13

.

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው::" የማቴዎስ ወንጌል 7: 4

"እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅናወተት ግዙ።" ትንቢተ ኢሳይያስ 55 : 1

Friday, September 23, 2011

ግሸን ደብረከርቤ ዳግማዊት ጎልጎታ - የግማደ መስቀሉ መገኛ

ዲያቆን መልአኩ እዘዘው


ግሸን ማርያም ደብር በወሎ ክፍለ ሀገር በአምባሰል አውራጃ ውስጥ የምትገኝ ደብር ናት፤ ይህች ደብር በሐይቅና በመቅደላ፤ በደላንታ፤ በየጁ መካከልና በበሸሎ ወንዝ አዋሳኝ በርዋ አንድ ዙሪያውን በገደል የተከከበች አምባ ናት፡፡ በበርዋ ከተገባ በኋላ ግቢዋ ከላይ ሜዳና መስቀለኛ ቦታ ነው፡፡ በትግራይ እንደ ደብረ ዳሞ በበጌምድር እንደዙር አምባ በመንዝ እንደ አፍቅራ ናት ፡፡

ወደዚህች ደብር ለመሔድ በረሐ አቋርጦ በሸሎን በመሻገር ፫ ሰዓት መንገድ አቀበት በመውጣት አንድ ቀን ሙሉ ተጉዞ ማታ ፲፪ ሰዓት ይገባል ፡፡ግሸን ማርያም በፊት ደብረ እግዚአብሔር ትባል ነበር ፡፡ይህ ደብረ እግዚአብሔር የሚለው ስያሜም በጻድቁ ንጉሥ ላሊበላ እጅ ከቋጥኝ ድንጋይ ተፈልፍሎ የተሠራ ቤተ መቅደስ በእግዚአብሔር  አብ ስም ስለነበረ ደብረ እግዚአብሔር ተብሎ የተጠራ ነው፡፡ ከዚያም በዓጼ ድግናዣን ዘመን መንግሥት የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ሲመሠረት ሐይቅ ደብር ነጎድጓድ ተብሎ ሲሰየም ግሸን  የሐይቅ ግዛት ስለሆነች ከደብረ እግዚአብሔር ደብረ ነጎድጓድ ተብላለች ፡፡

ከዚያም በ ፲፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በዓጼ ዘርአ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት የክርስቶስ ግማደ መስቀሉ ግሸን ገብቶ ሲቀመጥ ከደብረ ነጎድጓድ ደብረ ከርቤ ተብላለች የደብሩ አስተዳዳሪም መምህረ እሥራኤል ዘደብረ ከርቤ ይባል ነበር፡፡ ከደብረ ከርቤ ግሸን ማርያም ተብላለች፡፡

የግማደ መስቀሉ መምጣት ታሪክ
ዓለምንና በውስጡ የሚገኘውን ሁሉ ፍጡር ፈጥሮ የሚገዛውን አምላክ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ቤተ እሥራኤል በቀራንዮ ላይ በመስቀል ሰቀሉት ፡፡ መድኃኔዓለም በዕለተ ዓርብ ከቀኔ በዘጠኝ ሰዓት ቅድስት ነፍሱን ከቅድስት ሥጋው በገዛ ሥልጣኑ ከለየ በኋላ በኋላ ከመስቀሉ አውርደው ቀበሩት ፡፡በ፫ኛው ቀን ሲነሣ ተሰቅሎ የነበረው የእንጨት መስቀል ሌት ተቀን በሙሉ ሳያቋርጥ እንደፀሐይ ሲያበራ በተጨማሪም አጋንንት ሲያባርር ድውይ ሲፈውስ ሙት ሲያነሣ ቤተ እሥራኤል አይሁድ ቀንተው በዓዋጅ ትልቅ ጉድጓድ ቆፍረው በመቅበር የቤት ጥራጊና አመድ ጠቅላላ የቆሻሻ መከማቻ እንዲሆን ወሰኑ፡፡ ከዚያ ዘመን ጀመሮ እስከ ሦስት መቶ ዘመን ድረስ የተከማቸው ቆሻሻ እንደተራራ ሆነ፡፡
ከዚያ በኋላ የታላቁ ቆስጠንጢኖስ እናት እሌኒ ንግሥት የተባለች ደግ ሴት የክርስቶስን መስቀል መስከረም ፲፯ ቀን ፫፻፳ ዓ.ም. ላይ በዕጣን ጢስ ምልክት ቁፋሮ አስጀምራ መጋቢት ፲ ቀን አግኝታ በማውጣት ታላቅ ቤተ መቅደስ ጎልጎታ ላይ ሠርታ በክብር አስቀመጠችው ይህ መስቀልም ከዚያ ዘመን ጀምሮ እንደ ፀሐይ እያበራ ድውይ እየፈወሰ አጋንንት እያባረረ ልዩ ልዩ ተአምራትን እየሠራ ሙት እያነሳ ዕውር እያበራ ተአምራቱን ቀጠለ፡፡ ይህንንም ከኃያላን ነገሥታት መካከል የፋርስ ንጉሥ መስቀሉን ማርኮ ፋርስ ወስዶ አስቀመጠው በዚህ ጊዜ የኢየሩሳሌም ምዕመናን የሮማውን ንጉሥ ሕርቃልን ዕርዳታ በመጠየቅ እንዲመለስ አድርገው በኢየሩሳሌም ብዙ ዘመን ሲኖር እንደገና ኃያላን ነገሥታት ይህን መስቀል እኔ እወስድ እኔ እወስድ እያሉ ጠብ ፈጠሩ፡፡
በዚህ ጊዜ የኢየሩሳሌም ፤ የቁስጥንጥንያ ፤ የአንጾኪያ ፤ የኤፌሶን ፤ የአርማንያ ፤ የግሪክ ፤ የእስክንድርያ የመሳሰሉት የሃይማኖት መሪዎች ጠቡን አበረዱት ከዚህም አያይዘው በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የክርስቶስ መስቀል ከ፬ ከፍለው በዕጣ አድርገው በስምምነት ተካፍለው ከሌሎቹ ታሪካዊ ንዋያት ጋር በየሀገራቸው ወስደው በክብር አስቀመጡት፡፡ የቀኝ ክንፉ የደረሰው ለአፍሪቃ ስለነበር ከታሪካዊ ንዋያተ ቅድሳት ጋር በግብጽ የሚገኘው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ተረክቦ ወስዶ በክብር አስቀመጠው፡፡
ይህ ግማደ መስቀልም ለብዙ ዘመን በእስክንድርያ ሲኖር በግብጽ ያሉ እስላሞች እየበዙ ኃይላቸው እየጠነከረ ሔደ በእስክንድርያ የሚኖሩትን ክርስቲያኖች ሥቃይ ያጸኑባቸው ጀመር ክርስቲያኖቹም አንድ ሆነው መክረው ለኢትዮጵያዊ ዓፄ ዳዊት እንዲህ የሚል መልዕክት ላኩ “ንጉሥ ሆይ! በዚህ በግብጽ ያሉ እስላሞች መከራ አጽንተውብናልና ኃይልህን አንሥተህ አስታግሥልን ብለው ጠየቁት” ዳግማዊ ዓፄ ዳዊትም ለመንፈሳዊ ኃይማኖት ቀንተው የክርስቶስ ፍቅር አስገድዶአቸው ፳ ሽህ ሠራዊት አስከትለው ወደ ግብፅ ዘመቱ በዚህ ጊዜ በግብፅ ያሉ ኃያላን ፈሩ ተሸበሩ ንጉሡ ዳግማዊ ዳዊትም እንዲህ የሚል መልዕክት ለእስላሞች ላኩ በተፈጥሮ ወንድሞቻችሁ ከሆኑት ክርስቲያኖች ጋር ካልታረቃችሁ ሀገራችሁን መጥቼ አጠፋዋለሁ የሚል ማስጠንቀቂያ ላኩ ፡፡የንጉሡ መልዕክት ለእስላሞች እንደደረሳቸው ፈርተው እንደጥንቱ በየሃይማኖታቸው ፀንተው በሰላም እንዲኖሩ ከክርስቲያን ወንድሞቻቸው ጋር ታረቁ፡፡
 መታረቃቸውን ዳግማዊ ዳዊት ሰሙ በዚህም ጉዳይ ንጉሡ በጣም ደስ አላቸው እገዚአብሔርንም አመሰገኑ በግብፅ የሚኖሩ ክርስቲያኖችም ከ፲፪ ሺህ ወቄት ወርቅ ጋር ደስታቸውን ለኢትዮጵያዊው ንጉሥ  ለዳግማዊ ዳዊት በደብዳቤ አድርገው ላኩላቸው ንጉሡም የደስታውን ደብዳቤ ተመልከተው ደስ ኣላቸው ፤ ወርቁን ግን መልሰው በመላክ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ፃፉ በግብፅ የምትኖሩ የክርስቶስ ተከታዮች ሆይ እንኳን ደስ አላችሁ የላካችሁልኝን ፲፪ ሺህ ወቄት ወርቅ መልሼ ልኬላችኋለሁ የእኔ ዓላማ ወርቅ ፍለጋ አይደለም የክርስቶስ ፍቅር አስገድዶኝ በተቻለኝ ችግራችሁን ሁሉ አስወገድኩላችሁ አሁንም የምለምናችሁ በሀገሬ በኢትዮጵያ ረሀብና ቸነፈር ድርቅ ስለወረደብኝ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቅሎበት የነበረውን መስቀልና የቅዱሳንን አፅም ከሌሎች ክቡራን ዕቃዎች ጋር እንድትልኩልኝ ነው የሚል ነበር፡፡
በእስክንድርያም ያሉ ምእመናን ይህ መልዕክት እንደደረሳቸው ከሊቃነ ጳጳሳቱና ከኤጲስ ቆጶሳቱ ጋር ውይይት በማድረግ ይህ ንጉሥ ታላቅ ክርስቲያን ነው፡፡ ስለዚህ ልቡን ደስ እንዲለው የፈለገውን የጌታችንን ግማደ መስቀል ከቅዱሳን አጽምና ንዋየ ቅድሳት ጋር አሁን በመለሰው ፲፪ ወቄት ወርቅ የብርና የንሐስ የመዳብና የወርቅ ሣጥን አዘጋጅተን እንላክለት ብለው ተስማምተው በክብር በሥነ ሥርዓት በሠረገላና በግመል አስጭነው ስናር ድረስ አምጥተው ባስረከቡአቸው ጊዜ በእጃቸው እያጨበጨቡ በእግራቸው እያሸበሸቡ በግንባራቸው እየሰገዱ በክብር በደስታ ተቀበሉት ይህም የሆነው መስከረም ፳፩ ቀን ነው፡፡ በኢትዮጵያም ታለቅ ብርሃን ሌት ተቀን ፫ ቀን ሙሉ ሲበራ ሰነበተ፡፡
ግማደ መስቀሉ ወደ መካከለኛው ኢትዮጵያ ሳይደርስ በድንገት ዓፄ ዳዊት ስናር ላይ አረፉ፡፡ ግማደ መስቀሉም የግድ በዚያው በስናር መቆየት አስፈለገው፡፡ ከዚህ በኋላ የሟቹ የዳግማዊ ዳዊት ልጅ ዘርአ ያዕቆብ እንደነገሡ ወደ ሥናር ሔደው ግማደ መስቀሉን ከሌሎቹ ንዋያተ ቅድሳት ጋር አምጥተው በመናገሻ ከተማቸው በደብረ ብርሃን ላይ ቤተ መቅደስ ሠርተው ለማስቀመጥ ሲደክሙ በሕልማቸው አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል ወዳጄ ዘርአ ያዕቆብ ሆይ መስቀሌን በመስቀልኛ ቦታ ላይ አስቀምጥ የሚል ሕልም አዩ ፡፡ ንጉሡም መስቀለኛ ቦታ እየፈለጉ በኢትዮጵያ አውራጃዎች ሁሉ መስቀለኛ ቦታ በመፈለግ ከብዙ ቦታ ላይ አስቀምጠውት ነበር ለምሳሌ በሸዋ በደርሄ ማርያም ፤ በመናገሻ ማርያም ፤ በወጨጫ መስቀሉን አሳርፈውት ነበር፡፡ ነገር ግን የመጨረሻውን ቦታ ያላገኙ በመሆኑ በራዕይ እየደጋገገመ መስቀሌን በመስቀልኛ ቦታ ላይ አስቀምጥ እያለ ይነግራቸው ነበር፡፡
ዓፄ ዘርአያዕቆብም ለ፯ ቀናት ያህል ሱባዔ ገቡ በዚያም የተገለፀላቸው መስቀልኛውን ቦታ የሚመራህ ዓምድ ብርሃን ይመጣል አላቸው እርሳቸው ከዚያ እንደወጡ መስቀለኛውን ቦታ የሚመራ ዓምደ ብርሃን ከፊታቸው መጥቶ ቆመ በዚያ መሪነት ወደ ወሎ ክፍለ ሀገር አምባሰል አውራጃ ውስጥ ግሸን ከምትባል መርቶ አደረሳቸው ፡፡በርግጥም ይህች ግሽን የተባለች አምባ ጥበበኛ ሰው እንደቀረፃት የተዋበች መስቀልኛ ቦታ ሁና ስለአገኟት የልባቸው ስለደረሰ ደስ አላቸው ፡፡ በዚያችም አምባ ታላቅ ቤተ መቅደስ ሠርተው መስቀሉንና ሌሎች ንዋያተ ቅድሳቱን በየማዕረጋቸው የክብር ቦታ መድበው አስቀመጧቸው ዘመኑም በ፲፬ ኛው ክፍለ ዘመን ነው፡፡
 እስክንድርያ ሀገር ከመስቀሉ ጋር በልዩ ልዩ ሣጥን ተቆልፈው የመጡትም ዝርዝር
+ ጌታ በዕለተ ዓርብ ለብሶት የነበረው ቀይ ልብስ ከሮም የመጣ ከለሜዳው
ከአፍርጌ ሀገር የመጣው ሐሞት የጠጣበት ሰፍነጉ
ዮሐንስ የሳለው የኲርዓተ ርዕሱ ስዕል
+ ቅዱስ ሉቃስ የሣላቸው የእመቤታችን ስዕሎች
የበርካታ ቅዱሳን አጽምና በኢየሩሳሌም ውስጥ ከልዩ ልዩ ቅዱሳት መካናት የተቆነጠረ የመሬት አፈር
 + የዮርዳኖስ ውሃ
በግብጽ ውስጥ ከሚገኙት ታላላቅ ገዳማት የተቆነጠረ አፈር ነው፡፡ የነዚህንም ዝርዝር ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለግሼን ካህናት መስከረም ፳፩ ቀን ፩ ሺ ፬፻፵ ዓ.ም. ላይ ተናገሩ ፡፡በመጀመሪያም ይህ ግማደ መስቀል ከእስክንድርያ ስናር የገባው መስከረም ፲ ቀን ነው ወደ ኢትዮጵያም የገባው በመስከረም ፳፩ ቀን ነው፡፡ አሁንም በመጨረሻ ግሸን አምባ የገባው መስከረም ፳፩ ቀን ሲሆን ቤተ መቅደስ ተሠርቶ ቅዳሴ ቤቱ የተከበረውና አፄ ዘርዓያዕቆብ ለመላው ኢትዮጵያ በፅሑፍ በመዘርዘር የገለፁበትም መስከረም ፳፩ ቀን ነው፡፡
ስለዚህ ከዚህች በግሸን ደብር የክርስትና እምነት ያላቸው የኢትዮጵያ ምእመናን ከበረከተ መስቀሉና ከቅዱሳን አፅም በረከት ለማገኘት በየዓመቱ መስከረም ፳፩ ቀን እየመጡ ያከብራሉ፡፡ በዚያም ዘመን የነበሩት የኢትዮጵያ ጳጳሳት የነበሩት አባ ሚካኤልና አባ ገብርኤል የተባሉ ከንጉሡ ከዓፄ ዘርአ ያዕቆብ ጋር ሆነው የምህረት ቃል ኪዳን ለመቀበል በዚህች በግሸን ደብር ሱባዔ ገቡ በሱባዔአቸውም በመጨረሻ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጾ ይህች ቦታ እኔ ተወልጄ ያደኩባትን ኢየሩሳሌምን ትሁን የተሰቀልኩባትን ቀራንዮን ትሁን የተቀበርኩባትንም ጎልጎታን ትሁን በዚች ቦታ እየመጣ የሚማፀነውን ሁሉ ቸርነቴ ትጎበኘዋለች ጠለ ምህረቴንም አለይባትም ፤  ከሩቅም ሆነ ከቅርብ መጥቶ የተቀበረ ኢየሩሳሌም እንደተቀበረ ይሁን የሚል የምህረት ቃል ኪዳን ተገልጾላቸው በዚህ ለተገኙት ምዕመናን ሁሉ በጽሑፍ ካሰሙ በኋላ ጠቅላላ የግማደ መስቀሉንና የሌሎቹን ታሪካውያን ንዋያተ ቅዱሳትንም ዝርዝር ታሪክ የያዘውን መጽሐፈ ጤፉት ብለው ሰይመው ድንጋጌውን ሁሉ በመዘርዘር ለግሸን እግዚአብሔር አብ ሰጡ፡፡
 አፄ አርዓ ያዕቆብም በዚህ ብቻ ሳይወሰኑ እሌኒ እኅታቸው  የተሰኘችው በእመቤታችን ማርያም ስም ቤተ መቅደስ እንድትሠራ አዘው የእመቤታችን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን አጠገብ  አሳንጻ ጥር ፳፩ ቀን ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ ዓፄ ዘርአ ያዕቆብም ይህችን ደብር ደብረ ከርቤ ብለው በመሰየም እንኳንስ ሰው የሠገረ ቆቅ ፤ የበረረ ወፍ እንዳይገደል ዳሯ እሳት መሀሏ ገነት ትሁን ብለው ደንብና ሥርዓት በጤፉት መጽሐፍ ውስጥ አጽፈዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በየጊዜው የነገሡ የኢትዮጵያ ነገሥታትና የተሾሙ ጳጳሳት መሳፍንትና መኳንንት ልዩ ልዩ ንዋያተ ቅድሳትንና መጻሕፍትን የወርቅንና የብርን ሰን ፤ ብርና ጻሕል ጽዋን መስቀልን የመሳሰሉትን የሰጧት ምዕመናንም በየዓመቱ መስከረም ፳፩ ቀን በግሸን ማርያም ለመገኘት ከዓመት ወደ ዓመት እየበረከቱ ሔደዋል፡፡
በመስከረም 10 ፤ መስከረም 17 በዓለ መስቀል እና መስከረም 21 የግሸን በዓል ታሪክ ከረጅም በአጭሩ ይህንን ይመስላል ፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ምዕመናን የሆናችሁ ሁሉ ከበረከተ መስቀሉ ለመሳተፍ ወደ ግሸን ገሥግሱ፡፡


ልዑል እግዚአብሔር ከበረከተ መስቀሉ ያሳትፈን 
አሜን
መልካም የመስቀል በዓል
Source:http://www.melakuezezew.info/2011/09/blog-post_23.html

 

