13

.

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው::" የማቴዎስ ወንጌል 7: 4

"እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅናወተት ግዙ።" ትንቢተ ኢሳይያስ 55 : 1

Friday, October 14, 2011

የትምህርተ ሃይማኖት መቅድም

በመምህር ፍቅረማርያም ባዘዘው
የቦ/መ/ብ/ቅ/እግዚአብሔር አብ ቤ/ክ የመጽሐፍ መምህር
የትምህርተ ሃይማኖት መቅድም
በባለፈው ጽሑፋችን “ከእውቀት በፊት እምነት” እንደሚቀድም በጥቂቱ መሰረታዊውን መልእክት ለማስተላለፍ የተሞከረበት ነበር፡፡ ታዲያ ይህ ሃይማኖት ከእውቀት በፊት ዝም ብለን የምንቀበለው ለምንድን ነው የሚል ጥያቄ በእያንዳንዳችን አዕምሮ ውስጥ ያቃጭልብን ይሆናል ለዚህም እንደሚከተለው እንገልጻለን፡፡
í. እምነት ከአእምሮ (ከእውቀት) በላይ ነው፡፡
ምንም ያህል አዋቂዎች ብንሆን ከአእምሮ በላይ የሆነውን እግዚአብሔርን ልናውቀው አንችልም፡፡ አእምሮ ገደብ አለው፤ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው “ድንግል ሆይ የልጅሽን እራሱን በራሱ የሚሰውርበትን የባሕርይውን ጥልቀት፤ ምልዐት፤ ርቀት ሊመረምር ይወዳል ነገር ግን አልመረመረው ብሎ እንደ ባሕር ማዕበል ወዲያና ወዲህ ያማታዋል” ይላል፡፡ ይህ የሚገልጸው የሰውን ልጅ የእውቀት ገደብ ነው፡፡ እውቀታችን የተገደበ ነው፤ “ሰው እንዲህ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ ከመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ እመሰክራለሁ፡፡” ይላል፡፡ ሮሜ. 12፤3 ስለዚህ የሰው ልጅ የማይችለውን ነገር ሊያደርግ ቢፈልግ አይችልምና መቀበል ይኖርበታል ማለት ነው፡፡ በዚህ ዓለም ውስጥ ያለ ዕውቀት ደግሞ ምንም አይደለም፡፡ 1ኛ ቆሮ. 1፤20 “ጸሐፊ ማን ነው ጠቢብስ ማን ነው እግዚአብሔር የዚህን ዓለም ጥበብ ከንቱ (ስንፍና) አድርጎታል” ይላልና፡፡
î. እምነት ከስሜት በላይ ነው፡፡
ይህ ሲባል ስሜት ከሕዋሳት የምናረጋግጠው ነው፤ እግዚአብሔር ረቂቅ አምላክ (መንፈስ) ነው፤ ሥራዎቹ በአጠቃላይ መንፈሳዊ ናቸው እንጂ ቁስ አካል አይደሉም፡፡ ይህን መንፈሳዊ ሥራ በስሜት እንረዳዋለን እንኳን ብንል ከድካም ውጭ ሌላ  ፋይዳ አይኖረውም፡፡ ስለዚህም በስሜት የምንረዳው ሳይሆን የምንቀበለው ነው፡፡ ዮሐ.4፤24 “እስመ እግዚአብሔር መንፈስ ውእቱ፤ እግዚአብሔር መንፈስ ነውና፡፡” 1ኛ ቆሮ.3፤16
ï. ሃይማኖት በተስፋ የሚረዱት ነው፡፡
“ሃይማኖትሰ ጥይቅት ይእቲ ለዘይሴፍዋ፤ ሃይማኖት ተስፋ ለሚያደርጓት የተረዳች ናት” ዕብ. 11፤1 ስለዚህም ተስፋ የሌለው ሰው አያምንም፤ ካላመነ ደግሞ ተስፋ የለውም ማለት ነው፡፡ ሁልጊዜ በየደቂቃው የምንደግመውን ጸሎት ማለትም “አቡነ ዘበሰማያት” የሚለውን ጸሎት ብንመለከት “መንግሥትህ ትምጣ” ስንለው ዓይን ያላያትና ጆሮ ያልሰማትን መንግሥተ ሰማያትን ነው፡፡ ይህን የሚያደርገው ደግሞ ከማመን ጋር ተስፋ ሲኖረው ነው፡፡ ሃይማኖት የሌለው ሰው ግን ተስፋ አይኖረውም፡፡ ስለዚህ ይህን ዘለዓለማዊ መንግሥት ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያወርሰንን የምናረጋግጠው በሃይማኖት ብቻ ነው፡፡
የእግዚአብሔርን ቸርነት ረድኤትና ጸጋ እንዲሁም ጥበቃውን አምነን የምንጠብቀው በተስፋ ነው፡፡ ትውክልቱን በእግዚአብሔር ላይ ያደረገ ሰው ሁልጊዜ በተስፋ ይጠብቀዋል፡፡ እርሱ እግዚአብሔርም ይህንን ተስፋ (ተምኔት) ለሚጠባበቁት ሰዎች በእርግጥም የሚዘገይ አይደለም፡፡ ምን አልባት እንኳን ቢያዘገየው ሳያስብልን ርቶ ሳይሆን የለመነው ነገር ለእኛ ስለማይሆነን ብቻ ነው፤ ሰው እግዚአብሔርን ሲጠይቅ እኔ ያልኩት ይሁን ሳይሆን “አንተ ያልከው ይሁን” ብሎ መለመን አለበት፡፡ ቅዳሴ “ያረምም ከመ ዘኢይሰሚ ይጎነዲ ከመዘ ኢይሁል፤ እንደማይሰማ ዝም ይላል እንደማይሰጥ ይዘገያል” ይላል፡፡ ይሰጣል ነገር ግን ይዘገያል የሰዎቹ እምነት የሚረጋገጠው፤ ስለሰጠን ብቻ የምናምንበት ከሆነ እምነት አይደለም፡፡ እምነት ግን በእሳት ውስጥ ተፈትነው የሚያልፉበት የሕይወት መንገድ ነው፤ የነፍስ እረፍትም ይገኝበታል፡፡ ት.ኤር.6፤16 “በመንገድ ዳር ቁሙ የትኛው መንገድ መልካም እንደሆነ መርምሩ በዚያም ሂዱ በነፍሳችሁ እረፍትን ታገኛላችሁ” ይላልና፡፡ በእውነትና በሃይማኖት (በተስፋ) ለሚለምኑት ሰዎች ግን የዘገየ ቢመስል አይዘገይም፤ እርሱም አያስቀረውምና፡፡ በሕይወተ ሥጋ እያሉ ይቅርና ሙሴ በሕይወት ዘመኑ የተመኘውን ነገር ሳያይ ቢሚትም ጌታችን ግን ሙሴን ከመቃብር ውስጥ አስነስቶ በሕይወቱ ዘመን የጠየቀውን ጥያቄ እሙን ሲያደርግለት ይስተዋላል፡፡ (ዘጸ.33፤17፤ ማቴ.17፤3)
እግዚአብሔርን በተስፋ (በእምነት) ለሚጠባበቁት ሁሉ ከችግር የመቃብር ኑሮ ውስጥ ነገ እንደሚነሱ የተስፋ ትንሣኤ እንዳላቸው ሁሉም ሊያምነው ግድ ይላል፡፡
ይቆየን!

No comments:

Post a Comment