13

.

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው::" የማቴዎስ ወንጌል 7: 4

"እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅናወተት ግዙ።" ትንቢተ ኢሳይያስ 55 : 1

Monday, September 19, 2011

ነገረ ማርያም ክፍል፦ ፮ -

መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው

፩፦ ማኅደረ  መለኰት፤
            ማኅደር የሚለው፦ በቁሙ ሲተረጐም፦ ማደሪያ ፥ሰፈር ፥ቤት፥ በኣት፥ የመኝታ ቦታ ፥ እልፍኝ ፥በታላላቅ ቤት ውስጥ የሚሠራ ልዩ ልዩ ክፍል ፥ ደጃፍና መስኮት ያለው ፥ድንኳን ማለት ነው። ቃሉ ማደሪያነት ላለው ቦታ ኹሉ የሚነገር ነው።

           መለኰት፦ ማለት ደግሞ፦ አምላክነት ፥ ፈጣሪነት ፥ አምላክ መኾን ፥ ፈጣሪ መኾን ፥ ወይም የአምላክ ባሕርይ ፥ ጠባይ፥ ኹኔታ ማለት ነው። በአጠቃላይ አነጋገር፦ አገዛዝን ፥ጌትነትን ፥ ባሕርይን ፥ አምላክነትን ፥ ክብርን ፥ ስምን ያመለክታል።
፩፥፩፦ አገዛዝ፤
            ቅዱስ ዳዊት፦ «እግዚአብሔር በሰማይ ዙፋኑን አዘጋጀ ፥(ንጉሥ በዙፋኑ ተቀምጦ እንደሚፈርድ ይፈርዳል) ፥ በመንግሥቱም ሁሉን ይገዛል (እንደ ጌትነቱ ሁሉን ይገዛል ) ፥ በሁሉ ይፈርዳል። ቃሉን የምትፈጽሙ ብርቱዎችና ኃያላን ፥ (ሕጉን የምትጠብቁ ፣ ትእዛዙን የምታከብሩ ጽኑአን ኃያላንም የምትሆኑ ነቢያትና ካህናት) ፥ የቃሉንም ድምጽ የምትሰሙ መላእክቱ ሁሉ፥ (ከምስአል ማለትም ከመለመኛ ፣ ከመማለጃ ፣ ከመማጸኛ፣ ከመጠየቂያ ቦታ ፣ ከቤተ እግዚአብሔር፣ ምሥጢር የምታውቁ)፥ እግዚአብሔርን አመስግኑት፤ ሠራዊቱ ሁሉ ፥ ፈቃዱን የሚያደርጉ አገልጋዮቹ ፥ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል። (እናንተ ብቻ ሳትሆኑ፦ ከሃሊነቱን ማለትም ሁሉን ቻይነቱን ፣ኃይሉን የሚገልጽባቸው ሠራዊተ መላእክት ፥ ሕጉን አምልኮቱን የሚጠብቁ ሊቃነ መላእክትም ያመሰግኑታል)።» ካለ በኋላ፦ «ውስተ ኲሉ በሐውርት መለኮቱ። ፍጥረቶቹ ሁሉ፦ በግዛቱ ሥፍራ ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል። አንድም የጌትነቱ አገዛዝ በአራቱም መዓዝን ምሉዕ ነው።» ብሏል። መዝ ፥ ፻፪ ፥፲፱ -፳፪። በዚህ ጥቅስ ላይ ግዕዙ መለኮት ያለውን አማርኛው አገዛዝ ብሎ ተርጉሞታል። በመሆኑም በሰማይና በምድር ለእርሱ የማይገዛ ፥ ለእርሱ የማይንበረከክ የለም።
            ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ፦ «በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው ፥ (መለኰት የተዋሐደውን ሥጋ፦ ወልድየ ንበር በየማንየ ፣ ልጄ በቀኜ ተቀመጥ አለው) ፥ ከስምም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ሰጠው፤ (መለኰት የተዋሐደው ሥጋ፦ በተዋሕዶ፦ አምላክ ፣ ወልድ ፣ እግዚእ መባልን ገንዘብ አደረገ)፤ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥ (መላእክትና ደቂቀ አዳም ይሰግዱለት ዘንድ) ፥መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው። ( አንደበት ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስ በአብ ጌትነት ያለ ፣ በክብር አንድ የሆነ ጌታ እንደሆነ ያምን ዘንድ ነው) ፤ ያለው ለዚህ ነው። ፊል ፪፥፱-፲፩።
፩፥፪፦ ጌትነት፤
            ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «እውነትን አውቀው በክፋታቸው በሚለውጡአት፥ በአመጸኛውና በኃጢአተኛው ሰው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር መቅሠፍት ከሰማይ ይመጣል። እግዚአብሔር ስለ ገለጠላቸው፥ እግዚአብሔርን ማወቅ በእነርሱ ዘንድ ግልጥ ነው። » በማለት በኃጥአን ላይ ስለሚመጣው መቅሠፍት ከተናገረ በኋላ ፦ « ወዘኢያስተርኢ እግዚአብሔር እምፍጥረተ ዓለም ይትዓወቅ በፍጥረቱ ለፍጥረቱ ፥ በሐልዮ ወበአአምሮ ፥ ወከመዝ ይትአመር ኃይሉ ወመለኮቱ ዘለዓለም። የማይታየው የእግዚአብሔር ባሕርይ እርሱም የዘለዓለም ኃይሉና ጌትነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ የፈጠረውን በማሰብና በመመርመር ይታወቃል።» ብሏል። ሮሜ ፩፥፲፰-፳። በዚህ ጥቅስ ላይ ግዕዙ መለኮት ያለውን አማርኛው ጌትነት ብሎ ተርጉሞታል።
፩፥፫፦ ባሕርይ፤
            ባሕርይ፦ በቁሙ ሲተረጐም የነገር ሁሉ ሥር ፥መሠረት ፥ምንጭ ፥መውጫ ፥መፍለቂያ ፥ መገኛ ፥ ጠባይዕ ማለት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቈላስይስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ፦ «ዑቁ ኢይኂጠክሙ በጥበበ ነገር ዘይየውሁ ለከንቱ ፥ በሥርዓተ ትምህርተ ሰብእ ለስሒተ ዝንቱ ዓለም ፥ በክርስቶስ ሕግ ያይደለ ፥በሰው ሠራሽ ሥርዓት ለከንቱ የሚያታልሉ ሰዎች በነገር ማራቀቅ እንዳያታልሏችሁ ተጠንቀቁ። በእርሱ ፍጹም መለኮቱ (ባሕርዩ) በሥጋ ተገልጦ ይኖራልና። (ፍጹም መለኮቱ በከዊን ተዋሕዷልና፥ በተዋሕዶ ከሁለት አካል አንድ አካል ፥ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ሆኗልና።» ብሏል። ቈላ ፪፥፰-፱፡፡
፩፥፬፦ አምላክነት፤
            አምላክ፦ በቁሙ ሲተረጐም፦ ፈጣሪ፥ ገዥ ፥ ፈራጅ ፥ዳኛ፥ሠሪ፥ቀጪ፥ፈላጭ ቆራጭ ማለት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በዳግሚት መልእክቱ፦ «በአእምