13

.

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው::" የማቴዎስ ወንጌል 7: 4

"እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅናወተት ግዙ።" ትንቢተ ኢሳይያስ 55 : 1

Friday, October 21, 2011

ነገረ ቅዱሳን ክፍል 7


ክፍል ሦስት
ንዋያተ ቅድሳት
በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሚውሉ ንዋያት ሁሉ የተቀደሱ ናቸው። ምክንያቱም አገልግሎቱ የሚፈጸመው ቅድስና የባህርይ ገንዘቡ ለሆነ ለእግዚአብሔር ነውና ንዋያቱ ሁሉ ቅዱሳት ናቸው።

ጥቅስ፡
V  አንተም ክቡሩን ሽቱ ውሰድ የተመረጠ ከርቤ አምስት መቶ ሰቅል፥ ግማሽም ጣፋጭ ቀረፋ ሁለት መቶ አምሳ ሰቅል፥ የጠጅ ሣርም እንዲሁ ሁለት መቶ አምሳ ሰቅል፥ብርጕድም አምስት መቶ ሰቅል እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን፥ የወይራ ዘይትም አንድ የኢን መስፈሪያ ትወስዳለህ።በቀማሚም ብልሃት እንደ ተሠራ ቅመም፥ የተቀደሰ የቅብዓት ዘይት ታደርገዋለህ የተቀደሰ የቅብዓት ዘይት ይሆናል።የመገናኛውንም ድንኳን፥ የምስክሩንም ታቦት፥ገበታውንም ዕቃውንም ሁሉ፥ መቅረዙንም ዕቃውንም፥ የዕጣን መሠዊያውንም፥ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን መሠዊያና ዕቃውንም ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውንም ትቀባበታለህ። ሁሉንም ትቀድሳቸዋለህ፥ ቅድስተ ቅዱሳንም ይሆናሉ የሚነካቸውም ሁሉ ቅዱስ ይሆናል።” ዘጸ. 30፡22-29
V  ከጥሩ ወርቅም የተሠሩትን ጽዋዎችና ጕጠቶች፥ ድስቶቹንና ጭልፋዎቹንም፥ ማንደጃዎቹንም፥ ለውስጠኛውም ቤት ለቅድስተ ቅዱሳን ደጆች ለቤተ መቅደሱም ደጆች የሚሆኑትን የወርቅ ማጠፊያዎች አሠራ።1ነገ. 7፡50
በቤተክርስቲያን ለአገልግሎት የሚውሉ ንዋያተ ቅድሳትን በ2 ከፍለን እንመለከታለን፡
1.    የቤተመቅደስ አገልግሎት የሚሰጡ ንዋያተ ቅድሳት፡
እነዚህ ንዋያተ ቅድሳት የአምልኮ ሥርዓት በሚፈጸምበት ጊዜ አገልግሎት የሚሰጡ ንዋያት ናቸው። እነዚህም፡-
ሀ. ታቦተ ሕግ (ጽላት)