1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 3


1 እኔም፥ ወንድሞች ሆይ፥ የሥጋ እንደ መሆናችሁ፥ በክርስቶስም ሕፃናት እንደ መሆናችሁ እንጂ መንፈሳውያን እንደ መሆናችሁ ልናገራችሁ አልቻልሁም።
2 ገና ጽኑ መብል ለመብላት አትችሉም ነበርና ወተት ጋትኋችሁ፤
3 ገና ሥጋውያን ናችሁና እስከ አሁን ድረስ ገና አትችሉም። ቅናትና ክርክር ስለሚገኝባችሁ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደላችሁምን? እንደ ሰው ልማድስ አትመላለሱምን?
4 አንዱ። እኔ የጳውሎስ ነኝ፥ ሁለተኛውም። እኔ የአጵሎስ ነኝ ቢል ሰዎች ብቻ መሆናችሁ አይደለምን?
5 አጵሎስ እንግዲህ ምንድር ነው? ጳውሎስስ ምንድር ነው? በእነርሱ እጅ ያመናችሁ አገልጋዮች ናቸው፤ ለእያንዳንዳቸውም ጌታ እንደ ሰጣቸው ያገለግላሉ።
6 እኔ ተከልሁ አጵሎስም አጠጣ ነገር ግን እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር፤
7 እንግዲያስ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ የሚተክል ቢሆን ወይም የሚያጠጣ ቢሆን አንዳች አይደለም።
8 የሚተክልና የሚያጠጣ አንድ ናቸው፥ ነገር ግን እያንዳንዱ እንደ ራሱ ድካም መጠን የራሱን ደመወዝ ይቀበላል።
9 የእግዚአብሔር እርሻ ናችሁ፤ የእግዚአብሔር ሕንፃ ናችሁ፤ ከእርሱ ጋር አብረን የምንሠራ ነንና።
10 የእግዚአብሔር ጸጋ እንደ ተሰጠኝ መጠን እንደ ብልሃተኛ የአናጺ አለቃ መሠረትን መሠረትሁ፥ ሌላውም በላዩ ያንጻል። እያንዳንዱ ግን በእርሱ ላይ እንዴት እንዲያንጽ ይጠንቀቅ።
11 ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፥ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
12 ማንም ግን በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ ቢሆን በብርም በከበረ ድንጋይም በእንጨትም በሣርም ወይም በአገዳ ቢያንጽ፥ የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል፤
13 በእሳት ስለሚገለጥ ያ ቀን ያሳያልና፥ የእያንዳንዱም ሥራ እንዴት መሆኑን እሳቱ ይፈትነዋል።
14 ማንም በእርሱ ላይ ያነጸው ሥራ ቢጸናለት ደመወዙን ይቀበላል፤
15 የማንም ሥራ የተቃጠለበት ቢሆን ይጎዳበታል፥ እርሱ ራሱ ግን ይድናል ነገር ግን በእሳት እንደሚድን ይሆናል።
16 የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን?
17 ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ።
18 ማንም ራሱን አያታልል፤ ከእናንተ ማንም በዚች ዓለም ጥበበኛ የሆነ ቢመስለው ጥበበኛ ይሆን ዘንድ ሞኝ ይሁን።
19-20 የዚህች ዓለም ጥበብ በእግዚአብሔር ፊት ሞኝነት ነውና። እርሱ ጥበበኞችን በተንኰላቸው የሚይዝ፤ ደግሞም፦ ጌታ የጥበበኞችን አሳብ ከንቱ እንደ ሆነ ያውቃል ተብሎ ተጽፎአልና።
21 ስለዚህም ማንም በሰው አይመካ። ነገር ሁሉ የእናንተ ነውና፤
22 ጳውሎስ ቢሆን አጵሎስም ቢሆን ኬፋም ቢሆን ዓለምም ቢሆን ሕይወትም ቢሆን ሞትም ቢሆን ያለውም ቢሆን የሚመጣውም ቢሆን፥
23 ሁሉ የእናንተ ነው፥ እናንተም የክርስቶስ ናችሁ
              

"ወደ ማደሪያዎቹ እንገባለን እግሮቹ በሚቆሙበት ስፍራ እንሰግዳለን። " መዝሙረ ዳዊት 132:7

















 






















"የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና።" 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች  1:18

አበው ይናገሩ



                                                                                 ዘርዓቡሩክ ገ/ሕይወት

እስኪ ቀስቅሷቸው አበው ይናገሩ 
የምንኩስና ግብር ምን ነበር ምሥጢሩ 
የክርስትና ሕይወት ምን ነበር ተግባሩ
መቃብሩን ክፈቱና አበው ይመስክሩ፡፡

እኔስ ሰው አማረኝ የሃይማኖት ጀግና
ወልድ ዋሕድ ብሎ በእምነቱ የፀና 
ጀግና ሰው አማረኝ ጠላት አሳፋሪ 
ንጽህት ድንግል ብሎ እምነቱን መስካሪ፡፡

ነብያት በመጋዝ የተሰነጠቁት 
ሐዋርያት ቁልቁል የተዘቀዘቁት
ሰማዕታት በእሳት የተለበለቡት 
ቅዱሳን በገዳም ደርቀው የተገኙት 
ምሥጢሩ ምን ነበር? አበው ይናገሩት፡፡

ይናገር ዝቋላ ግሸን ላሊበላ 
የቅዱሳንን ዐፅም ለምን እንዳልበላ፡፡
ዋልድባ ይናገር ዜጋመልም ሳይቀር 
እንባቸው መፍሰሱ ለምን እንደነበር፡፡
ነበር ወይ ፈልገው ሹመት ሽልማት?
ወይስ ሀብት ንብረት የተሟላ ቤት?
ወይስ አምሯቸው ነው ፈልገው መሞት?
እናንተ ገዳማት ምሥጢሩን አውሩት፡፡

ጐበዝ ሰው አማረኝ በእምነቱ የፀና
ምግባር ሃይማኖቱ በእጅጉ የቀና፡፡
እንጦንስ የወለደው በምግባር በእምነት
ተምሮ ያደገ ከተክለሃይማኖት፡፡
የጊዮርጊስ ወገን የት ነው የማገኘው?
በመሀል ከተማ በአራዳ ውስጥ ነው?
ወይስ በዝቋላ በደብረ ሊባኖስ በደብረ ዳሞ ነው?

ወገን ሰው ናፈቀኝ ዐይኔን ሰው አማረው
የሃይማኖት ጀግና የትነው የማገኘው?
ልግባ ወይ ዋልድባ ጫካ ካለበት
ማኅበረ ሥላሴ ከቅዱሳን ቤት?
አክሱም ግሸን ማርያም ከቃል ኪዳን ቦታ 
ይገኛል ወይ ጀግና ጠላት የሚረታ?
ፈሪሐ እግዚአብሔር በልቡ ያደረ
ቤተ ክርስቲያንን ያልተደፋፈረ፡፡

የት ነው የማገኘው ለሃይማኖቱ ሟች 
ለተዋሕዶ እምነት ጠበቃ ተሟጋች፡፡ 
የወገን መመኪያ የከሀዲ መቅሰፍት 
ማነው እሱ ጀግና ተኝቶ እንደሆነ ይነሣ ቀስቅሱት፡፡ 
እስኪ ቀስቅሷቸው አበው ይናገሩ
የምንኩስና ግብ ምን ነበር ምሥጢሩ?
የክርስቲያን ሕይወት ምን ነበር ተግባሩ?
መቃብሩን ክፈቱት አበው ይመስክሩ፡፡

ወገን ሰው ናፈቀኝ ዐይኔን ጀግና አማረው 
በእምነቱ የፀና የትነው የማገኘው?
ብቅ ይበል እንየው እሱ ማነው ጀግና?

በጐችን ከተኩላ ነቅቶ የሚጠብቅ 
መከራ ቢከበው ከቶ የማይሰቀቅ
የሃይማኖት ጀግና ቆራጥ ሰው ገበሬ
እንደዚያ እንደ ጥንቱ ይገኛል ወይ ዛሬ?
የወገን የዘመድ ጥቅም ያላወረው
የመናፍቆች እጅ ኪሱን ያልዳበሰው 
የዓለም አሸክላ ልቡን ያልማረከው
የክርስቶስ ወዳጅ እሱ ጀግና ማነው?
ምሥጢርን ከምሥጢሩ አንድ አድርጐ ቀምሮ
ወልድ ዋሕድ ብሎ ሃይማኖት መስክሮ 
እንጦንስን መቃርስን በልቡ ያኖረ
ከአትናቴዎስ ከቄርሎስ ጥበብ የተማረ፡፡

ድንግል እመቤቴ ብሎ የሚመሰክር
መሆኗን የሚያምን ማኅደረ እግዚአብሔር
ቋቅ እንትፍ ብሎ የጠላ ክህደትን 
ትንታግ ምላስም ጭንግፍግፉን 
ልሳነ ጤዛ መናፍቅን 
ወልደ አርዮስ ዲቃላውን፡፡ 
በሰይፈ ሥላሴ የሚቀላ
ጀግና ማነው ዝቅ ይበላ፡፡

ነበር ወይ ያን ጊዜ ለሹመት መጓጓት 
እስኪ ጎርጎርዮሰ ይምጣና ጠይቁት
ፍቅርንም ይጠየቅ አባ ሕርያቆስ
ምሥጢርን ጠባቂ ወይም አባ መቃርስ፡፡

የክርስቶስ ባርያ የአጋንንት መቅሰፍት
ወንጌል አስተማሪ የሃይማኖት አባት 
ይህንን ጉድ እንዲያይ ይምጣ ተክለሃይማኖት
የጸሎት ገበሬ ገብረ መንፈስ ቅዱስንም ይነሣ ቀስቅሱት
ይነሣ ጊዮርጊስ ይመስክር ምሥጢር
የሃይማኖት ፍቅር ምን እንደነበር፡፡

ከእናቶቻችንም አሉ ለፍጥረት ያዘኑ 
ዲያብሎስ እንዲማር ጌታን የለመኑ፡፡
ስንቱን ልዘርዝረው የአባቶችን ሙያ 
መር ብለው የወጡት ከሥጋ ገበያ 
ጾም ጸሎት ነበረ የሃይማኖት ጋሻ
መልከስከስ ምንድነው እንደ አበደ ውሻ፡፡

እንደ መስኖ ውሃ ከነዱት መነዳት 
ዓላማው ምንድነው የዘመኑ ወጣት፡፡

እኔስ ሰው አማረኝ የሃይማኖት ጀግና
ወልድ ዋሕድ ብሎ በእምነቱ የፀና
ዐይኔን ሰው አማረው ጀግና ሰው ገበሬ 
ሃይማኖት መስካሪ እንደ ጥንቱ ዛሬ፡፡

ምንጭ፡- ማኅበረ ቅዱሳን
Source: http://kidanemhret.org/profiles/blog/show?id=2949235%3ABlogPost%3A188464&xgs=1&xg_source=msg_share_post

Wednesday, September 21, 2011

ሰዎች ንስሐ ላለመግባት ከሚያቀርቧቸው ምክንያቶች...

ሰዎች ንስሐ ላለመግባት ከሚያቀርቧቸው ምክንያቶች ውስጥ ጥቂቶቹ እና መፍትሄዎቻቸው


1- እኔ የሠራሁት ኃጢአት ሰው ሁሉ የሚሠራውን ነው እንጂ የተለየ አይደለም፡፡ 

አንዳንድ ሰዎች እነርሱ የሠሩት ብዙ ሰዎች የሚፈጽሙትን ኃጢአት ከሆነ በግል ልንጠየቅበት አይገባም በተናጠልም ንስሐ ልንገባበት አይገባም ብለው ያስባሉ፡፡ ለእነርሱ ኃጢአት መሥራት የኅብረተሰቡ ኃጢአትን መፈጸም ምክንያት እንደሆናቸው ይቆጥራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ኃጢአት ኃጢአት ነውና የፈጸመው ሰው ይጠየቅበታል፡፡ ስለዚህ ከኃጢአት መለየት አንጂ ሰው ኃጢአት ሠርቷል ብለን መልሰን እዚያ ውስጥ አንዘፈቅም፡፡
ለምሳሌ፡- በኖህ ዘመን ሰው ሁሉ በኃጢአት ውስጥ በነበረበት ጊዜ ኖህ በእግዚአብሔር ዘንድ ጻድቅ ነበር ዘፍ. 6፥5 ቅዱስ ጳውሎስም ይህን አለም አትምሰሉ ብሏል፡፡ ሮሜ. 12፥2
መላው የግብፅ ሕዝብ ጣኦት ሲያመልክ ጻድቁ ዮሴፍ የሚያመልከው እግዚአብሔርን ነበር፡፡
በባቢሎን የተማረኩት ሠልስቱ ደቂቅና ዳንኤል እንዲሁ እግዚአብሔርን ያመልኩ ነበር እንጂ በጣኦት አምልኮ ከባቢሎናውያን ጋር አልተባበሩም፡፡ ዳን. 2፥8
ማንኛውም ክርስቲያን በመንፈሳዊ ሕይወቱ የአለማውያንን ኑሮ ለመለወጥ ባይቻለውም እንኳ አለምንና አለማውያንን ከመምሰል ከእነርሱም ጋር ከመቀላቀል መጠንቀቅና መራቅ ይገባዋል፡፡
2- ውጫዊ ፈተና መደራረብ ምክንያት አድርገው ያቀርባሉ፡፡
ጠንካራና ልቦና ያለው ሰው በኃጢአት ለመውደቅ የፈተናን ብዛት ምክንያት አያደርግም፡፡ የውጭ ተጽዕኖን ለኃጢአቱ ምክንያት አድርጎ የሚያቀርብ ሰው ለትዕዛዛተ እግዚአብሔር ከበሬታ ለእግዚአብሔርም ፍቅር የሌለው ነው፡፡
ለምሳሌ፡- ዮሴፍ ኃጢአት ለመሥራት በቂ ምክንያት ነበረው፡፡ ያም ምክንያት ባርያ ታዛዥ ባይተዋር ስለሆንኩ ኃጢአትን ሠራሁ ለማለት በቂ ምክንያት ነበረው፡፡ እርሱ ግን እንዴት አድርጌ በእግዚአብሔር ፊት ኃጢያትን አደርጋለሁ አለ፡፡
ሳኦል ያለምንም በደል ዳዊትን ባሳደደው ጊዜ እግዚአብሔር ሳኦልን በዳዊት እጅ አሳልፎ ሰጠው፡፡ ዳዊትም ሳኦልን ለመበቀል በቂ ምክንያት ነበረው ያም ምክንያት
  • ኃጢአተኛ ስለሆነ
  • ክፉ ስለሆነ
  • እግዚአብሔርን ንቆ ከሥልጣን ስለ አወረደው
  • ለዳዊት ጠላት ስለሆነ ወዘተ… 1ሳሙ. 16፥14
ዳዊትም እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን አላነሳም አለ፡፡
በአጠቃላይ ማንኛውንም ኃጢአት ለመሥራት የእግዚአብሔር ፍቅር በልቡ የታተመ ሰው ምክንያት አይደረድርም፡፡
3- እኔ ደካማ ነኝ የእግዚአብሔር ትዕዛዛትም ከባድና አስቸጋሪ ናቸው ምን ላድርግ? ይላሉ፡፡
የእግዚአብሔር ዕርዳታ የረሳን እንደሆነ በእርግጥ ደካሞች ነን እግዚአብሔርን የሚያመልክ ሰው ብቻውን አይደለምና፡፡ ሰው በባህሪው ደካማ ቢሆንም በእግዚአብሔር እርዳታ የማይቻለው ነገር የለም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ›› ፊል. 4፥13 እንዳለ:: ዳዊት እኔ ደካማ ነኝ እግዚአብሔር ግን ይረዳኛል ባይል ኖሮ ጎልያድን ባልተዋጋም ነበር፡፡ የእርሱ የባህሪ ደካማነት በእግዚአብሔር ትዕዛዝና በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ከሚሠራው ሥራ ሊያስቀረው አልቻለም ይህም ሲባል፡-
1ኛ. ዳዊት በመጀመሪያ ለውጊያ ስላልተመለመለ ሊመለስ ይችል ነበር፡፡
2ኛ. ጎልያድ ግዙፍ ተዋጊና ባለ ብዙ መሣሪየ  በመሆኑ ሰው ሁሉ ስሚፈራው ዳዊትም ሊፈራው ይችል ነበር፡፡
3ኛ. ዳዊትን ማንም እንዲዋጋ አልጠየቀውም ነበር፡፡
4ኛ. የጦር መሪዎቹ ሁሉ ሳኦልን ጨምሮ ጎልያድን ፈርተውት ነበር ስለዚህ ዳዊት እኔ ትንሽና ደካማ ነኝ ለማለት በቂ ምክንያት ነበረው፡፡ ዳዊት ግን በእምነት ለድል በቃ፡፡   
እግዚአብሔር አምላካችን ልንፈጽመው የማንችለውን እንድንፈጽም አያዝዘንምና የእግዚአብሔር ትዕዛዛት ከባድና አስቸጋሪ እንደሆነ ማሰብ የለብንም፡፡ ፈጣሪያችን ያዝዘናል የምንፈጽምበትንም ኃይል ይሰጠናል፡፡ ከትዕዛዙም ጋር ደግሞ ፀጋው አለ፡፡ መንፈስ ቅዱስም በእኛ አድሮ ተግባሩን ለመፈጸም ያበረታናል፡፡ ያለበለዚያ ሊውጠን እንደሚያገሳ አንበሳ ሆኖ የሚመጣውን ሰይጣን መቋቋም ባልተቻለም ነበር፡፡ 1ጴጥ. 5፥8 
በመጨረሻ ነፍስን በመንከባከብና በመጠበቅ የሚከተሉትን ትዕዛዛት ዘወትር ማስታወስ ይገባል፡፡
            1ኛ. በመንፈስ ብንመላለስ የሥጋን ምኞት አንፈጽምም፡፡ ገላ. 5፥16
            2ኛ. መንፈስ የሞላብን መንፈስ ቅዱስ ያደረብን እንሁን፡፡ ኤፌ. 5፥18
            3ኛ. በመንፈስ የምንቃጠል እንሁን ሮሜ. 12፥11  
በዚህም እግዚአብሔርን በመንፈስ እናመልከዋለን ፊል. 3፥3 በመንፈስ እንጸልያለን በመንፈስም እንዘምራለን 1ቆሮ. 14፥15 የመንፈስ ፍሬዎችም እናፈራለን ገላ. 5፥22   
ስለዚህ ከንስሐ በኋላ ከእግዚአብሔር ፍቅር እንዳንለይ ከእቅፉም እንዳንወጣ የናቅናት ዓለምና የተውነው ኃጢአታችን እንዳይናፍቀን ወደ ነበርንበትም እንዳንመለስ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር የገባንለትን ቃል ኪዳን እንዳናፈርስ በእጅጉ ልንጠነቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ኃጢአትንም እንድንጠላው ተግተን መጸለይ ንሰሐ አባታችንንም በየቀኑ እያገኘን በመንፈሳዊ ሕይወት የምናድግ መሆን ይገባናል፡፡   
ሕይወታችን በእግዚአብሔር ተቃኝቶ የስሙ ቀዳሽ የክብሩ ወራሽ እንዲያደርገን የእግዚአብሔር አብ ጸጋ  የእግዚአብሔር ወልድ ቸርነት የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድነት የእመቤታችን አማላጅነት የቅዱሳን ተራዳዒነት አይለየን አሜን፡፡

Source: http://www.facebook.com/groups/180759695294706/doc/246724798698195/

ባሕረ ሐሳብ /የዘመን አቆጣጠር/


በዳዊት ደስታ




1. ባሕረ ሐሳብ ማለት ምን ማለት ነው?

ባሕረ ሐሳብ ማለት ቁጥር ያለው ዘመን ማለት ነው፡፡ በሌላ አገላለጽም የሐሳብ ባሕር ማለት ነው፡፡ በዓላት እና አጽዋማትን ለማውጣት የመደመር፣ የመቀነስ፣ የማባዛት ስሌትን ብቻ ሳይሆን ሐሳበ ፀሐይን፣ ሐሳበ ወርኅን፣ ሐሳበ ከዋክብትን ሐሳበ ዐበቅቴን ወዘተ አጠቃሎ የያዘ እንደ ባሕር የሰፋ በመሆኑ የሐሳብ ባሕር ተብሏል፡፡ የዘመን አቈጣጠር ማለት ስለማሕበራዊ ኑሮ ጠቄሜታና የሃይማኖት ተግባሮች ለማከናወን በሚያገለግል መልኩ ተፈጥሮአዊውን የወቅቶች ክፍፍል እርስ በርሳቸው የማመቻቸት ዘዴ ነው፡፡
ሐሳበ ዘመን የዘመን አቆጣጠር ማለት ሲሆን የሐሳበ ዘመን ትምህርት ባሕረ ሐሳብ ይባላል፡፡ ባሕረ ሐሳብ የሚለው ቃል ሐሰበ ቆጠረ ከሚለው ግስ የወጣ ዘመድ ዘር ነው፡፡ ስለዚህ ባሕረ ሐሳብ ማለት ቁጥር ያለው ዘመን ወይም ዓመተ ዓለም ማለት ነው፡፡ ባሕረ ሐሳብ መባሉም የባሕር አዝዋሪቱ፣ መንገዱን፣ ጥልቀቱና ስፋቱ ረዥምና ሰፊ እንደሆነ የባሕረ ሐሳብ ትምህርትም መንገዱን ስፋቱ ልዩ ልዩ በሆነ የአጽዋማትና የሱባዔያት ምሥጢር የተሰናዳ ስለሆነ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር /የጊዜ ቀመር/ አንድ ዓመት በውስጡ ዐሥራ ሦስት ወራትን የያዘ ሆኖ በአራት ወቅቶች የተከፈለ ነው፡፡ አራቱ ክፍላተ ዘመን የሚባሉት፡- “ክረምት ከሰኔ 26 ቀን - መስከረም 25 ቀን፣ መፀው /መከር/ ከመስከረም 26 ቀን - ታኅሣሥ 25 ቀን፣ በጋ /ሐጋይ/ ከታኅሣሥ 26 ቀን - መጋቢት 25 ቀን፣ ጸደይ /በልግ/ ከመጋቢት 25 ቀን - ሰኔ 25 ቀን ናቸው፡፡ ከክረምት በስተቀር እያንዳንዱ ወቅት በውስጡ ዘጠና ዘጠና ቀናት ይዟል፡፡ ክረምት ግን ለብቻው 95 ቀናትን የያዘ ነው፡፡

