13

.

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው::" የማቴዎስ ወንጌል 7: 4

"እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅናወተት ግዙ።" ትንቢተ ኢሳይያስ 55 : 1

Monday, September 19, 2011

ነገረ ማርያም ክፍል 3 - 4

መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው




«ዳግመኛ በሰማይ ሌላ ምልክት ታየ፤»



«ወአስተርአየ ካልእ ተአምር በውስተ ሰማይ፤» ቅዱስ ዮሐንስ የመጀመሪያውን ምልክት ፦ ታላቅ ፥ ገናና ፥ ደገኛ ካለ በኋላ የሁለተኛውን ግን ቀለል አድርጐ « ሌላ ምልክት በሰማይ ታየ ፤» ብሏል።

፯ ፥ ፩ ታላቅ ቀይ ዘንዶ፤
ይኸውም፦ « አርዌ ዐቢይ ወቀይሕ ፤» እንዲል፦ እሳት የሚመስል ቀይ ዘንዶ ነው። ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶችም ነበሩት፤ በራሶቹም ላይ ሰባት ዘውዶች ነበሩት። ዘንዶ (እባብ) የተባለውም ፦ የቀደመ ሰው አዳምን፦ እግዚአብሔርን ያህል አባት ፥ ገነትን ያህል ርስት ያሳጣው ጥንተ ጠላታችን ዲያቢሎስ ነው። ምክንያቱም በሥጋ ከይሲ ተሰውሮ አዳምንም ሔዋንንም አስቷቸዋልና። « እባብም እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠራቸው ከምድር አራዊት ሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነበር ፤ » ይላልና። ዘፍ ፫ ፥፩። እሳት የሚመስል ቀይ መባሉም ተፈጥሮው ልክ እንደ ሌሎቹ መላእክት ከእሳትና ከነፋስ በመሆኑ ነው። ይኽንንም ቅዱስ ዳዊት ፦ «መላእክቱን መንፈስ ፥ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል የሚያደርጋቸው።» በማለት ገልጦታል።መዝ ፩፻፫ ፥ ፬። ይህም እሳትና ነፋስ ኃያላን ፥ ረቂቃን እንደሆኑ ሁሉ መላእ ክትም፦ ኃያላን ፥ ረቂቃን ፥ ፈጣኖች ፥ ፈጻሚያነ መፍቅድ ናቸው ፥ ለማለት ነው።
፰ ፥ ሰባት ራሶች፤
ሰባት በዕብራዊያን ፍጹም ቁጥር ነው። ዲያቢሎስም ፍጹም ኃጢአትን ያሠራል። ሰባት ራሶች የተባሉትም ሰባቱ አርዕስተ ኃጣውእ (ዋና ዋና ኃጢአቶች ) ናቸው። እነዚህን ዋና የተባሉትን ፥ ከእግዚአብሔር አንድነት የሚለዩትን ፥ ከክብሩም የሚያርቁትን ኃጢአቶች በሰው አድሮ ያሠራው ሲያሠራም የሚኖረው እርሱ ነው።
፰፥፩፦ ኃጢአተ አዳም፤
«እባብም ለሴቲቱ ፦ ሞትን አትሞቱም ፤ ከእርሷ በበላችሁ ቀን ፥ ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ ፥ እንደ እግዚአብሔርም እንደምትሆኑ ፥ መልካምንና ክፉን እንደምታውቁ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ።» አላት። ዘፍ ፫፥፬። አዳምና ሔዋን በዚህ ምክር የሰባት ዓመት ንጽሕናቸውን አቆሸሹ ፥ ቅድስናቸውን አረከሱ፤ ከማዕረጋቸው ተዋረዱ ፥ ከሥልጣናቸው ተሻሩ ፥ ከገነት ተባረሩ። ዘፍ ፫ ፥ ፲፬።
፰፥፪ ፦ ቅትለተ አቤል፤
አዳም አቤልን «ይህ ብሩኅ ገጽ ያለው ልጄ መንግሥቴን የሚወርሰው እርሱ ነው፤» ይለው ነበር። ሁለተኛም ከቃየል ጋር መንታ ሆና የተወለደችውን መልከ መልካም አጋባው። ሦስተኛም አቤል ከበጐቹ በኲራት ፥ ቀንዱ ያልከረከረውን ፥ ጠጉሩ ያላረረውን ፥ጥፍሩ ያልዘረዘረውን ጠቦት መሥዋዕት እድርጐ ቢያቀርብ እግዚአብሔር ተቀበለው። በዚህ ሁሉ ምክንያት ቃየል ተበሳጨ። ልቡ አዘነ ፥ ፊቱ ጠቆረ። በዚህን ጊዜ ሰይጣን አዛኝ መስሎ ቀርቦ ነፍስ መግደልን ለቃየል አስተማረው። አንዱ ሰይጣን በሰው አምሳል ሁለተኛው ደግሞ በቊራ አምሳል ለቃየል ታዩት። በሰው አምሳል የታየው በቊራ አምሳል የታየውን በደንጊያ ሲገድለውም አየ። ከዚህ በኋላ ነው ወንድሙን አቤልን የገደለው። ዘፍ ፬፥፩-፰።
፰፥፫፦ ጥቅመ ሰናዖር ፤
የዓለም ሁሉ ቋንቋ አንድ ፥ ንግግሩም አንድ ነበር። ሰይጣን ልባቸውን አነሣሥቶት ጫፉ ሰማይ የሚደርስ ግንብ ለመሥራት በሰናዖር ሜዳ ተሰባሰቡ። ይኸውም ስለ ሁለት ነገር ነው። አንደኛው ፦ እንደ ኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ ቢመጣ ማምለጫ እንዲሆናቸው ነው። ሁለተኛው ደግሞ እግዚአብሔርን ለመውጋት ነው። በመጽሐፈ ኲፋሌ እንደ ተጻፈው አርባ ሦስት ዓመት ፈጅቶባቸዋል። ከዚህ በኋላ ፍላፃቸውን ወደ ላይ ቢወረውሩት በአየር ላይ ያሉ አጋንንት በምትሀት ደም እየቀቡ ይሰዱላቸው ነበር። አሁን ገና ባለቤቱን ወጋነው፥ ቀኝ አዝማቹን ፣ ግራ አዝማቹን ወጋነው ፥ አጋፋሪውን ወጋነው ይባባሉ ጀመር። ሥላሴ ፍጥረቱ ሁሉ በከንቱ ቢጐዳ አይወዱምና ለኃጢአት እንዳይግባቡ ሰባ ሁለት ቋንቋ አመጡባቸው። እነርሱም በምንም መግባባት ስላልቻሉ ትተውት ወረዱ። ግንቡንም ጣዖት አድርገው እንዳያመልኩት ሥላሴ ጽኑ ነፋስ አስነሥተው በትነውታል። በዚህም ምክንያት ባቢሎን ተብሎአል። ባቢሎን ማለት ዝርው (የተበተነ) ማለት ነው። አንድም ሕዝቡ በቋንቋ ፥ በነገር ተለያይተው በቦታ ስለተበተኑበት ባቢሎን ተብሏል። በዚህን ጊዜ ቋንቋ ከሦስት ተከፍሏል። ሠላሳ ሁለቱ በነገደ ካም ፥ ሃያ አምስቱ በነገደ ያፌት ፥ አሥራ አምስቱ በነገደ ሴም ቀርቷል።
፰፥፬ ፦ ኃጢአተ ሰዶም፤
