13

.

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው::" የማቴዎስ ወንጌል 7: 4

"እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅናወተት ግዙ።" ትንቢተ ኢሳይያስ 55 : 1

Thursday, March 6, 2014

"ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ፥ ሥራህ ታላቅና ድንቅ ነው" ቅ.ዮሐንስ ራእይ ም 15፡3-4


በሻሌ ንቡ ቅ/ሚካኤል ቅ/እስጢፋኖስ  ወአባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ቤተክርስቲያን


አሁን አገልግሎት እየሰጠ ያለው ቤተክርስቲያን











ከቤተመቅደሱ የተቆረጠው ማር ህዳር 12 ቀን 2006 ዓ.ም የቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ በዓል ሲከበር ለሕዝበ ክርስቲያኑ በታየበት ወቅት






ታላቁ ጻድቅ አቡነ ሠላማ ከሣቴ ብርሃን



ሕዳር 11 ቀን 2002 ዓ.ም የቅዱስ ሚካኤል ዋዜማ ወደ ቤተመቅደስ ገብቶ መንበሩ ላይ የሚገኘው የንብ መንጋ




ከቤተመቅደሱ የተቆረጠው የማር እንጀራ ለሕዝበ ክርስቲያኑ በታየበት ወቅት




ታሕሣሥ 9 ቀን 2004 ዓ.ም መጥቶ ወደ ግብር ቤት ገብቶ ሰፍሮ የሚገኘው የንብ መንጋ በከፊል






ታሕሣሥ 19 ቀን 2005 ዓ.ም መጥቶ ወደ ቤተመቅደሱ  ገብቶ 
በአጎበሩ

 ላይ 
ሰፍሮ የሚገኘው የንብ መንጋ በከፊል









ከቤተመቅደሱ የተቆረጠው የማር እንጀራ ለሕዝበ ክርስቲያኑ በታየበት  ወቅት



ከቤተመቅደሱ የተቆረጠው ማር ህዳር 12 ቀን 2006 ዓ.ም የቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ በዓል ሲከበር ለሕዝበ ክርስቲያኑ በታየበት ወቅት 



 ተዓምረኛው በሻሌ ንቡ ቅ/ሚካኤል ቤተክርስቲያን
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

“የእግዚአብሔርን ሥራ በምድር ያደረገውን ታምራት እንድታዩ ኑ” መዝ. 45፡8
በንብ መንጋ የተከበበው የበሻሌ (ንቡ) ቅ/ሚካኤል፣ ቅ/እስጢፋኖስ እና ወአባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ቤተክርስቲያን አመሰራረትና ገቢረ ተዓምራት አጭር መግለጫ

ቤተክርስቲያኑ ከመመስረቱ በፊት በቦታው ላይ ሲከናወኑ የነበሩ ልዩ ልዩ ታምራት፡-
  1. ለብዙ ዓመታት ከተለያየ ቦታ ተጣልተው የነበሩ ምዕመናን ቦታው ላይ እየመጡ እርቀ ሰላም ሲፈጽሙበት ኖረዋል፤
  2.  ቤተክርስቲያኑ ከተተከለበት ቦታ ትልቅ የጽድ ዛፍ ላይ የሚወጣው ሙጫ እንደ እጣን ጢስ ሽታ ለብዙ ዓመታት አካባቢውን መዓዛው (ሽታው) ያውድ ነበር፡፡
  3. በዚሁ ቦታ ላይ  ሌሊት ሌሊት  የመላዕክት ዝማሬ (ጣዕመ ዜማ) የከበሮ ድምጽ ይሰማ እንደነበረ በዕድሜ የገፉ የአካባቢው አዛውንቶች ተናግረዋል፡፡
  4. በአካባቢው ከሚኖሩ ምዕመናን መካከል በመልካም ስራቸው የታወቁና ከ90 ዓመት በላይ ዕድሜ የነበራቸው እናት የቅዱስ ሚካኤል ታቦት (ጽላት) እንደሚተከል በተደጋጋሚ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ይናገሩ ነበር፡፡
  5.  ቀደም ሲል በእነ አብርሃ ወአጽብሃ ዘመነ መንግሥት አካባቢ ጀምሮ ከተለያየ አካባቢ የሞቱ አባቶች አስከሬናቸው እየመጣ ሥርዓተ ቀብር ሲፈጸምበት የቆየ እና በተለያየ ጊዜ የቀስተ ደመና ብርሃን በመቃብሩ ላይ ይታይ እንደነበር በአካባቢው የሚኖሩ በዕድሜ የገፉ አዛውንቶች በግልጽ መስክረዋል፡፡ ዛሬም መቃብሩ በግልጽ ይታያል፡፡ ይህ ሁሉ ታሪክ ሲከናወን ከቆየ በኋላ እግዚአብሔር የፈቀደው ጊዜ ሲደርስ በአካባቢው ከሚኖሩ በዕድሜ ከገፉ አዛውንቶች መካከል በአንድ አርሶ አደር ምዕመን አማካኝነት በእግዚአብሔር ፈቃድ በተደጋጋሚ  ራዕይ ተገልጾላቸው ያርሱበት የነበረውን ይዞታቸውን መሬት ለዚህ ታቦት መትከያ ቤተክርስቲያን እንዲሰራ መሬት በመስጠት አሁን በሚገኘው መቃኞ ቤተክርስቲያን ግንቦት 12 ቀን 2001 ዓ.ም ታቦቱ ሊገባ ችሏል፡፡
በቤተመቅደሱ ስለሚገኘው የንብ መንጋ አገባብ (አመጣጥ)
እግዚአብሔር አስቀድሞ ቦታውን ስለመረጠው፡-
1. ሕዳር 12 ቀን 2002 ዓ.ም የቅዱስ ሚካኤል በዓል ሲከበር በዋዜማው ሊቃውንቱ በአገልግሎት ላይ እንዳሉ ማለትም ሕዳር 11 ቀን 2002 ዓ.ም ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ገደማ ከምስራቅ አቅጣጫ የንብ መንጋ መጥቶ የቃል ኪዳኑ ታቦት በሚገኝበት በመንበሩ ውስጥ ገብቶ ካደረ በኋላ በነጋታው ታቦቱ ወጥቶ በሚከበረበት ጊዜ ንቡ ከመንበሩ ወጥቶ እንደ ደመና ረቦ ካሉት ምዕመናን ጋር ታቦቱን ዙሮ አክብሯል፡፡ በዕለቱም ይህን አስደናቂ ታምር ያዩና የተመለከቱ ምዕመናንም በከፍተኛ ድምጽ እግዚአብሔርን አመስግነዋል፡፡
2. ሕዳር 11 ቀን 2004 ዓ.ም የድንግል ማርያም ዕለት ካህናቱ ቅዳሴ ገብተው በሚቀድሱበት ጊዜ ቅዱስ ወንጌል ሲነበብ የንብ መንጋ መጥቶ ከቤተክርስቲያኑ ጉልላት ላይ የመስቀል ምልክት ሰርቶ ከሰፈረ በኋላ ከቀኑ 11፡00 ሰዓት ላይ ተነስቶ ቤተክርስቲያኑን ዙሮ ወደ ቤተልሔም ውስጥ ገብቶ እስከአሁን ድረስ ሰፍሮ ይገኛል፡፡
3. ታህሳስ 9 ቀን 2004 ዓ.ም ከቀኑ 9፡00 ሰዓት የንብ መንጋ መጥቶ ከቤተክርስቲያኑ ጎን ላይ ከሰፈረ በኋላ ከቀኑ 11፡30 ተነስቶ ቤተክርስቲያኑን ዙሮ ወደ ግብር ቤት ገብቶ እስከአሁን ድረስ ሰፍሮ ይገኛል፡፡
4. ታህሳስ 19 ቀን 2005 ዓ.ም የቅዱስ ገብርኤል ዕለት ካህናት ቅዳሴ ገብተው በሚቀድሱበት ጊዜ ቅዱስ ወንጌል ሲነበብ የንብ መንጋ መጥቶ በሴቶች መግቢያ በር ወደቤተክርስቲያኑ ከገባ በኋላ በቀጥታ ወደ ቤተመቅደሱ ውስጥ ገብቶ  በአጎበሩ ላይ ሰፍሯል፡፡ ይህ በቤተክርስቲያናችን ላይ ያለው የንብ መንጋ ማሩ ተቆርጦ በተለያየ ጊዜ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ተሰጥቶ ከአገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ በጉበት፣ በካንሰር፣ በኪንታሮት፣ በስኳር፣ በአስም፣ በጨጓራ፣ በኩላሊት፣ በደም ግፊት፣ በኤች አይ ቪ፣ ሽባዎች፣ አይነስውራን፣ አፈ ዲዳዎወች፣ መስማት የተሳናቸው፣ በጭንቀትና በልዩ ልዩ በሽታ የታመሙ ሰዎች ማሩን በልተው ጸበሉን ጠጥተው እምነቱን ተቀብተው ከበሽታቸው ተፈውሰው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ እንዲሁም ለብዙ ዓመታት ልጅ አጥተው የነበሩ ሰዎች (መካኖች) በአንድ ጊዜ ሁለት ልጆች መንታ እንዲሁም በአንድ ጊዜ ሶስት ልጆች መንታ ወልደው ታቅፈው መጥተው ጥምቀተ ክርስትናቸውን በዚሁ ቤተክርስቲያን እንዲፈፀም ማድረጋቸውና ሌሎች በዚህ አነስተኛ ጽሁፍ ሊገለፁ የማይችሉ በርካታ ገቢረ ታምራትና ፈውሶች እስከአሁኗ ሰዓት እየተደረጉ ናቸው፡፡  ክብርና ምስጋና ለአምላካችን ለልዑል እግዚአብሔር ይሁን አሜን፡፡
በእግዚአብሔር ፈቃድ በንቦቹ የተደረገው ታምራት በከፊል
1.  ሕዳር 12 ቀን 2002 ዓ.ም የቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ በዓል ታቦቱ ወጥቶ በሚከበርበት ጊዜ ከቤተመቅደሱ ያለው ንብ ወጥቶ ታቦቱን አክብሯል፡፡
2.  የ2003 ዓ.ም የስቅለት በዓል ሲከበር ንሴብሆ እየተባለ በሚዘምርበት ጊዜ ንቡ ወጥቶ ቤተክርስቲያኑን ዙሮ ገብቷል፡፡
3.  መጋቢት 12 ቀን 2004 ዓ.ም የቅዱስ ሚካኤል ወርሃዊ በዓል ቅዳሴ እየተቀደሰ ሳለ የቤተመቅደሱ ንብ ከመንበሩ ላይ የመስቀል ምልክት ሰርቶ (ሰፍሮ) ታይቷል፡፡
4.  ሕዳር 11 ቀን  2005 ዓ.ም ንቡ ለመጀመሪያ ጊዜ የገባበትን ዕለት ለማስታወስ ከቀኑ 4፡00 ሰዓት ላይ ንቡ ወጥቶ ቤተክርስቲያኑን ዙሮ ገብቷል፡፡
5.  የ2005 ዓ.ም ፀሎተ ሐሙስ የሕጽበተ እግር ጸሎት ሲከናወን የመቅደሱ ንብ ወጥቶ ፀበሉ ላይ ሰፍሮ (ረቦ) ታይቷል፡፡ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል፡፡ ለዘላለሙ አሜን፡፡

