13

.

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው::" የማቴዎስ ወንጌል 7: 4

"እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅናወተት ግዙ።" ትንቢተ ኢሳይያስ 55 : 1

Monday, September 19, 2011

ነገረ ማርያም ክፍል ፲፩

በመልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው


«የኢየሱስ ክርስቶስ የትውልድ መጽሐፍ፤»

          ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌሉን መጻፍ የጀመረው፦ «የዳዊት ልጅ፥የአብርሃም ልጅ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የትወልድ መጽሐፍ፤» በማለት ነው። እንዲህም ያለበት ምክንያት ብዙ ዓይነት ልደታት ስላሉ ከእነዚያ የተለየ መሆኑን ለመግለጥ ነው። አምላክ በተዋሕዶ ሰው የሆነበት ምሥጢር ታላቅ በመሆኑ ተጠንቅቆ ጽፎታል። ፩ኛ ጢሞ ፫፥፲፮። ይኸውም፦ አድሮበት በሚኖር መንፈስ ቅዱስ ወደፊት በነገረ ክርስቶስ ዙሪያ አያሌ መናፍቃን እንደሚነሡ ስለሚያውቅ አስቀድሞ የኑፋቄን መንገድ ሲዘጋባቸው ነው።
፩፥፩፦ ልደተ አዳም፤
          «ወገብሮ እግዚአብሔር ለሰብእ እመሬተ ምድር፤ እግዚአብሔር አዳምን ከምድር መሬትን ነሥቶ ፈጠረው፤ በፊቱም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፤ (ሕይወት የምትሆነውን ነፍስን አሳደረበት)፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ። (አዳም ሕይወት በምትሆን ነፍስ ሕያው ባለአእምሮ ሆነ)፤» ይላል። ይህም፦ አንድ ሰው፦ ጐተራውን በፊት ሠርቶ ፥ በኋላ እህል እንደሚያኖርበት ፥ በፊት ሥጋን ፈጥሮ ኋላ ነፍስን አምጥቶ አሳደረበት ማለት አይደለም። እግዚአብሔር፦ ሥጋን ከአራቱ ባሕርያት (ከመሬት፣ ከነፋስ ፣ ከእሳት ፣ ከውኃ)፥ ነፍስንም እምኀበ ዐልቦ (ካለመኖር ወደ መኖር ፣ ከምንም አምጥቶ) የፈጠረው ፣ ያዋሐደው አንድ ጊዜ ነው። ዘፍ ፪፥፯።

          አዳም ማለት ከመሬት የተፈጠረ ማለት ነው፤ አንድም፦ የሚያምር ፥ ደስ የሚያሰኝ ፥ ውብ፥ ደግ፥ መልካም፥ መልከ መልካም ማለት ነው። ከመሬት በመፈጠሩም ከድንግል መሬት ተወለደ ይባላል። በዚህም ከድንግል ማርያም ለተወለደው ዳግማዊ አዳም ለሚባል ለኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ሆኗል። ከድንግል መሬት የተወለደው አንድ አዳም እንደሆነ ሁሉ፥ ከድንግል ማርያምም የተወለደው አንድ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። አዳም በዚህ ምድር የኖረው ለዘጠኝ መቶ ሠላሳ ዓመት ነው። ዘፍ ፭፥፭።
፩፥፪፦ ልደተ ሔዋን፤
          የሔዋን ልደት ከአዳም ጎን ነው፤ «እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ላይ እንቅልፍን አመጣ፤ አንቀላፋም፤ (ማእከለ ነቂሕ ወነዊም ሆነ፤ ይህም በእንቅልፍና በመንቃት መካከል ሆነ ማለት ነው)፤ ከጎኑም አጥንቶች አንድ አጥንትን ወስዶ ስፍራውን በሥጋ መላው። እግዚአብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት፤ (የሴት አካል ያላት አድርጎ ፈጠራት ፥ አንድም ስትፍት ብርህት አደረጋት)፤ ወደ አዳምም አመጣት። (መልክ ከደም ግባት አስተባብራ የያዘች የምታምር አድርጎ ወደ አዳም አመጣት)። አዳምም፦ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፤ ሥጋዋም ከሥጋዬ ናት፤ እርስዋ ከባልዋ ተገኝታለችና ሚስት ትሁነኝ፤ (ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል)፤ አለ።» ይላል። ዘፍ ፪፥፳፩። እናታችን ሔዋን ኅቱም ከሆነ ከአዳም ጎን እንደተወለደች ሁሉ፥ ጌታም በድንግልና ኅትምት ከሆነች ፥ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዷል።