የሰዶማውያን ኃጢአታቸው ወንድ ከወንድ ፥ ሴት ከሴት መጋባታቸው ነው። ይኽንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ፦ «ስለዚህም እግዚአብሔር ክፉ መቅሠፍትን አመጣባቸው ፤ ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባቸውን ትተው ለባሕርያቸው የማይገባውን ሠሩ። ወንዶችም እንዲሁ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን ትተው በፍትወት ተቃጠሉ፤ እርስ በራሳቸውም እየተመላለሱ ፥ ወንዶች በወንዶች ላይ የሚያዋርዳቸውን ነውር ሠሩ፤ ነገር ግን ፍጻሜአቸውን ያገኛሉ፤ ፍዳቸውን ያገኛሉ፤ ፍዳቸውም በራሳቸው ይመለሳል።» በማለት ገልጦታል። ሮሜ ፩፥፳፮። «የአምላክህንም ስም አታርክስ ፥ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ፤ ከሴትም ጋር እንደምትተኛ ከወንድ ጋር አትተኛ ፤ ጸያፍ ነገር ነውና።» የሚለውን አስቀድሞ በሕገ ልቡና የተሰጣቸውን ሕግ ተላለፉ። ዘሌ ፲፰፥፳፪። እግዚአብሔርም በሰዶምና በገሞራ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ከሰማይ እሳትና ዲን አዘነበ፤ እነዚያም ከተሞች በዙሪያቸው ያለውንም ሁሉ ፥ በከተሞችም የሚኖሩትን ሁሉ ፥ የምድርንም ቡቃያ ሁሉ ገለበጠ። አብርሃምም ወደ ሰዶምና ገሞራ ወደ አውራጃዎቿም ሁሉ ተመለከተ ፤ እነሆም፥ ነበልባል ከምድር እንደ ምድጃ ጢስ ሲወጣ አየ ይላል። ዘፍ ፲፱፥፳፫።
፰፥፭፦ ኃጢአተ እሥራኤል፤
የእሥራኤል ኃጢአት ከአምልኮተ እግዚአብሔር ወደ አምልኮተ ጣዖት ማፈግፈግ ነበር። እግዚአብሔር ከባርነት ቤት ካወጣቸው በኋላ በሲና ምድር በዳ የወርቅ ጥጃ ሠርተው በማምለክ አሳዝነውታል። ዘጸ ፴፪፥፬። ከሞአብ ልጆች ጋር ባመነዘሩም ጊዜ ብዔልፌጎር የተባለውን ጣዖት ተከትለው ነበር። ዘኁ ፳፭፥፩። ብዙ ጊዜ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ትተው በዙሪያቸው ያሉ አሕዛብን አማልክት በመከተል በመስገድም እግዚአብሔርን አስቆጥተውታል። እርሱም ለጠላቶቻቸው እያሳለፈ ይሰጣቸው ነበር። መሳ ፪፥፲፩ ፣ ፪ኛ ነገ ፲፯፥፯ ፣፳፩፥፲፩። በአጠቃላይ አነጋገር ጣዖትን ማምለክ የአጋንንት ማኅበርተኛ መሆን ነው። ፩ኛ ቆሮ ፲፥፳ ።
፰፥፮፦ ቅትለተ ዘካርያስ፤
ካህኑ ዘካርያስ ከሚስቱ ከኤልሳቤጥ ጋር በእግዚአብሔር ሥርዓትና በትእዛዙም ሁሉ ያለ ነውር የሚሄዱ ጻድቃን ነበሩ። ሉቃ ፩፥፮። ዘመን ከተላለፋቸው በኋላ በዕርግና ፥ በቅዱስ ገብርኤል ብሥራት መጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሐንስን ወለዱ። ሉቃ ፩፥፰ ፣ ፶፯። ጌታ በወንጌል እንደተናገረ ዘካርያስን በቤተ መቅደሱና በመሠዊያው መካከል እንዳለ ገድለውታል። ማቴ ፳፫፥፴፭። የዘካርያስም ደም ሰበዓ ዘመን ሙሉ ሲፈላ እንደ አቤል ደም ሲካሰስ ኖሯል። ታሪኩ እንዲህ ነው። ለአንድ ዓላዊ ፦ ሲፀነስ የአባቱን አንደበት የዘጋ ፥ ሲወለድ የከፈተ አንድ ሕፃን ከካህኑ ከዘካርያስ ቤት አለልህ አሉት። እርሱም ዘካርያስን አስጠርቶ ቢጠይቀው፦ «አዎን አለ፥ምነው ጠየቅኸኝ?» አለው። ዓላዊውም «ይኽንኑ እንድትነግረኝ ነው ፥ በል ሂድ ፤» ሲል መለሰለት። በዚህን ጊዜ ዘካርያስ «ይህ ዓላዊ ያለ ምክንያት አልጠየቀኝም ፤ ሀብት ሳላሳድርበት ልጄን ሊያስገድለው ነው።» ብሎ ከቤተ መቅደስ አግብቶ ሲጸልይለት ዓላዊው «ልጁን ግደሉ፤» ብሎ ጭፍራ ላከ። ከቤት ቢሄዱ አጡት። ወዲያው የእግዚአብሔር መልአክ ለኤልሳቤጥ ተገለጠላትና ፦ ይህ ዓላዊ ልጅሽን ሊያስገድልብሽ ነውና ፥ ወደ ገዳም (በረሀ) ይዘሽው ሂጂ ፤» አላት። እርሷም ልጁን ከዘካርያስ ተቀብላ የተባለችውን አድርጋለች። በመጨረሻም የተላኩት ጭፍሮች ወደ ቤተ መቅደስ ቢሄዱ ዘካርያስን አግኝተው ገድለውታል።
፰፥፯ ፦ ሞተ ወልደ እግዚአብሔር፤
በአይሁድ ልቡና አድሮ ፥ እንዳይሰሙ ፥እንዳይለሙ አዕምሮአቸውን አሳውሮ ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስን ያስገረፈ ያሰቀለ ሰይጣን ነው። ሥጋው አልቆ አጥንቱ እስኪቆጠር ድረስ ሰድስት ሺህ ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ጅራፍ ገርፈውታል። ራስ ራሱን በዘንግ ቀጥቅጠውታል። ይኽም አልበቃ ብሎ ልቡ ድረስ እስኪሰማው አክሊለ ሦክ ደፍተውበታል። እጆቹን የኋሊት አስረውታል። በጥፊ መትተውታል ፥ አክታቸውን ተፍተውበታል ( ከብርሃናዊ ፊቱ ላይ ለጥፈውበታል )። ከባድ መስቀል አሸክመውታል ፥ ከምድር ላይ አዳፍተውታል። ሳዶር ፥ አላዶር ፥ ዳናት ፥አዴራ ፥ ሮዳስ በተባሉ አምስት ቀኖት ቸንክረውታል። መራራ ሐሞት አጠጥተውታል ፥ ጐኑን በጦር ወግተውታል። በመጨረሻም «ተፈጸመ፤» በማለት በፈቃዱ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቷል። ዮሐ ፲፱ ፥፴።
፱፦ አሥር ቀንዶች፤
ቀንድ በምሳሌነት፦ ኃይልን ፥ ክብርን ፥ ሥልጣንን ፥ ንግሥናን ያመለክታል።
- «እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እስኪጠፉ ድረስ በእነዚህ ቀንዶች ሶርያውያንን ትወጋቸዋለህ።» ፩ኛ ነገ ፳፪፥፲፩።
- «ሐናም ጸለየች፤ እንዲህም አለች፦ ልቤ በእግዚአብሔር ጸና፤ ቀንዴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ከፍ ከፍ አለ።» ፩ኛ ሳሙ ፪፥፩
- «ለንጉሦቻችንም ኃይልን ይሰጣል፤ የመሲሑንም ቀንድ ከፍ ከፍ ያደርጋል።» ፩ኛ ሳሙ ፪፥፩።
- «በዚያ ለዳዊት ቀንድን አበቅላለሁ፤» መዝ ፩፻፴፩ ፥ ፲፯።
- «በዚያ ቀን ለእሥራኤል ቤት ቀንድን አበቅላለሁ፤» ሕዝ ፳፱፥፳፩።
እነዚህ ሁሉ ለፍጻሜው ለኢየሱስ ክርስቶስ የተነገሩ ናቸው። ይኽንንም ጻድቁ ካህን ዘካርያስ አድሮበት የሚኖር መንፈስ ቅዱስ ምሥጢሩን ፥ ጥበቡን ቢገልጥለት፦ «ይቅር ያለን ፥ ለወገኖቹም ድኅነትን ያደረገ የእሥራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን ፤ ከባርያው ከዳዊት ቤት የምንድንበትን ቀንድ አስነሣልን ፤ ከጥንት ጀምሮ በነበሩ በቅዱሳን ነቢያት አፍ እንደተናገረ። ከጠላቶቻችን እጅ ከሚጠሉንም ሁሉ እጅ ያድነን ዘንድ። ቸርነቱን ከአባቶቻችን ጋር ያደርግ ዘንድ ፥ ቅዱስ ኪዳኑንም ያስብ ዘንድ። ለአባታችን ለአብርሃም የማለውን መሓላ ያስብ ዘንድ።» በማለት ተናግሯል። ሉቃ ፩፥፷፯።
፱ ፥ ፩፦ የሳጥናኤል ውድቀት፤