2. አራቱ ክፍላተ ዘመን
የቅዱስ ያሬድ ድርሰቶች ጊዜ፣ ወር፣ ዘመን አላቸው፡፡ አንድን ዓመት በአራት ክፍለ ዘመን በመክፈል ድርሰቱን ውሱን አድርጎታል፡፡ ዘመኑም እንዲሁ በድርሰቱ የተወሰነ ሆኗል፡፡ እነዚህም ዘመናት ዘመነ መፀው፣ ዘመነ ሐጋይ፣ ዘመነ ጸደይ፣ ዘመነ ክረምት በመባል ይታወቃሉ፡፡
2.1. ዘመነ መፀው
መፀው በሌላ አነጋገር ጥቢ ይባላል፡፡ እንደ ሌሊት ከብዶ የሚታየው ክረምት አልፎ መስከረም ከጠባ በኋላ በ4ኛው ሳምንት ስለሚጀምር ነው ጥቢ የሚባል ተጨማሪ ስያሜ የተሰጠው፡፡
ዘመነ መፀው ከመስከረም 26 እስከ ታኅሣሥ 25 ድረስ ያለው ጊዜ ነው፡፡ የዕለቱ ቁጥርም 90 ይሆናል፡፡ ከዘመነ ክረምት ቀጥሎ በመሆኑ ዘመነ ክረምትን በማስቀደም ፅጌንና መፀውን በማስተባበር ቅዱስ ያሬድ የሚከተለውን ብሏል፡፡ “ግሩም በሆነው ኃይልህ እንመካ ዘንድ አንተ ዘመናትን ሠራህ ክረምትን ለዝናባት መፀውን ለአበቦች ሰጠህ” ድጓ ዘጽጌ ኩፋሌ 2 ኢዮ.2÷23 ኤር.5፥24/
መፀው መሬት በክረምት የተሰጣትን ዘር አበርክታ፣ አብዝታ ለፍሬ የምታደርስበት የምርት ወቅት ነው፤ መፀው በአብዛኛው የአዝመራ መሰብሰቢያ ጊዜው ነው፡፡ በዚህ ክፍለ ዘመን በዋናነት ሦስት ወራት ያገኛሉ፤ እነርሱም ጥቅምት፣ ኅዳርና ታኅሣሥ ናቸው፡፡ ይህ ወቅት በኢትዮጵያ ምድር አበቦች በየሜዳው በየሸንተረሩና በየተራራው ፈክተው የሚታዩበት አዝርእት የሚያሸቱበትና ለፍሬ የሚበቁበትን ወራት ይዞ ይገኛል፡፡
2.2. ዘመነ ሐጋይ /በጋ/
ዘመነ ሐጋይ ይህ የበጋ ወቅት ነው፡፡ “ሐጋይ”…. በጋ ሆነ ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ነው፡፡ ይህም ከታኅሣሥ 26 እስከ መጋቢት 25 ቀን ያለውን ጊዜ ያጠቃልላል፡፡ ሐጋይ በጋ የጥርን፣ የየካቲትንና የመጋቢትን ወር ይይዛል፡፡
ዘመነ ሐጋይ የቃሉ ትርጓሜ ዘመነ ፀሐይ ማለት ሲሆን ሥርወ ቃሉም ኃገየ … ከሚለው ግዕዝ የተገኘ ነው፡፡ ከአራቱ ክፍላተ ዘመን አንዱ እጅ ወይም አንድ አራተኛው ሐጋይ ይባላል፡፡ የሐጋይ ፍቺ በጋ እንደሆነ ሁሉ እንዲሁም መፀውም ጸደይም በእርሱ ስም በጋ ይባላሉ፡፡ “ዘጠኝ ወር በጋ” እንዲሉ፣ አንዳንድ ጊዜም መጽሐፍት በሁለት ከፍለው ይናገራሉ፡፡ “ክረምትና በጋን አንተ ሠራህ” ፤ “በበጋም በክረምትም እንዲህ ይሆናል” /መዝ.75፥17፣ ዘካ.14፥10፣ ዘፍ.10፥22/ እንዲል ኃጋይ ማለት መገኛ መክረሚያ በጋ፣ ፀደይ፣ ደረቅ ወቅት ነው፡፡
በዚህ ወቅት በመፀው ያሸተውና ያፈራው መኸር የሚታጨድበት፣ የሚሰበሰብበትና በየማሳው ከተከመረ በኋላ የሚበራይበት፣ በጎተራ የሚከተትበት በመሆኑ “የካቲት” የሚለውን ወር ይዞ እናገኘዋለን፡፡ የግብርናው ኅብረተሰብ እህሉን በጎተራው ከትቶ ለተወሰነ ጊዜ የሚያርፍበት በመሆኑ የዓመት በዓላት እንደ ልደት፣ ጥምቀት ያሉት፣ ዘመነ መርዓዊ የሚባለው የጋብቻ ዘመን በዚህ ወቅት የተካተቱ ናቸው፡፡
2.3. ዘመነ ጸደይ /በልግ/
ዘመነ ጸደይ ማለት የቃሉ ትርጉም ዘመን በልግ ማለት ነው፡፡ ጸደይ በበጋና በክረምት መካከል የሚገኝ በውስጡ የሚያዝያን፣ የግንቦትንና የሰኔ ወራትን የያዘ ክፍለ ዘመን ነው፡፡ በመሆኑም ጸደይ የሌሎች ወቅቶችን ባሕርያት አሳምሮ የያዘ ነው፡፡ ምክንያቱም በአንድ በኩል የበልግ አዝመራ የሚታጨድበት የሚወቃበትና የሚዘራበት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ለክረምት የሚዘራ ማሳ የሚታረስበት /ለዘር ዝግጁ የሚሆንበትን ጊዜ ነው፡፡ በአብዛኛው ግን ዘመነ በልግ ነው፡፡
ቅዱስ ያሬድ በድጓው “ይሁብ ዝናመ ተወን” የበልግ ዝናምን ይሰጣል እንዳለው የበልግ ወቅት ነው፡፡ ይህም ወቅት በልግ አብቃይ በሆነው የሀገራችን ክፍል የበልግ አዝመራ የሚዘራበት፣ በልግ አብቃይ ባልሆነው ክፍል ደግሞ መሬት ለክረምቱ የዙር ጊዜ የሚያዘጋጅበት ነው፡፡ “አንድ ሰኔ የነቀለውን ሁለት ሰኔ አይተካውም” እንደሚባለው የግብርናው ኅብረተሰብ ቀጣይ የግብርና ሥራውን በትጋት የሚሠራበት ወቅት ነው፡፡
2.4. ዘመነ ክረምት
ዘመነ ክረምት ማለት ዘመነ ውሃ ማለት ነውና በዚህ ዘመን ውኃ ይሰለጥናል፡፡ ውሃ አፈርን ያጥባል፣ እሳትን ያጠፋል፣ ቢሆንም በብሩህነቱ ከእሳት፣ በቀዝቃዛነቱ ከነፋስ፣ በእርጥብነቱ ከመሬት ጋር ተስማምቶ ይኖራል፡፡
ክረምት በውስጡ አራት ወራትን /ሐምሌ፣ ነሐሴ፣ ጳጉሜንና መስከረም/ የያዘ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ “ያረሁ ክረምተ በበዓመት፣ ይሰምዑ ቃሎ ደመናት፣ በየዓመቱ ክረምትን ያገባል፤ ደመናትም ቃሉን ይሰሙታል” ሲል በድጓው እንደነገረን የዘመናት ጌታ ልዑል እግዚአብሔር በየዓመቱ አዙሮ የሚያመጣልን ወቅት ነው፡፡ ደመናትም ለቃሉ ትእዛዝ ተገዢዎች በመሆን ዝናመ ምሕረቱን ጠለ በረከቱን የሚያወርዱበት ጊዜ ነው፡፡ ከሰኔ 26 እስከ መስከረም 25 ድረስ ያለውን ጊዜ ይይዛል፡፡

3. ዓመተ ወንጌላውያን
የሦስቱ ወንጌላውያን ማለትም የዮሐንስ፣ የማቴዎስና፣ የማርቆስ ዘመናት እያንዳንዳቸው ከመስከረም 1 ጀምሮ እስከ ጳጉሜን 5 ድረስ 365 ቀን ከስድስት ሰዓት ነው፡፡ ዘመነ ሉቃስ ግን ከመስከረም 1 እስከ ጳጉሜን 6 ቀን በመሆኑ 366 ቀናት ይኖሩታል፡፡

4. ወራት
በግዕዝ ቋንቋ “ወርሃ” የምንለው ቃል በአማርኛ ወር እንለዋለን ይህም ወደ ብዙ ቁጥር ሲለወጥ ወራት ይሆናል፡፡ በኢትዮጵያ ዘመን አቈጣጠር እያንዳንዳቸው 30 ቀናት ያሏቸው 12 ወራት፣ 5 ወይም በየአራት ዓመት 6 ቀናት የሆነች ጳጉሜን ያሉ ሲሆን በአውሮፓውያን አቈጣጠር ግን የየወሩ የቀናት ቁጥር ለየት ይላል፡፡


የወራቱ ስም
የግዕዝ መገኛው
አማርኛው ትርጉም
1
መስከረም
ከረመ
ከረመ/ረ ይጠብቃል/
2
ጥቅምት
ጠቀመ
ጠቀመ/ቀ ይጠብቃል/
3
ህዳር
ኀደረ
አደረ
4
ታኅሣሥ
ኀሠሠ
ፈለገ
5
ጥር
ጠየረ
መጠቀ/ወደ ላይ ተመረመረ
6
የካቲት
ከተተ
ሰበሰበ
7
መጋቢት
መገበ
መገበ/ገ ይጠብቃል/
8
ሚያዝያ
መሐዘ
ተጐዳን
9
ግንቦት
ገነባ
ገነባ
10
ሰኔ
ሠነየ
አማረ
11
ሐምሌ
ሐምለ
ለመለመ
12
ነሐሴ
ነሐሰ
ሠራ
5.ሳምንት
ሳምንት “ሰመነ” ስምንት አደረገ ከሚለው ከግዕዝ ቃል የተገኘ ነው፡፡ በሕገ ዑደት መሠረት ዕለት ከተነሣበት ማለትም ከእሑድ እስከ እሑድ ያለው ጊዜ ሳምንት ተብሎ ይጠራል፡፡ በዚህ ሳምንት ውስጥ ያሉት ቀናት እያንዳንዳቸው 24 ሰዓት ያላቸው ናቸው፡፡ እሑድ ማለት “አሐደ” አንድ አደረገ ከሚለው የግዕዝ ግስ የተገኘ ስለሆነ ትርጉሙ አንድ ማለት ነው፡፡ ሰኞ ሁለተኛ ፣ ማክሰኞ /ማግስት/ ሦስተኛ፣ ረቡዕ አራተኛ፣ ሐሙስ አምስተኛ፣ ዓርብ ስድስተኛ ፣ቅዳሜ ሰባተኛ ቀን ነው፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ዓለምን በስድስት ቀናት /ከእሑድ - ዐርብ/ ፈጥሮ ያረፈባትና ሰዎችም እንዲያርፉበት ያዘዛት ሰባተኛዋ ቀን በግዕዝ ቀዳሚት ሰንበት ተብላ ትጠራለች፡፡
6. የዕለታት ስያሜ
1. እሑድ ፡ አሐደ ከሚለው ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም አንድ አደረገ /የመጀመሪያ ሆነ/ ማለት ነው፡፡ በዚህ ቀን ፍጥረታት መፈጠር ስለጀመሩ እሑድ ተብሏል፡፡
2. ሠኑይ /ሰኞ/፡ ሠነየ ከሚል ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ሁለት አደረገ ማለት ነው፡፡ ለሥነ ፍጥረት ሁለተኛ ስለሆነ ሰኑይ/ ሰኞ/ ተብሏል፡፡
3. ሠሉስ/ማክሰኞ/ ፡ ሠለሰ ከሚል ግስ የተገኘ ሲሆን ሦስት አደረገ ማለት ነው፡፡ ማክሰኞ የሚለው የሰኞ ማግስት ማለት ነው፡፡
4. ረቡዕ ፡ረብዐ /አራት አደረገ/ ከሚል ግስ የተገኘ ሲሆን ለሥነ ፍጥረት አራተኛ ቀን ማለት ነው፡፡
5. ሐሙስ፡ ሐመሰ /አምስት አደረገ/ ከሚል ግስ የተገኘ ሲሆን ለሥነ ፍጥረት አምስተኛ ቀን ማለት ነው፡፡
6. ዓርብ ፡ ዓረበ ከሚል ግስ የተገኘ ሲሆን ተካተተ ማለት ነው፡፡ ፍጥረታት እሑድ መፈጠር ጀምረው አርብ ስለተካተቱ /ተፈጥረው ስለተፈፀሙ/ አርብ ተብሏል፡፡
7. ቅዳሜ፡ ቀዳሚት ማለት ሲሆን ሰንበተ ክርስቲያን ከሆነችው ከዕለተ እሑድ ቀድማ ስለምተገኝ ቀዳሚት ሰንበት /ቅዳሜ/ ተብላለች፡፡
7. የ2004 ዓ.ም. የአጽዋማትና የበአላት ማውጫ
መንበር ……………………………………… 17
ወንጌላዊ ……………………………….…… ዮሐንስ
ዕለት……………………………………….... ሰኞ
ዓበቅቴ ……………………………………..... 7
መጥቅዕ …………………………………....... 23
ጾመ ነነዌ ………………………………… ጥር 28
ዓብይ ጾም………………………………… የካቲት 12
ደብረ ዘይት ……………………………… መጋቢት 30
ሆሣዕና …………………………………… መጋቢት 9
ስቅለት …………………………………… ሚያዝያ 5
ትንሣኤ …………………………………… ሚያዝያ 7
ርክበ ካህናት ……………………………… ግንቦት 1
ዕርገት ……………………………………… ግንቦት 16
ጰራቅሊጦስ ………………………………… ግንቦት 26
ጾመ ሐዋርያት …………………………… ግንቦት 27
ጾመ ድኅነት ……………………………… ግንቦት 29
ማጠቃለያ
አሁን ያለውን የዘመን አቆጣጠር አስልተን እንድንቆጥር ያደረገው የባሕረ ሐሳብ ደራሲ የሆነው የእስክንድርያ 12ኛ ጳጳስ የነበረው ቅዱስ ድሜጥሮስ ነው፡፡ ይሄ አባት በደረሰልን የቁጥር ቀመር መሠረት በዓላትን አጽዋማትን መቼ እንደሚውሉ እያሰላን እንጠቀማለን አሁንም የአቡሻህር መምህራን ከመቁጠርያቸው ጀምሮ እስከ አቆጣጠራቸው እያስተማሩ ይገኛሉ፡፡ መነሻውም መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርገው ስሌቱን እያስፋፉት ይገኛል፡፡

Source: http://www.facebook.com/groups/giorgis/  Mehal Zege Church

Monday, September 19, 2011

ነገረ ማርያም ክፍል ፲፩

በመልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው


«የኢየሱስ ክርስቶስ የትውልድ መጽሐፍ፤»

          ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌሉን መጻፍ የጀመረው፦ «የዳዊት ልጅ፥የአብርሃም ልጅ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የትወልድ መጽሐፍ፤» በማለት ነው። እንዲህም ያለበት ምክንያት ብዙ ዓይነት ልደታት ስላሉ ከእነዚያ የተለየ መሆኑን ለመግለጥ ነው። አምላክ በተዋሕዶ ሰው የሆነበት ምሥጢር ታላቅ በመሆኑ ተጠንቅቆ ጽፎታል። ፩ኛ ጢሞ ፫፥፲፮። ይኸውም፦ አድሮበት በሚኖር መንፈስ ቅዱስ ወደፊት በነገረ ክርስቶስ ዙሪያ አያሌ መናፍቃን እንደሚነሡ ስለሚያውቅ አስቀድሞ የኑፋቄን መንገድ ሲዘጋባቸው ነው።
፩፥፩፦ ልደተ አዳም፤
          «ወገብሮ እግዚአብሔር ለሰብእ እመሬተ ምድር፤ እግዚአብሔር አዳምን ከምድር መሬትን ነሥቶ ፈጠረው፤ በፊቱም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፤ (ሕይወት የምትሆነውን ነፍስን አሳደረበት)፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ። (አዳም ሕይወት በምትሆን ነፍስ ሕያው ባለአእምሮ ሆነ)፤» ይላል። ይህም፦ አንድ ሰው፦ ጐተራውን በፊት ሠርቶ ፥ በኋላ እህል እንደሚያኖርበት ፥ በፊት ሥጋን ፈጥሮ ኋላ ነፍስን አምጥቶ አሳደረበት ማለት አይደለም። እግዚአብሔር፦ ሥጋን ከአራቱ ባሕርያት (ከመሬት፣ ከነፋስ ፣ ከእሳት ፣ ከውኃ)፥ ነፍስንም እምኀበ ዐልቦ (ካለመኖር ወደ መኖር ፣ ከምንም አምጥቶ) የፈጠረው ፣ ያዋሐደው አንድ ጊዜ ነው። ዘፍ ፪፥፯።