v  ታቦት ማለት ማደሪያ፣ መሰወሪያ፣ የእግዚአብሔር መገለጫ ማለት ነው። (ዘጸ. 13፡21-22)
v  ጽላት እግዚአብሔር አምላካችን ለሙሴ አስቀድሞ አሰርቱ ቃላትን በእጁ ጽፎ የሰጠው ቃሉ ተጽፎ የሚገኝበት ነው። (ዘጸ. 31፡18 “እግዚአብሔርም ከሙሴ ጋር በሲና ተራራ የተናገረውን በፈጸመ ጊዜ በእግዚአብሔር ጣት የተጻፈባቸውን ከድንጋይ የሆኑ ሁለቱን የምስክር ጽላቶች ሰጠው።”) ታቦት የሚባለው ጽላቱ የሚቀመጥበት ማደሪያ ነው። በአሁኑ ጊዜ ታቦትና ጽላት በአንድ ይጠራሉ።
v  እህት አብያተክርስቲያናት መሰዊያ (Altar) በማለት ይጠሩታል ክብሩም ልዩ ነው። እኛ መንበረ ታቦት ያለን በመሆኑ በእውነት ያለሐሰት የሚሻል እንዳለን እንናገራለን።  ጽላተ ኪዳኑ ማኅደረ እግዚአብሔር ነው፤ ያለታቦቱም መስዋዕት አይሰዋም።
v  በጽላቱ ላይ “አልፋ ወኦ ቤጣ የውጣ” የሚለው የእግዚአብሔር ስም ይቀረጽበታል። ከላይ ሥዕለ ሥላሴ ቀጥሎ ምስለ ፍቁር ወልዳ ዮሐንስ ፍቁረ እግዚእ እንዲሁም መቅደሱ የተሰራለት ወይም ቤተክርስቲያኑ የታነጸለት ጻድቅም ሆነ ሰማዕት፣ መልአክም ሆነ ሐዋርያ ስዕሉ ይቀረጽበታል፤ ስሙ ይጻፍበታል። ከዚህ በኋላ በኤጲስ ቆጶስ እጅ ተባርኮ እና ሜሮን ተቀብቶ በመንበሩ ይሰየማል።
v  በቅዳሴ ጊዜ ኅብስቱ እና ወይኑ ወደ ቤተመቅደስ ሲገባ ካህኑ ሥርዓተ ቅዳሴውን የሚያከናውነው፣ ኅብስቱን ሥጋ መለኮት ወይኑን ደመ መለኮት የሚለወጠው በታቦቱ ላይ ነው። ይህም አሁን ያለው ታቦት ከቀደመው ክብሩ እንደሚበልጥ ያስረዳል። የቀደመው የእንስሳ ደም ይሰዋበትና ይረጭበት ነበር፤ የአሁኑ ግን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ክቡር ሥጋውና ቅዱስ ደሙ ይቀርብበታል።
ለ. መስቀል
1.    የመጾር መስቀል
v  የመጾር መስቀል በሥርዓተ ቅዳሴ ጊዜ በዲያቆናት እጅ እንዲሁም በካህናት ለቡራኬ የሚይዙት ሲሆን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ሰበን (መግነዝ) ለሐዋርያት በእርገቷ ጊዜ የሰጠቻቸው ምሳሌ የሆነ አብሮ የሚንጠለጠልበት መስቀል ነው።


2.   የእጅ መስቀል
v  ይህ በቀሳውስት፣ ቆሞሳት፣ ጳጳሳት እጅ ቡራኬ የሚሰጡበት ወይም የሚባርኩበት መስቀል ነው። ያለመስቀል ሥርዓተ ቅዳሴን መፈጸም አይቻልም።