ሰይጣን በክህደቱ አጥቶት እንጂ ክብርም ፥ ኃይልም ሥልጣንም ነበረው። በአሥሩ የመላእክት ከተሞች በተሾሙ አሥር የመላእክት አለቆች ላይ የአለቃ አለቃ ነበር። የተፈጠረው የመላእክት አለቃ ሆኖ ነው። ይኽንንም ቀሌምንጦስ ተናግሮታል። እግዚአብሔር መላእክትን በነገድ መቶ ፥ በከተማ አሥር አድርጐ ፈጥሮ ተሰወራቸው። ይህም ካልፈለጉኝ አልገኝም ፥ ባሕርዬም አይመረምርም ሲላቸው ነው። ወዲያው፦ «እኛ ምንድር ነን? ከየት መጣን ? ማንስ ፈጠረን? በራስ በራሳችን ተፈጠርን ? ወይስ ከሌላ ነው?» አሉ። ዲያቢሎስ ከበታቹ እንዲህ ሲሉ ሰማ። ከበላዩ ደግሞ «ፈጠርኳችሁ፤» የሚል አጣ። በቦታው ከሁሉ በላይ አድርጎ ፈጥሮት ነበርና «እኔ ፈጠርሁ፤» ብሎ አሰበ ፥ አስቦም አልቀረ «እኔ ፈጠርኋችሁ፤» አለ። ይኽን ሰምተው «ሰጊድ ይገባዋል፤» ያሉ አሉ። «እኛም እንደ እርሱ ነን፤» ያሉም አሉ። « አምላክ ነኝ ያለስ ከእርሱ በቀር ሌላ የለምና ፥ ይሆንን?» ብለው የተጠራጠሩ አሉ። ሀልዎተ እግዚአብሔርን ሳይመረምሩ የቀሩም አሉ። እኲሌቶቹ ግን ፦ «በምን ፈጠርኋችሁ ይለናል። በቦታ ከበላይ በመሆን ፈጠርኋችሁ እንዳይለን ፥ እኛ የበታቾቻችንን መቼ ፈጠርናቸውና ነው?። በዚያውስ ላይ ምቀኞቹ አይደለንም፤ በእውነት ፈጣሪ ከሆነ ፈጥሮ ያሳየን ።» ብለው፦ «ፈጥረህ አሳየን፤» አሉት። እርሱም እፈጥራለሁ ብሎ ፥ እጁን ወደ እሳት ቢጨምር ፈጀውና « ዋይ» አለ። በዚህን ጊዜ «በአፍአ ያለውን (የሚነገረውንና እና የሚሠራውን ብቻ የሚያውቅ) አምላክ ቢሆን ነው እንጂ ውሳጣዊውን (ልብ ያሰበውን የሚያውቅ) አምላክ ቢሆን ኖሮ ገና ሳስበው ለምን አሰብከው ፥ «ባለኝ ነበር ፤» አለ። ወዲያው ልቡን ተሰማውና «ዋይ» አለ። እግዚአብሔር ግን ፈወሰው። ይህንንም ማድረጉ ንስሐ ቢገባ እንደሚምረው ሲነግረው ነበር።
ከዚህ በኋላ በመላእክት ሽብር ቢጸናባቸው፦ መልአከ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል፦ «ንቁም በበህላዌነ እስከ ንረክቦ ለአምላክነ ፤ አምላካችንን እስክናገኘው ድረስ በየህልውናችን ጸንተን እንቁም ፤» በማለት አጽንቷቸዋል። ይህም በጎ አርበኛ ጦር በተፈታ ጊዜ «አይዞህ ባለህበት ጽና፤» ብሎ እንደሚያጸናው ማለት ነው።« ወበእንተዝ ደለዎ ይፁር ዜናሃ ለማርያም ፤ በዚህ ምክንያት የድንግል ማርያምን ዜና ያደርስ ፥ ብሥራቷን ይናገር ዘንድ ተገባው ፤ » እንዲል ፥ ብሥራት ተሰጥቶታል። «በስድስተኛው ወር (አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ፥ ስድስተኛው ሺህ ደግሞ ሲጀምር) መልአኩ ገብርኤል . . . ወደ አንዲት ድንግል ተላከ» ይላል። ሉቃ ፩፥፳፮።
እግዚአብሔርም ጨርሶ ሳያስታቸው ብሎ እርሱ (ሳጥናኤል) በሌለበት በኲል በምሥራቅ ባሕረ ብርሃንን አፍስሶላቸዋል። ከዚህም ጋር ስሙ የተጻፈበት መጽሔተ ብርሃን ቢሰጣቸው አንድነቱ ሦስትነቱ(ምሥጢረ ሥላሴ) ተገልጦላቸው « አሐዱ አብ ቅዱስ ፥ አሐዱ ወልድ ቅዱስ ፥ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ፤» ብለው አመስግነውታል። እርሱን ግን ባደረው ጨለማ ጠቅልሎ በዕለተ እሑድ ከኢየሩሳሌም ሰማያዊት ወደ ኢዮር አውርዶታል።ከሰባቱ ሰማያት ሦስቱ ፦ ኢዮር ፥ራማ፥ኤረር የመላእክት ናቸው። በውስጣቸውም አስር የመላእክት ከተሞች አሉ። በእነርሱም ላይ አስር አለቆች ተሹመዋል። እግዚአብሔር ሳጥናኤል በሌለበት በኲል ባሕረ ብርሃንን ያፈሰሰላቸው «እኔ ፈጠርኩ » እንዳይል ነው።
ሳጥናኤል በኢዮር ሆኖ በዕለተ ሠሉስ የተፈጠሩ ዕፅዋት፥ አዝርዕት ፥ አትክልት ፥ጽጌያትን አይቶ እንዳያደንቅ፦ «እንዲህ አድርጐ አከናውኖ የፈጠረለት ቢኖር ነው፥ » አለ። እግዚአብሐርም «ከወደድሃት በዚያ ላኑርህ ፤» ቢለው «ደገኛይቱን ማን ከልክሎኝ ፤» አለ። ከዚህ በኋላ ለሚካኤልና ለገብርኤል «እናንተ ኢየሩሳሌም ሰማያት ይሏችኋል ፥ ሰባቱ ሰማያት እንኳ አያህሏትም። እኛ ከጩኸት በቀር የተጠቀምነው የለም። ገዢ ነኝ የሚለውን ወግተን እጅ እናድርግ።» ብሎ ላከባቸው። እነርሱም የተላኩትን ከንጉሥ ከተማ እንደገባ ዕብድ ውሻ አድርገው ሰደዷቸው። ተመልሰውም አልተቀበሉንም ቢሉት ፦ «ቀለምጺጸ እሳት (የእሳት ፍንጣሪ) የሆኑ ሚካኤል ገብርኤል በእኔ ዘንድ ምን ቁም ነገር ናቸው። ይልቁንስ ኑ ተሸከሙኝና እንሂድ ፤» አላቸው። በዚህን ጊዜ በአርባዕቱ እንስሳ (በኪሩቤል) አምሳል አራት ሁነው ተሸክመውት ሽቅብ እወጣለሁ ቢል ኃይል ተነሥቶታል። ወደ ታች እንጂ ወደ ላይ መውጣት የማይቻለው በመሆኑም ፦ «ጐየ እግዚእ ምስለ አርያሙ፤ እግዚአብሔር ሰማዩን (ጽርሐ አርያምን) ጠቅልሎ ሸሸ፤» ብሎ ተመለሰ።
ቅዱሳን መላእክት ግን ፍጥረትን ሲፈጥር እያዩ ያመሰግኑ ነበር። በዕለተ ረቡዕ ፀሐይ ፥ ከዋክብት ፥ ጨረቃ ፥ ሲፈጠሩ አይተው አመስግነው አመስግን ቢሉት ፦ «አንሰ ዕድው (ውፁዕ) እምዝንቱ ኅሊና፤» እንዲል፦ «እኔ ከዚህ ውጪ ነኝ ፥ ባይሆን አራተኛ አድርጋችሁ ብታመሰግኑኝ እወዳለሁ፤» አላቸው። እነርሱም «ይህ ስሑት ፍጥረት እንዲህ እያለ እስከ መቼ ሲታበይ ይኖራል?» ብለው ሄደው ቢገጥሙት ድል አደረጋቸው። ሁለተኛም ቢገጥሙት ዳግመኛ ድል አደረጋቸው። በዚህን ጊዜ፦ «እኛስ ለአምላክነትህ ቀንተን ነበረ ፥ አንተ ግን ፈቃድህ ሳይሆን ቀረ፤» ብለው ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክቱ ፦ «ፈቃዳችሁ ፈቃዴ ነው ፥ ነገር ግን ድል የሚነሣበትን (የሚሸነፍበትን) ታውቁ ዘንድ ነው፤» ብሎ ስሙ የተጻፈበትን ትእምርተ መስቀል ሰጣቸው። ያን ይዘው በዕለተ ረቡዕ ወደዚህ ዓለም አውርደውታል። በዚህን ጊዜ የእርሱ ወገኖች ለሦስት ተከፍለዋል። ሀለዎተ እግዚአብሔርን ሳይመረምሩ የቀሩ በአየር ቀርተዋል። ይሆን ፥ አይሆን ብለው የተጠራጠሩ በዚህ ዓለም ቀርተዋል። « አምላክ ነው ፥ ሰጊድ ይገባዋል፤» ያሉ አብረው እንጦሮጦስ ወርደዋል።


