13

.

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው::" የማቴዎስ ወንጌል 7: 4

"እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅናወተት ግዙ።" ትንቢተ ኢሳይያስ 55 : 1

Tuesday, August 13, 2013

ውዳሴሃ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ ዘደረሰ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ


በስመአብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ

ወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያም
ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ቅዱስ ማርቆስ እንደሣለው

ውዳሴ ማርያምን ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ፤ ኤፍሬም ለብሐዊ ተናግሮታል። ሶርያዊ በሀገሩ ነው፤ ለብሐዊ በተግባሩ ይሰኛል። ይህም ቅዱስ ኤፍሬም የያዕቆብ ዘንጽቢን ደቀመዝሙር ነው። ያዕቆብ ዘንጽቢንም ቁጥሩ ከሠለስቱ ምእት ነው። ለአውግዞተ አርዮስ ሲሄድ አስከትሎት ሂዶ ነበር። አርዮስን አውግዘው ሃይማኖት መልሰው ተመልሰው ካደሩበት ቦታ ዐምደ ብርሃን ከምድር እስከ ሰማይ ተተክሎ ሌሊት በሕልሙ ራእይ ያያል። ራእዩን እንደ ገለጽክልኝ ባለቤቱንም ግለጥልኝ ብሎ ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክት የታዘዘ መልአክ መጥቶ ባስልዮስ ዘቂሳርያ ነው። ለቤተክርስቲያን ዐምድ ጽንዕ ነውና ፤ በትምህርቱ የሰውን ልቡና ብሩህ ያደርጋልና እንዲህ ባለ አርአያ አየኸው አለው። ባስልዮስም ቁጥሩ ከሠለስቱ ምእት ነው። መምህርን ካወጡበት ሳያገቡ ትቶ መሄድ ፈሊጥ (ሥርዓት) አይደለምና መምህሩን ካወጣበት አግብቶ ስለ ሦስት ነገር ይሄዳል፤ መጀመሪያ እንዲህ ካለ ሰው ጋር ቢጫወቱ መንፈሳዊ ነገር ይገኛልና ብሎ ሁለተኛ በጆሮ የሰሙትን በዐይን ቢያዩት ይረዳልና ብሎ ሦስተኛ የመንፈስቅዱስ ነው ሰይጣን ተጫውቶብኝ ይሆን ብሎ ሄደ። ነገር ግን ሲደርስ እንዳየው ሆኖ አላገኘውም። በወርቅ ወንበር ተቀምጦ በወርቅ አትሮንስ የወርቅ ወንጌል አዘርግቶ ካባ ላንቃ ለብሶ ኩፋር ጠምጥሞ መነሳንሱን ቢያዩ የሐር፤ መያዣውን ቢያዩ የወርቅ መነሳንስ ይዞ ሲያስተምር አግኝቶታል። ቅዱስ ኤፍሬምም ለመንፈስቅዱስ ሁለት ግብር አለውን? ብሎ ሰይጣን ተጫውቶብኝ ይሆን እያለ ሲያወጣ ሲያወርድ አራት ነገር አይቶ ተረድቷል። መጀመሪያ ከአፉ ነጸብራቀ እሳት እየወጣ ሕዝቡን ሲዋሀዳቸው ያያል፤ ይህም ትምህርቱ ነው። ሁለተኛ ርግብ መጥታ በራሱ ላይ ስታርፍበት ሦስተኛ ተሐዋስያን ከልብሱ ላይ እያረፉ እንደ ቆሎ ሲረግፉ ያያል። 
ይህን መናፍቃን ፍጡር ፈጣሪ ይመስል ያቃጥላልን ብለው እንቃወማለን ይላሉ ቅዱስ ባስልዮስ ከከዊነ እሳት ማዕረግ ደርሶ ነበርና ያቃጥላል። አራተኛ "ስሙን ያያውቅ ሀገሩን ያይጠይቅ ኤፍሬም ሶርያዊ ኤፍሬም ለብሐዊ ብላችሁ ጥሩልኝ ከማዕዝነ ቤተክርስቲያን ባንዱ ቁሞ ይጸልይላችኋል" ብሎ አስጠርቶ በአስተርጓሚ ሲጫወቱ ጨዋታው ባይከተትለት አባቴ ጸልይና ያንተ ቋንቋ ለእኔ ይገለጥልኝ አለው።  ጸልዮ የባስልዮስ ቋንቋ ጽርዕ ነው፤ ለኤፍሬም የኤፍሬም ቋንቋ ሱርስት ነው ለባስልዮስ ተገልጾላቸው ሲጫወቱ አድረው ሲነጋ አሰናብተኝ ልሂድ አለው። መች ልትሄድ አምጥቶሃላ ልትኖር ነው እንጂ ብሎ ሕዝባዊ ነው ቢሉ ዲቁና ዲያቆን ነው ቢሉ ቅስና ሹሞ ከሀገረ ስብከቱ ሀገር ከፍሎ አስተምር ብሎ ሰጠው። 