በቤተክርስቲያኑ ላይ የቃል ኪዳኑ ታቦት የሚነግስበት ቀናት
1. ሕዳር 12፣ ጥር 12፣ ግንቦት 12 ቅዳሴ ቤቱ፣ ሰኔ 12 ቀን የመልዓኩ የቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በየዓመቱ ታቦቱ ወጥቶ ይነግሳል፡፡
2. ጥቅምት 17 እና ጥር 1 ቀን የሰማዕቱ የቅዱስ እስጢፋኖስ ዓመታዊ በዓል ታቦቱ ወጥቶ ይነግሳል፡፡
3. ታሕሳስ 18 እና ሐምሌ 26 ቀን የጻድቁ አቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ዓመታዊ በዓል ታቦቱ ወጥቶ ይነግሳል፡፡ በእነዚህ የንግስ በዓላት ላይ ከቤተመቅደሱ የተቆረጠው ማር ለመድኃኒትነት ይሰጣል፡፡
የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት፣ የቅዱስ እስጢፋኖስ እና የጻድቁ አቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን አማላጅነት ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን ፡፡
በ2006 ዓ.ም በቤተክርስቲያኑ አውደ ምህረት ላይ የሚደረጉ መንፈሳዊ ጉባዔያት
1ኛ. የካቲት 30 ቀን 2006 ዓ.ም ከጠዋቱ 2፡00-5፡00 ሰዓት ጉባኤው ይካሄዳል፡፡
2ኛ. መጋቢት 28 ቀን 2006 ዓ.ም ከጠዋቱ 2፡00- 5፡00 ሰዓት ጉባኤው ይካሄዳል፡፡
3ኛ. ጳጉሜን 2 ቀን 2006 ዓ.ም ከጠዋቱ 2፡00- 5፡00 ሰዓት ጉባኤው ይካሄዳል፡፡ በእነዚህ ጉባኤ ላይ ለመድኃኒነትነት ማር ይሰጣል፣
አድራሻ፡- በአዲስ አበባ በቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 10 የሚገኝ ሲሆን ከተለያየ አቅጣጫ ተነስተው መገናኛ ከመገናኛ ሲኤም ሲ መሪ አያት የሚለውን ትራንስፖርት ይዘው አያት አደባባይ ይውረዱ፡፡ ከአያት አደባባይ ባጃጆች እና ታክሲዎች በሻሌ ንቡ ሚካኤል እና እስጢፋኖስ ካሉ እስከቤተክርስቲያኑ ያደርሰዎታል፡፡
ለበለጠ መረጃ፡- 0911- 56 37 14/0913-14 80 07 ንቡ ሚካኤል ብለው ይደውሉ
ወደፊት የቤተክርስቲያኑን ታሪክ በሰፊው እናቀርባለን፡







Saturday, October 19, 2013

ማኅሌተ ጽጌ


ማኅሌተ ጽጌ፤ ምንጩ ትርጉሙ መልእክቱ 

        ይህ ድርሰት በማንኛውም ጊዜ የሚጸለይ ቢሆንም በተለየ ሁኔታ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውለው ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 5 ቀን ድረስ ባለው የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የስደት ዘመን ነው፡፡ በዚህ ወቅት በየሳምንቱ እሑድ ሌሊት በሙሉ የእመቤታችንን ከልጇ ጋር ወደ ግብፅ መሰደድና መንከራተት እያሰቡ የሚደረስ ምሥጋናና ጸሎት ነው፡፡
             በሀገራችን የመስከረምና የጥቅምት ወራት የአበባ ወራት /ዘመነ ጽጌ/ ናቸው፡፡ ይህም ወቅት ተራሮች በአበባ የሚያጌጡበትና ለዓይን ማራኪ የሚሆኑበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህም ዘመን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «ስለ ልብስስ ስለምን ትጨነቃላችሁ) የሜዳ አበቦች እንዴት እንዲያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፡፡ አይደክሙም፣ አይፈትሉም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ ሰሎሞንስ ስንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም፡፡ እግዚአብሔርን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ እናንተ እምነት የጐደላችሁ እናንተንማ ይልቁን እንዴት እንግዲህ ምን እንበላለን ምንስ እንጠጣለን) ምንስ እንለብሳለን) ብላችሁ አትጨነቁ ...» /ማቴ.5÷28-33/ በማለት የተናገረውን ቃል በማሰብ መጨነቅ የሚገባን መንግሥተ ሰማያት ለመግባት እንጂ በዚህ ዓለም ስላለው ነገር እንዳልሆነ ተራሮችን በአበባ ያለበሰ አምላክ በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረንን እኛን ለኑሮ የሚያስፈልገንን ምግብና ልብስ እንደማይነሳን እያሰብን የምንዘክርበት ወቅት ነው፡፡
                እንዲሁም ክቡር ዳዊት «ተዘከር እግዚኦ ከመ መሬት ንሕነ ወሰብእሰ ከመ ሳዕር መዋዕሊሁ ወከመ ጽጌ ገዳም ከማሁ ይፈሪ፤ አቤቱ እኛ አፈር እንደሆን አስብ ሰውስ ዘመኑ እንደሣር ነው እንደ ዱር አበባ እንዲሁ ያብባል ነፋስ በነፈሰበት ጊዜ ያልፋልና» /መዝ.1ዐ2÷14-16/ በማለት እንደ ተናገረው የሰው ሕይወት በሣር ይመሰላል፡፡ ሣር አድጐ አብቦ ከዚያ በኋላ ይደርቅና በነፋስ አማካኝነት ያ የረገፈው ሣር እየተነሣ የነበረበት ቦታ ስንኳ እስከማይታወቅ ድረስ ይሆናል፡፡ ሰውም ከአደገ በኋላ በሕማም ፀሐይነት ይደርቅና በሞት ነፋስነት ይወሰዳል፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ መቃብር ሲወርድ የነበረበት ቦታ ይዘነጋል፡፡ ስለዚህ ዘመነ ጽጌ ሰው ዘመኑ እንደ አበባ በቶሎ የሚረግፍ መሆኑን በማሰብ ይህ ዘመን ሳያልፍ መልካም ሥራ ለመሥራት ትንሣኤ ኅሊና የሚነሣበት ጊዜ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ለዘመነ ጽጌ የሠራው ድጓም ይህንኑ የሰውን ዘመን አጭርነት የሕይወቱን ኢምንትነት በዚህ ሕላዌ የተፈጠረ ሰው በዚህ ዓለም ክፉ ሥራ መሥራት እንደሌለበት ሁልጊዜ በተዘክሮተ ሞት እንዲኖር የሚያስረዳ ነው፡፡
                     በዘመነ ጽጌ ቅዱስ ያሬድ ከደረሰው ድጓ በተጨማሪ ከላይ እንደተጠቀሰው በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሣ አባ ጽጌ ድንግል ከዚሁ ዘመን ጋር የተያያዘ ድርሰት ደርሷል፡፡ ይህ ድርሰት በግጥም መልክ የተደረሰ በአብዛኛው አምስት ስንኞች ያሉት ሲሆን ብዛቱም 15ዐ ያክል ነው፡፡ ይህም ድርሰት «ማኅሌተ ጽጌ» በመባል የሚታወቀው ነው፡፡ ፍሬ ከአበባ አበባም ከፍሬ እንደሚገኘው ሁሉ ማኅሌተ ጽጌም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምንና ልጇን መድኃኒታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን በአበባና በፍሬ እየመሰለ የሚያስረዳ ድርሰት ነው፡፡ እርሷን በአበባ ሲመስል ልጇን በፍሬ እርሷን በፍሬ ሲመስል ደግሞ ልጇን በአበባ እየመሰለ ይናገራል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ «ትወጽእ በትር እምሥርወ እሴይ ወየዓርግ ጽጌ እምጉንዱ፤ ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፤ ከሥሩም ቁጥቋጦ ያፈራል»  /ኢሳ.11÷1/ ብሎ ከእሴይ ዘር የምትገኘውን እመቤታችንን በበትር ከርሷ የሚገኘውን ክርስቶስን ደግሞ በጽጌ መስሎ ትንቢቱን ተናግሯል፡፡ አባ ጽጌ ድንግልም ድርሰቱን በዚሁ አንጻር በመቀመር እያንዳንዱን መልክዕ እመቤታችንንና ልጇን አስተባብሮ በጽጌና በፍሬ በመመሰል የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ በምሥጢር በታሪክ፣ በጸሎትና በመሳሰለው መልክ ድንቅ በሆነና በተዋበ ሁኔታ አዋሕዶ ደርሶታል፡፡
                     እመቤታችን ጣዕሟንና ፍቅሯን እንዲሁም ምስጋናዋን ሲናፍቁ የነበሩትን ቅዱስ ኤፍሬምንና አባ ሕርያቆስን ውዳሴዋንና ቅዳሴዋን እንደገለጸችላቸው ለፍቅሯ ሲሳሳ ለነበረው ለአባ ጽጌ ድንግል ደግሞ ይህንን ማኅሌተ ጽጌን እንዲደርስ አድርጋዋለች፡፡ ከላይ እንደተገለጸው ማኅሌተ ጽጌ በመልክዕ አደራረስ ሥርዓት የተደረሰ ሲሆን ይህንንም ለመመልከት እንዲያመች በሚከተሉት ክፍሎች ከፋፍሎ ማቅረብ ይቻላል፡፡
1. ጸሎት
            በዚህ አገባብ ጸሎት ስንል በተለየ ሁኔታ ጸሎትነቱ የጐላውን ለማየት እንጂ ድርሰቱ በሙሉ ጸሎት ነው፡፡ ሌሎቹንም እንዲሁ ታሪክ፣ ተግሳጽ፣ ምሥጢር ተብለው መከፈላቸው በበዛውና በጐላው ለመግለጽ ነው እንጂ ሁሉም በሁሉ አለ፡፡ በጸሎትነታቸው ጐልተው ከሚታዩት ውስጥ የተወሰኑትን እንመለከታለን፡፡