«ዘንዶውም በወለደች ጊዜ ልጅዋን ሊበላ በዚያች ሴት ፊት አንጻር ቆመ፡፡» . . . . . .
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በመንፈስ ቅዱስ ግብር በድንግልና የፀነሰችውን አምላክ ፥ በድንግልና በወለደችው ጊዜ ፦ ሰብአ ሰገል ፦ ዜና ልደቱን በኮከብ ተረድተው ፥ በኮከብ ተመርተው ወደ ቤተልሔም መጥተው ነበር። ቤተልሔም ለመድረስ ሁለት ዓመት ፈጅቶባቸዋል። አመጣጣቸው፦ « የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት አለ? » እያሉ ነበር። ሠራዊቶቻቸውም ተከትለዋቸው ስለነበር ከተማይቱ ተሸበረች። ይህ ነገር ንጉሡ ሄሮድስን አስደነገ ጠው። በስውርም የካህናት አለቆችንና ጻፎችን አስጠርቶ ንጉሥ ክርስቶስ የተወለደው በቤተልሔም እንደሆነ አረጋገጠ። ሊቃውንቱን፦ ትንቢት ጠቅሰው ፥ ሱባዔ ቆጥረው እንዲያስረዱት በስውር የጠራቸው ፦ ሰብአ ሰገል፦ «እኛ እንኳን አውቀን ስንመጣ እርሱ የአገሩ ንጉሥ ሆኖ ሳለ እስከ አሁን አያውቅም?» ይሉኛል ብሎ ውዳሴ ከንቱን ሽቶ ነው።
ንጉሥ ሄሮድስ እንደገና ሰብአ ሰገልን በስውር ጠርቶ ኮከቡ የታየበትን ዘመን በጥንቃቄ ከእነርሱ ተረዳ። በልቡም፦ «ብላቴናው ለካ ሁለት ዓመት ሆኖታል፤» አለ። ሰብአ ሰገልንም «ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ መርምሩ ፥ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔ ደግሞ መጥቼ እንድሰግድለት ንገሩኝ ፤» ብሎ ወደ ቤተልሔም ሰደዳቸው። እንዲህም ማለቱ እውነት ሊሰግድለት ሳይሆን በልቡ ክፉ አስቦ ነው። ነገር ግን ፦ ልቡናንና ኲላሊትን የሚመረምር አምላክ የልቡን ሐሳብ ለመላእክት ገለጠላቸው። አንድም መላእክቱ የሰውን ልብ የማወቅ ጸጋው አስቀድሞ ተሰጥቷቸው ስለነበር ፥ በሄሮድስ በኲል እንዳይመለሱ፥ በሌላ ጐዳና እንዲጓዙ ለሰብአ ሰገል ነግረዋቸዋል። መንገዱም ቀንቶላቸው የሁለትን ዓመት በአርባ ቀን ገብተዋል።
በሄሮድስ ግን አስቀድሞ ክፉ ያሳሰበው ፥ ዘንዶ የተባለው ዲያብሎስ ሙሉ በሙሉ አደረበት። ዙፋኑ ፥ መሣሪያው አደረገው። ሰብአ ሰገል በሌላ ጐዳና ተመልሰው ወደ አገራቸው መግባታቸው ሄሮድስን ስላበሳጨው በቤተልሔምና በአውራጃዋ የሚገኙትን ሁለት ዓመትና ከዚያ በታች የሆኑ አሥራ አራት እልፍ ሕፃናትን አሳረደ። ይኸውም ከዚህ መካከል አይጠፋም ተብሎ በግምት ፥ በመላ ምት የሆነ ነው። በዚህም ፦ « ድምፅ በራማ ተሰማ ፥ ልቅሶና ብዙ ዋይታ ፤ ራሔል ስለ ልጆቿ አለቀሰች፤ መጽናናትም አልወደደችም ፥ የሉምና። » የተባለው ቃለ ኤርምያስ ነቢይ ተፈጸመ። ኤር ፴፩ ፥፲፭። ዘንዶው በፊቷ የቆመ እመቤታችን ግን መልአከ እግዚአብሔር እንደነገራቸው ሕፃኑን ይዛ ከጠባቂዋ ከጻድቁ ከዮሴፍ ጋር ወደ ምድረ ግብፅ ሸሸች። ይኸውም «ልጄን ከግብፅ ጠራሁት፤» የተባለው ቃለ ሆሴዕ ነቢይ እንዲፈጸም ነው። ማቴ ፪፥፩-፲፰ ፣ ሆሴ ፲፩፥፩። ልጅዋን ሊበላ የተባለውም ልጅዋን ሊገድል ማለት ነው።

