13

.

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው::" የማቴዎስ ወንጌል 7: 4

"እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅናወተት ግዙ።" ትንቢተ ኢሳይያስ 55 : 1

Thursday, September 8, 2011

ክርስቲያናዊ ሥነ - ምግባር

የመንፈሳዊ ትምህርት ማሰሪያው የምስጢራት መወሰኛው/የመጀመሪያው/ በጥሩ ሥነ ምግባር እራስንና ሌሎችን ቀርጾ መገኘት መሆኑን እምነታችንንና ምግባራችንን በጥሩ ሥራ መግለጽ አለብን ያዕ.2፡14
አንድ ሰው ጥሩ ወይም መጥፎ ሥነ ምግባር አለው ስንል ሥነ ምግባሩን በሁለት ነገሮች ማየት አለብን፡፡
1.  ውጫዊ ሥነ ምግባር
2.  ውስጣዊ ሥነ ምግባር
ነፍስና ስጋ እንደማይለያይ ሁሉ ሃይማኖትና ምግባር አይለያዩም፡፡ ያዕ. 2፡14

የሥነ ምግባር ሕግጋት

ሕግ ማለት ለማድረግ የሚያዝ ከማድረግ የሚከለክል ውሳኔና ሥርዓት ነው፡፡ ማንኛውም ክርስቲያን በእግዚአብሔር ዘንድ ቅድስናን አግኝቶ ይኖር ዘንድ የሥነ ምግባር ሕጎች የትኞቹ እንደሆኑ ግብራቸውና ስልታቸውን ለይቶ ማወቅ ይኖርበታል፡፡

                                  የሥነ ምግባር ሕጎች


- ክርስቲያን ሁሉ መንፈሳዊነትም ሥጋዊነትም ያለው ምድራዊ ፍጡር እንደመሆኑ እርሱንም የሚመለከተው ሕግ ሁለት ጠባይ ወይም በሁለት ክፍል ያለው ሕግ ይሆናል፡፡ ይኸውም
            - መንፈሳዊ/አምላካዊ/ ሕግ
            - ሥጋዊ ሕግ በመባል የሚታወቅ ነው፡፡

መንፈሳዊ /አምላካዊ/ ሕግ ለሰው ሁሉ ከልዑል እግዚአብሔር በተፈጥሮና በጽሑፍ የተሰጠው ሲሆን ዘለዓለማዊ በመሆኑ እና ከእግዚአብሔር በመገኘቱ መንፈሳዊ ሕግ ተብሏል፡፡

ኢ - ጽሑፋዊ ሕግ በሁለት ይከፈላል፡፡
-    ሕገ ልቡና
-    ሕገ ሕሊና

ሕገ ልቡና፡- ይህ ሕግ በሰው ልቦና አንድ ጊዜ ከተጻፈ በኋላ ሳያረጅ ሳያፈጅ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ ያለ የኖረ የተፈጥሮ ሕግ ነበር፡፡ ሮሜ. 1፡14 ሕገ ልቡና የተባለው ሰው በተባለው ሁሉ በልቦናው ተጽፎ የሚገኝ እያንዳንዱ ሰው ማንም ሳያስተምረው ክፉውንና ደጉን ለይቶ ሳይነግሩት እንዲያውቅ የሚያደርገው ስለሆነ ነው፡፡

 ሕገ ልቦና ሕገ ተፈጥሮአዊ ወይም ሕገ ጠባያዊ እየተባለ የሚጠራ ሲሆን ሰው የሚመሰገነው በተፈጥሮ የተሰጠውን ይህንን ሕግ በንጽሕና በመያዙና በማዳበሩ ነው፡፡
የሰው ልጅ ክፉውን ለይቶ ያውቅበት ዘንድ የተሰጠው ሕግ ነው፡፡

ሕገ ሕሊና፡- ሕገ ሕሊና ወይም ሕሊናዊ ሕግ የእግዚአብሔር ድምጽ ለነፍስ የሚተላለፍበት በማናቸውም ክርስቲያን ሁሉ አድሮ የሚሠራ ሥነ ምግባራዊ ሕግን እንድንፈጽም የሚያነቃ አርፈን እንቀመጣለን ብንል እረፍት የሚነሳ ነው፡፡ አንድ ሰው ነፍስ አጥፍቶ እንደሆነ የሚከስ አልምቶም ከሆነ እንዲደሰት የሚያደርግ የሕሊና ዳኛ ነው፡፡