1.1.  አንብርኒ ማርያም ውስተ ልብኪ ከመ ሕልቀት፣
ወከመ ማዕተብ ፁርኒ በመዝራዕትኪ ልዕልት፣
በእንተ ርስሐትየሰ ኢትመንንኒ ንግሥት፣
እስመ ወሀብኩ ንብረትየ ለፍቅርኪ ሞት፣
ዘአሰገርዎሙ ለሰማዕት በጽጌሁ ሕይወት፡፡
              ጠቢቡ ሰሎሞን «የምእመናንንና የክርስቶስን ነገር በምሥጢር በተናገረበት በመኃልይ መጽሐፉ «እንደ ማኅተም በልብህ እንደ ማኅተም በክንድህ አኑረኝ» /መኃ.9÷6/ ይላል፡፡ ይኸውም የምእመናንንና የክርስቶስን አንድነት የሚገልጽ ነው፡፡ «አንብርኒ ማርያም ውስተ ልብኪ ከመ ሕልቀት፤ ወከመ ማዕተብ ፁርኒ በመዝራዕትኪ ልዕልት» ማለቱ እመቤታችንን እንደ ማኅተም በልብሽ አኑሪኝ በማለት በእናትነትሽ፣ በአማላጅነትሽ አትርሽኝ ካለ በኋላ «በእንተ ርስሐትየሰ ኢትመንኒ ንግሥት» ይላል፡፡ ይኸም ማለት አትርሽኝ በልብሽ አኑሪኝ ብዬ የምለምንሽ አንቺ እንዳትረሽኝ የሚያደርግ መልካም ሥራ ኖሮኝ አይደለም፡፡ ስለዚህ በሰውነቴ ክፋት ምክንያት በኃጢ አቴና በወራዳነቴ ምክንያት እኔን ከማሰብ ከልቡናሽ አታውጪኝ በማለት እመቤታችን በርኅሩኅ ልቧ «መሐር ወልድየ ወተዘከር ኪዳንየ» እያለች እንድታዘክረን የሚያሳስብ ጸሎት ነው፡፡

ሶበ አተቦ ለማይ በቅዳሴኪ እንዘ ይጼሊ፣
ረሰዮ ኅብስተ ጽጌ ሃይማኖት ሳሙኤል ዘሐቅለ ዋሊ፣
ምሕረተ ወፍትሐ ለተአምርኪ አኀሊ፣
ሥረዪ ኃጢአትየ ወእጸብየ አቅልሊ፣
እስመ ኩሎ ገቢረ ማርያም ትክሊ፡፡
            አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ ቅዳሴ ማርያምን እየደገሙ ውኃው በተአምራት ኅብስት ይሆንላቸው ነበር፡፡ ይህን ተአምር ከአደነቀ በኋላ «ማርያም ሆይ ሁሉን ማድረግ ትችያለሽና ኃጢአቴን አስተስርይልኝ» ይላል፡፡ ጌታችን «እውነት እላችኋለሁ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ ይህን ተራራ ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል፤ የሚሳናችሁም ነገር የለም» /ማቴ.17÷1/ በማለት ላመነ የሚሣነው ነገር እንደሌለ ተናግሯል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መልአኩ «ትጸንሻለሽ፣ ትወልጃለሽ ...» ብሎ ባበሠራት ጊዜ ይህ እንደምን ይሆንልኛል)  ብላ ስትጠይቅ «ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም» ሲላት በፍጹም እምነት ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ እንደቃልህ ይሁልኝ» በማለት የተቀበለች ናት፡፡ ይህንንም ቅድስት ኤልሳቤጥ መንፈስ ቅዱስን ተመልታ «ከጌታ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና የታመነች ብፅዕት ናት» /ሉቃ.1÷453 ብላ መስክራለች፡፡ ላመኑ ሁሉ የሚቻል ከሆነ እመቤታችን ግን ቅዱሳን ሁሉ የሚማጸኑትን አምላክ በሥጋ ወልዳ ያስገኘች ስለሆነች ለእርሷ የሚሳናት ነገር የለም፡፡ ስለዚህም ነው ላንቺ የሚሳንሽ ነገር የለምና ኃጢአቴን አስተስርዪልኝ፣ የከበደኝን ሁሉ አቅልይልኝ በማለት የለመነው፡፡

1.2. «ተአምርኪ ማርያም ተሰብከ በኦሪት፣
አመ ተሰነዓውኪ ጳጦስ ምስለ መለኮት፣
ዘርእየኪ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
ጸልልኒ በአዕፁቅኪ ሐመልማላዊት ዕፀት
ሦከ ኃጢአትየ ያውዒ ጽጌኪ እሳት፡፡
              «ማርያም ሆይ ነበልባል ከሐመልማል ተዋሕዶ ሙሴ በደብረ ኮሬብ ባየ ጊዜ ተአምርሽ በኦሪት ተሰበከ ተነገረ፡፡ ምሳሌሽ በሐመልማልና በእሳት አምሳል የታየ ማርያም ሆይ ጽጌ ልጅሽ ኃጢአቴን ያጠፋልኝ ዘንድ በጥላሽ ሥር አስጠጊኝ፡፡
               ሙሴ በምድያም በስደት ሆኖ የአማቱን የዮቶርን በጎች እየጠበቀ ሳለ በኮሬብ ተራራ ድንቅ ራእይ ታየው፡፡ ቁጥቋጦው በእሳት ሲነድ፡፡ ቁጥቋጦውም ሳይቃጠል አየ፡፡ ዘጸ.3÷3፡፡ ይህ የምሥጢር ተዋሕዶ ተምሳሌታዊ ራእይ ነበር፡፡ ሐመልማል የእመቤታችን ምሳሌ ሲሆን እሳቱ ደግሞ የመለኮት ምሳሌ ነው፡፡ የሐመልማሉ ርጥበት እሳቱን አለማጥፋቱ አምላክ ሰው ሲሆን ከመለኮቱ ክብር ዝቅ ያለማለቱ ምሳሌ ነው፡፡ እሳቱ ደግሞ ሐመልማሉን አለማቃጠሉ መለኮት ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ በተዋሐደ ጊዜ እንዳጸናትና እንዳደረገችው የሚያስረዳ ነው፡፡