ሐ. የክህነት አልባሳት
የቀሳውስት አልባሳት
v  አሮንንና ልጆቹንም ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ አቅርበህ በውኃ ታጥባቸዋለህ። የተቀደሰውንም ልብስ አሮንን ታለብሰዋለህ በክህነትም ያገለግለኝ ዘንድ ቀብተህ ትቀድሰዋለህ።ልጆቹንም አቅርበህ ሸሚዞችን ታለብሳቸዋለህ በክህነትም ያገለግሉኝ ዘንድ አባታቸውን እንደ ቀባህ ትቀባቸዋለህ መቀባታቸውም ለልጅ ልጃቸው ለዘላለም ክህነት ይሆንላቸዋል።” ዘጸ. 40፡ 12-15 በተባለው የእግዚአብሔር ቃል መሰረት የክህነት አልባሳት ለእግዚአብሔር የተለዩ አገልግሎታቸውም ልዩ ነው። እንዲሁም በዘጸ.39፡1-ፍጻሜ “እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ በመቅደሱ ለማገልገል ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይ ግምጃም በብልሃት የተሠራ ልብስ፥ ለአሮንም የተቀደሰውን ልብስ አደረጉ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ ኤፉዱን ከወርቅ ከሰማያዊም ከሐምራዊም ከቀይ ግምጃም ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ አደረገ። ወርቁንም ቀጥቅጠው እንደ ቅጠል ስስ አድርገው እንደ ፈትል ቈረጡ። ብልህ ሠራተኛም እንደሚሠራ ሰማያዊ ሐምራዊም ቀይም ግምጃ የተፈተለም ጥሩ በፍታ ከእርሱ ጠለፉ።ሁለቱ ወገን እንዲጋጠም በሁለቱ ጫንቃዎች ላይ የሚጋጠም ልብስ አደረጉት። በላዩም መታጠቂያ ሆኖ በብልሃት የተጠለፈው የኤፉዱ ቋድ እንደ እርሱ ከእርሱም ጋር አንድ ነበረ ከወርቅና ከሰማያዊ ከሐምራዊ ከቀይ ግምጃም ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ የተሠራ ነበረ።እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ በወርቅ ፈርጥ የተያዙ የመረግድ ድንጋዮች ሠርተው እንደ ማኅተም ቅርጽ የእስራኤልን ልጆች ስም ቀረጹባቸው። …በቀሚሱም ታችኛ ዘርፍ ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ፥ ከተፈተለ በፍታም ሮማኖች አደረጉ።” ይላልና በትውፊትና በምሳሌ ዛሬም ቀሳውስትና ዲያቆናት የሚለብሱት ልብሰ ተክህኖ አለ። እነዚህንም እንደሚከተለው እንመለከታለን፡-
1.    የቀሳውስት ልብስ
1.1   ቀሚስ
v  በጥንት ዘመን አብደላከኒ የሚባል የካህናት ቀሚስ ነበር፤ አሁን ግን ጌጥነት ካላቸው ጨርቆች የሚሰራ ነው።
v  በመጀመሪያ የሚለበስ ልብስ ነው፤ በልክ እንዲሆን የታዘዘ ሲሆን ከረዘመ ማሳጠሪያ፣ ሰውነትን ማጠንከሪያ የሚሆን መታጠቂያ አለው።
1.2  ካባ ላንቃ
v  መደረቢያው ልብስ ካባ ላንቃ ይባላል። ከካባው ጋር ለምድ አብሮ ተሰፍቶ ስለሚገኝ ነው “ካባ ላንቃ” የተባለው። ለምዱ እግር ወይም ዘርፍ በየቦታው እንደ ላንቃ ስለሚወርድ ካባ ላንቃ ተባለ።
v  ልዩ ልዩ ቀለማት ካላቸው ጨርቆች የሚሰራ ነው። ወርቅና ሐሩ አብሮ ተፈትሎ ከተሰራ ጨርቅ ሊሰራ ይችላል።
1.3  ሞጣእት
v  በአንገት ተጠልቆ ፊት ለፊት የሚወርድ የደረት ልብስ ነው። ይህም በኦሪቱ ኤፉድ የሚባለው የአሮን ልብስ አምሳል ነው። ካባ ላንቃ በተሰራበት መንገድ የሚሰራ ይሆናል።
1.4  ቆብ (ቀጸላ፣ ሕባኔ)
v  በሥርዓተ ቅዳሴ ጊዜ ካህኑ ወይም ቄሱ በራሱ ላይ ደፍቶ የሚገባው ነው።
v  ምሳሌው፡

2.   የዲያቆናት ልብስ
2.1  ቀሚስ
ጌጥነት ካላቸው ጨርቆች የሚሰራ ነው። በመጀመሪያ የሚለበስ ልብስ ነው፤ በልክ እንዲሆን የታዘዘ ሲሆን ከረዘመ ማሳጠሪያ፣ ሰውነትን ማጠንከሪያ የሚሆን መታጠቂያ አለው።
2.2 ለምድ ላንቃ
v  በቀድሞ ዘመን ቀሚሱ ለብቻ ለምዱ ለብቻ ይዘጋጅ ነበር። አሁን ግን ለምዱ ከቀሚሱ ጋር አብሮ የሰፋል።
2.3 ከፋይ ድግድጋት
v  ከግብጽ ቤተክርስቲያን የተወሰደ ሲሆን ዲያቆናት አንዳንድ ጊዜ ለምድና ቀሚስ በመልበስ ፋንታ ቀሚስ ለብሰው በከፋይ መታጠቂያ በመስቀለኛ ቅርጽ ስለሚታጠቁና ስለሚያደገድጉ ከፋይ ድግድጋት ይባላል።
v  በአሁን ጊዜ ዲያቆናቱ እየተዉት ሰንበት ተማሪዎች ሲጠቀሙበት ይታያል።
2.4 አክሊል (ቆብ)
v  በሥርዓተ ቅዳሴ ጊዜ ዲያቆን አክሊል ወይም ቆብ አድርጎ ይቀድሳል።
v  ምሳሌው፡