የብረት በትር፤
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፦ አሕዛብን ሁሉ በብረት ዘንግ (በትር) የሚገዛቸውን ወንድ ልጅ (ወልደ አብን) ወለደችው። ቅድመ ዓለም ያለ እናት ከአብ ተወልዶ ወልደ አብ የተባለው ፥ ድኅረ ዓለም ከእመቤታችን ያለ አባት ተወልዶ ወልደ ማርያም ተባለ። ወልደ አብ ወልደ ማርያም በተዋሕዶ ከበረ። የብረት በትር የተባለው፦ ከባሕርይ አባቱ ከአብና ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ የሆነ ጽኑዕ ሥልጣኑ ነው። ቅዱስ ዳዊት ፦ «በትርህና ምረኲዝህ እነርሱ ያጸናኑኛል፤» ያለው ሥልጣኑን ነው። መዝ ፳፪፥፬። በትር ለበጐች መጠበቂያ ፥ ለተኲላት መቅጫ እንደሆነ ሁሉ ጽኑዕ የተባለ የእግዚአብሔር ሥልጣንም ለወገኖቹ መጠበቂያ ለአሕዛብ መቅጫ ነው። ወገኖቹ የተባሉትም ወደ ግብረ አሕዛብ በሚሳቡበት ጊዜ እነርሱንም ለትምህርት ይቀጣቸዋል። በተጨማሪም ፦ «ወትርዕዮሙ በበትረ ሐጺን ፥ ወከመ ንዋየ ለብሐ ትቀጠቅጦሙ። ደጋጐቹን በጽኑ ሥልጣን ትጠብቃቸዋለህ ፥ ክፉዎችን ግን እንደ ሸክላ ሠሪ ዕቃ ትቀጠቅጣቸዋለህ።» የሚል አለ። መዝ ፪፥፱። ሸክላ ሠሪ ፦ ሠርታ የጨረሰችውን ዕቃ ነቅዕ ያገኘችበት እንደሆነ ፥ ምን ብትደክምበት ፥ እንደገና ከስክሳ አፍርሳ ታድሰዋለች። እርሱም ከአራቱ ባህርያት የተፈጠረ ሰው በሥጋ ድካም ኃጢአት ቢሠራ (ነቅዕ ቢገኝበት) በንሰሐ ያድሰዋል። ቅዱስ ዮሐንስም ፦ « ወይወጽእ እምነ አፉሁ ሰይፈ በሊሕ ፥ ዘቦቱ ይቀሥፎሙ ለአሕዛብ። ወውእቱ ይርዕዮሙ በበትረ ኀጺን። አሕዛብን ይመታበት ዘንድ ፥ ከአፉ የተሳለ ሰይፍ ይወጣል፤ (አሕዛብን የሚያጠፋበት መቅሠፍት ከአፉ በሚወጣ ቃል ይታዘዛል) ፤ በጎ በጎዎቹን በተወደደ በጽኑዕ ሥልጣኑ ይጠብቃቸዋል።» በማለት ተመሳሳይ ነገር ተናግሯል። ራእ ፲፱፥፲፭።
ሥልጣን
ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክ ነው። ቅዱስ ዮሐንስ ፦ « የእግዚአብሔር ልጅ (ወልደ አብ) እንደመጣ (ከሰማይ ወርዶ ፥ ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ፥ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ በተዋሕዶ ሰው ሁኖ እንደተወለደ ) ፥ እውነተኛም የሆነውን እግዚአብሔርን (የባህርይ አባቱን አብን) እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደሰጠን እናውቃለን፤ እውነተኛም በሆነው በእግዚአብሔር ልጅ (በወልደ አብ) በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንኖራለን ፤ እርሱም እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው።» እንዳለ። ፩ኛ ዮሐ ፭፥፳። ቅዱስ ቶማስም ቢዳሰስለት «ጌታዬ» ቢፈጀው «አምላኬ» ብሎታል። ዮሐ ፳፥፳፰። በመሆኑም ኢየሱስ ክርስቶስ መለኰታዊ ባለሥልጣን ነው።
ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው ፦ (በተዋሕዶ ሰው በሆነበት ዘመን) ፦ በሥልጣን ያስተምራቸው ስለነበር ፥ ሕዝቡ በትምህርቱ ተደንቀዋል። ማቴ ፯፥፳፱። አጋንንትንም በሥልጣንና በኃይል ያዝዛቸው ከሰውም ልቡና ያስወጣቸው ነበር። ሉቃ ፬፥፴፮። በዚህ ሥልጣን ኃጢአትንም ያስተሰርይ ነበር። ማር ፪፥፲። «በሕይወትና በሞት ላይ ሥልጣን አለህና ፥ ወደ ሲኦል በሮች ታወርዳለህ ፥ ከሲኦልም ታወጣለህ ፤» እንዲል በሁሉ ላይ ባለሥልጣን ነው። ጥበብ ፲፮ ፥፲፬። እርሱም ራሱ «በሰማይና በምድር ሥልጣን አለኝ፤» ብሏል። ማቴ ፳፰፥፲፰። ስለ ሞቱና ስለ ትንሣኤውም ሲናገር ፦ « እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ (ነፍሴን በፈቃዴ ከሥጋዬ እለያታለሁ ) እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም። ላኖራት (ልለያት) ሥልጣን አለኝ ፥ ደግሞም ላነሣት (ነፍሴን ከሥጋዬ አዋህጄ ላስነሣት) ሥልጣን አለኝ፤» ብሏል። ዮሐ ፲፥፲፰። ይህ ሥልጣኑ፦ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ ነው። በሥላሴ በሥልጣን መበላለጥ ፥ በዘመን መቀዳደም የለምና። ይህም ይታወቅ ዘንድ፦ «እኔና አብ አንድ ነን፤» ብሏል። በመሆኑም እመቤታችን የዚህ ባለሥልጣን እናት ናት።