          አዳም ማለት ከመሬት የተፈጠረ ማለት ነው፤ አንድም፦ የሚያምር ፥ ደስ የሚያሰኝ ፥ ውብ፥ ደግ፥ መልካም፥ መልከ መልካም ማለት ነው። ከመሬት በመፈጠሩም ከድንግል መሬት ተወለደ ይባላል። በዚህም ከድንግል ማርያም ለተወለደው ዳግማዊ አዳም ለሚባል ለኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ሆኗል። ከድንግል መሬት የተወለደው አንድ አዳም እንደሆነ ሁሉ፥ ከድንግል ማርያምም የተወለደው አንድ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። አዳም በዚህ ምድር የኖረው ለዘጠኝ መቶ ሠላሳ ዓመት ነው። ዘፍ ፭፥፭።
፩፥፪፦ ልደተ ሔዋን፤
          የሔዋን ልደት ከአዳም ጎን ነው፤ «እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ላይ እንቅልፍን አመጣ፤ አንቀላፋም፤ (ማእከለ ነቂሕ ወነዊም ሆነ፤ ይህም በእንቅልፍና በመንቃት መካከል ሆነ ማለት ነው)፤ ከጎኑም አጥንቶች አንድ አጥንትን ወስዶ ስፍራውን በሥጋ መላው። እግዚአብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት፤ (የሴት አካል ያላት አድርጎ ፈጠራት ፥ አንድም ስትፍት ብርህት አደረጋት)፤ ወደ አዳምም አመጣት። (መልክ ከደም ግባት አስተባብራ የያዘች የምታምር አድርጎ ወደ አዳም አመጣት)። አዳምም፦ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፤ ሥጋዋም ከሥጋዬ ናት፤ እርስዋ ከባልዋ ተገኝታለችና ሚስት ትሁነኝ፤ (ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል)፤ አለ።» ይላል። ዘፍ ፪፥፳፩። እናታችን ሔዋን ኅቱም ከሆነ ከአዳም ጎን እንደተወለደች ሁሉ፥ ጌታም በድንግልና ኅትምት ከሆነች ፥ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዷል።
፩፥፫፦ ልደተ በግዕ፤
          እግዚአብሔር አብርሃምን ለበጎ ፈተነው፤ በሀገራቸው ልማድ፦ «አብርሃም፥አብርሃም» ብሎ በደጊመ ቃል ጠራው፤ አብርሃምም፦ «ጌታዬ፥ እነሆ አለሁ፤» አለ፤ እግዚአብሔርም፦ «የምትወደውን ልጅህን ይስሐቅን ከፍ ወደአለ ተራራ ይዘኸው ሂድ፥ ከዚያም በደረስህ ጊዜ በማሳይህ በአንድ ተራራ ላይ አውጥተህ ሠዋው፤» አለው። አብርሃምም፦ ልጁን ይስሐቅን ይዞ፥ሁለቱንም ሎሌዎቹን አስከትሎ አህያውን ጭኖ ተነሣ። እንጨትንም ለመሠዊያ ሰነጠቀ፤ ተነሥቶም እግዚአብሔር ወደአለው ቦታ ሄደ፤ በሦስተኛውም ቀን ደረሰ።
          አብርሃም ዓይኑን አንሥቶ ቦታውን ከሩቅ አየ። ሎሌዎቹንም፦ «አህያውን ይዛችሁ በዚህ ቆዩ፤ እኔና ልጄ ወደዚያ ተራራ ሄደን እንሰግዳለን፤ ሰግደንም ወደ እናንተ እንመለሳለን።» አላቸው። አብርሃም፦ መሥዋዕት የሚሠዋበትን እንጨቱን አንሥቶ ለይስሐቅ አሸከመው፤ እርሱም እሳቱንና ቢላዎውን በእጁ ያዘ፤ ሁለቱም አብረው ሄዱ። ይስሐቅም አባቱን አብርሃምን፦ «አባቴ» ብሎ ጠራው፤ እርሱም፦ «ልጄ ምንድን ነው?» አለው። ይስሐቅም፦ «እሳቱና እንጨቱ እነሆ አለ፤የመሥዋዕቱ በግ ግን ወዴት አለ?» አለው። አብርሃምም፦ «ልጄ ሆይ፥ የመሥዋዕቱን በግ እግዚአብሔር ያዘጋጃል፤» አለውና ጉዞአቸውን ቀጠሉ።
          እግዚአብሔር ወዳለውም ወደዚያ ቦታ ደረሱ፤ አብርሃምም በዚያ መሠዊያዉን ሠራ፤ እንጨትም ረበረበ፤ ይስሐቅም፦ እርሱ እንደሚሠዋ አውቆ፦ «እኔን ልትሠዋኝ ይመስለኛል ፥ ስለዚህ ስወራጭ፣ ስንፈራገጥ እጅህን እንዳላስቆርጥህ እሰረኝ፤» ብሎታል። በዚህን ጊዜ፦ እጁንና እግሩን አሥሮ ሠርጅቶ (ጠልፎ) ጣለው። ቀጥሎም የልጅ ዓይኑ ብክን ብክን ሲል ያሳዝናልና ራርቼ ትቼው ከፈጣሪዬ ጋር እጣላለሁ ብሎ፥ አንድም ልጁ ይስሐቅ፦ ዓይኔ ብክን ብክን ሲል አይተህ ራርተህ ትተወኝና ከፈጣሪህ ጋር ትጣላለህ ብሎት እንጨት በተረበረበበት በምሥዋዑ ላይ ደፍቶ በልቡ አስተኛው።
          አብርሃምም እጁን ዘረጋ፤ ልጁንም ያርድ ዘንድ ቢላዎውን አነሣ። እግዚአብሔርም ከሰማይ ጠርቶ፦ «በብላቴናው ላይ እጅህን አትዘርጋ፤ አንዳችም አታድርግበት፤ ለምትወድደው ልጅህ ከእኔ አልራራህለትምና፤ (ልጅህን ከእኔ ይልቅ አልወደድኸውምና)፤ አንተ እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደሆንህ አሁን አውቄአለሁ፤» አለው። አብርሃም ዓይኖቹን አቅንቶ በተመለከተ ጊዜ፦ በኋላው እነሆ፥ አንድ በግ ቀንዶቹ በዕፀ ሳቤቅ ተይዞ አየ፤ ሄዶም በጉን ወሰደውና በልጁ በይስሐቅ ፈንታ ሠዋው። አብርሃምም፦ በዚህ ተራራ እግዚአብሔር ፈጽሞ ታየኝ ሲል ያን ቦታ፦ «ራእየ እግዚአብሔር፤» ብሎ ጠራው።
          አብርሃም የአብ፥ ይስሐቅ ደግሞ የወልድ ምሳሌዎች ናቸው። አብርሃም ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ልጁን ይስሐቅን በሕሊናው እንደሠዋው፥ እግዚአብሔር አብም ተቀዳሚና ተከታይ የሌለውን አንድ የባሕርይ ልጁን ፥ ስለ ሰው ልጅ ፍቅር ለሞት አሳልፎ ሰጥቶታል። ይኽንንም ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ፦ «በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኝ እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲህ ወዶአልና።» በማለት ገልጦታል። ዮሐ ፫፥፲፮። በመጀመሪያዪቱም መልእክቱ ላይ፦ «በዚህም የእግዚአብሔር ፍቅሩ በእኛ ላይ ታወቀ፤ በእርሱ በሕይወት እንኖር ዘንድ አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና።» ብሏል። ፩ኛ ዮሐ ፬፥፱።
          ተራራው የቀራንዮ፥ የመሠዊያው እንጨት የመስቀል ፥ እሳቱ የመንፈስ ቅዱስ፥ ሁለቱ ሎሌዎች በግራና ቀኝ ለተሰቀሉ ሰዎች ፥ ቢላዎ የሥልጣነ እግዚአብሔር ምሳሌዎች ናቸው። ቢላዎ አጥንትን ከሥጋ እንደሚለይ፥ ጌታም በገዛ ሥልጣኑ ነፍሱን ከሥጋው ለይቷል። አብርሃም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በሰማበት በዚያ ሰዓት ወዲያው ልጁን በሕሊናው ሰውቶት ለሦስት ቀናት ተጉዟል። ከሦስት ቀን በኋላም ይስሐቅ ድኗል። ሕሊና አብርሃም የመቃብር ምሳሌ ነው፤ ይስሐቅ በሕሊና አብርሃም በተሠዋ በሦስተኛው ቀን መዳኑ፥ ጌታ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር አድሮ ለመነሣቱ ምሳሌ ነው። አንድም በጉ የጌታ፥ ይስሐቅ ደግሞ የአዳምና የልጆቹ ምሳሌዎች ናቸው። በጉ ከሰማይ ወርዶ በኅቱም ዕፅ ተይዞ (ከኅቱም ዕፅ ተወልዶ) መገኘቱ፥ ጌታ ከሰማይ ወርዶ ከድንግል ማርያም ለመወለዱ ምሳሌ ነው። ዕፀ ሳቤቅ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት። በጉ ስለ ይስሐቅ ፈንታ መሠዋቱ ጌታ ለአዳምና ለልጆቹ ተላልፎ በመስቀል ላይ ለመሠዋቱ ምሳሌ ነው። ሊቃውንቱ በጉ ከኅቱም ዕፅ ተወለደ ብለው ይተረጉሙታል። በዕፀ ሳቤቅ ቀንዶቹ ተይዞ የተገኘ አንድ በግ ብቻ ነው ፥ ከእመቤታችንም የተወለደው አንድ የቀራንዮ በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ዘፍ ፳፪፥፩። መጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሐንስ ኢየሱስ ክርስቶስን፦ «የዓለሙን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ፤» ያለው ለዚህ ነው። ዮሐ ፩፥፳፱።
፬፥፩፦ ልደተ አቤል፤
          አቤል የቃኤል ታናሽ ወንድም ነው፤ ልደቱ በዘር በሩካቤ ነው፤ ከእርሱ ጋር መንታ ሆና የተወለደችው አቅሌምያ ናት፥ መልከ ጥፉ ነበረች፤ አቤል ግን ብሩኅ ገጽ ነበረው። አባቱም፦ «ይህ ብሩኅ ገጽ ያለው ልጄ መንግሥቴን የሚወርሰው እርሱ ነው፤» ይለው ነበር። የሚታወቀው በገርነቱ በየዋህነቱ ነው፥ ለአዳምና ለሔዋን ይታዘዛቸው ነበር፤ አዳም በሳምንት ሦስት ጊዜ ለእግዚአብሔር ቊርባን ሲያቀርብ አይለየውም ነበር፥ ከቊርባኑም ይቀበል ነበር። ቃኤል፦ ከጸሎቱ፥ ከቊርባኑ ብዙ ጊዜ ሲቀር አቤል ግን አንድም ቀን አያስታጉልም ነበር፤ ብዙ ጊዜ ይጾም ብዙ ጊዜም ይጸልይ ነበር። አባቱ አዳም ባዘዘውና ባስተማረው መሠረት ንጹሕ መሥዋዕት በበጎ ኅሊና አቅርቧል፤ እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመልክቷል። ዘፍ ፬፥፬። ስለየዋህ ልቡናው ፥ ስለ መሥዋዕቱም ንጹሕነት እግዚአብሔር ተደስቶበታል። አቤል፦ ልክ እንደ አባቱ በሳምንት ሦስት ቀን መሥዋዕት ያሳርግ ነበር።
          ቃኤል አሥራ አምስት ዓመት ፥ አቤል ደግሞ አሥራ ሁለት ዓመት ሲሞላቸው፦ አባታቸው አዳም፦ ከቃኤል ጋር የተወለደችውን ውብ ለአቤል አጋባት፤ ከአቤል ጋር የተወለደችውን መልከ ጥፉ ደግሞ ለቃኤል አጋባት። ቃኤልም ስለ ሦስት ነገር በወንድሙ ተበሳጨበት። ፩ኛ፦ አልጋ ወራሽ በመሆኑ፤ ፪ኛ፦ መሥዋዕቱን እግዚአብሔር ስለተቀበለለት፤ ፫ኛ፦ በትዳሩ ቀንቶበት ተቆጣ። በመጨረሻም ሰይጣን እንደአስተማረው «ና፥ወደ ሜዳ እንሂድ፤» ብሎ፥ ራሱን በድንጋይ ገምሶ ገድሎታል። በግፍ የፈሰሰ የአቤል ደም፦ «ወንድሜ ቃኤል ገደለኝ፤» እያለ ጩኸቱን ለእግዚአብሔር አሰምቷል። ከሞተ በኋላም በደሙ በመናገሩ ለትንሣኤ ሙታን ምሳሌ ሆኗል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ ይኽንን ይዞ፦ «አቤል ከቃኤል ይልቅ የሚበልጥ መሥዋዕትን ለእግዚአብሔር አቀረበ፤ በዚህም ጻድቅ እንደሆነ ተመሰከረለት፤ ምስክሩም መሥዋዕቱን በመቀበል እግዚአብሔር ነው። በዚህም ከሞተ በኋላ ተናገረ።» በማለት ሃይማኖቱን ፥ ምግባሩን መስክሮለታል። ዕብ ፲፩፥፬። እግዚአብሔር ቃኤልን፦ «ወንድምህ አቤል ወዴት ነው?» ብሎ በጠየቀው ጊዜ፦ «አላውቅም፤ በውኑ የወንድሜ ጠባቂው እኔ ነኝን?» በማለት ተሳልቋል። እግዚአብሔርም፦ «ምን አደረገህ? የወንድምህ የአቤል የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል። አሁንም የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፍዋን በከፈተች በምድር ላይ አንተ የተረገምህ ነህ፤» ብሎታል። ዘፍ ፬፥፰-፲፩።
፪፦ ዳዊትና አብርሃም፤
          ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌላዊ፦ «ወልደ ዳዊት፥ ወልደ አብርሃም፤» በማለት ከነገሥታት ዳዊትን፥ ከአበው ደግሞ አብርሃምን አንሥቷል። ይኸውም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእነርሱ ብቻ ይወለዳል ለማለት ሳይሆን የተለያዩ ምክንያቶች ስላሉት ነው።
፪፥፩፦ ዳዊት ሥርወ መንግሥት ስለሆነ ነው፤
          ዳዊት፦ ከእሥራኤል ነገሥታት ሁሉ ይልቅ ታላቅና እጅግ ተወዳጅ ንጉሥ ነበር። የተወለደው እሴይ ከተባለ ሰው በይሁዳ ቤተልሔም ነው። ፩ኛ ሳሙ ፲፮፥፲። እግዚአብሔር ሳይጠራው በፊት የበጎች እረኛ ነበር። ፩ኛ ሳሙ ፲፮፥፲፩ ፣፲፯፥፴፬። ንጉሥ ሳኦል እግዚአብሔርን ከመከተል ወደ ኋላ በመመለሱ በእሥራኤል ላይ ንጉሥ እንዳይሆን እግዚአብሔር ናቀው። «ስላነገሥሁት ተጸጸትሁ፤» በማለትም ለነቢዩ ለሳሙኤል ነገረው። ፩ኛ ሳሙ ፲፭፥፲። ንጉሥ ሳኦል በዚህና በሌሎችም ምክንያቶች ሥርወ መንግሥት መሆን አልቻለም። «የእግዚአብሔርም መንፈስ ከሳኦል ራቀ፤ ክፉም መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ አስጨነቀው፤» ይላል። ፩ኛ ሳሙ ፲፮፥፲፬። በምትኩ ንጉሥ ይሆን ዘንድ ዳዊት በሳሙኤል እጅ ተቀባ። የእግዚአብሔርም መንፈስ ከዚያ ቀን ጀምሮ በዳዊት ላይ መጣ። ፩ኛ ሳሙ ፲፮፥፲፫። ዙፋኑን ከመውረሱ በፊት ግን ጋሻ ጃግሬ ሆኖ ሳኦልን አገልግሎታል። በገና እየደረደረም ርኲስ መንፈስን ያርቅለት ከስቃይም ያሳርፈው ነበር። ፩ኛ ሳሙ ፲፮፥፲፰-፳፫። በሰይፍ ተመትቶ፥ በጦር ተወግቶ፥ በፈረስ በሠረገላ ተገፍትሮ፥ አይወድቅ የነበረውን ታላቁን ጎልያድንም፦ በእግዚአብሔር ስምና ኃይል በወንጭፍ ድንጋይ ገድሎታል። ፩ኛ ሳሙ ፲፯፥፵፭-፶፮።
          የሳኦል ልጅ ናታን ዳዊትን እንደ ነፍሱ ስለወደደው ካባውን፥ ልብሱን፥ ሰይፉን፥ ቀስቱንና ዝናሩን ሸልሞታል። የእሥራኤል ሴቶችም እየዘመሩና እየዘፈኑ፥ እልልም እያሉ፥ ከበሮና አታሞ ይዘው ተቀብለውታል። «ሳኦል ሺህ ገደለ፤ ዳዊትም አሥር ሺህ ገደለ፤»እያሉ እየተቀባበሉ ይዘፍኑ ነበር። በዚህም ምክንያት ሳኦል እጅግ ተቆጣ፥ ነገሩም አስከፋው፥ በዳዊትም ላይ ቂም ያዘበት። ይሁን እንጂ ክፉ መንፈስ በየዕለቱ ሲያሰቃየው ዳዊት እየተጠራ በገና ይደረድርለት ነበር። በዚህ አጋጣሚም ዳዊትን ከግንቡ ጋር አጣብቆ ለመግደል ከአንዴም ሁለት ጊዜ ጦር ወርውሮበት ነበር። ዳዊት ግን ከፊቱ ዘወር ብሎ አመለጠ። እግዚአብሔር ከእርሱ ተለይቶ ከዳዊት ጋር ስለነበር ሳኦል ዳዊትን ይፈራው ነበር። ከዚህ የተነሣ የሺ አለቃ አድርጎ (ሻለቅነት ሹሞት) በሹመት ስም ከፊቱ አራቀው። ነገር ግን በፊታቸው ይወጣና ይገባ ስለነበረ እስራኤልና ይሁዳ ሁሉ ዳዊትን ወደዱት። ፩ኛ ሳሙ ፲፰፥፩-፲፮።
          ንጉሥ ሳኦል ዳዊትን በትዳር ሊያጠምደው ሞክሯል። ዳዊት ግን፦ «ለንጉሥ አማች እሆን ዘንድ እኔ ማን ነኝ? ሰውነቴስ ምንድን ናት? የአባቴስ ወገን በእስራኤል ዘንድ ምንድን ነው?» በማለት የትህትናን ነገር ተናገረ። የሳኦል ልጅ ሜሮብ ዳዊትን የምታገባበት ጊዜ ሲደርስ ለሚሆላዊው ለአድርኤል ተዳረች። ሜልኮል የተባለች ሴት ልጁ ደግሞ ዳዊትን ወደደችው ፥ ወሬውም ለሳኦል ደርሶ ነገሩ ደስ ስለአሰኘው «እርስዋን እሰጠዋለሁ፤ እርስዋም እንቅፋት ትሆንበታለች፤» አለ። ብላቴኖቹንም፦ «እነሆ ንጉሥ እጅግ ወድዶሃል፤ አሁንም ለንጉሥ አማች ሁን ብላችሁ በሥውር ለዳዊት ንገሩት፤» ብሎ አዘዛቸው። ዳዊት ይህን በሰማ ጊዜ፦ «እኔ የተዋረድሁና ክብር የሌለኝ ሰው ስሆን ለንጉሥ አማች እሆን ዘንድ ለእናንተ ትንሽ ነገር ይመስላችኋልን?» አላቸው። ንጉሡ ሳኦል፦ ይኽንን በነገሩት ጊዜ፦ «የንጉሡን ጠላቶች ይበቀል ዘንድ ከመቶ ፍልስጥኤማውያን ሸለፈት በቀር ንጉሥ ማጫ አይሻም ብላችሁ ለዳዊት ንገሩት፤» አላቸው። ሳኦል እንዲህ ማለቱ ብላቴናው ዳዊት በእነርሱ እጅ እንዲሞትለት ነው።ዳዊትና ሰዎቹም ዘምተው ሁለት መቶ ፍልስጥኤማውያንን ገደሉ። ሳኦልም ዕድሜውን ሁሉ ለዳዊት ጠላት ሆነ። ፩ኛ ሳሙ ፲፰፥፲፯-፴።
