13

.

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው::" የማቴዎስ ወንጌል 7: 4

"እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅናወተት ግዙ።" ትንቢተ ኢሳይያስ 55 : 1

Friday, October 21, 2011

ነገረ ቅዱሳን ክፍል 4


1.    ቅዱሳን ነቢያት
ነቢይ ማለት ቃልን ከእግዚአብሔር ተቀብሎ ለሕዝብ የሚናገር የእግዚአብሔር ሰው (1ሳሙ. 9፡6)፣ ባለራእይ (1ሳሙ.9፡9)፣ የእግዚአብሔር ባርያ (2ነገ.24፡21) ማለት ነው። ነቢያት ቃሉ ከእግዚአብሔር እንደመጣ ቢረዱም እንዴት እንደመጣላቸው ብዙ ጊዜ አይገልጡም ነበር። ብቻ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል” በማለት ትንቢት ይናገሩ ነበር። (አሞጽ. 1፡3፣ 6፡9፣ሚክ.3፡8)ቃሉ አንዳንድ ጊዜ በራእይ፣በህልም፣ በመልአክም ይገለጥላቸው ነበር። (ዘኁ. 12፡6፣ ዳን.10፡11) ቃሉን እስኪናገሩ ድረስ በእነርሱ ላይ እንደሸክም ነበር።
ከቅዱሳን ነቢያት ውስጥ፡
ሀ. ነቢዩ ሳሙኤል
·         ሳሙኤል አባቱ ህልቃና እናቱ መካን የነበረችው ሐና ትባላለች።
·         ሳሙኤል ማለት እግዚአብሔር ልመናዬን ሰማኝ፤ የእግዚአብሔር ስም ማለት ነው።
·         በ3 ዓመቱ በነሐሴ 26 ቀን ለቤተመቅደስ እናቱ እንደስእለቷ አስገባቸው በቤተመቅደስ አደገ።
·         በሰኔ 9 ቀን ሳሙኤል በቤተመቅደስ ሲያገለግል እግዚአብሔር ተገለጠለት (1ሳሙ. 2፡3)፣ አፍኒንና ፊንሐስ የሊቀካህኑ የኤሊ ልጆች በቤተመቅደሱ ውስጥ ያልተገባ ሥራ ሰርተው እግዚአብሔርን በማሳዘናቸው 3ቱም በእግዚአብሔር ከተቀጡ በኋላ ሳሙኤል በእነርሱ እግር ተተክቶ ቤተእግዚአብሔርን በቅዱስ የክህነት ስራ በማገልገል የእግዚአብሔር ታማኝ አገልጋይ የነበረ አባት ነው።
·         ሳሙኤል ሀብተ ክህነት፣ ሀብተ ምስፍና ሀብተ ትንቢት የተሰጠው የተጨነቀ ንጉሥ ዳዊትን በስደቱ ጊዜ ያጽናናው፣ የእስራኤልን ንጉሥ ሳዖልንና ዳዊትን የቀባ ነቢይ ነው።
·         ሠውን ከእግዚአብሔር ጋር በጸሎቱ ያስታረቀና በጸሎቱ ከሙሴ ጋር ተቆጠረ ታላቅ አባት ነው። (ት.ኤር.15፡1)
·         በ98 ዓመቱ በሰኔ 12 ቀን አርፏል፤ በአርማቴም በቤቱ ቀበሩት።
ለ. ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት
·         ዳዊት አባቱ እሴይ እናቱ ሁብቢ ይባላሉ። በነሐሴ 13 ቀን ተጸነሰ በሚያዝያ 6 ቀን በይሁዳ በቤተልሔም ሀገር ተወለደ። (1ሳሙ. 16፡10-11) ዳዊት ማለት ልበ አምላክ ማለት ነው። እረኛና ብላቴና ነበር።
·         የፍልስጤማውያኑን ሰው ጎልያድን በ12 ዓመቱ 5 ጠጠርን ከወንዝ ለቅሞ በወንጭፍ ወርውሮ የገደለ (1ሳሙ.12፡45-51)፣ ንጉሥ ሳዖል በጌልቦአ ተራራ በራሱ እጅ ከሞተ በኋላ አስቀድሞ በይሁዳ 7 ዓመት በመላው እስራኤል 33 ዓመት የነገሠ (2ሳሙ. 2፡4፤ 2ሳሙ. 5፡1-5) ቅዱስ አባት ነው።
·         “እግዚአብሔር እንደ ልቡ የሆነ ሰው መርጦአል” (1ሳሙ.13፡14) ተብሎ በእግዚአብሔር የተመረጠና ነገረ ሥጋዌን፣ ምሥጢረ ትንሣኤ እሙታን፣ ዳግም ምጽዓትን፣ ነገረ ማርያምን፣ ክብረ ቅዱሳንን፣ በስፋትና በጥልቀት የተናገረ የብሉይ ኪዳን “ወንጌላዊ” ነበር። (መዝ.21 (22)፡ 16-18 “ብዙ ውሾች ከብበውኛልና የክፋተኞች ጉባኤም ያዘኝ እጆቼንና እግሮቼን ቸነከሩኝ። አጥንቶቼ ሁሉ ተቈጠሩ እነርሱም አዩኝ ተመለከቱኝም። ልብሶቼን ለራሳቸው ተከፋፈሉ፥ በቀሚሴም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ።…”፣ መዝ. 46(47)፡4-5 “አምላክ በእልልታ፥ እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ።”፣ መዝ.49(50)፡ 1-5 “ከክብሩ ውበት ከጽዮን እግዚአብሔር ግልጥ ሆኖ ይመጣል። አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም እሳት በፊት ይቃጠላል፥ በዙሪያውም ብዙ ዐውሎ አለ።”፣ መዝ. 44(45)፡9 “የንጉሦች ሴት ልጆች ለክብርህ ናቸው በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች።”
·         ዳዊት ታላቅና ገናና ንጉሥ ከመሆኑ የተነሳ መንግሥቱ የመሲህ መንግሥት ምሳሌ ሆኗል፤ መሲሁም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዳዊት ስም ብዙ ጊዜ በመጽሐፍቅዱስ ተጠቅሶ ይገኛል። (ት.ኢሳ.9፡7፣ ኤር.23፡5-6፣ ኤር.3314-17፣ ህዝ. 34፡23፣ሆሴዕ 3፡5)
·         ቅዱስ ዳዊት 7 ሀብታት የተሰጡት አባት ነበር፤ እነዚህም
1.      ሀብተ ክህነት
2.     ሀብተ መንግሥት
3.     ሀብተ መዊዕ (የማሸነፍ ሀብት)
4.     ሀብተ ትንቢት
5.     ሀብተ ኃይል
6.     ሀብተ በገና