- ይኽ ሕግ አንድ ግብር እንዲፈጸም ወይም እንዳይፈጸም ማስጠንቀቂያና ምርጫን የሚያደርግ ሲሆን ከተደረግ በኋላ መጥፎ እንደሆነ መጸጸትን ሐዘንን ያመጣል መልካም ከሆነ ደግሞ ደስታን መጽናናትን ይሰጠናል፡፡ ማንኛውም የክርስትና ተከታይ የሆነ በስሙ የተጠራ ግን ሁሉ ፍለጋውን የሚከተሉ ሁሉ የራሱን ሕሊና ምርጫ ማክበር የእግዚአብሔርን ድምጽ መስማት ግዴታው ይሆናል፡፡ እየተጠራጠረ እያመነታም የሚሠራ ሰው ሁሉ ከሕሊናው ግምት ውጭ ይሠራል ማለት ነው፡፡ ይህም እርሱን መበደል ነው፡፡ ሮሜ. 14፡23 ስለዚህ ሳይሠራ ያመልጣል ከሁሉ አስቀድሞ በምንሠራው ሥራ እንደ ሃይማኖታችን ጽናት መጠራጠር አይገባንም፡፡ ይህንን ሁሉ ለማስወገድ ከሁሉ በፊት

1.  ጸሎት መጸለይ ማለት የሚሠሩትን ሁሉ ‹‹ ወይኩን ፈቃድከ ›› ብሎ መጠየቅ
2.  ዓለማዊ ማንኛውም ከእግዚአብሔር ፍቅር የተነሳ የእሱን አምልኮትና ፍቅር መግለጫ መሆን ይኖርበታል፡፡ አምላክ ሰውን አፍቅሮ አንድያ ልጁን ለእኛ አሳልፎ ቤዛ እንደሰጠ ሁሉ ዮሐ. 3፡16
3.  ስለ እግዚአብሔር ክብር ተብሎ የሚሰራ መሆን ይኖርበታል 1ቆሮ 10፡31
4.  ስለ ባልንጀራው ፍቅር መሆን ይገባዋል፡፡

አሥርቱ ትዕዛዛት

      ከእግዚአብሔር አምላክ በቀጥታ በሙሴ አማካኝነት ለእስራኤላውያን የተሰጠ ሕግ ነው፡፡ የተሰጡትም እስራኤላውያን ከግብጽ ከወጡ በ3ኛው ወር ፋሲካን ካከበሩ በ3ኛው ቀን በደብረ ሲና ሰፍረው ሳለ ነበር፡፡ ዘፀ. 19፡1-4 በዘዳ. 34፡28 ዘዳ. 4፡13 ላይ አሥሩ ትዕዛዛት አሥር መሆናቸውን እንረዳለን፡፡
በዝርዝር ተጽፈው የሚገኙት ግን በዘዳ. 20፡ 3 እና17 እና ዘዳ. 5፡5-21 ላይ ነው፡፡ አሥርቱ ቃላትና ስድስቱ ቃላተ ወንጌል ለእስራኤል ዘስጋና ለእስራኤል ዘነፍስ የተዘጋጁ ስለሆነ ሁላችንንም ይመለከታል፡፡ እነርሱም፡-

1.  ‹‹ እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ፡፡ ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ የማናቸውንም ምሳሌ የተቀረጸውን ምስል ለአንተ አታድርግ፤ አትስገድላቸው፤ አታምልካቸው ›› ዘፀ. 20፡2-6
2.  ‹‹ የእግዚአብሔር የአምላክን ስም በከንቱ አትጥራ፡፡ ›› ዘፀ. 20፡7
3.  ‹‹ የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ /አክብረውም/ ›› ዘፀ. 20፡ 8
4.  ‹‹ አባትህንና እናትህን አክብር ›› ዘዳ. 20፡12
5.  ‹‹ አትግደል ›› ዘፀ. 20፡13
6.  ‹‹ አታመንዝር ›› ዘፀ. 20፡14
7.  ‹‹ አትስረቅ ›› ዘፀ. 20፡15
8.  ‹‹ በሐሰት አትመስክር ›› ዘፀ. 20፡16
9.  ‹‹ አትመኝ ›› ዘፀ. 20፡17
10.  ‹‹ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ ›› ዘሌ. 19፡18