             ደራሲው የእመቤታችን ክርስቶስን የማስገኘት ተአምርና የእርሷ የአምላክ እናት መሆን ከጥንት ጀምሮ ሲነገር የኖረ መሆኑን ካስታወሰ በኋላ ጸሎቱን «ጸልልኒ በአዕፁቅኪ ሐመልማላዊት ዕፀት ሦከ ኃጢአትየ ያውኢ ጽጌኪ እሳት» በማለት ያቀርባል፡፡ ይኸም ማለት «ያ ከሐመልማል ጋር ተዋሕዶ የታየው እሳት ጽጌሽ/ ልጅሽ ክርስቶስ/ ኃጢአቴን ያስተስርይልኝ ዘንድ በአንቺ ሐመልማልነት አስጠጊኝ ማለት ነው፡፡
               ዳዊት «በአንቺ የሚኖሩ ሁሉ ደስ ይላቸዋል» /መዝ.8÷ኮ7/ ብሎ እንደተናገረ በእመቤታችን እናትነትና አማላጅነት ጥላ ሥር የሚኖሩ ከልጇ ከክርስቶስ ሥርየተ  ኃጢአትን አግኝተው፣ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ተጐብኝተው ደስተኞች እንደሚሆኑ የተናገረው ትንቢት መፈጸሙን የሚያስረዳ ነው፡፡
2. ታሪክ
            በብሉይና በሐዲስ ኪዳን በተለያዩ ጊዜያት የተፈጸሙትን ድርጊቶች እያነሣ የሚሔድና በዚያውም ከታሪኩ ጋር አብሮ ጸሎትና ምሥጢር የያዘ ነው፡፡ ታሪክን ከሚያነሡት መካከል የሚከተሉትን ለአብነት መመልከት ይቻላል፡፡

2.1. «እስከ መነነቶ ሜልኮል ቅድመ ታቦተ ሕግ ከመ ዘፈነ፣
ንጉሠ እስራኤል ኪያኪ ዘጸገየ ስነ፣
ቅድመ ገጸ ሥዕልኪ ድንግል እዘፍን አነ
ዘይሜንን ተአምረኪ ወስብሐተኪ ቁርባነ፣
በአፈ መላእክት ወሰብእ ለይኩን ምኑነ፡፡
              ዳዊት ታቦተ ጽዮንን ከአቢዳራ ቤት ወደ ከተማው ባስመጣ ጊዜ በሙሉ ኃይሉ በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ሲዘምር ሜልኮል ተመልክታ በልብዋ ናቀችው፡፡ በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር ስላዘነበባት ልጅ ሳትወልድ ሞታለች፡፡ ሳሙ.6÷12-23፡፡ ደራሲውም ይህንን ታሪክ ካስታወሰ በኋላ «ቅድመ ገጸ ሥዕልኪ ድንግል እዘፍን አነ» ዳዊት «ለእመቤታችን ምሳሌ በሆነች በታቦተ ጽዮን ፊት እንደዘመረ እኔም በሥዕልሽ ፊት ላንቺ እዘምራለሁ»፤ «ዘይሜንን ተአምረኪ ወስብሐትኪ ቁርባነ በአፈ መላእክት ወሰብእ ለይኩን ምኑነ ሜልኮል በዳዊት ይቀርብ የነበረውን የታቦተ ጽዮንን ምስጋና በመናቋ እንደተረገመች ያንቺንም ተአምርሽንና ምስጋናሽን የሚንቅ ሁሉ በሰውና በመላእክት አፍ የተረገመ» ይሁን የሚል ነው፡፡ ሜልኮል የምሳሌዋን የታቦተ ጽዮንን ምሥጋና በመናቋ ከተረገመች ዛሬ የአማናዊቷን ታቦተ ጽዮን የእመቤታችንን ምሥጋና የሚንቁና ምሥጋና የሚያቀርቡትን የሚነቅፉ ሰዎች ምን ያኽል የተረገሙ ይሆኑ) እነዚህም «በድፍረትና በመናቅም በጻድቅ ላይ የሚናገሩ የሽንገላ ከንፈሮች ድዳ ይሁኑ» /መዝ.3ዐ ÷18/ ባለው ርግማን የተረገሙ ናቸው፡፡
2.2. እንበይነ አውሎጊስ ለዳንኤል አመ አርአዮ ስቅለተ፣
ከመ እገሪሁ ሰዓምኪ ወሰአልኪዮ ምሕረተ፣
ለተአምረ ሣህል ወልድኪ በእንተ ፍቅረ ሰብእ ዘሞተ፣
እንዘ ታዘክሪዮ ድንግል ይምሐረኒ ሊተ፣
ከናፍሪሁ ጽጌ አንኂ ስዕመተ፡፡
                  አውሎጊስ የሚባል የወፍጮ ድንጋይ እየጠረበ በመሸጥ ከዚያ በሚያገኘው ትንሽ ገቢ የሚተዳደር ደኃ ሰው ነበር፡፡ የሚያኘውንም ገንዘብ ለራሱ ትንሽ ለዕለት ኑሮው ካስቀረበ በኋላ ከርሱ የባሰባቸው ችግረኞችን እየረዳ ይኖር ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን በዚህ ግብር ሳለ አባ ዳንኤል የሚባል ባሕታዊ ያየዋል፡፡ ይህም ባሕታዊ አውሎጊስ በዚህ በድህነት ኑሮው እንደዚህ ድሆችን የሚረዳ ከሆነ ብዙ ገንዘብማ ቢያገኝ ምን ያክል ብዙ ሰው በረዳና መልካም ሥራ በሠራ ነበር» ብሎ እግዚአብሔር ለዚህ ሰው ብዙ ሀብት እንዲሰጠው ሱባኤ ያዘ፡፡ እግዚአብሔርም ሀብት ለዚህ ሰው /ለአውሎጊስ/ እንደማይጠቅመው ቢነግረውም አባ ዳንኤል በራሱ ሀሳብ ብቻ በመጓዝ ሀብቱን እንዲሰጠው አጥብቆ ስለተማፀነ እንደለመነው ሊያደርግለት ጸሎቱን ተቀበለ፡፡ ከዚህ በኋላ አውሎጊስ እንደልማዱ ድንጋይ ሲቆፍር በማሰሮ የተቀበረ ወርቅ አገኘ፡፡ ወርቁን ወስዶ ለንጉሡ ሰጠ፡፡ ንጉሡ ወርቅ ሲያገኝ ለራሱ ሳያደርግ ለንጉሥ የሚያመጣ ሰው ምን ያክል ታማኝ ቢሆን ነው ብሎ በዚያው በቤተ መንግሥቱ እንደራሴ አድርጎ ሾመው፡፡ አውሎጊስ ከተሾመ በኋላ አጃቢው ክብሩና ሀብቱ ሲበዛ ትሩፋት መጨመሩ ቀርቶ የቀደመ ሥራውንም ተወ፡፡ ለተበደለ የማይፈርድ ባለጉዳይ የሚያጉላላ ሆነ፡፡ በዚህ ጊዜ አባ ዳንኤል በሕልም እግዚአብሔር ሲቆጣውና ሲፈርድበት አየ፡፡ የማይገባ ልመና ለምኖ አውሎጊስን የቀደመ ትሩፋቱን እንዲተውና አሁን እንዲበድል ምክንያት ሆኗልና፡፡ አባ ዳንኤል በደሉ ገብቶት ከሥዕለ ማርያም ሥር ወድቆ ተማፅኖ እመቤታችን ልጇን ተማጽና ይቅር አስባለችው፡፡
                  አባ ዳንኤል በሕልም ያየው ነገር ስለከበደው ምናልባት አውሎጊስ ድሀ በድሎ ፍርድ አጓድሎ እንደሆነ ብሎ ሊያየው ቢሄድ እርሱንም የማያናግረው ሆነ፡፡ «ስለ ሰው ፍቅር የሞተ ልጅሽን ስለ አባ ዳንኤል ለምነሽ እንዳስማርሽው እኔንም ይቅር እንዲለኝ የጽጌ ልጅሽን ምሕረት ለምኝልኝ» በማለት እኛንም ባላወቅነው እየገባንና እየፈረድን ለሚመጣብን ቅጣት እንድታስምረን የሚያመለክት ነው፡፡
2.3. ኦ ረዳኢተ ድኩማን ዘይረድአኪ ኢትኃሥሢ፣
እመንበረ ላዕክኪ በምዕር ከመ ገፍታዕኪዮ ለወራሲ፣
ለገፍትዖ ፀርየ ድንግል ኃይለ ጽጌኪ ልበሲ፣
እንዘ ይሣለቅ ተአምረኪ ወሐሰተ ይሬሲ፣
መፍትውኑ ከመ ይህየው ከይሲ፡፡
                  የእመቤታችንን ተአምር አሰባስቦ የጻፈው ቅዱስ ደቅስዮስ ነው፡፡ እመቤታችንም ለዚህ ውለታው ሌላ ሰው የማይቀመጥበት ሰማያዊ ወንበር እና ሌላ ሰው የማይለብሰው አጽፍ ሰጥታዋለች፡፡ ከደቅስዮስ ዕረፍት በኋላ በእርሱ ቦታ የተሾመው ኤጲስቆጶስ በዚህ መንበር ለመቀመጥና አጽፉን ለመልበስ ሲል «ተው ይህ ለደቅስዮስ ብቻ የተሰጠ ነው» ቢሉት «እኔም እንደርሱ ኤጲስ ቆጶስ ነኝ ከእርሱ በምን አንሳለሁ)» በማለት ከወንበሩ ሲቀመጥ ወዲያው ሞቷል፡፡ ከላይ የተጻፈው ድርሰትም የሚያስረዳው ይህንን ነው፡፡ «ድኩማንን፣ ችግረኞችን የምትረጅ አንቺ ግን ረዳት የማትሽ ሆይ ከወዳጅሽ ከደቅስዮስ ወንበር ላይ በትዕቢትና በድፍረት የተቀመጠውን እንደተቀበልሽው የእኔንም ጠላቶች አጋንንትን እኩያት ኃጣውእን ለማስወገድ የጽጌሽን ማለት የልጅሽን ኃይል ይዘሽ ተነሽ» በማለት ለወዳጆቿ የምትቆም እመቤታችን ከጠላታችን እንድትታደገን ከታሪኩ አንጻር የቀረበ ጸሎት ነው፡፡
2.4. «በጌጋየ አዳም ወሔዋን ሱራፌል ዘአጸዋ፣
እንበለ ጽጌኪ መኑ ለአንቀጸ ገነት ዘአርኃዋ፣
ተፈሥሒ ድንግል መያጢተ አዳም እምጼዋ፣
በተአምርኪ ውስተ ምድረ ጽጌ አቲዋ
ከመ ጣዕዋ አንፈርዓፀት ጼዋ፡፡
                   አዳምና ሔዋን ባጠፉት ጥፋት ከገነት ተባረው ወደ ምድረ ፋይድ እንዲወርዱ ተፈርዶባቸው፡፡ ገነትን ሱራፌል መልአክ በምትገለባበጥ የእሳት ሰይፍ ይጠብቅ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ የተዘጋጀት ገነትን «እንበለ ጽጌኪ መኑ ለአንቀጸ ገነት ዘአርኃዋ፤ ያለ አንቺ ጽጌ ያለ ክርስቶስ በሱራፌል ስትጠበቅ የነበረችውን ገነት ሊከፍታት የቻለ ማንም ፍጥረት የለም» ዘፍ.3÷24፡፡ ካንቺ በተገኘ በክርስቶስ ወደ ቀደመ ክብሯና ቦታዋ የተመለሰች ሔዋን የእናቱን ጡት ጠብቶ ደስ እንደሚሰኝ እንደሚዘል እንቦሳ ደስ ተሰኘች፡፡ በአጠቃላይ ይህ የሚያስረዳው ያለ ክርስቶስ ሰው መሆንና በመስቀል ተሰቅሎ ቤዛ መሆን ማንም የገነትን በር ሊከፍት እንደማይችል ሲሆን የተዘጋውን የገነት በር የከፈተና የሰው ልጅ ያጣውን የልጅነት ጸጋ የመለሰ ክርስቶስ ደግሞ ከእመቤታችን የተገኘ መሆኑን ነው፡፡ እግዚአብሔር በኢሳይያስ አንደበት «መድኃኒቴም አይዘገይም፤ ከጽዮን ለክብር እንዲሆን መድኃኒትን ለእስራኤል ሰጥቻለሁ» ኢሳ.4÷ኮ1፡፡ እንዳለ የተዋረደው የሰው ልጅ የከበረበትና የዳነበት መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ የተገኘው ጽዮንን ከተባለች ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ነው፡፡ ይህንን መድኃኒት ለዓለሙ ያበረከተች እርሷ ናት፡፡
3. ተግሣጽ
            አባ ጽጌ ድንግል ይህንን ማኅሌተ ጽጌ ሲደርስ ለመስቀልና ለእመቤታችን ክብርና ስግደት አይገባም የሚሉ ደቂቀ እስጢፋ የሚባሉ መናፍቃን ተነሥተው ነበር፡፡ በዘመኑ የነበሩት ንጉሥ አፄ ዘርዐ ያዕቆብ ጉባኤ አሠርተው አከራክረው መናፍቃኑ ተረትተዋል፡፡ አባ ጽጌ ድንግልም በማኅሌተ ጽጌ ውስጥ እነዚህን የእመቤታችንን ተአምርና ክብር በመግለጽ መናፍቃንን በመገሰጽ በዚህ የተግሣጽ ድርሰታቸው አስተምረዋል፡፡ ለምሳሌ የተወሰኑትን እንመልከት
ከመ ይትፌሣሕ ጻድቅ ሶበ ይሬኢ በቀለ፣