፩፥፫፦ ልደተ በግዕ፤
          እግዚአብሔር አብርሃምን ለበጎ ፈተነው፤ በሀገራቸው ልማድ፦ «አብርሃም፥አብርሃም» ብሎ በደጊመ ቃል ጠራው፤ አብርሃምም፦ «ጌታዬ፥ እነሆ አለሁ፤» አለ፤ እግዚአብሔርም፦ «የምትወደውን ልጅህን ይስሐቅን ከፍ ወደአለ ተራራ ይዘኸው ሂድ፥ ከዚያም በደረስህ ጊዜ በማሳይህ በአንድ ተራራ ላይ አውጥተህ ሠዋው፤» አለው። አብርሃምም፦ ልጁን ይስሐቅን ይዞ፥ሁለቱንም ሎሌዎቹን አስከትሎ አህያውን ጭኖ ተነሣ። እንጨትንም ለመሠዊያ ሰነጠቀ፤ ተነሥቶም እግዚአብሔር ወደአለው ቦታ ሄደ፤ በሦስተኛውም ቀን ደረሰ።
          አብርሃም ዓይኑን አንሥቶ ቦታውን ከሩቅ አየ። ሎሌዎቹንም፦ «አህያውን ይዛችሁ በዚህ ቆዩ፤ እኔና ልጄ ወደዚያ ተራራ ሄደን እንሰግዳለን፤ ሰግደንም ወደ እናንተ እንመለሳለን።» አላቸው። አብርሃም፦ መሥዋዕት የሚሠዋበትን እንጨቱን አንሥቶ ለይስሐቅ አሸከመው፤ እርሱም እሳቱንና ቢላዎውን በእጁ ያዘ፤ ሁለቱም አብረው ሄዱ። ይስሐቅም አባቱን አብርሃምን፦ «አባቴ» ብሎ ጠራው፤ እርሱም፦ «ልጄ ምንድን ነው?» አለው። ይስሐቅም፦ «እሳቱና እንጨቱ እነሆ አለ፤የመሥዋዕቱ በግ ግን ወዴት አለ?» አለው። አብርሃምም፦ «ልጄ ሆይ፥ የመሥዋዕቱን በግ እግዚአብሔር ያዘጋጃል፤» አለውና ጉዞአቸውን ቀጠሉ።
          እግዚአብሔር ወዳለውም ወደዚያ ቦታ ደረሱ፤ አብርሃምም በዚያ መሠዊያዉን ሠራ፤ እንጨትም ረበረበ፤ ይስሐቅም፦ እርሱ እንደሚሠዋ አውቆ፦ «እኔን ልትሠዋኝ ይመስለኛል ፥ ስለዚህ ስወራጭ፣ ስንፈራገጥ እጅህን እንዳላስቆርጥህ እሰረኝ፤» ብሎታል። በዚህን ጊዜ፦ እጁንና እግሩን አሥሮ ሠርጅቶ (ጠልፎ) ጣለው። ቀጥሎም የልጅ ዓይኑ ብክን ብክን ሲል ያሳዝናልና ራርቼ ትቼው ከፈጣሪዬ ጋር እጣላለሁ ብሎ፥ አንድም ልጁ ይስሐቅ፦ ዓይኔ ብክን ብክን ሲል አይተህ ራርተህ ትተወኝና ከፈጣሪህ ጋር ትጣላለህ ብሎት እንጨት በተረበረበበት በምሥዋዑ ላይ ደፍቶ በልቡ አስተኛው።
          አብርሃምም እጁን ዘረጋ፤ ልጁንም ያርድ ዘንድ ቢላዎውን አነሣ። እግዚአብሔርም ከሰማይ ጠርቶ፦ «በብላቴናው ላይ እጅህን አትዘርጋ፤ አንዳችም አታድርግበት፤ ለምትወድደው ልጅህ ከእኔ አልራራህለትምና፤ (ልጅህን ከእኔ ይልቅ አልወደድኸውምና)፤ አንተ እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደሆንህ አሁን አውቄአለሁ፤» አለው። አብርሃም ዓይኖቹን አቅንቶ በተመለከተ ጊዜ፦ በኋላው እነሆ፥ አንድ በግ ቀንዶቹ በዕፀ ሳቤቅ ተይዞ አየ፤ ሄዶም በጉን ወሰደውና በልጁ በይስሐቅ ፈንታ ሠዋው። አብርሃምም፦ በዚህ ተራራ እግዚአብሔር ፈጽሞ ታየኝ ሲል ያን ቦታ፦ «ራእየ እግዚአብሔር፤» ብሎ ጠራው።
          አብርሃም የአብ፥ ይስሐቅ ደግሞ የወልድ ምሳሌዎች ናቸው። አብርሃም ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ልጁን ይስሐቅን በሕሊናው እንደሠዋው፥ እግዚአብሔር አብም ተቀዳሚና ተከታይ የሌለውን አንድ የባሕርይ ልጁን ፥ ስለ ሰው ልጅ ፍቅር ለሞት አሳልፎ ሰጥቶታል። ይኽንንም ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ፦ «በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኝ እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲህ ወዶአልና።» በማለት ገልጦታል። ዮሐ ፫፥፲፮። በመጀመሪያዪቱም መልእክቱ ላይ፦ «በዚህም የእግዚአብሔር ፍቅሩ በእኛ ላይ ታወቀ፤ በእርሱ በሕይወት እንኖር ዘንድ አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና።» ብሏል። ፩ኛ ዮሐ ፬፥፱።
          ተራራው የቀራንዮ፥ የመሠዊያው እንጨት የመስቀል ፥ እሳቱ የመንፈስ ቅዱስ፥ ሁለቱ ሎሌዎች በግራና ቀኝ ለተሰቀሉ ሰዎች ፥ ቢላዎ የሥልጣነ እግዚአብሔር ምሳሌዎች ናቸው። ቢላዎ አጥንትን ከሥጋ እንደሚለይ፥ ጌታም በገዛ ሥልጣኑ ነፍሱን ከሥጋው ለይቷል። አብርሃም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በሰማበት በዚያ ሰዓት ወዲያው ልጁን በሕሊናው ሰውቶት ለሦስት ቀናት ተጉዟል። ከሦስት ቀን በኋላም ይስሐቅ ድኗል። ሕሊና አብርሃም የመቃብር ምሳሌ ነው፤ ይስሐቅ በሕሊና አብርሃም በተሠዋ በሦስተኛው ቀን መዳኑ፥ ጌታ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር አድሮ ለመነሣቱ ምሳሌ ነው። አንድም በጉ የጌታ፥ ይስሐቅ ደግሞ የአዳምና የልጆቹ ምሳሌዎች ናቸው። በጉ ከሰማይ ወርዶ በኅቱም ዕፅ ተይዞ (ከኅቱም ዕፅ ተወልዶ) መገኘቱ፥ ጌታ ከሰማይ ወርዶ ከድንግል ማርያም ለመወለዱ ምሳሌ ነው። ዕፀ ሳቤቅ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት። በጉ ስለ ይስሐቅ ፈንታ መሠዋቱ ጌታ ለአዳምና ለልጆቹ ተላልፎ በመስቀል ላይ ለመሠዋቱ ምሳሌ ነው። ሊቃውንቱ በጉ ከኅቱም ዕፅ ተወለደ ብለው ይተረጉሙታል። በዕፀ ሳቤቅ ቀንዶቹ ተይዞ የተገኘ አንድ በግ ብቻ ነው ፥ ከእመቤታችንም የተወለደው አንድ የቀራንዮ በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ዘፍ ፳፪፥፩። መጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሐንስ ኢየሱስ ክርስቶስን፦ «የዓለሙን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ፤» ያለው ለዚህ ነው። ዮሐ ፩፥፳፱።
፬፥፩፦ ልደተ አቤል፤
          አቤል የቃኤል ታናሽ ወንድም ነው፤ ልደቱ በዘር በሩካቤ ነው፤ ከእርሱ ጋር መንታ ሆና የተወለደችው አቅሌምያ ናት፥ መልከ ጥፉ ነበረች፤ አቤል ግን ብሩኅ ገጽ ነበረው። አባቱም፦ «ይህ ብሩኅ ገጽ ያለው ልጄ መንግሥቴን የሚወርሰው እርሱ ነው፤» ይለው ነበር። የሚታወቀው በገርነቱ በየዋህነቱ ነው፥ ለአዳምና ለሔዋን ይታዘዛቸው ነበር፤ አዳም በሳምንት ሦስት ጊዜ ለእግዚአብሔር ቊርባን ሲያቀርብ አይለየውም ነበር፥ ከቊርባኑም ይቀበል ነበር። ቃኤል፦ ከጸሎቱ፥ ከቊርባኑ ብዙ ጊዜ ሲቀር አቤል ግን አንድም ቀን አያስታጉልም ነበር፤ ብዙ ጊዜ ይጾም ብዙ ጊዜም ይጸልይ ነበር። አባቱ አዳም ባዘዘውና ባስተማረው መሠረት ንጹሕ መሥዋዕት በበጎ ኅሊና አቅርቧል፤ እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመልክቷል። ዘፍ ፬፥፬። ስለየዋህ ልቡናው ፥ ስለ መሥዋዕቱም ንጹሕነት እግዚአብሔር ተደስቶበታል። አቤል፦ ልክ እንደ አባቱ በሳምንት ሦስት ቀን መሥዋዕት ያሳርግ ነበር።
          ቃኤል አሥራ አምስት ዓመት ፥ አቤል ደግሞ አሥራ ሁለት ዓመት ሲሞላቸው፦ አባታቸው አዳም፦ ከቃኤል ጋር የተወለደችውን ውብ ለአቤል አጋባት፤ ከአቤል ጋር የተወለደችውን መልከ ጥፉ ደግሞ ለቃኤል አጋባት። ቃኤልም ስለ ሦስት ነገር በወንድሙ ተበሳጨበት። ፩ኛ፦ አልጋ ወራሽ በመሆኑ፤ ፪ኛ፦ መሥዋዕቱን እግዚአብሔር ስለተቀበለለት፤ ፫ኛ፦ በትዳሩ ቀንቶበት ተቆጣ። በመጨረሻም ሰይጣን እንደአስተማረው «ና፥ወደ ሜዳ እንሂድ፤» ብሎ፥ ራሱን በድንጋይ ገምሶ ገድሎታል። በግፍ የፈሰሰ የአቤል ደም፦ «ወንድሜ ቃኤል ገደለኝ፤» እያለ ጩኸቱን ለእግዚአብሔር አሰምቷል። ከሞተ በኋላም በደሙ በመናገሩ ለትንሣኤ ሙታን ምሳሌ ሆኗል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ ይኽንን ይዞ፦ «አቤል ከቃኤል ይልቅ የሚበልጥ መሥዋዕትን ለእግዚአብሔር አቀረበ፤ በዚህም ጻድቅ እንደሆነ ተመሰከረለት፤ ምስክሩም መሥዋዕቱን በመቀበል እግዚአብሔር ነው። በዚህም ከሞተ በኋላ ተናገረ።» በማለት ሃይማኖቱን ፥ ምግባሩን መስክሮለታል። ዕብ ፲፩፥፬። እግዚአብሔር ቃኤልን፦ «ወንድምህ አቤል ወዴት ነው?» ብሎ በጠየቀው ጊዜ፦ «አላውቅም፤ በውኑ የወንድሜ ጠባቂው እኔ ነኝን?» በማለት ተሳልቋል። እግዚአብሔርም፦ «ምን አደረገህ? የወንድምህ የአቤል የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል። አሁንም የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፍዋን በከፈተች በምድር ላይ አንተ የተረገምህ ነህ፤» ብሎታል። ዘፍ ፬፥፰-፲፩።