-    አሥርቱ ሕግጋት የብሉይ ኪዳን መሠረቶች ናቸው፡፡ የእግዚአብሔርን ሕግ ብትጠብቁ ብትፈጽሙትም ሕዝቤ ትሆናላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ ብሎ ቃልኪዳን ገባ፡፡ ሕዝቡም በአንድ አፍ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ‹‹እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን እንታዘዛለን›› ብለው ቃል ኪዳን ገቡ፡፡ ዘፀ. 19፡8፤ 24፡1-8 ቅዱስ ጳውሎስም እንደነገረን ይህ ፊተኛው ኪዳን ያለ ደም አልተመረቀምና ዕብ. 18፡ 22 ሙሴ ኪዳኑን ለማጽናት የደም መርጨትን ሥርዓት እንዳደረገ በሐዲስ ኪዳንም ቢሆን ሥነ ሥርዐቱ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ያላቸው ሕግጋት ናቸው፡፡ ማቴ 5፡17፣ 19፡15-22 ፣ዮሐ1፡12 እግዚአብሔር ሕዝቦቹና ልጆቹ ሊያረገን ይህን ታላቅ ተስፋ በመስጠት ቃል ከገባልን እኛ ደግሞ ትዕዛዙን ለመጠበቅ ምን ያህል ቃል ገብተንለታል? ጌታችን ብትወዱኝስ ትዕዛዜን ጠብቁ ዮሐ 14፡15 እንዲሁም ከሆነ እንደ እስራኤላውያን እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን እንታዘዛለን ብለን ከሁሉ በፊት ለእግዚአብሔር ቃል መግባት አለብን፡፡ ክርስትናውን ስንጀምር የመጀመርያ ሥራችን መሆን ያለበት ይህ ነው፡፡


                  የዐሥርቱ ትዕዛዛት ዓላማ

ዐሥርቱ ትዕዛዛት የተሰጡት በሚከተሉት ዓላማዎች ነው፡፡ ይኸውም፡-

1.  ከግብጽ ምድር ስላወጣቸው ውለታውን እንዲያስቡ
2.  ወደ ፊት በአረማዊያን መካከል ሲመላለሱ ከኃጢአት እንዲቆጠቡ
3.  መንፈሳዊ አካሄዳቸው ምን ምን አቅጣጫ መከተል እንዳለበት ለማሳየት ነው፡፡

የዐሥርቱ ትዕዛዛት አከፋፈል

የክርስቲያን ሕግ የፍቅር ሕግ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሌላውን የሚወድ ሕግን ፈጽሞበታል ካለ በኋላ ከዐሥርቱ ትዕዛዛት የተወሰኑትን በመጥቀስ ፍቅር የሕግ  ሁሉ ፍጻሜ መሆኑን በግልጽ ይነግራል፡፡ ሮሜ 13፡8-10 ታዲያ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረ ፍቅር በሁለት ይከፈላል፡፡ ማቴ 22፡34-41

ፍቅረ እግዚአብሔር       2 ፍቅረ ቢጽ

1ፍቅረ እግዚአብሔር ከአንደኛ ትዕዛዝ እስከ ሦስተኛው ያሉት ሲሆኑ እግዚአብሔርን የሚመለከቱ ናቸው፡፡

2ፍቅረ ቢጽ ከአራተኛ ትዕዛዝ እስከ አሥረኛ ትዕዛዝ ያሉት ሲሆኑ በለእንጀራን የሚመለከቱ ናቸው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በአዎንታዊና በአሉታ ከመነገራቸው አንጻር በሁለት ይከፈላሉ ይኸውም፡-
      1. ሕግ በአሉታ የተነገሩ /አታድርግ/
      2. ትዕዛዝ በአዎንታ የተነገሩ /አድርግ/

ከዚህም ሌላ ከአፈጻጸማቸው አንጻር ሲታዩ በሦስት ይከፈላሉ፡፡

1.  በሐልዮ የሚፈጸሙ 1፣3፣4 እና 9 በሐሳብ
2.  በነቢብ የሚፈጸሙ 2፣ 8 በመናገር
3.  በገቢር የሚፈጸሙ 5፣6፣7 እና 10 በሥራ ናቸው፡፡


ምንጭ ፡- ሕግጋተ እግዚአብሔር መጽሐፈ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ 3ኛ የተወሰደ እንዲሁም የ/መ/ገ/ጽ/ቅ/ጊ/ቤ/ክ/ሰ/ት/ቤት

No comments:

Post a Comment