13

.

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው::" የማቴዎስ ወንጌል 7: 4

"እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅናወተት ግዙ።" ትንቢተ ኢሳይያስ 55 : 1

Saturday, September 3, 2011

ታላቁ ሊቅ አለቃ አያሌው ታምሩ


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ።

«ክቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅድመ እግዚአብሔር።»
«የቅዱሳኑ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው።» (መዝ፤ ፻፲፭፣ ፯።)
፩፤ ልደታቸውና ትምህርታቸው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀዋሚ ምስክር የሆኑት አለቃ አያሌው ታምሩ፤ ከአባታቸው ከአቶ ታምሩ የተመኝና ከእናታቸው ከወይዘሮ አሞኘሽ አምባዬ፤ በጎጃም ክፍለ ሀገር በብቸና አውራጃ በእነማይ ወረዳ በታላቁ ደብር ወገዳም በደብረ ድማኅ ቅዱስ ጊዮርጊስ ልዩ ስሙ ቤተ ንጉሥ በተባለ ቦታ መጋቢት ፳፫ ቀን ሺሕ ፱፻፲፭ ዓመተ ምሕረት በዕለተ ሆሣዕና ተወለዱ።
ያለፈውንም የወደፊቱንም የሚያውቅ ልዑል እግዚአብሔር ለበለጠ ክብርና አገልግሎት ያዘጋጃቸው ቢሆንም ዕድሜአቸው ለትምህርት ሳይደርስ ገና የሦስት ዓመት ተኩል ሕፃን ሳሉ በፈንጣጣ ሕመም ምክንያት የዐይናቸውን ብርሃን አጥተዋል። የስምንት ዓመት ዕድሜ ልጅ ሳሉ በዓለ ተክለ አልፋን ለማክበር ከአባታቸው ጋር ወደ ዲማ እንደ ሄዱ በዚያው ትምህርታቸውን ለመቀጠል ስላሰቡ ወደ ቤታቸው አልተመለሱም። ከዚህ ጊዜ ጀምሮም በቅርብ ቤተ ዘመድ እየተረዱ ለአንድ ዓመት ያህል ሲማሩ ከቈዩ በኋላ አባታቸው ስላረፉ ኑሮአቸው በትምህርት ቤት ብቻ ስለ ተወሰነ ከቤተ ሰብእ ጋር የነበራቸው ግንኙነት እየቀነሰ መጣ። ይህም ሁኔታ የሚፈልጉትን ትምህርት በአንድ ልብ ለመቀጠል ግድ ብሎአቸዋል።
ክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ ምንም እንኳ ሥጋዊ የዐይን ብርሃናቸውን ቢያጡም ልበ ብርሃን በመሆናቸውና ትምህርትን ለመቀበል ፈጣን አእምሮን የታደሉ በመሆናቸው ካሰቡበት ለመድረስ አላገዳቸውም። በዚሁ መሠረት በ፲፭ ዓመት ዕድሜአቸው የቅኔ መምህር ለመሆን በቅተዋል። ስለ ዐይናቸው ብርሃንና ስለ ትምህርታቸው፤ «ምልጃ ዕርቅና ሰላም፤» በተባለው መጽሐፋቸው ገጽ ፬ ላይ እንዲህ ሲሉ ገለጸዋል። «ይህ ሁሉ የተገኘው ገና በልጅነት ዕድሜዬ፤ በቅዱስ ሐዋርያ ያዕቆብ እንደ ተነገረው የምመራበት፣ የምኖረበት በወሰድከው በዐይኔ ፈንታ ዕውቀት ስጠኝ ብዬ የለመንኩት አምላኬ፤ «ለምኑ ይሰጣችኋል፤ ሹ ታገኛላችሁ፤ በር ምቱ ይከፈትላችኋል፤ ለሚወደኝ እኔ ራሴን እገልጥለታለሁ፤» ሲል በሰጠው ተስፋና በለገሰኝ የአእምሮ ምጽዋት መሆኑን ስለምረዳ ነው፤» ብለዋል።
ታላቁ ሊቅ አለቃ አያሌው ታምሩ በተወለዱበት አካባቢ ባሳለፉአቸው ዓመታት የቀሰሙአቸው ዋና ዋና የቤተ ክርስቲያን ትምህርቶችና ያስተማሩአቸው መምህራን እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል።
ሀ፤ መሪጌታ ከበበው፣ መሪጌታ እውነቴ፣ መሪጌታ ክንፉና መሪጌታ አልማው ከተባሉት መምህራን ጸዋትወ ዜማን ከጣዕመ ዝማሬው ጋር፤
ለ፤ አለቃ ማርቆስ፣ መሪጌታ ወልደ ኪዳን፣ መሪጌታ ያሬድ ከተባሉት መምህራን የግእዝን ቋንቋ ከጠቅላላ ሙያው ጋር፤
ሐ፤ አባ አካሉ፣ መምህር እጅጉ (ዘወልደ ማርያም) ከተባሉት መምህራን የሐዲሳትን ጣዕመ ትርጓሜ፤ ከብሉያት አራቱን ብሔረ ነገሥት፤ ትርጓሜ ዳዊት ከነቢያትና ከሰሎሞን ጋራ፤ የውዳሴ ማርያምና የቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ።
ከላይ የተጠቀሱት ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ፤ ከዚህ ያልተጠቀሱትንም ሌሎች ትምህርቶች ሰንቀው ሰፊ አገልግሎት ወደሚሰጡበት ወደ አዲስ አበባ ከተማ በ፲፱፻፴፱ ዓመተ ምሕረት አጎታቸውን ታላቁን ሊቅ ክቡር መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬን ተከትለው መጡ።
ክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ ከዕውቀት ወደ ዕውቀት እያደጉ ከመሄዳቸውም በላይ ያወቅሁት ይበቃኛል ሳይሉ፤ ወደ አዲስ አበባም ከመጡ በኋላ፤
ሀ፤ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ መልካም ፈቃድ በጊዜው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ተብሎ በሚጠራው ትምህርት ቤት ከስመ ጥሩው መምህር ፊላታዎስ መጽሐፈ ኢሳይያስን፣ መጽሐፈ ዐሠርቱ ወክልኤቱ ደቂቀ ነቢያትን፣ መጽሐፈ አስቴርን፣ መጽሐፈ ዮዲትንና መጽሐፈ ጦቢትን ከነ ሙሉ ትርጓሜአቸው፤
ለ፤ በዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ትምህርት ቤት ከመጋቤ ምስጢር ጌራ ስምንቱን ብሔረ ኦሪትና መጽሐፈ ዳንኤልን ከነ ትርጓሜአቸው፤
ሐ፤ ከመምህር ጽጌ (ኋላ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ዘጎጃም) የአርባዕቱን ወንጌል ትርጓሜ፤
መ፤ ከመምህር ገብረ ማርያም መጽሐፈ ኪዳንንና ትምህርተ ኅቡዓትን ተምረዋል።
አባታችን አለቃ አያሌው ታምሩ የቅድስት ተዋሕዶ ሃይማኖታቸውን ዕውቀት ካደላደሉ በኋላ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና በሌሎች አብያተ ክርስቲያን መካከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ፤ እንዲሁም ባለ ማወቅ የተሳሳቱትን ለመመለስ፤ የእምነታቸውን መሠረትና የእንግሊዝኛ ቋንቋ፣ እንዲሁም ለዐይነ ሥዉራን የተዘጋጀውን የብሬል ጽሑፍ ለመማር ወደ እንጦጦ ወንጌላዊት ሚስዮን ትምህርት ቤት ገቡ። በዚያም የፈለጉትን ያህል መቀጠል ባይችሉም የብሬል ጽሑፍና መጠነኛ የሆነ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተምረው ወጥተዋል።
ክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ ስለ ትምህርታቸው በአጠቃላይ፤ «የኢትዮጵያ እምነት በሦስቱ ሕግጋት፤» በተባለው መጽሐፋቸው ገጽ ፲፭ ላይ የገለጹትን እንጠቅሳለን። «ትምህርቴ እንደ መምህሮቼና እንደ ትምህርት ቤቶቹም ብዛት ሙሉ አይደለም። ዕውቀቴም አነስተኛ ነው። ይህንኑ ከመምህራኑ ከሞላ ጎደል የሰማሁትን የትምህርት ጣዕም በጥቂቱ እንዳውቀውና እንዳስተውለኝ ያደረገኝ፤ ምሬቱንም ያጠነከረብኝ ዐዲሱ ዘመን ብዙ የትምህርት ዐይነቶችን ስላስገኘና በወንጌላዊት ሚሲዮን ትምህርት ቤት በነበርኩበት ጊዜ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንና በሌሎቹ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን ልዩነት በደንብ ለማጥናት ስላገዘኝ፤ ከዚያ ወዲህ ራሴን መቆጣጠር ስጀምር ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት በሎንዶን ያሳተሙትን መጽሐፍ ቅዱስ በቤተ መጻሕፍት ወመዘክር አዘውትሬ መመልከቴ፣ ከመልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬና ከመምህር ይኄይስ ወርቄ ጋር በጥብቅ መነጋገሬ ነው። ሆኖም ዕውቀቴ በዚህ ሁሉ ፍጹም ሊሆን አልቻለም። ግን ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ፤ ስለ ቀናችው ሃይማኖቷና ስለ ተቀደሰው ምግባሯ፤ በእግዚአብሔርና በሷ መካከልም ስላለው ጥሩ ፍቅር በሕሊናዬ የሚወጣው የሚወርደው ሐሳብ እንደ እሳት ያቃጥለኛል። ቆሜ ተቀምጨ፣ ተኝቼ ተነሥቼ በምሄድበትና በማርፍበት፣ በምበላበትና በምጠጣበት ጊዜ ሁሉ ትሩር አድርጌ የምመለከተው እሱን ብቻ ነው። በዚህ ምክንያት በመኝታዬ ጊዜ እንኳ የጤና ዕንቅልፍ አጥቼ ሕልም ይሆንብኝና፤ «ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር፤» «አሐዱ ነገሩ ለኲሉ ዓለም፤» ያመጽኡ እምሳባ ወርቀ ወስኂነ፤» «ቃል ወልድ እኁየ ናሁ ውእቱ መጽአ፤» «ንግሥተ አዜብ ትትነሣእ አመ ዕለተ ደይን፤» «ናሁ መሰግላን መጽኡ እምብሔረ ጽባሕ፤» «ሁር ትልዎ ለዝንቱ ሠረገላ፤» «ቃል ሥጋ ኮነ፤» «ተሣሃለነ በሞተ ወልዱ፤» ስለሚሉትና እነሱንም ስለ መሳሰሉት ቃላት ሙሴን፣ ዳዊትን፣ ኢሳይያስን፣ ንግሥተ ሳባን፣ ማቴዎስን፣ ዮሐንስን፣ ሉቃስን፣ ፊልጶስንና ጳውሎስን ስጠይቅ አድራለሁ። ይሁን እንጂ፤ «ጥበብን የሚሻ ሰው ቢኖር ሳያወላውል ሳይጠራጠር ከእግዚአብሔር ይለምን፤ እግዚአብሔርም ንፍገት የሌለው አምላክ ነውና ይሰጠዋል፤» (ያዕ፤ ፩፣ ፭።) ብሎ ሐዋርያው ያዕቆብ እንደ ተናገረው፤ እግዚአብሔር አምላኬ የለመንኩትን ስላልነሣኝ፤ በዕውቀቴ ሳይሆን በቸርነቱ እየተረዳሁ ይህን መጽሐፍ ሳዘጋጅ ምስጋናዬን ለሱ አስቀድማለሁ፤» በማለት ገልጸዋል።
፪፤ መንፈሳዊ አገልግሎትና አስተዳደር።
ሀ፤ ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ዛሬ የክቡር ዐፅማቸው ማረፊያ በሆነው ደብረ አሚን ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን የቅኔ መምህርነት አገልግሎታቸውን በ፲፱፻፴፱ ዓመተ ምሕረት ጀመሩ። በመቀጠልም በዚሁ ደብር፤ መጀመሪያ የሊቀ ጠበብትነት ማዕረግ አግኝተው ያገለገሉ ሲሆን ኋላም የዚሁ ደብር አስተዳዳሪ በመሆን ሰፊ አገልግሎት አበርክተዋል።
ለ፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሊቃውንት ጉባኤ ተመርጠው ከሰኔ ወር ፲፱፻፵፰ ዓመተ ምሕረት ጀምሮ የስብከተ ወንጌል ክፍል አባል ሆነው አገልግለዋል።
ሐ፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሊቃውንት ጉባኤ አባልና ዋና ሰብሳቢ ሆነው ሠርተዋል። በዚህም የሥራ ዘመናቸው፤ የቤተ ክርስቲያን የወንጌል ትምህርት በመሆኑ ይህ አገልግሎት ሳይበረዝና ሳይከለስ እምነቱም፣ ትምህርቱም፣ ሥርዐቱም ተጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ የሚያስችለውን መንገድ ለመቀየስ በተሰጣቸው ኀላፊነት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሌት ተቀን ሠርተዋል። ዐልፎ ዐልፎም ከውስጥም ሆነ ከውጪ ለሚነሡት መናፍቃን መልስ በመስጠት፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ በየጊዜው የሚታተሙትን መጻሕፍት በማረምና ለኅትመት እንዲበቁ በማድረግ፤ ስለ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ ስለ ቅድስት ሀገራችን ኢትዮጵያ ለሚጠየቁ ጥያቄዎች መልስ በመስጠት፤ በበዓላትም ሆነ በሌሎች አጋጣሚዎች በራዲዮ፥ በቴሌቪዥን፥ በመጽሔቶችና በጋዜጦች ትምህርትና ምክር በማስተላለፍ ሀገራዊና ሃይማኖታዊ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል። ክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ በነበራቸው ዕውቀትና ኀላፊነት፤ ሐዲስ ኪዳንን በግእዝና በአማርኛ ፥ መጽሐፈ ግጻዌ፥ ሃይማኖተ አበው የተባሉትን መጻሕፍት ከሌሎች የጉባኤው አባላት ጋር ተርጉመው እንዲታተሙ አድርገዋል። ከነዚህም በተጨማሪ በግላቸው ገድለ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን፥ ገድለ ቅዱስ ጊዮርጊስን፥ ገድለ ቅዱስ ቴዎድሮስ በናድልዮስን ከግእዝ ወደ አማርኛ ተርጉመዋል።
መ፤ ከሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢነት ሥራቸው ላይ ደርበው በተጨማሪ የኢተዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ መሥሪያ ቤት የታሪክና የሥነ ጽሑፍ ማደራጃ ዋና መምሪያ ሥራ አስኪያጅ በመሆን አገልግለዋል።
ሠ፤ በኢተዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ መንበርነት በሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት የአስተዳደር ጉባኤ ውስጥ አባል ሆነው ሠርተዋል።
ረ፤ በትንሣኤ ዘጉባኤ ማሳተሚያ ድርጅት ውስጥ የመጻሕፍት አዘጋጅ ኮሚቴ አባል ሆነው አገልግለዋል።
ሰ፤ በቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ መንፈሳዊ ኰሌጅ ከ፲፱፻፶፬ እስከ ፲፱፻፷፬ ዓመተ ምሕረት፤ እንዲሁም በተግባረ እድ ትምህርት ቤትና በቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት መንፈሳዊ ትምህርት አስተምረዋል።
ቀ፤ ከኢትዮጵያ ዓይነ ሥውራን ማኅበር መሥራቾች አንዱ ሲሆኑ፤ መጀመሪያ የማኅበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት ኋላም የቦርድ ሊቀ መንበር በመሆን አገልግለዋል።
፫፤ በግላቸው ያዘጋጁአቸው መጻሕፍት።
ክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ በሕይወት ዘመናቸው ያበረከቷቸው አገልግሎቶች ዝርው ሆነው አልቀሩም። በመጽሐፍ ጥራዝ አዘጋጅተውና አሳትመው ለትውልድ ያስተላለፏቸው መጻሕፍት ዘጠኝ ሲሆኑ በይዘታቸው በሁለት የተከፈሉ ናቸው። በአንደኛው ክፍል ያሉት የቤተ ክርስቲያንንና የኢተዮጵያን ማንነት ለኢትዮጵያውያን ለማስተማር የተዘጋጁ ሲሆኑ፤ በሁለተኛው ክፍል ያሉት ደግሞ ከቤተ ክርስቲያን ውስጥም ሆነ ከቤተ ክርስቲያን ውጪ ለተነሡና ለሚነሡ መናፍቃን መልስ በመስጠት የምእመናንን ልቦና ለማጽናት የሚያስችል መልእክት የሚያስተላልፉ ናቸው። ከነዚህ መጻሕፍት ውስጥ ዐምስቱ በቤተ ክህነት አገልገሎት ላይ የተዘጋጁ ሲሆኑ፤ አራቱ ደግሞ ከቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በግፍ ከታገዱበት ከ፲፱፻፹፰ ዓመተ ምሕረት በኋላ የተዘጋጁ ናቸው።
በቤተ ክህነት አገልገሎት ላይ በነበሩበት ጊዜ ያዘጋጇቸው፤ «መች ተለመደና ከተኲላ ዝምድና»፥ «የኢትዮጵያ እምነት በሦስቱ ሕግጋት»፥ «የኑሮ መሠረት ለሕፃናት»፥ «ወላዲተ አምላክ በኢትዮጵያ»፥ «የጽድቅ በር» የተባሉት መጻሕፍት ናቸው። ከሥራ ገበታ ከታገዱ በኋላ በመኖሪያ ቤታቸው ሆነው ያዘጋጇቸው፤ «ምልጃ፥ ዕርቅና ሰላም»፥ «ተአምርና መጽሐፍ ቅዱስ»፥ «መልእክተ መንፈስ ቅዱስ»፥ «ዜና ሕይወት ዘቅድስተ ቅዱሳን እመ አምላክ» የተባሉት ናቸው።
፬፤ የቤተ ሰብእ ሁኔታ።
ክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ በቤተ ክርስቲያን ሥርዐት መሠረት በሥርዐተ ተክሊል ከወይዘሮ ርብቃ ልሳነ ወርቅ ጋር ሚያዝያ ፲፪ ቀን ፲፱፻፶ ዓመተ ምሕረት ጋብቻ ፈጽመው ፲፬ ልጆችና ፲፪ የልጅ ልጆች ለማፍራት ታድለዋል።
፭፤ ስለ ቅን አገልግሎታቸው የተሸለሟቸው ሽልማቶች።
ክቡር አባታችን አለቃ አያሌው ታምሩ እጅግ ይወዷቸውና ያከብሯቸው በነበሩት በግርማዊ ቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ መልካም ፈቃድ፤
፩ኛ፤ በ፲፱፻፵፩ ዓመተ ምሕረት የመምህራን ሽልማት ሜዳይ፤
፪ኛ፤ በ፲፱፻፷፪ ዓመተ ምሕረት የኢትዮጵያ የክብር ኰከብ የፈረሰኛ ደረጃ ኒሻን ተሸልመዋል።
፮፤ ከቤተ ክህነት አገልግሎት ስለ መሰደዳቸው።
ክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት፥ ትምህርት፥ ሥርዐትና አስተዳደር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለወጠና እየተበላሸ መሄዱ በእጅጉ ያሳዝናቸው ስለ ነበር፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ የሊቃውንት ጉባኤ ዋና ሰብሳቢ እንደ መሆናቸው መጠን፤ ጥፋቱ እንዲታረም ብዙ አቤቱታና ተማጽኖ ጉዳዩ ወደሚመለከተው ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ፤ ሲኖዶሱን በመሠረተና በሚመራው በመንፈስ ቅዱስ ስም ተማጽነው ቢያቀርቡም ሲኖዶሱ ጉዳዩን ለማፈን ከመሞከር በስተቀር ምንም እርምጃ ሳይወስድ ቀርቷል። እሳቸውም ያቀረቡት ጥያቄ መፍትሔ ባለማግኘቱ ጉዳዩን ለሚመለከተው ለኢተዮጵያ ሕዝበ ክርስቲያን ለማሳወቅና፤ በቤተ ክርስቲያን ላይ ዐመፅ የሚፈጽሙትን ፓትርያርኩንና የእሳቸው ተባባሪ የሆኑ ጳጳሳትን ባላቸው ከፍተኛ ኀላፊነተና ሥልጣነ ክህነት በሥልጣነ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፥ በሥልጣነ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ለማውገዝ ተገደዋል። ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናት በጸሎተ ቅዳሴ ጊዜ የዐመፀኛውን ፓትርያርክ ስም እንዳይጠሩ ውግዘት አስተላልፈዋል። ምእመናንም ከዐመፀኞች ካህናት ምንም ዐይነት አገልገሎት ማገኘት የማይችሉ መሆናቸውን ተገንዝበው ሕይወታቸውን በጥንቃቄ እንዲመሩ አሳስበዋል።
በዚህም ምክንያት ከ፶ ዓመት በላይ ካገለገሉበት የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በሐሰት ክስና የእምነት ክሕደት ቃላቸውን ባልሰጡበት ሁኔታ ያለ ምንም ጡረታ ከሥራ ገበታቸው ላይ በግፍ እንዲነሡ በመደረጉ ከሚያዝያ ወር ፲፱፻፹፰ ዓመተ ምሕረት ጀምሮ እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው በመኖሪያ ቤታቸው ተወስነው ኖረዋል። በነዚህ ዓመታትም በየዕለቱ ለጸሎት ባዘጋጇት አነስተኛ ክፍል በመገኘት ወደ ልዑል እግዚአብሔር በመጸለይና በማልቀስ ይተጉ ነበር። ምእመናንም በተኲላ እንዳይነጠቁ በተለያዩ ጋዜጦች ትምህርትና ማበረታቻ ሲሰጡ ኖረዋል። ከቤተ ክህነት በግፍ ተሰድጄአለሁ በማለትም ሥራቸውን አልዘነጉም፤ ከላይ ከጠቀስናቸው መጻሕፍት ውስጥ አራቱን ያዘጋጁት በዚሁ ጊዜ ውስጥ ነበር። እንዲሁም መኖሪያ ቤታቸው ድረስ እየመጡ ለሚጠይቋቸው ሰዎች መልስና ምክር በመስጠት አገልግሎታቸውን ሳያቋርጡ ቤተ ክርስቲያን የጣለችባቸውን ኀላፊነት ሲወጡ ኖረዋል።
፯፤ ዕረፍታቸውና የቀብራቸው ሥነ ሥርዐት። ክቡር አባታችን ምንም አገራቸውንና ቤተ ክርስቲያናቸውን ለማገልገል በቁርጥ ዐሳብ ሲሠሩ ቢኖሩም፤ ከአዳም ጀምሮ ለሰው ልጆች ሁሉ የተሰጠውን የሥጋ ሞት ለመቅመስ የእሳቸውም ተራ በመድረሱ፤ ለጥቂት ቀናት በሕመም ከሰነበቱ በኋላ ነሐሴ ፲፬ ቀን ፲፱፻፺፱ ዓመተ ምሕረት፤ እጅግ ይወዷት የነበረችው የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም መታሰቢያ የሆነው ጾመ ፍልሰታ ሱባዔ ሲጠናቀቅ በልጇ ፈቃድ የሰላም ዕንቅልፍ እንዳንቀላፉ ያለ ምንም ጻዕር ከዚህ ዓለም ወደ ዘለዓለም ሕይወት ተሸጋግረዋል። ከማረፋቸው ሦስት ቀናት በፊትም በተለየ የተመስጦ ራእይ ውስጥ ሆነው ብዙ ምስጢር ያላቸው ቃላት የተናገሩ ሲሆን፤ ከነዚህ ውስጥም፤ «የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በመወከል ወደ ግብጽ ቤተ ክርስቲያን ሄደህ እንድታስተምር ተብዬ ተጠርቼአለሁና ልብሴን ስጡኝ፤ ከመንበረ ማርቆስ የወርቅ ሰዓትና የወርቅ ሣህን ተሸለምኩ፤ የተሸለምኩትን የወርቅ ሰዓት ስጡኝ፤» የሚሉ ይገኙባቸዋል።
የክቡር አባታችን የቀብር ሥነ ሥርዐት ነሐሴ ፲፯ ቀን ፲፱፻፱፺፱ ዓመተ ምሕረት ብዙ ዘመን ባገለገሉበት የአዲስ አበባው ደብረ አሚን ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን በዙ ሕዝብ በተገኘበት ተፈጽሟል። የዕረፍታቸው ፵ኛ ቀን መታሰቢያም መስከረም ፲፯ ቀን ፳፻ ዓመተ ምሕረት በጸሎት ታስቦ ውሏል።
ስለ ክቡር አባታችን አለቃ አያሌው ታምሩ ከብዙ በጥቂቱ፥ ከረጅሙ ባጭሩ ለመጥቀስ ሞከርን እንጂ የእሳቸው ትምህርት በብዙ ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ የተጻፈ መሆኑ እሙን ነው። ትጉሁ የወንጌል ገበሬ አባታችን አባታቸው ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ተናገረው ለእግዚአብሔር ኖረው ለእግዚአብሔር የሞቱ፤ ደም አልባ ሰማዕትነትን የተቀበሉ አባት ናቸው። ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለ፤ «እኔ በሕይወት ብኖር ክርስቶስን ለማገልገል ነው፤ ብሞትም ዋጋ አለኝ።» (ፊልጵ፤ ፩፥ ፳፩።)
አምላካችን እግዚአብሔር ለአባታችን አለቃ አያሌው ታምሩ (አቡነ ወልደ ጊዮርጊስ) በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ዕረፍተ መንግሥተ ሰማያትን ያድልልን። ለባለ ቤታቸው፥ ለልጆቻቸው፥ ለልጅ ልጆቻቸው፥ በመንፈሳዊ ዕውቀት ኰትኲተው ላሳደጓቸው፤ እንዲሁም ለሚወዳቸውና ለሚያፈቅራቸው የኢትዮጵያ ሕዝበ ክርስቲያን መጽናናቱን ይስጥልን።
ክብር ምስጋና ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ፤ እንዲሁም ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ይሁን። አሜን።
ለክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ የመንፈቅ መታሰቢያነት የተዘጋጀውን መጽሔት እዚህ ጋር ያውርዱ።