7.     ሀብተ ፈውስ ናቸው።
·         እድሜ ዘመኑን እግዚአብሔርን በማገልገልና በመፍራት ኖሮ በታህሳስ 23 ቀን አርፎ በኢየሩሳሌም ተቀብሯል።
ሐ. ኤልያስ ቴስብያዊ
·         ኤልያስ ማለት ቀናኢ ለአምላኩ ማለት ነው። አንድም እግዚአብሔር አምላክ ነው ማለት ነው።
·         አባቱ ኢያሴንዩ እናቱ ቶና ይባላሉ።
·         በጥር 1 ቀን ተወለደ በወገቡም ጠፍር ይታጠቅ ነበር። (2. ነገ. 1፡8)
·         ንጉሥ አክአብንና ሚስቱ ኤልዛቤልን የገሰጸ፤ ሰማይን ለጠል ምድርን ለዘር 3ዓመት የከለከለ (1ነገ. 17)፣ በጸሎቱ ዝናብ እንዲዘንብ እህልም እንዲትረፈረፍ ያደረገ፣ የመበለቲቷን ልጅ ከሞት ያስነሳ (1ነገ.17፡17-22)፣ ኤልሳዕን ደቀመዝሙሩ አድርጎ በግብረ መንፈስቅዱስ የጠራ፣ የዮርዳኖስን ባህር የከፈለ (2ነገ.2፡8)፣ የናቡቴን ደም ያፈሰሱት አክአብና ኤልዛቤልን የቀሰፈ አባት ነው።
·         ሞትን ሳይቀምስ ወደ ብሔረ ሕያዋን በእሳት ሰረገላ ያረገ (2ነገ.2፡11) መንፈሱን በሁለት እጥፍ በኤልሳዕ ላይ ያሳደረ ቅዱስ አባት ነው።
መ. ኢሳይያስ ነቢይ
·         ኢሳይያስ ማለት መድኃኒት፣ ድኅነት ማለት ሲሆን አባቱ አሞጽ እናቱ ስፊያ ይባላሉ። የትውልድ ዘሩ ከስምዖን ሲሆን ግንቦት 28 ቀን ማክሰኞ እለት ተወለደ።
·         ዓበይት ነቢያት ከሚባሉት ውስጥ የመጀመሪያው ሲሆን “የብሉይ ዘመን ወንጌል ሰባኪ (ወንጌላዊ)” ይሉታል። ይህም ነገረ ሥጋዌን፣ ነገረ ማርያምን በዝርዝር ከልደት - ዳግም ምጽዓት ድረስ በዝርዝር በማስረዳት የተናገረ ነቢይ ስለሆነ ነው።
·         በግንቦት 28 ቀን “ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።” የሚለው ምሥጢር ተገልጾለት ጽፏል።
·         ነቢዩ ኢሳይያስ የነበረበት ጊዜ ከ740 – 688 ዓ.ዓ ሲሆን በአክአዝና በህዝቅያስ ዘመን የቤተመንግሥት አማካሪ የነበረ ታላቅ ነቢይ ነው።
·         በሕዝቅያስ ላይ 15 ዓመት እንዲጨመር ያደረገ፣ የነገሥታትን መጽሐፍ፣ የትንቢት መጽሐፍን የጻፈ (2ዜና፡26፣ ኢሳ. 8፡1)፣ ት.ኢሳይያስን ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ700 የጻፈ፣ ሰንበትን ማክበር እንዲገባ ያስተማረ ታላቅ አባት ነው። (ኢሳ.5፡8)
·         በመስከረም 6 ቀን በመጋዝ ለሁለት ተሰንጥቆ በሰማዕትነት አርፏል።
ሰ. ነቢዩ ኤርምያስ
·         ኤርምያስ ማለት እግዚአብሔር ከፍ ያደርጋል ማለት ሲሆን አባቱ ኬልቅያስ (ካህን ነበር) እናቱ ማርታ ይባላሉ። ሀገሩ ይሁዳ ሲሆን ልዩ ስሙ አናቲት ይባላል።
·         ገና በእናቱ ማኅጸን ሳለ የተመረጠና የተቀደሰ ነቢይ ነው። (ኤር. 1፡4)
·         ነቢዩ ኤርምያስ በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ ሴዴቅያስ በኢዮአቄም ዘመን በ629 ዓ.ዓ እስራኤልን መጥፋት ትንቢት ተናገረ። የእስራኤልን መጥፋት የማይፈልገውን አቤሜሌክን “ለድውያን የምንቀባውን እጽ አምጣ” ብሎት 66 ዓመት እንዲተኛ ያደረገ፣ ባሮክን መቃብረ ነገሥትን እንዲጠብቅ አደረገ በእብራይስጥ ቋንቋ ህዝቡን ስለእስራኤል መጥፋት አስተማረ፣ ከምርኮ መልስ በኋላ ቤተመቅደሱን አሰርቶ፣ ንዋያተ ቅድሳቱን አሰናድቶ ዳግም እግዚአብሔርን እንዳይበድሉ የመከረ የገሰጸ ታላቅ ነቢይ ነው።
·         በግንቦት 5 ቀን ነገረ ሥጋዌን ሲናገር “የአምላክን ልጅ አምላክን አየሁት” ይለናል ብለው ነደንጊያ ወግረው በሰማዕትነት አርፏል። (ተረ. ኤር. 11፡54፤ ዕብ. 11፡37)
ረ. ነቢዩ ሕዝቅኤል
·         ሕዝቅኤል ማለት እግዚአብሔር ብርታትን ይሰጣል ማለት ሲሆን አባቱ ቡኤዝ (ቡዝ) እናቱ ህሬ (ሌዋዊት) ይባላሉ። ሀገሩ ቤተሰማርያና ኢየሩሳሌም ሲሆን ኖሬም ይባላል። ነገዱ ከሌዊ ወገን ነው።
·         በሐምሌ 7 ቀን ተወለደ። የመጀመሪያ ስሙ ፒታጎሮስ ይባል ነበር። ከዓበይት ነቢያት ውስጥ ቁጥሩ 3ኛ ነው።
·         30 ዓመት ሲሞላው  ሐምሌ 27 ቀን እግዚአብሔር በኪሩቤል ላይ እንዳለ በራእይ የተገለጸለት፤ ስለኢየሩሳሌም በጠላት እጅ መውደቅ፣ የንስሐ ስብከቱ፣ ስለአሕዛብ ነገስታት የተናገረው ትንቢት፣ በባቢሎን ከኢኮንያን ጋር አብሮ ተማርኮ በ592ዓ.ዓ ስለምርኮኞች ትንቢት የተናገረ ነቢይ ነው።
·         ስለ ነገረ-ማርያም በሰፊው የተናገረ ይህም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን በሁለት ወገን ድንግል መሆኗን በትንቢቱ የሰበከ ታላቅ ነቢይ ነው። (ት.ሕዝ. 44፡ 1-2  “ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በስተ ውጭ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር አመጣኝ ተዘግቶም ነበር። እግዚአብሔርም፦ ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም፥ ሰውም አይገባበትም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል።”)
·         ኢየሩሳሌም ከመፍረሷ በፊትና በኋላ ፤ ከስደት በፊትና በኋላ የነበረ ነቢይ ነው።
·         የኢዩቤልዩ በአል መከበር የጀመረው በዚህ ነቢይ ጊዜ ሲሆን ትንቢተ ሕዝቅኤልን በእብራይስጥ ቋንቋ ጽፎታል። ነቢዩ ሕዝቅኤል ስለቤተክርስቲያን ስራና አቀማመጥ፣ ስለ ዕቃ ቤት (ቤተመዛግብት)፣  ስለደጀ ሰላም አቀማመጥ፣ ስለ ቤተልሔም አሰራር በሰፊው የተናገረ ነቢይ ነው።
·         50 ዓመት ሲሞላው በሰማዕትነት ሚያዝያ 5 ቀን አርፏል።
ሠ. ነቢዩ ዳንኤል
·         ዳንኤል ማለት እግዚአብሔር ፈራጅ ነው፣ ዳኛ ማለት ሲሆን ከክርስቶስ ልደት በፊት (ክ.ል.በ) 600 ዓመት ናቡከደነጾር በዳርዮስ ዘመን የሕዝቅኤል ወዳጅ የነበረ ነቢይ ነው።
·         የነበረበትም ዘመን አይሁድ በአረማውያን ንጉሥ አገዛዝ የወደቁበት ዘመንና ምርኮኝነት፣ ስደት፣ ጭቆና ይደርስባቸው በነበረበት ጊዜ ነበር። ዳንኤልም በምርኮ ላይ ሳለ አጥብቆ ይጾም፣ ይጸልይ ነበር።
·         ከዓበይት ነቢያት አንዱ ሲሆን ሶስናን ከእደረበናት (ከሐሰተኛ መምህራን) ያዳናት ነቢየ እግዚአብሔር ነው።
·         ለመጀመሪያ ጊዜ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን “መሲህ” በማለት የጠራው ይህ ታላቅ ነቢይ ነበር። (ት.ዳን. 9፡25-26 “ስለዚህ እወቅ አስተውልም ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት ጀምሮ እስከ አለቃው እስከ መሢሕ ድረስ ሰባት ሱባዔና ስድሳ ሁለት ሱባዔ ይሆናል እርስዋም በጭንቀት ዘመን ከጎዳናና ከቅጥር ጋር ትሠራለች። ከስድሳ ሁለት ጊዜ ሰባትም በኋላ መሢሕ ይገደላል፥ በእርሱም ዘንድ ምንም የለም የሚመጣውም አለቃ ሕዝብ ከተማይቱንና መቅደሱን ያጠፋሉ ፍጻሜውም በጐርፍ ይሆናል፥ እስከ መጨረሻም ድረስ ጦርነት ይሆናል ጥፋትም ተቀጥሮአል።”) እርሱም ከአዳም እስከ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ድረስ 7ቱን ሱባዔና 62 ሱባዔ ቆጥሮ ዕለቱን ያገኘና የተረጎመ ነቢይ ነው።
·         ስለ ዳግም ምጽዓት ራእይን የተመለከተና የጻፈ ነቢይ ነው። (ት.ዳን.12፡1-13 “በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል ሕዝብም ከሆነ ጀምሮ እስከዚያ ዘመን ድረስ እንደ እርሱ ያለ ያልሆነ የመከራ ዘመን ይሆናል በዚያም ዘመን በመጽሐፉ ተጽፎ የተገኘው ሕዝብህ ሁሉ እያንዳንዱ ይድናል።በምድርም ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉቱ ብዙዎች ይነቃሉ እኵሌቶቹ ወደ ዘላለም ሕይወት፥ እኵሌቶቹም ወደ እፍረትና ወደ ዘላለም ጕስቍልና።...የዘወትሩም መሥዋዕት ከቀረ ጀምሮ፥ የጥፋትም ርኵሰት ከቆመ ጀምሮ ሺህ ሁለት መቶ ዘጠና ቀን ይሆናል።የሚታገሥ፥ እስከ ሺህ ሦስት መቶ ሠላሳ አምስት ቀንም የሚደርስ ምስጉን ነው። አንተ ግን እስከ ፍጻሜው ድረስ ሂድ አንተም ታርፋለህ፥ በቀኑም መጨረሻ በዕጣ ክፍልህ ትቆማለህ።”
·         በግንቦት 12 ቀን ወደ አናብስት (አንበሶች) ጉድጓድ የተጣለ (ዳን. 6፡1)፣ በሰኔ 13 ቀን ቅዱስ ገብርኤል የተላከለት፣ ትንቢተ ዳንኤልን፣ ተረፈ ዳንኤልን፣ ዜና ዳንኤልንና መጽሐፈ ዳንኤልን የጻፈና የተናገረ ታላቅ ነቢይ ነው።
እንዲሁም በመንፈስቅዱስ ተመርተው ትንቢትን የተናገሩ ቅዱሳን ነቢያት በቃል እና በጽሑፍ ነቢያት ሲመደቡ ከጽሑፍ ነቢያት ውስጥ ከላይ ከተቀስናቸው ዓበይት ነቢያት በተጨማሪ 12ቱ ደቂቀ ነቢያት (በምሥጢርና በመንፈስ የዓበይት ነቢያት ልጆች) ይገኛሉ። እነርሱም፡
1.      ነቢዩ ሆሴዕ
2.     ነቢዩ አሞጽ
3.     ነቢዩ ሚክያስ
4.     ነቢዩ ኢዩኤል
5.     ነቢዩ አብድዩ
6.     ነቢዩ ዮናስ
7.     ነቢዩ ናሆም
8.     ነቢዩ ዕንባቆም
9.     ነቢዩ ሶፎንያስ
10.    ነቢዩ ሐጌ
11.     ነቢዩ ዘካርያስ
12.    ነቢዩ ሚልክያስ ናቸው።

2.   ቅዱሳን ሐዋርያት
ሐዋርያ የሚለው ቃል ሖረ ከሚለው የግዕዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ሄደ፣ ተጓዥ ማለት ነው። ለነቢያት የተነገረው ቃለ ትንቢት መድረሱንና በዘመናቸው መፈጸሙን ለዓለም እንዲያስተምሩ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ኑ ተከተሉኝ” ብሎ የጠራቸውና የመረጣቸው ናቸው። በአይሁዳውያን ዘንድ አላዋቂ ከሚባሉት ዘንድ የተመረጡ ናቸው። (ያዕ.2፡5 “የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ባለ ጠጎች እንዲሆኑ ለሚወዱትም ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድሆች አልመረጠምን?