ባስልዮስም ይህን መልበሱ ስለ ክብረ ወንጌል ነው ዛሬ ካህናት አክሊል ደፍተው ኩፋር ጠምጥመው ካባ ላንቃ ለብሰው ሥጋውን ደሙን እንዲያከብሩ እንዲለውጡ እርሱስ በውስጥ የሚለብሰው ማቅ ነበር። ከዚህ በኋላ ከአዋልደ ነገሥት የምትሆን አንዲት ሴት ነበረች። ኃጢአቷን እየጻፈች የምታኖር። ስለምን ቢሉ ለመንገር ብትፈራ። አንድም ቢበዛ አንድ ቀን መጥታ እንደ ተጠቀለለ ይዛ አባቴ በዚህ ያለው ይፋቅልሽ በለኝ አለችው። ይፋቅልሽ አላት ገልጣ ብታይ አንዲት ቀርታ አየች፤ ይህችንሳ አለችው። ይህስ ለቅዱስ ኤፍሬም ቢቻል እንጂ ለእኔ አይቻለኝም አላት። አሁን ለርሱ የማይቻለው ሆኖ አይደለም። ቅዱሳን የራሳቸው ክብር ከሚገለጥ የወንድማቸው ክብር ቢገለጥ ይወዳሉና። ዳግመኛም ስትመጥ ስትሄድ ድካም ያለባት ነውና ቀኖና ይሁናት ብሎ ነው። ሄዳ አባቴ በዚህ ያለው ኃጢአትሽ ይፋቅልሽ በለኝ አለችው። ይህስ ለሊቀጳጳሱ ለባስልዮስ ቢቻለው እንጂ ለእኔ አይቻለኝም አላት። አሁን ለርሱ የማይቻለው ሆኖ አይደለም። ቅዱሳን የራሳቸው ክብር ከሚገለጥ የወንድማቸው ክብር ቢገለጥ ይወዳሉና ነው። ዳግመኛም ስትሄድ ስትመጣ ድካም ያለባት ናትና ቀኖና ይሁናት ብሎ። ስትሄጅ ግን እንደቀደመው በሕይወተ ሥጋ አታገኚውም ሙቶ ሊቀብሩት ይዘውት ሲሄዱ ታገኛለሽ ሳትጠራጠሪ ካስክሬኑ ላይ ጣይው ይፋቅልሻል አላት።ብትሄድ ሞቶ ሊቀብሩት ይዘውት ሲሄዱ አገኘት። ሳትጠራጠር ከአስክሬኑ ላይ ብትጥለው ተፍቆላታል። ይህም የካህናትን መዓርግ ደግነት ያጠይቃል። በሕይወተ ሥጋም ሳሉ ከሞቱም በኋላ ኃጢአት እንደሚያስተሰር። ስምዖን ዘዓምድ የያዕቆብ ዘንጽቢን ደቀመዝሙር ነው። አብሮት ተምመሯል። ሊጠይቀው መጣ። ሰላም ለኪ ኦ እግዝእትየ ቅድስት ድንግል እያለ ሲያስተምር ሰማው። ኦ እግዝእትየን ከማን አገኘሐው መምህራችን ለእነገረን አለው። ነግሮናል እንጂ አልነገረንም ይመስክር ይመስክር ተባብለው ከመቃብሩ ላይ ቢሄዱ ዐሥሩ ጣቶቹ እንደፋና እያበሩ ተነስቶ "በሕይወትየ እብለኪ ሠላም ለኪ፤ ኦ ቅድስት ድንግል ከመ ስምዖን ዘዓምድ። ወድኅረ ሞትየሰ ኵሎሙ አዕዕምትየ ይብሉኪ ወይዌድሱኪ ሰላም ለኪ ኦ እግዝእትየ ቅድስት ድንግል ከመ ኤፍሬም ሶርያዊ" ብሎ መስክሮላታል።
ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ

ይህም ለቅዱስ ኤፍሬም ጸጋው ክብሩ ነው። ከሞተ በኋላ የሚናገረውን ዐውቆ ማመስገን። ሶርያዊ በሀገሩ ያሰኘው እስከዚህ ነው። ለብሐዊ በተግባሩ ሞ ቢረሌ መርጠብ ብርጭቆ ኩዝ ካቦ እየሰራ የዓመት ልብሱን የዕለት ምግቡን እያስቀረ ይመጸውት ነበር። ሲመጸውትም በሥላሴ በመላእክት በጻድቃን ስም አይመጸውትም በእመቤታችን ስም ይመጸውት ነር። ስለምን ነው ቢሉ የእመቤታችን ፍቅር ባያደርሰው ነው። እመቤታችንን ከመውደዱ የተነሳ እመቤቴ ምስጋናዋ እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደመባሕር አሸዋ በዝቶልኝ እንደ ልብስ ለሼው እንደ ምግብ ተመግቤው ጠግቤው እያለ ሲመኝ ይኖር ነበር። የሻቱትን መግለጽ ለእግዚአብሔር ልማዱ ነውና ገልጾለት ከአራት ሺህ በላይ ድርሰት ደርሷል።
ከዕለታት በአንድ ቀን በዕለተ ሰኑይ ጊዜው ነግህ ነው የነግህ ተግባሩን አድርሶ ከመካነ ግብሩ ተቀምጦ ሳለ እመቤታችን ትመጣልች። የብርሃን ምንጣፍ ይነጠፋል የብርሃን ድባብ የዘረጋል። ከዚያም ላይ ሁና "ሰላም ለከ ኦ ፍቁርየ ኤፍሬም" ትለዋለች። እርሱም ታጥቆ እጅ ነሥቶ ይቆማል። ወድሰኒ ትለዋለች። "ምድራውያን ጻድቃን ሰማዕታት ሰማያውያን መላእክት አንቺን ማመስገን የማይቻላቸው ለእኔ እንደምን ይቻለኛል?" አላት። "በከመ አለበወከ መንፈስቅዱስ ተናገር" አለችው። በተረቱበት መርታት ልማድ ነውና። "እፎኑ ይከውነኒ ዝንቱ እንዘ ኢየአምር ብእሴ(ይህ ነገር አንደምን ይሆንልኛል?) ብትለው መልአኩ መንፈሰ እግዚአብሔር ቅዱስ ይመጽእ ላዕሌኪ (መንፈስቅዱስ ይጸልልሻል)" ብሏት ነበርና። ከዚህ በኋላ ባርክኒ ይላታል። በረከተ ወልድየ ወአቡሁ ወመንፈስቅዱስ ይኅድር በላዕሌከ  ትለዋለች።  ተባርኮ ምስጋናዋን ይጀምራል።  
"በረከተ ወልድየ ወአቡሁ ወመንፈስቅዱስ ይኅድር በላዕሌከ" ብላ ስትባርከው