በተበቅሎ ፀር ያርኢ ዘተአምርኪ ኃይለ፣
እፎ የሐዩ እመአምላክ እንተ ኪያከ ፀአለ፣
አኮኑ በፍትሐ ጽጌኪ ይሙት ተብህለ፣
ላዕለ አቡሁ ወእሙ ዘአሕስመ ቃለ፡፡
            ጻድቅ እግዚአብሔር ጠላቶቹን ሲበቀልለት ሲያይ ደስ ይለዋል፡፡ ይኸውም የአንቺን ተአምር ኃይል ያሳይ ዘንድ ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ያንቺን ተአምር የሚንቁና አንቺን የማያከብሩ ከሐድያን እንዴት በሕይወት ሊኖሩ ይገባቸዋል) ምክንያቱም «በልጅሽ በክርስቶስ ትእዛዝ «እናቱን ወይም አባቱን የሚሰድብ ፈጽሞ ይገደል» /ዘጸ.21÷17/ ተብሎ ተፈርዷልና፡፡ እናት አባቱን የሰደበ ሞት የሚገባው ከሆነ ክርስቶስ ሰማያዊውን አምላክ ወልዳ፣ ጡቷን አጥብታ፣ አዝላ፣ ተሰዳ ለዓለም ሕይወት ባበረከተችው በድንግል ማርያም ላይ ቃልን የተናገረማ እንዴት ያለ መከራ ይጠበቀው ይሆን)
4. ምሥጢር
              በዚህ ርዕሰ ጉዳይ የምናየው በብሉይና በሐዲስ የተነገረውን እያመሰጠረ፣ በብዙ አምሳልና ትንቢት ይነገር የነበረውን የአምላክን ከድንግል መወለድ፣ ትንቢቱን ከፍጻሜው ጋር እያዛመደ የሚናገረውን ነው፡፡ ከዚህም ውስጥ የተወሰኑትን እናያለን፡፡
4.1 «ዘብኪ ተባረኩ ወተቀደሱ አሕዛብ፣
 ትእምርተ ግዝረቱ ወዘርዑ ለአብርሃም አብ
ጽጌ ድንግልናኪ በግዕ ለቤዛ ይስሐቅ ውሁብ
ማርያም ፅፀ ሳቤቅ ወምሥራቅ ዘያዕቆብ
ወላዲቱ ለሥርግው/ለስግው/ ኮከብ»
              «አሕዛብ በአንቺ የተባረኩብሽ የአብርሃም የግዝረትና የዘሩ ምልክት አንቺ ነሽ፡፡ የድንግልናሽ ጽጌ በግዕ /በግ/ የይስሐቅ ቤዛ ሆኖ ተሰጠ፡፡ ማርያም ሆይ የተወደደውን ኮከብ የወለድሽ የያዕቆብ ምሥራቅ ነሽ፡፡»
                እግዚአብሔር አብርሃምን ከሀገሩና ከወገኑ ተለይቶ እርሱ ወደ ሚያሳየው ሀገር እንዲሄድ ካዘዘው በኋላ «በዘርዕከ ይትባረኩ ኩሎሙ አሕዛበ ምድር፤ በዘርህ የምድር አሕዛብ ይባረካሉ» /ዘፍ.12÷3/ ብሎ ቃል ኪዳን፣ ከአሕዛብ የሚለይበትና እግዚአብሔርን የሚያመልክ መሆኑ የሚታወቅበት ምልክት የሚሆን ግዝረትን ሰጠው፡፡ እንዲህ ሲል «በእኔና በአንተ መካከል ከአንተም በኋላ በዘርህ መካከል የምትጠብቁት ቃል ኪዳን ይህ ነው፡፡ ከእናንተ ወንድ ሁሉ ይገረዝ፡፡ በእኔና በአንተ ላለውም ቃል ኪዳን ምልክት ይሆናል» /ዘፍ.17÷9-11/፡፡ «አሕዛብ ሁሉ በአንተ ይባረካሉ» የሚለው ተስፋ በይስሐቅ አልተፈጸመም፡፡ ምክንያቱም በሰው ላይ የተጣለው ርግማን በይስሐቅ አልተወገደም በይስሐቅ የሚወገድ ቢሆን ኖሮ ይስሐቅ በተሰዋና ዓለምን ባዳነ ነበር፤ ክርስቶስም ወደዚህ ዓለም መምጣትና መሞት ባላስፈለገው ነበር፡፡ ስለዚህ ያ በዘርህ አህዛብ ይባረካሉ ተብሎ ለአብርሃም የተነገረው ተስፋ የተፈጸመው ክርስቶስ ከእመቤታችን በድንግልና ሲወለድ ሰው ሲሆን ነው፡፡ አምላክ ሊዋሐደው የሚችል ንጹሕ ሥጋና ነፍስ ይዛ ተገኝታ ለአብርሃም የተነገረውን ተስፋ እንድናገኝ አድርጋለችና፡፡
                  ለአብርሃም የተሰጠው ግዝረት የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ ያንጊዜ ያመነና ያላመነ የሚለው በግዝረት እንደነበረ ሁሉ ዛሬ ደግሞ በሕዝብና በአሕዛብ መካከል መለያው ምልክቱ ጥምቀት ነው፡፡ ከአሕዛብ የሚለየንን፣ የእግዚአብሔር ልጆችና የመንግሥቱ ወራሾች የሚያደርገንን ጥምቀት ተጠምቆ ተጠመቁ ያለንን ክርስቶስን ያገኘነው ከእመቤታችን በመወለዱ ነው፡፡ ለዚህ ነው
«ዘብኪ ተባረኩ ወተቀደሱ አሕዛብ
ትእምርተ ግዝረቱ ወዘርዓ ለአብርሃም አብ»
ያለው፡፡ ክርስቶስ ሰው የሆነው ከአብርሃም ዘር ነው፡፡ /ዕብጠ2.16/፡፡ ክርስቶስን ያስገኘች እመቤታችን የአብርሃም ዘር መሆኗን ወንጌላዊው ማቴዎስ በምዕራፍ አንድ በሚገባ አስረድቷል፡፡ ለአብርሃም የተሰጠው ተስፋ በእርሱ አማናዊ መሆኑንም ያጠይቃል፡፡
4.2 ጽጌ ድንግልናኪ በግዕ ለቤዛ ይስሐቅ ወሁብ
ማርያም ፅፀ ሳቤቅ ወምስራቅ ዘያዕቆብ
ወላዲቱ ለሥርግው ኮከብ
ይስሐቅ ለመሥዋዕት በቀረበ ጊዜ ከመሞት ያዳነው በግ ከዚህ መጣ ሳይባል በዕፀ ሳቤቅ ተይዞ ተገኝቷል፡፡ /ዘፍጠ22.13/፡፡ አብርሃም በጉን ሰውቶ የታሰረውን ይስሐቅን ፈትቶታል፡፡ ይስሐቅ የዓለሙ ምሳሌ ሲሆን በጉ የክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ በጉ የተያዘበት ዕፀ ሳቤቅ ደግሞ የእመቤታችን ምሳሌ ነው፡፡ በጉ በዕፀ ሳቤቅ ታስሮ እንደተገኘ ክርስቶስ ሰው የሆነው ከእመቤታችን ነው፡፡ ያ በግ ቤዛ ሆኖ ይስሐቅን ከሞት እንዳዳነው ሁሉ ክርስቶስም ስለ ዓለሙ ኃጢአት ሞቶ ለዓለሙ ቤዛ ሆኖአል፡፡ /ዮሐጠ3.16ጠ17/፡፡
ደራሲው የምሳሌውን መፈጸም ካስረዳ በኋላ «ወምሥራቅ ዘያዕቆብ» ይላል፡፡ በለዓም « ኮከብ ይሠርቅ እም ያዕቆብ ወየአትት ኃጢአተ እም እስራኤል፤ ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል ኃጢአተኝነትንም ከእስራኤል ያስወግዳል. . .» ብሎ ትንቢት የተናገረለትን ኮከብ የወለደች እርሷ መሆኗን የሚያስረዳ ነው፡፡ /ዘኁል.22.17 ፤ኢሳ.27.9፣59.20፤ ሮሜ.11.26/ ፡፡
4.3. «ሰመዩኪ ነቢያት እለርእዩ ኅቡአተ፣
ገነተ ጽጌ ዕፁተ ወኆኅተ ምሥራቅ ኅትምተ፣
እግዚአብሔር ወሀበ እንዘ ይብል ለቤተ ዳዊት ትእምርተ
ከመ ትፀንሲ ድንግል ወትወልዲ ሕይወተ
ኢሳይያስኒ ነገረ ክሡተ፡፡»
ትርጉም
           «ምሥጢርን ያዩ ነቢያት የተዘጋች የምሥራቅ በር የታተመች ገነት እያሉ ጠሩሽ፡፡ እግዚአብሔር ለዳዊት ቤት ድንግል በድንግልና ፀንሳ በድንግልና እንደምትወልድ በኢሳይያስ አማካኝነት በግልጽ ተናገረ፡፡»
         ከሩቅ ያለውንና ወደፊት የሚሆነውን በትንቢት መነጽር አቅርበው ያዩና ሥውሩ ምሥጢር የተገለጠላቸው ነቢያት «ገነተ ጽጌ ዕፁተ፤ ወልኅተ ምሥራቅ ኅትምተ፤ የታተመች ምንጭ የተዘጋች የምሥራቅ በር» እያሉ ጠሩሽ፡፡
          ሰሎሞን በመኃልዩ ፡ «እኅቴ ሙሸራ የተቆለፈች ገነት የተዘጋ ምንጭ ናት» ይላታል፡፡ በዚህም እመቤታችንን
ሀ/ በተቆለፈች ገነት
ለ/ በታተመች ምንጭ መስሏታል፡፡ ለምን?
ሀ/ የተቆለፈች ገነት
           በውስጥዋ አትክልት ሲኖር ነገር ግን ወደዚህች ቦታ የሚደርስ የለም ተቆልፎአልና፡፡ እመቤታችንም በንጽሕናና በድንግልና የታጠረች ስለሆነች ከእርስዋ የተወለደ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡
           የተክል ቦታ ዘር ሳይዘራባት ወይንም ተክል ሳይተከልባት እንዲሁም የሚንከባከበው ሳይኖር ሊያፈራ አይችልም፡፡ ይህች ገነት ምንም ነገር የማይደርስባት የተቆለፈች ስትሆን አትክልት ግን አለባት፡፡ እመቤታችንም በድንግልናና በንጽሕና የፀናች ስትሆን እንበለ ዘር ክርስቶስን አስገኝታለች፡፡
ለ/ የታተመች ምንጭ
            ምንጩ የታተመ ሲሆን ነገር ግን ውኃ ያለው ነው፡፡ እመቤታችንም በድንግልና የፀናች ስትሆን በእናትነት ክርስቶስን ወልዳለች፡፡ ሕዝቅኤልም «ወርኢኩ ኆኅተ በምሥራቅ፣ ኅቱም በዐቢይ መንክር ማኅተም አልቦ ዘቦኦ ዘእንበለ እግዚእ ኃያላን ቦአ ውስቴታ ወወጽኣ. . .፤ ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከተው በስተውጭ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር አመጣኝ ተዘግቶም ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም ሰውም አይገባበትም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል፡፡» አለኝ ይላል፡፡ /ሕዝቅ.44÷1- 3/፡፡
            የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ማለቱ ከሦስቱ አካል አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነስቶ ፍፁም ሰው ሆኖ ከእርስዋ ተፀንሶ ተወልዷልና ነው፡፡
             ይህ ሕዝቅኤል ያየው ሕንፃ በጥሬ ትርጉሙ ተወስዶ ቤተመቅደስ ነው እንዳይባል ቤተመቅደስ የሚሠራው ሕዝቡ አምልኮቱን ሊፈጽምበት ስለሆነ ከተሠራ በኋላ ለምን ይዘጋል) «በመካከላቸው አድር ዘንድ መቅደስ ይሥሩልኝ)» እንዲል፡፡/ዘጸ.25÷8፡፡/
            ይኸው ነቢይ ስለ ቤተመቅደስ በተናገረበት ቦታ «. . . ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን ፡፡ የደኅንነቱን መሥዋዕት ባቀረበ ጊዜ ወደ ምሥራቅ የሚመለከተው በር ይከፈትለት» ይላል፡፡ /ምዕ.46÷12/፡፡ ሰሎሞንና ሕዝቅኤል ስለእርስዋ የተምሳሌትነትና በትንቢት የተናገሩላት እርስዋ ድንግል ማርያም መሆንዋን ከዘከረ በኋላ ነቢያት ብቻ ሳይሆኑ ራሱ እግዚአብሔርም ምልክት መስጠቱን እንዲህ ሲል ይገልጻል፡፡ «እግዚአብሔር ወሀበ እንዘ ይብል ለቤተ ዳዊት ትእምርተ ከመ ትፀንሲ ድንግል ወትወልዲ ሕይወተ ኢሳይያስኒ ነገረ ክሡተ» ይላል፡፡
             ነቢዩ ኢሳይያስ «ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል. እነሆ ድንግል ትፀንሳለች.ወንድ ልጀም ትወልዳለች. ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች» /ኢሳ.7÷13-14/ በማለት እግዚአብሔር ሰውን ይቅር የማለቱና የሰጠውን ተስፋ የመፈጸሙ ምልክት በድንግልና መውለድ መሆኑን ተናገረ፡፡ መልአኩ ለእረኞች የጌታን መወለድ ብሥራት ከነገራቸው በኋላ ሄደው እንዲያገኙት ሲልካቸው «ይህም ምልክት ይሆንላችኋል» ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ» ነበር ያላቸው፡፡ /ሉቃ.2÷12/፡፡ ሰብአ ሰገልም «ሕፃኑን ከእናቱ  ከማርያም ጋር አዩት»/ማቴ 2÷11/፡፡ የድኅነታችን ምልክት የክርስቶስ በድንግልና ከእመቤታችን መወለድና መታየት ነው፡፡ እኛም እንደ ሰብአ ሰገል እውነተኛውን ክርስቶስን የምናገኘው ከእናቱ ጋር ነው፡፡ የእውነተኛ ሃይማኖት ምልክትም ናት፡፡ ክርስቶስን በእኛ ባሕርይ ከመውለዷም በላይ በስደቱ፣ በመዋዕለ ትምህርቱ በስቅለቱ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት ሲያድል ሁሉ አልተለየችም፡፡ ስለዚህ እኛም ረቂቅ ምሥጢርን ዐይተው በተለያየ ስያሜ እንዳመሰገኗት ነቢያት ልናመሰግናት ይገባል፡፡ ይኸውም የሚጠቅመው ራሳችንን ነው፡፡ እርስዋማ ምን ጊዜም የተመሰገነች ናት፡፡
4.4. ማዕረረ ትንቢት ማርያም ዘመነ ጽጌ እንግዳ 
ወዘመነ ፍሬ ጽጋብ ዘዓመተ ረኃብ ፍዳ
ብኪ ተአምረ ዘይቤ ኢዩኤል ነቢየ ኤልዳ
ያንጸፈጽፍ እምአድባሪሁ ወእም አውግሪሁ ለይሁዳ
ፀቃውዓ መዓር ጥዑም ወሃሊብ ፀዓዳ»
ትርጉም
           «በመከር ጊዜ አበባ በአበባ ጊዜ ደግሞ መከር አዝመራ ማጨድና መሰብሰብ የለም፡፡ ምክንያቱም ጊዜያቸው የተለያየ ስለሆነ፡፡ ለምሳሌ በመስከረም ወር የአበባ ጊዜ በመሆኑ አዝመራ መሰብሰብ የለም፡፡»
               «የትንቢት መከር መካተቻ የሆንሽ. እንደ ዘመነ ጽጌ የረሃብን ዘመን ያስወገድሽ ማርያም ሆይ የኤልዳ ነቢዩ ኢዩኤል /ከይሁዳ ተራሮች ጣፋጭ ማርና ፀዓዳ ወተት ይፈሳል ብሎ/ የተናገረው ትንቢት በአንቺ ታወቀ፤ ተፈጸመ፡፡» እመቤታችን ነቢያት የተናገሩት የትንቢት ዘር ተፈጸመባት፡፡ ማለትም ነቢያት የአምላክን ሰው የመሆን ነገር በተለያየ ሁኔታ ተናግረዋል፡፡ ጌታችን ነቢያት የተናገሩት ትንቢት መፈጸሙንና ይህንን ፍጻሜ ለማየት የታደሉት ሐዋርያት መሆናቸውን «አንዱ ይዘራል አንዱም ያጭዳል የሚለው ቃል እውነት ሆኖአል፡፡ እኔም እናንተ ያልደከማችሁበትን ታጭዱ ዘንድ ሰደድኳችሁ፡፡ ሌሎች ደከሙ እናንተም በድካማቸው ገባችሁ» በማለት ተናግሮአል፡፡/ዮሐ.4.37ጠ38/፡፡ ይህም ነቢያት የዘሩት ትንቢት በሐዋርያት ዘመን ለአጨዳ /ለፍሬ/ መድረሱን መናገሩ ነው፡፡ ስለሆነም «ማዕረረ ትንቢት፤ የትንቢት መካተቻ» ማርያም አላት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ፍሬ ክርስቶስን ያስገኘችና ከእሴይ ስር በትር ትወጣለች» እየተባለ የተነገረላት በመሆንዋ በአበባ ትመሰላለች፡፡፡ ስለዚህ እመቤታችን በመከር ወራት የምትገኝ አበባ ናት፡፡ በመከር ጊዜ የአበባ መገኘት ያልተለመደ ስለሆነ «ወዘመነ ጽጌ እንግዳ፤ እንግዳ የሆነ አበባ» አላት፡፡
ከዚህ በኋላ
«ብኪ ተአምረ ዘይቤ ነቢየ ኤልዳ፣
ያንጸፍጽፍ እም አድባሪሁ ወእም አውግሪሁ ለይሁዳ፣
ፀቃውዓ መዐር ጥዑም ወሀሊብ ፀዓዳ. . .»
በማለት ነቢዩ ኢዩኤል የተናገረውን ትንቢት አፈጻጸም ይናገራል፡፡
             ነቢዩ ኢዩኤል በዘመኑ ጽኑ ረኀብ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቡን በምሕረት እንደሚጎበኛቸውና ረሀቡ እንደሚጠፋ ይነግራቸው ነበር፡፡ «ብዙ መብል ትበላላችሁ.ትጠግቡማላችሁ ከዚህ በኋላ እንዲህ ይሆናል፤ ተራሮች በተሃ ጠጅ ያንጠበጥባሉ.ኮረብቶችም ወተትን ያፈስሳሉ.በይሁዳም ያሉት ፈፋዎች ሁሉ ውኃን ያጎርፋሉ»/ኢዩ.3÷18፤ 2÷26/፡፡
                «ብኪ ተአምረ ዘይቤ ኢዩኤል ነቢየ ኤልዳ፤ያንጸፍጽፍ እምአድባሪሁ ወእምአውግሪሁ ለይሁዳ ፀቃውዐ መዓር ወሀሊብ ፀዓዳ»፡፡ ይህም ማለት ነቢዩ ኢዩኤል ከይሁዳ ተራሮችና ኮረብቶች ጣፋጭ ሣርና ፀዓዳ ወተት ይፈሳል ይመነጫል ያለው በአንቺ ተፈጸመ ማለት ነው፡፡ ይህም እመቤታችን ክርስቶስን በወለደች ዕለት መሪሩ ጣፍጦ፣ ይቡሱ ለምልሞ ተገኝቷል፡፡ ይህ ለጊዜው ሲሆን ፍጻሜው ደግሞ ከእርሷ በነሣው ሥጋና ደም ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ፣ ከልጅነት ተራቁቶ፣ በረሀበ ነፍስና በጽምዓ ነፍስ ተይዞ የነበረውን የሰው ልጅ ከጎኑ ውኃን ለጥምቀት፤ ሥጋውንና ደሙን ምግበ ነፍስ አድርጎ የአምስት ሺህ አምስት መቶውን ዘመነ ረሀብ እንዳስወገደልን ያስረዳል፡፡
4.5. አርምሞትኪ ማርያም ኃለፈ እምአንክሮ
እስከ ንሬኢ ሕዝብኪ ለተአምርኪ ግብሮ
ገነትኪ ትፅጊ ሰላመ ወተፋቅሮ
ዕለ ያማስኑ ለዓፀደ ወይንነ ወፍሮ
 ቈናጽለ ንዑሳነ አፍጥኒ አሥግሮ
ትርጉም
              «እመቤታችን ማርያም ሆይ አርምሞሽ ከማድነቅ በላይ ሆነ. በማድነቅ የማይፈጸም ሆነ፡፡ የወይን ቦታችንን የሚያጠፉትን ጥቃቅኑን ቀበሮዎች ለማጥመድ /ለመያዝ/ ፍጠኚ፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ «ወትወዲዮ ለኩሉ ውስተ ልባ፤ ነገሩን ሁሉ በልቡናዋ ትጠብቀው ነበር፡፡»/ሉቃ 2÷51/ ሲል የእመቤታችንን አርምሞ እንዴት አስደናቂ እንደሆነ ገልጾአል፡፡ እመቤታችን ማንም ፍጡር ያልሰማውን ብሥራተ መልአክ የሰማች ለማንም ያልተደረገውን በድንግልና መፅነስና መውለድ የታደለች ማኅፀኗን ዓለም አድርጎ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ሲመሰገንባት የመላእክትን ቅዳሴ የሰማች ፈጣሪዋን የመገበች ከሰው ወገን ይቅርና ከሱራፌልና ከክሩቤል የሚበልጥ ክብርና ጸጋ የታደለች ስትሆን እርሷ ግን በዚህ ዓለም ስትኖር ሁሉንም ነገር በልቧ ውስጥ ከማኖር በስተቀር ይህንን አየሁ ይህንን ሰማሁ አላለችም፡፡ ሔዋን ዕፀ በለስን ወደ መብላትና ጸጋዋን ወደማጣት ያደረሳት ለእርስዋና ለአዳም ብቻ የተነገረውን ምሥጢር አውጥታ ለዲያብሎስ በመናገርዋ ነበር፡፡ እመቤታችን ግን ሁሉን በልቧ መዝገብ በመያዟ የተመሰገነች ሆነች፡፡