ሐዋርያት ብሎ ከሰየማቸው በኋላ ለጊዜው በምድረ እስራኤል እየዞሩ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” እያሉ እንዲያስተምሩ አዘዛቸው። ይህንን አገልግሎት ለመፈጸም ሲሄዱ ለእግራቸው ጫማ፤ ለእጃቸው በትር፤ ለስንቃቸው ገንዘብ እንዳይዙ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስጠንቅቋቸው ነበር። ሲያስተምሩም መከራና ሞትን እንዳይፈሩ፣ በተከሰሱ ጊዜ ጠበቃን እንዳይፈልጉ፣ በሚናገሩበት ጊዜ ምን እንናገራለን? ብለው እንዳይጨነቁ ተነግሯቸዋል። (ማቴ. 10፡1-11) ወንጌልን ለዓለም እንዲያደርሱና እርሱም ሁልጊዜ ከእነርሱ ጋር መሆኑን ከነገራቸው በኋላ ወንጌልን እየሰበኩ ከክርስቶስ ፍቅር ማንም፣ ምንም እንደማይለያቸው አውቀው ለዓለም እንዳዳረሱ እናያለን። (ማቴ. 28፡19-20)
ቅዱሳን ሐዋርያት ሥልጣነ ክህነት የተሰጣቸው ይህም በምድር ያሰሩት በሰማይ የታሰረ፤ በምድር የፈቱት በሰማይ የተፈታ ይሆን ዘንድ ሥልጣን የተሰጣቸው፣ አእይንተ እግዚአብሔር ናቸው። (ማቴ. 16፡19፣ 18፡18፣ ዮሐ. 20፡23) በኋላም ግልገሎቼን አሰማራ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ፣ በጎቼን አሰማራ በሚል ቃለ ትዕዛዝ የምዕመናንን ህይወት አስረክቧቸዋል። (ዮሐ.21፡15)
ቅዱሳን ሐዋርያት በቁጥር 12 ሲሆኑ እነርሱም፡
ሀ. ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ
·         አባቱ ዮና ሲባል ሀገሩ ከገሊላ ባህር አጠገብ ልዩ ስሙ ቤተሳይዳ ሲሆን የመጀመሪያ ስሙ ስምኦን ይባላል። ስምኦን ማለት እግዚአብሔር ሰማኝ ማለት ነው፤ጴጥሮስ ማለት መሰረት፣ የማይፈነቀል ዓለት ማለት ነው። የብጽዕይት (በስእለት የተገኘ) ልጅ ነው። በ5 ዓመቱ በቅፍረ ናሆም አጠገብ ባለው ትምህርት ቤት ገብቶ የተማረ፤ በተፈጥሮው ችኩል፣ ፈጣን የነበረ፣ ስራውም አሳ ማጥመድ የመበረ ሲሆን ጌታችን ከስራው ላይ ጠርቶታል። በአረማይክ ቋንቋ ኬፋ ማለት በግሪክ ጴጥሮስ ማለት ነው።
·         ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያርግ ሊቀ ሐዋርያት አድርጎ ሾመው፤ ስለዚህም ሊቀጳጳሳት ሊቀ ሐዋርያት ጴጥሮስ ይባላል። ከምሥጢር ሐዋርያት ውስጥ አንዱ ነው።
·         ጌታችን “ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል? (ማቴ.16፡13)” ባላቸው ጊዜ እውነተኛ መሲህ ወልደ እግዚአብሔር መሆኑን የመሰከረ፣ የመንግሥተ ሰማያት ቁልፍ በእርሱ በኩል የተሰጠ፣ በንሰሐ እንባው ከጌታችን የታረቀ፣ በበአለ 50 (ጰራቅሊጦስ) በአንድ ጊዜ 3000 ሰው የመለሰ፤ ስለወንጌል አብዝቶ መከራን የተቀበለ፣ አናንያንና ሰጲራን (ባልና ሚስቶቹን) በውሸታቸው የቀሰፈ፣ በሽተኛን የፈወሰ፣ ሙትን ያስነሳ፣ በሕዳር 22 ቀን ቆርነሌዎስን ያስተማረና ያጠመቀ
·         በወህኒ በጣሉት ጊዜ በሚያዝያ 12 ቀን ቅዱስ ሚካኤል ትጥቅህን ታጠቅ ተብሎ ከእስር የወጣ፣ ከአንጾኪያ ሄዶ በታችኛው እስያ እየዞረ ያስተማረ
·         በሰኔ 20 ቀን በእርሱ ባራኪነት በጳውሎስና በበርናባስ አስተማሪነት የመጀመሪያዋን ቤተክርስቲያን በፊሊጵስዮስ ሀገር የሰራ
·         ሮም ሀገር ሄዶ በኔሮን ቄሳር ፊት የመሰከረ፣ በመስከረም 25 ቀን መከራን የተቀበለና መልእክታቱን የጻፈ፣ ዜና ሐዋርያት እንዲዘጋጅ ያደረገ፣ ገድላትን ድርሳናትን ቅዱሳት መጻሕፍትን የሚያጣምሙ መናፍቃንን አጥብቆ የተቃወመና ምላሽ የጻፈ (2ጴጥ. 3፡16 “በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ፥ ያልተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች ሌሎችን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ።”፣ 1ጴጥ.4፡17 “ፍርድ ከእግዚአብሔር ቤት ተነሥቶ የሚጀመርበት ጊዜ ደርሶአልና፤ አስቀድሞም በእኛ የሚጀመር ከሆነ ለእግዚአብሔር ወንጌል የማይታዘዙ መጨረሻቸው ምን ይሆን? ጻድቅም በጭንቅ የሚድን ከሆነ ዓመፀኛውና ኃጢአተኛው ወዴት ይታይ ዘንድ አለው?”)
·         በሮም ከተማ በኔሮን ቄሳር ትእዛዝ በ64 ዓ.ም በሐምሌ 5 ቀን በተወለደ በ68 ዓመቱ በሰማዕትነት የቁልቁሊት (ተዘቅዝቆ) ተሰቅሎ አርፏል።
ለ. ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ
·         አባቱ እልፍዮስ ወይም እልፍልዮን ይባላል። ትውልዱ ይሁዳዊ ሲሆን የመጀመሪያ ስሙ ሌዊ ነው። ማቴዎስ ማለት ህሩይ፣ የተመረጠ ማለት ነው። በጥር 12 ቀን ተወለደ በጥር 5 ቀን ተሾመ ስራውም ቀራጭነት ነበር። በስራውም ላይ ሳለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያነት ጠርቶታል። እርሱም ሁሉን ትቶ ተከትሎታል።
·         ጌታችንን በቤቱ ጋብዞ በማዕድ አብሮት የተቀመጠ፣ መጀመሪያ በእግር ኋላ በግብር የተከተለው ሐዋርያ ነው። ከጌታችን እግር ስር ስለኖረ ወንጌሉን ለመጻፍ እረድቶታል።
·         ማቴዎስ ወንጌሉን ሲጽፍ በጌታችን የልደት የዘር ሃረግ ጀምሯልና ከኪሩቤል ገጻት በገጸ ሰብእ (በሰው ገጽ ባለው) ይመሰላል። በወንጌሉ ላይ ስለእርቅ፣ ስለሰላም፣ ስለምጽዋዕት፣ ስለጸሎት፣ ስለደግና ክፉ ባሪያ፣ ስለጌታችን ስብከት፣ ጌታችን ስላደረጋቸው ተዓምራት፣ ስለደብረታቦርና የፊልጶስ ቂሳርያ ህዝቦች ማን እንደሚሉት፣ ስለዕርገት፣ ስለሐዋርያት መመረጥና ወደዓለም መሰማራት፣ ስለጥምቀት፣ ስለዮሐንስ መጥምቅ፣ ስለንግሥተ ሳባ፣ ስለሰዶምና ገሞራ፣ ስለነነዌ ሰዎች፣ ስለኖኅ ዘመን፣ ስለትንሣኤና ዳግም ምጽዓት አጥብቆ በስፋት ጽፏል። ሲጽፍም 28 ምዕራፎች በ125 አርዕስቶች ለይቶ ነው።