ሲያመሰግናትም ደቀመዝሙር ቅኔ ቆጥሮ እንዲቀኝ ድርሰት አስቦ እንዲጽፍ አይደለም። ብልህ ደቀመዝሙር ያጠናውን ቀለም ከመምህሩ ፊት ሰተት አድርጎ እንዲያደርስ እንደዚያ ነው እንጂ።
ስታስደርሰውም ከሰባት ከፍላ አስደርሳዋለች። ስለምን ቢሉ በሰባቱ ዕለታት መመስገን ፈቃዷ ቢሆን አንድም ሰባቱ ዕለታት ምሳሌዋ ናቸውና በዕለተ እሑድ ትመሰላለች፤ በዕለተ እሑድ አሥራወ ፍጥረታት፤ አራቱ ባሕርያት ተገኝተዋል። ከሷም ለዘኮነ ምክንያተ ፍጥረት በሕላዌሁ እንዲለው አሥራወ ፍጥረት ጌታ ተገኝቷልና። በዕለተ ሰኑይ ትመሰላለች፤ በዕለተ ሰኑይ ከዚህ እስከ ብሩህ ሰማይ መልቶ የነበረውን ውሃ ከሦስት ከፍሎታል። አንዱን እጅ ከላይ ሰቅሎታል ሐኖስ ነው። አንዱን እህ በዙሪያው ወስኖታል። አንዱን እጅ አጽንቶ የብርሃን ማኅደር አድርጎታል፤ ጠፈር ነው። ጠፈር የእመቤታችን፤ ብርሃን የጌታችን ምሳሌ ነው። ይህማ ጠፈር ምሳሌ ሆነች እንጂ የዕለቲቱ ምሳሌ ሆነቻ ብሎ ዕለቲቱ የእርሷ ጠፈር ከእርሷ የነሳው ሥጋ ብርሃን የጌታችን ምሳሌ አድርጎታል።
በዕለተ ሠሉስ ትመሰላለች፤ በዕለተ ሠሉስ “እግዚአብሔርም፦ ምድር ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን በምድርም ላይ እንደ ወገኑ ዘሩ ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን ታብቅል አለ እንዲሁም ሆነ።” እንዳለ በእጅ የሚለቀሙ አትክልት፤ በምሳር የሚቆረጡ ዕፅዋት በማጭድ የሚታጨዱ አዝርዕት ለሥጋውያን ምግብ እንዲሆኑ ተገኝተዋል። ከእርሷም የመንፈሳውያን ምግብ የሚሆን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገኝቷልና።
በዕለተ ረቡዕ ትመሰላለች። በዕለተ ረቡዕ ለይቁሙ ብርሃናት በገጸ ሰማይ ባለ ጊዜ ለሥጋውያን ምግብ የሚሆኑ ፀሐይ ጨረቃ ከዋክብት ተገኝተዋል። ከእርሷም ለመንፈሳውያን ምግብ የሚሆን ጌታ ተገኝቷልና።
በዕለተ ሐሙስ ትመሰላለች። በዕለተ ሐሙስ “እግዚአብሔርም አለ፦ ውኃ ሕያው ነፍስ ያላቸውን ተንቀሳቃሾች ታስገኝ፥ ወፎችም ከምድር በላይ ከሰማይ ጠፈር በታች ይብረሩ” እንዳለ በእግራቸው የሚሽከረከሩ፣ በክንፋቸው የሚበሩ በልባቸው የሚሳቡ በደመነፍስ ሕያዋን ሆነው የሚኖሩ ፍጥረታት ተገኝተዋል። ከሃ ተገኝተው በረው በረው የሄዱ አሉ ፤ ከውሃ ከዚያው የቀሩም አሉ። በረው በረው የሄዱት ያልተጠመቁ (ኢጥሙቃን) ምሳሌ ሲሆን ከውሃው የቀሩት የተጠመቁ (የጥሙቃን) ምሳሌ ነው። በልባቸው የሚሳቡ  የሰብአ ዓለም፤ በእግራቸው የሚሽከረከሩ ከትሩፋት ወደ ትሩፋት የሚሄዱ የባሕታውያን፤ በክንፋቸው የሚበሩ ተመስጦ ያላቸው የሰማዕታት ምሳሌ፤ ዕለቲቱ የቅድስት ድንግል ማርያም፣ ባሕር የጥምቀት፣ ምሳሌ ነው።
በዕለተ ዐርብ ትመሰላለች። በዕለተ ዐርብ በኵረ ፍጥረት አዳም ተገኝቷል፤ ዳግማይ አዳም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእርሷ ተገኝቷልና በዕለተ ዐርብ ትመሰላለች።
በዕለተ ቀዳሚት ሰንበት ትመሰላለች። በዕለተ ቀዳሚት ሥጋዊ ዕረፍት ተገኝቷል። “እግዚአብሔርም የሠራውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ፈጸመ በሰባተኛውም ቀን ከሠራው ሥራ ሁሉ ዐረፈ” እንዲል ከእርሷም የመንፈሳውያን ዕረፍት ጌታ ተገኝቷልና።


አዳን ከሆነው ልጅሽ እመቤታችን ጽንዕት በድንግልና ፀጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝልን።
                           "ጾሙን በሠላም አስፈጽሞ ለትንሣኤዋ እና ለእርገቷ በሠላም ያድርሰን"
                                                     ወስብሐት ለእግዚአብሔር