          ንጉሥ ሳኦል፦ በፍልስጥኤማውያን ወረራ መካከል በጊልቦዓ ተራራ ላይ በገዛ እጁ ከሞተ በኋላ፦ ዳዊት አስቀድሞ በይሁዳ፥ በኋላም በመላው እስራኤል ላይ ነገሠ። ፪ኛ ሳሙ ከምዕራፍ ፪ እስከ ምዕራፍ ፭። በዘመነ መንግሥቱ እግዚአብሔር እየረዳው ታላላቅ ሥራዎችን በማከናወኑ ስመ ጥር ነበር። ከዘመነ መሳፍንት ጀምሮ እስራኤልን ሲያጠቁ የነበሩትን ፍልስጥኤማውያንን አሸንፏል። ፪ኛ ሳሙ ፭፥፲፰-፳፭። አሕዛብን በማስገበር ሀገሩን አስፍቷል። ፪ኛ ሳሙ ፰፥፲፪። ኢየሩሳሌም የተባለችውን የተመሸገች ከተማ ወርሮ ኢያቡሳዊያንን አሸንፎ መናገሻ ከተማ አድርጓታል፤ በዚህም ምክንያት የዳዊት ከተማ ተብላለች። ፪ኛ ሳሙ ፭፥፩-፲። ታቦተ ጽዮንንም ወደዚያ በማምጣት፦ መሥዋዕት የሚሠዋባት፥ አምልኮት የሚፈጸምባት መንፈሳዊ ሥፍራ እንድትሆን ለዚህ ክብር አብቅቷታል። የመቅደሱንም ሥርዓት አሻሻሏል። ፪ኛ ሳሙ ፮፣ ፩ኛ ዜና ፳፰፥፫። ብዙ መዝሙራትንም ጽፏል። ዳዊት ታላቅና ገናና፥ መንፈሳዊም በመሆኑ መንግሥቱ ለክርስቶስ መንግሥት ምሳሌ ሆኖአል። ፪ኛ ሳሙ ፯፥፰ ፣ ኢሳ ፱፥፯ ፣ ኤር ፳፫፥፭ ፣ ፴፫፥፲፬ ፣ ሕዝ ፴፬፥፳፫ ፣ ፴፯፥፳፬።
፪፥፪፦ ዳዊት ትንቢት ስለተነገረለትም ነው፤
          ትንቢት ለሌሎችም የተነገረ ቢሆንም የዳዊት ግን ይበዛል። «እግዚአብሔር ለዳዊት እንዲህ ሲል በእውነት ማለ፤ አይጸጸትምም ፥ ከሆድህ ፍሬ በዙፋንህ ላይ አስቀምጣለሁና፤ ልጆችህ ኪዳኔን፥ ይህንንም የማስተምራቸውን ምስክሬን ቢጠብቁ ፥ ልጆቻቸው በዙፋንህ ላይ ለዘለዓለም ይቀመጣሉ።» ይላል። ፻፴፩፥፲፩። ይህ ትንቢት ለጊዜው ለሰሎሞን ሲሆን ለፍጻሜው ለጌታ ነው። ትርጉሙም ከባሕርይህ የተከፈለ ልጅህን ክርስቶስን በዙፋንህ አስቀምጥልሃለሁ ሲለው ነው። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል፦ እመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያምን ባበሠራት ጊዜ፦ «እግዚአብሔር አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤» ያለው ለዚህ ነው። ሉቃ ፩፥፴፪። ነቢዩ ኢሳይያስም፦ «ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤» ካለ በኋላ «በዳዊት ዙፋን መንግሥቱ ትጸናለች፤ ለሰላሙም ፍጻሜ የለውም፤» ብሏል። ኢሳ ፱፥፮። በተጨማሪም፦ «ከእሴይ ሥር በትር ትወጣለች፤ አበባም ከግንዱ ይወጣል፤» ብሏል። ኢሳ ፲፩፥፩። ትርጉሙም፦ ከነገደ እሴይ (ከዳዊት ወገን) በትረ ሕይወት እመቤታችን ትወለዳለች፥ ከእርሷም አበባ ክርስቶስ ይወለዳል ማለት ነው። ነቢዩ ኤርምያስም፦ «እነሆ ለዳዊት የጽድቅ ቊጥቋጥ አበቅልለታለሁ፤ እርሱም ፍርድንና ጽድቅን በምድር ያደርጋል፤» የሚል አለ። ኤር ፴፫፥፲፬። ትርጉሙ ካለፈው ጋር አንድ ነው፥ አይለወጥም። በትንቢተ ሕዝቅኤል ላይ ደግሞ፦ «በላያቸውም አንድ እረኛ አቆማለሁ፤ እርሱም ባሪያዬ ዳዊት ነው፤ እረኛም ይሆናቸዋል።» ተብሎ ተነግሯል። በተጨማሪም፦ «ባሪያዬም ዳዊት በላያቸው ንጉሥ ይሆናል፤ ለሁሉም አንድ እረኛ ይሆንላቸዋል፤ በፍርዴም ይሄዳሉ፥ ትእዛዜንም ይጠብቃሉ፤ ያደርጓትማል።» ይላል። ሕዝ ፴፯፥፳፬። ሕዝ ፴፬፥፳፫።ይህም ለፍጻሜው ለክርስቶስ የተነገረ ቃለ ትንቢት ነው። ይኽንንም የትንቢቱ ባለቤት ራሱ ኢየሱስ ክርሰቶስ፦ «መልካም እረኛ እኔ ነኝ መልካም እረኛ ስለበጎቹ ነፍሱን ይሰጣል። . . . . . እረኛው አንድ መንጋውም አንድ ነው፤» በማለት ነግሮናል። ዮሐ ፲፥፲፩፣፲፮።
፪፥፫፦ አብርሃም ሥርወ ሃይማኖት ስለሆነ ነው፤
          አብርሃም፦ እግዚአብሔርን ያገኘው በሥነ ፍጥረት ተመራምሮ ነው። አብርሃም የኖረው የጣኦት አምልኮት በተስፋፋባት በካራን ነው። ካራን፦ በነነዌና በኤፍራጥስ ወንዝ መካከል የነበረ ከተማ ነው። የአብርሃም አባት ታራ ጣዖት እየሠራ ይሸጥ ይለውጥ ነበር። ይህም ልማድ ከአያቱ ከሴሩሕ ጀምሮ ተያይዞ የመጣ ነው። ሴሩሕ ናኮርን ወለደ፥ ናኮር ታራን ወለደ፥ታራ ደግሞ አብርሃምን ወለደ። ኩፋሌ ፲፥፳፮-፴።
፪፥፫፥፩፦ አብርሃም የጣዖት አምልኮትን ተቃወመ፤
          አብርሃም ከልጅነቱ ጀምሮ፦ ጣዖታቱን በመከተልና ኃጢአትን በመሥራት እንደሚሳሳት የምድርን ስሕተት ያውቅ ነበር። አባቱም መጽሐፍ አስተምሮታል፤ የሁለት ሱባዔ ዓመት ልጅ በነበረ ጊዜም ለጣዖት እንዳይሰግድ አባቱን ከመከተል ተለየ። ከሰዎች ልጆች ስሕተትም ያድነው ዘንድ፥ ዕጣውም ርኲሰትንና ፌዝን በመከተል ወደ ስሕተት እንዳይሆን ሁሉን ወደ ፈጠረ ወደ እግዚአብሔር ይጸልይ ጀመር። ኩፋሌ ፲፥፴፩-፴፫።
          አብርሃም አባቱን ታራን፦ «ምንት ተድላ ወረድኤት ለነ አባ፤ አባቴ ሆይ፥ ከእነዚህ ከጣዖታቱ ለእኛ ምን ረድኤትና ደስታ አለን?» አለው። ታራም አብርሃምን፦ «ልጄ፥እኔም እንደማይረባንና እንደማይጠቅመን አውቃለሁ፤ ነገር ግን የዚህ ሀገር ሰዎች በፍቅረ ጣዖት የሰከሩ ስለሆኑ እንዳያጠፉን ፈርቼ ነው፤» <እንደ ወንዙ ይሻገሩ፥ እንደ ሀገሩ ይኖሩ፤> ብዬ ነው፤» አለው። ኩፋሌ ፲፥፵፪-፵፭።
          ታራ፦ እንጨት ጠርቦ ፥ደንጊያ አለዝቦ ጣዖት ከሠራ በኋላ፥ አብርሃምን፦ «ወደ ገበያ ሒደህ ሸጠህ ና፤» አለው። አብርሃምም በመንገድ ሳለ፦ «አፍ እያለው የማይናገር፥ እጅ እያለው የማይዳስስ፥ እግር እያለው የማይራመድ ይህ ምንድነው?» አለ። ከገበያውም ገብቶ፦ «አፍ እያለው የማይናገር እጅ እያለው ያማይዳስስ፥ እግር እያለው የማይራመድ ጣዖት ግዙ፤» አላቸው። «ባለቤት ያቀለለውን ገንዘብ ባለዕዳ አይቀበለውም፤» እንዲል፦ «እርሱ እንዲህ እያለ ያራከሰው ለእኛ ምን ይረባናል?» ብለው የማይገዙት ሆኗል።
          አብርሃም ጣዖቱን ይዞ ወደ ቤቱ ሲመለስ፦ «ርቦኛል አብላኝ፥ ጠምቶኛል አጠጣኝ፤» ቢለው የማይመልስለት ሆነ። ሁለተኛም፦ «የደከመው ሰው ቢያጫውቱት ይበረታልና አጫውተኝ፤» ቢለው ዝም አለው። በመጨረሻም፦ «ይህስ ፍጡር ነው እንጂ ፈጣሪዬ አይደለም ድዳ ነው፥ ልቡናንም የሚያስት ነው፤ ፈጣሪዬ ሌላ ነው፤» ብሎ ከትከሻው አውርዶ በደንጊያ ቀጠቀጠው።
፪፥፫፥፪፦ አብርሃም ፈጣሪውን ፈለገ፤
          አብርሃም ፈጣሪውን ለማግኘት ባደረገው ጉዞ ፍጥረታትን ይመለከት፥ ይመረምር ጀመር። ተራራውን ከፍ ብሎ ቢያየው፦ «አምላክስ ይህ ነው፤» አለ። ይህንንም፦ አንዱ ተራራ ሌላውን ሲበልጥ አይቶ፦ «በፈጣሪ መብለጥ መበላለጥ የለበትም፥ ስለዚህ ይህም አምላክ አይደለም፤» አለ። ሁለተኛም ነፋስ፦ ባሕር ሲገሥጽ፥ ዛፍ ሲያናውጥ አይቶ፥ «አምላክስ ይህ ነው፤» አለ። ነፋስንም፦ ተራራ ሲገታው፥ መዝጊያ ሲመልሰው አይቶ፦ «ፈጣሪንስ የሚገታው የለም፥ ይህም አምላክ አይደለም፤» አለ። ሦስተኛም፦ የባሕሩን ማዕበልና ሞገድ አይቶ «አምላክስ ይህ ነው፤» አለ። ባሕርም ሲሞላና ሲጐድል አይቶ፦ «በፈጣሪስ ሕፀፅ (ጉድለት) የለበትም ፥ ይህም አምላክ አይደለም፤» አለ። አራተኛም፦ እሳት፦ ደረቁን ከርጥቡ ለይቶ ሲበላ፥ ቋያውን ሲያቃጥል አይቶ፦ «አምላክስ ይህ ነው፤» አለ። እርሱንም ውኃ ሲያጠፋው፥ መንገድ ሲከለክለው አይቶ፦ «ይህም አምላክ አይደለም፤» አለ። አምስተኛም፦ ፀሐይ በዓለሙ መልቶ ሲያበራ አይቶ፦ «አምላክስ ይህ ነው፤» ብሏል። እርሱም፦ በምሥራቅ ወጥቶ በምዕራብ ሲገባ አይቶ «በፈጣሪስ መውጣት መግባት የለበትም፥ ቀን ቢመግበን ማታ ማን ይመግበናል? ለዚህም ፈጣሪ አለው፤» አለ። ከዚህ በኋላ፦ «አምላከ ፀሐይ ተናበበኒ፤ የፀሐይ አምላክ አነጋግረኝ፤» ብሎ ጮኸ። እግዚአብሔርም ድምፁን አሰምቶታል፤ አንድም መልአከ እግዚአብሔር ተገልጦለት፦ «እነዚህ ሁሉ ፍጡራን ናቸው ፥ የፈጠራቸው አለ፤» ብሎታል። አብርሃምን ሥርወ ሃይማኖት ያሰኘው ይህ ነው። አብርሃም ፈጣሪውን በማግኘቱ ፥ በሌሊት ተነሥቶ፥ የጣዖታቱን ቤት በውስጡ ያለውንም ዕቃ ሁሉ አቃጠለ። እንዲህ ማድረጉንም ያወቀ ሰው የለም፤ ወንድሙ አራን ግን ጣዖታቱን አድናለሁ ብሎ ከእሳቱ ገብቶ፥ ተቃጥሎ ሞቷል። ኩፋ ፲፩፥፩-፫።
          አብርሃም፦ እግዚአብሔርን ፈልጎ ካገኘ በኋላ በጣዖት መንደር እንዲኖር አልተፈቀደለትም። «ፃእ እምድርከ ወእምአዝማዲከ ወእምቤተ አቡከ፤ ወሑር ውስተ ምድር እንተ አርእየከ። ወእሬስየከ ሕዝበ ዐቢየ ወእባርከከ፤ ወአዐቢ ስመከ፥ ወትከውን ቡሩከ፤ ወእባርኮሙ ለእለ ይባርኩከ፥ ወእረግሞሙ ለእለ ይረግሙከ። ከአባትህ ወገን ከዘመዶችህ ተለይተህ ከአገርህ ውጣ፤ እኔ ወደማሳይህ ወደ ከነዓንም ሂድ። ብዙ ወገን አደርግሃለሁ፥ አከብርሃለሁ፤ ስምህንም አከብረዋለሁ፥አገነዋለሁ፥አበ ብዙኃን እንድትባል አደርግሃለሁ። የሚመርቁህን እመርቃቸዋለሁ፥የሚረግሙህን ሰዎች አጠፋቸዋለሁ፤» ተብሏል። አብርሃምም በፍጹም ሃይማኖት፦ ከዘመዶቹ ተለይቶ ከሀገሩ ወጥቷል፥ እግዚአብሔርን አምኖ ወደማያውቀው ሀገር ተጉዟል። ዘፍ ፲፪፥፩-፫። እግዚአብሔር ጠርቶናል፥ እግዚአብሔርን እናገለግላለን የምንል ሰዎች ከአብርሃም ተምረን ከመንደር ልንወጣ ማለትም ከዘረኝነት ልንላቀቅ ይገባናል፤ መንፈሳዊ ሆነናል ካልን በኋላም የሥጋ ዝምድና ከመቊጠር ልንጠበቅ ያስፈልገናል። ለሃይማኖት ሰው ሁሉ አገሩ፥ ሁሉ ወገኑ ነውና።
          አብርሃም የመቶ ዓመት ሽማግሌ ከሆነ በኋላ ከቃል ኪዳን ሚስቱ እድሜ ከተጫናት (ዘጠና ዓመት ከሞላት) ከሣራ ይስሐቅን የወለደው በሃይማኖት ነው። በአንድነት በሦስትነት የሚመሰገኑ ሥላሴን በድንኳኑ ባስተናገደ ጊዜ፦ «ሶበ ገባእኩ እመጽእ ኀቤከ አመ ከመ ዮም ትረክብ ሣራ ወልደ፤ እንደ ዛሬ ጊዜ ተመልሼ በረድኤት ወደ አንተ በመጣሁ ጊዜ ሣራ ወንድ ልጅን ትወልዳለች፤» የተባለውን በሃይማኖት ተቀበለ። ተስፋውን የሰሙት ሐምሌ ሰባት ቀን ነው፤ በተነገራቸው ተስፋ መሠረት ይስሐቅ የተፀነሰው በመስከረም ልደቱ ደግሞ በሰኔ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ፦ የአብርሃምን ሃይማኖት ሲመሰክር፦ «ስለዚህም እግዚአብሔር ለአብርሃምና ለዘሩ የሰጠው ተስፋ የታመነ ይሆን ዘንድ፥ የሚጸድቁ በእምነት እንጂ የኦሪትን ሥራ በመፈጸም ብቻ እንዳይደለ ያውቁ ዘንድ እግዚአብሔር ጽድቅን በእምነት አደረገ። ለብዙዎች አሕዛብ አባት አደርግሃለሁ ተብሎ እንደተጻፈ ሙታንን በሚያስነሣቸው፥ የሌሉትንም እንዳሉ በሚያደርጋቸው በአመነበት በእግዚአብሔር ፊት አብርሃም የሁላችን አባት (የሃይማኖት አባት፥ የሃይማኖት ሥር፥ የሃይማኖት መሠረት) ነው። አብርሃም ዘርህ እንዲህ ይሆናል ብሎ እግዚአብሔር ተስፋ እንደሰጠው ተስፋ ባልነበረ ጊዜ የብዙዎች አሕዛብ አባት እንደሚሆን አመነ። አብርሃም የመቶ ዓመት ሽማግሌ ስለሆነ እንደ ምውት (እንደ ሬሣ) የሆነውን የራሱን ሥጋና የሳር ማኅፀን ምውት (ሙቀት ልምላሜ የተለየው) መሆኑን እያየ በእምነት አልተጠራጠረም፤ በእምነት ጸና እንጂ፤ ለእግዚአብሔርም ክብርን ሰጠ። እግዚአብሔርም የሰጠውን ተስፋ ሊያደርግለት እንደሚችል በፍጹም ልብ አመነ።»ብሏል።ሮሜ ፬፥፲፮-፳፮።
          የአብርሃም እምነት በነገር ሁሉ ነው፤ አብርሃም የዘጠና ዘጠኝ ዓመት በነበረ ጊዜ እግዚአብሔር ተገልጦለት፦ «በፊትህ የሄድሁ ፈጣሪህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፤ በፊቴ መልካም አድርግ፤ ንጹሕም ሁን፤ ቃል ኪዳኔንም በእኔና በአንተ መካከል አጸናለሁ፤ እጅግም አበዛሃለሁ፤» አለው። አብርሃምም በግንባሩ ወደቀ፤ (ሰገደ)፤ እግዚአብሔርም አብርሃምን፦ አንተ ደግሞ ቃል ኪዳኔን ትጠብቃለህ፤ አንተም ከአንተም በኋላ ዘርህ በትውልዳቸው። በእኔና በአንተ መካከል፥ ከአንተም በኋላ በዘርህ መካከል የምትጠብቋት ቃል ኪዳኔ ይህች ናት፤ ከእናንተ ወንድ ሁሉ ይገረዝ። የሰውነታችሁን ቊልፈት ትገረዛላችሁ፤ በእኔና በእናንተ መካከል ላለውም ቃል ኪዳን ምልክት ይሆናል። ሕፃኑንም በስምንተኛው ቀን ትገርዙታላችሁ፤» አለው። ዘፍ ፲፯፥፩-፱። አብርሃም ይህን ሥርዓተ ግዝረት የተቀበለው በእምነት ነው። በመሆኑም ወዲያው በቤተሰቦቹ ላይ ተግባራዊ አድርጐታል። እርሱም ራሱ በዘጠና ዘጠኝ ዓመቱ ተገዝሯል። ዘፍ ፲፯፥፳፫። ይህም የእምነት ምልክት ሆኖ እስከ ጥምቀተ ክርስትና አድርሷል። ምክንያቱም ግዝረት የጥምቀት ምሳሌ ነበርና ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «እግዚአብሔር አብርሃምን ሳይገዘር በእምነት እንደ አጸደቀው በእርሱ ላይ ይታወቅ ዘንድ ግዝረትን የጽድቅ ማኅተም ትሆነው ዘንድ ምልክት አድርጎ ሰጠው፤» ብሏል። ሮሜ ፬፥፲፩። በቈላስይስ መልእክቱም፦ «የኃጢአትን ሰውነት ሸለፈት በመግፈፍ በክርስቶስ መገረዝ በሰው እጅ ያልተደረገ መገረዝን በእርሱ ሆናችሁ ተገረዛችሁ። በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችኋል፤ በእርስዋም ከሙታን ለይቶ ባስነሣው በእግዚአብሔር ረዳትነትና በሃይማኖት ከእርሱ ጋር ተነሥታችኋል።» በማለት ተናግሯል። ቈላ ፪፥፲፩።
          አብርሃም ልጁ ይስሐቅን በመሠዊያ ላይ አጋድሞ ሊሠዋው እጁን ያነሣው በእምነት ነው። «እኔ ለእግዚአብሔር ብዬ ስሠዋው፥ እግዚአብሔር ደግሞ ለእኔ ብሎ ከሞት አሥነስቶ በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃል ያለኝን ቃል ኪዳኑን ይፈጽምልኛል፤» ብሎ አምኗል። ይኽንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «አብርሃምም እግዚአብሔር በፈተነው ጊዜ ልጁን ይስሐቅን ይሠዋው ዘንድ በእምነት ወሰደው። በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃል ብሎ ተስፋ ያናገረለትን አንድ ልጁን አቀረበው። እግዚአብሔር ከሙታን ለይቶ ሊያስነሣው እንደሚችል አምኖአልና፤» በማለት ተናግሯል። ዕብ ፲፩፥፲፯-፲፱።
፪፥፫፥፫፦ አብርሃምም ትንቢት ተነግሮለታል፤
          እግዚአብሔር፦ አብርሃምን፦ «ከሀገርህ ውጣ፥ ከዘመዶችህም ተለይ፤» ባለው ጊዜ፦ «የምድር አሕዛብ በአንተ ይባረካሉ፤ (አብርሃምን ያከበረ ያክብርህ እያሉ በአንተ ይመራረቃሉ)፤» ብሎታል። ዘፍ ፲፪፥፫። ይህም፦ በረከተ ሥጋን በረከተ ነፍስን የሚያድል፥ መርገመ ሥጋን መርገመ ነፍስን የሚያጠፋ አምላክ ኢየሱስ ክርሰቶስ ከእርሱ ወገን እንደሚወለድ የሚያመለክት ቃለ ትንቢት ነበር። እግዚአብሔር በአንድነት በሦስትነት ለአብርሃም ተገልጦ ወደ ድንኳኑ በገባ ጊዜም፦ «የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ወደ አንተ ተመልሼ እመጣለሁ፤» ብሎታል። ይህም ለጊዜው ይስሐቅ እንደሚወለድ የሚገልጥ ቃለ ትንቢት ሲሆን ለፍጻሜው ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእርሱ ወገን ማለትም የባሕርዩ መመኪያ ከሆነች ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ እንደሚወለድ የሚያጠይቅ ነበር። ዘፍ ፲፰፥፲።


