በቀሲስ ለማ በሱፍቃድና
በመ/ር መንግስተ አብ አበጋዝ
...ይህ ኃይለ ቃል ለታላቁ ጻድቅ ለሎጥ የተሰጠ መመሪያ ነው፤የሰዶም ከተማ ነዋሪዎች በግብረ ሰዶም /ወንድና ወንድ መጋባት/ ኃጢአት የታወቁ ነበሩ፡፡ በዚህ ምክንያት እግዚአብሔርከተማዋን ያጠፋት ዘንድ አሰበና ሁለቱን መላእክት ላከ፡፡ ከማጥፋቱም በፊት ደጋግ ሰዎች አብረው እንዳይጠፉ መላእክቱ ያወጧቸው ዘንድ ስለሚገባ ሎጥን ከነቤተሰቡ እንዲህ አሉት «ራስህን አድን ወደኋላ አትይ በዚህም ዙሪያ ሁሉ አትቁም እንዳ ትጠፋም ወደተራራው ሸሽተህ አምልጥ» ብለው ከዚያ እንዲወጣ አድርገውታል፡፡ጻድቁ ሎጥም ወደ ተራራ በመሸሽ ከነቤተሰቡ መዳኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ይነግሩናል፡፡
እንግዲህ ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ስለተራራዎች ታሪካዊነት በስፋት ተጽፏል ድንቅ ድንቅ ሥራዎች የተሠሩባቸው ተራራዎች አሉ፡፡ ከእነዚህም ደብረሲና በግብፅ በስተምሥራቅ ከእስራኤል ደግሞ በስተደቡብ ይገኛል የእግዚአብሔር ተራራ ደብረ ኮሬብም ይባላል /ዘዳ 3÷1/፡፡
የሞርያ ተራራ አብርሃም ልጁ ይስሐቅን ይሠዋ ዘንድ መሠውያ ያዘጋጀበት ታላቅ ድንቅ ምስጢር የተገለጠበት ተራራ ነው፡፡ እነዚህ በብሉይ ኪዳን ድንቅ ሥራ ከተሠራባቸው ተራራዎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
በሐዲስ ኪዳን በጎ ሥራ የተሠራበት ተራራ ደግሞ ደብረ ዘይት የወይራ ዛፍ የበዛበት ተራራ ሲሆን በጣም ከፍታ ያለው ተራራ ነው፡፡ ጌታችን በዘመነ ሥጋዌው ቀን ሲያስተምር ውሎ ማታ የሚያድረው በዚህ ተራራ ላይ ነበር ፤ ነገረ ምጽአትንም ያስተማረው በዚህ ተራራ ላይ ነው /ማቴ.24÷1/፡፡ በተራራው ላይ ሆኖ ኢየሩሳሌምን፣ ኤዶምያስን ሞአብን ቁልጭ አድርጐ ማየት ይቻላል፡፡
ይህ ተራራ በብሉይ ኪዳንና በሐዲስ ኪዳን ታላላቅ ድንቅ ድንቅ ሥራዎች ተሠርተውበታል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊትም የዚህን ተራራ ታላቅነት ሲገልጥ «ታቦር ወአርሞንኤም በስመዚኣከ ይትፌሥሑ ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል» በማለት በተራራው አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች በእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ እንደሚደሰቱ ለመግለጽ በተራራዎቹ አንጻር ተናግሯል፡፡
በዚህ ተራራ ላይ ባርቅና ዲቦራ የእስራኤል ጠላት የነበረውን ሲሳራን ድል አድርገውበታል፡፡ «የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሔደህ ወደ ታቦር ተራራ ውጣ ከአንተ ጋር ከንፍታሌምና ከዛብሎን ልጆች አሥር ሺሕ ሰዎች ውሰድ ...» በማለት በእግዚአብሔር ትእዛዝና አጋዥነት ጠላትን ድል ያደረጉበት ተራራ ነው፡፡
ደብረ ታቦር በሐዲስ ኪዳን
