13

.

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው::" የማቴዎስ ወንጌል 7: 4

"እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅናወተት ግዙ።" ትንቢተ ኢሳይያስ 55 : 1

Friday, November 18, 2011

“ማር ይስሐቅ”


በክንፈ ሚካኤል
በአብ ስም አምነን አብን ወላዲ ብለን፤ በወልድ ስም አምነን ወልድን ተወላዲ ብለን፤ በመንፈስቅዱስ ስም አምነን መንፈስቅዱስን ሠራጺ ብለን፤ ምንም ለአጠይቆ አካላት ሦስት ስላልን በባሕርይ፣ በህልውና አንድ አምላክ ብለን አምነን ንዑድ ክቡር የሚሆን የአባታችን የማር ይስሐቅን ነገር የሚናገር መጽሐፍን እናስተዋውቃለን።


ይህን መጽሐፍ ማር ይስሐቅ ተናግሮታል። የማር ይስሐቅ ብሔረ ነገዱ ሀገረ ሙላዱ ሶርያ ነው። መጽሐፍ የተማረበት ምሥጢር ያገመረበት ቂሳርያ ነው። ቂሳርያ ለምን ሄደ ቢሉ ከኤፍሬም ዘንድ። የኤፍሬም ሀገሩ ሶርያ አይደለምን ቢሉ ለዚህስ ምክንያት አለው፤ አርዮስ ሎቱ ስብሐት ወልድ ፍጡር በባሕርየ መለኮቱ አለ፤ ንጉሡ ቆስጠንጢኖስ ጉባኤ በኒቅያ ይሁን ብሎ አዋጅ ነገረ። በዚህ ምክንያት ሦስት መቶ አሥራ ስምንት ሊቃውንት ተሰበሰቡ። ከኒህ አንዱ ያዕቆብ ዘንጽቢን ሲሆን ቅዱስ ኤፍሬምም የያዕቆብ ዘንጽቢን ደቀ መዝሙር ነው። ከጉባኤው ሲሄድ አስከትሎት ሄዷል። አርዮስን ረተው ለይተው ሲመለሱ ቂሳርያ አደሩ። በዚያን ሌሊት ራእይ ያያል። ዓምደ ብርሃን ተተክሎ ጨለማውን ሲያርቀው አየ። ማን እንደሆነ ግለጽልኝ ብሎ ቢያለመክት ባስልዮስ ዘቂሳርያ መሆኑን ገለጸለት። የእርሱን ነገር ስለምን ገለጸለት ቢሉ በቦታ ቢለይ በማዕረግ እንዳልተለየ ለማጠየቅ ነው። በዓምድ መታየቱ ስለ ምንድን ነው ቢሉ ዓምድ ቤትን ያጸናል እርሱም የምእመናንን ልቡና ያጸናልና ነው። ብርሃኑ ጨለማውን እንዲያርቅ እርሱም ከምእመናን ልቡና ክህደትንና ድንቁርናን ያርቃልና ለምክንያት ዓምደ ብርሃኑ ታየው። ለጊዜው ልቅር ብሎ አሰበ፤ ኋላ ግን እንኳን መምህር ሌላውን ቢሆን ያወጡትን ከቦታው አግብቶ መሄድ ይገባልና መምህሩ ያዕቆብ ዘንጽቢን ከቦታው አግብቶ ተመልሷል። መመለሱም ስለሦስት ነገር ነው፤ በዓይነ ነፍስ ያዩትን በዓይነ ሥጋ ማየት ይገባልና። ዳግመኛ ከእንደዚህ ያለ ሰው ቢጫወቱ ጸጋ ክብር ይገኛልና፤ ሦስተኛ የመንፈስቅዱስ ይሆን ወይስ ሰይጣን በምትሃት ተጫውቶብኝ ነው ብሎ ተመለሰ። ስለተመለሰ እንዳየው ሁኖ አላገኘውም። ኩፋር ለብሶ፣ ኩፋር ጠምጥሞ፣ ገበታው የወርቅ፣ ወንጌል በወርቅ አትሮንስ አዘርግቶ፣ ጉባኤ ሰርቶ ሲያስተምር አገኘው። “ወተኀዘበ ልቡ ለኤፍሬም” እንዲል ልቡናው ተጠራጠረበት። “እስመ ውስተ ምይንት ነፍስ ኢተኀድር ጥበብ ወውስተ ሥጋ ዘቅኑይ ለኃጢአት ኢየኀድር መንፈስ” ይላል፡ በውኑ በእንደዚህ ያለ ሰው ጸጋ እግዚአብሔር ታድራለእን በምኑናን በትሑታን ታድራለች እንጂ አለ። በኋላ ግን አራት ነገር አይቶ ተረዳ፤ መጀመሪያ ካፉ ነጸብራቀ እሳት እየወጣ ሕዝቡን ሲዋሃዳቸው ያያል። ሁለተኛ ርግብ በራሱ ላይ ተቀምጣበት ተመለከተ። ሦስተኛ ተሐዋስያን ከልብሱ ላይ ሲያርፉ እሳት እንደገባ ጅማት እርር ኩምትር እያሉ እንደ ቆሎ ሲረግፉ ያያል። አራተኛ ሰርሖተ ሕዝብ ካደረገ በኋላ “ኤፍሬምን ጥሩልኝ” ብሎ በስሙ አስጠራው። እርሱም “አስቀድሞ ካየሁት አሁን የሰማሁት ይብለጥ ስሜን አያውቅ ሀገሬን አይጠይቅ” ብሎ አደነቀ። በመጣም ጊዜ ባስተርጓሚ ሲጫወቱ “ቋንቋህ ይገለጽልኝ ዘንድ ጸልይልኝ” አለው። ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክት የባስልዮስ ቋንቋ ጽርዕ ነበር፤ የኤፍሬም ቋንቋ ሱርስት ነበርና ለባስልዮስ ተገልጾላቸው ሲጫወቱ አድረዋል። አሰናብተኝ ልሂድ ቢለው “መች ልትሄድ መጥተሃል” ብሎ ሕዝባዊ ነበር ቢሉ ዲቁና፤ ዲያቆን ነበር ቢሉ ቅስና ሹሞት ባጠገቡ የሚያስተምር ሆኗል። በዚህ ጊዜ ማር ይስሐቅ ተወለደ። ለትምህርት ሲደርስ አባት እናቱ ከኤፍሬም ዘንድ ሰደዱት ስለምን ቢሉ አጎቱ ነውና ተግቶ ነቅቶ ያስተምረዋል ብለው አንድም ሕጻን ከእናት ከአባቱ ካልተለየ አይማርም ብለው እንዲማር አንድም የተማረ ግብረ ገብ ነበርና ወደ እርሱ ዘንድ ሰደዱት። ማር ይስሐቅም ብሉይንና ሐዲስን ተማረ፣ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን አጸና። ከዚህ በኋላ እናትና አባቱ የካህን ሙያ እንደተማረ የጨዋ ሙያ ይማርልን ስደድልን አሉት፤ ሲሔድ ሕሊና ሥጋዊ ሕሊና መንፈሳዊ ሰውነቱን እንደ ሜዳ አድርገው ይራወጹበት ጀመረ። ሕሊና ሥጋዊ የካህን ሙያ ተምሬ በላይ እንደሆንሁ የጨዋ ሙያ ተምሬ በላይ እሆናለሁ ማለት ነው፤ ይህስ ትዕቢት ነው ብሎ በሕግ ጸንቼ ሥጋውን ደሙን ተቀብዬ ገንዘቤን መጽውቼ እኖራለሁ ማለት ነው። ሕሊና መንፈሳዊ ዓለም እንደ ጥላ ያልፋል እንደ አበባ ይረግፋል ብሎ መተው ነው። አንድም አንድ ወገን በሕሊና ሥጋዊ ቆሞ ለሕሊና መንፈሳዊ አጋዥ  ሆኖ ከዚህ ደርሼ ልምጣ ብሎ ዱር ለዱር ሄዶ ከአባ እብሎይ ገዳም ገባ። 25 ዓመት ገዳሙን እያገለገለ ዓይነ ምድር እየማሰ ቆየ። አባ እብሎይ ሲያርፉ እርሱን ባየሁበት ቦታ ማንን አያለሁ ብሎ አናብስት፣ አናምርት፣ አክይስት፣ አቃርብት ካሉበት ልምላሜ ዕጽ ነቅዐ ማይ ከሌለበት ሄደ ከዚያ ተገልጾለት ማር ይስሐቅን በጽርዕ ቋንቋ ጽፎታል።
