፡፡ ጦብያም ይህንን ቃል በሰማ ጊዜ ደስ አለውና ከእርሷ በስተቀር ሌላ እንዳያገባ በሙሉ አሳቡ ወሰነ፡፡
ከዚህ በኋላ ወደ ራጉኤል ቤት እንደ ደረሱ ሣራ በደስታ ተቀበለቻቸው የሣራ አባትም ጦብያን ገና እንዳለው ሚስቱ አድናን ‹ይህ ልጅ የእኔ ዘመድ ጦቢትን ይመስላል› አላት ከዚያም ጋር አያይዞ ‹ልጆች ከየት ሀገር መጣችሁ?› አላቸው፡፡ እነሱም ‹ከነነዌ ሀገር ነው የመጣን› አሉት፡፡ ‹ከዚያም ሀገር ጦቢት የሚባል ወንድም ነበረኝ ታውቁት ይሆን?› ሲል ጠየቃቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ጦቢያ አባቱን ሲጠራለት ‹እናውቀዋለን፡፡ እኔም ራሴ የጦቢት ልጅ ነኝ› አለው፡፡ ከዚያ በኋላ ራጉኤል ‹የወንድሜ ልጅ ነህን?› ብለ እቅፍ አድርጐ ሳመው፡፡ አድናም ሳመችውና ሁሉም ተያይዘው የናፍቆት ልቅሶ ተላቀሱ፡፡ ከወንድሙ እንደ መጡም ሲገነዘብ በግ አርዶ በጥሩ ሁኔታ ጋበዛቸው፡፡
ራትም ከበሉ በኋላ ጦብያ ቅዱስ ሩፋኤል በመንገድ የነገረውን በልቡ ሲያወጣ ሲያወርድ ስለ ዋለ  ቅዱስ ሩፋኤልን ያንን በመንገድ የነገርከኝን አሁን ፈጽምልኝ ሲለው ሰምቶ ስለ ልጅቷ መሆኑን ስለ ገባው ራጉኤል ጦብያን ‹ልጄ ይህች ልጅ ላንተ የምትገባ ናት ሰጥቸሃለሁ አይዞህ አትጠራጠር አሁንም ብላ ጠጣ ለዛሬም ደስ ይበልህ አለውና ሣራ ካለችበት የጫጉላ ቤት አግብተው ዘጉት፡፡ ጦብያም ሣራን በይ እኅቴ ኑሮዋችን እንዲቃናልንና ጋብቻችን እንዲባረክልን አስቀድመን ወደ ፈጣሪያችን ጸሎት እናድርግ› አላትና አብረው ጸሎት ካደረጉ በኋላ ያንን የያዘውንና የዓሣ ጉበትና ሐሞት ከዕጣን ጋር ጨምሮ ቢያጤስበት በሣራ አድሮ ባሎችዋን ይገድልባት የነበረው አስማንድዮስ የተባለው ጋኔን ከሣራ ለቆ ወጥቶ ሄደ ሁለተኛም ሊመለስ አልቻለም፡፡ እነርሱም በሰላምና በጤና አደሩ፡፡ የጦብያንና የሣራን ጋብቻ የባረከ ቅዱስ ሩፋኤል ስለሆነ ‹መልአከ ከብካብ› ይባላል፡፡
ከዚያ በኋላ የጤንነታቸውን ነገር ሲረዱ የሰርጉ ቀን የሚሆን የ14 ቀን በዓል እስኪፈጸም ድረስ ጦብያ ወደ ሀገሬ እሄዳለሁ ብሎ እንዳያውከው በማለት አማለው፡፡
ጦብያ የዓሣውን ሐሞትና ጉበቱን ይዞ ስለ ነበር የአባቱን ዓይን ቀባው ወዲያውም ዓይኖቹ ተከፈቱ
የ14 ቀን በዓለ መርዓ ከተፈጸመ በኋላ ግን ጥሬ ገንዘብና የከብት ስጦታ አድርጐ መርቆ ወደ ሀገሩ ሰደደው፡፡ ወላጆቹ ጦቢትና አድና ግን በመዘግየቱ ልጃችን ምን አግኝቶት ይሆን? እያሉ ለጊዜው ሳያዝኑ አልቀሩም፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሚስቱንና ግመሎቹን ይዞ ሲመጣ በክብርና በደስታ ተቀበሉት፡፡ የጦብያ አባት ጦቢትም ልጅህ መጣ ሲሉት ዓይነ ሥውር ስለ ነበር እርሱን እቀበላለሁ ሲል ስለ ወደቀ ወዲያው ጦብያ የዓሣውን ሐሞትና ጉበቱን ይዞ ስለ ነበር የአባቱን ዓይን ቀባው ወዲያውም ዓይኖቹ ተከፈቱ፡፡
 የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ እኔ ሩፋኤል 
ነኝ› ሲል ገለጠላቸው፡፡ እነርሱም ወድቀው የአክብሮት ስግደት ሰገዱለት
በመጨረሻም ከጦብያ ጋር ሄዶ የነበረው  መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤልን የድካሙን ዋጋ ገንዘብ ለመስጠት ጠሩት እርሱ ግን ጦቢትንና ጦብያን ‹ፈጣሪያችሁን አመስግኑ እናንተ እስከ ዛሬ ድረስ ከየት እንደመጣሁ ማን እንደ ሆንኩ አላወቃችሁኝም፡፡ የእግዚአብሔር ምሥጢር ግን በክብር ሊገለጥ ይገባል እንጂ ሊሰውሩት ስለማይገባ የእኔን ተፈጥሮና ስም ልነግራችሁ እፈልጋለሁ ተፈጥሮዬ መልአክ ነኝ፣ ሥራዬም የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ እኔ ሩፋኤል ነኝ› ሲል ገለጠላቸው፡፡ እነርሱም ወድቀው የአክብሮት ስግደት ሰገዱለት፡፡ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት፡፡ /መጽ. ጦቢት/፡፡
ስለዚህ እንግዶችን መቀበል አንርሳ፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳንዶች ሳያውቁ የመላእክትን እንግድነት ተቀብለዋልና፡፡ ዕብ. 13.1-2 ፡፡
ጦቢት ከእህሉ ከፍሎ ለተራበ የሚያበላ ከልብሱ ለተራቆተ ሰው የሚያለብስ እግዚአብሔርን ዘወትር የሚያመሰግን ለወገኖቹ የሚራራ አሥራት በኩራት የሚያወጣ ሰው ነበር፡፡ በመሆኑም በሥራው ሁሉ እንዲረዳው በችግሩ ጊዜ እንዲያጸናው ቅዱስ ሩፋኤል ተልኮለታል፡፡ እኛም በሕይወታችን የጐደለብንን ነገር እንዲሞላልን ጐዳናችንን እንዲያስተካክልልን ከክፉ ጋኔን እንዲጠብቀን አምላክ ቅዱስ ሩፋኤል ተለመነን ቅዱስ ሩፋኤልንም አማልደን ማለትን ገንዘብ እናድርግ፡፡
ጳጉሜ የዘመን መሸጋገሪያ እንደ ሆነች ዕለተ ምጽአትም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የምንሸጋገርባት ስለሆነች ከወዲሁ የቅዱስ ሩፋኤልን የመታሰቢያ በዓሉን ስናከብር በአማላጅነቱ ከቅዱሳን ኅብረት እንዲደምረን በንስሐ ታጥበን ደጅ ልንጠና ይገባል፡፡ 
ቅዱስ ሩፋኤል ልመናው ይደረግልን በረከቱ ይደርብን፡፡ አሜን፡፡
source: http://kidanemhret.org/profiles/blog/show?id=2949235%3ABlogPost%3A178468&xgs=1&xg_source=msg_share_post