Source: http://www.facebook.com/groups/180759695294706/doc/192983760738966/

ነገረ ማርያም ክፍል ፲

መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው

 
የሰው ልጅ ባሕርይ በአዳም ኃጢአት ምክንያት አድፎ ቆሽሾ ይኖር ነበር። በዚህም ምክንያት ጽድቁ ሁሉ የመርገም ጨርቅ ሆኖበት ፥ በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስ ተጨምሮበት ወደ ሲኦል ሲጋዝ ኖሯል። ይህንንም ታላቁ ነቢይ ኢሳይያስ፦ «ሁላችን እንደ ርኲስ ሰው ሆነናል ፥ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው፤ ሁላችንም እንደ ቅጠል ረግፈናል ፦ በደላችንም እንደ ነፋስ ወስዶናል፤ » በማለት ገልጦታል። ኢሳ ፷፬፥፮ ። እንዲህም ማለቱ፦ ነቢያት እና ካህናት አምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመት የጸለዩት ጸሎት ፥ የሰዉት መሥዋዕት ፥ በዕደ እግዚአብሔር ለመያዝ አበቃቸው እንጂ፦ ለክብር ፣ ለልጅነት ፣ ለገነት ለመንግሥተ ሰማያት እንዳላበቃቸው ለመናገር ነው። እንደ «ቅጠል ረግፈናል፤» ያለውም፦ ለጊዜው በመዓት፣ በመቅሠፍት መርገፍን ሲሆን ፥ ለፍጻሜው በአካለ ነፍስ በሲኦል መርገፍን ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «ስለዚህም በአንድ ሰው በደል ምክንያት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባች፤ ስለዚችም ኃጢአት ሞት ገባ፤ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስለ አደረጉ በሰው ሁሉ ላይ ሞት መጣ። . . . ነገር ግን በአዳም ኃጢአት ምክንያት ከአዳም እስከ ሙሴ (እስከ ክርስቶስ) የበደሉትንም ያልበደሉትንም ሞት ገዛቸው፤ ሁሉ በአዳም አምሳል ተፈጥሮአልና ፥ አዳምም ይመጣ ዘንድ ላለው ለእርሱ አምሳል ነውና፤» ብሏል። ሮሜ ፭፥፲፪-፲፬።           ከሰው ወገን ባሕርይዋ ያላደፈባት ፥ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ ያልወደቀባት ፥ ጥንተ አብሶ (የአዳም የጥንት በደል) ያልነካት ፥ በሥጋም በነፍስም ፍጽምት ሆና የተፈጠረች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ብቻ ናት። በዚህም ምክንያት የአዳም ኃጢአት እንደ ቅጠል ላረገፈው የሰው ዘር በጠቅላላ የባሕርዩ መመኪያ ሆናለታለች። ነቢዩ ኢሳይያስ፦ « የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ፥ እንደ ሰዶም በሆንን ፥ እንደ ገሞራም በመሰልን ነበር፤» ያለው ለፍጻሜው ስለ እርሷ ነው። ኢሳ ፩፥፱። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ የነሣውን (ነፍስንና ሥጋን ነሥቶ የተዋሐደው) ከአብርሃም ዘር እንጂ ከመላእክት የነሣው አይደለምና። (የመላእክትን ባሕርይ ባሕርይ አላደረገም)።» ያለው እመቤታችንን ነው። ዕብ ፪ ፥ ፲፮።  ይህንን ጠንቅቆ የሚያውቅ ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬምም በዕለተ ሰንበት የውዳሴ ማርያም ድርሰቱ፦ «ጸጋን የተመላሽ ሆይ ፥ ከቅዱሳን ሁሉ ይልቅ ትለምኝልን ዘንድ ለአንቺ ይገባል፤ አንቺ ከሊቃነ ጳጳሳት ትበልጫለሽ፤ ከነቢያትም ከመምህራንም ትበልጫለሽ፤ ከሱራፌልና ከኪሩቤል ግርማ የሚበልጥ የመወደድ ግርማ አለሽ፤» ካላት በኋላ፦ «በእውነቱ የባሕርያችን መመኪያ አንቺ ነሽ፤» ብሏታል።
          አምላካችን በሁሉ ባዕለጸጋ ነው፥ ሁሉ የእርሱ ነው ፥ የእርሱ ብልጽግና የማይጎድል ብልጽግና ነው፤ ይኽንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «የእግዚአብሔር ባለጠግነት፥ ጥበብና ዕውቀት እንዴት ጥልቅ ነው!» ብሏል። ሮሜ ፲፩፥፴፫። እግዚአብሔርም ከዚህ ጥልቅ ከሆነ ብልፅግናው ለሰው ልጆች ሁሉ ጸጋ አድርጎ በልግስና ሰጥቷል፥ በየጊዜውም በጸጋ ላይ ጸጋ ይጨምራል። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ፦ «እኛም ሁላችን ከሙላቱ በጸጋ ላይ ጸጋ ተቀበልን። ኦሪት በሙሴ ተስጥታ ነበርና፤ ጸጋና እውነት በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነልን፤»ያለው ለዚህ ነው። ዮሐ ፩፥፲፮።
          የባዕለጸጎች ባዕለጸጋ የሆነ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ የእኛን ባሕርይ በመንሣቱ፦ «ነገር ግን የባርያን መልክ ይዞ ፥ በሰው ምሳሌ ሆኖ ራሱን ዝቅ አደረገ። እንደ ሰው ራሱን አዋረደ፤» ተብሏል። ፊል ፪፥፯። በቆሮንቶስ መልእክትም ላይ ፦ «የጌታችን የኢየሱስ ክርሰቶስን ቸርነቱን ታውቃላችሁ፤ በእርሱ ድህነት እናንተ ባለጸጎች ትሆኑ ዘንድ እርሱ ባለጸጋ ሲሆን፥ ስለእናንተ ራሱን ድሃ አደረገ፤» የሚል ተጽፏል። ፪ኛ ቆሮ ፰፥፱። ከሁሉም በላይ ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ሁሉ የእርሱ ሲሆን ፦ «ለቀበሮዎች ጉድጓድ ለሰማይም ወፎች መስፈሪያ አላቸው፥ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም፤» ብሏል። ማቴ ፰፥፳።
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆነ እንጂ፦ ከባሕርዩ ምንም አልተለወጠም። የእኛን ባሕርይ በተዋሕዶ ገንዘብ አድርጎ ሰው ሆኗል። እርሱ በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነው፥ የክብር አምላክ ሲሆን በተዋሕዶ ከበረ፥ ተባለ፤ ሕይወት ሲሆን ነፍስን ነሣ፥ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ፦ «ሕይወት በእርሱ ነበረ፥ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረ፤» ብሏል። ዮሐ ፩፥፬። በመልእክቱም፦ «ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና በጆሮአችን የሰማነውን ፥ በዓይናችንም የተመለከትነውንም ፥ እጆቻችንም የዳሰሱትን እንነግራችኋለን። ሕይወት ለእኛ ተገልጻለችና አየናት፤ ምስክርም ሆንን፤ ለእናንተም ከአብ ዘንድ ያለችውንና ለእኛ የተገለጠችውን የዘለዓለምን ሕይወት እንነግራችኋለን፤» በማለት ነግሮናል። ፩ኛ ዮሐ ፩፥፩። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፦ «የሕይወትንም ራስ ገደላችሁት ፤ » በማለት አይሁድን የወቀሳቸው እርሱ ሕይወት ስለሆነ ነው። የሐዋ ፫፥፲፭። ጌታችንም ፦ «እኔ ሕይወት ነኝ፤» በማለት ለደቀመዛሙርቱ ነግሮአቸዋል። ዮሐ ፲፬፥፮።
          አንድ ክርስቶስ (ወልድ ዋሕድ) የሕይወት እንጀራ ሲሆን ባሕርያችንን በመንሣቱ ማለትም ረሀብ የሚስማማውን የሥጋን ባሕርይ በመዋሐዱ ተራበ፥ ዮሐ ፮፥፴፭፤ ማቴ ፳፩፥፲፰፤ የሕይወት ውኃ ሲሆን ተጠማ፥ ዮሐ ፬፥፲፤ ፲፱፥፳፰፤ ተንገላታ፥ « ለሞት እስከመድረስም ታዘዘ፤ ሞቱም በመስቀል የሆነው ነው።» እንዲል፦ እስከ መስቀል ሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ፤ ፊል ፪፥፰። ጌታችን ከባሕርይ አባቱ ከአብ፥ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በፈቃድ አንድ ሲሆን፦ «አባቴ ሆይ ፥ የሚቻልስ ከሆነ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን ፈቃድህ ይሁን እንጂ የእኔ ፈቃድ አይደለም፤ » ያለው ለዚህ ነው። ማቴ ፳፮፥፴፱። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «ልጅም ቢሆን መከራን ስለተቀበለ መታዘዝን አወቀ፥ ከተፈጸመም በኋላ ለሚታዘዝለት ሁሉ ሕይወትን የሚሰጥ የዘላለም መድኅን ሆነ፤» ብሏል። ዕብ ፭፥፰።
          እርሱ በባሕርዩ ሞት የለበትም፥ ሕያወ ባሕርይ ነው፤ ጌታችን ፦ ቅዱስ ዮሐንስን፦« አትፍራ፥ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፤ ሞቼም ነበረሁ፤ እነሆም፥ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ሕያው ነኝ፤ የሞትና የሲኦል መክፈቻም በእኔ ዘንድ አለ፤» ያለው ለዚህ ነው። ራዕ ፮፥፲፯። ጌታችን ሞት የሚስማማውን የሥጋን ባሕርይ በመዋሐዱ ሞተ፥ሞተ የተባለውም ነፍስ ከሥጋ በመለየቷ ነው። «ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ፤» እንዲል፦ ከሥጋ የተለየች ያቺ ነፍስ የእርሱ ናት። ዮሐ ፲፱፥፴። በሉቃስ ወንጌል ደግሞ ፦ «አባት ሆይ ፥ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ፤» የሚል አለ። ሉቃ ፳፫፥፵፮። ጌታችን «ነፍሴ» ማለቱ በተዋሕዶ የራሱ ገንዘብ ስላደረጋት ነው። «እነሆ በጎና ጻድቅ ሰው የሸንጎ አማካሪም የሆነ ፥ ዮሴፍ የሚባል ሰው ነበረ፤ ይህም በምክራቸውና በሥራቸው አልተባበረም ነበር፤ አርማትያስ ከምትባል ከይሁዳ ከተማ ሆኖ እርሱ ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ይጠባበቅ ነበር። ይኸውም ወደ ጲላጦስ ቀርቦ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው። » እንዲል፦ ነፍስ የተለየችው ሥጋም በተዋሕዶ የእርሱ ገንዘብ ነው። ዮሐ ፲፱፥፴፰።
          መለኮት የእኛን ባሕርይ ተዋሐደ፥ ስንል ፦ የተዋሐዶው ምሥጢር የሰው አእምሮ ሊረዳው ከሚችለው በላይ ነው፥ ይህም፦ በሥጋ እውቀት የሚረዱት አይደለም ማለት ነው። ለመሆኑ የነፍስን እና የሥጋን ተዋሕዶ ልንረዳ የምንችለው በምን መልክ ነው? ነፍስ በባሕርይዋ የሥጋን ፈቃድና ምቾት ባትካፈልም፦ ፈቃዷን የምትፈጽመው በሥጋ ላይ ነው። ሥጋ የእርሱን ፈቃድ ትቶ ለእርሷ ፈቃድ እንዲገዛ ሁልጊዜ ትፈልጋለች። ቅዱስ ጳውሎስ፦ «እላችኋለሁ፤ በመንፈስ (በፈቃደ ነፍስ) ኑሩ እንጂ የሥጋችሁን ፈቃድ አታድርጉ። ሥጋ፦ መንፈስ (ነፍስ) የማይሻውን ይሻልና፥ መንፈስም (ነፍስም) ሥጋ የማይሻውን ይሻልና፥ የምትሹትንም እንዳታደርጉ እርስ በርሳቸው ይጣላሉ፤» ያለው ለዚህ ነው፤ ገላ ፭፥፲፮። ክርስቶስም ፦ በመለኮቱ ሕማም (መከራ) የማይስማማው ሲሆን ሕማም የሚስማማትና ሁሉን አዋቂ የሆነች ነፍስ ያለውን ሥጋ ተዋሕዷል።
          ጌታ በሥጋው መከራ ሲቀበል፦ በተዋሐደው ሥጋ መከራ ተቀበለ፥ በዚህም አሥራ ሦስቱን ሕማማተ መስቀል ገንዘብ አደረገ። በመሆኑም ከተዋሕዶ በኋላ ጌታን ለሁለት ከፍሎ በመለኮቱ መከራ አልተቀበለም፥ በሥጋው ብቻ መከራ ተቀበለ አይባልም። አንድ ሰው ሥጋም ነፍስም ስላለው አንድ ሰው እንጂ ሁለት አይባልም፤ ነፍሱ ከሥጋው ጋር በተዋሕዶ አንድ ስለሆነች አንድ ሰው መባሉ ግድ ነው። ክርስቶስም በተዋሕዶ የከበረ አምላክ ስለሆነ አንድ እንጂ ሁለት አይባልም። ከዚህ በመቀጠል ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት፦
የጽላት ፥ የታቦት ምሳሌነት፦
          የጽላት የታቦት ምንጭ እግዚአብሔር ነው ፥ ልበ-ወለድ አይደለም። «እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር በሲና ተራራ የተናገረውን በፈጸመ ጊዜ ሁለቱን የምስክር ጽላት ፤ በእግዚአብሔር ጣት የተጻፈባቸውን ( በግብር አምላካዊ ተጽፈው የተገኙትን) የድንጋይ ጽላት ለሙሴ ሰጠው።» እንዲል፦ ጽላትን ቀርጾ አክብሮ ለሙሴ የሰጠው እግዚአብሔር ነው። ዘጸ ፴፩፥፲፰። «ጽላቱም በዚህና በዚያ በሁለት ወገን ተጽፎባቸው ነበር። ጽላቱ የእግዚአብሔር ሥራ ነበሩ፤ ጽሕፈቱም በጽላቱ ላይ የተቀረጸባቸው የእግዚአብሔር ጽሕፈት ነበረ፤» ይላል። ዘጸ ፴፪፥፲፭።
          ጽላቱ በተሰበሩ ጊዜም፦ እንደገና የቀደሙትን አስመስሎ እንዲቀርጽ እግዚአብሔር ለሙሴ ፈቅዶለታል። እግዚአብሔር ሙሴን፦ «የቀደሙትን ጽላት አስመስለህ ሁለት ጽላት ቀርጸህ እኔ ወደምገለጽበት ተራራ ውጣ ፥ ቀድሞ በሰበርካቸው ጽላቶች ተጽፈው የነበሩ አሥሩ ቃላትም በእነዚህ ጽላቶች ጽፌ እሰጥሃለሁ፤ ማለዳ ወደ ደብረ ሲና ትወጣለህና ተዘጋጅተህ ንጹህ ሁነህ እደር ፥ ማልደህም ወደ ደብረ ሲና ወጥተህ ቁም፤ ሌላ ሰው ግን ካንተ ጋር ወጥቶ ከተራራው ላይ አብሮህ የሚቆም አይኑር፥ ላሞችም በጎችም ቢሆኑ በተራራው አቅራቢያ ሊሠማሩ አይገባም፤» አለው። ሙሴም የቀደሙትን ጽላቶች አስመስሎ ሁለት የእብነበረድ ጽላት ቀርጾ ይዞ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ማልዶ ገሥግሦ ወደ ደብረ ሲና ወጣ።
          እግዚአብሔርም በደመና ወርዶ ፥ በደብረ ሲና ራስ ላይ ቁሞ ፥ እኔ፦ «መሓሪ ወመስተሣህል ነኝ፤ » ብሎ ተናገረ። በሙሴም ፊት በብርሃን ሠረገላ ሁኖ የጌትነቱን ስም እየጠራ አለፈ፤ «ስሜም፦ ይቅር ባይ ፥ ከመዓት የራቀ ፥ ቸርነቱ የበዛ ፈጥሮ የሚገዛ መባል ነው፤ የአብርሃምን መሓላ አጽንቼ ፥ ለአእላፈ እሥራኤል ቸርነትን የማደርግ ፥ አመጽን፣ በደልን ፣ ኃጢአትን የማርቅ ፥ ይቅር የምል እኔ ነኝ፤ በድሎ የማይመለሰውን ግን ከኃጢአት አላነጻውም፤ (ይቅር አልለውም) ፤» አለ። አመጻ የድፍረት ፥ በደል የስህተት ፥ ኃጢአት የድካም ነው።
          ሙሴ የእግዚአብሔርን ቃል በሰማ ጊዜ፦ ደንግጦ ፥ አንገቱን ሰበር አድርጎ ለእግዚአብሔር የፍርሃት ስግደት ሰገደ፤ እግዚአብሔርንም፦ «በአንተ ዘንድ ሞገስን (ባለሟልነትን) ካገኘሁ ፥ አንተ ጌታዬ ከእኔ ጋር በረድኤት አብረኸኝ ሂድ ፥ እሥራኤል ክሣዳ ልቡናቸው በኃጢአት የጸና ነውና የወገኖችህን ፍጹም ኃጢአት ይቅር በል፥ ይህን ያደረግህልን እንደሆነ ለአንተ ስንገዛ እንኖራለን፤» አለው። እግዚአብሐርም ሙሴን፦ «በወገኖችህ ዘንድ የኪዳን ምልክት ይሆን ዘንድ ብርሃን በፊትህ እሥልብሃለሁ፥ በአራቱም መዓዝን ባሉ በአሕዛብ ዘንድ ሁሉ ተደርጎ የማያውቅ ጭጋግ ተአምራት አደርግልሃለሁ፤ እኔም የማደርግልህ ነገር ድንቅ ነውና አንተ በመካከሉ ያለህበት ይህ ሕዝብ ሁሉ የእግዚአብሔርን ሥራ ያያል፤ » አለው። ከዚህም አያይዞ አያሌ ትእዛዛትን አዝዞታል።
          በመጨረሻም እግዚአብሔር ሙሴን፦ «በእነዚህ ቃሎች ከአንተ ከእሥራኤል ጋር ቃል ኪዳን አድርጌአለሁና (ሕጌን ቢጠብቁ እጠብቃቸዋለሁና) እነዚህን ቃሎች (የነገርኩህን ሁሉ) ጻፍ፤» አለው። በዚያ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በእግዚአብሔር ፊት ነበረ፤ እንጀራም አልበላም ፤ ውኃም አልጠጣም፤ በጽላቱም አሠሩን የቃል ኪዳን ቃሎች ጻፈ። ዘጸ ፴፬፥፩-፳፰።
          የቀደመው ጽላት የአዳም ምሳሌ ነው፤ ጽላቱ እምኀበ አልቦ እንደተገኘ ፥ አዳም እንበለ ዘርእ ለመገኘቱ ምሳሌ ነው፤ ጽላቱ ሁለት ወገን መሆኑ ለነፍሱና ለሥጋው ምሳሌ ነው፤ ጽላቱ በጣዖት ምክንያት መሰበሩ ደግሞ አዳም በኃጢአት ምክንያት ለመጎዳቱ ምሳሌ ነው፤ የመጀመሪያው ጽላት በእግዚአብሔር እጅ መሠራቱ አዳም በእግዚአብሔር እጅ ለመፈጠሩ ምሳሌ ነው። ቅዱስ ዳዊት፦ «እጆችህ ሠሩኝ ፥ አበጃጁኝም፤» ያለው ለዚህ ነው። መዝ ፻፲፰፥፸፫። የኋለኛው ጽላት የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ነው። ሁለት መሆኑ የነፍሷና የሥጋዋ ምሳሌ ነው። በጽላቱ ላይ ቃለ እግዚአብሔር መቀረጹ፥ ከሦሥቱ አካላት አንዱ አካላዊ ቃል (ቃለ አብ ፥ ቃለ መንፈስ ቅዱስ) ከሰማይ ወርዶ፥ በመንፈስ ቅዱስ ግብር በማኅፀኗ ሰው ሁኖ ለመቀረጹ ምሳሌ ነው። የኋለኛው ጽላት ከሰው ወገን በሙሴ እጅ መቀረጹ ፥ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሰው ወገን በሕግ በሆነ ሩካቤ ፥ ከቅዱስ ኢያቄምና ከቅድስት ሐና ለመወለዷ ምሳሌ ነው። ይኽንን በተመለከተ፦ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ ላይ ፦ «ድንግል ሆይ ፥ በኃጢአት ፍትወት የተጸነስሽ አይደለም ፥ በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ፤» ብሏል። (ቅዳ፡ ማር፡ ቁጥር ፴፰)
          እግዚአብሔር ጽላቱን ለሙሴ ከመስጠቱ በፊት የጽላቱን ማደሪያ ታቦቱን እንዲያዘጋጅ ነግሮታል። ከምንና እንዴት መሥራት እንዳለበትም አስተምሮታል። ይኽንንም ፦ «ከማይነቅዝ (ሽምሸርሰጢን ከሚባል) ዕፅ ቆርጠህ የምስክሩን ታቦት ሥራ፤ . . .  በውስጥና በውጭም በጥሩ ወርቅ ለብጠው፤ በእርሱም ላይ በዙሪያው የወርቅ አክሊል አድርግለት። አራት የወርቅ ቀለበቶችም አድርግለት፤ » በማለት ነግሮታል። ዘጸ ፳፭፥፲-፲፪። ታቦት የትስብእት ፥ ወርቅ ደግሞ የመለኮት ምሳሌዎች ናቸው፤ ታቦቱ በውስጥም በውጭም በወርቅ እንደተለበጠ፥ በወርቅ የተመሰለ መለኮትም፦ በውጭ የሚታይ ሥጋን እና በውስጥ ያለች የማትታይ ነፍስንም ተዋሕዶ ሰው ሆኗል። ታቦቱ ከማይነቅዝ ዕፅ መሠራቱም፦ የጌታችን ሥጋው በመቃብር፦ የማይፈርስ የማይበሰብስ ለመሆኑ ምሳሌ ነው። ይኽንን በተመለከተ ባለቤቱ ራሱ በነቢዩ በዳዊት አድሮ፦ «ነፍሴን (ሰውነቴን) በሲኦል አትተዋትምና ፥ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተወውምና፤» ብሏል። መዝ ፲፭ ፥፲። ታቦቱ የተለበጠበት ወርቅ ንጹህ መሆኑ፦ እግዚአብሔር በባሕርዩ ንጹሕ ለመሆኑ ምሳሌ ነው። ጌታ በተወለደ ጊዜ ሰብአ ሰገል ወርቅ መገበራቸው እርሱ ባወቀ «ንጹሐ ባሕርይ ነህ፤ » ሲሉት ነበር ፥ አንድም ወርቅ መለኮትህ ትስብእትን ተዋሕዷል ማለትም ነው። ማቴ ፪፥፲፩። ቅዱስ ኤፍሬምም በእሑዱ የውዳሴ ማርያም ድርሰቱ ፦ «ከማይነቅዝ እንጨት የተቀረጸ በውስጥና በውጭ በወርቅ የተለበጠ ታቦት ፥ ያለመለየትና ያለመለወጥ ሰው የሆነ ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ይመስልልናል። ይኽውም መለወጥ የሌለበት ንጹሕ መለኮት ነው፥ ከአብ ጋር የተካከለ ነው።» ብሏል።
የሁለቱ አዕዋፍ ምሳሌነት፤
          በኦሪቱ ለምጽ የርኲሰት ምልክት ስለነበረ፥ እግዚአብሔር በልሙጻን ላይ ከመንጻታቸውና ከነጹም በኋላም ሕግ ሠርቶባቸው ነበር። ይኽንንም፦ «ለምጽ የያዘው ሰው ሕጉ ይህ ነው፤ ከለምጽ በነጻበት ቀን ወደ ካህኑ ይወስዱታል ካህኑም ከሰፈር ወደ ውጭ ይወጣል፤ ካህኑም ያየዋል፤ እነሆም ፥ የለምጹ ደዌ ከለምጻሙ ላይ ቢጠፋ ፥ ካህኑ ስለሚነጻው ሰው ሁለት ንጹሐን ወፎች በሕይወታቸው ፥ የዝግባም እንጨት ፥ቀይ ግምጃም ፥ ሂሶጵም ያመጣ ዘንድ ያዝዛል። ካህኑም ከሁለቱ ወፎች አንደኛዋን በሸክላ ዕቃ ውስጥ በምንጭ ውኃ ላይ ያርድ ዘንድ ያዝዛል። ያልታረደችውን ወፍ ፥ የዝግባውንም እንጨት ፥ ቀዩንም ግምጃ ፥ ሂሶጱንም ወስዶ በታረደችው ወፍ ደም ውስጥ ይነክራቸዋል። ከለምጹም በሚነጻው ሰው ላይ ሰባት ጊዜ ይረጫል፤ ንጹሕም ይሆናል፤ ያልታረደችውንም ወፍ ወደ ሜዳ ይለቃታል።» በማለት ነግሮታል።ዘሌ ፲፬፥፩-፯።
          ሁለቱ ወፎች ንጹሐን መሆናቸው፦ መለኮትም  ፥ የተዋሐደው ሥጋም ንጹሐን ለመሆናቸው ምሳሌዎች ናቸው። አንዷ ወፍ ታርዳ በፈሰሰው ደም ሁለተኛዋ ወፍ ተነክራ በሕይወት መኖሯ ፦ ጌታ በተዋሐደው ሥጋ፦ ደሙን በመስቀል ላይ አፍስሶ ነፍሱን ከሥጋው ለይቶ ቢሞትም፦ በመለኮቱ ሕያው ለመሆኑ ምሳሌ ነው። ይኽንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፦ «ስለ እኛ ፥ ስለ ኃጢአታችን በሥጋ ሞተ፤ በመንፈስ (በመለኮት) ግን ሕያው ነው፤» ብሏል። ፩ኛ ጴጥ ፫፥፲፰። የምንጩ ውኃ ደግሞ ለጥምቀት ውኃ ምሳሌ ነው። ይኸውም፦ «ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ያልተወለደ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፤»ተብሎ የተነገረለት ነው። ዮሐ ፫፥፭። እርሱም ራሱ በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠምቆ፦ በጥምቀቱ የባረከው የቀደሰው ነው። ማቴ ፫፥፲፫።
          የእኛን ባሕርይ በመንሣት በተዋሕዶ ሰው የሆነ ጌታ፦ በሚበሩ አዕዋፍ የተመሰለው ከሰማይ ሰማያዊ መሆኑን ለመግለጥ ነው። ይኽንንም፦ «ከሰማይም ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም ፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ (ወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስ) ነው።» በማለት ጌታችን ነግሮናል። ዮሐ ፫፥፲፫። እንግዲህ ለምጻሙ ሰው በወፉ ደም ተረጭቶ ከለምጹ ፈጽሞ እንደሚነጻ ፥ የአዳም ልጆችም በመስቀል ላይ በፈሰሰ በክርስቶስ ደም፦ ከኃጢአት ፈጽመን ነጽተናል፤» ያለው ለዚህ ነው። ፩ኛ ዮሐ ፩፥፯። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም፦ «ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከማይረባና ከማይጠቅም ሥራችሁ የተቤዣችሁ በሚጠፋ በወርቅ ወይም በብር እንዳይደለ ታውቃላችሁ። ነውርና እድፍ እንደሌለው በግ በክርስቶስ ክቡር ደም ነው እንጂ፤» ብሏል። ፩ኛ ጴጥ ፩፥፲፰። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ፦ «እግዚአብሔር በገዛ ደሙ የዋጃትን ቤተ ክርስቲያንን ጠብቁ፤» ብሏል። የሐዋ ፳፥፳፰።
          እግዚአብሔር ባሕርያችንን ነሥቶ ሰው ሆነ ፥ እኛን መሰለን ፥ የሥጋ ዘመድ ሆነን ፥ የምንለው የባሕርያችን መመኪያ በሆነች እመቤት ፥ በቅድስት ድንግል ማርያም ተመክተን ነው። እርሷን ምክንያተ ድኂን አድርጎ በደሙ ፈሳሽነት ስላዳነን እንመካባታለን ፥ ለድኅነተ ዓለም፦ በመልዕልተ መስቀል የተቆረሰ ሥጋ ፥ የፈሰሰ ደም ፥ አሳልፎ የሰጣት ነፍስ ፥ የባሕርያችን መመኪያ ከሆነች ከእርሷ የነሣው ነውና። ለዚህም ነው፥ የጌታን አዳኝነት ስንናገር እመቤታችንን መተው የማንችለው፤ ለሚያስተውል ሰው ነገረ ማርያም ነገረ ክርስቶስ ነውና።      


Source: http://www.facebook.com/groups/180759695294706/doc/183920784978597/

ነገረ ማርያም ክፍል፦ ፱

መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው




፲፦ ቃል ሥጋ የሆነው በተዋሕዶ ነው፤

ካለፈው የቀጠለ፦

            አካላዊ ቃል እግዚአብሔር ሰው የሆነው በተዋሕዶ ነው። ተዋሕዶውም እንደ ነፍስና እንደ ሥጋ ተዋሕዶ ነው። ነፍስ ረቂቅ ናት ፥ ሥጋ ደግሞ ግዙፍ ነው፤ ነፍስ ረቂቅነቷን ሳትለቅ ፥ ሥጋም ግዝፈቱን ሳይተው በተዋሕዶ ጸንተው ይኖራሉ። በመሆኑም አንድ ሰው እንጂ ሁለት አይባሉም።
          ቅዱስ ቄርሎስ፦ የተዋሕዶን ነገር በብረትና በእሳት እየመሰለ አስተምሯል። «በእግዚአብሔር ቃል፦ በረቂቅ ባሕርይ የሆነውን ተዋሕዶ አንካድ ፤ ብረት ከእሳት በተዋሐደ ጊዜ፦ ከእሳትም በመዋሐዱ የእሳትን ባሕርይ ገንዘብ ያደርጋል፤ (ማቃጣል መፋጀት ይጀምራል)፤ ብረት በመዶሻ በሚመታበት ጊዜ፦ ከእሳቱ ጋር በአንድነት(በተዋሕዶ) ይመታል፤ ነገር ግን ከመዶሻው የተነሣ የእሳት ባሕርይ በምንም በምን አይጐዳም፤ ሰው የሆነ አምላክ ቃልም በመለኮቱ ሕማም ሳይኖርበት፦ በሥጋ እንደታመመ እናስተውል፤» ብሏል። (ሃይ ፡ አበው ፸፫ ፥፲፪)።
          ቅዱስ አትናቴዎስ፦ የተዋሕዶን ምሥጢር ሲያስረዳ፦ «አሁንም በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ እንደሆነ ሰምተህ ዕወቅ፤ አምላክ ብቻ ከሆነማ እንደምን በታመመ ነበር? ወይስ እንደምን በሰቀሉት ነበር? ወይስ እንደምን በሞተ ነበር? ይህ ሥራ፦ (ሕማምና ሞት) ከእግዚአብሔር የራቀ ነውና፤ ዘዳ ፴፪፥፵። ሰው ብቻ ከሆነ በታመመ በሞተ ጊዜ ሞትን እንደምን ድል ይነሣው ነበር? ይህ ከሰው ኃይል በላይ ነውና። ፩ኛ ቆሮ ፭ ፥፲፫ ፣ ዕብ ፭፥፩-፬።» ብሏል። ስለ እመቤታችን ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ሲናገር ደግሞ፦ «ድንግል ወንድ ሳታወቅ ሊዋሐደው በፈጠረው ሥጋ የፀነሰችውን ወለደች፤ ያለ ኃጢአት ያለ ምጥ ወለደችው፤ የአራስነት ግብር አላገኛትም፤ ያለ ድካም ያለ መታከት አሳደገችው፤ ያለ ድካም አጠባችው፤ ለሥጋ በሚገባ ሕግ ምን አበላዋለሁ? ምን አጠጣዋለሁ? ምን አለብሰዋለሁ? ሳትል አሳደገችው፤» ብሏል። (ሃይ ፡ አበው ፳፯ ፥፮ ፣ ፳፰፥፲፱)። በተጨማሪም፦ «ዳግመኛም በክህደታቸው አስበው፦ ማርያም የወለደችው፦ ገዥ ፥ ፈጣሪ እንዳይደለ የሚናገሩ የመናፍቃን ልጆች ፈጽመው ምላሽ ይጡ፤ እግዚአብሔር ቃል ሥጋን ካልተዋሐደ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜ እንደምን አማኑኤል ተባለ? ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከሥጋችን ሥጋ ፥ ከነፍሳችን ነፍስ ነሥቶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆነ ማለት ነው። ኢሳ ፯፥፲፬ ፣ ማቴ ፩፥፲፰-፳፭። እንኪያስ ቃል ሥጋን ካልተዋሐደ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ በእውነት ለዘለዓለሙ የከበረ አምላክ ከሁሉ በላይ የሚሆን እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ በሥጋ ታመመ ብሎ እንደምን ጻፈ? ሮሜ ፭፥፯-፲፪ ፣ ፱፥፩-፭፤» ብሏል። (ሃይ ፡ አበው ፴፭፥፲፱)።
          የቅዱስ ባስልዮስ ወንድም ቅዱስ ጎርጎርዮስ፦ «ትስብእትን ከመለኮት ልዩ ነው ፥ አትበሉ፤ ከተዋሕዶ በኋላ አይለይምና፥ አይቀላቀልምና፤ መለኮትን ከተዋሐደው ከትስብእት ልዩ ነው ፥ አትበሉ፤ በርሱ ያለውን ተዋሕዶውን እመኑ እንጂ፤» ብሏል። (ሃይ ፡ አበው ፴፭ ፥፲፱)። በተጨማሪም፦ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች የጻፈውን መልእክት በተርጐመበት አንቀጽ፦ «እግዚአብሔር አብን በመልክ የሚመስለው በባሕርይ የሚተካከለው ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የሆነበትን ሥራ በልቡናችሁ ዕወቁ፤ ሽቶ(ፈልጎ) ቀምቶ ከእግዚአብሔር ጋር የተካከለ አይደለም፤ ራሱን አዋርዶ ሰው ኹኖ የተገዥን ባሕርይ ተዋሕዶ ነው እንጂ። ፊል ፪፥፭-፰። ሥጋን ከመዋሐድ የበለጠ በእግዚአብሔር ዘንድ ምን ድህነት አለ? ነገር ግን እርሱ ነገሥታትን ፥ መኳንንትን ፥የሚገዛ ሲሆን፦ እኛን ወደ መምሰል በመጣ ጊዜ፥ የተገዥን ባሕርይ በተዋሐደ ጊዜ ፥ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ አላነሰም። ምድርን የፈጠረ እርሱን በትውልድ እንበልጣለን የሚሉ ሐና ቀያፋ ዘበቱበት፤ ፍጥረትን ሁሉ የሚገዛ እርሱ የሚያርፍበት ቦታ አላገኘም፤ በሥጋ በተወለደ ጊዜ ላሞች በሚያድሩበት በረት አስተኙት እንጂ። መዝ ፳፫፥፩፤፺፪፥፩፤፺፭፥፲፫፤ ማቴ ፰፥፳፣ ሉቃ ፪፥፩-፯። የማይለወጥ ንጹሕ ቃል የሚለወጥ የሰውን ባሕርይ ተዋሐደ፤» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፴፭፥፳፱-፴፫)።
          ቅዱስ አብሊድስ፦ «ዳግመኛም ቃልን ከሥጋ አዋሕደን እንሰግድለታለን፤ . . . ፍጡር ሥጋን ፈጣሪ እንደተዋሐደው እናምናለን፤ ፈጣሪ ከፍጡር በተዋሐደ ጊዜ ፦ አንድ አካል በመሆን የጸና አንድ ባሕርይ ሆነ፤ ሁለት አካል ሁለት ባሕርይ አይደለም፤ የመለኮትንና የትስብእትን ተዋሕዶ እናውቃለን፤ ባሕርያችን ሁለት (ነፍስና ሥጋ) ሲሆን አንድ ይሆናል፤ አንድ አካል አንድ ባሕርይ በመሆን ያድጋል፤ አንድ ሰውም ይባላል፤ ዘፍ ፩፥፳፮፣ ዕብ ፪፥፲፬።» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፴፱፥፳፩-፳፬) ። በተጨማሪም፦ «ከአብ ጋር አንድ ነው፥ እንዳልነው ሁሉ ሥጋን በመዋሐድ ከሰው ጋር አንድ ነው፥ እንላለን፤ መለኮትም ለሰው የሚገባ ስምን ገንዘብ ያደርጋል፤ ሥጋን በመዋሐድ ከእኛ ባሕርይ ጋር አንድ ስለሆነ ከእርሱም ጋር አንድ ስለአደረገው። ኢሳ ፱፥፮ ፣ ማቴ ፩፥፳፪ ፣ ፊል ፪፥፭። ከተዋሐደው ከሥጋ ባሕርይ ምንም አልተለወጠም፤ አንድ መሆንም ሰውን ወድዶ ስለ መዋሓዱ የመለኮት ባሕርይ እንዳልተለወጠ መጠን ፥ ከእርሱ ጋር አንድ ከሚሆን ከእግዚአብሔር ጋር ገንዘቡ የሚሆን መተካከል ያለበት ስም ነው። ማቴ ፳፰፥፲፱ ፣ ሉቃ ፩፥፴፪ ፣ ዮሐ ፩፥፩ ፤ ፲፥፴ ፣ ፩ኛ ቆሮ ፰፥፮፤» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፵፥፲፮)።
          ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ደግሞ፦ «በዘመኑ  ሁሉ የማይለያዩትን የአምላክነትን የሰውነትን ግብራት በተዋሕዶ አጸና፤ ክርስቶስ በመለኮቱ ያይደለ በሥጋ አንደታመመ ተናገረ፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንደተናገረ መለኮት ከትስብእት አልተለየም፤ መለኮትና ትስብእት አንድ ባሕርይ በመሆን ተዋሓዱ እንጂ። ፩ኛ ጴጥ ፫፥፲፰ ፣፬-፩። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ፦ መለኮትንና ትስብእትን አንድ አድርጎ እርሱን የክብር ባለቤትን ባልሰቀሉትም ነበር ብሎ ተናገረ፤ ፩ኛ ቆሮ ፪፥፰።» ብሏል።  (ሃይ፡ አበው ፶፯ ፥ ፴፮)።
          ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም፦ ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ዕብራውያን ሰዎች የጻፈውን መልእክት በተረጎመበት እንቀጽ፦ «የተዋሐደውን ሥጋ ከመላእክት ባሕርይ የነሣው አይደለም ፥ ከአብርሃም ባሕርይ ነሣው እንጂ። ዕብ ፪ ፥ ፲፯። ለዚህ ታላቅ ፍቅር አንክሮ ይገባል፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ ለሰው ወገን ለተደረገ ለማይመረመር ለዚህ ፍቅር አንክሮ ይገባል፤ ይህ ለመላእክት ያላደረገው ነው። የተደረገውን አስተውል፤ እግዚአብሔር ከእኛ ባሕርይ የተዋሐደው ተዋሕዶ ጥቂት ክብር አይምሰልህ፤ ይህንን ለመላእክት አላደረገውምና ፥ የመላእክት ባሕርይ አልተዋሐደችውምና ፥ የተዋሐደችው የእኛ ባሕርይ ናት እንጂ። ባሕርያችንን ተዋሕዷል እንጂ። ከባሕርያችን ከፍሎ ተዋሐደ ለምን አላለም? ወዳጁ እንደኮበለለ እስኪያገኘውም ድረስ እንደሄደና እንዳገኘው ሰው የእኛ ባሕርይ እንደዚህ ከእግዚአብሔር ተለይታ ነበርና፤ ከእርሱም ፈጽማ ርቃ ነበርና፤ ሥጋ በመሆን ገንዘብ እስኪያደርጋት ድረስ ፈጥኖ ፈለጋት ፤ እርሷም ተዋሐደችው፤ ይህንንም ተዋሕዶ እኛን በመውደድ እንዳደረገው የታወቀ ነው። መኃ ፫፥፬ ፣ ማቴ ፲፰፥፲፪ -፲፬፤» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፷፫፥፪-፭)። በተጨማሪም፦ «ተዋሕዶንም አስረዳለሁ፤ እግዚአብሔር ቃል በአካሉ ፍጹም የሚሆን ነፍስ ፣ ዕውቀት ያለው ሥጋን ከእኛ ባሕርይ ነሥቷልና፤ እርሱንም ተዋሕዷልና፤ ስለዚህም ነፍስን ሥጋን ተዋሕዶ ሰው የሆነ እግዚአብሔር ቃል አንድ አካል አንድ ባሕርይ እንደሆነ እንናገራለን፤» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፷፯፥፴)።
          እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፦ ጌታን፦ በድንግልና መውለዷ በራሱ ምሥጢረ ተዋሕዶን ያስተምረናል። ይኸውም፦ በመንፈስ ቅዱስ ግብር በድንግልና የጸነሰችውን አምላክ በድንግልና የወለደችው፦ መለኮት ከእርሷ የነሣውን ሥጋና ነፍስ በመዋሐዱ ነው። ምክንያቱም፦ በተዋሕዶ የመለኮት ገንዘብ ለሥጋ፥ የሥጋም ገንዘብ ለመለኮት ሆኗልና። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል፦ እመቤታችንን ባበሠራት ጊዜ፦ «ከአንቺ የሚወለደው የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል፤ (የእግዚአብሔር አብ ልጅ፦ እግዚአብሔር ወልድ ነው፥ ከሦሥቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ ነው) ፤ ማለቱም ለምሥጢረ ተዋሕዶ ምስክር ነው። ሉቃ ፩፥፴፭። ምክንያቱም መለኮት በማኅፀን ነፍስን እና ሥጋን ባይዋሐድ ኖሮ ከእመቤታችን የሚወለደው የእግዚአብሔር ልጅ፥ ከሦስቱ ቅዱስ(ከሥላሴ) አንዱ ቅዱስ ነው ፥ አይባልም ነበር።
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፦ በመዋዕለ ሥጋዌው ያደረጋቸው ተአምራትም ምሥጢረ ተዋሕዶን የሚያሳዩ ናቸው። ለምሳሌ፦ ሁለት ማየት የተሳናቸውን ሰዎች በእጆቹ በዳሰሳቸው ጊዜ፦ ተፈውሰዋል። ይህም ሊሆን የቻለው መለኮት በተዋሐዶ ከሥጋ ጋር ስለነበረ ነው። ማቴ ፱፥፳፯-፴፩። ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ፦ ዓይነ ስውር የነበረውንም ብላቴና በምራቁ  አፈሩን ለውሶ በዚያ ፈውሶታል። ምራቅ የሥጋ ነው፤ ነገር ግን መለኮት ሥጋን ስለተዋሐደው ፥ ከተዋሕዶ በፊት የሥጋ ብቻ የነበረ ምራቅ የብላቴናውን ዓይን አብርቶለታል። ዮሐ ፱፥፩-፲፪።
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ከሙታን ተለይቶ የተነሣው፦ መግነዝ ሳይፈታለት ፥ መቃብር ሳይከፈትለት ነው። ሥጋ በራሱ መቃብር ሳይከፈትለት መውጣት አይችልም ። መለኮት ግን የሚያግደው የለም። በመሆኑም፦ መለኮታዊ አካልና ባሕርይ ፥ ከሥጋ አካልና ባሕርይ ጋር ተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ በመሆኑ፦ ልዩነት ሳይኖር መቃብሩ እንደታተመ ከመቃብር ወጥቷል። ከትንሣኤው በኋላም በሩ ሳይከፈት ደቀመዛሙርቱ ወደነበሩበት ቤት ገብቷል። ደቀመዛሙርቱ፦ ይህ ምሥጢር ረቅቆባቸው፦ በእርሱ አምሳል ምትሐት የሚያዩ መስሏቸው ነበር። እርሱ ግን፦ « ምን ያስደነግጣችኋል? በልባችሁስ እንዲህ ያለ ሐሳብ ለምን ይነሣሣል? እጄንና እግሬን እዩ፤ ዳስሱኝም፤ እኔ እንደሆንሁም ዕወቁ፤ በእኔ እንደምታዩት ለምትሐት አጥንትና ሥጋ የለውምና፤» ብሎ ተዳሰሰላቸው። ይህ የዳሰሱት አካል ነው፥ መዝጊያው ሳይከፈት የገባው። ምክንያቱም መዝጊያና ግድግዳ የማያግደው መለኮት እንደ ነፍስና ሥጋ ተዋሕዶታልና። ማቴ ፳፰፥፩-፲ ፣ ሉቃ ፳፬፥፲፮ ፣ ዮሐ ፳፥፲፱።
          ጌታችን፦ በዝግ ቤት ለደቀመዛሙርቱ በተገለጠላቸው ጊዜ ቶማስ አልነበረም። የሆነውን ሁሉ በነገሩት ጊዜ፦ «የችንካሩን ምልክት በእጁ ካላየሁ ፥ ጣቴንም ወደተቸነከረበት ካልጨመርሁ ፥ እጄንም ወደጎኑ ካላገባሁ አላምንም፤ አላቸው። ከስምንት ቀን በኋላም በሩ እንደተዘጋ ፥ ቶማስ ባለበት ተገልጦላቸው፦ «ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ »አላቸው። ከዚህም በኋላ ቶማስን ፦ ጣትህን ወዲህ አምጣና እጆቼን እይ ፤ እጅህንም አምጣና ወደ ጎኔ አግባ፤ እመን እንጂ ተጠራጣሪ አትሁን፤» አለው። ቶማስም ፦ ከዳሰሰ በኋላ፦ «ጌታዬ አምላኬም» ብሎ መለሰ። የዳሰሰው አካል፦ እሳተ መለኮት የተዋሐደው በመሆኑ እጁን ፈጅቶታል። በመሆኑም ቢዳሰስለት፦ «ጌታዬ» ቢፈጀው፦ «አምላኬ» ብሏል። ዮሐ ፳፥፳፰።
          ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊም፦ አይታይ አይዳሰስ የነበር መለኮት የሚታይ የሚዳሰስ ሥጋን ተዋሕዶ በሰውነት ( ነፍስንም ጭምር በመዋሐድ) በመገለጡ፦ «ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያ የነበረውንና በጆሮአችን የሰማነውን ፥ በዓይኖቻችንም ያየነውን፥ የተመለከትነውንም ፥ እጆቻችንም የዳሰሱትን እንነግራችኋለን። ሕይወት ለእኛ ተገልጻለችና አየናት ፥ ምስክርም ሆንን፤ ለእናንተም ከአብ ዘንድ ያለችውንና ለእኛ የተገለጠችውን የዘለዓለምን ሕይወት እንነግራችኋለን፤» ብሏል። ፩ኛ ዮሐ ፩፥፩።
፲፩፦ አካልና ባሕርይ፤
          አካልና ባሕርይ አይነጣጠሉም፤ አካል ባለበት ባሕርይ አለ፤ ምክንያቱም የባሕርይ መገለጫው አካል ነውና። (ባሕርይ አካልን አስገኝቶ በአካል ላይ ይገለጣል)። ለምሳሌ፦ እሳት አካልም ባሕርይም አለው፤ አካሉ፦ በእንጨት በከሰል ላይ ይገለጣል ፥ ባሕርዩ ደግሞ፦ መፋጀት ማቃጠል ነው። በመሆኑም፦ የሚፋጀውን ወይም የሚያቃጥለውን የእሳት ባሕርይ፦ ከአካሉ መነጠል ወይም መለየት አይቻልም። ውኃም፦ እንዲሁ፦ አካልም ባሕርይም አለው። አካሉ፦ በማድጋ ተቀድቶ ፥ በቀላያት ተዘርግቶ ቦታ በመያዙ ይታወቃል፤ ባሕርዩ ደግሞ ርጥበት ነው፤ ይህንንም ርጡብ የሆነ የውኃ ባሕርይ ከውኃ አካል መለየት አይቻልም። አካሉ ባለበት ቦታ ሁሉ ባሕርዩ አለ።
፲፩፥፩፦ ሥጋዊ አካልና ባሕርይ፤
          ከራስ ጠጉር እስከ እግር ጥፍር ፥ በአጥንት፥ በጅማት ፥ በሥጋ ፥ በቁርበት ተያይዞና ተሸፍኖ ያለው በአንድነት አካል ይባላል። ፍጹም ገጽ ፥ ፍጹም መለክ ያለው ነው፤ ራሱን የቻለ ፥ ለራሱ የበቃ እኔ የሚል ፥ የባሕርይ የግብር እና የስም ባለቤት ነው። የሥጋ አካል፦ ግዙፍ ፥ ውሱን፥ የሚዳሰስና የሚጨበጥ ነው፤ የሥጋ ባሕርይ ደግሞ፦ መራብ ፥ መጠማት ፥ መድካም ፥ ማንቀላፋት ፥ መሞት ነው።
፲፩፥፪፦ መለኮታዊ አካል እና ባሕርይ፤
          መለኮታዊ አካል፦ ረቂቅ፥ የማይጨበጥ ፥ የማይዳሰስ፥ እሳታዊና ምሉዕ ነው።
-       «ዙፋኖችም እስኪዘረጉ ድረስ አየሁ፤ በዘመናት የሸመገለውም ተቀመጠ፤ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ፥ የራሱም ጠጉር እንደ ነጭ ሱፍ ነበረ፤ ዙፋኑም የእሳት ነበልባል ነበረ፤» ዳን ፯፥፱።
-       «ራሱ ምዝምዝ ወርቅ ነው ፥ ቈንዳላው የተዝረፈረፈ ነው፤» መኃ ፭፥፲፩።
-       «የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃኑ ፥ ጆሮቹም ወደ ልመናቸው ናቸውና፤» መዝ ፴፫፥፲፭።
-       «ቅንድቦቹም የሰው ልጆችን ይመረምራል፤» መዝ ፲፥፬።
-       «እጆችህ ሠሩኝ አበጃጁኝም፤» መዝ ፻፲፰፥፸፫።
-       «እግዚአብሔር የኖኅን የመሥዋዕቱን መዓዛ አሸተተ፤» ዘፍ ፰፥፳፩።
-       «ንስር ጫጩቶቹን በክንፎቹ በታች እንደሚሰበስብ ፥ በጎኑም እንደሚያቅፍ፥ በክንፎቹ አዘላቸው፤ በደረቱም ተሸከማቸው።» ዘዳ ፴፪፥፲፩።
-       «ወገቡን በጽድቅ ይታጠቃል፤ እውነትንም በጎኑ ይጎናጸፋል።» ኢሳ ፲፩፥፭።
-       «የጌታችን እግሮቹ በሚቆሙበት ቦታ  እንሰግዳለን፤» ፻፴፩፥፯።
-       «ሰማይ የእግዚአብሔር መቀመጫ ነውና፤» ማቴ ፭፥፴፫።
-       «እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናግሮአልና ፥ ሰማይ ስማ ፤ ምድርም አድምጪ፤» ኢሳ ፩፥፪ ።
-       «በእግዚአብሔር ቃል ሰማያት ጸኑ፥ ሠራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ፤» መዝ ፴፪፥፮።
          መለኮታዊ ባሕርይ ደግሞ፦ ጥንት የሌለው ቀዳማዊ ፥ እስከ የሌለው ዘለዓለማዊ ነው። ፊተኛውና ኋለኛ፥ መጀመሪያና መጨረሻ ፥ እርሱ ነው ፤ ፈጣሪ ፥ ሁሉን ቻይ ነው፤ የሚሳነው ነገር የለም፤ ሕያው ነው፤ ምሉዕ በኲለሄ ነው፤ የማይለወጥ ፥ የማይታመም ፥ የማይራብ ፥ የማይጠማ ፥ የማይደክም ፥ የማይሞት ነው።
-       «አልፋና ዖሜጋ ፥ ቀዳማዊና ደኃራዊ ፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ ፤» ራእ ፥፳፪፥፲፫።
-       «አትፍራ ፥ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ ፤ ሞቼም ነበረሁ፤ እነሆም፥ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ሕያው ነኝ፤» ራእ ፩፥፲፯።
-       «ሁሉ በእርሱ ሆነ፤ ከሆነውም ሁሉ ያለ እርሱ ምንም የለም፤» ዮሐ ፩፥፫።
-       «ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና፤ » ሉቃ ፩፥፴፯።
-       «እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም፤» ሚል ፫፥፮።
-       «አቤቱ ፥ በሰማይና በምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነውና፤ ታላቅነትና ኃይል ፥ ክብርም ፥ ድልና ጽንዕ የአንተ ነው፤. . አቤቱ ፥ አንተም ሁሉን ትገዛለህ፤ የሥልጣን ሁሉ ጌታ ነህ፤ ኃይልና ብርታት በእጅህ ነው፤ ኃያል ነህ፤» ፩ኛ ዜና ፳፱፥፲፩።
-       «ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ ፥ አንተ በዚያ አለህ፤ ወደ ጥልቁም ብወርድ ፥ አንተ በዚያ አለህ፤» መዝ ፻፴፰፥፯።
-       «ከዘላለም እስከ ዘለዓለም ድረስ መቼም መች አንተ ነህ» መዝ ፹፱፥፪።
፲፪፦ አንድ አካል ፥ አንድ ባሕርይ፤
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ በተዋሕዶ ከሁለት አካል፦ አንድ አካል ፥ ከሁለት ባሕርይ፦ አንድ ባሕርይ ሆኗል። ይህም ማለት፦ የሥጋ አካል እና የመለኮት አካል ተዋሕደው አንድ ሲሆኑ ፥ የሥጋ ባሕርይና የመለኮት ባሕርይም ተዋሕደው አንድ ሆነዋል። በመሆኑም ኢየሱስ ክርስቶስ በተዋሕዶ አንድ አካል እና አንድ ባሕርይ ነው። ከተዋሕዶ በኋላ ሁለትነት የለም።
          ቅዱስ አቡሊዲስ ወደ ቅዱስ ዲዮናስዮስ በላከው መልእክቱ፦ «ወንጌላዊ ዮሐንስም ቃል ሥጋ እንደሆነ በተናገረ ጊዜ፦ አንድ ገዥ ነው አለ፤ ዮሐ ፩፥፲፬፣፩ኛ ቆሮ ፰፥፮። ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው ፥ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው አንድ ወልድ ተብሎ ከተጠራ ፥ ሁሉ የተፈጠረበት እርሱ አንደ አካል አንድ ባሕርይ ነው፤ ወደ ሁለትነት መከፈል የለበትም። ለሥጋውም ከመለኮቱ ወደ አንድ ወገን የተለየ ባሕርይ የለውም። ሰው፦ አንድ አካል አንድ ባሕርይ እንደሆነ ሁሉ፥ ሰው የሆነ የባሕርይ ገዥ ክርስቶስም፦ እንዲሁ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው እንጂ፤ ፊል ፪፥፭-፰። አንዱን ክርስቶስ አንድ እንደሆነ ካላወቁትስ፦ እነሆ ፥ ዳግመኛ አንዱን ሰው ወደ ብዙ ወገን ሊከፋፍሉት ይገባቸዋል፤ ብዙ ባሕርያትም እንዳሉት ሊናገሩ ይገባል። ምክንያቱም ከብዙ ወገን የተጠራቀመ ነውና፤ ከአጥንት ፥ ከጅማት ፥ ከአሥራው ፥ ከሥጋ ፥ ከቁርበት፥ከጥፍር ፥ ከጠጉር ፥ ከደም ፥ከነፍስ የተጠራቀመ ነውና፤ እነዚህም ሁሉ እርስ በርሳቸው ልዩ ልዩ ናቸው። ነገር ግን በእውነት አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው፤ እንዲሁም መለኮት ከትብስእት አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው፤ ወደ ሁለት አካል ፥ ወደ ሁለት ባሕርይ አይከፈልም። ዮሐ ፫፥፲፫ ፣ ሉቃ ፩፥፴፪። . . . ያለዚያ ከሰማይ የወረደ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል እንጂ የሰው ልጅ አይባልም፤ ከድንግል ማርያም የተወለደውም የሰው ልጅ ይባላል እንጂ የእግዚአብሔር ልጅ አይባልም። . . . ለእኛ ግን ከሰማይ በወረደ ፥ ከድንግል በተወለደ፥ በአንድ እግዚአብሔር እናምን ዘንድ ፥ እግዚአብሔር ያጻፋቸው መጻሕፍት ያስተምሩናል። ፩ኛ ቆሮ ፰፥፮ ፣ ገላ ፬፥፬ ፣ ዮሐ ፭፥፳፯ ፣ ሉቃ ፩፥፴፪። . . . ሁለት ባሕርይ ብለው የሚያምኑ ለአንዱ እንዲሰግዱ ፥ ለአንዱ እንዳይሰግዱ፤ በመለኮት ባሕርይ እንዲጠመቁ ፥ በሥጋ ባሕርይ እንዳይጠመቁ ግድ ይሆንባቸዋል። እምነታችን በጌታችን ሞት እንደምንከብር ከሆነ፦ የሚታመም ትስብእትና የማይታመም መለኮት አንድ ባሕርይ ይሆናል። መክበራችን እንዲህ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ በጌታችን ሞትም ፍጹማን እንሆናለን፤» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፴፱፥፮-፲፯)።
          ከዚህም በተጨማሪ፦ «እንዲሁም ከእግዚአብሔር አብ ጋር በአምላክነት ክብር አንድ ነው እንላለን፤ ሥጋም ይህን አንድ ስምን (ክርስቶስን) ገንዘብ ያደርጋል፤ እግዚአብሔር አብን፦ በመልክ ከሚመስለው ፥ በባሕርይ ከሚተካከለው ከቃል ጋር አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነውና። ዮሐ ፩፥፲፬ ፣ ፲፰፤ ከአብ ጋር አንድ ነው፥ እንዳልነው፦ ሥጋን በመዋሐድ ከሰው ጋር አንድ ነው፥ እንላለን፤ መለኮትም ለሰው የሚገባ ስምን ገንዘብ ያደርጋል፤ ሥጋን በመዋሐድ ከእኛ ባሕርይ ጋር አንድ ስለሆነ ከእርሱም ጋር አንድ ስለአደረገው፤» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፵፥፲፭-፲፮)። ቅዱስ ኤራቅሊስም፦ «እግዚአብሔር ያለመለወጥ እንደምን ሰው እንደሆነ ፥ቃል ከፈጠረው ሥጋ ጋር ያለ መቀላቀል እንደምን አንድ አካል አንድ ባሕርይ እንደ ሆነ ፥ እግዚአብሔር የሥጋን ባሕርይ፦ ያለዘር፥ ያለሩካቤ ፥ እንደምን እንደተዋሐደ መላልሰህ በልቡናህ ብትመርምር፦ ይህ ድንቅ ምሥጢር የጎላ የተረዳ ሆኖ ታገኘዋለህ፤» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፵፱፥፳፭)።