የቤተክርስቲያን ታሪክ


እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱም  የቀደመውንም መንገድ ጠይቁ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደሆነች ዕወቁ በእሷም ላይ ሂዱ ለነፍሳችሁ እረፍትን ታገኛላችሁ፡፡ ኤር6፡16
 የቤተክርስቲያን ታሪክ ትርጉም
የቤተክርስቲያን ታሪክ ማለት የክርስትና ዕምነት ታሪክ ማለት ነው፡፡ በቤተክርስቲያን ታሪክ የክርስትና ዕምነት የአምላክ መገለጥ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በዘመንና በቦታ የተደረገ ስለሆነ መቼ፣ እንዴት እንደሆነ የምናውቅበትና በጉዞው ሁሉ የገጠሙትን ችግሮችና የምንማርበት ነው፡፡
 
የቤተክርስቲያን ታሪክ ጥቅም
የቤተክርስቲያን ታሪክ የዓለም ታሪክ አንዱን ክፍል ይዞ ስለሚገኝ የሕዝቦችን የሥልጣኔ እርምጃና ታሪክ ለማጥናት ለሚፈልግ ሰው ጠቃሚ መረጃ ይሰጣል፡፡
አንድም ምዕመን የቤተክርስቲያን ታሪክን ለማጥናት በሚፈልግበት ጊዜ

-    የዕምነቱን ታሪክ ለማወቅ
-    አባቶች በየጊዜው ስላስተማሩበት የትምህርት የሕዝብ ፀባይ እንዴት እንደተሻሻለ ለማወቅና ለማነጽ
-    የቤተክርስቲያንን ከፍተኛነትንና ጠቃሚነት ለመገንዘብና ራሱንም በእምነት ለማጽናት ከፍተኛ ጥቅም አለው፡፡

የቤተክርስቲያን ታሪክ ጥናት ምንጮች
የቤተክርስቲያንን ታሪክ በዝርዝር ለማጥናት ለሚፈልግ ሰው
-    በብሉይ ኪዳንና ሐዲስ /መጽሐፍ ቅዱስ/ እና የትርጓሜ መጽሐፍት፣
-    የቤተክርስቲያን ታሪክ አባቶች የጻፏቸው መጻሕፍት / በየጊዜው በተደረጉ ጉባዔዎች የተወሰኑትንና ነገሥታት ለቤተክርስቲያን የደነገግናቸው ሕጎች
-    ታሪኩ በተፈጸመበት ቦታ ተገኝተውና ታሪኩ በተፈጸመበት ዘመን የኖሩ የቤተክርስቲያን የውጭ ታሪክ ጸሐፊዎች የጻፏቸው መጻሕፍት
-    በየጊዜው የተገኙ የክርስቲያናት መቃብራት፣ መቅደሶች፣ ስዕሎች፣ ገንዘቦች፣ ጽሑፎችና እነዚህን የመሳሰሉት ቅርጾች /ለማገናዘብያነት የሚረዱ/
የቤተክርስቲያን  ትውፊታዊ መረጃዎች ያስፈልጉታል፡፡

የቤተክርስቲያን ዘይቤያዊ ፍቺ
1)  ‹‹ቤተ ክርስቲያን›› የግእዝ ቃል ሲሆን በአማርኛ እንጠቀምበታለን፡፡ ፍቺውም የክርስቲያኖች ቤት የክርስቲያኖች መኖርያ ማለት ነው፡፡ በዚህ ቀጥተኛ አፈታት መሠረት ሕፃኑ፣ ሽማግሌው፣ ወንዱ፣ ሴቱ፣ሁሉም በአንድ ላይ ተሰብስበው ጸሎት የሚያደርስበት የጌታችን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደሙ የሚፈተትበት ቅዱስ ቦታ /ሕንፃ ቤተክርስቲያንን/ ያመላክታል፡፡ የሐዋ 20፡28፣ 1ኛጢሞ3፡15፣ 1ኛ ነገ9፡3

2)  ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክ የዓለም መድኃኒት መሆኑን የሚያምኑ ሰዎች ሁሉ ቤተክርስቲያን ይባላሉ፡፡የያዕቆብ የእስራኤል ወገን የሆኑ በሙሉ ቤተእስራኤል እንደሚባሉ በክርስቶስ ክርስቲያን የሆኑ የክርስቲያን ወገኖችም ቤተክርስቲያን ይባላሉ፡፡ ሐዋ5፡11፣ የሐዋ12፡1፣ 1ኛ ቆሮ3፡16፣ 2ኛ ቆሮ6፡16፣ ዮሐ14፡23፣ የሐዋ 9፡3

3)  የክርስቲያኖችም ማኅበር ፣ የክርስቲኖች ጉባዔ ፣ የክርስቲያኖች ስብስብ /አንድነት/ ቤተክርስቲያን ይባላል፡፡ ሮሜ16፡1፣ 1ኛጴጥ5፡13

የቤተክርስቲያን ዕድሜ 
አንዳንድ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ቤተክርስቲያን የሚለው ቃል በምሥጢራዊ አፈታት ሲፈቱ ቤተክርስቲያን ማለት እግዚአብሔር ከሰውና ከመላእክት ጋር ያለው ግንኙነት ነው ይላሉ፡፡ በዚህም መሠረት የቤተክርስቲያን ዕድሜ በሦስት ይከፍሉታል፡፡
1. ሰው ከመፈጠሩ በፊት በዓለመ መላእክት የነበረች የቅዱሳን መላእክት አንድነት፤
2. በዘመነ ብሉይ የነበሩ ደጋግ አባቶች ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቸው ግንኙነት፤
3. በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ደም የተመሠረተችውና በመንፈስ ቅዱስ የምትመራው ዓማናዊት ቤተክርስቲያን /የምዕመናን አንድነት / እሷም የፀጋና የፅድቅም ምንጭ ናት፡፡ ኤፌ3፡9
እነዚህ የቤተክርስቲያን ዕድሜዎች በዝርዝር ስንመለከታቸው

1)  ዓለመ መላእክት እግዚአብሔር መላእክትን በከተማ በነገድ መቶ አድርጎ ከፈጠራቸው በኋላ ተሰወረባቸው፤ እነርሱም ፈጣሪያቸን ማን ይሆን እያሉ ይጠይቁ ጀመር በዚህ ጊዜ በክብር ከፍ ብሎ ይገኝ የነበረው ሳጥናኤል ‹‹እኔ ፈጠርኳችሁ›› በማለቱ ክርክር ተነስቶ መላእክት ለሁለት ተከፈሉ፡፡ በመጨረሻም ሳጥናኤልና ሠራዊቱን ወደ ዘላለም ፍርድ፣ ባሉበት የጸኑትን ቅዱሳን መላእክት ደግሞ የዘላለም ህይወትና ክብር ተሰጣቸው፡፡ በዚህም መላእክት ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ጀመሩ፡፡ ራዕ12፡28፣ ኢሳ14፡15

2)  በብሉይ ዘመን የነበሩ ደጋግ አባቶች

በአራት ይከፈላሉ፡፡ እነሱም

1. ዘመነ አበው            3. ዘመነ ነገሥታት  
2. ዘመነ መሣፍንት        4. ዘመነ ነብያት /ካህናት/ ናቸው፡፡
የቤተክርስቲያን ታሪክ ከአዳም እስከ ክርስቶስ እርገት 5500 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ 34 ዓመተ ምህረት ነው፡፡ /ከፍጥረተ ዓለም እስከ ጰራቅሊጦስ/

ምንጭ ፡- የ/መ/ገ/ጽ/ቅ/ጊ/ቤ/ክ/ሰ/ት/ቤት

አዕማደ ምሥጢራት!


አዕማድ ቋሚ ፣ ተሸካሚ ፣ ምሰሶ ማለት ነው፡፡ ቤተክርስቲያንም የእምነት መሠረት የሆኑትን ትምህርቶች አዕማደ ምሥጢራት ትላቸዋለች፡፡ አዕማድ የተባሉት ልቦናን ከኑፋቄ ፣ ከጥርጥር የሚያድኑ ስለሆነ ነው፡፡ ምሰሶ የሌለው ቤት እንደሚወድቅ ሁሉ አዕማደ ምሥጢራትም ያላመነ ፣ ያላወቀ ሰው ቢኖር ይወድቃል፡፡

አዕማደ ምሥጢራት አምስት ናቸው፡፡ እነዚህም

  1. ምሥጢረ ሥላሴ
  2. ምሥጢረ ሥጋዌ
  3. ምሥጢረ ጥምቀት
  4. ምሥጢረ ቁርባን
  5. ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን ናቸው፡፡

ምሥጢር መባላቸው ስለምንድን ነው

 ምሥጢር
አመሠጠረ ከሚለው ግስ የተገኘ ቃል ሲሆን ስውር ፣ ድብቅ ፣ ሽሽግ ማለት ሲሆን አምስቱ አዕማደ ምሥጢራትም ምሥጢር የተባሉበት ምክንያት
  • በሥጋው ጥበብ ምርምር መረዳት ስለማይቻሉ
  • ላመኑት እንጂ ላላመኑት ሰዎች የተሰወሩ በመሆኑ


ምሥጢር በሁለት ይከፈላል፡፡ እነርሱም፡-

የፈጣሪ ምሥጢር፡- ሊገለጥ የማይችል ነው፡፡ ከ እስከ የሌለው ምሥጢርም ይባላል፡፡

የፍጡራን ምሥጢር፡- በጊዜ የሚገለጥ /የሚታወቅ/ ነው፡፡ የሰውና የመላእክት ምሥጢር በዚህ ውስጥ የሚካተት ነው፡፡
ምሥጢረ ሥላሴ
ሥላሴ፡- የግእዝ ቃል ሲሆን ሦስትነት ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር አንድ ሲሆን ሦስት ፣ ሦስት ሲሆ አንድ ነው፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ሦስትነት ልዩ ሦስት ነው፡፡ ሦስት ብቻ ተብሎ አይቆምምና ሦስት ሲሆን አንድም ነው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር የአንድነት የሦስትነት ባለቤት በመሆኑ ሥላሴ ይባላል፡፡

የእግዚአብሔር አንድነት

እግዚአብሔር አንድ ነው ስንል በመለኮት ፣ በባሕርይ ፣ በአገዛዝ ፣  በሥልጣን ፣ በሕላዌ /ሕልውና/ በመፍጠር በልብ በቃል በእስትንፋስ ይህን ዓለም በመፍጠር እና በማሳለፍ ይህን በመሳሰለው ነው፡፡

  በመፍጠር መዝ 101፡25 ፣ ዘፍ 1፡1 ፣ ኢሳ 66፡1-2 
  በሥልጣን ዮሐ 10፡30 
  በመለኮት መለኮት ማልኩት ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል የተገኘ ሲሆን መንግስት ግዛት ማለት ነው፡፡ ይህም ለእግዚአብሔር ብቻ የተሰጠ ነው፡፡ ቆላ 2፡9፣ 1ኛ ጴጥ 1፡3 
  በሕላዌ /ሕልውና/  አኗኗር ማለት ነው፡፡ መብለጥ ፣ መቅደም ፣ መቀዳደም የለባቸውም፡፡ ዮሐ 1፡1-2፣ ዮሐ 14፡10 

የእግዚአብሔር ልዩ ሦስትነት

እግዚአብሔር በስም፣ በአካል፣ በግብር ሦስት ነው፡፡

የስም ሦስትነት አብ ወልድ መንፈስቅዱስ ናቸው፡፡ ማቴ 28፡19፡፡
  እግዚአብሔር አብ፡- ከዘለዓለም እስከዘለዓለም ከሦስቱ አካላት የአንዱ የአብ ስም ነው፡፡ 1ኛ ጴጥ 1፡2፣ ዮሐ 3፡16
  እግዚአብሔር ወልድ፡- ከዘለዓለም እስከዘለዓለም ከሦስቱ አካላት የአንዱ የወልድ ስም ነው፡፡ ወልድ ሰው በሆነ ጊዜ በተለያ ስሞች ተጠርቷል፡፡ እነዚህም፡-
  ኢየሱስ- መድኃኒት አዳኝ ማለት ነው፡፡ ማቴ 1፡21
  ክርስቶስ- መስሕ /ንጉሥ/ ማለት ነው፡፡ ሉቃ 2፡11፣ ዮሐ 4፡25
  አማኑኤል-እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው ማለት ነው፡፡ ትን.ኢሳ 7፡14 ፣   ማቴ 1፡21



እግዚአብሔር ወልድ አምላክ ስለመሆኑ ማስረጃ

ዮሐ 20፡9 ፣ ሮሜ 10፡12 ፣ ዮሐ 1፡1 ፣ ዮሐ 1፡14 ፣ ዮሐ 20፡28 ፣ ዮሐ 4፡42 ፣ የሐዋ.ሥራ 20፡28 ፣ ራዕይ 1፡8 ፣ ትን.ኢሳ 9፡6 ፣ ራዕይ 22፡12 ፡፡

   እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ፡- ከዘለዓም እስከ ዘለዓለም ከሦስቱ አካላት የአንዱ መንፈስ ቅዱስ ስሙ ነው፡፡

መንፈስ ቅዱስ በተለያዩ ስሞች ይጠራል፡፡
  • መንፈስ- ዮሐ 3፡5 ፣ 1ኛ ቆሮ 12፡4 ፣ ዘፍ 1፡2 ፣ ትን.ኢሳ 48፡16
  • የእግዚአብሔር መንፈስ - ት.ኢሳ 61፡6
  • ጰራቅልጦስ /አጽናኝ/ እየተባለ ይጠራል፡፡ ዮሐ 15፡26 ፣ ዮሐ 14፡16 ፣ ዮሐ 16፡7
  • የእውነት መንፈስ፡፡ ዮሐ 15፡26

በአጠቃላይ ሥላሴ በስም ሦስትነት ቢኖራቸውም አንዱ በአንዱ ስም ሊጠራ አይችልም፡፡
የአካል ሦስትነት
    ለአብ ፍጹም ገጽ ፣ ፍጹም መልክ ፣ ፍጹም አካል አለው፡፡
    ለወልድም ፍጹም ገጽ ፣ ፍጹም መልክ ፣ ፍጹም አካል አለው፡፡
    ለመንፈስ ቅዱስም ፍጹም ገጽ ፣ ፍጹም መልክ ፣ ፍጹም አካል አለው፡፡
የግብር ሦስትነት
የአብ ግብሩ መውለድ ማስረጽ ፣ የወልድ ግብሩ መወለድ ፣ የመንፈስ ቅዱስ ግብሩ መስረጽ ነው፡፡ አብ ወልድን ውልዷል ፤ መንፈስ ቅዱስን አስርጽዋል ፤ መንፈስ ቅዱስ ሰርጽዋል፡፡ ወልድ ተወልዷል ፤ መንፈስ ቅዱስ ሰርጽዋል፡፡

  • አብ ወልድን ወለደ ማለት ፤ ከአካሉ ከባሕርይው ፤ አስገኘው ማለት ነው፡፡
ምሳሌ የሰው ነፍስ ልብነቷ /አሳቢነቷ/ ቃልነቷን እንደሚያስገኘው
  • ወልድ ከአብ ተወለደ ማለት ፤ አብን አክሎ አብን መስሎ ከአብ ተገኘ ማለት ነው፡፡
ምሳሌ የነፍስ ቃልነቷ ከልብ እንደተገኘ
  • አብ መንፈስ ቅዱስን አሰረጸው ማለት ፤ ከአካሉ ከባሕርይው አስገኘው ማለት ነው፡፡
ምሳሌ የነፍስ ልብነቷ እስትንፋስነት /ሕይወትነቷን/ እንዳስገኘ ማለት ነው
  • መንፈስ ቅዱስ ከአብ ሰረጸማለት ፤ አብን አህሎ አብን መስሎ ከአብ ተገኘ ማለት ነው፡፡
ምሳሌ የነፍስ እስትንፋስነቷ ከልብ እንደተገኘ

ለምሥጢረ ሥላሴ የፍጡራን ማስረጃ


የሰው ነፍስ፡- የመናገር ፣ የማሰብ ፣የመተንፈስ /የሕያውነት/ ሁኔታ አላት፡፡ ማሰብ በአብ ፤ መናገር በወልድ ፤ ሕያውነት በመንፈስ ቅዱስ ይመሰላሉ፡፡ የነፍስ ልብነቷ ቃልነቷን ሕይወትነቷን ከራሷ ታስገኛለች፡፡ ነፍስ ስትገኝ በሦስትነቷ በአንድ ጊዜ ተገኘች እንጂ ልብነቷ ቀድሞ ቃልነቷ እስትንፋስነቷ በኋላ አልተገኘም፡፡ ነፍስ በኩነታት ሦስትነት ቢኖራትም በአካል አንድ ናት፤ ሥላሴ ግን አብ አካላዊ ልብ፤ ወልድ አካላዊ ቃል ፤ መንፈስ ቅዱስ አካላዊ እስትንፋስ ነው፡፡

ፀሐይ፡- አንድ ስትሆን ሦስትነት አላት፡፡ አካሏ ፣ ብርሃኗ ፣  ሙቀቷ ናቸው፡፡ አካሏ በአብ፣ ብርሃኗ በወልድ፣ ሙቀቷ በመንፈስ ቅዱስ ይመስላል፡፡

ባሕር፡- ስፋቱ በአብ፣ ርጥበቱ በወልድ ፣ ማዕበሉ በመንፈስ ቅዱስ ይመሰላል፡፡

ስለ ምሥጢረ ሥላሴ የማገናዘቢያ ጥቅሶች

            በብሉይ ኪዳን     
ት.ኢሳ 48፡12 ፣ መዝ 117፡16፣ ዘኁ 6፡24 ፣ ዘፍ 3፡22 ፣ት.ኢሳ 6፡3 

            በሐዲስ ኪዳን
1ኛ ቆሮ 19፡14 ፣ ማቴ 17፡15 ፣ ሉቃ3፡22 ፣ ማቴ 28፡19 ፣ ማቴ 3፡16 ፣ ዩሐ 16፡7 ፣ የሐዋ.ሥራ 7፡55 ፣ ዮሐ 14፡15 ፣ ራዕይ 14፡1-2

ምሥጢረ ሥጋዌ

ሥጋዌ ‹‹ተሰገወ›› ከሚለው የግዕዝ ግስ የወጣ ሲሆን ሥጋን መንሳት /ሰው መሆን/ ማለት ነው፡ ምሥጢረ ሥጋዌ ከሦስቱ አካላት አንዱ እግኢአብሔር ወልድ ሰው የመሆኑ ምሥጢር ነው፡፡ ሰው ሆነ ማለትም የሰውን ባሕርያት ነፍስና ሥጋን በረቂቅ ባሕርይው ተዋሐደ ማለት ነው፡፡

አምላክ ለምን ሰው ሆነ?

 - እግዚአብሔር አዳምና ሔዋንን ለማዳን ቃል ኪዳን ስለገባላቸው ቃል ኪዳኑን ለመጠበቅ አምላክ ሰው ሆነ፡፡ ዘፍ 2፡17 ፣ 1ኛ ተሰ 5፡9 ፣ ገላ 4፡4፡፡ በስመጨረሻ ሁሉን አሟልቶ በአርአያውና በምሳሌው ለፈጠረው ሰው ፍጽም የሆነ ፍቅሩን በገሀድ ለማሳየት አምላክ ሰው ሆነ፡፡ ዮሐ 3፡6
 - ምድር ለመልካም ተፈጥራ ሳለ ስለሰው ኃጢአት በመረገሟ በቅዱሳን እግሮቹ ተራምዶ ሊቀድሳት በደሙ ፈሳሽነት ሊያነጻት አምላክ ሰው ሆነ፡፡ ት.ኢሳ 45፡18 ፣ ዘፍ 3፡17 ፡፡
 - ሰው በምድር ካለ የሚቀናቀነው የለም ስለሆነም በልብ መታበይ አምላክ ነኝ እንዳይል ሁሉን የፈጠረ አምላክ መኖሩን ሊያስረዳ፡፡
   ዲያብሎስ አዳም ሔዋንን ከይሲ / እባብ/ ሰውነት አድሮ እንዳሳታቸቸው እርሱም በሰው አካል አድሮ ሊያድናቸው፡፡

አምላክ ሰው ባይሆን ማዳን አይችልም ነበረን?

      ፍርድ እንዲገባ

-  አምላካችን ሁሉን ማድረግ የሚችል የማይሳነው ነው፡፡ ዘፍ 18፡14 ፣ ኢዮ 39፡4
ሉቃ 1፡37 ነገር ግን ሥርዓት አልባ አይደለም ፤ ሁሉን በሥርዓት ያደርጋል፡፡ 1ኛ ቆሮ 14፡33
-  የፍርድ ቃልን የሚለውጥ አይደለምና በመሐሪነቱ አንጻር ግን ይቅር ባይ ነው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ትክክለኛና የማይሻር ዳኝነቱን ሊያሳይ ሰው ሆነ፡፡
ዕብ 6፡17፣ ማቴ 7፡7 ያዕ 2፡5

   ፍጹም ፍቅሩን ሊያስረዳን


-  የበደለ ኃጢአትን የሠራ ሰው ነው፡፡ በእግዚአብሔር ጥተኛ ፍርድ መሠረት የኃጢአትን ዋጋ መክፈል ያለበት ሰው ነው፡፡ ነገር ግን ከሰው ልጆች መካከል ባሕርይው ያላደፈበት ወንጀለኛ ያልሆ ስለጠፋ ሁሉም ራሱ መዳ የሚያስፈልገው ስለሆነ ፍጡር ሰው ፍጡር ሰዎችን ማዳን አልቻለም፡፡ ስለዚህ የማይለወጥ አምላክ ለተሠራው በደል የሚከፍል ሞትን ይፈጽም ዘንድ ሰው ሆነ፡፡ ከአመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ፡፡ ት.ኢሳ 59፡16 ፣ ሮሜ 3፡23
ሮሜ 5፡6


የአምላክ ሰው መሆን /መወለድ/

ከቅድስት ድንግል ማርያም ሲወለድ ማኅተመ ድግልናዋ ሳይለወጥ ነው፡፡ በዚህ ድግል ስትባል ትኖራለች፡፡ ምሳሌው አምላክ ሰውም ሲባል መኖሩ ነው፡፡ በሌላ በኩል ከድንግል ማርያም ያለ ዘር ሩካቤ መወለዱ ለአካላዊ መሲህ መለያ ምልክቱ ነው፡፡ ሕጻናትን በማሕጸን የሚፈጥር የእግዚአብሔር ልጅ በሥጋና በነፍስ በሕጻናት ጽንስ መጠን በድንግል ማርያም ማሕፀን ተጸነሰ፡፡

ጌታ ከጽንስ ጀምሮ የሰውነት ጠባዩ አልተለወጠም፡፡ 9ወር ከ5 ቀን ሲሆ ተወለደ፡፡ በልደቱም እናቱ ጭንቅ ምት አላገኛትም፡፡ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አምላክን በድንግልና መውለድ ከሌሎች ሴቶች ፀንሶ መውለድ ይለያል፡፡ 

Source:
Kidane Mhret blog

«አልብኪ ነውር ወኢምንትኒ ላዕሌኪ፤» መኃ 4:7


የትንቢተ ነቢያት ማረፊያ ፡-የስብከተ ሐዋርያት መነሻ.የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ምሥጢር ነገረ ማርያም ነው፡፡ ያለ ነገረ ማርያም ነገረ ክርስቶስን መናገር አይቻልም፡፡ በክርስትና ሃይማኖት ታሪክ የተነሡ አያሌ መናፍቃን የመጀመሪያ ችግራቸው የነገረ ማርያምን አማናዊ ትምህርት መቀበል ነበር ፡፡ ያም ችግራቸው ክርስቶስን በትክክል እንዳያምኑት አድርጓቸዋል፡፡ በነገረ ማርያም ላይ የተጣራ ትምህርትና እምነት ቢኖራቸው ኖሮ ለኑፋቄ አይጋለጡም ነበር ፡፡ ንስጥሮስ፡- «አምላክ ወልደ አምላክ» ብሎ በክርስቶስ ለማመን የተሳነው « ወላዲተ አምላክ . ወላዲተ ቃል. እመ እግዚአብሔር » ብሎ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ለማመን በመቸገሩ ነበር፡፡ 
ነገረ ማርያምን ከነገረ ክርስቶስ መለየት አይቻልም ፡፡ የተዋሐደ ነው ፡፡ ስለ እመቤታችን የሚነገረው ክፉም ሆነ በጎ ክርስቶስን ይነካዋል፡፡ የእግዚአብሔርን የማዳን ሥራ በምንናገርበት ጊዜ እመቤታችንን ወደ ጎን መተው አይቻልምና፡፡ ምክንያቱም ወልዳ ያስገኘች. አዝላ የተሰደደች. በማስተማር ጊዜው ከአገር አገር አብራው የተንከራተተች ናትና ፡፡ በተሰቀለበት ዕለትም ከእግረ መስቀሉ አልተለየችም፡፡ በአጠቃላይ አነጋገር ምክንያተ ድኂን አድርጓታል፡፡ 

ስለ ነገረ ድኅነት ስንናገር ጌታ ድኅነታችንን በመስቀል ላይ ፈጸመ የምንለው የዕለት ፅንስ ሆኖ በእመቤታችን ማኅፀን የጀመረውን ነው ፡፡ ሥጋውን ቆረሰልን .ደሙን አፈሰሰልን . ነፍሱን አሳልፎ ሰጠልን ብንል ከእርሷ የነሳውን ነው፡፡ ከእርሷ ነሥቶ በመስቀል ላይ የፈተተውን ሥጋውን እና ደሙንም የሕይወት ማዕድ አድርጎ ሰጥቶናል፡፡ መለኰታዊውን ፍህም በማኅፀን ከመሸከም ጀምሮ ይህ ታላቅ ምሥጢር የተፈጸመባት በመሆኑ መልዕልተ ፍጡራን መትሕተ ፈጣሪ ሆና ትመሰገናለች ፡፡ በመዝሙራችንም ሆነ በቅዳሴአችን ከስመ ሥላሴ ቀጥሎ የምንዘምረው የእመቤታችንን ምሥጋና ነው ፡፡ ቅዱስ ዳዊት ፡- « መሠረቶቿ የተቀደሱ ተራሮች ናቸው ፤ ከያዕቆብ ድንኳኖች ይልቅ . እግዚአብሔር የጽዮንን ደጆች ይወድዳቸዋል፤ የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ. ስለ አንቺ የተነገረው ነገር ድንቅ ነው ፡፡» ያለው ለዚህ ነው ፡፡ መዝ 86.1-3 ፡፡ እርሷም እሳተ መለኰትን በማኅፀንዋ ተሸክማ ፡- « ሰውነቴ እግዚአብሔርን ታከብረዋለች ፡፡ ልቡናዬም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች ፡፡ የባርያውን ትሕትና ተመልክቷልና ፡፡ (ትንቢተ ኢሳያስን ተመልክቼ አምላክን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና ከምትወልደው እመቤት ዘመን ቢያደርሰኝ ገረድ ሆኜ አገለግላታለሁ የሚለውን የልቤን አሳብ አይቷልና፡፡) እነሆ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብዕፅት ይሉኛል፡፡ ታላቅ ሥራን ሠርቶልኛልና ስሙም ቅዱስ ነው ፡፡ » ብላለች ፡፡ ሉቃ 1.46 ፡፡ ለእመቤታችን የተደረገላት ታላቅ ሥራ ፡- 1ኛ ከጥንተ አብሶ ነፃ ሆና መፈጠሯ ነው ፤ 2ኛ ፡- ከሀልዮ . ከነቢብ . ከገቢር ኃጢአት ነፃ መሆኗ   ነው ፤ 3ኛ ከልማደ አንስት ነፃ መሆኗ ነው ፤ 4ኛ ሰማይና ምድር የማይችሉትን . ኪሩቤል እሳታዊ መንበሩን የሚሸከሙለትን . ሱራፌል መንበሩን የሚያጥኑለትን . መላእክት የሚንቀጠቀጡለትን በማኅፀኗ መሸከሟ ነው፡፡ በመሆኑም እንደ ቅዱስ ዳዊት « ሀገረ እግዚአብሔር ድንግል ማርያም ሆይ ለአንቺ የተደረገው ነገር ዕፁብ ድንቅ ነው ፤» እያልን እናመሰግናታለን ፡፡
       
 እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ንጽሕት እምንጹሐን . ቅድስት እምቅዱሳን ናት ፡፡ ከተለዩ የተለየች. ከተከበሩ የተከበረች. ከተመረጡ የጠመረጠች ማለት ነው፡፡ ይኽውም እንደሌላው መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ ስላልወደቀባት ነው፡፡ ይህም ይታወቅ ዘንድ ጠቢቡ ሰሎሞን « ለስእርተ ርእስከ. ለርእስኪ. ለገጽከ=. ለቀራንብትከ=. ለአዕይንትከ=. ለአእዛንኪ . ለመላትሕኪ ለአዕናፍኪ. ለከናፍርኪ. ለአፉከ=. ለአስናንኪ.  . . . ለክሣድኪ . . . ለአጥባትኪ፤ » እያለ መልክአ ማርያምን ማለትም የውስጥ የአፍአ ውበቷን ከማድነቅ ጋር « ወዳጄ ሆይ. ሁለንተናሽ ውብ ነወ<. ምንም ነውር የለብሽም ፤» ብሏታል ፡፡ መኃ. 4.7 ፡፡ ነውር የተባለውም መርገመ ሥጋን መርገመ ነፍስን ያመጣ የጥንት በደል (ጥንተ አብሶ) የሚባለው የአዳም ኃጢአት
ነው፡፡

      
    እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድመ ጸኒስና ቅድመ ወሊድ. ጊዜ ጸኒስና ጊዜ ወሊድ. ድኅረ ፀኒስና ድኅረ ወሊድ ድንግል እንደሆነች የታመነ ነው፡፡ ኢሳ 7.04 ፤ ሕዝ #4.1-4 ፡፡ ይህም ንጽሐ ሥጋን ንጽሐ ነፍስንና ንጽሐ ልቡናን አስተባብራ. አንድ አድርጋ ይዛ መገኘቷን ያረጋግጥልናል፡፡ በመሆኑም ጠቢቡ ፡- « ምንም ነውር የለብሽም ፤ » ሲል፡- የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ፡- « ደስ ያለሽ. ጸጋንም የተመላሽ ሆይ. ደስ ይበልሽ ፤ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነው ፤ ከሴቶች ተለይተሸ አንቺ የተባረክሽ ነሽ ፤ » ብሎ ከማብሠሩ በፊት. ባበሠራት ጊዘ?. ካበሠራትም በኋላ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ሉቃ 1.!6 ፡፡ ምክንያቱም ፡- መልአኩ ገብርኤል ወደ አንዲት ድንግል ተላከ ፤ ይላልና ነው ፡፡ ይህም ድንጋሌ ሥጋን ብቻ ሳይሆን ድንጋሌ ነፍስንም የሚያመለክት ነው ፡፡ ድንጋሌ ነፍስን ገንዘብ ማድረጓም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በጥንተ አብሶ የተያዘችበት ጊዜ ፈጽሞ እንዳልነበረ ያሳየናል፡፡ ጠቢቡም ፡- «ወዳጄ ሆይ. ሁለንተናሽ ውብ ነው ፤» ማለቱ ለዚህ ነውና ፡፡
« ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ፤ » ኢሳ1.9
ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ የነገረ ድኅነት ምሥጢር ተገልጦለት ያለፈውን ያለውን እና የሚመጣውን አገናዝቦ ሲናገር ፡- « የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ. እንደ ሰዶም በሆንን . እንደ ገሞራም በመሰልን ነበር ፡፡ » ብሏል፡፡ ኢሳ 1.9 ፡፡ ይህም ለፍጻሜው ለእመቤታችን የተነገረ ትንቢት ነው ፡፡ ከዚህም በበለጠ ኹኔታ ትርጓሜ የማያሻው ደረቅ ትንቢት ሲናገረም፡- « ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ ድንግል ትፀንሳለች. ወልድንም ትወልዳለች. ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች ፡፡» ብሏል ኢሳ 7.04 ፡፡
          እነ ኢሳይያስ በጥንተ አብሶ ምክንያት ፡- « ሁላችን እንደ ርኵስ ሰው ሆነናል ፤ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው ፤ » ኢሳ %4.6፤ ቢሉም ፡- እግዚአብሔር ባወቀ ጥንተ አብሶ ፈጽሞ ባልደረሰባት በእመቤታችን ይመኩ. ተስፋም ያደርጉ ነበር ፡፡ ለዚህም ነው፡- « እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ . . . ፤ » ያሉት ፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከጥንተ አብሶ ገና ከጧቱ ንጽሕት ሆና የተዘጋጀች ጥንተ መድኃኒት ናትና ነው፡፡ ቅዱስ ኤፍሬምም ፡- « መመኪያ አክሊላች. ጥንተ መድኃኒታችን. የንጽሕናችን መሠረት ፤» እያለ ያመሰገናት ለዚህ ነው ፡፡
«በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖር ነበር»
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓለም ከመፈጠሩ በፊት በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖር ነበር ፡፡ ይህንንም ሊቁ ቅዱስ ያሬድ « ዘእንበለ ይትፈጠር ሰማይ ወምድር. ወዘእንበለ ይሣረር ምድረ ገነƒ. ሀለወት ስብሕት ቅድስት ወቡርክት ይእቲ ማርያም. እንተ ተሰምየት ሰንበተ ክርስቲያን ፣ ጽዮን ፣ ቅድስት፣ እሞሙ ለሰማዕት ወእኅቶሙ ለመላእክት፡፡ የመላእክት እህታቸው፣ የሰማዕታት እናታቸው፣ ጽዮን ፣ ቅድስት፣ የክርስቲያን ሰንበት የተባለች. የተመሰገነች. በንጽሕና በድንግልና የተለየችና የተባረከች እርሷ ማርያም ሰማይና ምድር ሳይፈጠር የገነት ምድርም መሠረት ሳይጣል ነበረች፡፡ » ብሏል ፡፡ ዳግመኛም « በቤተልሔም ተወሊዶ መድኅን ክብረ ቅዱሳን . ፍስሐ ለኵሉ ዓለም. ወሠርዐ ሰንበተ ለሰብእ ዕረፍተ. ወይቤላ እግዚአብሔር ለማርያም ፡- አዝማንየ አዝማንከ=. አምጣንየ አምጣንኪ. ማርያም ሐቀፍኪዮ ወአነ ዮም ወለድኩዎ ፡፡ ለዓለሙ ኹሉ ደስታ የሚሆን የቅዱሳን ክብር መድኃኔዓለም በቤተልሔም ተወልዶ ፡- ለሰው ልጅ ዕረፍት ሰንበትን ሠራ. እግዚአብሔር ማርያምን ፡- ዘመኖቼ ዘመኖችሽ. መጠኖቼ መጠኖችሽ ናቸው ፤ እኔ ዛሬ ወለድኩት፡- ማርያም ሆይ አንቺ ታቀፍሺው ፡፡ » የሚል አለ ፡፡ ቅዱስ ያሬድ በድጓው እንደገለጠው እግዚአብሔር እመቤታችንን « ዘመኖቼ ዘመኖችሽ ናቸው ፤» ማለቱ ዓለም ከመፈጠሩ ዘመን ከመቆጠሩ በፊት በእርሱ ኅሊና መኖሯን የሚያስረዳ ነው፡፡ « መጠኖቼ መጠኖችሽ ናቸው ፤» ማለቱ ደግሞ እርሱ ቅድመ ዓለም አካላዊ ቃል ወልድን ያለ እናት ወልዶት አባት እንደሆነው እርሷም ድኅረ ዓለም አካላዊ ቃል ወልድን ያለ አባት ወልዳው እናት እንደሆነችው የሚያመለክት ነው ፡፡ ምሥጢራዊ መልእክቱም « ወላጆች ( አባትና እናት ) ለወለዱት ልጅ እኩል እንደሆኑ ሁሉ ወልድን በመውለድ በወላጅነት መሰልሽኝ ተስተካከልሺኝ ፤ » ሲላት ነው ፡፡ ይህም ፈጣሪን እና ፍጡርን የማነፃፀር የማስተካከል ሳይሆን የተሰጣትን ክብርና ልዕልና የማሳየት ነው፡፡ ለምሳሌ ጌታ ደቀመዛሙርቱን ፡- « እውነት እውነት እላችኋለሁ . በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል ፤ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል፡፡» ብሏቸዋል ፡፡ ዮሐ 14 .12 ፡፡ ይህም በማስተማርና ተአምራት በማድረግ እንደሚመስሉት ሲነግራቸው ነው ፡፡ «የሚበልጥ ያደርጋል፤» ማለቱም ፡፡ እርሱ ያስተማረው ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ነው፡፡ እነርሱ ግን ከዚህ በላይ ሃያ ሠላሳ ዓመት የሚያስተምሩ ስለሆነ ነው፡፡ እርሱ ለአብነት ሁለት ሦስት ሙት ቢያነሣ እነርሱ ደግሞ በስሙ ከዚያ በላይ ብዙ ስለሚያስነሡ ነው፡፡
«እመቤታችን በአዳም ባሕርይ ውስጥ»
          « ማርያምሰ ተኀቱ እምትካት ውስተ ከርሱ ለአዳም. ከመ ባሕርይ ጸአዳ፤እመቤታችን ማርያም ከጥንት ጀምሮ በአዳም ባሕርይ ውስጥ እንደ ነጭ ዕንቁ ታበራለች ፤ » ይላል ፡፡ ይህንንም በድጓው የተናገረው ቅዱስ ያሬድ ነው ፡፡ እመቤታችን በአዳም ባሕርይ ውስጥ እንደ ነጭ ዕንቁ ማብራቷ ከጥንተ አብሶ ነፃ ሆና መፈጠሯን የሚያመለክት ነው፡፡ አዳም ይኽንን ስለሚያውቅ ነው . እመቤታችንን ተስፋ ያደረገው ፡፡ ምክንያቱም በውስጡ እንደ ነጭ ዕንቁ ስታበራ ይታወቀው ነበርና ነው ፡፡ አባ ሕርያቆስ ይህ ምሥጢር ተገልጦለት « ከገነት በተሰደደ ጊዜ የአዳም ተስፋው አንቺ ነበርሽ ፤» እያለ እመቤታችንን አመስግኗታል፡፡ ይህም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትእዛዝን በመተላለፍ በአዳም ላይ ከመጣ ጥንተ በደል በአምላካዊ ምሥጢር ተጠብቃ ከአዳም ወደ ሴት. ከሴት ወደ ኖኅ. ከኖኅ ወደ ሴም. ከሴም ወደ አብርሃም ስትቀዳ የኖረች ንጽሕት ዘር መሆኗን ያስረዳል ፡፡ ከላይ እንደተገለጠው ነቢዩ ኢሳይያስ « እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ » ያለው ይኽንን ነው ፡፡
« አንፂሖ ሥጋሃ ቀዲሶ ኪያሃ ኀደረ ላዕሌሃ»
ቅዱስ ያሬድ በሌላ አንቀጽ « ሥጋዋን አንጽቶ. እርሷን ቀድሶ. በእርሷ ላይ አደረ ፤» ብሏል፡፡ ይኽንን ንባብ በመያዝ ትርጓሜውንና ምሥጢሩን ቸል በማለት « ያነጻት የቀደሳት ከጥንተ አብሶ ነው ፤ » የሚሉ አሉ፡፡ ነገር ግን አይደለም፡፡ ጥንቱንም ንጽሕት ቅድስት አድርጐ በፈጠራት በእርሷ አደረ ማለት እንጂ ፡፡ « ልዑል ማደሪያውን ቀደሰ፤ ( ለየ ) ፤ » እንዲል ፡፡ መዝ #5.4 ፡፡ ይህም ሁሉ ከተያዘበት ከጥንተ አብሶ ለይቶ ፈጠራት ማለት ነው፡፡ ጊዜው ሲደርስ ሥላሴ፡- አብ ለማጽናƒ. ወልድ ለለቢሰ ሥÒ. መንፈስ ቅዱስ ለማንፃት በማኅጸነ ድንግል አድረዋል፡፡ እዚህ ላይ « መንፈስ ቅዱስ ለማንፃት ፤» ማለቱ ፡- የመንፈስ ቅዱስ ግብሩ ማንፃት. መቀደስ መሆኑን ለመግለጥ እንጂ እድፍ ጉድፍ ኖሮባት አይደለም ፡፡ ለምሳሌ እግዚአብሔር የሰማይ ማደሪያውን ባለማለፍ ጸንታ የምትኖረውን እሳታዊ ዙፋን የተዘረጋባትን . ሰባት እሳታዊ መጋረጃዎች የተጋረዱባትን . ፀዋርያነ መንበሩ ኪሩቤልና ዐጠንተ መንበሩ ሱራፌል ያሉባትን ጽርሐ አርያምን ጥንቱኑ ንጽሕት ቅድስት አድርጐ ፈጥሯታል ፡፡ ቅዱስ ያሬድ ይኽንን ምሳሌዋ በማድረግ እመቤታችንን « ከሰማያት በላይ ያለ የአርያም የልዑል ሥፍራ ምትክ በምድር ላይ ከፍተኛ አርያምን ሆንሽ ፤ » ብሏታል ፡፡ በመሆኑም ያቺ ጥንቱኑ ንጽሕት ቅድስት ሆና እንደተፈጠረች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ጥንቱኑ ንጽሕት ቅድስት ሆና ተፈጥራለች እንጂ ኖራ ኖራ በኋላ የነፃች አይደለችም ፡፡ ለምሳሌ « ቃልህ እጅግ የነጠረ ነው ፤» የሚል ገጸ ንባብ ይገኛል፡፡ መዝ )08.)# ፡፡ ይህም የእግዚአብሔር ቃል ልክ እንደ ቅቤ . እንደ ብረት ወይም እንደ ወርቅ ኖሮ ኖሮ የነጠረ ወይም ነጥሮ እድፍ ጉድፍ የወጣለት ነው አያሰኝም ፡፡ በመሆኑም እመቤታችንን በአባ ሕርያቆስ ምስጋና እግዚአብሔር አብ በሰማይ ሁኖ ምሥራቅንና ምዕራብን . ሰሜንና ደቡብን ዳርቻዎችንም ሁሉ በእውነት ተመለከተ ተነፈሰ አሸተተም. እንደ አንቺ ያለ አላገኘም፡፡ የአንቺን መዓዛ ወደÅ. ደም ግባትሽንም ወደÅ. የሚወደውንም ልጁንም ወደ አንቺ ሰደደ ፡፡ » እያልን ልናመሰግናት ይገባል፡፡ « እንደ አንቺ ያለ አላገኘም ፤» ማለቱም ፡- « እንደ አንቺ በጥንተ አብሶ ሳይያዝ የተገኘ የለም . ከአንቺ በቀር ሁሉ ተይዟል ፤ » ማለት ነው ፡፡
« ቀዳማዊ አዳም ወዳግማዊ አዳም »
          ቀዳማዊ አዳም የሚባለው ከምድር አፈር የተፈጠረው ሰው ነው ፡፡ « እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር ፈጠረው ፤ በፊቱም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ ፡፡» እንዳለ ፡፡ ዘፍጥ 2.7 ፡፡ ዳግማዊ አዳም የተባለው ደግሞ በተለየ አካሉ ከሰማይ ወርዶ. በማኅጸነ ድንግል ማርያም አድሮ. ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ በተዋሕዶ ሰው ሁኖ የተወለደው የባሕርይ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ይኽንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ፡- « አሁንም ክርስቶስ ከሞቱ ሰዎች ሁሉ አስቀድሞ ( በኵር ሆኖ ) ተነሥቷል ፡፡ በመጀመሪያው ሰው
( በቀዳማዊ አዳም ) ሞት መጥቷል“. በሁለተኛው ሰው ( በዳግማዊ አዳም በክርስቶስ ) ትንሣኤ ሙታን ሆነ ፡፡ ሁሉ በአዳም እንደሚሞት እንዲሁ በክርስቶስ ሁሉ ሕያዋን ይሆናሉ፡፡ . . . መጽሐፍ እንዲህ ብሏል. የመጀመሪያው ሰው አዳም በነፍስ ሕያው ሆኖ ተፈጠረ ፤ ሁለተኛው አዳም ግን ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው ፡፡ ነገር ግን አስቀድሞ ሥጋዊው ቀጥሎም መንፈሳዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው መጀመሪያ አይደለም ፡፡ የመጀመሪያው ሰው ከመሬት የተገኘ መሬታዊ ነው ፤ ሁለተኛው ሰው ከሰማይ የወረደ ሰማያዊ ነው፡፡ » በማለት ገልጦታል፡፡ 1ኛ ቆሮ 05.!-#5 ፡፡ ከዚህም የመጀመሪያው ፍጡር ሁለተኛው ፈጣሪ. የመጀመሪያው ከምድር ሁለተኛው ከሰማይ መሆኑን እንረዳለን ፡፡ እንግዲህ የሚያንሰው ቀዳማዊ አዳም ከመጀመሪያው ንጽሕት ከነበረች መሬት ተፈጠረ እያልን የሚበልጠውን ዳግማዊ አዳምን ከመጀመሪያው ንጽሕት ካልነበረች. በጥንተ አብሶ አድፋ ጐድፋ ከነበረች ከድንግል ማርያም ተወለደ ማለት ክርስቶስን ከአዳም ማሳነስ መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡
«ብሥራተ ገብርኤል ወፅንሰት፡፡ »
የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ተልኮ ወደ እመቤታችን በመጣ ጊዜ ፡- « ደስ ያለሽ. ጸጋንም የተመላሽ ሆይ. ደስ ይበልሽ ፤ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነው ፤ ከሴቶች ተለይተሸ አንቺ የተባረክሽ ነሽ ፡፡» በማለት አመስግኗታል፡፡ ሉቃ 1.!8 ፡፡ ከእርሷ በፊት ይህን በሚመስል ምስጋና የተመሰገነ ማንም አልነበረም ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ለእመቤታችን የተሰጠ ምስጋና ነው ፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በጥንተ አብሶ ተይዛ ቢሆን ኖሮ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል « ጸጋን የተመላሽ ሆይ » አይላትም ነበር፡፡ ምክንያቱም ጥንተ አብሶ ጸጋዋን ጐዶሎ ያሰኝባት ነበርና ፡፡ ከላይ እንደገለጥነው እነ ኢሳይያስን ጽድቃቸውን የመርገም ጨርቅ ያሰኘባቸው ጥንተ አብሶ ነው፡፡ የቅድስናን ሥራ እየሠሩ « ሁላችንም እንደ ርኵስ ሰው ሆነናል ፤ » ያሰኛቸው ይኽው ነው ፡፡ ኢሳ %4.6 እነ ኤርምያስንም ፡- « ለሥጋ ለባሽ ሁሉ ሰላም የለም፡፡ ስንዴ ዘሩ እሾህንም አጨዱ ፤ » አሰኝቷቸዋል፡፡ ኤር 02. 03፡፡ እመቤታችን ግን ከመጀመሪያው ንጽሕት ቅድስት በመሆኗ « ጸጋን የተመላሽ ሆይ ፤ » ተብላለች፡፡

          አንዳንዶች፡- ለእመቤታችን ጥንተ አብሶ የጠፋላት መልአኩ ባበሠራት ጊዜ ነው ይላሉ፡፡ ይህም አባባላቸው ሁለት ጥያቄዎችን ያስነሣል፡፡ 1ኛ ፡- ከዚህ በፊት መልአክ ያበሠራቸው ማኑሄና ሚስቱ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ለምን ጥንተ አብሶ አልጠፋላቸውም; መሳ 03.2 ሉቃ 1.8 ፤ 2ኛ ፡- ጥንተ አብሶ የሚጠፋው በብሥራተ መልአክ ቢሆን ኖሮ አካላዊ ቃል ከሰማይ ወርዶ ከድንግል ማርያም ተወልዶ ሰው መሆን . መከራ መቀበልና በመስቀል ላይ መሞት ለምን አስፈለገው; በልዑል መንበሩ እንደተቀመጠ እልፍ አዕላፋት ወትእልፊተ አዕላፋት መላእክትን ልኮ በብሥራት ብቻ ጥንተ አብሶን አያጠፋም ነበር;

          አንዳንዶች ደግሞ « ጌታ በተፀነሰ ጊዜ በዚያ ቅጽበት ነው የጠፋላት ፤ » ይላሉ፡፡ ይህም ፡- «ጌታ የመጣው ጥንተ አብሶን እንዴት አድርጐ ለማጥፋት ነው; » የሚል ጥያቄ ያስነሣል ፡፡ መልሱም « በመስቀል ላይ በሚፈጽመው ቤዛነት በሚከፍለው መሥዋዕትነት ነው፤» የሚል ይሆናል ፡፡ እንግዲህ እመቤታችን ጥንተ አብሶ ነበረባት የሚሉ ከሆነ «እርሷም በጥንተ አብሶ እንደተያዙ እንደማናቸውም ሰው ናት፤ » ማለታቸው ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ እንደማናቸውም ሰው በመስቀል ላይ በሚፈጸም ቤዛነት ብቻ ከጥንተ አብሶ ትድን ነበር እንጂ ተቃዋሚዎቹ እንደሚሉት ሊሆን አይችልም፡፡
« ሰው አይደለችም ወይ
ነቢዩ ኢሳይያስ ፡- « በትር ከእሴይ ሥር ትወጣለች. አበባም ከእርሷ ይወጣል፤» በማለት ስለ እመቤታችንም ስለ ጌታም ትንቢት ተናግሯል፡፡ ኢሳ 01.1 ፡፡ የበትር ምሳሌነት ለእመቤታችን ሲሆን የአበባ ምሳሌነት ደግሞ ለጌታ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድም በዚህ ትንቢት ላይ ተመሥርቶ ፡- « ትወጽእ በትር እምሥርወ ዕሴይ. ወየዐርግ ጽገ. ይእቲ በትር አምሳለ ማርያም ቅድስት ይእቲ. ወጽጌ ዘወጽአ እምኔሃ ፤ አምሳሉ ዘወልድ ዘኀደረ ላዕሌሃ. ቃል ሥጋ ኮነ ወተወልደ እምኔሃ፤ ከነገደ ዕሴይ በትር ትወጣለች. አበባም ከእሷ ይወጣል. ይህችውም በትር የማርያም አምሳል ናት ፤ ከእርሷ የሚወጣውም በትር የወልድ ምሳሌ ነው፤ የአብ አካላዊ ቃል በማኅጸኗ አድሮ ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷም ነፍስን ነሥቶ በተዋሕዶ ሰው ሁኖ ከእርሷ ተወለደ፤ » ብሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪም ቅዱስ ማቴዎስ እንደነገረን የእመቤታችን የዘር ሐረግ (የዘር ቅጂዋ) ከዕሴይ ወደ ዳዊት ወደ ሰሎሞን . ከዚያም ሲወርድ እስከ አልዓዛር .ከዓልዓዛር ደግሞ ሴት ልጁ ወደምትሆን ወደ ቅሥራ. ከቅሥራም ወደ ኢያቄም የደረሰ ነው፡፡ በእናቷ በኵል ደግሞ ከሊቀ ካህናቱ ከአሮን ወገን ናት፡፡ በመሆኑም ከሰው ወገን የተወለደች ሰው ናት፡፡

ካቶሊኮች፡- ጥንተ አብሶን የሸሹ መስሏቸው « ሰው አይደለችም . ኃይል አርያማዊት ናት » እያሉ ነው፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ይኽንን የካቶሊኮች አመለካከት የሸሹ መስሏቸው «እንደማናቸውም ሰው ጥንተ አብሶ የነበረባት ሰው ናት፡፡ » ይላሉ ፡፡ የሁለቱም « ከድጡ ወደ ማጡ » ነው ፡፡ የሁለተኛዎቹ አስተሳሰብ « ከሰው ወገን የተወለደች ሰው እስከሆነች ድረስ. የሰው ልጅ ተብላ እስከተጠራች ድረስ የግድ ጥንተ አብሶ ነበረባት ያሰኛል ፤ » የሚል ነው፡፡ ይህም አንድ መሠረታዊ ጥያቄ ያስነሣል፡፡ ይኽውም ፡- « የሰው ወገን . የሰው ልጅ ለመባል የግድ የጥንተ አብሶ መኖር ያስፈልጋል ወይ; » የሚል ነው ፡፡ እንዲህስ ከሆነ ቀዳማዊ አዳም ከመበደሉ በፊት ለምን ሰው ተባለ; መርገመ ሥጋን መርገመ ነፍስን ያጠፋ ዳግማዊ አዳም ክርስቶስም ለምን የሰው ልጅ ተባለ; ያሰኛል፡፡ መናፍቃኑ እነደሚሉት ቢሆን ኖሮ፡- እነ ኢሳይያስ « እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ ፤» እያሉ አይመኩባትም ነበር፡፡ እነ ሰሎሞንም « አልብኪ ነውር » እያሉ አያመሰግኗትም ነበር፡፡ እነ ቅዱስ ኤፍሬም « አክሊለ ምክሕነ. ወጥንተ መድኃኒት. ወመሠረተ ንጽሕነ ፤ » እነ አባ ሕርያቆስም ፡- « ወኢረከበ ዘከማኪ፤ » አይሏትም ነበር፡፡ ስለዚህ ብርሃኑን ከጨለT. በጐውን ከክñ. ስንዴውን ከእንክርዳድ ለይተን አባቶቻችን ባቆዩልን ልንጸና ያስፈልጋል፡፡ ነገሩ የእውቀት ብቻ ሳይሆን የእምነት ነውና፡፡ የዕውቀት ሰዎች ሁለት ዓይነት ናቸው ፡፡ የመጀመሪያዎቹ እውቀታቸውን በትህትና ይዘው በእምነት የሚኖሩ ሲሆኑ ሁለተኛዎቹ ግን በእውቀታቸው ሲታበዩ በጥርጥር ማዕበል የሚመቱ . በኑፋቄ የሚለዩ . በክህደት የሚወድቁ ናቸው፡፡ ትእቢት ዲያቢሎስ የተያዘበት አሽክላ ነው፡፡ በንስሐ የማይመለሰው ለዚህ ነው፡፡ ዲያቢሎስ የትዕቢት እንጂ የእውቀትም የሥልጣንም ችግር አልነበረበትም፡፡ እነ አርዮስ. እነ ንስጥሮስ. እነ መቅዶንዮስም የትዕቢት እንጂ የእውቀት ችግር አልነበረባቸውም፡፡ ነገር ግን እውቀታቸውን ለክፋት ተጠቀሙበት ፡፡ እስከ ዓለም ፍጻሜ ለሚነሡ መናፍቃንም መጥፎ አብነት ሆኑበት፡፡ ስለዚህ ከዚህ እንዲሠውረን ተግተን ልንጸልይ ይገባናል፡፡ ለዚህም የእግዚአብሔር ቸርነት . የንጽሕተ ንጹሐን . የቅድስተ ቅዱሳን እመቤታችን የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን አሜን ፡፡


ይህ ጽሑፍ በማህበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ የወጣ ነው www.mahiberekidusan.org
Source: Bete Dejene

ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ፦ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት፤ (ክፍል ፩)



ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት፤ ምክንያቱም የአንድ የክርስቶስ አካል ናትና። ይህች የክርስቶስ አካል የሆነች ቤተ ክርስርስቲያን መሠረቷም ጉልላቷም ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይህንንም ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ፦ «እርሱም (ክርስቶስ)ከሁሉ በፊት ነው፤ (ለዘመኑ ጥንት የሌለው ቀዳማዊ ነው)፤. . . እርሱም የአካሉ ማለትም የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤. . . እርስዋም አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚሞላ የእርሱ ሙላቱ ናት፤» ሲል ገልጦአታል። ኤፌ ፩፥፳፫፣ ቈላ ፩፥፲፰። በተጨማሪም በቆሮንቶስ መልእክቱ ላይ «የእግዚአብሔር ጸጋ እንደተሰጠኝ መጠን እንደ ብልሃተኛ የአናጺ አለቃ መሠረትን መሠረትሁ፥ ሌላውም በላዩ ያንጻል። እያንዳንዱ ግን በእርሱ ላይ እንዴት እንዲያንጽ ይጠንቀቅ። ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ ሊመሠርት አይችልምና፤ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።» ብሎአል። ፩ኛ ቆሮ ፫፥፲-፲፩።
          በክርስቶስ ደም ላይ የተመሠረተችው ይህች ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያዪቱ ቤተ ክርስቲያን ናት። የሐዋ ፳፥፳፰፣ ዕብ ፫፥፲፬። በመሆኑም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የምታስተምረው ትምህርት ሁሉ እውነት ነው። ምክንያቱም እውነት የባሕርይ ገንዘቡ ከሆነ ከእውነተኛው ምንጭ የተቀዳ ነውና። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን እኔ ከጌታ ተቀብያለሁና፤» ሲለ እንደተናገረ ቤተ ክርስቲያንም ለእኛ ያስተላለፈችው ከጌታ የተቀበለችውን ንጹሕ ትምህርት ነው። ፩ኛ ቆሮ ፲፩፥፳፫። ይኸውም በዓይኖቿ ያየችውን፥ በጆሮዎቿ የሰማችውን ፥በእጆቿም የዳሰሰችውን ነው። ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ፦ «ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን፥ በዓይኖቻችን ያየነውን፥ የተመለከትነውንም፥ እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤ ሕይወትም ተገለጠ፤ አይተንማል፥ እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም (ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በቅድምና የነበረውን፥ ፈጥሮም የሚገዛውን) ለእኛም የተገለጠውን (በመለኰት ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ በተለየ አካሉ ከሰማየ ሰማያት በመውረድ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ በመወለድ ሰው ሆኖ የታየውን) የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን፤ » ያለው። ፩ኛ ዮሐ ፩፥፩-፫። ስለሆነም፥ የቅዱሳን ሐዋርያትን ትምህርት በመያዟ፥ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን የምትባለው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፥ ክርስቶስን በቅዱሳን ሐዋርያት ዓይኖች አይታዋለች፥ በጆሮዎቻቸው ሰምታዋለች፥ በእጆቻቸውም ዳስሰዋለች። ይህም፦ ቤተ ክርስቲያንን ብፅዕት ያሰኛታል። ምክንያቱም ጌታ ደቀመዛሙርቱን፦ «የእናንተ ግን ዓይኖቻችሁ ስለሚያዩ፥ ጆሮዎቻችሁም ስለሚሰሙ ብፁዓን ናቸው፤» ብሎአቸዋልና። ማቴ ፲፫፥፲፮።
          ብፅዕት፥ ንጽሕት እና ቅድስት የሆነችው ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል በመሆኗ ሁለንተናዋ የሚሰብከው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ «መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፥ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤» ሲል እንደተናገረ፥ ቤተክርስቲያን ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ እየሰበከች ያለችው በደሙ የዋጃትን ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። ፩ኛ ቆሮ ፩፥፳፪-፳፫፣ የሐዋ ፳፥፳፰።
          ብዙ ሰዎች ስብከት ሲባል «ኢየሱስ ጌታ ነው፤» እያሉ እንደ ዓለማውያን መፈክር በባዶ ሕይወት ባዶ ጩኸት ማስተጋባት ይመስላቸዋል። ነገር ግን አይደለም፤ ምክንያቱም ጌታችን በወንጌል፦ «በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ፥ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም። በዚያን ቀን ብዙዎች፦ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንት አላወጣንምን፥ በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንምን? ይሉኛል። የዚያን ጊዜም፦ ከቶ አላውቃችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ።» ብሎአልና።  ማቴ ፯፥፳፩-፳፫።
          በክርስትና ትምህርት ኢየሱስ ክርስቶስ የሚሰበከው በሕይወት(በኑሮ)ነው። በመሆኑም ጌታችን በወንጌል፦ «መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ፤» ሲል አስተምሮአል። ማቴ ፭፥፲፮። ለዚህም ነው ቤተ ክርስቲያን በኑሮዋ ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስን የምትሰብከው። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ትምህርቷ በጆሮ የሚሰማ ብቻ ሳይሆን በዓይን የሚታይና በእጅም የሚዳሰስ ነው። ይኽንን በመሰለ የትምህርት አሰጣጥ ዘዴም ቤተ ክርስቲያን ሁል ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስን ትሰብከዋለች።
፩ኛ፦ በክቡር መስቀሉ ትሰብከዋለች፤
          ጌታችን መርገመ ሥጋንና መርገመ ነፍስን አጥፍቶ ድኅነተ ምዕመናንን የፈጸመው በዕፀ መስቀል ላይ ነው። ገላ ፫፥፲፫፣ ኤፌ ፪፥፲፬-፲፯፣ ፊል ፪፥፰፣ ዕብ ፲፪፥፩-፪። ይኽም መስቀል የክርስቶስ ኃይሉ የተገለጠበትና በደሙም የከበረ ነው። ፩ኛ ቆ ፩፥፲፰። ጌታችን በዚህ መስቀል ዲያቢሎስን ድል ካደረገው በኋላ እኛም ድል እያደረግነው እንድንኖር ኃይላችን የሆነውን መስቀል አስታጥቆናል። ኤፌ ፪፥፲፮። በመሆኑም እንደ ሐዋርያው እንደ ቅዱስ ጳውሎስ በመስቀሉ እንመካለን። ገላ ፮፥፲፬። መመካትም ብቻ ሳይሆን የጌታችን እግሮች ለድኅነተ ምዕመናን በችንካር ላይ ቆመው ለዋሉበት ለክቡር መስቀሉ እንሰግዳለን። ምክንያቱም ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በትንቢት፦ «እግሮቹ በሚቆሙበት ሥፍራ እንሰግዳለን፤» ብሎአልና መዝ ፩፻፴፩፥፯። በዚህም መሰረት ቤተ ክርስቲያን ከፍ አድርጋ በጉልላቷ ላይ የተከለችውና ዕለት ዕለትም ካህናት በክርስቶስ ስም ምዕመናንን የሚባርኩበት ቅዱስ መስቀል የሚሰብከውና የሚናገረው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
፪ኛ፦ በቅዱሳት ሥዕላት ትሰብከዋለች፤
          በዘመነ ብሉይ ሥዕለ ኪሩብን እንዲያዘጋጅ ለሙሴ የነገረው እግዚአብሔር ነው። ሙሴም የታዘዘውን ፈጽሟል፤ ዘጸ ፳፭፥፳፩-፳፪። እግዚአብሔርም አስቀድሞ እንደተናገረ በሥዕሉ እያደረ አነጋግሮታል። ዘኁ ፯፥፹፱። ንጉሡ ሰሎሞንም በዘመኑ የእግዚአብሔርን  ቤተ  መቅደስ ሠርቶ ከጨረሰ በኋላ በግምቡ ዙሪያ ሥዕለ ኪሩብን በማሠራቱ እግዚአብሔር ሥራውን ወዶለታል። ፩ኛ ነገ ፮፥፳፫-፳፱፣ ፪ኛ ዜና ፯፥፲፩-፲፪። ከዚህም የምንማረው ቅዱሳት ሥዕላትን መሥራት የተጀመረው በእግዚአብሔር ትእዛዝ መሆኑን ነው። ይህ ትእዛዝ በአዲስ ኪዳንም አልተሻረም። ምክንያቱም ተሽሮ ቢሆን ኖሮ ጌታችን የገንዘብ ለዋጮችን ገበታዎችና የርግብ ሻጮችን ወንበር ገልብጦ ከቤተ መቅደስ ባስወጣ ጊዜ ሥዕሉንም ባስወጣ ነበርና ነው። ማቴ ፳፩፥፩-፲፫። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን በእግዚአብሔር ትእዛዝ መሠረት በመቅደሷ በቅድስቷና በቅኔ ማኅሌቷ ዙሪያ የጌታችንን ብሥራቱን፥ ልደቱን፥ ስደቱን፥ ጥምቀቱን፥ ተአምራቱን፥ መከራ መስቀሉን፥ ርደተ መቃብሩን፥ ትንሣኤውን፥ ዕርገቱንና ዳግም ምጽአቱን የሚያመለክቱ ቅዱሳት ሥዕላትን በመሣል ክርስቶስን በሥዕል ትሰብከዋለች። በቤተ ክርስቲያን ቅዱሳት ሥዕላት ማስተማሪያ ብቻ አይደሉም። ልክ እንደ በትረ ሙሴ፥ እንደ ኤልያስ መጐናጸፊያ፥ እንደ ኤልሳዕ ቅርፊትና ጨው፥ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ የልብስ ቁራጭ፥ እንደ ቅዱስ ጴትሮስም ጥላ ያኃይለ እግዚአብሔር መገለጫዎችና የበረከት መገኛዎች ናቸው። ዘጸ ፬፥፲፪፣ ፪ኛ ነገ ፪፥፰፣ ፪ኛ ነገ ፪፥፳፩፣ ፮፥፮፤ የሐ ፭፥፲፭፣ ፲፱፥፳፪። በመሆኑም ለቅዱሳት ሥዕላት ይሰገዳል።
፫ኛ፦  በጽላቷ ትሰብከዋለች፤
          ሕጉና ትእዛዙ የተቀረጸበትን ፅላት አስቀድሞ ለሙሴ የሰጠ እግዚአብሔር ነው። ዘጸ ፴፩፥፲፰። በኋላም በተሰበሩት ምትክ ሙሴ እንዲያዘጋጅ የፈቀደ እግዚአብሔር ነው። ዘጸ ፴፬፥፩። የጽላቱ ማደሪያ ታቦትን የደፈረ ኦዛንም የቀሰፈ እግዚአብሔር ነው። ታቦቱን ላከበረ ለአቢዳራም በረከቱን ያትረፈረፈ እግዚአብሔር ነው። ፪ኛ ሳሙ ፮፥፮-፲፪። በአዲስ ኪዳንም፦ «እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም።» ያለ ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ማቴ ፭፥፲፯። ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ፦ «በሰማይም ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ፥ የኪዳኑም ታቦት በመቅደሱ ታየ፥ መብረቅና ድምፅም ነጐድጓድም የምድርም መናወጥ ታላቅም በረዶ ሆነ፤» ብሎአል። ራእ ፲፩፥፲፱፤ በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን ጽላትን አክብራ ይዛለች። በእነዚህም ጽላት ላይ ከስም ሁሉ በላይ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተቀርጾባቸዋል። ከዚህም ጋር «በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ ለኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይንበርከኩ።» የሚለው የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስ ቃል ተቀርጾባቸዋል። ፊል ፪፥፲። በመሆኑም በጽላቱ ፊት የሚሰገደው ለኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው። ለዚህም ነው ቤተ ክርስቲያን ኢየሱስ ክርስቶስን በጽላቷ ትሰብከዋለች ያልነው።    
፬ኛ፦ በንዋ ቅዱሳት ትሰብከዋለች፤
          የቤተ መቅደስ መገልገያዎች በዘይት (በሜሮን) እንዲከብሩ ያደረገ፥ ተቀብተው ቅድስተ ቅዱሳን ይሆናሉ፥ የነካቸውም ቅዱስ ይሆናል ያለ እግዚአብሔር ነው ። ዘጸ ፴፥፳፪-፴፫። በመሆኑም እግዚአብሔር የሚገለገልባቸው የቤተ መቅደስ መገልገያዎች ሁሉ በሜሮን የከበሩ ናቸው። እነዚህም የከበሩ ንዋየ ቅዱሳት ከአገልግሎታቸው በተጨማሪ እያንዳንዳቸው ራሱን የቻለ መንፈሳዊ መልእክት ያስተላልፋሉ። ስለሆነም፦ መቋሚያው፥ ከበሮው፥ ጸናጽሉ፥ ካባው፥ ጥምጥሙ፥ አክሊሉ፥ ቆቡ፥ ቀሚሱ፥ ጻሕሉ፥ እርፈ መስቀሉ፥ ጽንሐው ወዘተ. . . የሚሰብከው ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። (ኆኅተ ሰማይ የሚለውን የቀሲስ ያሬድ ገብረ መድኅንን ድንቅ መጽሐፍ ያንብቡ)።
፭ኛ፦ በቅዱስ ቁርባን ትሰብከዋለች፤
          የአዲስ ኪዳን ቁርባን የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም ነው። በመሆኑም በቤተ ክርስቲያን ኅብስቱ ተለውጦ ሥጋ መለኰት፥ ወይኑም ተለውጦ ደመ መለኰት ይሆናል። ይኽንንም፦ «እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ሥጋዬ ነው፤ ጽዋንም አንሥቶ . . .  ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው።» ብሎ የሰጠ ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ማቴ ፳፮፥፳፮-፳፯። በተጨማሪም፦ «እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስን ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው። እኔ በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም  እውነተኛ መጠጥ ነውና። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በእርሱ እኖራለሁ፤» ብሎአል። ዮሐ ፮፥፶፫-፶፮። ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «ስለዚህ ሳይገባው ይህን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት። ሰው ግን ራሱን ይፈትን፥ እንዲሁም ከእንጀራው ይብላ ከጽዋውም ይጠጣ፤ ሳይገባው የሚበላና የሚጠጣ የጌታን ሥጋ ስለማይለይ ለራሱ ፍርድ ይበላልና፥ ይጠጣልምና።» በማለት ቅዱስ ቁርባንን ማክበር በንጽሕናም ሆኖ መቀበል እንደሚገባ የተናገረው። ፩ኛ ቆሮ ፲፩፥፳፯-፳፱። ስለሆነም ቤተ ክርስቲያን ይኽንን መሠረት በማድረግ በቅዱስ ቁርባን የክርስቶስን ሕይወትነት ትሰብካለች።
፮ኛ፦ በምስጋናዋ ትሰብከዋለች፤
          ቤተ ክርስቲያን ከዓመት እስከ ዓመት የማይቋረጥ ምስጋና በመዓልትም በሌሊትም ለእግዚአብሔር ታቀርባለች። በኪዳን፥ በመዝሙር፥ በቅዳሴና በማኅሌት እግዚአብሔርን ታመሰግነዋለች። ይህም ምስጋና ከብሉይ ኪዳንና ከሐዲስ ኪዳን ከመጽሐፍተ ሊቃውንትም የተውጣጣ ነው። ለምሳሌ በመጽሐፈ ግጻዌው መሠረት በየዕለቱ በሚቀደሰው ቅዳሴ ላይ ከቅዱስ ወንጌልና ከቅዱሳት ሐዋርያት መልእክታት የሁለቱ ይነበባል። በመጨረሻም (ከቅዳሴው በኋላ) ይተረጐማል ፥ ይመሰጠራል ወደ ህይወት ተለውጦ ይሰበካል። በመሆኑም ንባቡም ሆነ ትርጉሙ እንዲሁም ምሥጢሩ የሚሰብከው ኢየሱስ ክርስቶስን ነው።
፯ኛ፦ በአጽዋማት ትሰብከዋለች፤
          በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሰባት አጽዋማት አሉ። እነዚህም የሚሰብኩት ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። ፩ኛ፦ ዐቢይ ጾምን የምንጾመው ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ፦ እጸድቅ አይል ጻድቅ፥ እከብር አይል ክቡር ሲሆን በገዳመ ቆሮንቶስ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት በመጾም ባርኮና ቀድሶ ስለሰጠን ነው። በመጨረሻም ዲያቢሎስን ድል ነሥቶታል። ይሀም ብትጾሙ ጥንተ ጠላታችሁን ዲያቢሎስን ድል ትነሡታላችሁ ብሎ አብነት ሲሆነን ነው። ፪ኛ፦ ዓርብና ረቡዕን (ጾመ ድኅነትን) የምንጾመው ጌታችን በዕለተ ረቡዕ በአይሁድ ሸንጐ ሞት ስለተፈረደበትና በዕለተ ዓርብ ደግሞ  ድኅነታችንን በመስቀል ላይ የፈጸመበት ዕለት ስለሆነ ነው። ፫ኛ፦ ጾመ ነቢያትን የምንጾመው ቅዱሳን ነቢያት ጌታ ይወርዳል ይወለዳል ብለው በተስፋ በደጅ ጥናት በእርሱ ስም የጾሙት ጾም በመሆኑ ነው። እኛም ይኽንኑ በማሰብና ከቅዱሳኑም በረከት ለመሳተፍ ከበዓለ ልደት በፊት በስሙ እንጾማለን። ምክንያቱም ጌታ በወንጌል፦ «እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል። ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፥ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል፤» ብሎአልና። ማቴ ፲፥፵-፵፩። ፬ኛ፦ ጾመ ሐዋርያትን የምንጾመው ቅዱሳን ሐዋርያት የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ተቀብለው «የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስሙ ሕይወት መድኃኒት ነው፤» ብለው ለመስበክ ከመሰማራታቸው በፊት በስሙ የጾሙት ጾም በመሆኑ ነው። ፭ኛ፦ የገሃድን ጾም የምንጾመው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት ዓርብ ወይም ረቡዕ በሚውልበት ጊዜ ለውጠን በዋዜማው ማክሰኞ ወይም ሐሙስ  ነው። ይኸውም፦ ትንቢተ ነቢያት የተፈጸመበትን፥ ምሥጢረ ሥላሴ የተገለጠበትን፥ የጸጋ ልጅነታችን የተመለሰበትን፥ በዮርዳኖስ ተጥሎ የነበረው የዕዳ ደብዳቤያችን የተፋቀበትን ሰማያት ተከፍተው ምሥጢር የታየበትን፥ ጥምቀታችን የተባረከበትንና የተቀደሰበትን በዓለ ጥምቀት በታላቅ ደስታ ለማክበር ነው። ፮ኛ፦ ጾመ ፍልሰታን የምንጾመው ቅዱሳን ሐዋርያት እመቤታችን ካረፈች በኋላ ቅዱሳን መላእክት አሳርገዋት ስለነበር ሥጋዋን ለማግኘት እርሱን ተማጽነው በእርሱ ፈቃድ የእናቱን  ሥጋ ያገኙበት ጾም ስለሆነ ነው። ፯ኛ፦ ጾመ ነነዌን የምንጾመው ሰብአ ነነዌ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት ጾመው ምሕረትን ከጌታ ያገኙበት፥ እርሱም የወደደው ጾም ስለሆነ ነው። በመሆኑም ይኽንን የምሕረትና የይቅርታ ጾም ብንጾም ጌታ ይምረናል ብለን በማመን ነው የምንጾመው።
፰ኛ፦ በበዓላት ትሰብከዋለች፤
          በዓላትን ባርኰና ቀድሶ እንዲያከብሩት ለሰው ልጆች የሰጠ እግዚአብሔር ነው። ይኸውም ገና ከመጀመሪያው ቀዳሚት ሰንበትን በማክበሩና በመቀደሱ ታውቋል። ዘጸ ፳፥፲፩። በዚህም ምክንያት ሰንበትን አለማክበር ከባድ ቅጣትን ያስከትል ነበር። ዘኁ ፲፭፥፴፪-፴፮። እስራኤል ዘሥጋ ዕለቱን በሚገባ ባለማክበራቸው በነቢያት ተወቅሰዋል። ሕዝ ፳፥፲፪-፲፮፣ አሞ ፰፥፮። በአዲስ ኪዳንም ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዕለተ ሰንበትን አክብሮአል። ሉቃ ፬፥፲፮። ጌታ የተቃወመው የፈሪሳውያንን የሰንበት አከባበር ሥርዓት እንጂ የሰንበትን ክብር አይደለም። ማቴ ፲፪፥፩-፬። ከሰንበትም ሌላ አይሁድ በእግዚአብሔር ትእዛዝ የፋሲካን፥ የመከርን፥ የዳስን፥ መለከቶች የሚነፉበትን፥ የማስተስረያን፥ የፉሪምን፥ የመቅደስ መታደስ መታሰቢያን በዓል በመንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ያከብሩ ነበር።
          በአዲስ ኪዳን ደግሞ ቤተ ክርስቲያን በማኅሌት እና በቅዳሴ የምታከብራቸው ዘጠኝ ዓበይት በዓላት እና ዘጠኝ ንዑሳን በዓላት አሉ። እነዚህም ብሥራት፥ ልደት፥ ጥምቀት፥ ደብረ ታቦር፥ ሆሳዕና፥ ስቅለት፥ ትንሣኤ፥ ዕርገት፥ ጰራቅሊጦስ እና የመስከረም መስቀል፥ ስብከት፥ ብርሃን፥ ኖላዊ፥ ግዝረት፥ ልደተ ስምዖን፥ቃና ዘገሊላ፥ ደብረ ዘይት፥ የመጋቢት መስቀል ናቸው። ሌሎችም የጌታ በዓላት አሉ። በእነዚህም የተከበሩና የተቀደሱ ዕለታት በሁሉ ማለትም በቅዳሴውም፥ በማኅሌቱም፥ በትምህርቱም የሚሰበከው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ከዚህም ጋር ቤተ ክርስቲያን የእመቤታችንን እና የቅዱሳንን በዓላት በታላቅ መንፈሳዊ ሥርዓት ታከብራለች። ይኽንንም የምታደርገው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው። ምክንያቱም እመቤታችን ከፍጥረታት ሁሉ በላይ የሆነችበትን ጸጋና ክብር ያገኘችው ለጌታ እናትነት በመመረጧ ነውና። ለዚህም ነው እግዚአብሔር የላከው ቅዱስ ገብርኤል፦ «ደስ ይበልሽ፥ ጸጋን የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺም ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ። . . . ማርያም ሆይ በእግዚአብሔር ዘንድ ጸጋን አግኝተሻልና፤» ሲለ ያመሰገናት። ሉቃ ፩፥፳፰፣፴። መንፈስ ቅዱስ ያደረባት ኤልሳቤጥም፦ «አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፥ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይደረግልኛል? እነሆ የሰላምታሽ ድምፅ በጆሮዬ በመጣ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና። ከጌታ የተነገረላት ይፈጸማልና ያመነች ብፅዕት ናት።» በማለት አመስግናታለች። ሉቃ ፩፥፵፫-፵፭። እርሷም፦ «እነሆ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤» ብላለች። ሉቃ ፩፥፵፰። ቅዱሳን መላእክትም ለመዳን የተመረጡትን የሚረዱት በእርሱ ስም ነውና። ይኽንን በተመለከተ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት፦ «የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩ ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል፤» ብሏል። መዝ ፴፫፥፯። ዕብ ፩፥፲፬። ቅዱሳን ነቢያትም ትንቢት የተናገሩት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና። ለዚህም ነው፥ ፊልጶስ፦ «ሙሴ በሕግ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉትን. . .  ኢየሱስን አግኝተነዋል፤» ያለው። ዮሐ ፩፥፵፮። ጌታም ከትንሣኤው በኋላ በኤማሁስ ጐዳና ያገኛቸውን ሉቃስንና ቀለዮጳን፦ «እናንተ የማታስተውሉ፥ ነቢያትም የተናገሩትን ሁሉ ልባችሁ ከማመን የዘገየ፤ ክርስቶስ ይህን መከራ ይቀበል ዘንድና ወደ ክብሩ ይገባ ዘንድ ይገባው የለምን?» ካላቸው በኋላ ስለ እርሱ ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ በመጻሕፍት የተጻፉትን ተርጉሞላቸዋል። ሉቃ ፳፬፥፳፭-፳፯። ለደቀመዛሙርቱም ተርጉሞላቸዋል። ሉቃ ፳፬፥፵፬-፵፯። ቅዱሳን ሐዋርያትም መከራውን ሁሉ ሳይሰቀቁ እስከ አጽናፈ ዓለም የሰበኩት ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። የሐዋ ፪፥፴፮፣ ፰፥፴፭፣ ፱፥፳፯፣ ፲፮፥፴፩። ጌታም አስቀድሞ «ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ፤» ብሎአቸዋል። የሐዋ ፩፥፰። ቅዱሳን ጻድቃንም ከዓለም ተለይተው፥ በገዳም ተወስነው፥ ግርማ ሌሊትን፥ ደምፀ አራዊትን፥ ጸብአ አጋንንትን ሳይሰቀቁ በገድል ሲቀጠቀጡ የኖሩት በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው።   ቅዱሳን ሰማዕታትም በመጋዝ የተተረተሩት፥ በሰይፍ የተመተሩት፥ በእሳት የተቃጠሉት በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው። አያሌ ተአምራትን ያደረጉትም በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው።  የሐዋ ፫፥፮። በመሆኑም ቅዱሳን በገድል የተቀጠቀጡት፥ ተአምራት ያደረጉትና የሚያማልዱትም በእርሱ ስም ስለሆነ ይህ ሁሉ የሚነገርበት በዓላቸው የሚሰብከው ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። በአጠቃላይ የቅዱሳን ሕይወታቸው የሚሰብከው ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። ምክንያቱም ቅዱሳን እርሱን መስለው ተገኝተዋልና። ፩ኛ ቆሮ ፲፩፥፩።
፱ኛ፦ በባህል ትሰብካዋለች፤
          ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ትርጉም ባለው ባህሏም የምትሰብከው ኢየሱስ ክርሰቶስን ነው። ለዚህም የምዕመናንን ሕይወት መመልከት ብቻ ይበቃል። ለምሳሌ ምዕመናን እንደ ባህል አድርገው በግንባራቸውና በእጃቸው ላይ የሚነቀሱት የመስቀል ቅርጽ የሚሰብከው የኢየሱስ ክርስቶስን ቤዛነት ነው። በተለይም እናቶቻችን በቀሚሶቻቸውና በነጠላዎቻቸው ላይ የሚጠልፉት በሐረግ የተንቆጠቆጠ የመስቀል ቅርጽ የሚሰብከው የመስቀሉን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። በየክብረ በዓሉ የምንለብሰው ነጩ ልብሳችንም የሚሰብከው የክርስቶስን ብርሃንነት ነው። ይህንን ልብስ ቅዱሳን መላእክት በጌታ ትንሣኤና ዕርገት ጊዜ ለብሰውት ታይተዋል። ዮሐ ፳፥፲፪፣ የሐዋ ፩፥፲። በአጸደ ነፍስ ያሉ ቅዱሳንም ልብሳቸው ነጭ ነው። ራእ ፮፥፲፩። የጌታም ልብስ በደብረ ታቦር እንደ ብርሃን ነጭ ሆኗል። ማቴ ፲፯፥፪። ለዘመን መለወጫ፥ ለመስቀል፥ ለደብረ ታቦር በዓላት የሚበራውም ችቦ የሚሰብከው የኢየሱስ ክርስቶስን ብርሃንነት ነው። ሌሎችም ይኽንን የመሰሉ የተቀደሱ ባህሎች አሉ።
፲ኛ፦ በሥርዓት ትሰብከዋለች፤
          ቤተ ክርስቲያን ለቅዳሴዋ፥ ለማኅሌቷ፥ ለመዝሙሯ፥ ለጾሟ፥ ለጸሎቷ ሁሉ ሥርዓት አላት። ምክንያቱሞ እግዚአ ብሔር የሚመለከው በዘፈቀደ ሳይሆን በሥርዓት ነውና። ጥንት በኦሪቱ ቤተ መቅደስ፥ እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠው ሥርዓት ነበር። በዚህም ምክንያት ለመብራቱ፥ ለዕጣኑ፥ ለመሥዋዕቱ፥ ለታቦቱ ወዘተ. . . ሥርዓት ነበረው። ይህንንም ሥርዓት «በምን አለበት?» የተላለፉትን ሰዎች እግዚአብሔር ቀጥቷቸዋል። ዘኁ ፲፮፥፩-፶፣ ኢያ ፮፥፲፰፣ ዘሌ ፲፥፩፣ ፩ኛ ሳሙ ፬፥፩-፳፪፣ ፪ኛ ዜና ፳፮፥፲፯፣ ፩ኛ ሳሙ ፮፥፲፱፣ ፪ኛ ሳሙ ፮፥፲፩፣ ፩ኛ ሳሙ ፲፥፭፣ ፩ኛ ሳሙ ፲፫፥፰፣ ዳን ፭፥፩-፴፩፣ የሐዋ ፭፥፩-፴፩፣ ፰፥፬-፳፬፣ ፲፱፥፲፩-፲፯። በአዲስ ኪዳንም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ በስምንተኛው ቀን ሥርዓተ ግዝረትን ለመፈጸም ወደ ቤተ ግዝረት ሄዷል። ይህንንም ሉቃስ ወንጌላዊ፦ «ሊገርዙት ስምንት ቀን በሞላ ጊዜ በማኅፀን ሳይረገዝ በመልአኩ እንደተባለ ስሙ ኢየሱስ ተብሎ ተጠራ።» ሲል ገልጦታል። ሉቃ ፪፥፳፩። አርባ ቀን በሞላውም ጊዜ ሥርዓት ለመፈጸም ወደ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ወስደውታል። ሉቃ ፪፥፳፪-፳፬። ዘጸ ፲፫፥፪፤ ዘሌ ፲፪፥፩። የአሥራ ሁለት ዓመት በሆነውም ጊዜ የፋሲካን በዓል ለማክበር እንደ በዓሉ ሥርዓት ወደ ኢየሩሳሌም ሄዷል። ሉቃ ፪፥፵፩። ሥርዓተ ጾምን ሲፈጽምም እንደነ ሙሴ እንደነ ኤልያስ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ጾሟል። ማቴ ፬፥፪፣ ዘጸ ፴፬፥፳፰፤ ፩ኛ ነገ ፲፱፥፰። ሥርዓተ ጥምቀትንም በዮርዳኖስ ፈጽሟል። ማቴ ፫፥፲፫-፲፯። በቃና ዘገሊላ ሠርግ ቤትም በመገኘት ሥርዓተ ተክሊልን ባርኳል። ዮሐ ፪፥፩-፲፩። ሥርዓተ ጸሎትንም ፈጽሟል። ሉቃ ፳፪፥፴፱-፵፮፣ የሐ ፲፩፥፵፭። ይኽንንም ያደረገው ምሳሌውን ትቶልን ለመሄድ ለአብነት ነው። ለዚህም ነው ጌታችን «ከእኔ ተማሩ፤» ያለው። ማቴ ፲፩፥፳፱። በተጨማሪም የደቀመዛሙርቱን እግር በማጠብ ሥርዓተ ትህትናን በፈጸመ ጊዜ «እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና፤» ብሎአል። ዮሐ ፲፫፥፲፭። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም «የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና። ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና።» ሲል ምዕመናንን አስተምሯል። ፩ኛ ጴጥ ፪፥፳፩።
          እንግዲህ ኢየሱስ ክርስቶስን አብነት አድርጋ ለሁሉ ነገሯ ሥርዓት ያላት ቤተ ክርስቲያን፥ በሥርዓቷ የምትሰብከው ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። ለምሳሌ ለሕፃናት ሥርዓተ ጥምቀትን ከፈጸመችላቸው በኋላ ስመ ክርስትና ትሰጣቸዋለች። ገብረ ወልድ፥ ተክለ ወልድ፤ ወለተ ወልድ፤ ገብረ ኢየሱስ፤ ወልደ ኢየሱስ፥ ኃይለ ኢየሱስ፥ አምኃ ኢየሱስ፤ ወለተ ኢየሱስ፥ አመተ ኢየሱስ፥ ፍቅርተ ኢየሱስ፥ ገብረ ክርስቶስ፤ ወለተ ክርስቶስ ወዘተ. . . ብላ ትሰይማቸዋለች። በዚህም የሚሰበከው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በምዕመናን አንገት ላይ የሚታሰረው ክርና መስቀሉም የሚሰብከው ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። በጸሎት ጊዜ ገጽን በትእምርተ መስቀል በማማተብና ነጠላን አመሳቅሎ በመልበስም የሚሰበከው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እንዲሁም ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት፦ «በቀን ሰባት ጊዜ አመሰግንሃለሁ፤» መዝ ፩፻፲፰፥ ፩፻፷፬ ሲል በተናገረው መሠረት ሰባቱ የጸሎት ጊዜያትም የሚናገሩት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ፩ኛ፦ ነግህ (ማለዳ)፦ ጌታችን በዚህ ሰዓት በጲላጦስ ፊት ቆሞ ተወቅሶበታል። ማቴ ፳፯፥፩። ፪ኛ፦ ሠለስት(ሦስት ሰዓት)፦ ጌታችን የተገረፈበት ሰዓት ነው፤ ዮሐ ፲፱፥፩። ፫ኛ፦ ቀትር (ስድስት ሰዓት)፦ ጌታችን የተሰቀለበት፥ መራራ ሐሞት የጠጣበት፥ልብሱን የተገፈፈበት ሰዓት ነው፤ ማር ፲፭፥፳፭። ፬ኛ ተሰዓት (ዘጠኝ ሰዓት)፦ ጌታችን ሰባቱን አጽርሐ መስቀል የተናገረበትና ቅድስት ነፍሱን ከክቡር ሥጋው በፈቃዱ የለየበት ሰዓት ነው። ማቴ ፳፯፥፶፣ ማር ፲፭፥፴፬። ፭ኛ ሠርክ (አሥራ አንድ ሰዓት)፦ ጌታችን ወደ ከርሠ መቃብር የወረደበት ሰዓት ነው፤ ማቴ ፳፯፥፷። ፮ኛ፦ ንዋም (የመኝታ ሰዓት)፦ ጌታችን ሥርዓተ ጸሎትን ያስተማረበት ሰዓት ነው፤ ማቴ ፳፮፥፴፰-፵፫። ፯ኛ፦ መንፈቀ ሌሊት፦ ጌታችን የተወለደባት፥ ሞትን ድል አድርጐ የተነሣባትና ዳግም የሚመጣባት ሰዓት ነው። ሉቃ ፪፥፰፣ ማቴ ፳፰፥፩፣ የሐዋ ፩፥፲፩።
፲፩ኛ፦ በፊደሎች ትሰብከዋለች፤
          ቤተ ክርስቲያን ቀርጻ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያበረከተቻቸው ከሀ - ፐ ያሉት ፊደሎች የሚሰብኩት ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። ለምሳሌ «ሀ» ብሂል፦ ሀልዎቱ ለአብ እምቅድመ ዓለም፤ የአብ አኗኗሩ ከዓለም በፊት ነው፤ «ለ» ብሂል፦ ለብሰ ሥጋ እምድንግል፤ ክርስቶስ ከድንግል ሥጋ ለበሰ፤ «ሐ» ብሂል፦ ሐመ ወሞተ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ አሥራ ሦስቱን ሕማማት በመስቀል ላይ ተቀብሎ ሞተ፤ «መ» ብሂል፦ መንክር ግብሩ ለእግዚአብሔር፤ የእግዚአብሔር ሥራው ድንቅ ነው፤ «ሠ» ብሂል ሠረቀ በሥጋ፤ በሥጋ ተገለጠ፤ «ረ» ብሂል፦ ረግዓት ምድር በቃሉ፤ ምድር በቃሉ ረጋች፤ «ሰ» ብሂል፦ ሰብአ ኮነ እግዚእነ፤ ጌታችን ሰው ሆነ፤ «ቀ» ብሂል፦ ቀዳሚሁ ቃል፤ ቃል በመጀመሪያ ነበረ፤ «በ» ብሂል፦ በትኅትናሁ ወረደ፤ ጌታችን በትህትና ከሰማየ ሰማያት ወረደ፤ ማለት ነው። ወዘተ . . .