«ልጅዋም ወደ እግዚአብሔር ፥ ወደ ዙፋኑም ተወሰደ።»

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት እለት ወደ ሰማይ ያረገ አይደለም። ወደ ሰማይ ያረገው በዚህ ምድር ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ቆይቶ ፥ የማዳን ሥራውንም በመልዕልተ መሰቀል ከፈጸመ በኋላ ነው። ከሙታን ተለይቶ በተነሣ በአርባኛው ቀን በርቀት (በመርቀቅ ) ሳይሆን በርኅቀት (ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ እያለ በመራቅ) ዐርጓል። «እስከ ቢታንያም ወደ ውጭ አወጣቸው፤ እጁንም አንሥቶ በላያቸውም ጭኖ ባረካቸው። እየባረካቸውም ራቃቸው፤ ወደ ሰማይም ዐረገ።» ይላል። ሉቃ ፳፬፥፶። ደቀመዛሙርቱ ዓይኖቻቸው ከሰማዩ ላይ ተተክለው ፥ አንጋጠው የቀሩት ለዚህ ነበር። « ይህንም እየነገራቸው ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ተቀበለችው ፤ እነርሱም ወደ እርሱ እያዩ ወደ ሰማይ ዐረገ፤ ከዓይናቸውም ተሰወረ። » ቅዱሳን መላእክትም ነጫጭ ለብሰው በመገለጥ ፦ «እናንተ የገሊላ ሰዎች ሆይ ፥ ወደ ሰማይ እያያችሁ ለምን ቆማችኋል? » አሉአቸው። የሐዋ ፩፥፱። ቅዱስ ዳዊት ፦ እግዚአብሔር በእልልታ ፥ ጌታችንም በመለከት ድምጽ አረገ።» በማለት አስቀድሞ ትንቢት ተናግሮ ነበር። መዝ ፵፮ ፥፭።
ይህ እንዲህ ከሆነ ፥ ለምን ሕፃኑ ፥ «ወደ እግዚአብሔር፦ ወደ ዙፋኑም ተነጠቀ ፤ (ተወሰደ)፤» ተባለ እንል ይሆናል? አምላካችን ከሰማይ ወረደ ፥ ከድንግል ማርያም ተወለደ ፥ በምድር ላይ ተመላለሰ የምንለው ከሰማይ ዙፋኑ ሳይነቃነቅ ነው። ሥጋንና ነፍስን የተዋሐደው ፥ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት የተገለጠው ፥ ምሉዕ በኲለሄ የሆነ አምላክ ነው። አባ ሕርያቆስ ይህንን ምሥጢር ሲያብራራ « ከአባቱ አጠገብ ሳይለይ ቃል (አካላዊ ቃል ወልድ) ወደ አንቺ መጣ ፥ ሳይወሰን ፀነስሽው ፤ በላይ ሳይጐድል ፥በታችም ሳይጨምር በማኅፀንሽ ተወሰነ፤ » ብሏል። ቅዳሴ ማርያም ቁ ፵፮ ። ቅዱስ ዮሐንሰ አፈወርቅም፦ « ዳግመኛ የዋህድ አነዋወሩ እንደምን እንደሆነ ፥ መውረዱም እንዴት እንደሆነ ፥ መወለዱም እንዴት እንደሆነ እንናገራለን። ከአባቱ ሳይወጣ መጣ ፥ ከአነዋወሩ ሳይለይ ወረደ። ከሦስትነቱ ሳይለይ መጣ ፥ ከአንድነቱም ሳይለይ ወረደ። ከዙፋኑ ሳይለይ በድንግል ማኅፀን አደረ። ምላቱ ሳይወሰን በማኅፀን ተፀነሰ ፥ በላይ ሳይጐድል በማኅፀን ተወሰነ ፥ በታችም ሳይጨመር ተወለደ። » ብሏል። ቅዳሴ ዮሐ አፈ ቁ ፳፭። ጌታችን በተወለደ ዕለት ቅዱሳን መላእክት ወደ ሰማይ ቢወጡ እንደ ቀድሞው ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በአንድነት ቢያገኙት ፦ « ክብር ለእግዚአብሔር በሰማያት ፤» ብለው አመሰገኑት። ወደ ምድር ሲመለሱ ደግሞ በእመቤታችን እቅፍ ቢያገኙት ፦ « ሰላምም በምድር ፥ ለሰው ልጅም በጎ ፈቃድ ሆነ፤ » ብለዋል። ሉቃ ፪፥፲፬። እንግዲህ ፦ « ወደ እግዚአብሔር ፥ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ ፤» ማለት እንደ ሰውነቱ የተሰደደ አምላክ በሰማይ ዙፋኑ እንዳለ መናገር ነው። ከዙፋኑ ሳይለይ ተወለደ ፥ እንደተባለው ከዙፋኑ ሳይለይ ተሰደደ ተብሎ ይነገራል።

« እግዚአብሔር ወደ አዘጋጀላት ቦታ ወደ በረሃ ሸሸች፤»
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፦ በዘመኑ ሁሉ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ስድሳ ቀን በዚያ ትጠበቅ ዘንድ እግዚአብሔር ወደ አዘጋጀላት ቦታ ከዘንዶው (ከሄሮድስ) ፊት ወደ በረሃ ሸሸች። ይኸውም ወደ ምድረ ግብፅ ነው። በዚህም ፦ «እነሆ ፥ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ተቀምጦ ወደ ግብፅ ይመጣል፤ የግብፅም ጣዖታት በፊቱ ይርዳሉ ፥ የግብፅም ልብ በውስጥዋ ይቀልጣል።» የሚለው ቃለ ኢሳይያስ ነቢይ ተፈጽሟል። ኢሳ ፲፱፥፩። ፈጣን ደመና የተባለችው እመቤታችን ናት። ቅዱስ ዮሐንስ በቁጥር ወስኖ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ስድሳ ቀን ያለው አርባ ሁለቱን ወራት ማለትም በስደት የምታሳልፈውን ሦስት ዓመት ከመንፈቅ ነው። እግዚአብሔር ያዘጋጀላት ሥፍራ የተባለችውም ደብረ ቊስቋም ናት።

« ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉት፤»
እግዚአብሔር ዲያብሎስን ከኢየሩሳሌም ሰማያዊት ወደ መላእክት ሀገር ወደ ኢዮር ያወረደው ዕለቱን ወደ እንጦሮጦስ ማውረድ አቅቶት አይደለም። ለንሰሐ ጊዜ ሲሰጠው እንጂ። እርሱ ግን ባለፈው እንደተመለከትነው በአመጹ ገፋበት። በዚህም ምክንያት ፦በሰማይ ሰልፍ (ጦርነት) ሆነ፤ ቅዱስ ሚካኤልና ሠራዊቱ ዲያብሎስንና ሠራዊቱን ተዋጉት። እርሱም ሠራዊቱን አሰልፎ ተዋጋቸው። ነገር ግን፦ ስሙ የተጻፈበት ትእምርተ መሰቀል ተሰጥቷቸው ስለነበር አልቻላቸውም። ከዚህም በኋላ በሰማይ ቦታ አልተገኘላቸውም። ዓለሙን ሁሉ የሚያሰተው ዲያብሎሰና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀድሞው እባብ (በሥጋ ከይሲ ተሰውሮ አዳምንና ሔዋንን ያሳታቸው) ወደ ምድር ተጣለ፤ ሠራዊቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ። በሰማይም፦ «የአምላካችን ማዳንና ኃይል ፥ መንግሥትም ፥ የመሢሑም ሥልጣን ሆነች፤ አባቶቻችንን ፥ በእግዚአብሔር ፊት በቀንና በሌሊት ሲያጣላቸው የነበረው ከሳሽ ወድቋልና። እነርሱም ከበጉ ደም የተነሣ ፥ ከምስክራቸውም ቃል የተነሣ ድል ነሡት ፤ ሰውነታቸውን እስከ ሞት ድረስ አልወደዱምና። (በሰማዕትነት አልፈዋልና)። ስለዚህ ሰማያትና በውሰጣቸው የምትኖሩ (ሰማያውያን መላእክትና በሰማያዊ ግብር ጸንታችሁ የምትኖሩ ቅዱሳን) ሆይ ፥ ደስ ይበላችሁ ፤ ነገር ግን ለምድርና (ሳይጠመቁ በአሕዛብነት ለሚኖሩና) ለባሕር (ተጠምቀው ምግባር ለሌላቸው) ወዮላቸው ! ሰይጣን ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ ከክፉ መርዙ (ከጽኑዕ ማሳቱ) ጋር ወደ እናንተ ወረዷልና፤» የሚል ድምጽ ተሰማ። ይህ ከሰማይ የተሰማ ድምጽ፦ ጥንት በዓለመ መላእክት ፥ ስሙ የተጻፈበት የብርሃን መላእክት የተሰጣቸው ቅዱሳን ዲያብሎስን ድል መንሳታቸውን፦ በአዲስ ኪዳን ሥጋው በተቆረሰበት፥ ደሙ በፈሰሰበት የመስቀል ኃይል ዲያብሎስን ድል እያደረጉ ለሚኖሩ ቅዱሳን አርአያ ፥ ምሳሌ አድርጐ አቅርቧል። አንድም አነጻጽሮ ተናግሯል።