3.   ማኅፈዳት
v  5 የልብስ መጠቅለያዎች ወይም መሸፈኛዎች ናቸው። ብዙውን ጊዜ በጥቁር ጨርቅ የሚሰሩ ናቸው። አንደኛው ከጻሕሉ ስር በታቦቱ ላይ ይነጠፋል፤ ሁለተኛው በጻሕሉ ላይ ይነጠፋል፤ ኅብስቱ የሚጠቀለልበት ነው፤ ሦስተኛው የመሥዋዕቱ ልብስ ነው፤ ቁመቱ ከምስራቅ ወደ ምዕራብ ሆኖ ይለብሳል። አራተኛው ከሰሜን ወደ ደቡብ ሆኖ ይለብሳል፤ አምስተኛው ከሰሜን ምስራቅ (መስዕ) ወደ ደቡብ ምዕራብ (አዜብ) ሆኖ ይለብሳል።
v  ምሥጢሩ፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከብቶች በረት ሲወለድ በጨርቅ መጠቅለሉንና በበለስ ቅጠል መሸፈኑን የሚያስረዳ፤ አንድም ዮሴፍና ኒቆዲሞስ በድርብ በፍታ የገነዙትን የሚያመለክት ነው።
4.   መንጦላዕት
v  በሦስቱም የመቅደስ በር የሚጋረዱ መጋረጃዎች ናቸው። እነርሱም የመቅደሱን ክብር የሚሰጡ ናቸው። መጋረጃዎቹ የሚከፈቱበትና የሚዘጉበት ጊዜ አለ። በመጀመሪያ ቅዳሴ “አእኑየ” ከሚለው ምዕዳን ጀምሮ እስከ “ሚመጠን” እስከሚለው ድረስ ይዘጋል። “ስግዱ” ተብሎ ከታወጀ እና “ፍትሐት ዘወልድ” እና “በእንተ ቅድሳት” ሲጸለይ ከተከፈተ ጀምሮ እስከ ፍሬ ቅዳሴ ድረስ ይከፈታል። ከፍሬ ቅዳሴ እስከ ሦስተኛው “ጸሎተ ፈትቶ” ማለትም “አርህዉ ኆኅተ መኳንንት” ብሎ ንፍቁ ዲያቆን ማሳሰቢያ እስከሚሰጥ ድረስ ይዘጋል። “አርህዉ ኆኅተ መኳንንት” ሲል ይከፈታል፣ በቁርባን ጊዜ ይዘጋል።
5.   ልብሰ ታቦት (መጎናጸፊያ)
v  ይህ ለአክብሮተ ሥጋውና ደሙ በቅዳሴ ጊዜ መንበሩ ወይም መሰዊያው የሚለብሰው፣ ታቦት በወጣ ጊዜ የሚጎናጸፈው ነው። ስለዚህ ስሙ መጎናጸፊያ ይባላል።
መ. መንበረ ታቦት
v  መንበር የታቦት ወይም የጽላት መቀመጫ ዙፋን ነው። መሥዋዕተ ኦሪቱ ይቃጠልበት፣ ይሰዋበት በነበረው ፈንታ መንበሩ ይገባ ስለነበር ከታቦቱ ጋር “መሰዊያ” ይባላል።