Friday, September 2, 2011

ወደ ተራራው ሸሽተህ አምልጥ ዘፍ.19÷18

                                                                                                                                                             በቀሲስ ለማ በሱፍቃድና
                                                                                                                                                             በመ/ር መንግስተ አብ አበጋዝ


...ይህ ኃይለ ቃል ለታላቁ ጻድቅ ለሎጥ የተሰጠ መመሪያ ነው፤የሰዶም ከተማ ነዋሪዎች በግብረ ሰዶም /ወንድና ወንድ መጋባት/ ኃጢአት የታወቁ ነበሩ፡፡ በዚህ ምክንያት እግዚአብሔርከተማዋን ያጠፋት ዘንድ አሰበና ሁለቱን መላእክት ላከ፡፡ ከማጥፋቱም በፊት ደጋግ ሰዎች አብረው እንዳይጠፉ መላእክቱ ያወጧቸው ዘንድ ስለሚገባ ሎጥን ከነቤተሰቡ እንዲህ አሉት «ራስህን አድን ወደኋላ አትይ በዚህም ዙሪያ ሁሉ አትቁም እንዳ ትጠፋም ወደተራራው ሸሽተህ አምልጥ» ብለው ከዚያ እንዲወጣ አድርገውታል፡፡ጻድቁ ሎጥም ወደ ተራራ በመሸሽ ከነቤተሰቡ መዳኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ይነግሩናል፡፡


እንግዲህ ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ስለተራራዎች ታሪካዊነት በስፋት ተጽፏል ድንቅ ድንቅ ሥራዎች የተሠሩባቸው ተራራዎች አሉ፡፡ ከእነዚህም ደብረሲና በግብፅ በስተምሥራቅ ከእስራኤል ደግሞ በስተደቡብ ይገኛል የእግዚአብሔር ተራራ ደብረ ኮሬብም ይባላል /ዘዳ 3÷1/፡፡

የሞርያ ተራራ አብርሃም ልጁ ይስሐቅን ይሠዋ ዘንድ መሠውያ ያዘጋጀበት ታላቅ ድንቅ ምስጢር የተገለጠበት ተራራ ነው፡፡ እነዚህ በብሉይ ኪዳን ድንቅ ሥራ ከተሠራባቸው ተራራዎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

በሐዲስ ኪዳን በጎ ሥራ የተሠራበት ተራራ ደግሞ ደብረ ዘይት የወይራ ዛፍ የበዛበት ተራራ ሲሆን በጣም ከፍታ ያለው ተራራ ነው፡፡ ጌታችን በዘመነ ሥጋዌው ቀን ሲያስተምር ውሎ ማታ የሚያድረው በዚህ ተራራ ላይ ነበር ፤ ነገረ ምጽአትንም ያስተማረው በዚህ ተራራ ላይ ነው /ማቴ.24÷1/፡፡ በተራራው ላይ ሆኖ ኢየሩሳሌምን፣ ኤዶምያስን ሞአብን ቁልጭ አድርጐ ማየት ይቻላል፡፡

ይህ ተራራ በብሉይ ኪዳንና በሐዲስ ኪዳን ታላላቅ ድንቅ ድንቅ ሥራዎች ተሠርተውበታል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊትም የዚህን ተራራ ታላቅነት ሲገልጥ «ታቦር ወአርሞንኤም በስመዚኣከ ይትፌሥሑ ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል» በማለት በተራራው አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች በእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ እንደሚደሰቱ ለመግለጽ በተራራዎቹ አንጻር ተናግሯል፡፡

በዚህ ተራራ ላይ ባርቅና ዲቦራ የእስራኤል ጠላት የነበረውን ሲሳራን ድል አድርገውበታል፡፡ «የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሔደህ ወደ ታቦር ተራራ ውጣ ከአንተ ጋር ከንፍታሌምና ከዛብሎን ልጆች አሥር ሺሕ ሰዎች ውሰድ ...» በማለት በእግዚአብሔር ትእዛዝና አጋዥነት ጠላትን ድል ያደረጉበት ተራራ ነው፡፡

ደብረ ታቦር በሐዲስ ኪዳን

ይህ ተራራ እንደ ብሉይ ኪዳን ሁሉ በሐዲስ ኪዳንም ድንቅ ሥራ ተሠርቶበታል፡፡ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የክብሩን ብርሃን /ብርሃነ መለኮቱን/ የገለጠው በዚሁ ተራራ ላይ ነው /ማቴ.17÷1-9/ በቂሳርያ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያትን ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደሆነ ይሉታል) /ማን ይሉታል፡፡/ ብሎ በጠየቀ ከስድስት ቀን በኋላ ከሐዋርያት ሦስቱን ማለትም ጴጥሮስን ያዕቆብንና ወንድሙ ዮሐንስን/ ይዞ ወደ ረጅም ተራራ አወጣቸው ከብሔረ ሕያዋን ነቢዩ ኤልያስን ከብሔረ ሙታን ደግሞ ነቢዩ ሙሴን አመጣቸው በፊታቸውም ተለወጠ ፊቱም እንደፀሐይ በራ ኤልያስና ሙሴ ከፈጣሪያቸው ጋር ሲነጋገሩ ታዩ፡፡

ከነቢያት ሁለቱ ከሐዋርያት ደግሞ ሦስቱ በድምሩ አምስቱም አንድ ላይ ሆነው ቅዱስ ጴጥሮስ ባየ ጊዜ እንዲህ አለ «ሠናይ ለነ ሀልዎ ዝየ» በዚህ መኖር ለኛ መልካም ነው አለ፡፡ ከዚህ በላይ የሚያስደስት ነገር የለምና ሁልጊዜ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ሲሆን ደስተኛ ይሆናል ከጭንቀቱም ይረጋጋል ይህም ምሳሌ ነው፡፡

ተራራ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ናት

በቤተክርስቲያን ብሉያቱ ሐዲሳቱ ይነገርባታል ይፈጸምባታል ሁሉም አንድ ሆኖ ያገለግላታል ይገለገልባታል የታመመ ይፈወስባታል የሞቱ ሕያዋን ይሆኑባታል፡፡

ጌታችንም ከብሉይ ኪዳን ሙሴንና ኤልያስን ከሐዲስ ኪዳን ሦስቱን ሐዋርያት ያመጣው ሁለቱም ኪዳናት ብሉይና ሐዲስ በቤተክርስቲያን አገልግሎታቸው እንደሚቀጥል ለማሳየት ነው፡፡

በብሉይ ኪዳን ዘመን ባርቅና ዲቦራ ሲሳራን ድል እንዳደረጉበት በአዲስ ኪዳንም ጌቶችን ደቀመዛሙርቱን ሲፈታትን የነበረውን ዲያብሎስን ድል ነስቶበታል /አድርጐበታል/፡፡ ቅድስት ቤተክርስቲያንም አጋንንትን ኑፋቄን /ጥርጥርን/ ድል እናደርግ ዘንድ ታስችለናለች፡፡ «ወኮነት ደብረ ታቦር አምሳለ ቤተክርስቲያን እስመ አስተጋብአት ውስቴታ እምነ ብሉይ ወሐዲስ፤ ደብረ ታቦር የቤተ ክርስቲያን አምሳል ሆነች ከብሉያትና ሐዲሳት በውስጧ ሰብስባለችና» እንዲል፡፡ በደብረ ታቦር በቅዱስ ጋብቻ የጸኑ እና ደናግል እኩል በፈጣሪያቸው ፊት መቆማቸውንም እናያለን፡፡በቤተክርስቲያንም ደናግል መነኮሳትም ሕጋውያን ካህናትም አንድ ሆነው ያለ ልዩነት የሚያገለግሉባት ቅድስት ቤት መሆኗን ለማጠየቅ ለመግለጽ ነው፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ «በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህንን ድምፅ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን፤» /’ጴጥ.1÷18/ በማለት እንደተናገረው፡፡
ሰው ሁልጊዜ መነሻውና መድረሻው ቤተ ክርስቲያን ከሆነ የሚሰማው ድምፅ ለሕይወተ ሥጋ ወነፍስ የሚበጅ ነው በቤተ ክርስቲያን አዘውትሮ መገኘት ወደዚያም መሸሽ ከእግዚአብሔር ጋር መኖር ነውና፡፡ጌታችንም ከብሉይ ኪዳን ሙሴንና ኤልያስን ከሐዲስ ኪዳን ሦስቱን ሐዋርያት ያመጣው ሁለቱም ኪዳናት ብሉይና ሐዲስ በቤተክርስቲያን አገልግሎታቸው እንደሚቀጥል ለማሳየት ነው፡፡

በብሉይ ኪዳን ዘመን ባርቅና ዲቦራ ሲሳራን ድል እንዳደረጉበት በአዲስ ኪዳንም ጌቶችን ደቀመዛሙርቱን ሲፈታትን የነበረውን ዲያብሎስን ድል ነስቶበታል /አድርጐበታል/፡፡ ቅድስት ቤተክርስቲያንም አጋንንትን ኑፋቄን /ጥርጥርን/ ድል እናደርግ ዘንድ ታስችለናለች፡፡ «ወኮነት ደብረ ታቦር አምሳለ ቤተክርስቲያን እስመ አስተጋብአት ውስቴታ እምነ ብሉይ ወሐዲስ፤ ደብረ ታቦር የቤተ ክርስቲያን አምሳል ሆነች ከብሉያትና ሐዲሳት በውስጧ ሰብስባለችና» እንዲል፡፡ በደብረ ታቦር በቅዱስ ጋብቻ የጸኑ እና ደናግል እኩል በፈጣሪያቸው ፊት መቆማቸውንም እናያለን፡፡በቤተክርስቲያንም ደናግል መነኮሳትም ሕጋውያን ካህናትም አንድ ሆነው ያለ ልዩነት የሚያገለግሉባት ቅድስት ቤት መሆኗን ለማጠየቅ ለመግለጽ ነው፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ «በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህንን ድምፅ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን፤» /’ጴጥ.1÷18/ በማለት እንደተናገረው፡፡
ሰው ሁልጊዜ መነሻውና መድረሻው ቤተ ክርስቲያን ከሆነ የሚሰማው ድምፅ ለሕይወተ ሥጋ ወነፍስ የሚበጅ ነው በቤተ ክርስቲያን አዘውትሮ መገኘት ወደዚያም መሸሽ ከእግዚአብሔር ጋር መኖር ነውና፡፡

ተራራ የወንጌል ምሳሌ ናት

ወደተራራ ላይ ሲወጡ ይደክማል መንገዱም ያስቸግራል፡፡ ከዚህ የተነሣ ብዙ ሰው ወደ ተራራ ለመውጣት ያለው ፍላጎት ዝቅተኛ ነው፡፡ትልልቅ ተራራ ላይ ያሉትን ገዳማትና አድባራትን ለመሳለም ለመጐብኘት ያለው ፍላጐት ዝቅተኛ የሚሆነውም ለዚህ ነው፡፡
ከተራራው ላይ ከተወጣ በኋላ ግን ደስ ይላል፡፡ አየሩም ቀዝቀዝ ያለ ነው፤ድካሙ ሁሉ ይረሳል ከተራራው ላይ ሆነው ግራና ቀኝ ከተማዎች፣ መንደሮች፤ የመሳሰሉት ሲታዩ ያስደስታሉ፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ወንጌልም ሰ !ማሯት ታስቸግራለች ቶሎ ግልጽ አትሆንም ለማወቅ ለመረዳት ድካም ትጠይቃለች፡፡ ምስጢሩን መጠየቅ መላልሶ መማር ...ያስፈልጋል፡፡ ከተማሩ በኋላ ግን ደስ ታሰኛለች፡፡ ሁሉም ነገር ቀላል መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

ተራራ የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ናት

ከተራራ ላይ መውጣት ብዙ ድካም እንዳለው ሁሉ መንግሥተ ሰማያትንም ለመውረስ ብዙ ድካም አለ፡፡ ወደ ተራራ ላይ ሲወጣ በቀስታ በእርጋታ በማስተዋል በመጓዝ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ 12÷2፡፡በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ በማለት እንደተና ገረው መንግሥተ ሰማያት ለመውረስ አንዱና ትልቁ መሣሪያ ትዕግሥት ነው፡፡
ሁሉም ምሳሌዎች ምስጢር አላቸው የደብረ ታቦርንም በዓል ስናከብር የተራራውን ምስጢር በተራራው ላይ የተገኙትን የሁለቱን ነቢያትና የሦስቱን ሐዋርያት ምስጢራዊ ምክንያት፣ የተነገረውን ትንቢታዊ ቃል በማስታወስ መሆን አለበት፡፡ በተራራው ላይ የተፈጸመውን ድንቅ ነገር፣ ከነቢያትና ከሐዋርያት መታደመም ጋር የተከናወነውን ምስጢር በማስተዋል መረዳት ከቻልን በዓሉን ማክበራችን ትርጉም እንዳለው እንረዳለን፡፡

መጽሐፋዊ ትውፊቱ

ቡሄ፡- ቡሄ ማለት ብራ ብርሃን ደማቅ ማለት ነው፡፡ ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት በዓል የሚዘከርበት፤ እና ለበዓሉም ችቦ ስለሚበራ የብርሃን በዓል ለማለት የቡሄ በዓል እንላለን፡፡

ወቅቱ የክረምት ጨለማ አልፎ የብርሃን ወቅት፤ ሰማይ ከጭጋጋማነት ወደ ብሩህነት የሚለወጥበት፤ የመሸጋገሪያ ወቅት ነው፡፡ «ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፣ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት» እንዲሉ፡፡ በሌላ በኩልም «ቡኮ/ሊጥ» ተቦክቶ ዳቦ የሚጋገርበት «ሙልሙል» የሚታደልበት በዓል በመሆኑ ቡሄ ተብሏል፡፡

ጅራፍ

በደብረ ታቦር በዓል በትውፊታዊ መልኩ የሚታየው ምስጢር በኢየሩሳሌም ስለሚሆነው የጌታችን ምስጢራዊ ሞቱ ነው፡፡ ጅራፍ መግመድ እና ጅራፍ ማጮኽ ሁለት ዓይነት ምስጢር ይዞ የሚከወን ትውፊታዊ ተግባር ነው፡፡ የመጀመሪያው ግርፋቱን እና ሞቱን እናስብበታለን፡፡ እንዲሁም ድምፁን ስንሰማ የባሕርይ አባቱን የአብን ምስክርነት ቃል፣ እንደ ነጎድጓድ ድምፅ ያስታውሰናል፡፡
የጅራፍን ትውፊታዊነት /ውርስ/፣ መጽሐፋዊ ትምህርትና ምስጢር ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ ጨዋታውን በተራራማ አካባቢ፣ ከመኖሪያ ቤት ርቆና፣ በሜዳ ማድረጉ ጠቃሚ ነው፡፡ ጅራፍን በርችት መቀየር የሚያመጣውን የምስጢር ተፋልሶ ብቻ መመልከት ከማኅበራዊ ጎጂ ገጽታው በላይ እንድናስወግደው ያስገድደናል፡፡

ችቦ

ችቦ የጌታችንን ብርሃነ መለኮት መገለጥ የሚያመለክት ነው፡፡ በመሆኑም ችቦ ለኩሰን በዓሉን እናከብራለን፡፡ የዚህ ትውፊታዊ የትመጣ ግን በብርሃኑ ድምቀት የቀኑን መምሸት ያልተረዱ እረኞች በሜዳ ቀርተዋልና ወላጆች ከመንደር ችቦ ለኩሰው ልጆቻቸውን ፍለጋ ሔደዋልና ታሪኩን እያዘከርን በዓሉን እናከብራለን፡፡

የችቦው መንደድም ሌላ ትርጉም አለው፡፡ አንድ ምእመን ለሌላው ምእመን መካሪ አስተማሪ መሆኑን፤ መከራ እየተቀበለም አርአያ ምሳሌ ብርሃን መሆኑን ያሳያል፡፡ በሃይማኖትም አርአያ ምሳሌ ይሆንላቸዋል፡፡

ሙልሙል

በችቦ ብርሃን ልጆቻቸውን ፍለጋ የወጡ ወላጆች ዳቦ ጋግረው ይዘውላቸው ወጥተዋል፡፡ ስጦታው ቤተሰባዊነትን፣ ፍቅርንና መተሳሰብን መግለጫ ነው፡፡ ወደ ቤታችን «ቡሄ» እያሉ ለሚመጡ አዳጊዎችም ዘምረው እንዳበቁ የሚሰጥ «ሙልሙል» ዳቦ አለ፡፡ በምሳሌ ሐዋርያት ምስራች ሊነግሩን፣ ወንጌል ሊሰብኩን በደጃፋችን ቆመው «ቡሄ በሉ» የሚሉንን አዳጊዎች የሚበሉትን መስጠታችን ምሳሌያዊ /መጽሐፋዊ/ ነው፡፡ ጌታችን ደቀመዛርቱን ባስተማራችሁበት፣ በደረሳችሁበት ተመገቡ ብሏቸዋል፡፡ /ማቴ 10.12/ ሕፃናቱም ሊዘምሩ ሲመጡ ዳቦ መስጠት ልማዳዊ ብቻ አይደለም፡፡ ሕፃናቱ የደቀመዛሙርት ምሳሌ ናቸው መዝሙራቸው ደግሞ ሐዋርያት «የምስራች» ይዘው የመምጣታቸው ምሳሌ ነው፡፡

ሐዋርያት በገቡበት አገር አስተምረው አጥምቀው የጸጋ ልጅነትን አሰጥተው በረከት አድለው እንደሚሔዱም፤ ልጆችም ዘምረው፣ አመስግነው፣ መርቀው «ውለዱ ክበዱ፤ ሀብተ አግኙ፣ የመንግሥተ ሰማያት ወራሾች ያድርጋችሁ. . .» ይላሉ፡፡

በአጠቃላይ በዓለ ደብረ ታቦር ከነዚህ ምስክር ካላቸው ትምህርቶቹ፣ ምስጢር ከሚራቀቅባቸው ትርጓሜያቱና ከትውልድ ትውልድ በቅብብል ከተላለፈው ቅዱስ ትውፊት ጋር ሃይማኖታዊ ባሕል ሆኖ ሊቀጥል ይገባዋል፡፡ ይህን ማድረግ የሚቻለው ግን አዳጊዎች ሃይማኖታዊ ትውፊቱን ይዘው እንዲያድጉ ጥቆማ በመስጠት፣ ግጥም በመግጠምና ምስጢሩን በማብራራት የመጀመሪያዎቹ ባለድርሻዎች ወላጆች ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የሚሰሙ ግጥሞች ስድብ፣ ፌዝና ሥላቅ የተቀላቀለባቸው ይሆናሉ፡፡ ሕፃናቱም ዝማሬውን ሲጀምሩ «ከሰጡን እንነሣ ከነሱን እናርዳ» ብለው ይጀምሩታል፡፡ከሰጡን እንመርቃለን ካልሰጡን እንራገማለን በማለት፡፡አሳሳቢው ነገር ደግሞ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ወደ ገንዘብ ማግኛነት የቀየሩ ሁኔታዎች መታየታቸው ነው፡፡ ዳቦ /ሙልሙል/ ትምህርቱንም፣ ምስጢሩንም፣ ትውፊቱንም በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል፡፡
ቤተክርስቲያን የምስጢር ግምጃ ቤት ናት የምታከናውነውን ሁሉ ከበቂ መረጃ ጋር ነው ተግባራዊ የምታደርገው፡፡ በተለይ ወጣቱ ክፍል ይህንን አውቀን ተረድተን ለቀሪው ትውልድ ማስተላለፍ እንችል ዘንድ ከክፉ ጠላት ከሰይጣን ፈተና፣ በሽታ ከመሳሰሉት ችግሮች ለመዳን ወደ ተራራዋ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመሸሸ ከክፉ ነገሮች ሁሉ ማምለጥ ይቻላል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር የሚጠለሉ ሁሉ ዕድሜያቸው ይረዝማል፡፡ አስተዋዮችም ይሆናሉ ሁሉን ማየትና የሚጠቅማቸውን መምረጥ ይችላሉ በሥነ ምግባር የታነፁ አገርንና ወገንን የሚጠቅሙ ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያን በመጠጋት ከክፉ ሁሉ የሚያመልጡ ይሆናሉ ለዚህም የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡
የአምላካችን ቸርነት አይለየን