                ከክርስቶስም ሆነ ከእመቤታችን የተማርነው አርምሞን ነው፡፡ ክርስቶስን ጲላጦስና ሊቃነ ካህናቱ ከየት መጣህ) ማነህ) ትምህርትህስ ምንድነው) እያሉ ሲጠይቁት ዝመ ነው ያላቸው፡፡ ልሰቅልህ ሥልጣን አለኝ ሲለው ብቻ ነው መልስ የመለሰለት፡፡ ስለዚህ እኛም ከአባታችን ከክርስቶስና ከእናታችን ከድንግል ማርያም ያየነውን አብነት ማንሣት ይገባናል፡፡ /ዮሐ.19÷9፤ ማቴ.27÷14/፡፡
              ደራሲው የእመቤታችንን አርምሞ ካደነቀ በኋላ ጠቢቡ ሰሎሞን «አሥግሩ ለነ ቈናጽለ ንዑሳነ እለያማሰኑ ዓፀደ ወይንነ፤ የወይናችንን ቦታ የሚያጠፉትን ጥቃቅኑን ቀበሮዎች አጥምዳችሁ ያዙልን» /መኃ 2÷15/ እንዳለ የወይን ቦታ የተባለ የሕግ መጠበቂያ ልባችንን ሊያበላሹ ውር ውር የሚሉትን በቀበሮ የተመሰሉ መናፍቃንንና አጋንንትን እንድታስታግስልንና እንድታስወግድልን ይጸልያሉ፡፡
«ትመስል እምኪ ማርያም ዕለተ ሣልስተ ወራብዕተ ዘወለደት ጽጌ ወፀሐየ ዓለም ብርህተ
ካዕበ ትመስል ሳብእተ ዕለተ
እስመ ፈረየት ኪያኪ ተአምረ ግዕዛን ሰንበተ
ለዕለ በሰማይ ወምድር ዘኮንኪ ዕረፍተ፡፡»
                «ማርያም ሆይ እናትሽ/ሐና/ጽጌያት የተፈጠሩባትን ሦስተኛዋን ቀን ፀሐይ የተፈጠረችበትን አራተኛውን ቀን /ረቡዕ/ እንዲሁም እግዚአብሔር ሥራውን የፈጸመባትንና ያረፈባትን ሰባተኛዋን ቀን ትመስላለች፡፡ ምክንያቱም በሰማይና በምድር ላሉ ሁሉ ዕረፍት የሆንሻቸውን አንቺን ወልዳለችና፡፡»
             እግዚአብሔር በዕለተ ሠሉስ /በ3ኛው ቀን/ ዕጸዋትን ፈጠረ፡፡ /ዘፍ 1÷11-13/፡፡ ከእነዚህ ዕጸዋት ጽጌያት /አበቦች/ ከጽጌያት ደግሞ ፍሬ ይገኛል፡፡ ቅድስት ሐናን ጽጌያት በተፈጠሩበት በዕለተ ሠሉስ እመቤታችንን በጽጌ ጌታን ደግሞ ከጽጌው በተገኘ ፍሬ መስሏቸዋል፡፡ በአራተኛው ቀን /በዕለተ ረቡዕ ፀሐይንና ጨረቃን፣ከዋክብትን ፈጠረ፡፡ ሐናን በዕለቱ፣ እመቤታችንን በፀሐይ መሰላቸው፡፡ በሰባተኛው ቀን /በሰንበት/ ለሰው ሁሉ ዕረፍት እንዲሆን ለአብነት እግዚአብሔር አረፈ ተባለ፡፡ በዚህች ዕለት ሰው ሁሉ ከሥጋዊ ድካምና ውጣ ውረድ አርፎ ፈጣሪውን እያመሰገነ ይውላል፡፡ በእመቤታችንም ሰው ሁሉ ከመከራ ሥጋና ከመከራ ነፍስ አርፎ ተግባረ ነፍስ እየሠራ ፈጣሪውን «ወሠርዓ ሰንበተ ለሰብእ ዕረፍተ፤ ሰንበትን ለሰው ዕረፍት ሠራ» እያለ ሲያመሰግን ይውላል፡፡
4.6. «በላዕሌኪ ወበዮርዳኖስ ወበታቦር ሥልሰ ጊዜያተ
ዘአልቦ ተውሳከ ወአልቦ ሕፀተ
ለውሉደ ሰብእ ያርኢ ዘሥላሴሁ ገጻተ
ጽጌኪ ድንግል ተአምሪሁ ከሠተ
ወበጸዳሉ አብርሀ ጽልመተ»
ትርጉም
              በአንቺ ላይ በዮርዳኖስና በደብረ ታቦር ለሰው የአካሉን ሦስትነት ገለጸ አስረዳ፡፡ ድንግል ሆይ ጽጌሽ ተኣምራቱን ገለጸ በብርሃኑም ጨለማን አራቀ፡፡እግዚአብሔር አንድነቱንና ሦስትነቱን በግልጽ ያሳየው በእመቤታችን በዮርዳኖስና በደብረ ታቦር ነው፡፡
ሀ/ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ሲያበሥራት እንዲህ አላት «መንፈሰ እግዚአብሔር ቅዱስ ይመጽእ ላዕሌኪ ወኃይለ ልዑል ይጼልለኪ፡፡»
መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል የልዑል ኃይልም ይጸልለሻል»/ሉቃ 1÷35/፡፡ መንፈሰ እግዚአብሔር ብሎ መንፈስ ቅዱስን፣ የልዑል ኃይል ብሎ ወልድን ልዑል ብሎ አብን በማንሣት ሦስትነታቸውን አስረዳ፡፡ እመቤታችን ወልድ በተለየ አካሉ ሥጋ ሊዋሐድ፤ አብ ለአጽንዖ፤ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ የአምላክ እናት ለመሆን እንድትበቃ ለማድረግ ሦስቱም ተሳትፈዋል፡፡
ለ/ በዮርዳኖስ «ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ እነሆ ሰማያት ተከፈቱ. የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ፤ እነሆም ድምጽ ከሰማያት መጥቶ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው» አለ፡፡/ማቴ.3÷16-17/፡፡ ወልድ በተጠማቂነት. አብ በደመና ሆኖ ልጄ ነው እያለ ሲመሰክር መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በርግብ አምሳል ሲወርድ በአንድ ጊዜ ታይተዋል፡፡ አንድ ገጽ የሚሉ ሰባልዮሳውያን ላይጠገኑ ተሰበሩ፡፡ አንድ ራሱ በተለያየ ስም ተጠራ እንዳይሉ በአንድ ጊዜ ሦስቱም በየራሳቸው መገለጫ ወልድ በተዋሐደው ሥጋ አብ በደመና መንፈስ ቅዱስ በርግብ ተገለጡ፡፡
ሐ/ በደብረ ታቦርም አብ በደመና ሆኖ «በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት» በማለት ተናግሮአል፡፡ /ማቴ.1÷17-19/፡፡
4.7. «ዕፀ ደንጐላ ዘቆላ ወአኮ ዘደደክ
ዘጸገይኪ ጽጌ በማዕከለ አይሁድ አስዋክ
ተአምረ ድኂን ማርያም ዘልማድኪ ምሒክ
መሐክኒ ለምእመንኪ እምፃዕረ ኩነኔ ድሩክ
ተአምኖትየ ብኪ ኢይኩን በበክ፡፡»
                  እሾህ በሆኑ አይሁድ መካከል ያለሽ የደጋ ያይደለሸ የቆላ የሱፍ አበባ ማርያም በአንቺ መታመን በከንቱ እንዳይሆንብኝ እኔን ምእመንሽን /የታመንኩብሽን/ ከክፉ ኩነኔ አድኝኝ አንቺ ምሕረት ልማድሽ ነውና፡፡» በመኃልየ መጽሐፉ ሰሎሞን «ወከመ ጽጌ ደንጉላት በማዕከለ አሥዋክ ከማሁ አንቲኒ እንተ ኅቤየ በማዕከለ አዋልድ፤ በእሾህ መካከል እንዳለ የሱፍ አበባ እንዲሁ አንቺ ነሽ» ይላል፡፡ /መኃ.2÷2/፡፡
                 የቆላ ሱፍ ዙሪያውን እሾህ ቢከበውም ከማበብና ከማፍራት ወደኋላ አይልም፡፡ እመቤታችንም ብዙ ተአምር እያዩ በማያምኑና ሁልጊዜ ምልክትን በሚፈልጉ በክፉዎች አይሁድ መካከል መሆኗ በሃይማኖት ከማበብና ፍሬ ትሩፋት ከመሥራት አልከለከላትም፡፡ ደራሲው አባ ጽጌ ድንግልም የሰሎሞን የትንቢት ቃል እመቤታችን በአይሁድ መካከል ፍሬ ክርስቶስን በማስገኘቷ መፈፀሙን የሚያስረዳ ነው፡፡ ይህን ትንቢቱንና ፍጻሜውን ካስረዳ በኋላ «መሐክኒ ለምዕመንኪ እምፃዕረ ኩነኔ ድሩክ ተአምኖትየ ብኪ ኢይኩን በበክ» ይላል፡፡ ማለትም «በአንቺ እናትነትና ቃል ኪዳን የምታመን እኔን ከክፉ ፍርድ አድኝኝ፣ በአንቺ መታመኔና አንቺን ተስፋ ማድረጌ ለከንቱ አይደለምና በማለት ጸሎቱን ያቀርባል፡፡
                  እስከ አሁን በመጠኑ ለማየት እንደሞከርነው የማኅሌተ ጽጌ ድርሰት እጅግ በጣም በምሥጢርና በኃይለ ቃል የታጀበና ልዩ የሆነ ውበትና ጣዕም ያለው ነው፡፡ ይህንን ለመረዳት የሚቻለው እንዳለ ግእዙን ማንበብ፣ መረዳት ሲቻል ነው፡፡ እንኳን በግጥም መልክ የተደረሰ ድርሰት ይቅርና ተራ ንባብና ድርሰት እንኳ ሲተረጉሙት መንፈሱን መልቀቁ የማይቀር ነው፡፡ በተለይም ይህ የቅኔ ዓይነት አካሄድ ያለው ድርሰት ሲተረጎም እየተፍረከረከ ትክክለኛ መልእክቱን ለማስተላለፍ ፍዝ ይሆናል፡፡
                መልክዐ መልክዖችን መተርጎም ችግሩ ይህ ነው፡፡ አማርኛው ትርጉም መልእክቱን አልችል ይላል፡፡ ሆኖም የማኅሌተ ጽጌን ምንነት መጠነኛ ግንዛቤ ሊያስገኝ በሚችል መልኩ ለመግለጽ ተሞክሮአል፡፡፡ ይህም የእግዚአብሔርን ጸጋ ሁላችንም በመቅረብ እንድናውቅና ማኅሌተ ጽጌን በመጸለይና ማኅሌቱን በመቆም የእመቤታችንን በረከትና ረድኤት የልጇን የክርስቶስን ምሕረት ለማግኘት ያበቃናል፡፡ 
ለዚህም እመአምላክ ድንግል ማርያም በረድኤቷና በበረከቷ አትለየን፡፡ 
Source. http://www.daateklehaymanot.org