ይህ ተራራ እንደ ብሉይ ኪዳን ሁሉ በሐዲስ ኪዳንም ድንቅ ሥራ ተሠርቶበታል፡፡ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የክብሩን ብርሃን /ብርሃነ መለኮቱን/ የገለጠው በዚሁ ተራራ ላይ ነው /ማቴ.17÷1-9/ በቂሳርያ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያትን ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደሆነ ይሉታል) /ማን ይሉታል፡፡/ ብሎ በጠየቀ ከስድስት ቀን በኋላ ከሐዋርያት ሦስቱን ማለትም ጴጥሮስን ያዕቆብንና ወንድሙ ዮሐንስን/ ይዞ ወደ ረጅም ተራራ አወጣቸው ከብሔረ ሕያዋን ነቢዩ ኤልያስን ከብሔረ ሙታን ደግሞ ነቢዩ ሙሴን አመጣቸው በፊታቸውም ተለወጠ ፊቱም እንደፀሐይ በራ ኤልያስና ሙሴ ከፈጣሪያቸው ጋር ሲነጋገሩ ታዩ፡፡
ከነቢያት ሁለቱ ከሐዋርያት ደግሞ ሦስቱ በድምሩ አምስቱም አንድ ላይ ሆነው ቅዱስ ጴጥሮስ ባየ ጊዜ እንዲህ አለ «ሠናይ ለነ ሀልዎ ዝየ» በዚህ መኖር ለኛ መልካም ነው አለ፡፡ ከዚህ በላይ የሚያስደስት ነገር የለምና ሁልጊዜ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ሲሆን ደስተኛ ይሆናል ከጭንቀቱም ይረጋጋል ይህም ምሳሌ ነው፡፡
ተራራ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ናት
በቤተክርስቲያን ብሉያቱ ሐዲሳቱ ይነገርባታል ይፈጸምባታል ሁሉም አንድ ሆኖ ያገለግላታል ይገለገልባታል የታመመ ይፈወስባታል የሞቱ ሕያዋን ይሆኑባታል፡፡
ጌታችንም ከብሉይ ኪዳን ሙሴንና ኤልያስን ከሐዲስ ኪዳን ሦስቱን ሐዋርያት ያመጣው ሁለቱም ኪዳናት ብሉይና ሐዲስ በቤተክርስቲያን አገልግሎታቸው እንደሚቀጥል ለማሳየት ነው፡፡
በብሉይ ኪዳን ዘመን ባርቅና ዲቦራ ሲሳራን ድል እንዳደረጉበት በአዲስ ኪዳንም ጌቶችን ደቀመዛሙርቱን ሲፈታትን የነበረውን ዲያብሎስን ድል ነስቶበታል /አድርጐበታል/፡፡ ቅድስት ቤተክርስቲያንም አጋንንትን ኑፋቄን /ጥርጥርን/ ድል እናደርግ ዘንድ ታስችለናለች፡፡ «ወኮነት ደብረ ታቦር አምሳለ ቤተክርስቲያን እስመ አስተጋብአት ውስቴታ እምነ ብሉይ ወሐዲስ፤ ደብረ ታቦር የቤተ ክርስቲያን አምሳል ሆነች ከብሉያትና ሐዲሳት በውስጧ ሰብስባለችና» እንዲል፡፡ በደብረ ታቦር በቅዱስ ጋብቻ የጸኑ እና ደናግል እኩል በፈጣሪያቸው ፊት መቆማቸውንም እናያለን፡፡በቤተክርስቲያንም ደናግል መነኮሳትም ሕጋውያን ካህናትም አንድ ሆነው ያለ ልዩነት የሚያገለግሉባት ቅድስት ቤት መሆኗን ለማጠየቅ ለመግለጽ ነው፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ «በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህንን ድምፅ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን፤» /’ጴጥ.1÷18/ በማለት እንደተናገረው፡፡