«ወንድ ልጅ የወለደችውን ያቺን ሴት አሳደዳት፤»
ዘንዶው ወደዚህ ዓለም እንደ ወረደ ፥ አንድም ፈጽሞ ድል እንደተነሣ (እንደተሸነፈ) ባወቀ ጊዜ፦ ወንድ ልጅ (ኃያል ወልድን) የወለደችውን ያቺን ሴት (ከሴቶች ሁሉ ተለይታ የተባረከችውን እመቤት) በሄሮድስ አድሮ አሳደዳት። ለሴቲቱም (ለድንግል ማርያም) ከዘንዶው ፊት ርቃ ፥ አንድ ዘመን (አንድ ዓመት) ፥ ዘመናትም (ሁለት ዓመት) ፥ የዘመንም እኲሌታ (መንፈቅ) ማለትም ሦስት ዓመት ከስድሰት ወር ወደምትጠበቅበት ወደ በረሃ (ወደ ግብፅ) እንድትበርር ፥ ሁለቱ የታላቁ ንስር ክንፎች (ንጽሐ ሥጋ እና ንጽሐ ነፍስ) ተሰጧት። ዘንዶውም እየበረረ (ለክፋት እየተፋጠነ) ተከተላት። ጎርፉ ይወስዳትም ዘንድ (ሠራዊቱ ይገድላት ዘንድ) ፥ ከአፉ እንደ ታላቅ ወንዝ ያለ ብዙ ውኃ በዚያች ሴት በስተኋላ አፈሰሰ። (እመቤታችን ስትሰደድ፦ ንጉሡ ሄሮድስ በአፉ ቃል የሚታዘዙ አያሌ ሠራዊት ከበስተኋላዋ ላከባት)። ምድሪቱም ሴቲቱን ረዳቻት፤ ምድሪቱ አፉዋን ከፍታ ዘንዶው ከአፉ ያፈሰሰውን ውኃ መጠጠችው። (የሄሮድስ ሠራዊት የበረሃው ሐሩር እንደ እሳት ወላፈን እየገረፋቸው ፥ የአሸዋው ግለት እንደ ከሰል ፍም እየፈጃቸው ሳይመለሱ በዚያው ቀርተዋል)። ዛፏ እንኳን ሳትቀር እንደ በር ተከፍታ በመዘጋት እመቤታችንን ሠውራታለች። ያቺ ዛፍ እስከዛሬ ድረስ በግብፅ ትገኛለች።
እመቤታችን በስደት ጊዜ ብዙ ተንገላታለች ፤ ተርባለች ፥ ተጠምታለች ፥ እንደ የኔቢጤም ለምናለች። ነገር ግን ሰይጣን ከፊት ለፊት እየቀደመ የሰውን ልብ ያጸናባቸው (ያስጨክንባቸው) ነበር። ይልቁንም ኰቲባ የተባለች የቤት ሠራተኛ እመቤታችንን ዘልፋታለች ፥ ልጇንም ከክንዶቿ ነጥቃ ከመሬት ጥላባታለች። ጻድቁ ዮሴፍም እመቤታችንን፦ « እንዳታ ነሺው ፥ ተአምራቱን ይግለጥ ፤ » ብሏታል። በዚህን ጊዜ ሰዎቹ ወደ አራዊትነት ተለውጠው የገዛ ውሾቻቸው አሳድደዋ ቸዋል። ይህም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ወደ አውሬነት ተለውጦ ለሰባት ዓመት ከዱር አራዊት ጋር እንደኖረው ማለት ነው። «ጠጉሩም እንደ አንበሳ ፥ ጥፍሩም እንደ ንስር እስኪረዝም ድረስ ከሰዎች ተለይቶ ተሰድዶ ፤ እንደ በሬም ሣር በላ፤ አካሉም በሰማይ ጠል ረሰረሰ።» ይላል። ዳን ፫ ፥፴፫።
ዳክርስና ጥጦስ የተባሉ ሽፍቶችም እመቤታችንን አስደንግጠዋታል። ዘራፊዎችም ነፍሰ ገዳዮችም ነበሩ። ለጊዜው የያዙትን ወስደውባቸው ከፊታቸው ዘወር ቢሉም ወዲያው እርስ በርሳቸው መጨቃጨቅ ጀመሩ። ጭቅጭቁም ጥጦስ «እንመልስላቸው፤» ሲል ፥ ዳክርስ ደግሞ «አንመልስላቸውም፤» የሚል ነበረ። እመቤታችን ግን «እንግደላቸው ፥ እንግደላቸው ፤» የሚባባሉ መስሏት ፦ «በውኑ ልጄን ከሞት ላላድነው ነው ፥ከሀገሬ የተሰደድኩት? » ብላ አለቀሰች። ለራሷ አላሰበችም። በዚህን ጊዜ ሕፃኑ ኢየሱስ ክርስቶስ በአዋቂ ቃል፦ «እናቴ ሆይ ፥ አታልቅሺ ፥ አንዱም ለእኔ አንዱም ለሰይጣን ነው፤» አላት። በመጨረሻም ጥጦስ የራሱን ድርሻ በሙሉ ለዳክርስ ከለቀቀለት በኋላ የእመቤታችንን መለሱላት። ጥጦስም እመቤታችንን ላግዝሽ ብሎ ሕፃኑን ተሸከመላት። በጉዞውም እንደ በትር ይመረኰዝበት የነበረው ሰይፍ ምንም ሰይነካው ስብርብር ብሎ ስለወደቀበት አዘነ። ጌታም በአዋቂ ቃል፦ «አይዞህ አትዘን ፤ » ካለው በኋላ በተአምር እንደቀድሞው አደረገለት። ጌታችን ሰይፉን በኃይሉ ሰባብሮ ያሳየው በሰይፍ መመካት ከንቱ መሆኑን ሲያስተምረው ነበር። ጥጦስ ጌታን በተሸከመው ጊዜ ከልብሱ ላይ ወዙ ስለፈሰሰበት እንደ ናርዶስ ሽቶ መዓዛው ከሩቅ ያውድ ነበር። ጌታችን በቀራንዮ በተሰቀለ ጊዜ «አንዱም ለእኔ ፤» የተባለ ጥጦስ በቀኙ ተሰቅሏል። «አንዱም ለሰይጣን ፤» የተባለ ዳክርስ ግን በግራው ተሰቅሏል።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሦሰት ዓመት ከመንፈቅ በስደት ከተንከራተተች በኋላ፦ የእግዚአብሔር መልአክ ለአረጋዊው ለዮሴፍ በግብፅ ሀገር በህልም ታየው። «የሕፃኑን ነፍሰ የሚሹ ሙተዋልና ፥ተነሥተህ ሕፃኑን እና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ሀገር ሂድ አለው። እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑን እና እናቱን ይዞ ወደ እስራኤል ምድር ገባ። አርኬላኦስም በአባቱ በሄሮድስ ፋንታ በይሁዳ እንደ ነገሠ በሰማ ጊዜ ፦ «የክፉ ልጅ ክፉ» ብሎ ወደዚያ ለመሄድ ፈራ፤ በህልምም ተገልጦለት ወደ ገሊላ አውራጃ ሄደ። በነቢያት ፦ «ልጄ ናዝራዊ ይባላል፤» የተባለው ይፈጸም ዘንድ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ ኖረ። ከግብፅ የተመለሱት በኢትዮጵያ በኲል ነው። ይህም ፦ «የኢትዮጵያ ድንኳንች ሲጨነቁ አየሁ ፤» ተብሎ በነቢዩ በዕንባቆም ትንቢት የተነገረበት ነው። ዕንባ ፫፥፯። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፮ የእመቤታችን የስደት መታሰቢያ ነው። ማኅሌተ ጽጌ ይቆማል፥ ቅዳሴ ማርያም ይቀደሳል። ገዳማውያንን አብነት ያደረጉ ምእመናንም በፈቃዳቸው ይጾሙታል።
«ዘንዶው በባሕር አሸዋ ላይ ቆመ፤»
ዘንዶውም በሴቲቱ (በእመቤታችን) ላይ ተቈጥቶ ፥ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርም ያላቸውን የቀሩትን ልጆቿን ሊወጋቸው ሄደ። ዘንዶውም በባሕር አሸዋ ላይ ቆመ። ባሕር የተባለች ዓለም ናት፤ ባሕር በማዕበል በሞገድ ስትናወጥ እንደምትኖር ሁሉ ዓለምም በማዕበለ ኃጢአት በማዕበለ ክህደት ፥ በሞገደ ኃጢአት በሞገደ ክህደት ስትናወጥ ትኖራለች። አሸዋ የተባሉት ደግሞ በዚህ ዓለም እንደ አሸዋ የበዙ መናፍቃን እና አሕዛብ ናቸው። አሸዋ ቈሪር ፥ ክቡድ እንደሆነ ሁሉ እነርሱም ቈሪራነ አእምሮ ፥ ክቡዳነ አእምሮ ናቸው፡፡ አንድም ኃጢአታቸው ክህደታቸው እንደ አሸዋ የበዛ ነው። ኢዮብ መከራውን ከባሕር አሸዋ እንደሚከብድ ተናግሯል። ኢዮ ፮፥፫። ከአብርሃም ወገን የሚወለዱ ጻድቃን በከዋክብት ሲመሰሉ ኃጥአኑ ደግሞ በአሸዋ ተመስለዋል። ዘፍ ፳፪፥፲፯ ፣ ሲራ ፵፬፥፳፩። እንግዲህ ፦ «ዘንዶውም በባሕር አሸዋ ላይ ቆመ፤» ማለት፦ በመናፍቃን ፥ በአሕዛብ ልቡና አደረ ማለት ነው።

 Source: http://www.facebook.com/groups/180759695294706/doc/183919174978758/

No comments:

Post a Comment