ማር ይስሐቅን ከጽርዕ ወደ ዓረብ የሚመልሰው ጠፍቶ ለብዙ ጊዜያት ቆየ። በኋላም ኒክፋር የሚባል ሊቀ ጳጳስ ስምዖን ሚካኤል የሚባሉ ኤጲስ ቆጶሳት ረብ (ጥቅም) እንዳለበት አውቀው የሚመልስላቸው አጥተው ይኖሩ ነበርና ከብዙ ጥረት በኋላ አንድ ግብር የገባ የተማረ ቋንቋ የሚያውቅ ዲያቆን ተገኝቶ እርሱ ተርጉሞላቸዋል። ወደ ሀገረ ኢትዮጵያ መቼ መጣ ቢሉ ፊልክስዮስ በአጼ ድልነዓድ (ሠይፈ አርአድም) ጊዜ ሲገባ ማር ይስሐቅ ወደ ግዕዝ የተተረጎመበት ጊዜ ባይታወቅም በሰሊክ ዘደብረ ሊባኖስ የተድባበ ማርያም መነኩሴ በአጼ ገላውዴዎስ ጊዜ ተርጉሞታል የሚል ታሪክ አለ።
መጽሐፈ መነኮሳት የሚባሉት ሦስት መጻሕፍት ሲሆኑ እነዚህም ፊልክስዮስ፣ ማር ይስሐቅና አረጋዊ መንፈሳዊ ሲሆኑ፤ ፊልክስዮስ የቅዱሳን መነኮሳትን ታሪካቸውን ይናገራል፣ ዓረጋዊ መንፈሳዊ ጸጋቸውን ማዕርጋቸውን፣ ማር ይስሐቅ ጾራቸውን፣ ግብራቸውን ይናገራል።
ከዚህ ታላቅ መጽሐፍ ውስጥ አንዱን አንቀጽ እነሆ፡-
አንቀጽ 13፡ ገጽ 148
ዝልፋ ወትረ ለነፍስከ ኦ እኁ
ወንድሜ ሰውነትህን ዘወትር ዝለፋት
ወበላ ናሁ በጽሐ ተኃልፎትኪ እምሥጋ
ከሥጋ የምትለዪበት የምታልፊበት ጊዜ ደርሷል በላት።
ለምንት ትትፌሥሒ በዘአንቲ ሀለውኪ ዮም ቦቱ ወተኀድጊዮ
ትትፌሥሒ በዘሀለውኪ ብለህ ግጠም ባለሽበት ኋላ ጥለሽው በምትሄጅ ሥራ ዛሬ ለምን ደስ ይልሻል
ዘትዴለዊ ለርእየቱ ኅዳጦ ዘመነ
እርሱን በማየት ጥቂት ዘመን ተድላ ደስታ የምታደርጊበት
ወተኃጥኢዮ እስከ ለዓለም
ኋላ ብዙ ዘመን በምታጭው
አጽምዒ ኀበ ዘቅድሜኪ
ርእዪ ሲል ነው የቀደመ ሥራሺን ዕወቂ
ወሐልዪ ዘገበርኪ ምንት ውእቱ
የሠራሽው ሥራ ምንም እንደሆነ አስቢ አለ። ጽድቅም እንደሆነ ኃጢአትም እንደሆነ ማለት ነው።
ወምስለ መኑ አኀለፍኪ መዋዕለ ሕይወትኪ
ያለ ዘመንሽን ከማን ጋራ ፈጸምሽው። ከጌታ ጋራ ነው ከሰይጣን ጋራ
አው መኑ ዘይትቄከፍ ጻማ ምግባርኪ
ደክመሽ የሠራሽውን የሚቀበልሽ ማነው። ጌታ ነው ወይስ ሰይጣን ነው
ወለመኑ ዘአስተፍሣሕኪዮ በተጋድሎትኪ
በትሩፋትሽ ማንን ደስ አሰኘሽ። ጌታን ነው ወይስ ሰይጣንን ነው
ከመ ይጻዕ ለቀበላኪ በጊዜ ፀዓትኪ
በጊዜ ሞትሽ ሊዋሃድሽ የሚመጣው ማን ነው
ወመኑ ውእቱ ዘተሐሥየ በሑረትኪ ከመ ታዕርፊ ውስተ መርሶሁ
በመንግሥተ ሰማይ አርፈሽ ትኖሩ ዘንድ በስራሽ ደስ ያለው ማን ነው። ሰይጣን አለመሆኑ በዚህ ይታወቃል። ሰይታን በመንግስተሰማይ ስንኳን ሌላ ሊያሳርፍበት እሱ ሊያርፍበት ቦታ የለውምና።
ወበእንተ ምንት ፃመውኪ ወተመንደብኪ
ለማን ብለሽ ደከምሽ ለማን ብለሽ መከራ ተቀበልሽ’ ለመንግስተ ሰማይ ብለሽ ነው ወይስ ለገሃነም ብለሽ ነው።
ወምንት ክዋኔሁ ከመ ትርብሒዮ በፍሥሐ
ደስ ብሎሽ ታገኚው ዘንድ አኳሆኑስ ምንድን ነው።
ወአይኑ ዕፀ ሕይወት ዘአጥረይኪ በዓለም ዘይመጽእ ከመ ይትቀበልኪ በጊዜ ፀአትኪ።
ነፍስሽ ከሥጋሽ በተለየች ጊዜ በመንግሥተ ሰማይ ይዋሃድሽ ዘንድ ገንዘብ ያደረግሽው ምንድን ነው። አንድም ገንዘብ ያደረግሽው ምግባር ምንድን ነው።
ወበአይ ገራህት ተዓስቡኪ (ማቴ. 20፡1-8)
በማናቸው እርሻ ሊያውሉሽ ተቃጸሩሽ ማለት በማናቸው ማዕርግ ተቃጸሩሽ በባለሠላሳው ነው በባለስልሳው ነው ወይስ በባለመቶው ነው።
ወመኑ ውእቱ ዘተከሀልኪ ላዕለ አግብዖ ሀስብ ኀቤኪ በጊዜ ዕርበታ ለፀሐየ ተፈልጦትኪ (ማቴ. 1፡ 8)
ነፍስሽ ከስጋሽ የምትለይበት ፀሐይ ዕድሜሽ በገባ ጊዜ ዋጋሽን እሰጥሻለሁ ያለሽ ማነው ጌታን ነው ዲያብሎስን ነው። ጌታ ቢሆን ክብር ይሰጣታልና ዲያብሎስ ቢሉ ፍዳ ያመጣባታልና እንዲህ አለ።
ኦ ነፍስ ሕቲ ርእስኪ
ነፍስ ሆይ ሰውነትሽን መርምሪ።
ወነጽሪ በአይ ምድር ይከውን መክፈልትኪ
እጻሽ በማናቸው ቦታ እንደሆነ እወቂ አለ። መንግስተ ሰማይም እንደሆነ ገሃነምም እንደሆነ እወቂ።
ወለእለ ይትአገሱ ኃዘናተ ወትካዛተ ወፃዕቃተ
ጭንቅ ጭንቅ ለሚሆን መከራውን ለሚታገሱ
ወዘዘዚአሁ ሥቃጣተ
ልዩ ልዩ የሚሆን ሥቃይ ለሚታገሡ ሰዎች የሚሰጥ ክብር
ይኩነነ ለኩልነ አስተርእዮታቲከ
ለሁላችን የሚደረግ ምሥጢር የሚገለጽባት
ኀርክቦ ድልዋነ ሎቱ
ክብሩን በቅተን እናገኘው ዘንድ። አንድምይርከብነ ድልዋነ ጸጋው የበቃን ሆነን ያገኘን ዘንድ
በጸጋሁ ለመድኃኒነ
በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቸርነት
ወበአፍቅሮቱ ሰብአ
ሰውን በመውደዱ
ይእዜኒ
ዛሬ ባለው ዓለም
ወበዓለም ዘይመጽእ
በሚመጣው ዓለም
ወእስከ ለዓለመ ዓለማት
በማይፈጸመው ዓለም ሰውን በመውደዱ አሜን። በእውነት።

ውድ አንባብያን ሕይወቶን እንዲያቀኑ፣ በሃይማኖት እንዲጸኑ “ማር ይስሐቅን” አንብቡ እንላለን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ፤ ወለወላዲቱ ድንግል፤ ወለመስቀሉ ክቡር
 ምንጭ፡ ፍኖተ - ብርሃን መጽሔት በቦሌ መ/ብ/ቅ/እግዚአብሔር አብ ቤ/ክ ሰ/ት/ቤት የሚዘጋጅ

22ቱን ሥነ-ፍጥረት እና 22ቱ የእግዚአብሔር ኅቡዕ ስሞች



22ቱን ሥነ-ፍጥረት ምሳሌ በማድረግ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት የእግዚአብሔርን ኅቡዕ ስሞች እንደሚከተለው በዝሙሩ አመስግኖታል።  በመዝሙረ ዳዊት 118
1.     አሌፍ ፡ ዓለምን ከነጓዟ ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ የፈጠረ እግዚአብሔር ማለት ነው።
2.    ቤት፡ እግዚአብሔር ሁሉን መስጠት የሚችል ቸር ለጋስ ባለጸጋ ማለት ነው።
3.    ጋሜል፡ እግዚአብሔር ሊመረመር የማይችል ግሩም ድንቅ ማለት ነው።
4.    ዳሌጥ፡ እግዚአብሔር በጌትነቱ ዙፋን ለዘለዓለም ይኖራል ማለት ነው።
5.    ፡ እግዚአብሔር በአንድነቱ በሦስትነቱ ለዘለዓለም ይኖራል ማለት ነው።
6.   ዋው፡ እግዚአብሔር በመንግሥት በሥልጣን በአገዛዝ በባህርይ አንድ አምላክ የሆነ ማለት ነው።
7.    ዛይ፡ እግዚአብሔር በሥራው ሁሉ እየታሰበ ሲመሰገን የሚኖር ፈጣሪ ማለት ነው።
8.    ሔት፡ እግዚአብሔር በመንግሥቱ ሽረት በባሕርዩ ኅልፈት የሌለበት ለዘለዓለም ሕያው የሆነ ማለት ነው።
9.   ጤት፡ እግዚአብሔር ጥበብን የሚገልጽ ከጥበበኞች ይልቅ ጥበበኛ የሆነ አምላክ ማለት ነው።
10.  ዮድ፡ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለ እሱ ኃያልና ጽኑዕ የሆነ ማለት ነው።
11.    ካፍ፡ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የሌለ ሁሉን ማድረግ የሚቻለው አምላክ ማለት ነው።
12.  ላሜድ፡ እግዚአብሔር ልዑለ ባሕርይ የሆነ ማለት ነው።
13.  ሜም፡ እግዚአብሔር ንጹሕ ባሕርይ የሆነ አምላክ ማለት ነው።
14.  ኖን፡ እግዚአብሔር የነገሥታት ንጉሥ የገዥዎች ገዥ የሆነ አምላክ ማለት ነው።
15.  ሳምኬት፡ እግዚአብሔር ሁሉን የሚገዛ አምላክ ማለት ነው።
16.  ዔ፡ እግዚአብሔር ታላቅና ገናና የሆነ አምላክ ማለት ነው።
17.  ፌ፡ እግዚአብሔር ተወዳጅ የሆነ አምላክ ማለት ነው።
18.  ጻዴ፡ እግዚአብሔር ሐሰት የሌለበት እውነተኛ አምላክ ማለት ነው።
19.  ቆፍ፡ እግዚአብሔር ለልበ ቅኖችና ለየዋሃኖች ቅርብ የሆነ አምላክ ማለት ነው።
20. ሬስ፡ እግዚአብሔር ክብሩ ከእርሱ ለእርሱ የተገኘ የሁሉ ጌታ ማለት ነው።
21.  ሳን፡ እግዚአብሔር በሥራው ሁሉ የተመሠገነ ማለት ነው።
22. ታው፡ እግዚአብሔር እንቅልፍ የሌለበት ትጉህ፤ ድካም የማይሰማው ጽኑዕ የሆነ ፈጣሪ ማለት ነው።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ፤ ወለወላዲቱ ድንግል፤ ወለመስቀሉ ክቡር
ምንጭ፡ መዝሙረ ዳዊት
የቦ/መ/ብ/ቅ/እግዚአብሔር አብ ቤ/ክ ሰ/ት/ቤት

Thursday, November 17, 2011

ሰው




በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
"ሰው ሁን"
ሰው ማለት ነፋሳዊነት፣ እሳታዊነት፣ ውኃዊነት፣ መሬታዊነት ባሕርያት ያሉት በነፍስ ተፈጥሮውም ነባቢት ለባዊትና ሕያዊት የሆነች ነፍስ ያለችው ፍጥረት ነው፡፡ እንዲህ ብለን ግን የሰውን ተፈጥሮ ጠቅልለን መናገር አይቻለንም፡፡ ምክንያቱም ሰውን ከሌሎች ፍጥረታት ይልቅ እጅግ ልዩ በሆነ መልኩ በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል ተፈጥሮአልና፡፡ ስለዚህም ቅዱሳን አባቶች  ከዚህ በላይ ከሰጠነው ትንታኔ በመውጣት እንዲህ ብለው ሰው ለሚለው ስያሜ ትርጓሜ ይሰጡታል፡፡

ቅዱስ ባስልዮስ ዘቄሳርያ “ከትምህርቶች ሁሉ ታላቁ ትምህርት ራሰን ማወቅ ነው፡፡ አንድ ሰው ራሱን ካወቀ እግዚአብሔርን ያውቀዋል፡፡ እግዚአብሔርን ካወቀ ደግሞ እግዚአብሔር አምላኩን ይመስላል፡፡” ሲል ቅዱስ ይስሐቅም “አንተ በልብህ ንጹሕ ከሆንህ ሰማይ በውስጥህ ነው፡፡ በውስጥህም መላእክትንና የመላእክትን ጌታ ትመለከታቸዋለህ” (The Orthodox Church by Timothy Ware) ቅዱስ ይስሐቅ እንዲህ ማለቱ ያለ ምክንያት ሆኖ አይደለም፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ቃሉን በተግባር መልሰው ለሚተገብሩ ሰዎች “የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ ማደሪያ እናደርጋለን፡፡”(ዮሐ.14፡23) የሚለውን ይዞ ነው፡፡ አካላችን በሰማይ የሚኖረው አባታችን ማደሪያ ከሆነ እኛም ሰማይ ሆንን ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በእኛ ሰውነት ውስጥ ካለ ደግሞ ቅዱሳን መላእክትም መገኘታቸው እርግጥ ነው፡፡

ከዚህ ጠንከር ባለ መልኩ ደግሞ የአሌክሳንደሪያው ቅዱስ ቀሌምንጦስ “ወንድምህን አስተውለህ ስትመለከተው እግዚአብሔርን ትመለከተዋለህ” ይላል፡፡ ቅዱስ ኤፍሬምም “በሰው ላይ በአመፃ የምትነሣሣ ከሆነ በእግዚአብሔር ላይ እንደተነሣሣህ ቁጥር ነው፡፡ ለባልንጀራህ አክብሮትን የቸርከው ከሆነ እነሆ እግዚአብሔርን አከበርኽ፡፡” ይላል፡፡

ቅዱስ ሄሬኔዎስ፣ ቅዱስ አትናቴዎስ፣ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ እንዲሁም ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ በአንድነት “ሰው በጸጋ አምላክ ይሆን ዘንድ ከሦስቱ አካላት አንዱ እግዚአብሔር ቃል ሰው ሆነ” ብለው ያስተምራሉ፡፡ (The Image and likeness of God by Vladimir Lossky) በእርግጥ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም የማቴዎስን ወንጌል በተረጎመበት በሁለተኛ ድርሳኑ ገጽ  9 ላይ “He suffered Himself of to be called also the Son of David, that  He might make thee Son of God.  “አንተን የእግዚአብሔር ልጅ ያደርግህ ዘንድ የዳዊት ልጅ መባልን መረጠ፡፡ ቅዱስ ኤፍሬምም “ሙሴ በነዝር እባብ የተነደፉት እስራኤላውያን ከፍ ተብሎ በተሰቀለው የነሐስ እባብ እንደ ተፈወሱ አስተዋለ፡፡ በእርሱም በጥንቱ እባብ የተነደፉትን የሚያድነውን(ክርስቶስን) ከሩቅ ተመለከተው፡፡ ሙሴ እርሱ ብቻ ከእግዚአብሔር የጸጋው ብርሃን ተካፋይ እንደሆነ አስተዋለ፡፡ በእርሱም እግዚአብሔር ቃል ወደ እዚህ ዓለም በመምጣት አማልክት ዘበጸጋን በትምህርቱ እንደሚያበዛቸው ተመለከተ፡፡” ይላል፡፡

እኚሁ አባቶች ሰው ገና ሲፈጠር በጸጋ አምላክ እንዲሆን ተደርጎ መፈጠሩንም ያስረዳሉ፡፡ ለምሳሌ  ቅዱስ ኤፍሬም “ጌታ ሆይ ሠዓሊ ቀለማትን አዋሕዶ ሥዕሉን እንዲሥል አንተም አርአያህንና አምሳልህን እንዲመስሉ ሁለቱን አካላት አዋሕደህ አንድ አካል በማድረግ በራስህ መልክ  ፈጠርካቸው፡፡ ወደ ራስህ አርአያ ተመለከትኽ የራስህን አርአያና አምሳል በእጆችህ ሣልኸው፡፡ ጌታ ሆይ እነሆ የሣልኸውን ሥዕል አንተው ሰው በመሆን ገለጥኸልን፡፡” ሲል ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ ሰው ገና ከአፈጣጠሩ በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ስለመፈጠሩ ሲያስረዳ  “በአዳምና በሔዋን አስቀድሞ ያሳየን ምሳሌ ይፈጸም ዘንድ የሙሽራው ጎን በጦር ተወጋ፤ ከጎኑም ቤተክርስቲያን በፈሰሰው ደሙ መሠረታት(በደሙ የዋጃትን ቤተክርስቲያን አንዲል የሐዋ.20፡28)፤ እግዚአብሔር ይህን ባወቀ አዳምንና ሔዋንን በብቸኛ ልጁ አርዓያና አምሳል ፈጠራቸው፡፡” ብሎ ጽፎልን እናገኛለን ፡፡ (Spirituality in Syrian Tradition by Sebastian brock) ስለዚህም ወደ ድምዳሜው ስንመጣ ሰው ማለት በጸጋ አምላክ ሆኖ የተፈጠረ ፍጥረት መሆኑን በእነዚህ ሁሉ ቅዱሳን አባቶች አስተምህሮ መረዳት እንችላለን፡፡ በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ተፈጠረም ስንል የጸጋ እውቀት የተሰጠው ክፉውን ከበጎ መለየት የሚችል ፍጡር መሆኑን ያስረዳናል፡፡ ከላይ ከሰጠናቸው ትንታኔዎች ተነሥተን ሰው ለሚለው ስያሜ ትርጉም ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ ከሦስቱ ባሕርያተ ነፍስ ተፈጠረ ብለን ብቻ የምንቋጨው እንዳልሆነ መረዳት እንችላለን፤ እጅግ ሰፊ ትርጉም ያለውና በውስጡም ታላቅ የሆነ መልእክትን እንደያዘ እንገነዘባለን፡፡ ይህን እጅግ ሰፊና ጥልቅ የሆነ ትርጉም የያዘው “ሰው” የሚለው ስያሜ ለመረዳት መልክና ምሳሌ ወይም አርአያና አምሳል የሚሉትን ቃላት አስቀድሞ መረዳት ይገባናል፡፡

መልክ (አርአያ) ማለት ምን ማለት ነው?

መልክ (አርአያ) ማለት ሰው እግዚአብሔር አምላኩን ይመስል ዘንድ በተፈጥሮ የተሰጡት ባሕርያት ናቸው፡፡ እነዚህ ባሕርያት ከሰው ፈጽሞ የሚወሰዱ አይደሉም፡፡ ብዙ ቅዱሳን አባቶች መልክ (አርአያ) ለሚለው ቃል ትርጉም ሲሰጡ ሲለያዩ ይታያሉ፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ዘፍጥረትን በተረጎመበት ድርሳኑ ላይ መልክ (አርአያ) ማለት ለሰው በተፈጥሮ ፍጥረታትን ለሚገዛበት ባሕርይው የተሰጠው ስያሜ ነው ይላል “እርሱ (ሙሴ) በእግዚአብሔር መልክ ሲል በምድር ያሉትን ሁሉ ሰው የሚገዛቸው መሆኑን የሚያመለክተን ነው፡፡ በምድር ላይ ከሰው በላይ የሆነ ፍጥረት የለውም” ይላል፡፡ እንዲሁም ይህ ቅዱስ ስለ ሰው ተፈጥሮ ሲያስተምር “ ሰው ከሚታዩት ፍጥረታት በላይ የሆነ ፍጥረት ሲሆን ለዚህ ፍጥረት ሲባል ሁሉም ፍጥረታት ተፈጠሩ” ይላል፡፡ ያም ማለት ሰማይ፣ ምድር፣ ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት፣ ተሳቢና ተራማጅ እንዲሁም በምድር ላይ ያሉ ፍጥረታት ሁሉ ለእርሱ ተፈጠሩ”

አንዳንድ ቅዱሳን ሰው በእግዚአብሔር መልክ መፈጠሩን መንፈሳዊ ከሆነው ተፈጥሮው ጋር አገናኝተው ያስተምራሉ፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ኤፍሬም በእግዚአብሐር መልክ የተፈጠረችው ነፍሳችን ናት ብሎ ሲያስተምር “አንተ መንፈሳዊ ተፈጥሮ አለህ፤ ነፍስ የእግዚአብሔር አርዓያና አምሳል ናት” ይላል፡፡ ሰው በነፍስ ተፈጥሮው ነጻ ፈቃድ፣ ነገሮችን የማገናዘብ ችሎታ እንዲሁም ሓላፊነት የሚሰማው ሆኖ የተፈጠረ ፍጥረት ነው፡፡ በእነዚህ ሰው እግዚአብሔር አምላኩን ይመስላል፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ ግን ነፍሳችንም ሥጋችንም በእግዚአብሔር አርዓያ እንደተፈጠሩ ግልጽ በሆነ መልኩ ሲያስረዳ  “በአዳምና በሔዋን አስቀድሞ ያሳየን ምሳሌ ይፈጸም ዘንድ የሙሽራው ጎን በጦር ተወጋ፤ ከጎኑም (በፈሰሰው ደሙ) ቤተክርስቲያን ተመሠረተች፤ እግዚአብሔር ይህን ባወቀ አዳምንና ሔዋንን በብቸኛ ልጁ አርአያና አምሳል ፈጠራቸው፡፡” ይለናል፡፡

ሰው ሰማያዊት አካል ስላለችው ረቂቁን ዓለም የመረዳት ችሎታ ሲኖረው ምድራዊውም አካል ስላለው ምድራዊውም እውቀት አለው፡፡ ሰውን ከሰማያውያን መላእክትና ከምድራውያን መላእክት ጋር ስናስተያየው ለሁለቱም ዓለማት እንግዳ እንዳልሆነ በሁለቱም ዓለማት እኩል የመኖር ተፈጥሮአዊ ባሕርይ እንዳለው፣ የሰማያውያንንም የምድራውያንንም እውቀት ገንዘቡ ያደረገ ፍጥረት መሆኑን ስናስተውል በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ መፈጠሩን እንገነዘባለን ፡፡

እግዚአብሔር አምላክ የሰማያውያንም የምድራውያንም ፍጥረታት እውቀት ባለቤት ነው፡፡ ሰውም በጸጋ ለሰማያውያን መላእክት ለምድራውያን ፍጥረታት እውቀት ባይተዋር አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በላይ በሰማይ በታች በምድር ከሰማይም በላይ ከሰማይም በታች ይኖራል፡፡ ሰው ሙሉ ለሙሉ አይሁን እንጂ በታች በምድር ግዙፋን ፍጥረታትን ሲገዛ በላይ በሰማይ ደግሞ ከሰማያውያን መላእክት ጋር እኩል በምስጋና ይሳተፋል፡፡ ከዚህም ተነሥተን ሰው በሁለት ዓለማት እኩል የመኖር ተፈጥሮ እንዳለው ማስተዋል እንችላለን፡፡

ቅዱስ ጎርጎርዮስ ሰው በእግዚአብሔር መልክ ተፈጠረ ስንል  በነፍሱም በሥጋውም እንደሆነ ሲያስረዳ እንዲህ ብሎ ጽፎልን እናገኛለን፡፡ “ሰው ምድራዊና መንፈሳዊ አካል ያለው ፍጥረት ሆኖ በመፈጠሩ ከመላእክት በተለየ በእግዚአብሔር አርዓያና አምሳል ተፈጠረ ተባለለት፡፡ ሰው ምድራዊ ተፈጥሮ ባይኖረው ኖሮ በእግዚአብሔር አርአያ ተፈጠረ ባላልነው ነበር፡፡ ስለዚህም ሰው በምድራዊው ተፈጥሮውም የእግዚአብሔርን መልክ ይዟል፡፡” ብሎ ያስተምራል፡፡

በእርግጥ ይህ እውነት ነው፡፡ ለምሳሌ እግዚአብሔር ፍጥረትን ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ ፈጥሮአቸዋል፡፡ ወደ መኖርም ባመጣቸው ፍጥረታትም ሌሎችንም ፍጥረታትን ፈጥሮአል፡፡ ለምሳሌ ብንወስድ የሰው ተፈጥሮ አንዱ ነው፡፡ እግዚአብሔር አስቀድሞ ምድርን ፈጠራት፡፡ ከምድርም አፈር ሰውን አበጀው፡፡ ይህ ዓይነት ባሕርይ እንደ እግዚአብሔር አይሁን እንጂ በሰውም ላይ ይታያል፡፡ ሰው ምንም እንኳ ነገሮችን ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ እንደ አምላኩ አይፍጠር አንጂ የተፈጠሩ ፍጥረታትን በመጠቀም ምድራዊው አኗኗሩ ቀላልና ምቹ አንዲሆንለት ሲል ከመላእክት በተለየ እጅግ ድንቅና ሊታመኑ የማይችሉ ተግባራትን ሲከውን ይታያል፡፡ በዚህም አምላኩን ይመስላል፡፡

ምሳሌ(አምሳል) ማለት ምን ማለት ነው ?

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እኛ የሰው ልጆች በእግዚአብሔር መልክ(አርአያ) የመፈጠራችን ዓለማው እግዚአብሔርን እንደ ችሎታችን መጠን እርሱን መስለን እንመላለስ ዘንድ ነው ይላል፡፡ ከዚህ ተነሥተን ምሳሌ (አምሳል) ስንል በተፈጥሮ የተሰጠንን ዕውቀት ተጠቅመን በተግባር እርሱን የምንመስልበት ሂደት እርሱ ምሳሌ (አምሳል)ይባላል፡፡ እግዚአብሔር በባሕርይው ፍቅር ነው፣ ትሑትና የዋህ ነው፣ ቅን ፈራጅ ነው፣ ጻድቅ ነው፣ ርኅሩኅ ነው፣ መሐሪ ነው፣ ታጋሽ ነው፡፡ እነዚህ ባሕርያት ሁሉ በእኛ ተፈጥሮ ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ እነዚህን ባሕርያት ወደ ተግባር መልሰን ስንፈጽማቸው እግዚአብሔርን መስለነዋል ወይም የእግዚአብሔር ምሳሌ ወይም አምሳል በእኛ ላይ ተንጸባርቆ ይታያል፡፡

አንዳንዶች “እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ፡፡”(ዘፍ.2፡7) የሚለውን ቃል ይዘው መንፈስ ቅዱስ ወደ ነፍስነት ተቀይሮ ለሰው ልጅ ተሰጠው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ይህ ግን ፈጽሞ ስህተት ነው፡፡ የአሌክሳንደሪያው ቅዱስ ቄርሎስ እንዲህ ዓይነት አመለካከት ላላቸው ወገኖች አንዲህ በማለት ይመልስላቸዋል፡- “በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት ሲል መንፈስ ቅዱስ ለሰው ነፍስ ሆነው ብላችሁ ትተረጉማላችሁን? እንዲህ ብሎ ማሰብ በራሱ በደል መሆኑን አትገነዘቡምን? እንዲህ የምትሉ ከሆነ እንግዲህ ነፍስ የማትለወጥ ናት ማለት ነዋ ! ያም ማለት ለለውጥ አትገዛም፡፡ ሁል ጊዜም ባለመለወጥ ትኖራለች ማለታችሁ ነው፡፡ ነገር ግን ነፍስ ለለውጥ የምትገዛ ናት፡፡ ስለዚህም የማይለወጠውን መንፈስ ቅዱስን ወደ ነፍስ ባሕርይ ተለወጠ በማለት ሳታችሁ፡፡ ስለዚህም እኛ እንዲህ ብለን አናስተምርም፡፡ ነገር ግን ከማይለወጠው መንፈስ ቅዱስ ነፍስ ተሰጠች እርሱዋም በመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ከበረች እንላለን፡፡”

ከዚህ የምንረዳው ፍጥረት የሆነች ሕያዊት ነፍስ ከእግዚአብሔር መሰጠቷን ነው፡፡ እቺን ነፍስ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በጸጋው አምላኳዋን እንድትመስል ያግዛታል፡፡ አዳምና ሔዋን በበደላቸው ምክንያት ያጡት የመንፈስ ቅዱስ ድጋፍ ነው፡፡ ይህም ጌታችን መድኃኒታችን በንፍሃት መንፈስ ቅዱስን በሐዋርያት ላይ እስኪያሳድር ድረስ ቀጥሎ ነበር፡፡ (ዮሐ.21፡22)

እኛ የሰው ልጆች የመንፈስ ቅዱስን እገዛ በኃጢአት ምክንያት ከማጣታችን የተነሣ ምንም እግዚአብሔርን በጸጋ የምንመስልበት ተፈጥሮ ቢኖረንም አልተቻለንም ነበር፡፡ ወደዚህ ወደ ቀደመ ክብራችን ለመመለስ ሰው ግዴታ ሊጠመቅና ሰውነቱን የመንፈስ ቅዱስ ቤተመቅደስ ሊያደርገው ይገባል፡፡ እንዲህ ከሆነ በእርሱ ሰውነት ውስጥ ያደረው መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር አምላክን መስሎ የሚኖርበትን ጸጋ ያገኛል፡፡ በእርሱም በተፈጥሮ ያገኘውን እግዚአብሔርን የመምሰል አቅም ተጠቅሞ በጸጋ እግዚአብሔርን ወደ መምሰል ያድጋል፡፡

ስለዚህ አንድ ሰው በትክክለኛው ተፈጥሮ ለመኖር ከፈቀደ የግድ ተጠምቆ ክርስቲያን በመሆን የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ሊያገኝ ይገባዋል፡፡ ያለበለዚያ ምኞት ቢኖረው እንኳ በትክክለኛው ተፈጥሮ መኖር ይሳነዋል፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ከቅድስት ድንግል ማርያም በነሣው ሰውነቱ በኩል ሰው እንደሆነ እንዲሁ እኛም ከመንፈስ ቅዱስ ተካፋዮች በመሆን እርሱን በጸጋ ወደ መምሰል ልንመጣ ይገባናል፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ስለዚህ ሲያስረዳ “በሥጋዊ ልደት ካልተወለደ በቀር መንፈሳዊ የሆነውን እርሱን ግዘፈ አካል አለው አንደማንለው ሁሉ አንዲሁ እኛም መንፈሳዊ በሆነ ልደት ካልተወለድን በቀር መንፈሳውያን አንባልም” ይለናል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስም በመንፈስ ቅዱስ ካልሆነ በቀር ጽድቅን መፈጸም እንደሚሳነን ሲያስረዳ “የማደርገውን አላውቅምና የምጠላውን ያን አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን እርሱን አላደርግም፡፡ …በውስጥ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛልና፤ ነገር ግን በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝን ሌላ ሕግ አያለሁ፡፡ እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል …” ይልና በቀጣዩ ምዕራፍ ላይ ለዚህ መልስ ሲሰጥ “እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኩነኔ የለባቸውም፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና፡፡” ይላል (ሮሜ 7፡15-25፣8፡1-2)

እንግዲህ እኛ ክርስቲያኖች እዳ አለብን “እንደ ሥጋ ፈቃድ ግን እንኖር ዘንድ ለሥጋ አይደለም፡፡ እንደ ሥጋ ፈቃድ ብንኖር እንሞት ዘንድ አለን፡፡ በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብንገድል በሕይወት እንኖራለን፡፡” (ሮሜ.8፡12-17) አሁን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ተጠምቀን እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚያግዘንን የመንፈስ ቅዱስ ጸጋን አግኝተናል፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረው “መልካምን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጥረናል፡፡” (ኤፌ.2፡10) ስለዚህ እንፍራ ከአሁን በኋላ ለምንፈጽማቸው ኃጢአቶች ምንም ምክንያት ማቅረብ አንችልም፡፡ ጽድቅን ከማድረግ ብንመለስ ወይም እያወቅን ከመፈጸም ብንለግም ቅጣቱ በእኛ ላይ ይከፋል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በውስጣችን ያደረውን መንፈስ ቅዱስን ሰምተን ለመታዘዝና እርሱን መስለን ለመመላለስ ያብቃን፡፡ 
ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይሁን ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን፡፡
Source: www.eotc-mkidusan.org