ሰው ሁልጊዜ መነሻውና መድረሻው ቤተ ክርስቲያን ከሆነ የሚሰማው ድምፅ ለሕይወተ ሥጋ ወነፍስ የሚበጅ ነው በቤተ ክርስቲያን አዘውትሮ መገኘት ወደዚያም መሸሽ ከእግዚአብሔር ጋር መኖር ነውና፡፡ጌታችንም ከብሉይ ኪዳን ሙሴንና ኤልያስን ከሐዲስ ኪዳን ሦስቱን ሐዋርያት ያመጣው ሁለቱም ኪዳናት ብሉይና ሐዲስ በቤተክርስቲያን አገልግሎታቸው እንደሚቀጥል ለማሳየት ነው፡፡
በብሉይ ኪዳን ዘመን ባርቅና ዲቦራ ሲሳራን ድል እንዳደረጉበት በአዲስ ኪዳንም ጌቶችን ደቀመዛሙርቱን ሲፈታትን የነበረውን ዲያብሎስን ድል ነስቶበታል /አድርጐበታል/፡፡ ቅድስት ቤተክርስቲያንም አጋንንትን ኑፋቄን /ጥርጥርን/ ድል እናደርግ ዘንድ ታስችለናለች፡፡ «ወኮነት ደብረ ታቦር አምሳለ ቤተክርስቲያን እስመ አስተጋብአት ውስቴታ እምነ ብሉይ ወሐዲስ፤ ደብረ ታቦር የቤተ ክርስቲያን አምሳል ሆነች ከብሉያትና ሐዲሳት በውስጧ ሰብስባለችና» እንዲል፡፡ በደብረ ታቦር በቅዱስ ጋብቻ የጸኑ እና ደናግል እኩል በፈጣሪያቸው ፊት መቆማቸውንም እናያለን፡፡በቤተክርስቲያንም ደናግል መነኮሳትም ሕጋውያን ካህናትም አንድ ሆነው ያለ ልዩነት የሚያገለግሉባት ቅድስት ቤት መሆኗን ለማጠየቅ ለመግለጽ ነው፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ «በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህንን ድምፅ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን፤» /’ጴጥ.1÷18/ በማለት እንደተናገረው፡፡
ሰው ሁልጊዜ መነሻውና መድረሻው ቤተ ክርስቲያን ከሆነ የሚሰማው ድምፅ ለሕይወተ ሥጋ ወነፍስ የሚበጅ ነው በቤተ ክርስቲያን አዘውትሮ መገኘት ወደዚያም መሸሽ ከእግዚአብሔር ጋር መኖር ነውና፡፡
ተራራ የወንጌል ምሳሌ ናት
ወደተራራ ላይ ሲወጡ ይደክማል መንገዱም ያስቸግራል፡፡ ከዚህ የተነሣ ብዙ ሰው ወደ ተራራ ለመውጣት ያለው ፍላጎት ዝቅተኛ ነው፡፡ትልልቅ ተራራ ላይ ያሉትን ገዳማትና አድባራትን ለመሳለም ለመጐብኘት ያለው ፍላጐት ዝቅተኛ የሚሆነውም ለዚህ ነው፡፡
ከተራራው ላይ ከተወጣ በኋላ ግን ደስ ይላል፡፡ አየሩም ቀዝቀዝ ያለ ነው፤ድካሙ ሁሉ ይረሳል ከተራራው ላይ ሆነው ግራና ቀኝ ከተማዎች፣ መንደሮች፤ የመሳሰሉት ሲታዩ ያስደስታሉ፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ወንጌልም ሰ !ማሯት ታስቸግራለች ቶሎ ግልጽ አትሆንም ለማወቅ ለመረዳት ድካም ትጠይቃለች፡፡ ምስጢሩን መጠየቅ መላልሶ መማር ...ያስፈልጋል፡፡ ከተማሩ በኋላ ግን ደስ ታሰኛለች፡፡ ሁሉም ነገር ቀላል መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡
ተራራ የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ናት
ከተራራ ላይ መውጣት ብዙ ድካም እንዳለው ሁሉ መንግሥተ ሰማያትንም ለመውረስ ብዙ ድካም አለ፡፡ ወደ ተራራ ላይ ሲወጣ በቀስታ በእርጋታ በማስተዋል በመጓዝ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ 12÷2፡፡በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ በማለት እንደተና ገረው መንግሥተ ሰማያት ለመውረስ አንዱና ትልቁ መሣሪያ ትዕግሥት ነው፡፡