ሰ. ጻሕል
v  የክቡር ሥጋው ማስቀመጫ እና ማክበሪያ ነው። ይኸውም ከወርቅና ከብር፣ ከነሐስና ከብረት የሚሰራ ነው። የተለየ ቅርጽ የተለየ ምልክት ያለው ነው።
v  ምሳሌውም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት በረት ቦታ አንድም የመቃብሩ ቦታ ምሳሌ ነው።
ረ. ጽዋዕ
v  የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ደም የሚቀርብበት ንዋየ ቅዱስ ነው።
v  ከወርቅ ከብር ከመዳብ ከነሐስ ወይም ከብረት የሚሰራ ነው።
v  ምሳሌውም፡ በዕለተ ሐሙስ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ፦ ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው።” ማቴ 26፡27 ብሎ የሰጠበት ጽዋዕ አንድም መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል ጌታችን በተሰቀለ እና ደሙ በፈሰሰ ጊዜ በብርሃን ጽዋዕ ተቀብሎ በዓለምም ላይ እንደረጨ የሚያስረዳ ነው።
ሠ. እርፈ መስቀል
v  የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ደም ለማቀበል የሚያገለግል ንዋየ ቅዱስ ነው። ይኸውም ጽዋዕ ከተሰራበት ቁስ የሚሰራ ሲሆን በደሙ በያዣ በኩል በጣም ጎድጎድ ያለ ልዩ ቅርጽም ያለበት ወደ እጅ መያዣው ጋር መስቀል ያለበት ነው።
v  ምሳሌውም፡ የሱራፊ ጉጠት ምሳሌ ነው። የሱራፊ ጉጠት ፍም ይዟል፤ እርፈ መስቀሉም የመለኮትን እሳታዊ ደም ይይዛል። የሱራፊ ጉጠት የያዘው ፍም የኢሳይያስን ከንፈር ከለምጽ አድኗል፤ ቅዱስ ደሙም ምዕመናንን ለኃጢአት አድኗል። (ት.ኢሳ. 6፡6-7 "ከሱራፌልም አንዱ እየበረረ ወደ እኔ መጣ፥ በእጁም ከመሠዊያው በጕጠት የወሰደው ፍም ነበረ። አፌንም ዳሰሰበትና። እነሆ፥ ይህ ከንፈሮችህን ነክቶአል በደልህም ከአንተ ተወገደ፥ ኃጢአትህም ተሰረየልህ አለኝ።”)
ሸ. ዓውድ
v  በድርገት ጊዜ ጻሕል የሚደረግበት ሰፋ ያለ ጻሕል ነው። ክቡር ሥጋው እንዳይነጥብ መጠበቂያና ሰፋ፣ ጎላም ብሎ እንዲታይ የሚያደርግ ነው። የሚሰራው ከብረት፣ ከነሃስ፣ ከእንጨትም ነው። ስሙ እንደሚያመለክተው አደባባይ ማለት ስለሆነ ጌታችን የተፈረደበት የጲላጦስ አደባባይ ምሳሌ ነው።
ቀ. አጎበር
v  በዓውዱ ላይ የሚደፋ አራት ማዕዘን ሦስት እግር ያለው እንጨት ወይም ብረት ሊሆን ይችላል። ይህም ክቡር ሥጋውን ልብሱ እንዳይነካው ከፍ አድርጎ ልብሱን የሚይዝ የሚከላከል ነው። እንዲሁም መጎናጸፊያውን ከፍ አድርጎ ክብሩን የሚገልጽ ነው።
በ. ጽንሐሕ
v  የእጣን ማሳረጊያ ንዋይ ቅዱስ ነው። ይኸውም ከወርቅ፣ ከብር፣ ከብረት ሊሰራ ይችላል። በኦሪት የወርቅ ማዕጠንት እንዲሰራ እግዚአብሔር ለሙሴ ያዘዘው ነው። በዚህ ምሳሌ ዛሬ ድረስ ይሰራል።
ተ. መሶበ ወርቅ
v  ኅብስተ ቁርባን ከቤተልሔም ወደ ቤተመቅደስ የሚመጣበት ነው። ከስንደዶ፣ አክርማ፣ ከአለላ፣ ከወርቅ፣ ከብርና ከሌሎች ከከበሩ ማዕድናት የሚሰራ ነው።
v  መለኮትን በማኅጸኗ 9 ወር ከ5 ቀን የተሸከመችና በቤተልሔም ተጉዛ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ነው።