፪፦ ዳዊትና አብርሃም፤
          ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌላዊ፦ «ወልደ ዳዊት፥ ወልደ አብርሃም፤» በማለት ከነገሥታት ዳዊትን፥ ከአበው ደግሞ አብርሃምን አንሥቷል። ይኸውም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእነርሱ ብቻ ይወለዳል ለማለት ሳይሆን የተለያዩ ምክንያቶች ስላሉት ነው።
፪፥፩፦ ዳዊት ሥርወ መንግሥት ስለሆነ ነው፤
          ዳዊት፦ ከእሥራኤል ነገሥታት ሁሉ ይልቅ ታላቅና እጅግ ተወዳጅ ንጉሥ ነበር። የተወለደው እሴይ ከተባለ ሰው በይሁዳ ቤተልሔም ነው። ፩ኛ ሳሙ ፲፮፥፲። እግዚአብሔር ሳይጠራው በፊት የበጎች እረኛ ነበር። ፩ኛ ሳሙ ፲፮፥፲፩ ፣፲፯፥፴፬። ንጉሥ ሳኦል እግዚአብሔርን ከመከተል ወደ ኋላ በመመለሱ በእሥራኤል ላይ ንጉሥ እንዳይሆን እግዚአብሔር ናቀው። «ስላነገሥሁት ተጸጸትሁ፤» በማለትም ለነቢዩ ለሳሙኤል ነገረው። ፩ኛ ሳሙ ፲፭፥፲። ንጉሥ ሳኦል በዚህና በሌሎችም ምክንያቶች ሥርወ መንግሥት መሆን አልቻለም። «የእግዚአብሔርም መንፈስ ከሳኦል ራቀ፤ ክፉም መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ አስጨነቀው፤» ይላል። ፩ኛ ሳሙ ፲፮፥፲፬። በምትኩ ንጉሥ ይሆን ዘንድ ዳዊት በሳሙኤል እጅ ተቀባ። የእግዚአብሔርም መንፈስ ከዚያ ቀን ጀምሮ በዳዊት ላይ መጣ። ፩ኛ ሳሙ ፲፮፥፲፫። ዙፋኑን ከመውረሱ በፊት ግን ጋሻ ጃግሬ ሆኖ ሳኦልን አገልግሎታል። በገና እየደረደረም ርኲስ መንፈስን ያርቅለት ከስቃይም ያሳርፈው ነበር። ፩ኛ ሳሙ ፲፮፥፲፰-፳፫። በሰይፍ ተመትቶ፥ በጦር ተወግቶ፥ በፈረስ በሠረገላ ተገፍትሮ፥ አይወድቅ የነበረውን ታላቁን ጎልያድንም፦ በእግዚአብሔር ስምና ኃይል በወንጭፍ ድንጋይ ገድሎታል። ፩ኛ ሳሙ ፲፯፥፵፭-፶፮።
          የሳኦል ልጅ ናታን ዳዊትን እንደ ነፍሱ ስለወደደው ካባውን፥ ልብሱን፥ ሰይፉን፥ ቀስቱንና ዝናሩን ሸልሞታል። የእሥራኤል ሴቶችም እየዘመሩና እየዘፈኑ፥ እልልም እያሉ፥ ከበሮና አታሞ ይዘው ተቀብለውታል። «ሳኦል ሺህ ገደለ፤ ዳዊትም አሥር ሺህ ገደለ፤»እያሉ እየተቀባበሉ ይዘፍኑ ነበር። በዚህም ምክንያት ሳኦል እጅግ ተቆጣ፥ ነገሩም አስከፋው፥ በዳዊትም ላይ ቂም ያዘበት። ይሁን እንጂ ክፉ መንፈስ በየዕለቱ ሲያሰቃየው ዳዊት እየተጠራ በገና ይደረድርለት ነበር። በዚህ አጋጣሚም ዳዊትን ከግንቡ ጋር አጣብቆ ለመግደል ከአንዴም ሁለት ጊዜ ጦር ወርውሮበት ነበር። ዳዊት ግን ከፊቱ ዘወር ብሎ አመለጠ። እግዚአብሔር ከእርሱ ተለይቶ ከዳዊት ጋር ስለነበር ሳኦል ዳዊትን ይፈራው ነበር። ከዚህ የተነሣ የሺ አለቃ አድርጎ (ሻለቅነት ሹሞት) በሹመት ስም ከፊቱ አራቀው። ነገር ግን በፊታቸው ይወጣና ይገባ ስለነበረ እስራኤልና ይሁዳ ሁሉ ዳዊትን ወደዱት። ፩ኛ ሳሙ ፲፰፥፩-፲፮።