ሁሉም ምሳሌዎች ምስጢር አላቸው የደብረ ታቦርንም በዓል ስናከብር የተራራውን ምስጢር በተራራው ላይ የተገኙትን የሁለቱን ነቢያትና የሦስቱን ሐዋርያት ምስጢራዊ ምክንያት፣ የተነገረውን ትንቢታዊ ቃል በማስታወስ መሆን አለበት፡፡ በተራራው ላይ የተፈጸመውን ድንቅ ነገር፣ ከነቢያትና ከሐዋርያት መታደመም ጋር የተከናወነውን ምስጢር በማስተዋል መረዳት ከቻልን በዓሉን ማክበራችን ትርጉም እንዳለው እንረዳለን፡፡
መጽሐፋዊ ትውፊቱ
ቡሄ፡- ቡሄ ማለት ብራ ብርሃን ደማቅ ማለት ነው፡፡ ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት በዓል የሚዘከርበት፤ እና ለበዓሉም ችቦ ስለሚበራ የብርሃን በዓል ለማለት የቡሄ በዓል እንላለን፡፡
ወቅቱ የክረምት ጨለማ አልፎ የብርሃን ወቅት፤ ሰማይ ከጭጋጋማነት ወደ ብሩህነት የሚለወጥበት፤ የመሸጋገሪያ ወቅት ነው፡፡ «ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፣ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት» እንዲሉ፡፡ በሌላ በኩልም «ቡኮ/ሊጥ» ተቦክቶ ዳቦ የሚጋገርበት «ሙልሙል» የሚታደልበት በዓል በመሆኑ ቡሄ ተብሏል፡፡
ጅራፍ
በደብረ ታቦር በዓል በትውፊታዊ መልኩ የሚታየው ምስጢር በኢየሩሳሌም ስለሚሆነው የጌታችን ምስጢራዊ ሞቱ ነው፡፡ ጅራፍ መግመድ እና ጅራፍ ማጮኽ ሁለት ዓይነት ምስጢር ይዞ የሚከወን ትውፊታዊ ተግባር ነው፡፡ የመጀመሪያው ግርፋቱን እና ሞቱን እናስብበታለን፡፡ እንዲሁም ድምፁን ስንሰማ የባሕርይ አባቱን የአብን ምስክርነት ቃል፣ እንደ ነጎድጓድ ድምፅ ያስታውሰናል፡፡
የጅራፍን ትውፊታዊነት /ውርስ/፣ መጽሐፋዊ ትምህርትና ምስጢር ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ ጨዋታውን በተራራማ አካባቢ፣ ከመኖሪያ ቤት ርቆና፣ በሜዳ ማድረጉ ጠቃሚ ነው፡፡ ጅራፍን በርችት መቀየር የሚያመጣውን የምስጢር ተፋልሶ ብቻ መመልከት ከማኅበራዊ ጎጂ ገጽታው በላይ እንድናስወግደው ያስገድደናል፡፡
ችቦ
ችቦ የጌታችንን ብርሃነ መለኮት መገለጥ የሚያመለክት ነው፡፡ በመሆኑም ችቦ ለኩሰን በዓሉን እናከብራለን፡፡ የዚህ ትውፊታዊ የትመጣ ግን በብርሃኑ ድምቀት የቀኑን መምሸት ያልተረዱ እረኞች በሜዳ ቀርተዋልና ወላጆች ከመንደር ችቦ ለኩሰው ልጆቻቸውን ፍለጋ ሔደዋልና ታሪኩን እያዘከርን በዓሉን እናከብራለን፡፡
የችቦው መንደድም ሌላ ትርጉም አለው፡፡ አንድ ምእመን ለሌላው ምእመን መካሪ አስተማሪ መሆኑን፤ መከራ እየተቀበለም አርአያ ምሳሌ ብርሃን መሆኑን ያሳያል፡፡ በሃይማኖትም አርአያ ምሳሌ ይሆንላቸዋል፡፡
ሙልሙል