አርጋኖን ዘሃሙስ : ምዕራፍ 1

በዕብራይስጥ ማሪሃም የተባልሽ የተመረጽሽ ድንግል እመቤቴ ማርያም ሆይ መላእክትን ለፈጠረ በኪሩቤል ላይ ለሚቀመጥ እናቱ ለምኝልኝ፡፡፪. ከሚያሰጥም ባሕር ማዕበልም ሞገድ፡፡ ከከበደ ዓለም ኅልፈት ጥፋት በጸሎትሽ አድኝኝ፡፡፫. አምላክን የወለድሽ ድንግል ሆይ በላዬ ያደረውን የኃጢአቴን ሽታ አርቂው፡፡ በጸሎትሽም መዓዛእንደ ኪሩቤል ዕጣን ሽታ እንደ ሱራፌልም ጽንሐሕ ጸሎቴ ደግሞ ያማረ የተወደደ እግዚአብሔርምየተቀበለው ይሁን፡፡፬. ምስጋናን የተመላሽ ድንግል ሆይ እንዳልወድቅ ከመሰናክል አድኝኝ ደግፊኝ፡፡ ጥልቅቅ የሚያደርግአእምሮ የሚያሰጥ ወይን መጠጥን እንደጠጣ ልቤ ዕውቀት አጥቷልና፡፡፭. ሕጉን ትእዛዙን ለመጠበቅ እያሰብሁ ሌሊቱን ሁሉ እደክማለሁ፡፡ ጥቂትም ቆይቶ አናዋዋርየሚለውጥ ሐሳብ ይመጣብኛል፡፡ የዚህን ዓለም ማሠሪያ ከኔ ቁረጭው ሰውነቴ በርሱ ገመድ ተይዟልናለርሱም ከገዛት ነጻ አድርጊኝ፡፡፮. ጸጋ ክብርን የተመላሽ ድንግል ሆይ ከመግፋት ከመገፋት አድኝኝ፡፡ ቅድስና የተመላሽ ድንግል ሆይከመበደል ሌላውንም ከመበደል አድኝኝ፡፡ ከደም አፍሳሽ አድኝኝ፡፡ እኔም ደግሞ የሌላውን ደምከማፍሰስ ሠውሪኝ፡፡፯. የተድላ መፍሰሻ ድንግል ሆይ ከሽንገላ አድኝኝ፡፡ ከሸንጋይም ደግሞ ሠውሪኝ፡፡ የምስጋና መፍሰሻድንግል ሆይ ከሽሙጥ ከስድብ ከሚያስሽሟጥጥና ከሚሰድብ ደግሞ ሠውሪኝ፡፡ተድላ መፍሰሻ ድንግል ሆይ ከሽንገላ አድኝኝ፡፡ ከሸንጋይም ደግሞ ሠውሪኝ፡፡ የምስጋና መፍሰሻድንግል ሆይ ከሽሙጥ ከስድብ ከሚያስሽሟጥጥና ከሚሰድብ ደግሞ ሠውሪኝ፡፡፰. የባለ ጸግነትና የክብር መፍሰሻ ድንግል ሆይ ሰውን ከሰው ከማጣላት አድኝኝ፡፡ ሰውን ከሰውከሚያጣላ ሐሰተኛ ደግሞ ሰውሪኝ የሕይወት የመድኃኒት ምንጭ ሆይ ከቂምና ከቅናት አድኝኝ ከቂመኛከቀናተኛ ደግሞ አድኝኝ፡፡፱. የፈውስ መቅጃ የበረከት አዘቅት ድንግል ሆይ ከፀብ ከክርክር አድኝኝ፡፡ ከሚጣላና ከሚከራከርአድኝኝ፡፡ እሳት የሚለብሱ ኪሩቤልና ሱራፌል በመብረቅ ክንፍ የሚጋርዱሽ የንጉሠ ነገሥት ማደሪያየምትሆን የብርሃን ድንኳን ሆይ፡፡ በሕይወት በመድኃኒት ጋሻ ጋርጅኝ ከአጋንንት ፍላፃ እንድድን፡፡፲. ይቅር ባይ በሆነ ልጅሽም መጋረጃ ሸፍኝኝ፡፡ ሰወን ከሰው ማጣላትን ከተመላ ከመላስ ነገርእንድሠወር አጥሯ ቅጥሯ የማይፈርስ መሠረቷ የማይናወጽ ለዘለዓለም ጸንታ የምትኖር አዳራሽ ሆይ፡፡የመሃይምናን መኖሪያ ወደሚሆን ዕድል ፈንታዬን ጽዋ ተርታዬን ገነት መንግሥተ ሰማያትንአድርጊልኝ፡፡፲፩. ድንግልና አበባን በቅድስናም የበረከት ፍሬን ያፈራች የወይን ቦታ ሆይ፡፡ ንስሐ ፍሬን እንዳፈራንጹሑንም መሥዋዕት እጅ መንሻ አድርጌ ለልጅሽ እንዳቀርብ አድርጊልኝ ለበጎ ሥራም የዋህ ልቡናትሑት ሰብና ስጭኝ፡፡፲፪. ከምድር እስከ ሰማይ የትምደርስ የወርቅ መሰላል ሆይ የመለኮት አንድነት ሦስትነት ወዳለበት፡፡ምሕረት ምንጭ ወደሚቀዳበት ጸሎቴን አሳርጊልኝ፡፡ ጽዋ ተርታዬን ዕድል ፈንታዬንም ይቅር መባልአድርጊልኝ፡፡ ነገር ግን በፍርድ አይደለም ባንቺ በረከት በማቸነፍ ነው እንጂ፡፡፲፫. የልዑል እግዚአብሔር የበኩር ልጁ የጌትነቱ መሣሪያ የብርሃን መጋረጃ ድንግል ሆይ ከክፉ ዕለትከጥፋት ሰዓት በቀን ከሚወረወር ጦር በጨለማም ሌሊት ከሚመላለስ ነገር ሠውሪኝ፡፡፲፬. ከዓውሎ ነፋሰ የተነሣ ምዕመናንን የምታሻግር የመድኃኒት ድልድይ የድኅነት መርከብ ሆይከኃጢአት ማዕበል ሞገድ አሻግሪኝ መርከብ ሰውነቴን እንዳያነዋውፀው፡፡፲፭. የንጹሓን የደናግል መመኪያቸው ንጽሕት ድንግል ሆይ ከኃጢአት ርኩሰት ከማመንዘርም መተዳደፍንጹሕ አድርጊኝ የቅዱሳን ሁሉ መመኪያቸው ቅድስት ድንግል ሆይ በልጅሽ ደም ንጹሕ አድርጊኝ፡፡በበህር ልጅኝ በጎኑ ፈሳሽ የጸዳሁ አድርጊኝ፡፡፲፮. ደስ ያላቸው የምእመናን ሁሉ መመከያቸው ፍሥሕት ድንግል ሆይ ለዘለዓለም በማያልቀው በልጅሽደስታ ደስ አሰኝኝ ያለ ርኩሰት የሠርግ ቤት የመንፈስ ቅዱስ ሙሽራ የመለኮት ዙፋን ድንግል ሆይ፡፡ልቡናዬን ከምታረክሰው ነፍሴንም ከምትጠብሳት ከሥጋ ፈቃድ ንጹሕ አድርጊኝ፡፡፲፯. እንደ ባሕር ከጠለቀው ርኩስ ሣቅ ጨዋታ ከክፉውም ከሴሰኝነት ማዕበል ሞገድ የምታሻግር የወርቅመሰላል ድንግል ሆይ ከዕዳ በደል ረግረግ አሻግሪኝ፡፡፲፰. ኖኅ ከማየ አይኅ ረግረግ የዳነባት መርከብ ድንግል ሆይ የሰው ሁሉ ልጆች ከሚመጣው መቅሠፍረግረግ የዳነባት መርከብ ድንግል ሆይ የሰው ሁሉ ልጆች ከሚመጣው መቅሠፍትፈግረግ አውጭኝ በኃጢአት እንደኔ የረከሰ ሰው የለምና ዘፍጥረት ፯፣ ፳፫፡፡፲፱. በጎ ሥራዬም ሁሉ እንደ ግዳጅ ጨርቅ ነው፡፡ ርኩሰቴም ደግሞ ከደመ ሕርስ ሁሉ እጽፍ ድርብእንደሚሆን የወለደች ሴት ርኩሰት ሁና እንደምትሰነብት እንደ ሰባቱ ቀር ርኩሰት ያለ ነው፡፡፳. ለመንጻቴ ማንን እጠራለሁ፡፡ ቁስሌንስ ለመፈወስ ወደ ማን እጮሃለሁ የኃጥአን ዕዳ በደላቸውንጹሕ መሆና የቁስለኞችም የቁስላቸው መፈወሻ ከምትሆን ካንቺ ሌላ፡፡፳፩. ከልጅሽ ሌላ ባለመድኃኒት አልሻም፡፡ ከጸሎትሽም ረዳትነት በቀር ደግሞ ኃጢአቴንየሚያስተሠረይልኝ አልፈልግም፡፡ ንጽሕት ሆይ ከርኩሰቴም ከዕዳም በደሌም ሁሉ ንጹሕ አድርጊኝ፡፡ከሥጋና ከነፍስ ቁስሌም ፈውሽኝ፡፡፳፪. ለደዌ መድኃኒት ይሹለታል ለቁስልም አቃቄር መልካሙን ቅመም ይፈልጉለታል የኃጢአት ቁስልግን ያለ ልጅሽ ፈቃድ አይጠግም፡፡

ሶስቱ ምክሮች


ባንድ ወቅት ባልና ሚስት አብረው ሲኖሩ በማህላቸው ልዩ የሆነ ፍቅር
ነበራቸው፡፡ ሁለት ልጆችም ነበራቸው፡፡ በቤታቸው የሚላስ የሚቀመስ
በመጥፋቱ ይህንን ችግር ለዘለቄታው ለመፍታት ባል ራቅ ብሎ ሊሰራ
ተስማምተው፤ ባል ራቅ ወዳለ ከተማ ሄዶ መስራት ጀመረ፡፡ በተከታታይ ለ
13 ዓመታት ሰራ ከዚያም ወደናፈቁት ቤተሰቦቹ ለመሄድ ተነሳ፡፡
ያልገመተው ነገር ከቀጣሪዎቹ ምን?
ደሞዝ፡ ደሞዙ ምን ሆነ? በተለያየ ምክንያት
ተቆራርጦ ከሚጠብቀው ከግማሽ በታች የሆነውን 3000 (3 ሺ) ተሰጠው፡፡
ምን ያድርግ? ተመልሶ እዛው ስራውን ይቀጥል? ወደ ናፈቁት
ቤተሰቦቹ ይሂድ? ይቻላል ግን ተመልሶ ቢሰራ ደሞዙ መቆራረጡ አይቀሬ
ነው፣ ወደ ቤተሰቦቹ እንዳይሄድ በ13 ዓመት ይህን ብቻ ሰራሁ ቢል ማን
ያምነዋል? ሰለዚህ ሌላ ቦታ ለመስራት ወሰነ ጉዞ ---------------- አንድ አባት
አገኘ --------“ወዴት ትሄዳለህ ልጄ ምንስ ትፈልጋለህ?” አሉት፣ አሱም
ሁሉንም ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ነገራቸው፡፡ አኝህ አባት አንዲህ
አሉት “እንግዲያውስ የምትፈልገውን ማግኘት ቀላል ነው፡፡” እሱም "እነዴት
አባቴ?" ሲል ጠየቃቸው እሳቸውም "በል አንድ ሺ ብሩን አምጣና
እነግርሀለሁ" አሉት የቸገረው ነውና ነገሩ አሱም አንስቶ አነድ ሺ ብሩን
ይሰጣል እኝህ አባትም "አቆራጭ ነው ብለህ በማታውቀው መንገድ አትሂድ"
ይሉታል፡፡ "ሁለተኛውን ሺ አምጣና ሁለተኛውን መንገድ ልንገርህ" ይሉታል
አሱም በየዋህነት ሁለተኛውን ሺ ይሰጣል ፣ "በማያገባህ አትግባ"
ይሉታል፡፡ "ይህው ነው አባቴ" ቢላቸው "አዎን ልጄ ይልቁኑም 3ኛውን
አምጣና በጣም አስፈላጊውንና የመጨረሻውን ስጦታዬን ልሰጥህ" አሉት፡፡
ሰጠ፡፡ እሳቸውም "ክፉ ለማድረግ አትቸኩል" ብለው "በል ልጄ በቀጥት
ወደ ቤትህ ሂድ" ብለው በባዶ ኪስ ግን ከሱሰት ምክሮች ጋር አሰናበቱት፡፡
እሱም ጉዞውን ወደ ቤቱ አደረገ፡፡ በመንገድ ነጋዴዎች አግኝቶ እያወጋ ሲጎዝ
መሸ ነጋዴዎቹ ለምን ባቆራጭ አንሄድም በማለት ጉዞ ጀመሩ አሱም
አብሯቸው ጉዞ እንደጀመረ የኛ አባት ምክር ትዝ አለው "አቆራጭ ነው ብለህ
በማታውቀው መንገድ አትሂድ" የሚለው ስለዚህ ተመልሶ በሚያውቀው
መንገድ ተጉዞ ብቻውን ከጨለመ ከተማ ገባ፡፡ "የመሸበት አንግዳ ንኝ
አሳድሩኝ" ማለት ጀመረ----------አነድ ሰው ተጠግቶት "የውልህ ወንድሜ አዛ
ሰው ቤት ሂድ ያሳድርሀል ነገር ግን እዛ ሰው ቤት የገባ አይወጣም
ለማንኛውም አድልህን ሞክር" አለው፡፡ አሱም የተባለበት ቤት አንኮክቶ "ቤት
የእንግዳ" ነው ተብሎ ገባ፡፡ ታዲያ ከቤቱ ባለቤት ጋር ሲያወጉ ከየት
እንደመጣ ቢነግረው ባለቤቱ ተገርሞ "አነዴት ሆነህ ተረፍክ? በል" ቢለው ባለ
ፀጋው "ከመኑ?" አለ እንግዳው “ምነው ባልከው መስመር ይመጡ የነበሩ
ነጋዴዎች ተዘርፈው ግማሾቹም ተገለው ዘሬ ከተማው ለቀሶ ብቻኮ ነው፡፡”
ትዝ አለው ያቺ በአንድ ሺ ብር የገዛት ምክር በብር የማትገዛው ሕይወቱን
አተረፈችለት ማለት ነው፡፡ ስለ መሽ የቤቱ አመቤት ምግብ ለእንግዳው
ልታቀርብ ከጎዳ ብቅ አለች "ጥያችሁ ጠፋሁ አደል?" አለች፡፡ እንግዳው
አይኑን ማመን አልቻለም የተወሰነ አካሏ ብቻ ነው ሰው የሚመስለው በዛላይ
ማስፈራቷ ወደ ጎዳ አስክትገባ ናፈቀ "ከዚህች ጋር አነዴት ትኖራለህ?" ብሎ
አስኪጠይቅ፡፡ ወደ ጎዳ ገባች ሊጠይቅ ሲል አነድ ነገር ትዝ አለው የኛ አባት
ምክር "በማያገባህ አትግባ" የሚለው፡፡ ሆዱ መጠየቅ አየፈለግ ፍላጎቱን
ተቐቌሞ አደረ ፡፡ ደግሞ ሌላ ፈተና የቤቱ ባለቤት ከመሄድህ በፊት የማሳይህ
ነገር አለኝ ብሎ ወደ ጓሮ ወሰደውና የሰው አፅም የሞላበት ሜዳ አሳየው
አንግዳውም "ይሄ ደሞ ምንድነው?" ማለት ፈልጎ ነበር ግን በማያገባህ አትግባ
ብሎ ራሱን፤ራሱን አየነቀነቀ ዝም አለ፡፡ የቤቱባለቤትም ተገርሞ እንዲህ
አለው "በእውነት አንተ የምትገርም ሰው ነህ ይህ የምታየው ሁሉ ስለ ሚሰቴ
የማየገባቸውን አስተያየት ስለ ሰጡ የተገደሉ እንዳነተ አዚህ ቤት በእንግድነት
የመጡ ነበሩ፡፡ አነተ ግን ታላቅ ሰው ሰለሆንክ የሀብቴን ¼ ሰጥቼሀለሁና ይዘህ
ትሄዳለህ" ተብሎ ባለ ብዙ ሀብት ሆኖ ወደ ቤቱ ሄደ፡፡
እዛች ደሳሳ ጎጀ የደረሰው ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ነበር፡፡ ሁሉም ነገር
ቢለወጥም ቤቱን ግን አላጣውም በትልቅ አንጨት የምትዘጋ
(የምትደገፍ) በሩን ገፋ ሲያደርጋት ተከፈተች፡፡ አይኑ ግን ከማያምነው
ነገር ላይ አረፈ ሚስቱ ሁለት ጎረምሶች ማህል ተኝታለች ጎነበስ ሲል
ጎራዴውን አየ አነሳው አነገታቸውነ ሊቆርጠው በንዴት ጦፎ
እጁን ወደ ላላላላላላላለይይይይይ አነሳ-----------3ተኛው ምክር ትዝ
አለው "ክፉ ለማድረግ አትቸኩል" የሚለው፡፡
ከቤቱ ውጪ በተጋደመው ዛፍ ላይ ቁጭ አለ በተቀመጠበት አነቅልፍ
ይዞት ሄደ፡፡ ነጋ ሚሰት በጠዋት ተነስታ ደፋ ቀና ስትል ድንገት
ባሏን አየችው አልልታዋን አቀለጠችው-----ዘላ ተጠመጠመችበት
ከአንቅልፍ የነቃው ባል በመደናገጥ ስሜት ሳለ አጆቹን ይዛ
ወደቤት ገብታ ሁለቱን ጎረምሶች አስተዋወቀች ""ይህ
የመጀመሪያ ልጅህ ይህ ደሞ ሁለተኛው""" ብላ፡፡ እነግዲህ
የመጨረሻው ምክር የልጆቹን ነፍስ ከማጠፋት ረዳው ማለት ነው፡፡
ሁላችሁም አስቲ ራሳችሁነ ጠይቁ ይህ ሰው ያለነዚህ ምክሮች ቢመጣ ምን
ይፈጠር ነበር?
የሚያስተምረን ነገር ካለ ምን ያስተምረናል አናንተ ምን ተማራችሁበት?
አንድ አኔ የተማርኩበትን ልጥቀስላችሁ
እኔ ይህ ነገር ትዝ ባለኝ ቁጥር የሚያስታውሰኝ በትንቢተ ኤርምያስ ም6
ቁ16 ላይ "በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱም፤ የቀደመችውን መንገድ
ጠይቁ፤ መልካሚቱን መንገድ ወዴት አነደሆነች ጠይቁ፤ በእርሷም ላይ ሂዱ
ለነፍሳችሁም መድሀኒት ታገኛላችሁ፤ እነርሱ ግን "አንሄድባትም" አሉ፡፡"
ካንድ ቦታ የሚያደርሱ የሚመስሉ ብዙ መንገዶች ሊኖሮ ይችላሉ፤ ሐዋርያው
"ቅን የምትመስል መንገድ አለች" እነዳለው፡፡ አንዳንዶች መፆም ሲከብዳቸው
አቆራጭ መንገድ ይፈልጋሉ ከዚያም ጌታ ፆሞልኛል ይላሉ፤ አነዚህን ሰዎች
ግን አንድም ቀን ጌታ በልቶልኛልና አልበላም ብለው አያውቁም፡፡
አነዳንዴም ስታናግሯቸው አኛ ጌታን ምሰሉ ነው የተባልንው ይላሉ ታዲያ
ጌታን መምሰል እንዲህ ነው? መልሱን ለናንተ
ትቼዋለሁ፡፡
እንደ ይሁዳ ወደ ገነት ለመግባት አቐራጭ መንገድ መፈለጉ ብልጣ ብልጥ
ለመሆን መሞከሩ መጨረሻው ሞት ስለሚሆን በመጽሐፍ የተፃፈውን ተምሮ
ጠይቆ ተረድቶ በቀደመችው መንገድ መጎዝ እንጂ አቐራጭ መፈለጉ
አያዋጣም፡፡ "የዋሃን ብፁዓን ናቸው፤ ምድርን የወርሳሉና" አንዲል ማቴ 5:-5
የተባልንውም እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብ የዋሆች ሁኑ ነው፡፡ ሰፊ ነገር
ብል ደስ ባለኝ፤ ሁላችሁም በየራሳችሁ የምትሰጡትን አስተያየት ለመስማት
ዝግጁ ነኝ፡፡ ሁለት እውነት የለም፤ ያለው አነድ አውነት ብቻ ነው፡፡
"---------------- ሃይማኖት አንዲት ናት፤ ጥምቀትም አነዲት ናት---------"
ኤፌ 4:-4 አምላከ ቅዱሳን ይጠብቀን!

Source:

Tewahido Communion

Wednesday, August 31, 2011

ቅዱስ ፓሊካርፕ

በአልታዬ ገበየሁ
የልጅነት ሕይወት

ምንም እንኳን የልጅነት ሕይወቱ በደንብ ባይታወቅም እንደ ሲ.ፒ ኤስ ክላርክ ገለጻ አንዲት ደግ ሴት በራእይ ቤቷን እንደሚያስተዳድርላት ስለተገለፀላት በባሪያነት እንደገዛችውና ካደገ በኋላም በንብረቷ ላይ እንደሾመችው፣ ለአንድ አንድ ጉዳዮችም ከሀገር ወደ ሀገር ስትዘዋወር ንብረቷን ለተቸገሩ ሰዎች እንዳከፈፋለ፣ ወደ ሀገሯ ስትመለስም ሌላኛው ባሪያዋ፣ ፖሊካርፐስ ያደረገውን በመንገድ ላይ እንደነገራት፣ ቤቷ ስትደርስ ግን ንብረቷ በሙሉ እንደነበረ ሆኖ በማግኘቷ ወሬውን ያወራትን ባሪያ ስለ ጥፋቱ ልትቀጣው ስትል በቅዱስ ፓሊካርፕ ምልጃ ይቅር እንደተባለ የሚገልጽ ሐተታ ይገኛል።

በራእይ 2፡8 ላይ “በሰምርኔስም ወዳለው ወደ ቤተክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ . . .” የተባለለት መልእክተኛ ቅዱስ ፓሊካርፕ እንደሆነ ብዙ አባቶች ይስማሙበታል።

ቅዱስ ፓሊካርፕ ጳጳስ ከሆነ በኋላ ስለ ማንነቱ በመጥቀስ የገለጹ ምንጮች፡
>የቅዱስ አግናጢዮስ መልእክት
>የራሱ የቅዱስ ፓሊካርፕ መልእክት ወደ ፊልጵስዮስ ሰዎች
>የቅዱስ ሄሬኔዎስ ስብስቦች
የቅዱስ ፓሊካርፕን ገድል የሚተርከው የሰርምኔሳውያን መልእክቶች ናቸው።

የቅዱስ አግናጢዮስ መልእክቶች ከሚባሉት 7ቱ መልእክቶች አራቱ የተጻፉት በሰርምኔስ እያለ ነበር። ከእነዚህ ሁለቱ የማግኔዚያና የኤፌሶን መልእክቶቹ ውስጥ ስለ ቅዱስ ፓሊካርፕ የሚናገሩ መልእክቶች ይገኛሉ። 7ኛው መልእክቱ ደግሞ የተጻፈው ለቅዱስ ፓሊካርፕ ነው። በዚህ ለእሱ በጻፈው መልእክት ውስጥ መግቢያው ላይ ለፓሊካርፕ ያለውን አመለካከት አጉልቶ በሚያሳይ መልኩ “አንተን ለማየት ያበቃኝን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ” በማለት ይናገራል።

ቅዱስ ሄሬኔዎስ ስለ ቅዱስ ፓሊካርፕ ሲገልጽ እርሱ የቀደመውንና የአሁኑን የሚያገናኝ ድልድይ እንደሆነ አድርጎ ሲሆን እርሱንም (ቅዱስ ፓሊካርፕን) በአራት የተለያዩ ቦታዎች ላይ ጠቅሶታል። እነዚህም፡
=>ቅዱስ ፓሊካርፕ ከፓፒያስ ጋር ስላለው ግንኙነት ሲጠቅስ ሁለቱም በአንድ ወቅት የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ተማሪዎች እንደሆኑ ይገልጽልናል። (Against Heresies Book.33 verse 4)

=>የሮማ ካህን ለነበረውና በኋላ ወደ መናፍቅነት ለተቀየረው ለመናፍቁ ፍሎረንስ በጻፈው የተቃውሞ መልእክቱ ቅዱስ ፓሊካርፕን ከልጅነቱ ጀምሮ እንደሚያውቀውና ያስተምር የነበረው ትምህርት ሁሉ አሁን ከተማራቸው በበለጠ በደንብ እንደሚያስታውሳቸው እየገለጸ የተናገረበት (Eusebius, Church History Book 5.20 verse 4-6 )

=>ለ ጳጳስ (ፓፕ) ቪክቶር በጻፈው መልእክት ቅዱስ ፓሊካርፕ ሮምን እንደጎበኘ፤ ይህም የሆነው በወቅቱ የፋሲካ በዓል አከባበር ላይ የተነሳውን ውዝግብ ለመፍታት እንደነበረ የገለጸበት ነው። (Church History Book 5.24 verse 16)