·         ወንጌሉን የጻፈው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዐረገ በ8ኛው ዓመት ቀላውዴዎስ ቄሳር በነገሰ በአንደኛው ዓመት በፍልስጤም ሀገር ሆኖ በእብራይስጥ ቋንቋ በከለዳዊ ጻፈው። በዛን ጊዜ ህዝቡ ሁለቱንም ቋንቋ ይናገር ነበርና ነው።
·         ቅዱስ ማቴዎስ ከፍልስጤም ተነስቶ በእስያ አድርጎ ደቀመዛሙርቶቹን ማርቆስንና ሌሎቹንም ይዞ ማርቆስን በግብጽ ትቶ ወደ ኢትዮጵያ መትቶ ናዕድር በምትባል ከተማ ገብቶ ያስተማረ (ይህ ናዕድር የተባለ ከተማ ይገኝ የነበረው በአክሱም ሲሆን የእነራስ ስሁል ሚካኤል ከተማ ነው።)
·         ቅዱስ ማቴዎስን ዮስጦስ የተባለው መኮንን ራሱን ካስቆረጠ በኋላ ሰውነቱን ከፋፍሎ ሥጋውን ለአእዋፍ ሰጠው። ዚማኮስ የተባለው ደቀመዝሙሩ ቀብሮታል። ዕለተ ዕረፍቱም ጥቅመት 12 ቀን ነው።
ሐ. ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ወልደነጎድጓድ
·         አባቱ ዘብድዮስ እናቱ ሰሎሜ ይባላሉ። በመስከረም 30 ቀን ተወለደ። በእናቱ በኩል ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጋር የአንድ አያት ልጆች ናቸው። ይህም ሄርሜላ እና ማጣት ባልና ሚስት ሲሆኑ 3 ልጆችን ወልደዋል፤ ትልቋ ሶፍያ፣ ማርያም እና የመጨረሻዋ ሃና ናቸው። ሶፍያ ኤልሳቤጥን፣ ኤልሳቤጥ ዮሐንስ መጥምቁን ወለደች። ማርያም ሰሎሜን፣ ሰሎሜ ዘብድዮስን አግብታ ዮሐንስና ያዕቆብን ሌሎችንም ወለደች። ሃና ኢያቄምን አግብታ የብጽእይት ልጇን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ወልዳለች። ስለዚህም የጌታችን ወንድም ያሰኘው ይህ ነው።
·         ፍቁረ እግዚእ ይባላል ይህም ጌታችን የሚሰራውን ሁሉ ይነግረው ነበርና ጌታችን የሐዋርያትንም እግር ሲያጥብ ታጥቋት የነበረችውን ለእርሱ ሰጥቶታልና፤ ነባቤ መለኮት (ታኦሎጎስ) ይባላል ምሥጢረ መለኮትን በመመርመርና በመጻፍ ወንጌሉን ጀምሯልና በገጸ ንስር ይመሰላል። በስሙ የተጠሩ 3 መልእክታትን እና ራዕይ ዮሐንስን በፍጥሞ ደሱት በመከራ (በእስር) ላይ ሳለ ተገልጾለት ጽፏል። ወንጌሉን በዮናኒ ቋንቋ ጌታችን በዐረገ በ30 ዓ.ም ሄሮን በነገሠ በ7ዓመት በጥር 20 ቀን ጽፏል።
·         አሳ አጥማጅ ነበር፣ የተመረጠው ከአሳ ማጥመድ ስራው ነበር።
·         በህጻንነቱ እናቱ ስለሞተችበት እመቤታችን ተንከባክባ አሳድጋዋለች።
·         ጌታችን ከዋለበት እየዋለ፣ ካደረበት እያደረ ከጽንሰቱ - ዕርገቱ ድረስ ያለውን ጻፈ። በጌታችን ሞት አጥብቆ ስላዘነ 70 ዘመን ሙሉ ፊቱ ተጨማዶ (ቁጽረ ገጽ ሆኖ)፣ አይኑ ፈዞ ኖረ። 
·         ከእግረ መስቀል ስር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን እናት አድርጎ ተሰጥቶታል፤ ለመላው ዓለም እናት ተደርጋ በቅዱስ ዮሐንስ አማካኝነት ተሰጥታለች።
·         እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከዚህ ዓለም ባረፈችበት ጊዜ መልአኩ ነጥቆ በዕፀ ሕይወት ስር አብሯት ተቀምጧል።
·         ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር በሰማርያ ሄዶ ነበር፤ ወደ ሮም ገብቶ ሲያስተምር ለመጀመሪያ ጊዜ የጌታችንን ሥነ-ስቅለት ሥዕል ስሏል። ሥዕሉን ተመልክቶ ቢስመው ለ15 ሰዓት ያህል ከንፈሩ ተጣብቆ ቆይቷል።
·         በጥር 4 ቀን ወደ ብሄረ ህያዋን አርጓል።


መ. ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ወልደ ዘብዴዎስ
·         ያዕቆብ ማለት አዕቆጼ ሰኮና (                 ) ማለት ነው። በትምህርቱ የአይሁድን ትምክህት መመጻደቅ ይነቅፋል። የዮሐንስ ወንድም ነው። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እናቱ ስላረፈችበት አሳድጋዋለች።
·         የኦሪት ምሁር ነውና የሀገሩን በሬ እንዲሉ የአይሁድ ጸባያቸውን የሚያውቅ ነውና እርሱ ያስተምራቸው ብለው በኢየሩሳሌም ኤጲስ ቆጶስነት ሹመውታል።
·         አይሁድ ለምቀኝነት አያርፍምና በምን ነገር እናጣላው ብለው “ተነሳ ዐረገ ስለምትለው ስለኢየሱስ ክርስቶስ ንገረን” ቢሉት መንበር አዘርግቶ ከዚያ ላይ ሆኖ ስለኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክነት ሲያስተምራቸው ጎትተው አውርደው ቀጥቅጠው በሰማዕትነት በ62ዓ.ም በሐምሌ 18 አርፏል።
ሰ. ሐዋርያው ቅዱስ በርተሎሜዎስ
·         በርተሎሜዎስ ማለት አትክልተኛ ማለት ነው።
·         ሀገረ ስብከቱ አልዋህ ነው፤ ቅዱስ ጴጥሮስ አብሮት ሄዶአብረው ሲያስተምሩ በርበር የሚባሉ አረማውያን ተመቅኝተው ይብሏችወ ብለው አራዊት ለቀቁባቸው። ወደ ጌታ ቢያመለክቱ አንድ ገጸ ከልብ (  ) ተነስቶ አራዊቱን ፈጅቶላቸዋል። በዚህም ተዓምር ብዙዎች አምነው ተጠምቀዋል።
·         በሚያስተምርበት ጊዜ ብዙ ተዓምራትን አድርጓል፤ በአንድ ቀን ነግህ ወይን ተክሎ ዕለቱን ለመስዋዕት አድርሷልና አትክልተኛ መባሉ ስለዚህም ነው።
·         ንጉሡ አግሪጳ ጣዖት ካላመለክ ብሎ በርጥብ አጎዛ አስጠቅልሎ ከባህር አስጥሎት በሰማዕትነት መስከረም 1 ቀን አርፏል። ሥገውን ምዕመናን አግኝተው በክብር ቀብረውታል።
ረ. ሐዋርያው ቅዱስ ማትያስ