ቸ. ቃጭል (ቃለ ዓዋዲ፣ መረዋ)
v  በቅዳሴ ጊዜ የሚቃጨልና ድምጽን የሚሰጥ ንዋየ ቅዱስ ነው። የሚቃጨለውም ወይም የሚመታውም ወደ ቅዳሴ ሲገባ፣ “ጻዑ ንዑሰ ክርስቲያን” ሲባል፣ በእግዚኦታ ጊዜ፣ ድርገት ሲወርድ፣ በጸሎትና በምህላ ጊዜ ይቃጨላል። በሰሙነ ሕማማት ጊዜ ደውልን ተክቶ ያገለግላል።
v  ምሳሌነቱ፡ በበረሃ የአዋጅ ነጋሪ ቃልን እየተናገረ መንገዱን የጠረገ የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ምሳሌ ነው። (የአዋጅ ነጋሪ ቃል። የእግዚአብሔርን መንገድ በምድረ በዳ ጥረጉ፥ ለአምላካችንም ጐዳና በበረሀ አስተካከሉ።ኢሳ.40፡3)
ኀ. ደውል
v  ኖኅ መርከቡን ለመስራት እጸ አብኖስ በሚባል እንጨት ቁመቱ ሦስት ክንድ፣ ስፋቱ አንድ ክንድ አድርጎ ሰርቶ በየዕለቱ በነግህ ለጸሎት፣ በቀትር ለምግብ፣ በሰርክ ለማሰናበት ሦስት ጊዜ እየደወለ ይጠቀምበት ነበር ይላል ቀሌምንጦስ። የደውሉም አገልግሎት እንዲህ እያለ ከኖኅ እስከ ሙሴ ደርሷል። (ዘኁ 10፡2 “ሁለት የብር መለከቶች አጠፍጥፈህ ለአንተ አድርግ ማኅበሩን ለመጥራት ከሰፈራቸውም ለማስጓዝ ይሁኑልህ።”) በዚህም ምሳሌ “ሥርዓተ ሰማይ ተሰርዓ በምድር” የሚለውን አብነት በማድረግ ለቤተክርስቲያናችን ለመንፈሳዊ አገልግሎት እንጠቀምበታለን። (ራእ. 4፡1 “ከዚያ በኋላም አየሁ፥ እነሆም በሰማይ የተከፈተ ደጅ፥ እንደ መለከትም ሆኖ ሲናገረኝ የሰማሁት ፊተኛው ድምፅ። ወደዚህ ውጣና ከዚህ በኋላ ሊሆን የሚያስፈልገውን ነገር አሳይሃለሁ አለ።”)
v  አገልግሎቱም ሌሊት የተኙትን በመቀስቀስ ለሰዓታትና ለማኅሌት 15 ጊዜ ይደወላል፤ በነግህ በ3 ሰዓት ለዋዜማ ቁመት 12 ጊዜ ይደወላል፤ በሰርክ ለቅዳሴ መግቢያ 3 ጊዜ ይደወላል፤ በጻዑ ንዑሰ ክርስቲያን ጊዜ 3 ጊዜ ይደወላል፤ በእግዚኦታ ጊዜ 7 ጊዜ ይደወላል፤ በድርገት ጊዜ 5 ጊዜ ይደወላል።
v  ምሳሌውም የቀርነ መለከት ሲሆን 15 ጊዜ መደወሉ የ15ቱ ነቢያት ምሳሌ ነው፤ 12 ጊዜ መደወሉ የ12ቱ ሐዋርያት ምሳሌ ነው፤ ሌሊት መደወሉ ነቢያት በዘመነ ጽልመት መኖራቸው ምሳሌ ነው፤ በሰርክ መደወሉ ብርሃን የተባለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመገለጹ ምሳሌ ነው።


