እመቤቴ የተመረጥሽ ድንግል ማርያም ሆይ በዕብራይስጥ ማሪሃም የተባልሽ አምላክ ካንቺ ጋራ በመሰደዱ በግብፅ መከራሽ እማልድሻለሁ፡፡ መንገድ በመሄድ የድካምሽ አሳብ በልጅሽ ፊት ይቁም ስለ ኃጢአቴ መማለጃ ይሆን ዘንድ፡፡
በምድረ ግብፅ ያገኘሽ የረኃብና የጽምዕ ሐሳብ በበኩር ልጅሽ ፊት ይቁም ስለ ኃጢአቴ ማቃለያ ይሆን ዘንድ፡፡ ካይንሽ የፈሰሰው የዕንባ ጎርፍ በፊትሽ የተንጠባጠበው በልጅሽ በወዳጀሽ ፊትም የወረደው፡፡ አሁንም ደግሞ በልጅሽ በወዳጅሽ ፊት ይቁም ስለ ኃጢአቴ ማዘከሪያ ይሆን ዘንድ፡፡
የሠራሁትን ኃጢአት ባስበው ልቡናዬ እጅግ ደነገጠብኝ፡፡ አእምሮ ሳለኝ አለል ዘለል እያልኩ በጽርዓት መኖሬን ባሰብሁት ጊዜ ልቡናዬ እጅግ ደነገጠ፡፡ የኃጢአቴን ብዛት በተቆጣጠርሁ ጊዜ ልቡናዬ እጅግ ደነገጠ አንድ ሰዓት ስንኳን ኃጢአት ለመስራት አላቋረጥኩም፡፡
በሰውና መላእክት ጉባኤ መካከል ራቁቴን መቆሜን አሰብሁ፡፡ በዓይነ ልቡናዬ እመለከት ዘንድ ወዲህና ወዲያ ተመላለስሁ፡፡ ምናልባት የሚረዳኝ ባገኝ፡፡ ከዚህ እጅግ የሚያስፈራው ከሠራሁት ኃጢአት ፍዳ የተነሣ ምናልባት የሚዋሰኝ ባገኝ ብዬ፡፡ ነገር ግን በማማለድ እኔን ለማዳን የምትቸይውን አንቺን አማላጅ አገኘሁ፡፡ ዘወትርም ከኔ እንዳትርቂ ዐወቅሁ፡፡
እንዲህ በፍቅር ያዝሁሽ በጣቶቼ አይደለም በሃይማኖት ያዝሁሽ በመዳሰስ አይደለም በእደ ሕሊና ያዝሁሽ በእደ ሥጋ አይደለም፡፡ እደ ሕሊናየን ግን የሰው ኃይለኝነት ሊያስተወው አይችልምና፡፡ የሰይፍ ስለትም ሊቆርጠው አይችልም፡፡
ልትደገፊኝ ያዝሁሽ ልትጥይኝ ግን አይደለም ወደ ላይ ከፍ ከፍ ልታደርጊኝ ያዝሁሽ ወደ ታች ልታወርጅኝ ግን አይደለም፡፡ ለዘለዓለሙ ያዝሁሽ ለዕድሜ ልክ ብቻ አይደለም፡፡ እናቴ ሆይ ነፍሴ ባንቺ ዘንድ ትክበር ስለቸርነትሽም እመቤቴ ነሽ፡፡ ስለ ፍቅርሽ የታመንሽ ስለ ልጅሽም የመድኃኒት ቀንድ ሆይ አስቢኝ እንደ ወደቅሁም እቀር ዘንድ አትርሺኝ፡፡
(በአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ - መጽሐፈ አርጋኖን)
No comments:
Post a Comment