·         ማትያስ ማለት ምትክ ማለት ሲሆን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዐረገ  በኋላ ሐዋርያት 120 ከእመቤታችን ጋር ሆነው በጽርሐ - ጽዮን በማርያም የማርቆስ እናት ቤት ለጸሎት ይተጉ በነበረበት ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ የአስቆሮቱ ይሁዳ ምትክ የሚሆን አንድም በነቢዩ ቅዱስ ዳዊት የተነገረው ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ “ዘመኖቹም ጥቂት ይሁኑ ሹመቱንም ሌላ ይውሰድ።” መዝ 108(109)፡8 ተብሎ የተነገረበት የአስቆሮቱ ይሁዳን ሹመት የሚወስድ እንምረጥ በማለቱ ዮሴፍንና ማትያስን አቁመው “የሁሉን ልብ የምታውቅ አንተ ጌታ ሆይ፥ ይሁዳ ወደ ገዛ ራሱ ስፍራ ይሄድ ዘንድ በተዋት በዚህች አገልግሎትና ሐዋርያነት ስፍራን እንዲቀበል የመረጥኸውን ከእነዚህ ከሁለቱ አንዱን ሹመው አሉ። ዕጣም ተጣጣሉላቸው፥ ዕጣውም ለማትያስ ወደቀና ከአሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋር ተቈጠረ።” ሐዋ. 1፡24-26
·         ሀገረ ስብከቱ በላዕተ ሰብእ (ሰው የሚበሉ ሰዎች) ደረሰው፤ በዚያ ሀገር ያሉ ሰዎች እንደ አራዊት ሥጋ የሚመገቡ ነበሩ፤ ከአደባባያቸው ገብቶ ሲያስተምር ይዘው ዓይኑን አውጥተው እንደላም ሳር እየመገቡ ከዝግ ቡት አስቀመጡት በ40 ቀን ዓይነ ምድሩ ሲለወጥ ሊመገቡት። ከዚህ አስቀድሞ እግዚአብሔር ሐዋርያው እንደርያስን ልኮለት ዓይኑን ፈውሶት፣ ከእስሩ ፈትቶት ወጥተው ሲያስተምሩ ሊጣሏቸው መጡ፤ ወደ ጌታችን ዘንድ ቢያመለክቱ ውሃ እስከ አንገታቸው አጠለቃቸው፤ ኋላ ግን ጸልየው አድነዋቸዋል። በዚህም ተዓምራት ብዙሃን አምነው ተጠምቀዋል። ጠባያቸውንም ቀይረው እህል የሚመገቡ ሆነዋል።
·         ቤተክርስቲያን አሳንጾ፣ ቀሳውስት ሾሞ፣ ሥጋ ወልደ እግዚአብሔርን ደመ ወልደ እግዚአብሔርን የሚመግባቸው ሆኗል።
·         30 ዘመን ካስተማራቸው በኋላ ወንጌል ካልደረሰበት ደማስቆ ወረደ። አረማውያን በብረት አልጋ አስተኝተው 24 ቀን እሳት ሲያነዱበት ቆይተዋል፤ እርሱ ግን ሰውነቱ አምሮ መልኩ ደምቆ ይገኝ ነበር። በዚህ ተዓምር አምነው ተጠምቀዋል።
·         በይሁዳ ከተሞች እየተዘዋወረ አስተምሮ በመጋቢት 8 ቀን በፊላዎን አርፏል።
ሠ. ሐዋርያው ቅዱስ ታዴዎስ
·         ቀዳሜ ስሙ ልብድዮስ ነው፤ ልብድዮስ ማለት አሳ አስጋሪ ማለት ነው። አንድም ካህነ አምላክ (የአምላክ አገልጋይ) ማለት ነው። ታዴዎስ ማለት ዘርዕ ወማዕረር (    ) ማለት ነው፤ ኦሪትን በዘር ወንጌልን በመከር መስሎ አስተምሯልና፤ በነግህ ስንዴ ዘርቶ ለመስዋዕት አድርሷልና።
·         አፍራቅን ያሉትን ሰዎች ገበሬውን ምክንያት በማድረግ የሚበሉት ሄዶ እስኪያመጣላቸው ድረስ ዘር ዘርተው አግርቶ፣ ከብቶቹም ውሃ ሲጠጡ ተመልክቶ ለሀገሩ ሰዎች ቢነግራቸው በክፋት ተነሳስተው ሊዋጋቸው ዘማሴትን ይዘው ቢመጡ በንፋስ አውታር ወደ ሰማይ ሰቅለዋት ስትገረፍ አይተው በተዓምራት አምነው ተጠምቀዋል።
·         ሐዋርያው ቶማስን “ባለጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢገባ ይቀላል አለ።” ማቴ. 19፡24 ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረውን አንድ መሰርይ ሰው ቢፈትነው ወደ ሐዋርያው ታዴዎስ መጥቶ ቢጠይቀው ሐዋርያው ቅዱስ ታዴዎስ በተግባር በመርፌ ቀዳዳ ግመሏን 3 ጊዜ እንደ ክር ስቦ አሳልፏታል።
·         ሐዋርያው ታዴዎስ ወንጌልን ሲያስተምር ቆይቶ በሐምሌ 2 ቀን በደንጊያ ተወግሮ በሰማዕትነት አርፏል።
ሸ. ሐዋርያው ቅዱስ እንድርያስ
·         እንድርያስ ማለት ጽኑዕ፣ በኩር ማለት ሲሆን የቅዱስ ጴጥሮስ ወንድም ነው።
·         የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ደቀመዝሙር ሳለ ዮሐንስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አሳይቶት ከእርሱ ጋር ዋለ። (“በነገው ደግሞ ዮሐንስ ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ቆመው ነበር ኢየሱስም ሲሄድ ተመልክቶ። እነሆ የእግዚአብሔር በግ አለ። ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ተከተሉት።ኢየሱስም ዘወር ብሎ ሲከተሉትም አይቶ። ምን ትፈልጋላችሁ? አላቸው።እርሱም፦ ረቢ፥ ወዴት ትኖራለህ? አሉት፤ ትርጓሜው መምህር ሆይ ማለት ነው።መጥታችሁ እዩ አላቸው። መጥተው የሚኖርበትን አዩ፥ በዚያም ቀን በእርሱ ዘንድ ዋሉ፤ አሥር ሰዓት ያህል ነበረ። ከዮሐንስ ዘንድ ሰምተው ከተከተሉት ከሁለቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ ነበረ።እርሱ አስቀድሞ የራሱን ወንድም ስምዖንን አገኘውና። መሢሕን አግኝተናል አለው፤ ትርጓሜውም ክርስቶስ ማለት ነው።ወደ ኢየሱስም አመጣው። ኢየሱስም ተመልክቶ። አንተ የዮና ልጅ ስምዖን ነህ፤ አንተ ኬፋ ትባላለህ አለው፤ ትርጓሜው ጴጥሮስ ማለት ነው።” ዮሐ.1፡36-43) ጴጥሮስንም ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ያመጣው እርሱ ነው።
·         ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንድርያስ ከወንድሙ ስምዖን ጋር አሳ በሚያጠምዱበት ጊዜ “በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ” ተብሎ ተጠርቷል። (ማር.1፡16-17)