=>በሮማ ቤተክርስቲያን ላይ በጻፈው መልእክቱ ቅዱስ ፓሊካርፕ ያለፈውንና (የሐዋርያትን ዘመን) የአሁኑን ዘመን የሚያገናኝ አባት መሆኑን የገለጠ ሲሆን መነሻውም የሮማ አብያተክርስቲያናት የሐዋርያት የመጨረሻ አድርገው የሚናገሩት ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ ሰማዕትነት የተቀበሉበትን ዘመን 67 ዓ.ምን ሲሆን የሐዋርያን አበው መጨረሻ ብለው የሚጠሩት ደግሞ ቅዱስ ቀሌምንጦስ ዘሮምን ነው። በእሲያ አብያተ ክርስቲያናት የሐዋርያት ዘመን የሚባለው እስከ ቅዱስ ዮሐንስ ከዚህ ዓለም መለየት 100 ዓ.ም ሲዘልቅ የሐዋርያን አበው ደግሞ እስከ ቅዱስ ፓሊካርፕ ሰማዕትነት 155 ዓ.ም ድረስ ያለው እንደሆነ ይታመናል። ይሁን እንጂ በሮማ ቤተክርስቲያን የሐዋርያትን ትምህርት እስከ መጨረሻ የተማሩት አበው በእኛ ዘንድ ነበሩ የቤተክርስቲያን አስተዳደር ስልጣንም (Apostolic Succession) በእኛ በኩል ያለው ነው ትክክል ብለው ለሚሉት የተቃዉሞ መልእክት የጻፈበትና እሱ ራሱ የሐዋርያት ተማሪ የነበረውን ቅዱስ ፓሊካርፕን በዓይኑ እንዳየውና እሱም (ቅዱስ ፓሊካርፕ ከሐዋርያት የሰማውን እንዳስተማራቸው ከሱ ሰማው ያለውን በመረጃ እየጠቀሰ የጻፈበት መልእክት ነው። (Against Heresies (Book III, Chapter 3 verse 4)

የቅዱስ ፓሊካርፕን ገድል የሚተርከው የሰርምኔሳውያን መልእክት
የቅዱስ ፓሊካርፕ ሰማዕትነት
የቅዱስ ፓሊካርፕ የሰማዕትነት ገድል ጸሐፊ የሰርምኔስ ቤተክርስቲያን ስትሆን የተጻፈውም ለፊሎሜሊየም ቤተክርስቲያንና ለተቀሩት የአለም አብያተክርስቲያናት በሙሉ ነው ፤ ታሪኩም እንደዚህ ይነበባል።

በወቅቱ ክርስቲያኖች ከፍተኛ ሰማዕትነትን የሚቀበሉበት ወቅት ነበር። ኢ-አማናዊያኑም ለዚህ ሁሉ ተጠያቂ ያደረጉት ቅዱስ ፓሊካርፕን ነበር። ለዚህም እርሱን በመግደል የክርስቲያኖችን ታሪክ ለመዝጋት ስላሰቡ እርሱን ካለበት ፈልገው የሚያመጡ ወታደሮች አዘዙ። ወዳጆቹም ይህንን ሲሰሙ ከከተማ አውጥተው በገጠር ወዳለች ወደ አንድ የእርሻ ቤት እንዲሸሸግ አደረጉት። እርሱም በዚህች ቤት ጊዜውን በጸሎት ያሳልፍ ጀመር። በሦስተኛው ቀን በሰመመን የተኛበት ትራስ ሲቃጠል ራእይ አየ። አብረውት ላሉትም “በሕይወት ወደ እሳት በመጣል ሰማዕትነትን እቀበላለሁ” አላቸው። ፈላጊዎቹም ተከታትለው ያለበትን ሲያውቁ ከዛ እልፍ ብሎ ወደ ሌላ ቤት ሔደ። ባጡትም ጊዜ በዛ የነበሩ ሁለት ሰዎችን እያሰቃዩ ያለበትን እንዲናገሩ ይጠይቋቸው ጀመር፤ አንዱ አገልጋይም በመጨረሻ ያለበትን ተናገረ። ሄሮድ የሚባለው አዛዥም ወታደሮቹን ወደዛ ላከ። ምንም አሁንም ማምለጥ ቢችልም እስቲ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንይ በማለት ዓርብ ቀን ተያዘ። ወጥቶም ፈላጊዎቹን በሞቀ ሰላምታና በፍቅር ተቀበላቸው። ከእነርሱም “ይህን የተከበረን ሰው ለመያዝ ነው ይህን ያህል ድካም የተደረገው?” ያሉ ነበሩ። የሚበላና የሚጠጣ እንዲያቀርቡላቸው ካደረገ በኋላ ለአንዲት ሰዓት ታገሱኝ ብሎ ብቻውን ሊጸልይ ዘወር አለ። የእግዚአብሔርንም ጸጋ ተሞልቶ ለሁለት ሰዓት ሳያቋርጥ ፀለየ። ሊይዙት ከመጡትም ውስጥ ይህን የተከበረ ሽማግሌና የእግዚአብሔርን ሰው ተቃውመው ሊይዙት በመምጣታቸው ተጸጽተው ንሰሐ ገቡ። ጸሎቱንም ሲጨርስ በቅርብም በሩቅም ያሉትን፣ የጎበኙትን፣ የሚታየውንም የማይታየውንም፣ ስለዚህ ዓለምና ስለ አንዲቷ ቤተክርስቲያን ጸሎት አደረገ። በመጨረሻም በአህያ አስቀምጠው ወደ ከተማ ወሰዱት።

ሔሮድና የሔሮድ አባት ኒካቴስ በሰረገላቸው ይዘውት እየተጓዙ “ቄሳርን ጌታ ማለትና ለአማልክቱ መስዋዕት ማቅረብ ምን ጉዳት አለው? እንዲህ አድርገህ ራስህን ብታድን ምናለበት?” እያሉ ሊያግባቡት ሞከሩ፤ እርሱም ምንም ሳይመልስ ዝም አላቸው። አብዝተው ሲጨቀጭቁትም “እንደምትሉኝ አላደርግም” አላቸው። እነርሱም እንዳማይሆንላቸው ሲያውቁ በብዙ እየሰደቡ እየበረረ ከሚሄድ ሰረገላቸው ላይ የሰማንያ ስድስት ዓመቱን አዛውንት ወርውረው ጣሉት፤በዚህም እግሩ ተሰበረ።

ወደ ስታዲየምም ሲገባ “ፓሊካርፕ ሆይ በርታ! ማንነትህንም አሳይ!” የሚል ድምፅ ተሰማ። ይህንን ድምፅም አብረውት ያሉት ሁሉ ሰሙ። ማን እንደተናገረ ግን አላወቁም። ብዙ ሕዝብም ቅዱስ ፓሊካርፕ ማን እንደሆነ ለማየት ይረባረቡ ነበር። በዛም “እባክህ በዚህ ዕድሜህ ራስህን አታዋርድ” እያሉ እንደ ባህላቸው ሊያግባቡት ሞከሩ። በመቀጠል “በቄሳር ማል ኢኣማንያን ይጥፉ (ክርስቲያኖችን ኢ-አማንያን ብለው ያምኑ ስለነበር)” በል አሉት። እርሱም ወደ ሕዝቡ ዞሮ “ ኢ-አማንያን ይጥፉ” አለ። እነርሱም ደስ ብሏቸው “በል በቄሳር ማል፤ ክርስቶስንም ስደበው” አሉት። እርሱም “”ሰማንያ ስድስት ዓመት ሙሉ አገልግዬዋለሁ፣ አንዳች ክፉ ነገርም አልደረሰብኝም ታዲያ ያዳነኝን፣ ንጉሤን እንዴት አድርጌ እሰድበዋለሁ?” አላቸው። አገረ ገዢውም ተስፋ ባለ መቁረጥ “እባክህ በቄሳር ማል” አለው። ቅዱሱ አባታችንም “እኔ ክርስቲያን ነኝ፤ የክርስቲያን አስተምህሮ ደግሞ ምን እንደሆነ ለማዋቅ ከፈለጋችሁ ትሰሙ ዘንድ አንዲት ቀን ስጡኝ” አላቸው። አገረ ገዢውም “ሀሳብህን ቀይር አለበለዚያ ለአውሬዎች እጥልሃለው” አለው። ቅዱስ ፓሊካርፕም “እባክህ ፍጠን መጥፎውን በመልካም እንጂ መልካሙን በመጥፎ ልንለውጥ አልተማርንም” አለው። አገረ ገዢውም “አውሬዎችን ካልፈራህ ወደ እሳት እንድትጣል አደርግሃለው” አለው ። ቅዱስ ፓሊካርፕም “ለሰዓታት በርቶ በሚጠፋ እሳት ታስፈራራኛለህን? እግዚአብሔርን ለሚክዱ በፍርድ ቀን ዘለዓለም የማይጠፋ እሳት እንዳለ አስተውለሃል? ለምን ትዘገያለህ በል የፈቀድከውን አድርግ” አለው።

በስተመጨረሻ ሕዝቡ በታላቅ ድምፅ “ይህ የእስያውያን (የምስራቅ አብያተክርስቲያናት) መምህር፣ የክርስቲያኖች አባት፣ አማልክቶቻችንን የሚንቅ፣ ብዙዎችን አማልክቶቻችንን እንዳያመልኩ፣ እንዳይሰውላቸው የሚያስተምር ለአውሬዎች ይጣል” በማለት ጮኹ። አንደ ወዳጁና እንደ ጓደኛው (ቅዱስ አግናጢዮስ) ለአውሬዎች ሊጥሉት ከተዘጋጁ በኋላ ከአውሬ ጋር የሚታገሉትን የሚመለከቱ ተመልካቾች ስለሌሉ አስቀድሞ እርሱ ራሱ በራእይ እንዳየው በእሳት ይጣል ዘንድ ተፈረደበት።

እርሱን ለማቃጠል ይረዳ ዘንድም እንጨት ከሚገባው በላይ በፍጥነት ሰበሰቡ። ለዚህም አይሁድ በሚደንቅ ሁኔታ ተባበሯቸው። ልብሱንም፣ ጫማውንም አወለቀ። በአከባቢው ያሉ ክርስቲያኖችም ሰውነቱን ለመንካት ተጋፉ። በመጨረሻ እሳቱ ሲያቃጥለው እንዳይሸሽ በሚስማር ከእንጨት ጋር ሊቸነክሩት ፈለጉ። እርሱ ግን “እንደዚሁ በእሳት እንድቃጠል ተውኝ፤ ጥንካሬን የሰጠኝ ከእሳትም እንዳልወጣ ይረዳኛል” አላቸው። እነርሱም በሚስማር መምታቱን ትተው እጁን ወደ ኋላ አሰሩት። እርሱም ለመስዋዕት ተመርጦ እንደቀረበ አውራ በግ ራሱን ለመስዋዕትነት አቀረበ ፤ እንዲህ በማለትም ጸለየ፦

“ሁሉን ቻይ የሆንከው፣ የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ፣ የቅዱሳንና የመላእክት ሁሉ ፈጣሪ፤ አንተን ያወቅንበት የተወዳጁና የቅዱሱ ልጅህ የኢየሱስ ክርስቶስ አባት ሆይ በዚህች ቀንና ሰዓት ስለ አንተ ሰማዕትነትን ከተቀበሉት ጋር፣ ክርስቶስ ከተቀበለው ጽዋ ጋር፣ ሕያው ለሚሆን ለማይበሰብስና ለዘለዓለም የነፍስና የሥጋ ትንሣኤ ስላበቃኸኝ አመሰግንሃለሁ። . . .” ይህንን ብሎ ሲጨርስ እሳቱን ለኮሱት። ይሁን እንጂ እሳቱ ምንም ጉዳት አላደረሰበትም ፤ ይልቅስ በወቅቱ የሚያስደስት መዓዛ ያለው ሽታ ከእሳቱ ይወጣ ነበር። እነርሱም በጦር እንዲወጋ አደረጉ። በዚህም እሳቱን እስኪያጠፋ ድረስ ብዙ ደም ፈሰሰው። በወቅቱ ክርስቲያኖቹ ሥጋውን ለመውሰድ ቢፈልጉም “ሥጋውን ይዘው ክርስትናን ያስፋፉበታል” በሚል እንዳይወስዱ ተከለከሉ፤ ከዛም በእሳት አቃጠሉት። ክርስቲያኖችም አጥንቶቹን እና አመዱን ወስደው አስቀመጡት። እግዚአብሔር በፈቀደ ሰዓትም በዚህ ሰማዕት አጽም ዙሪያ በመሰባሰብ በደስታ በዓሉን ይዘክራሉ፣ ያስባሉ።

የሰማዕትነቱ ቀን
አንድ አንድ ምንጮች ዕለተ ዕረፍቱን ቅዳሜ የካቲት 23 ቀን 155/156 ዓ.ም በ8፡00 ሰዓት እንደሆነ ሲገልጹ በስንክሳራችን ግን በየካቲት 29 167 ይታሰባል።

የቅዱስ ፓሊካርፕ መልእክት ወደ ፊልጵስዮስ ሰዎች
ቅዱስ ፓሊካርፕ ይህንን መልእክት የጻፈው ቅዱስ አግናጢዮስ የፊልጵስዮስ ሰዎችን ጎብኝቶ ከሄደ በኋላ ነው። የጻፈበት ምክንያትም የሚያጽናና እና የሚያበረታታ ምክር ጻፍልን፤ እንዲሁም በእጅህ የሚገኙ የቅዱስ አግናጢዮስ መልእክቶች ካሉ ላክልን ብለው በጻፉለት መሠረት ነው። ከመልእክቱም በከፊል እነሆ፦

1. “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የማያምኑትን እግዚአብሔር የልጁን ደም ከእነርሱ ይፈልጋል። ልጁን ከሙታን ያስነሣ እኛንም ያስነሣናል። ፍቃዱን እንፈጽም፣ ትእዛዙንም እናክብር እርሱ የሚወደውንም እንውደድ። ከርኵሰት ራቁ፣ ለምድራዊ ሀብትም አትጓጉ፣ ገንዘብን አትውደዱ፣ ክፉ አትናገሩ፣ በሐሰት አትመስክሩ፣ በክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፣ አትፍረዱ፣ ይቅርታንና ምሕረትን አድርጉ” እያለ ጌታችን በማቴ 5 ላይ ያስተማራቸውን ስድስቱን ቃላተ ወንጌልን እየጠቀሰ ይመክራቸዋል። 2

2. ስለ ቅድስና የምጽፍላችሁ ራሴን እንደ አንዱ ቆጥሬ አይደለም ፤ ጻፍልን ስላላችሁኝ ነው እንጂ። እኔም ሆንኩ ማናችንም የተባረከው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ደረሰበት ጥበብ አልደረስንም። እሱ በመካከላችሁ በነበረበት ጊዜ ስለ እውነት ቃል አስተማራችሁ። ከእናንተ ሲለይ መልእክት ጻፈላችሁ። አስተውላችሁ ካጠናችሁት ወደ ተስፋ የሚያደርሳችሁ፣ በእምነት የሚያሳድጋችሁ፣ ለእግዚአብሔርና ለጎረቤቶቻችሁ ፍቅር እንዲኖራችሁ የሚያደርግ ነው። 3

3. የገንዘብ ፍቅር የኃጢአት ሥር ነው። ወደዚች ምድር ስንመጣ ምንም ይዘን እንዳልመጣን ስንሔድም ምንም ይዘን አንሔድም። የጽድቅን ጥሩር እንታጠቅ። መጀመሪያ እኛ ለራሳችን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ማክበርን እንማር። በመቀጠል ሚስቶቻችሁ በተሰጣቸው እምነት እንዲሔዱ፣ በንጹህ ፍቅርና በእውነት ባሎቻቸውን እንዲወዱ፣ ሁሉንም ሰው በእኩል ዓይን እንዲመለከቱ፣ ልጆቻውን እግዚአብሔርን ማወቅንና መፍራትን እንዲያስተምሩ አስተምሯቸው። መበለቶችን አዘውትረው መጸለይና ክብራቸውን መጠበቅን አስተምሯቸው። ስም ከማጥፋት፣ ክፉ ከመናገር፣ በሐሰት ከመመስከር ራቁ። እንዲሁም ምንም ዓይነት ምክንያት፣ ሰበብ ወይም የልብ ምሥጢር ከእግዚአብሔር እንደማይሰወር እወቁ። 4

4. ለዲያቆናት፡ የእግዚአብሔርና የክርስቶስ አገልጋይ እንጂ የሰው ስላልሆናችሁ በቅድስናው ፊት ነውር የሌለባችሁ ሁኑ። መንታ ምላስ፣ ስም ማጥፋት፣ የገንዘብ ፍቅር ከእናንተ ይራቅ። ለወጣቶች፡ በሁሉ ነገር ነውር የሌለባቸሁ ይሁኑ፣ በተለይ ንጽህናቸውን ለመጠበቅ ይጠንቀቁ። እንደ ሙሽራ ራሳቸውን ከክፉ ነገር ሁሉ ይጠብቁ። በዚህ ነው ከዚህ ዓለም የዝሙት ወጥመድ የሚያመልጡት። ይህ የመንፈስ ጠላት ነው። ዝሙት፣ መሽቀርቀር እና ርኵሰት የእግዚአብሔርን መንግሥት አያስወርስም። ደናግላንም ነውር የለሽና፣ ንጹሀን መሆን አለባቸው። እግዚአብሔር እንደማይዘበትበት በማወቅ ትእዛዙን በማክበር እንኑር። ታጋሽ፣ ርህሩህ፣ ጠንካራ ሰራተኛ፣ በክርስቶስ እውነት የምንጓዝ እንሁን። በዚህ ዓለም እሱን ካስደሰትነው፣ የሚቀጥለው ዓለምም ወራሾች እንሆናለን። ቃል እንደገባልንም ከሙታን ያስነሳናል፤ በእርሱ ካመንንና እንደሚገባው ሆነን ከኖርን ከእርሱጋርም ገዢዎች እንሆናለን። 5

5. ካህናት ሩህሩሆች፣ መሐሪዎች፣ የሚቅበዘበዙትን የሚመልሱ፣ በሽተኞችን የሚጎበኙ፣ መበለቶችን፣ ወላጅ አልባዎችን፣ ድሆችን የማይተዉ ነገር ግን በእግዚአብሔር ዘንድም በሰው ዘንድም የሚያስፈልጋቸውን የሚያቀርቡላቸው ይሁኑ . . . ። 6

6. ማንም ክርስቶስ በሥጋ እንደተወለደ የማያምን የክርስቶስ ጠላት ነው። የመስቀሉን ነገር የማይመሰክር እርሱ ዲያብሎስ ነው። ማንም የክርስቶስን ድንቅ ስራ ለራሱ ፈቃድ በመቀየር ትንሣኤ ሙታን የለም የሚል፣ ፍርድ የለም የሚል እርሱ የሰይጣን የበኩር ልጅ ነው። ስለዚህ የእነዚህን ከንቱ አስተምህሮ በመተው ከመጀመሪያው ለእኛ ወደተሰጠን ቃል እንመለስ ፤ በጾምና በጸሎትም እንጠብቀው። . . . 7

7. መታዘዝንና የቅድስናን ስራ እንድትሰሩ አሳስባችኋለው። በዓይናችሁ ያያችሁትን የተከበረውን የአግናጢዮስን፣ የዞሲመስን፣ የሩፈስን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ከእናንተ ጋር ያሉትን እያያችሁ እንዲሁም ቅዱስ ጳውሎስና ሌሎች ሐዋርያት ይህችን ዓለም እንደማትገባ አውቀው በእምነትና በቅድስና እንጂ በከንቱ እንዳልደከሙ ፣ አሁንም አብረውት ከተሰቃዩት ከጌታ ጋር የሚገባቸው ቦታ ላይ እንዳሉ እያሰባችሁ የትዕግስትንም ነገር ተለማመዱ። 9

8. መልካም ስታደርጉ አታበላልጡ። ምጽዋት ከሞት ትታደጋለች። 10

9. በአንድ ወቅት በእናንተ መካከል ካህን ስለነለበረው ስለ ቫለንስ በጣም አዝናለሁ። እርሱ ካህን የነበረ ቢሆንም በቤተክርስቲያን የተሰጠው ቦታ ምን ያህል ትልቅ እንደሆነ አልተረዳም። . . . ስለ ጌታ ፍርድ የማያውቅ ማን አለ? ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረው ፣ ቅዱሳን በዓለም እንደሚፈርዱ አታውቁምን? ወንድሞች ሆይ ስለ ቫለንስ እና ስለ ባለቤቱ በጣም አዝናለሁ። ጌታም እንደ ጣላት ሳይቆጥረው ለንሰሐ ያበቃው ዘንድ እመኛለሁ። እናንተም እንደ ተቸገሩና እንደ ጠፉ አባሎቻችሁ በመቁጠር ወደእናንተ በመመለስ ሙሉ ትሆኑ ዘንድ ስለእርሱ ልትጸልዩ ይገባል። 11

10. ቅዱስ አግናጢዮስ የእናንተን መልእክት ሰው ካገኘው እንድልክላችሁ እንደጻፈልኝ፣ እናንተም ማንም ወደ ሶርያ ቢወጣ ደብዳቤያችንን ይዞልን ይመለስ በማለት እንደጻፋችሁልኝ እኔም ሁነኛ ሰው ካገኘሁ የፍላጎታችሁን አደርጋለሁ። ቅዱስ አግናጢዮስ ለእኛ የጻፈውን መልእክትና ባጠቃለይ በእኛ ዘንድ የሚገኙ መልእክታቱን እንደጠየቃችሁን ከዚህ መልእክት ጋር አያይዘን ልከንላቸኋል። ከእነርሱም እንደምታተርፉ እናምናለን። ስለ እምነትና ስለ ትዕግስት እንዲሁም በጌታ ዘንድ ንጹህ የሚያደርጓችሁን ነገሮች ታገኙባቸዋላችሁ። ቅዱስ አግናጢየስንና አብረውት የነበሩትን እያከበራችሁ እንደ ሆነ በማወቃችን ደስ ብሎናል። 13

ይህ የቅዱስ ፓሊካርፕ መልእክት ምን ያህል በሐዲስ ኪዳን ቃላት የበለጸገ እንደሆነ ስንረዳ ዛሬ ዛሬ መጽሐፍ ቅዱስ ተበርዟል የሚሉትም ሆኑ ሌሎች ቅዱሳን መጻሕፍትን አንቀበልም የሚሉት ምንኛ ሞኝ እንደሆኑ እንረዳለን። ከዚህ ባሻገር ቅዱስ ፓሊካርፕ በዚህ መልእክቱ የሚነግረን ምክሮች በጣም የሚደንቁና ትክክለኛ ክርስቲያኖች እንድንሆን ምን ያህል እንደሚረዱን ሳንገነዘብ አንቀርም። በመጨረሻም ቅዱስ ፓሊካርፕ በዚህ በሽምግልናው ዘመን ሰማዕትነትን ለመቀበል የነበረው ቁርጠኛነት ክርስትና ምን ያህል ዋጋ የሚከፈልባት እንደሆነች እና ያለ ተጋድሎ የእግዚአብሔርን መንግሥት ማሰብ እንደማይገባን፣ የቅዱሳኑን ፈለግ መከተል እንደሚገባን እና እነርሱ ያለ ምክንያት ለነፍሳቸው እንዳልራሩ እንድናስተውል ይረዳናል።
የቅዱስ ፓሊካርፕ ጸሎቱና በረከቱ በእኛ ይደርብን ለዘለዓለሙ አሜን።