          ንጉሥ ሳኦል ዳዊትን በትዳር ሊያጠምደው ሞክሯል። ዳዊት ግን፦ «ለንጉሥ አማች እሆን ዘንድ እኔ ማን ነኝ? ሰውነቴስ ምንድን ናት? የአባቴስ ወገን በእስራኤል ዘንድ ምንድን ነው?» በማለት የትህትናን ነገር ተናገረ። የሳኦል ልጅ ሜሮብ ዳዊትን የምታገባበት ጊዜ ሲደርስ ለሚሆላዊው ለአድርኤል ተዳረች። ሜልኮል የተባለች ሴት ልጁ ደግሞ ዳዊትን ወደደችው ፥ ወሬውም ለሳኦል ደርሶ ነገሩ ደስ ስለአሰኘው «እርስዋን እሰጠዋለሁ፤ እርስዋም እንቅፋት ትሆንበታለች፤» አለ። ብላቴኖቹንም፦ «እነሆ ንጉሥ እጅግ ወድዶሃል፤ አሁንም ለንጉሥ አማች ሁን ብላችሁ በሥውር ለዳዊት ንገሩት፤» ብሎ አዘዛቸው። ዳዊት ይህን በሰማ ጊዜ፦ «እኔ የተዋረድሁና ክብር የሌለኝ ሰው ስሆን ለንጉሥ አማች እሆን ዘንድ ለእናንተ ትንሽ ነገር ይመስላችኋልን?» አላቸው። ንጉሡ ሳኦል፦ ይኽንን በነገሩት ጊዜ፦ «የንጉሡን ጠላቶች ይበቀል ዘንድ ከመቶ ፍልስጥኤማውያን ሸለፈት በቀር ንጉሥ ማጫ አይሻም ብላችሁ ለዳዊት ንገሩት፤» አላቸው። ሳኦል እንዲህ ማለቱ ብላቴናው ዳዊት በእነርሱ እጅ እንዲሞትለት ነው።ዳዊትና ሰዎቹም ዘምተው ሁለት መቶ ፍልስጥኤማውያንን ገደሉ። ሳኦልም ዕድሜውን ሁሉ ለዳዊት ጠላት ሆነ። ፩ኛ ሳሙ ፲፰፥፲፯-፴።
          ንጉሥ ሳኦል፦ በፍልስጥኤማውያን ወረራ መካከል በጊልቦዓ ተራራ ላይ በገዛ እጁ ከሞተ በኋላ፦ ዳዊት አስቀድሞ በይሁዳ፥ በኋላም በመላው እስራኤል ላይ ነገሠ። ፪ኛ ሳሙ ከምዕራፍ ፪ እስከ ምዕራፍ ፭። በዘመነ መንግሥቱ እግዚአብሔር እየረዳው ታላላቅ ሥራዎችን በማከናወኑ ስመ ጥር ነበር። ከዘመነ መሳፍንት ጀምሮ እስራኤልን ሲያጠቁ የነበሩትን ፍልስጥኤማውያንን አሸንፏል። ፪ኛ ሳሙ ፭፥፲፰-፳፭። አሕዛብን በማስገበር ሀገሩን አስፍቷል። ፪ኛ ሳሙ ፰፥፲፪። ኢየሩሳሌም የተባለችውን የተመሸገች ከተማ ወርሮ ኢያቡሳዊያንን አሸንፎ መናገሻ ከተማ አድርጓታል፤ በዚህም ምክንያት የዳዊት ከተማ ተብላለች። ፪ኛ ሳሙ ፭፥፩-፲። ታቦተ ጽዮንንም ወደዚያ በማምጣት፦ መሥዋዕት የሚሠዋባት፥ አምልኮት የሚፈጸምባት መንፈሳዊ ሥፍራ እንድትሆን ለዚህ ክብር አብቅቷታል። የመቅደሱንም ሥርዓት አሻሻሏል። ፪ኛ ሳሙ ፮፣ ፩ኛ ዜና ፳፰፥፫። ብዙ መዝሙራትንም ጽፏል። ዳዊት ታላቅና ገናና፥ መንፈሳዊም በመሆኑ መንግሥቱ ለክርስቶስ መንግሥት ምሳሌ ሆኖአል። ፪ኛ ሳሙ ፯፥፰ ፣ ኢሳ ፱፥፯ ፣ ኤር ፳፫፥፭ ፣ ፴፫፥፲፬ ፣ ሕዝ ፴፬፥፳፫ ፣ ፴፯፥፳፬።
፪፥፪፦ ዳዊት ትንቢት ስለተነገረለትም ነው፤
          ትንቢት ለሌሎችም የተነገረ ቢሆንም የዳዊት ግን ይበዛል። «እግዚአብሔር ለዳዊት እንዲህ ሲል በእውነት ማለ፤ አይጸጸትምም ፥ ከሆድህ ፍሬ በዙፋንህ ላይ አስቀምጣለሁና፤ ልጆችህ ኪዳኔን፥ ይህንንም የማስተምራቸውን ምስክሬን ቢጠብቁ ፥ ልጆቻቸው በዙፋንህ ላይ ለዘለዓለም ይቀመጣሉ።» ይላል። ፻፴፩፥፲፩። ይህ ትንቢት ለጊዜው ለሰሎሞን ሲሆን ለፍጻሜው ለጌታ ነው። ትርጉሙም ከባሕርይህ የተከፈለ ልጅህን ክርስቶስን በዙፋንህ አስቀምጥልሃለሁ ሲለው ነው። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል፦ እመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያምን ባበሠራት ጊዜ፦ «እግዚአብሔር አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤» ያለው ለዚህ ነው። ሉቃ ፩፥፴፪። ነቢዩ ኢሳይያስም፦ «ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤» ካለ በኋላ «በዳዊት ዙፋን መንግሥቱ ትጸናለች፤ ለሰላሙም ፍጻሜ የለውም፤» ብሏል። ኢሳ ፱፥፮። በተጨማሪም፦ «ከእሴይ ሥር በትር ትወጣለች፤ አበባም ከግንዱ ይወጣል፤» ብሏል። ኢሳ ፲፩፥፩። ትርጉሙም፦ ከነገደ እሴይ (ከዳዊት ወገን) በትረ ሕይወት እመቤታችን ትወለዳለች፥ ከእርሷም አበባ ክርስቶስ ይወለዳል ማለት ነው። ነቢዩ ኤርምያስም፦ «እነሆ ለዳዊት የጽድቅ ቊጥቋጥ አበቅልለታለሁ፤ እርሱም ፍርድንና ጽድቅን በምድር ያደርጋል፤» የሚል አለ። ኤር ፴፫፥፲፬። ትርጉሙ ካለፈው ጋር አንድ ነው፥ አይለወጥም። በትንቢተ ሕዝቅኤል ላይ ደግሞ፦ «በላያቸውም አንድ እረኛ አቆማለሁ፤ እርሱም ባሪያዬ ዳዊት ነው፤ እረኛም ይሆናቸዋል።» ተብሎ ተነግሯል። በተጨማሪም፦ «ባሪያዬም ዳዊት በላያቸው ንጉሥ ይሆናል፤ ለሁሉም አንድ እረኛ ይሆንላቸዋል፤ በፍርዴም ይሄዳሉ፥ ትእዛዜንም ይጠብቃሉ፤ ያደርጓትማል።» ይላል። ሕዝ ፴፯፥፳፬። ሕዝ ፴፬፥፳፫።ይህም ለፍጻሜው ለክርስቶስ የተነገረ ቃለ ትንቢት ነው። ይኽንንም የትንቢቱ ባለቤት ራሱ ኢየሱስ ክርሰቶስ፦ «መልካም እረኛ እኔ ነኝ መልካም እረኛ ስለበጎቹ ነፍሱን ይሰጣል። . . . . . እረኛው አንድ መንጋውም አንድ ነው፤» በማለት ነግሮናል። ዮሐ ፲፥፲፩፣፲፮።