·         ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሲያገለግል 5 እንጀራ የያዘውን ብላቴና ወደ ጌታ ያደረሰ ደቀመዝሙር ነበር። (ዮሐ.6፡8-9፣ ዮሐ.12፡21-22)
·         ጌታችንን ስለኢየሩሳሌም መፍረስ ከጠየቁት አንዱ ነበር። (ማር.13፡3-4)
·         ሀገረ ስብከቱ ልዳ ሲሆን በታህሳስ 4 ቀን አርፏል።
ቀ. ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ
·         ፊልጶስ ማለት ስውር ቦታ ማለት ነው።
·         ሀገረ ስብከቱ አፍራቅያ ሲሆን ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር ሲሄድ ኤላውትሮስ ዘጋኔንን ከከተማው በር አግኝተው ጋኔኑን አውጥተው ፈውሰው ይዘውት ገቡ፤ ትልቅ ዓምድ አግኝተው ወጥተህ መስክር ብለው ዓምዱን አውርደው አወጡት። ከዚያ ላይ ሆኖ ሲመሰክር ንውጽውጽታ ሆነ በድንጋጤ የሞቱም አሉ፤ በዚህም ተዓምር በአምላካችሁ እናምናለን ብለው ተምረው አምነው ተጠምቀዋል።
·         ነቢያተ ሐሰትንና የሐሰት ካህናትን ተመቅኝተው ከንጉሥ አስፈርደው ቁልቁል አሰቅለው በሰማዕትነት በሕዳር 18 ቀን አርፏል።
በ. ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ
·         ቶማስ ማለት ፀሐይ ማለት ነው። ቀዳሚ ስሙ ዲዲሞስ ሲሆን ዲዲሞስ ማለት ጨለማ ማለት ነው።
·         ጌታችን ከሙታን ከተነሳ በኋላ ያየው በ8ኛው ቀን እሑድ ሲሆን ያመነውንም በጦር የተወጋ ጎኑን ደሶ ነው። የእመቤታችንን ዕርገቷን አስቀድሞ ያየው እርሱ ነው።
·         ሀገረ ስብከቱ ሕንደኬ ነው። ምክንያት ይሁነኝ ብሎ በ30 ብር ተሽጦ ከመስፍነ ብሄሩ ሉክዮስ ቤት እያገለገለ ይኖር ነበር። ምን ትችላለህ ቢለው ሕንፃ ማነጽ ሐውልት ቢል ብዙ ገንዘብና ወርቅ ሰጥቶት ቢሄድ እርሱ ከዚህ በላይ ሕንፃ ማነጽ የለም በማለት ለነዳያን መጽውቶታል። የሉክዮስንም ሚስት ከነአገልጋዮቿ አስተምሮ አጥምቋቸዋል። ሉክዮስ መጥቶ ያነጽከው ህንጻና ሐውልት የታለ ቢለው ያነጽኳቸው ሕንፃዎች እኚህ ናቸው ብሎ ያመኑትን ቢያሳየው አታለልከኝ ብሎ እጅ እግሩን አስሮ ቆዳውን አስገፍፎ ስልቻ አሰፍቶ በአሸዋ መልቶ አሸክሞ ገበያ ለገበያ ሲያዞረው ሚስቱ ተመልክታ በድንጋጤ ሞታለች። አዝኖ ተክዞ ሚስቴ የሞተች ባንተ ምክንያት ነውና ካስነሳሃት በአንተ አምላክ አምናለሁ ቢለው ጌታችን ቁስሉን እንደ ውሃ አቀዝቅዞለት ካለችበት ሄዶ ስልቻውን ቢያስነካት ተነስታለች በዚህም ሉክዮስ አምኖ ተጠምቋል።
·         ስልቻውን ተሸክሞ ከቦታ ወደ ቦታ እየተዘዋወረ ሙት እያስነሳ ድውይ እየፈወሰ አህዛብን አሳምኖ አጥምቋል። ቀንጦፍያ ሲደርስ አንድ አረጋዊ 7 ልጆቹን ገድለውበት ሲያዝን ደርሶ ስልቻውን እያስነካ 7ቱንም አስነስቶለታል። በኢናስም የቃሉን ትምህርት የእጁን ተዓምራት ተመልክተው ከንግስቲቱ ጀምሮ እስከ ባሪያዎቿ ድረስ አምነው ተጠምቀዋል። ኋላ ግን ካህናተ ጣዖት ጥቅም የሚቀርባቸው ቢሆን በተንኮል ከንጉስና ከመኳንንቱ ጋር አጣልተው በዚህ በግንቦት 26 ቀን በ72ዓ.ም አንገቱን በሰይፍ አስመትረው በሰማዕትነት አርፏል።
ተ. ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ወልደ እልፍዮስ
ቸ. ሐዋርያው ቅዱስ ናትናኤል (ቀነናዊ ስምዖን)
·         ናትናኤል ማለት ሀብተ እግዚአብሔር ማለት ነው። ቀዳሜ ስሙ ስምዖን ሲሆን ትውልዱ ከነገደ ብንያም ነው። የተወለደው በቃና ሲሆን አባቱ ቀለዮጳ ይባላል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስምዖን በተወለደበት ዘመን ተወልዷል። ወደ ጌታችን ዘንድ ያቀረበው ፊልጶስ ነው።
·         “ፊልጶስ ናትናኤልን አግኝቶ። ሙሴ በሕግ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አግኝተነዋል አለው።ናትናኤልም። ከናዝሬት መልካም ነገር ሊወጣ ይችላልን? አለው። ፊልጶስ፤ መጥተህ እይ አለው።ኢየሱስ ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ። ተንኰል የሌለበት በእውነት የእስራኤል ሰው እነሆ አለ። ናትናኤልም። ከወዴት ታውቀኛለህ? አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ ፊልጶስ ሳይጠራህ፥ ከበለስ በታች ሳለህ፥ አየሁህ አለው።ናትናኤልም መልሶ፦ መምህር ሆይ፥ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ አለው።ኢየሱስም መልሶ፦ ከበለስ በታች አየሁህ ስላልሁህ አመንህን? ከዚህ የሚበልጥ ነገር ታያለህ አለው።” ዮሐ.1፡46-51 በዚህ ጊዜ ከሞት እንዳዳነው አውቆ አምኖ የተከተለው ሐዋርያ ነው።
·         ሀገረ ስብከቱ ሰሜን አፍሪካን ይዞ ግብጽ ድረስ ነው። ቢያስተምራቸው ህዝቡ ትምህርቱን ሰምተው ተዓምራቱን አይተው አምነው ተጠምቀዋል። ጣዖት አምላኪዎች ተመቅኝተው ከንጉሥ እንድርያኖስ ነገር ሰርተው አጣሉት። እርሱም በንጉሱ ፊት ሳይፈራ ስለወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ልደቱን፣ ጥምቀቱን፣ ሞቱን፣ ትንሣኤውን፣ ዕርገቱን ዳግም ምጽዓቱን መሰከረ፣ አስተማረው። እርሱ ግን ማን ፈቀደልህ ብሎ በሠይፍ አስመትሮ በሰማዕትነት በሐምሌ 10 ቀን አርፏል።\
እንዲሁም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አምነው የተከተሉት ሐዋርያት ብቻ ሳይሆኑ 36 ቅዱሳት አንእስት እና 72 አርድዕትም ነበሩ፤ በአጠቃላይ 120 ነበሩ። የእነዚህም ቅዱሳን ስማቸውን እንደሚከተለው ይሆናል፤
72ቱ ቅዱሳን አርድዕት
.