2.   የቅኔ ማኅሌት ንዋያተ ቅድሳት፡
ሀ. ከበሮ
v  ከበሮ የሚለው ቃል አታሞ፣ ነጋሪት፣ ለክብረ-በአል የሚመታ፣ ትእምርተ ክብር፣ ጯሂ፣ ተሰሚ ማለት ነው።
ጥቅስ፡
V   “የአሮን እኅት ነቢይቱ ማሪያምም ከበሮ በእጅዋ ወሰደች ሴቶችም ሁሉ በከበሮና በዘፈን በኋላዋ ወጡ።” ዘጸ. 15፡20
V  “በከበሮና በዘፈን አመስግኑት በአውታርና በእምቢልታ አመስግኑት።” መዝ.150፡4
V  “ዝማሬውን አንሡ ከበሮንም ስጡ፥ ደስ የሚያሰኘውን በገና ከመሰንቆ ጋር በመባቻ ቀን በከፍተኛው በዓላችን ቀን መለከትን ንፉ።” መዝ.80(81)፡2
V  “ስሙን በዘፈን ያመስግኑ፥ በከበሮና በመሰንቆም ይዘምሩለት።”መዝ.149፡3
V  “ዮዲትም ፈጣሪያችንን እግዚአብሔርን ከበሮ እየመታችሁ አመስግኑት። ብላለች” ዮዲት 16፡2
v  ከበሮ ከከብት ቆዳ ተጠፍሮ ከእንጨት ወይም ከብር የሚሰራ የዜማ መሳሪያ ነው።
v  ምስጢሩ፡
o   ከበሮ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ፡-
§   ሽፋኑ (ግምጃ) ለመዘባበቻ አይሁድ ሸፍነው “መኑ ጸፍዓከ ወመኑ ኮርአከ ተነበይ ለነ ክርስቶስ፡  በጥፊ የመታህ ማን ነው? ትንቢት ተናገር እያሉ ይጠይቁት ነበር።” ሉቃ.22፡64 እያሉ የሸፈኑበት ግምጃ ምሳሌ ነው። አንድም ዮሴፍና ኒቆዲሞስ በድርብ በፍታ የገነዙበትን መግነዝ ያስረዳል።
§   ከበሮ ግራና ቀኝ መመታቱ “ዘበእንቲአሃ ለቤተክርስቲያን ተጸፋእከ በውስተ ዓውድ ከመትቀድሳ፡                                               “ ያለውን በማስታወስ የግራና የቀኝ ጉንጩ ምሳሌ ነው።
§  ድምጹ የወንጌል ወይም “ኤሎሔ ኤሎሔ ላማ ሰበቅታኒ”ማቴ. 27፡46፣ ማር.15፡34 ምሳሌ ነው።
§  ጠፍሩ ጌታችን 6666 ጊዜ መገረፉና በሰውነቱ ላይ የወጣውን ስፍር ቁጥር የሌለውን ሰንበር ምሳሌ ነው።  አንድም ሰፊውና ጠባቡ እንደተያያዙበት መለኮት በሥጋ ማርያም እንደተዋሐደ፤ አንድም መለኮታዊ ፍቅሩ ወደ ምድር እንደሳበውና እንደተወለደ ያጠይቃል።
§  ማንገቻው የተገረፈበት ጅራፍ ምሳሌ ነው።
§  አካሉ (በብር ወይም በእንጨት የሚሰራው) የተቀበረበት መቃብር ምሳሌ ሲሆን አንዱ ሰፊ መሆኑ የማይመረመር ረቂቅ ሰፊ፣ ምሉዕ በኩልሄ፡ በሁሉ ቦታ ያለ የሆነ መለኮታዊ ባህርይን ሲያጠይቅ አንዱ ጠባብ መሆኑ በጠባብ ደረት፣ በአጭር ቁመት የማይወሰነው መወሰኑን፣ መወለዱን ያጠይቃል።
§  በውስጡ ያለው ጠጠር በአዲስ መቃብር ውስጥ 3 መዓልትና 3 ሌሊት ማደሩን ሲያጠይቅ በብዛት አንድ ብቻ ሲሆን 3 ወይም 5 ይደረጋል። ይህም 3 ከሆነ ምሥጢረ ሥላሴን፤ 5 ከሆነ 5ቱ ዓዕማደ ምሥጢራትን ያስረዳል።
ለ. ጸናጽል
v  ጸነጸለ፣ መታ ካለው ግሥ የተገኘ ነው። ጸናጽላት በሚልበት ጊዜ ብዛትን ጸናጽል በሚልበት ጊዜ ነጠላን የሚያመለክት ሲሆን ትርጉሙም ሻኩራ፣ ቃጭል እንደማለት ነው።
v  ጸናጽል ከነሃስ፣ ከብርና ከሌላም ማዕድን ሊሰራ የሚችል የዜማ መሳሪያ ነው። ጸናጽል ያማረ ድምጽ ያለው ሆኖ መልክና ልዩ ጌጥ አለው። መዝ. 150፡5 “ድምፁ መልካም በሆነ ጸናጽል አመስግኑት እልልታ ባለው ጸናጽል አመስግኑት።” እንዲል።
v  በጥንት ዘመን ግብጻውያን እግዚአብሔርን ያመሰግኑበት እንደነበር ይነገራል። “ዳዊትና የእስራኤልም ቤት ሁሉ በቅኔና በበገና በመሰንቆም በከበሮም በነጋሪትና በጸናጽል በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኃይላቸው ይጫወቱ ነበር።”2 ሳሙ. 6፡5