፪፥፫፦ አብርሃም ሥርወ ሃይማኖት ስለሆነ ነው፤
          አብርሃም፦ እግዚአብሔርን ያገኘው በሥነ ፍጥረት ተመራምሮ ነው። አብርሃም የኖረው የጣኦት አምልኮት በተስፋፋባት በካራን ነው። ካራን፦ በነነዌና በኤፍራጥስ ወንዝ መካከል የነበረ ከተማ ነው። የአብርሃም አባት ታራ ጣዖት እየሠራ ይሸጥ ይለውጥ ነበር። ይህም ልማድ ከአያቱ ከሴሩሕ ጀምሮ ተያይዞ የመጣ ነው። ሴሩሕ ናኮርን ወለደ፥ ናኮር ታራን ወለደ፥ታራ ደግሞ አብርሃምን ወለደ። ኩፋሌ ፲፥፳፮-፴።
፪፥፫፥፩፦ አብርሃም የጣዖት አምልኮትን ተቃወመ፤
          አብርሃም ከልጅነቱ ጀምሮ፦ ጣዖታቱን በመከተልና ኃጢአትን በመሥራት እንደሚሳሳት የምድርን ስሕተት ያውቅ ነበር። አባቱም መጽሐፍ አስተምሮታል፤ የሁለት ሱባዔ ዓመት ልጅ በነበረ ጊዜም ለጣዖት እንዳይሰግድ አባቱን ከመከተል ተለየ። ከሰዎች ልጆች ስሕተትም ያድነው ዘንድ፥ ዕጣውም ርኲሰትንና ፌዝን በመከተል ወደ ስሕተት እንዳይሆን ሁሉን ወደ ፈጠረ ወደ እግዚአብሔር ይጸልይ ጀመር። ኩፋሌ ፲፥፴፩-፴፫።
          አብርሃም አባቱን ታራን፦ «ምንት ተድላ ወረድኤት ለነ አባ፤ አባቴ ሆይ፥ ከእነዚህ ከጣዖታቱ ለእኛ ምን ረድኤትና ደስታ አለን?» አለው። ታራም አብርሃምን፦ «ልጄ፥እኔም እንደማይረባንና እንደማይጠቅመን አውቃለሁ፤ ነገር ግን የዚህ ሀገር ሰዎች በፍቅረ ጣዖት የሰከሩ ስለሆኑ እንዳያጠፉን ፈርቼ ነው፤» <እንደ ወንዙ ይሻገሩ፥ እንደ ሀገሩ ይኖሩ፤> ብዬ ነው፤» አለው። ኩፋሌ ፲፥፵፪-፵፭።
          ታራ፦ እንጨት ጠርቦ ፥ደንጊያ አለዝቦ ጣዖት ከሠራ በኋላ፥ አብርሃምን፦ «ወደ ገበያ ሒደህ ሸጠህ ና፤» አለው። አብርሃምም በመንገድ ሳለ፦ «አፍ እያለው የማይናገር፥ እጅ እያለው የማይዳስስ፥ እግር እያለው የማይራመድ ይህ ምንድነው?» አለ። ከገበያውም ገብቶ፦ «አፍ እያለው የማይናገር እጅ እያለው ያማይዳስስ፥ እግር እያለው የማይራመድ ጣዖት ግዙ፤» አላቸው። «ባለቤት ያቀለለውን ገንዘብ ባለዕዳ አይቀበለውም፤» እንዲል፦ «እርሱ እንዲህ እያለ ያራከሰው ለእኛ ምን ይረባናል?» ብለው የማይገዙት ሆኗል።
          አብርሃም ጣዖቱን ይዞ ወደ ቤቱ ሲመለስ፦ «ርቦኛል አብላኝ፥ ጠምቶኛል አጠጣኝ፤» ቢለው የማይመልስለት ሆነ። ሁለተኛም፦ «የደከመው ሰው ቢያጫውቱት ይበረታልና አጫውተኝ፤» ቢለው ዝም አለው። በመጨረሻም፦ «ይህስ ፍጡር ነው እንጂ ፈጣሪዬ አይደለም ድዳ ነው፥ ልቡናንም የሚያስት ነው፤ ፈጣሪዬ ሌላ ነው፤» ብሎ ከትከሻው አውርዶ በደንጊያ ቀጠቀጠው።
፪፥፫፥፪፦ አብርሃም ፈጣሪውን ፈለገ፤
          አብርሃም ፈጣሪውን ለማግኘት ባደረገው ጉዞ ፍጥረታትን ይመለከት፥ ይመረምር ጀመር። ተራራውን ከፍ ብሎ ቢያየው፦ «አምላክስ ይህ ነው፤» አለ። ይህንንም፦ አንዱ ተራራ ሌላውን ሲበልጥ አይቶ፦ «በፈጣሪ መብለጥ መበላለጥ የለበትም፥ ስለዚህ ይህም አምላክ አይደለም፤» አለ። ሁለተኛም ነፋስ፦ ባሕር ሲገሥጽ፥ ዛፍ ሲያናውጥ አይቶ፥ «አምላክስ ይህ ነው፤» አለ። ነፋስንም፦ ተራራ ሲገታው፥ መዝጊያ ሲመልሰው አይቶ፦ «ፈጣሪንስ የሚገታው የለም፥ ይህም አምላክ አይደለም፤» አለ። ሦስተኛም፦ የባሕሩን ማዕበልና ሞገድ አይቶ «አምላክስ ይህ ነው፤» አለ። ባሕርም ሲሞላና ሲጐድል አይቶ፦ «በፈጣሪስ ሕፀፅ (ጉድለት) የለበትም ፥ ይህም አምላክ አይደለም፤» አለ። አራተኛም፦ እሳት፦ ደረቁን ከርጥቡ ለይቶ ሲበላ፥ ቋያውን ሲያቃጥል አይቶ፦ «አምላክስ ይህ ነው፤» አለ። እርሱንም ውኃ ሲያጠፋው፥ መንገድ ሲከለክለው አይቶ፦ «ይህም አምላክ አይደለም፤» አለ። አምስተኛም፦ ፀሐይ በዓለሙ መልቶ ሲያበራ አይቶ፦ «አምላክስ ይህ ነው፤» ብሏል። እርሱም፦ በምሥራቅ ወጥቶ በምዕራብ ሲገባ አይቶ «በፈጣሪስ መውጣት መግባት የለበትም፥ ቀን ቢመግበን ማታ ማን ይመግበናል? ለዚህም ፈጣሪ አለው፤» አለ። ከዚህ በኋላ፦ «አምላከ ፀሐይ ተናበበኒ፤ የፀሐይ አምላክ አነጋግረኝ፤» ብሎ ጮኸ። እግዚአብሔርም ድምፁን አሰምቶታል፤ አንድም መልአከ እግዚአብሔር ተገልጦለት፦ «እነዚህ ሁሉ ፍጡራን ናቸው ፥ የፈጠራቸው አለ፤» ብሎታል። አብርሃምን ሥርወ ሃይማኖት ያሰኘው ይህ ነው። አብርሃም ፈጣሪውን በማግኘቱ ፥ በሌሊት ተነሥቶ፥ የጣዖታቱን ቤት በውስጡ ያለውንም ዕቃ ሁሉ አቃጠለ። እንዲህ ማድረጉንም ያወቀ ሰው የለም፤ ወንድሙ አራን ግን ጣዖታቱን አድናለሁ ብሎ ከእሳቱ ገብቶ፥ ተቃጥሎ ሞቷል። ኩፋ ፲፩፥፩-፫።
          አብርሃም፦ እግዚአብሔርን ፈልጎ ካገኘ በኋላ በጣዖት መንደር እንዲኖር አልተፈቀደለትም። «ፃእ እምድርከ ወእምአዝማዲከ ወእምቤተ አቡከ፤ ወሑር ውስተ ምድር እንተ አርእየከ። ወእሬስየከ ሕዝበ ዐቢየ ወእባርከከ፤ ወአዐቢ ስመከ፥ ወትከውን ቡሩከ፤ ወእባርኮሙ ለእለ ይባርኩከ፥ ወእረግሞሙ ለእለ ይረግሙከ። ከአባትህ ወገን ከዘመዶችህ ተለይተህ ከአገርህ ውጣ፤ እኔ ወደማሳይህ ወደ ከነዓንም ሂድ። ብዙ ወገን አደርግሃለሁ፥ አከብርሃለሁ፤ ስምህንም አከብረዋለሁ፥አገነዋለሁ፥አበ ብዙኃን እንድትባል አደርግሃለሁ። የሚመርቁህን እመርቃቸዋለሁ፥የሚረግሙህን ሰዎች አጠፋቸዋለሁ፤» ተብሏል። አብርሃምም በፍጹም ሃይማኖት፦ ከዘመዶቹ ተለይቶ ከሀገሩ ወጥቷል፥ እግዚአብሔርን አምኖ ወደማያውቀው ሀገር ተጉዟል። ዘፍ ፲፪፥፩-፫። እግዚአብሔር ጠርቶናል፥ እግዚአብሔርን እናገለግላለን የምንል ሰዎች ከአብርሃም ተምረን ከመንደር ልንወጣ ማለትም ከዘረኝነት ልንላቀቅ ይገባናል፤ መንፈሳዊ ሆነናል ካልን በኋላም የሥጋ ዝምድና ከመቊጠር ልንጠበቅ ያስፈልገናል። ለሃይማኖት ሰው ሁሉ አገሩ፥ ሁሉ ወገኑ ነውና።
          አብርሃም የመቶ ዓመት ሽማግሌ ከሆነ በኋላ ከቃል ኪዳን ሚስቱ እድሜ ከተጫናት (ዘጠና ዓመት ከሞላት) ከሣራ ይስሐቅን የወለደው በሃይማኖት ነው። በአንድነት በሦስትነት የሚመሰገኑ ሥላሴን በድንኳኑ ባስተናገደ ጊዜ፦ «ሶበ ገባእኩ እመጽእ ኀቤከ አመ ከመ ዮም ትረክብ ሣራ ወልደ፤ እንደ ዛሬ ጊዜ ተመልሼ በረድኤት ወደ አንተ በመጣሁ ጊዜ ሣራ ወንድ ልጅን ትወልዳለች፤» የተባለውን በሃይማኖት ተቀበለ። ተስፋውን የሰሙት ሐምሌ ሰባት ቀን ነው፤ በተነገራቸው ተስፋ መሠረት ይስሐቅ የተፀነሰው በመስከረም ልደቱ ደግሞ በሰኔ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ፦ የአብርሃምን ሃይማኖት ሲመሰክር፦ «ስለዚህም እግዚአብሔር ለአብርሃምና ለዘሩ የሰጠው ተስፋ የታመነ ይሆን ዘንድ፥ የሚጸድቁ በእምነት እንጂ የኦሪትን ሥራ በመፈጸም ብቻ እንዳይደለ ያውቁ ዘንድ እግዚአብሔር ጽድቅን በእምነት አደረገ። ለብዙዎች አሕዛብ አባት አደርግሃለሁ ተብሎ እንደተጻፈ ሙታንን በሚያስነሣቸው፥ የሌሉትንም እንዳሉ በሚያደርጋቸው በአመነበት በእግዚአብሔር ፊት አብርሃም የሁላችን አባት (የሃይማኖት አባት፥ የሃይማኖት ሥር፥ የሃይማኖት መሠረት) ነው። አብርሃም ዘርህ እንዲህ ይሆናል ብሎ እግዚአብሔር ተስፋ እንደሰጠው ተስፋ ባልነበረ ጊዜ የብዙዎች አሕዛብ አባት እንደሚሆን አመነ። አብርሃም የመቶ ዓመት ሽማግሌ ስለሆነ እንደ ምውት (እንደ ሬሣ) የሆነውን የራሱን ሥጋና የሳር ማኅፀን ምውት (ሙቀት ልምላሜ የተለየው) መሆኑን እያየ በእምነት አልተጠራጠረም፤ በእምነት ጸና እንጂ፤ ለእግዚአብሔርም ክብርን ሰጠ። እግዚአብሔርም የሰጠውን ተስፋ ሊያደርግለት እንደሚችል በፍጹም ልብ አመነ።»ብሏል።ሮሜ ፬፥፲፮-፳፮።