ስም
መታሰቢያ ቀን
1
ማርቆስ ዮሐንስ ወንጌላዊው
ሚያዝያ 30
2
እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት
ጥር 1 እና ጥቅምት 17
3
ጳውሎስ ሐዋርያ
ሐምሌ 5
4
ጢሞቴዎስ ወልዱ ለጳውሎስ
ህዳር 27 ጥቅምት 26
5
ሲላስ ወልዱ ለጳውሎስ
ጥቅምት 15
6
በርናባስ ወልዱ ለጳውሎስ

7
ቲቶ ወልዱ ለጳውሎስ
ታህሳስ 18 ጳጉሜ 2
8
ፊልሞና ወልዱ ለጳውሎስ
መጋቢት 7 ሕዳር 7
9
ቀሌምንጦስ ወልዱ ለጳውሎስ
መጋቢት 12
10
ዘኪዎስ ወልዱ ለማቴዎስ
ጥር 28
11
ቆርነሌዎስ ወልዱ ለጳውሎስ
መስከረም 11
12
ቴዎፍሎስ ወልዱ ለሉቃስ
መስከረም 1
13
ኤውዴዎስ
ሰኔ 21
14
አግናቴዎስ
ነሐሴ 23
15
አናንያኖስ ዘይሰመይ ይሁዳ
ነሐሴ 3
16
ማልኮስ (አግሊጦስ)
መስከረም 24
17
ኤሌናስ (ኢተኮስ)
ሚያዝያ 16
18
አርሳጢስ (አርጣቦሉ)
ሚያዝያ 29
19
አስተራቲዎስ ሀናንያ
መጋቢት 7 እና ሰኔ 26
20
አርሰጦበልስ ወልዱ ለጳውሎስ
መጋቢት 19
21
ጋይዮስ
ሚያዝያ 23
22
እድማጥስ
መስከረም 16
23
ሉኪዮስ
ታህሳስ 29
24
ድዮናስዮስ
ጥር 21
25
መርአንዮስ  (ዊይዳ)
ነሐሴ 6
26
አርክቦንዮስ
ህዳር 24
27
አናሲሞስ
ጳጉሜ 3
28
ከርላዲስ ወልዱ ለፊልጶስ
ሐምሌ 10
29
አኪላስ
መጋቢት 15
30
ንኪትስ (ኢያሶን)
ግንቦት 3
31
ቀርጾስ (ጢባርዮስ)
መስከረም 21
?32
ክርስቶፎሮስ (የአውሬ መልክእ ነበረው)
ሚያዝያ 2
33
ፊልጶስ ካልዕ
ጥቅምት 14
34
ጰርኮሮስ
ሰኔ 8
35
ኒቃሮና (3 ጊዜ ሞቶ የተነሳ)

36
ጢሞና ኡቲቦስ ረድዑ ለዮሐንስ ወንጌላዊ
ሚያዝያ 16 እና ሰኔ 8
37
ጰርሚና
መስከረም 21
38
ኒቆላዎስ ወልዱ ለሉቃስ
ሚያዝያ 15
39
ሉቃስ ወንጌላዊ ወልዱ ለዮሐንስ
ጥቅምት 22
40
ዮሴፍ
ነሐሴ 25
41
ኒቆዲሞስ
ሚያዝያ 6
?42
ያዕቆብ እሁሁ ለእግዚእነ
ጥቅምት 26 እና የካቲት 18
43
አብሮኮሮስ
መጋቢት 1 እና ጥር 20
44
ሮፎስ ወይም አንሲፎሮስ
መጋቢት 25
45
እስክንድሮስ
መጋቢት 1
46
ስልዋኖስ
የካቲት 11
47
ሳንቲኖስ (እንደ በቅሎ ተጎትቶ የሞተው)
መጋቢት 5
48
ኢዩስጦስ
ሚያዝያ 16
49
አክዩቁ (አጋቦስ)
የካቲት 4 እና ሚያዝያ 15
50
አፍሮዲጡ (አፍሮዲጦስ)
ግንቦት 23
51
አንሞስ (በጉድጋድ ጥለው ያሰቃዩት)
ታህሳስ 9
52
ገማልኤል
ሐምሌ 5
53
አንዲራኒቆስ
ጥር 8 እና ግንቦት 22
54
አናንያ
ጥቅምት 4 እና ሰኔ 27
55
ድርሶቅላ
ሰኔ 7
56
አቄላ
ሚያዝያ 5
57
ኤጴንጢስ
ሕዳር 15
58
አንድራኒቆስ (ጴጥሮስ)
ሕዳር 3
59
ዮልያል (ዮልዮስ)
ግንቦት 23
60
ጰልያጦስ
ሐምሌ 19
61
መርማርያን (በመጋዝ ሰንጥቀው የገደሉት)
መጋቢት 5
62
ኬፋ ወልዱ ለሉቃስ
ሰኔ 25
63
ኡርባኖስ ወልዱ ለቶማስ
ሰኔ 9
64
ስጠክን ወልዱ ለማትያስ
ሕዳር 13
65
አጤሌን ወልዱ ለፊልጶስ
ጥር 12
66
አክሌምንጦስ ወልዱ ለያዕቆብ
ጥር 21
67
ሔሮድያኖስ ወልዱ ለቶማስ
ሰኔ 21
68
ጥርፌና ወልዱ ለታዴዎስ
ህዳር 3
69
ጠርፌስ ወልዱ ለበርተለሜዎስ
መጋቢት 16
70
አስከሪጦስ ወልዱ ለጴጥሮስ
ሰኔ 25
71
ሉቅዮስ ወልዱ ለያዕቆብ ወልደዘብዴዎስ
ህዳር 3
72
ሱሲ ወልዱ ለማቴዎስ
መጋቢት 9

36ቱ ቅዱሳን አንእስት
ተ.ቁ
ስም
የመታሰቢያ ቀን
1
ኤልሳቤጥ
የካቲት 16
2
ሐና
መስከረም 7
3
ቤርዜዳን (ቤርስት)
ታህሳስ 10
4
መልቲዳን (ማርና)
ጥር 4
5
ሰሎሜ
ግንቦት 25
6
ማርያም መግደላዊት
ነሐሴ 6
7
ማርያም እንተ ህፍረት እህተ አልዓዛር
የካቲት 6
8
ሐና ነቢይት
የካቲት 20 እና ጥቅምት 6
9
ማርያም እሙ ለደቂቀ ዘብዴዎስ
ጥር 18
10
ሶፍያ (በርበራ)
ጥር 30
11
ዮልያና (ዮና)
ሕዳር 18
12
ሶፍያ (መርኬዛ)
ጥር 30
13
አውጋንያ (ጲላግያ)
ጥቅምት 11
14
አርሴማ
ግንቦት 11
15
ዮስቲና
ጥር 30
16
ጤግላ
ነሐሴ 6
17
አርኒ (ሶፍያ)
ሕዳር 10
18
እሌኒ
ጥር 29
19
ኢዮጰራቅሊያ
መጋቢት 26 እና ነሐሴ 2
20
ቴዎክላ (ቴዎድራ)
ጥር 4
21
ክርስቲያና (አጥሩኒስ)
ሕዳር 18
22
ጥቅሞላ (አሞና)
ጥር 30
23
ጲስ
ጥር 30
24
አላጲስ
ጥር 30
25
አጋጲስ
ጥር 30
26
አርሶንያ (አርኒ)
ጥር 30
27
ጲላግያ
ጥር 30 እና ጥቅምት 11
28
አንጦልያ (ሉክያ)
የካቲት 25
29
አሞን (ሶፍያ)
ጥር 15 እና ነሐሴ 3
30
ኢየሉጣ
ነሐሴ 6
31
መሪና
ሐምሌ 27
32
ማርታ እህተ አልዓዛር
ጥር 18 እና ግንቦት 27
33
ማርያም የማርቆስ እናት
ጥር 30
34
ሳራ (ሶፍያ) የይሁዳ እናት
ጥር 30
35
ዮሐና (ዮላና) የኩዛ ሚስት
ታህሳስ 26
36
ሶስና
ግንቦት 12

እነዚህ ጌታችንን ሲከተሉ ግማሹ በጉልበታቸው ግማሹ አብሮ በማደርና አብሮ በመዋል ከጌታችን ሳይለዩ አገልግለው በኋላ መንፈስቅዱስ በወረደበት ጊዜ አብረው ስለነበሩ ግምሹ ከሐዋርያት ጋር ተከፋፍለው ተሰማርተዋል። ለእያንዳንዳቸውም እንደ ሐዋርያት 36ቱ ቅዱሳት አንእስትም አንድ ስም ብቻ አልነበራቸውም፤ በግሪክኛ፣ በሮማይስጥኛ፣ በአረማይክኛ፣ በዕብራይስጥኛ የ12ቱም የ72ቱም የ36ቱም ቅዱሳት የተለያየ ስም እንዳላቸው ተገልጿል።
  ይቆየን...
የቦ/መ/ብ/ቅ/እግዚአብሔር አብ ቤ/ክ ሰ/ት/ቤት

No comments:

Post a Comment