v  አሰራሩም ከላዩ ቀስተደመና ይመስላል፤ ከታች መጨበጯው አንድ ሆኖ የላም ምስል ነበረበት። በዚህም መሳሪያ ዕብራውያን ይገለገሉበት ነበር። በቤተክርስቲያናችንም የምንገለገልበት ጸናጽል ልዩ ቀስተ ደመና መምሰሉ “እሰይም ቀስተ በውስተ ደመና፡ለዘላለም የማደርገው የቃል ኪዳን ምልክት ይህ ነው” ዘፍ. 9፡12 ብሎ እግዚአብሔር ለኖኅ ያሳየው የምህረት ቃልኪዳን መታሰቢያ መሆኑን፤ አራቱ ዘንጎች የአራቱ ባህርያተ ሥጋ (መሬት፣ እሳት፣ ነፋስና ውሃ)፤ ቅጠሎቹ የፍጥረታት ምሳሌ መሆናቸውን ይኸውም ከ4ቱ ባህርያት የተፈጠሩትን ፍጥረታት ሁሉና ሰውንም አላጠፋም ብለህ ቃልኪዳን ሰጥተሃልና ኪዳንህን አስብልን በኃጢአታችን አታጥፋን ብለው ማመስገናቸውን የሚያመለክት ነው፤ አንድም መሰላሉ ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ ተኝቶ ያየው መሰላል ምሳሌ ነው።( ዘፍ. 28፡11-13 “…ሕልምም አለመ እነሆም መሰላል በምድር ላይ ተተክሎ፥ ራሱም ወደ ሰማይ ደርሶ፥ እነሆም የእግዚአብሔር መላእክት ይወጡበት ይወርዱበት ነበር።”) በግራና በቀኝ ባሉት ዓምዶች መካከል ያሉት ሁለት ቀጫጭን ዘንጎች ወይም ጋድሞች የመሰላል፣ የተንጠለጠሉት ቅጠሎች በመሰላሉ ላይ ይወጡና ይወርዱ የነበሩት መላእክት ምሳሌ አንድም በግራና በቀኘ የቆሙት ዓምዶች የብሉይ ኪዳንና የሐዲስ ኪዳን ምሳሌ፤ ሁለቱ ጋድሞች የፍቅረ እግዚአብሔርና የፍቅረ ቢጽ ምሳሌ ናቸው።
v  ጥቅስ፡
o   2 ዜና. 29፡ 25 “ይህንም ትእዛዝ እግዚአብሔር በነቢያቱ እጅ አዝዞአልና እንደ ዳዊትና እንደ ንጉሡ ባለ ራእይ እንደ ጋድ፥ እንደ ነቢዩም እንደ ናታን ትእዛዝ፥ ጸናጽልና በገና መሰንቆም አስይዞ ሌዋውያንን በእግዚአብሔር ቤት አቆመ።”
o   1 ዜና. 15፡16 “ዳዊትም በዜማ ዕቃ በመሰንቆና በበገና በጸናጽልም እንዲያዜሙ፥ ድምፃቸውንም በደስታ ከፍ እንዲያደርጉ መዘምራኑን ወንድሞቻቸውን ይሾሙ ዘንድ ለሌዋውያን ኣለቆች ተናገረ።”
o   2 ሳሙ. 6፡5 “ዳዊትና የእስራኤልም ቤት ሁሉ በቅኔና በበገና በመሰንቆም በከበሮም በነጋሪትና በጸናጽል በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኃይላቸው ይጫወቱ ነበር።”
o   2 ዜና.5፡13 “መለከቱንም የሚነፉ መዘምራኑም በአንድነት ሆነው እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ። እግዚአብሔር ቸር ነውና፥ ምሕረቱም ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ እያሉ በአንድ ቃል ድምፃቸውን ወደ ላይ ከፍ አድገው በመለከትና በጸናጽል በዜማም ዕቃ ሁሉ እግዚአብሔርን ባመሰገኑ ጊዜ፥ ደመናው የእግዚአብሔርን ቤት ሞላው።”
o   መ.እዝራ 3፡10 “አናጢዎቹም የእግዚአብሔርን መቅደስ በመሠረቱ ጊዜ ካህናቱ ልብሳቸውን ለብሰው መለከቱን ይዘው፥ የአሳፍም ልጆች ሌዋውያን ጸናጽል ይዘው እንደ እስራኤል ንጉሥ እንደ ዳዊት ሥርዓት እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ዘንድ ቆሙ።”
ሐ. መቋሚያ
v  መቋሚያ ማለት መደገፊያ፣ መመርኮዣ ማለት ነው።
v  ምሳሌነቱ እግዚአብሔር ለአዳም ተስፋ አድርጎ የሰጠው የመስቀል ምሳሌ ነው። በመሆኑም ቅዱስ ያሬድና አባ እንጦንስ በማኅሌትና በጸሎት ወይም በሰዓት ጊዜ መቋሚያ እንዲያዝ አድርገዋል። በመሆኑም ቅዱስ እንጦንስ በጸሎት ጊዜ፤ ቅዱስ ያሬድ በማኅሌት ጊዜ መቋሚያን ተጠቅመዋል።
v  ሙሴ ባህረ ኤርትራን የከፈለበት በትረ መስቀልን በትከሻው ይዞ (ንሴብሆ ለእግዚአብሔር ስቡሃ ዘተሰብሃ) በማለት ያመሰገነውን ምስጋና የሚያሳስብ እንደሆነ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ያስተምራሉ።

No comments:

Post a Comment