          የአብርሃም እምነት በነገር ሁሉ ነው፤ አብርሃም የዘጠና ዘጠኝ ዓመት በነበረ ጊዜ እግዚአብሔር ተገልጦለት፦ «በፊትህ የሄድሁ ፈጣሪህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፤ በፊቴ መልካም አድርግ፤ ንጹሕም ሁን፤ ቃል ኪዳኔንም በእኔና በአንተ መካከል አጸናለሁ፤ እጅግም አበዛሃለሁ፤» አለው። አብርሃምም በግንባሩ ወደቀ፤ (ሰገደ)፤ እግዚአብሔርም አብርሃምን፦ አንተ ደግሞ ቃል ኪዳኔን ትጠብቃለህ፤ አንተም ከአንተም በኋላ ዘርህ በትውልዳቸው። በእኔና በአንተ መካከል፥ ከአንተም በኋላ በዘርህ መካከል የምትጠብቋት ቃል ኪዳኔ ይህች ናት፤ ከእናንተ ወንድ ሁሉ ይገረዝ። የሰውነታችሁን ቊልፈት ትገረዛላችሁ፤ በእኔና በእናንተ መካከል ላለውም ቃል ኪዳን ምልክት ይሆናል። ሕፃኑንም በስምንተኛው ቀን ትገርዙታላችሁ፤» አለው። ዘፍ ፲፯፥፩-፱። አብርሃም ይህን ሥርዓተ ግዝረት የተቀበለው በእምነት ነው። በመሆኑም ወዲያው በቤተሰቦቹ ላይ ተግባራዊ አድርጐታል። እርሱም ራሱ በዘጠና ዘጠኝ ዓመቱ ተገዝሯል። ዘፍ ፲፯፥፳፫። ይህም የእምነት ምልክት ሆኖ እስከ ጥምቀተ ክርስትና አድርሷል። ምክንያቱም ግዝረት የጥምቀት ምሳሌ ነበርና ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «እግዚአብሔር አብርሃምን ሳይገዘር በእምነት እንደ አጸደቀው በእርሱ ላይ ይታወቅ ዘንድ ግዝረትን የጽድቅ ማኅተም ትሆነው ዘንድ ምልክት አድርጎ ሰጠው፤» ብሏል። ሮሜ ፬፥፲፩። በቈላስይስ መልእክቱም፦ «የኃጢአትን ሰውነት ሸለፈት በመግፈፍ በክርስቶስ መገረዝ በሰው እጅ ያልተደረገ መገረዝን በእርሱ ሆናችሁ ተገረዛችሁ። በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችኋል፤ በእርስዋም ከሙታን ለይቶ ባስነሣው በእግዚአብሔር ረዳትነትና በሃይማኖት ከእርሱ ጋር ተነሥታችኋል።» በማለት ተናግሯል። ቈላ ፪፥፲፩።
          አብርሃም ልጁ ይስሐቅን በመሠዊያ ላይ አጋድሞ ሊሠዋው እጁን ያነሣው በእምነት ነው። «እኔ ለእግዚአብሔር ብዬ ስሠዋው፥ እግዚአብሔር ደግሞ ለእኔ ብሎ ከሞት አሥነስቶ በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃል ያለኝን ቃል ኪዳኑን ይፈጽምልኛል፤» ብሎ አምኗል። ይኽንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «አብርሃምም እግዚአብሔር በፈተነው ጊዜ ልጁን ይስሐቅን ይሠዋው ዘንድ በእምነት ወሰደው። በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃል ብሎ ተስፋ ያናገረለትን አንድ ልጁን አቀረበው። እግዚአብሔር ከሙታን ለይቶ ሊያስነሣው እንደሚችል አምኖአልና፤» በማለት ተናግሯል። ዕብ ፲፩፥፲፯-፲፱።
፪፥፫፥፫፦ አብርሃምም ትንቢት ተነግሮለታል፤
          እግዚአብሔር፦ አብርሃምን፦ «ከሀገርህ ውጣ፥ ከዘመዶችህም ተለይ፤» ባለው ጊዜ፦ «የምድር አሕዛብ በአንተ ይባረካሉ፤ (አብርሃምን ያከበረ ያክብርህ እያሉ በአንተ ይመራረቃሉ)፤» ብሎታል። ዘፍ ፲፪፥፫። ይህም፦ በረከተ ሥጋን በረከተ ነፍስን የሚያድል፥ መርገመ ሥጋን መርገመ ነፍስን የሚያጠፋ አምላክ ኢየሱስ ክርሰቶስ ከእርሱ ወገን እንደሚወለድ የሚያመለክት ቃለ ትንቢት ነበር። እግዚአብሔር በአንድነት በሦስትነት ለአብርሃም ተገልጦ ወደ ድንኳኑ በገባ ጊዜም፦ «የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ወደ አንተ ተመልሼ እመጣለሁ፤» ብሎታል። ይህም ለጊዜው ይስሐቅ እንደሚወለድ የሚገልጥ ቃለ ትንቢት ሲሆን ለፍጻሜው ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእርሱ ወገን ማለትም የባሕርዩ መመኪያ ከሆነች ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ እንደሚወለድ የሚያጠይቅ ነበር። ዘፍ ፲፰፥፲።


Source: http://www.facebook.com/groups/180759695294706/doc/192983760738966/

No comments:

Post a Comment