ዘመነ አስተምህሮ

አትም ኢሜይል
ኅዳር 6/2004 ዓ.ም
በቤተ ክርስተያናችን የዘመን አቆጣጠር /አከፋፈል/ መሠረት ከኀዳር 6 ጀምሮ እስከ ታኀሣሥ 13 ድረስ ያለው ወቅት ዘመነ አስተምህሮ ይባላል፡፡

መሀረ ማለት ይቅር አለ ማለት ሲሆን፤ ዘመነ አስተምህሮ ማለት ይቅርታ የመጠየቅ /የምልጃ/ ዘመን ማለት ነው፡፡ ዘመኑ ቤተ ክርስቲያን ስለ ልጆቿ ይቅርታ የምትጠይቅበት፤ ምዕመናንንም ስለ በደላቸው ይቅርታ የሚጠይቁበት፤ ስለዚህም በስፋት ትምህርት የሚሰጥበት ዘመን ነው፡፡
በዚህ ዘመን ያሉት አምስት እሑዶችና በእነዚህ እሑዶች የሚጀምሩት ሳምንታት አስተምህሮ፣ ቅድስት፣ ምኩራብ፣ መጻጉዕ፣ እና ደብረ ዘይት በመባል ይጠራሉ በየሳምንቱ ቤተ ክርስቲያን የምታቀርበውን ትምህርት በየጊዜው እናከብራለን የመጀመሪያውን ሳምንት /የአስተምህሮ/ ትምህርት እነሆ: -

እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል፤ በደላችንን ይቅር በለን /ማቴ.6-12/

ይህ ቃል የተወሰደው ጌታችን በደቀ መዛሙርቱ በኩል እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ለሚኖሩ /ዛሬም ላለን/ ክርስቲያኖች እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ ብሎ ካስተማረው ፀሎት ነው፤

በሰማይ የምትኖር አባታችን ሆይ ስምህ ይቀደስ መንግሥትህ ትምጣ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን፤ የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን፤ እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን፤ ከክፉም አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን፤ መንግሥት ያንተ ናትና ኃይልም ክብርም ለዘለዓለም አሜን/ ማቴ.6. 9-14/

ይህ ጸሎት በጥንታውያን የቤተ ክርስቲያን አባቶች እና ሊቀውንት «የጌታ ጸሎት» ተብሎ ይጠራል፡፡ በእኛ ቤተ ክርስቲያን የጸሎቱን የመጀመሪያ ሐረግ በመያዝ «አባታችን ሆይ» ወይም በግእዝ «አቡነ ዘበሰማያት» እንለዋለን፡፡

ይህ ጸሎት ጌታችን ራሱ ያስተማረው በመሆኑ በቤተ ክርስቲያን ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ የሌሎች ጸሎታት ሁሉ ማሰሪያ /ማሳረጊያ/ ሆኖም ያገለግላል፡፡ በውስጡም «አባታችን ሆይ» ከምትለው ከመጀመሪያዋ ሀረግ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ እጅግ ጥልቅ የሆኑና ነፍስን የሚያጠግቡ ወደ ሰማይ ከፍ የሚያደርጉ መንፈሳዊና ነገረ መለኮታዊ መልእክቶችን ያዘለ ነው፡፡

ይህ የዘመነ አስተምህሮ የመጀመሪያው ሳምንት ስለ ይቅርታ የሚሰበክበት ነውና በጸሎቱ ውስጥ ስለዚህ የሚናገረውን አንቀጽ መሠረት አድርገን እንማራለን፤

«እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን» ከዚህ ቃል በርካታ ነገሮችን እንማራለን፤

1. እግዚአብሔር ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን እንደሚወድ

አምላካችን ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ባይወድ ኖሮ ይቅርታን እንድንጠይቅ አይነግረንም ነበር፡፡ አዎ እኛ ከተመለስን ምንም ያህል በደለኛ ብንሆን ይቅር ሊለን፤ ምንም ያህል ብንቆሽሸ ሊያድነን ዝግጁ ነው፡፡ እንዲህ እያለ ይጠራናል፤ «እናንተ ሸክማችሁ የከበዳችሁ፤ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ»፡፡ ስለዚህ በዚሀ ጸሎትም ላይ «በደላችንን ይቅር በለን» ብለን እንድንጠይቀው አስተማረን፤ ይቅር ይለን ዘንድ፡፡

2. ይቅር ለመባል ምን ማድረግ እንዳለብን፤

ይቅር ሊለን ስለ ወደደም ይቅርታን ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለብን በዚሁ ቃል ነግሮናል፤ ማድረግ ያለብን ምንድን ነው?
- ኀጢአታችንን ማወቅ፣ ማመን፣ ማስታወስ
- የበደሉንን ይቅር ማለት
- ይቅርታን መለመን

ኅጢአታችንን ማወቅ /ማመን/

ጌታ «በደላችንን ይቅር በለን» ብለን እንድንጸልይ ሲነግረን በመጀመሪያ ደረጃ በደለኛ እንደሆንን እያስታወስን /እንድናስታውስ እያደረገን/ ነው፡፡

ሁልጊዜም በማሰብ፣ በመናገርና በማድረግ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የሆነውን ልባችንን /ኅሊናችንን/ እና ሰውነታችንን እናቆሽሻለን፤ መድኃኔዓለም ክርስቶስ የሞተለትን ማንነታችንን እናጎድፋለን፡፡ ይህም የሰው ልጆች በቅድስና እርሱን መስለን እንድንኖር በኋላም የተዘጋጀልንን የዘለዓለም መንግሥት እንድወርስ ብቻ ፈቃዱ የሆነውን እግዚአብሔርን ያሳዝናል፤ በአርአያውና በአምሳሉ ለክብር የፈጠረው ሰውነታችን መጉደፍ ያስቆጣዋል፤ ንጹሐ ባሕርይ የሆነ እርሱ ኀጢአት አይስማማውምና፡፡

እንግዲህ ይቅር ለመባል በመጀመሪያ እንዲህ ኀጢአት እየሠራን መሆኑን ማወቅና ማመን ያስፈልገናል፡፡ ወደዚህ ዕውቀት ለመድረስም የቅዱሳት መጻሕፍትን ቃል መማር የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም ስህተት የሚታወቀው ያለውን ሁኔታ /ድርጊታችንን ንግግራችንን፣ ሀሳባችንን.. / መሆን ከነበረበት /ከትክክለኛው/ ጋር በማነጻጸር በሚዛን ላይ በማስቀመጥ ነው፡፡ የማነጻጻሪያ ሚዛኖቻችን ደግሞ በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፉ ሕግጋትና ትዕዛዛት ናቸው፡፡ እነዚህን ስናውቅ ጉድለቶቻችን፣ ድካሞቻችን ፍንተው ብሎ ይታዩናል፡፡ አሊያ ግን እየበደለን ያልበደልን ሊመስለን ይችላል፡፡

የበደሉንን ይቅር ማለት

ጌታ በዚህ ጸሎት ይቅርታ እንድንጠይቀው በማስተማር ይቅር ሊለን እንደሚወድ ዝግጁም እንደሆነ ቢነግረንም ይቅር ለመባል ግን እኛ የበደሉንን ይቅር ማለታችን የግድ እንደሆነ በግልጽ አስቀምጦልናል፤
«በደላችንን ይቅር በለን» ከማለታችን በፊት «እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል» እንድንል ያዘዘን እኛ ይቅርታ የምናገኘው ሌሎችን ይቅር ስንል ብቻ መሆኑን ለማመልከት ነው፡፡

ጌታችን ይህንን ጉዳይ በሌሎች የተለያዩ ቦታዎችም በተደጋጋሚ አስተምህሮናል፤ በዚሁ በተራራው ስብከት ይኸው ጉዳይ ሁለት ጊዜ በጌታችን ትምህርት ተሰጥቶበታል፡፡

«እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል፡፡ » /ማቴ.7-2/

በሌላ ቦታም እንዲህ ሲል ይህንኑ ጉዳይ በምሳሌ አስተምሯል፤

መንግስተ ሰማያት ባሮቹን ለመቆጣጠር የወደደን ንጉሥ ትመስላለች መቆጣጠርም በጀመረ ጊዜ እልፍ መክሊት ዕዳ ያለበትን አንድ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፡፡ ባለ እዳው ሰው የሚከፍለው ስላጣ እርሱና ሚስቱ ልጆቹም ያለውም ሁሉ እንዲሸጥና ዕዳው እንዲከፈል ንጉሡ አዘዘ፡፡ በዚህም ጊዜ ባርያው ወድቆ ሰገደለትና ጌታ ሆይ ታገሰኝ፤ ሁሉንም እከፍልሃለሁ አለው፡፡ የዚያም ባርያ ጌታ አዘነለትና ለቀቀው፡፡ ይህ ባርያ ግን ወጥቶ ከባልጀሮቹ /እንደርሱ ባርያ ከሆኑት/ መቶ ዲናር ዕዳ ያለበትን አንዱን አገኘና ዕዳህን ክፈለኝ ብሎ ያዘና አነቀው፡፡ ባልንጀራው ባርያም ወድቆ ታገሰኝ፤ ሁሉንም እከፍልሃለሁ፤ ብሎ ለመነው፡፡ እርሱ ግን ሊተወው አልወደደም፡፡ ዕዳውን እስኪከፍልም በወኅኒ አኖረው፡፡ ይህንን ያዩ ሰዎችም አዘኑ፤ ሄደውም የሆነውን ሁሉ ለንጉሡ ተናገሩ፡፡

«ከዚህ ወዲያ ንጉሡ ጠርቶ፣ አንተ ክፉ ባርያ ስለ ለመንከኝ ያን ዕዳ ሁሉ ተውሁልህ፤ እኔ እንደ ማርሁህ ባልንጀራህን የሆነውን ባርያ ልትምረው ለአንተስ አይገባህምን አለው፡፡ ጌታውም ተቆጣና ዕዳውን ሁሉ እስኪከፍለው ድረስ ለሚያሰቃዩት አሳልፎ ሰጠው፡፡»

ጌታ ይህንን ምሳሌ ከተናገረ በኋላ የምሳሌውን ትርጉም እንዲህ ሲል ገልጦታል፤ ብሏል፤ «ከእናንተ እያንዳንዱ ወንድሙን ከልቡ ይቅር ካላለ እንዲሁ ደግሞ የሰማዩ አባቴ ያደርግባችኋል»/ማቴ.18. 23- 35/

በአጠቃላይ ይቅር ለመባል ይቅር ማለት የግድ ነው፡፡ በእኛ ላይ የሚፈረድብን ፍርድ በእኛው እጅ ላይ ነው፡፡ ጌታችን በእነዚህ ትምህርቶች እንዲህ እያለን ነው «እኔ እናንተ ላይ የምፈርደው እናንተ በራሳችሁ ላይ በፈረዳችሁበት መንገድ /መልኩ ነው/»፡፡

ይቅርታ መጠየቅ

ኀጢአታችንን ካወቅንና ካመንን፣ የበደሉንንም ከልብ ይቅር ካልን በኋላ ይቅር እንድንባል መጠየቅ /መለመን/ አለብን ፡፡
«ይቅር በለን» ብላችሁ ጸልዩ ብሎ በማስተማሩ ይህንን እንረዳለን፡፡ ወደ ንስሐ አባት መሄድና ኀጢአትን ተናዞ ቀኖና መቀበል የሚገባው መጀመሪያ በዚህ መልኩ ስለ ኀጢአት ካለቀሱ በኋላ ነው፡፡ ከዚያም ቀኖና ተቀብለን ስንፈጽምም ሆነ ከዚያ በኋላ ይኸው ስለ ኀጢአት ይቅርታ መጠየቁ ይቀጥላል፡፡

በእርግጥም ይቅርታ የምንጠይቀው አዳዲስ ስለ ሠራናቸውና ንስሐ ገና ስላልገባንባቸው ኀጢአቶቻችን ብቻ ሳይሆን ንስሐ ስለ ገባንባቸው ስለ ቀደሙት በደሎቻችንም ጭምር ነው፡፡ እንደ ቅዱስ ዳዊት «የቀደመ በደላችንን አታስብብን ምሕረትህ በቶሎ ታግኘን» /መዝ.78-8/ እያልን ሰለ ቀደሙ በደሎቻችንንም እያሰብን በሕይወታችን ዘመን ሁሉ መጠየቅ አለብን፡፡

ይቅርታ የምንጠይቀው ስለምናውቃቸው /ስለምናስተውላቸው/ ኀጢአቶቻችን ብቻ ሳይሆን ስለ ማናስተውላቸውም መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ «ይቅር ብለን» ስንል እኛ ካስተዋልናቸው መንገዶች ውጪ በብዙ መልኩ እርሱን እንደምንበድል አስበን ተማጽኗችን ስለነዚህም መሆን አለበት፡፡

ስለዚህ ለጸሎት ከመቆማችንና የጌታን ጸሎት ከመጸለያችን በፊት የበደሉንን ይቅር እንዳልን እርግጠኛ መሆን አለብን እኛ የበደሉንን ይቅር እንዳልን ልንል ነውና፡፡

«እኛንም በደላችንን ይቅር በለን» ስንልም ከላይ ያየናቸውን ነገሮች ሁሉ እያሰብን፤ ይቅር ሊለን የወደደ አምላካችንንም እያመሰገንን መሆን አለበት፡፡ በእውነት ይህንን ጸሎት የምንጸልየው በዚህ መልኩ ነውን? ካልሆነ ልምምዱን ዛሬውኑ እንጀምረው፡፡ ይህንን ማድረግ እንችል ዘንደ የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Source: www.eotc-mkidusan.org