በችቦ ብርሃን ልጆቻቸውን ፍለጋ የወጡ ወላጆች ዳቦ ጋግረው ይዘውላቸው ወጥተዋል፡፡ ስጦታው ቤተሰባዊነትን፣ ፍቅርንና መተሳሰብን መግለጫ ነው፡፡ ወደ ቤታችን «ቡሄ» እያሉ ለሚመጡ አዳጊዎችም ዘምረው እንዳበቁ የሚሰጥ «ሙልሙል» ዳቦ አለ፡፡ በምሳሌ ሐዋርያት ምስራች ሊነግሩን፣ ወንጌል ሊሰብኩን በደጃፋችን ቆመው «ቡሄ በሉ» የሚሉንን አዳጊዎች የሚበሉትን መስጠታችን ምሳሌያዊ /መጽሐፋዊ/ ነው፡፡ ጌታችን ደቀመዛርቱን ባስተማራችሁበት፣ በደረሳችሁበት ተመገቡ ብሏቸዋል፡፡ /ማቴ 10.12/ ሕፃናቱም ሊዘምሩ ሲመጡ ዳቦ መስጠት ልማዳዊ ብቻ አይደለም፡፡ ሕፃናቱ የደቀመዛሙርት ምሳሌ ናቸው መዝሙራቸው ደግሞ ሐዋርያት «የምስራች» ይዘው የመምጣታቸው ምሳሌ ነው፡፡
ሐዋርያት በገቡበት አገር አስተምረው አጥምቀው የጸጋ ልጅነትን አሰጥተው በረከት አድለው እንደሚሔዱም፤ ልጆችም ዘምረው፣ አመስግነው፣ መርቀው «ውለዱ ክበዱ፤ ሀብተ አግኙ፣ የመንግሥተ ሰማያት ወራሾች ያድርጋችሁ. . .» ይላሉ፡፡
በአጠቃላይ በዓለ ደብረ ታቦር ከነዚህ ምስክር ካላቸው ትምህርቶቹ፣ ምስጢር ከሚራቀቅባቸው ትርጓሜያቱና ከትውልድ ትውልድ በቅብብል ከተላለፈው ቅዱስ ትውፊት ጋር ሃይማኖታዊ ባሕል ሆኖ ሊቀጥል ይገባዋል፡፡ ይህን ማድረግ የሚቻለው ግን አዳጊዎች ሃይማኖታዊ ትውፊቱን ይዘው እንዲያድጉ ጥቆማ በመስጠት፣ ግጥም በመግጠምና ምስጢሩን በማብራራት የመጀመሪያዎቹ ባለድርሻዎች ወላጆች ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የሚሰሙ ግጥሞች ስድብ፣ ፌዝና ሥላቅ የተቀላቀለባቸው ይሆናሉ፡፡ ሕፃናቱም ዝማሬውን ሲጀምሩ «ከሰጡን እንነሣ ከነሱን እናርዳ» ብለው ይጀምሩታል፡፡ከሰጡን እንመርቃለን ካልሰጡን እንራገማለን በማለት፡፡አሳሳቢው ነገር ደግሞ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ወደ ገንዘብ ማግኛነት የቀየሩ ሁኔታዎች መታየታቸው ነው፡፡ ዳቦ /ሙልሙል/ ትምህርቱንም፣ ምስጢሩንም፣ ትውፊቱንም በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል፡፡
ቤተክርስቲያን የምስጢር ግምጃ ቤት ናት የምታከናውነውን ሁሉ ከበቂ መረጃ ጋር ነው ተግባራዊ የምታደርገው፡፡ በተለይ ወጣቱ ክፍል ይህንን አውቀን ተረድተን ለቀሪው ትውልድ ማስተላለፍ እንችል ዘንድ ከክፉ ጠላት ከሰይጣን ፈተና፣ በሽታ ከመሳሰሉት ችግሮች ለመዳን ወደ ተራራዋ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመሸሸ ከክፉ ነገሮች ሁሉ ማምለጥ ይቻላል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር የሚጠለሉ ሁሉ ዕድሜያቸው ይረዝማል፡፡ አስተዋዮችም ይሆናሉ ሁሉን ማየትና የሚጠቅማቸውን መምረጥ ይችላሉ በሥነ ምግባር የታነፁ አገርንና ወገንን የሚጠቅሙ ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያን በመጠጋት ከክፉ ሁሉ የሚያመልጡ ይሆናሉ ለዚህም የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡
የአምላካችን ቸርነት አይለየን
No comments:
Post a Comment