          የአንጾኪያው ሊቀ ጳጳሳት የከበረ ሰማዕት አግናጥዮስም፦ ጌታ በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ የመሆኑን ነገር ሲናገር፦ «ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእውነት ተወለደ፤ በእውነት አደገ ፥ በእውነት በላ ፥ ጠጣ ፥ በእውነት ተሰቀለ፥ በእውነት ታመመ ፥ ሞተ ፥ ተቀበረ ፥ ከሙታንም ተለይቶ ተነሣ። አመክ. ፮፥፲፪፣ ማቴ ፩፥፲፰-፳፭ ፣፲፩፥፲፪-፳ ፣ ሉቃ ፪፥፵-፶፪፣፩ኛ ቆሮ ፲፭፥፫። ይህንን እንዲህ ያመነ ብፁዕ ነው፤ ይህንን የካደ ግን እኛ ተስፋ ከምናደርጋት ከተመሰገነች ሕይወት የተለየ ነው። ፩ኛ ዮሐ ፪፥፳፭። ወልድ ዋሕድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚከፍሉት፣ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ከሆነ በኋላ፦ ሁሉት አካል ሁለት ባሕርይ የሚያደርጉት፦ ስለ መልካም ሥራ አንወግርህም፥ ስለ ስድብ ፥ አንተም ሰው ስትሆን ራስህን አምላክ ስለማድረግህ ነው እንጂ ብለው በአመፃቸው ከሚናገሩ  አምላክን ከሰቀሉ ከአይሁድ ጋር ይቆጠራሉ። ዮሐ ፲፥፴፪ ፣ ፩ኛ ቆሮ ፰፥፮። በወልደ እግዚአብሔር፦ ድካም ሕፀፅ አለበት የሚሉ፥ ሁለት አካል ሁለት ባሕርይ የሚያደርጉትም ዕድል ፈንታቸው ከከሐድያን አይሁድ ጋር የተካከለ ነው።» ብሏል። ዮሐ ፫፥፴፮፣ (ሃይ፡ አበው ፲፪፥፪-፭)።


          ኢየሱስ ክርስቶስን ሁለት አካል ማለት ሦስት የሆኑትን የሥላሴ አካላት አራት ማድረግ ነው። ሁለት ባሕርይ ማለትም አንድ የሆነውን የሥላሴ ባሕርይ ሁለት ማድረግ ነው። ይኽንን በተመለከተ፦ ሐዋርያዊ (እንደ ሐዋርያት የሆነ) ቅዱስ አትናቴዎስ፦ የሃይማኖትን ነገር በተናገረበት ድርሳኑ፦ «ሰው ሆነ ፥ ስለ ማለት ፈንታም ራሳቸውን ለመጉዳት ልበ ወለድን ነገር ፈጥረው፦ እግዚአብሔር በሰው አደረ አሉ፤ መለኮትና ትስብእት እርስ በርሳቸው ተዋሐዱ ስለ ማለት ፈንታ ሰው ሠራሽን ነገር ፈጥረው ተናገሩ፤ የጌታችን የኢየሱስ አካል አንድ ነው ፥ ስለ ማለት ፈንታ ሁለት አካል፣ ሁለት ባሕርያት፣ሁለት ገጽ ብለው አመኑ፤ በሦስት አካለት ስለማመን ፈንታም ሊያምኑበት ሊያስተምሩት በማይገባ ሥራ አራት ብለው አመኑ፤» ብሏል። (ሃይ፡አበው ፳፭፥፳)።

          ቅዱስ ባስልዮስ ደግሞ፦ «ይህን አንድ ወልድን፦ ሁለት አካል ሁለት ባሕርይ አንለውም፤ መለኮት ፥ በገንዘቡ አካል ፥ በገንዘቡ ባሕርይ ፣ ትስብእትም፦ በገንዘቡ አካል ፥ በገንዘቡ ባሕርይ ልዩ እንደሆኑ አንናገርም፤ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው ፥ እንላለን እንጂ። ፩ኛ ቆሮ ፰፥፮ ፣ ፪ኛ ቆሮ ፭፥፲፬። ቅዱስ ጴጥሮስም ሁለት አካል ሁለት ባሕርይ ብሎ አልተናገረም፤ አንድ አካል አንድ ባሕርይ መሆኑን አምኖ ክርስቶስ ስለ እኛ በሥጋ ታመመ አለ እንጂ። ፩ኛ ጴጥ ፪፥፳፩።» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፴፪፥፲፱)። ቅዱስ ቴዎዶጦስም፦ «ክርስቶስን የሚለየው ማነው? የአንዱን ስም ምሥጢርስ የሚከፍል ማነው? አንዱን ስም ሁለት ሲሉት ቢገኙ ጥቅሙ ምንድር ነው? አምላክ ሰው ካልሆነ፦ ተራበ ፥ ተጠማ እንዴት ተባለ? ትስብእትን ከእግዚአብሔር ቃል የሚለዩ ፥ በባሕርይ ስም አንድ የሆነውንም የሚከፍሉ ፥ አንዱ ክርስቶስ ሁለት እንደሆነ የሚናገሩ ፥ በነገርም ብቻ አንድ ነው የሚሉ እነዚያ እስኪ ይንገሩን። ፩ኛ ቆሮ ፲፪፥፫፤» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፶፫፥፴፫)።
          በዚሁ መጽሐፍ በቃለ ግዝት ላይ፦ «አንዱ ከእግዚአብሔር አብ ፥ አንዱ ከድንግል ማርያም ብሎ ሁለት ወልድ የሚል፦ ከእግዚአብሔር የተወለደው ከድንግልም የተወለደው አንድ አይደለም የሚል ቢኖር እግዚአብሔር ለወዳጆቹ ከነገራቸው ልጅነት ይለይ። እኛ ክርስቶሳውያን ግን በተዋሕዶ ሰው የኾነው አምላክ በእውነት ባሕርዩ አንድ ነው፤ አካሉ አንድ ነው፤ ገጹ አንድ ነው፤ ነፍስም ሥጋም አለው ልንል ይገባናል፤ ሁለት ባሕርያት ፥ ሁለት አካላት ፥ ነፍስና ሥጋም ያለው ስለሆነም፦ አንዱ ሰው ሁለት ነዋ? ለእኛስ ከዚህ ትምህርት አንድነት የለንም፤ በጎላ በተረዳ ልትናገሩት የሚገባውስ ይህ ነው፤ ከድንግል ማርያም ነፍስን ሥጋን ነሥቶ ሰው የሆነ የእግዚአብሔር አብ ልጅ መድኃኒታችን ክርስቶስ አንድ ነው ፥ ማለት ነው። ይህም በማይነገር በማይመረመር ድንቅ በሚሆን ተዋሕዶ ተደረገ፤ የማይታየው እርሱ ከሚታየው ጋር ፥ ዘመን የማይቆጠርለት ዘመን ከሚቆጠርለት ጋር፥ አንድ የኾነው አንዱ ነው፤ ሁለት አይደለም፤ ሳይለወጥ ሰው የኾነ እግዚአብሔር ቃል አንድ ባሕርይ ፥ አንድ አካል ፥ አንድ ገጽ ነው እንጂ፤» ይላል። (ሃይ፡ አበው ፻፳፥፯)

Source: http://www.facebook.com/groups/180759695294706/doc/183920548311954/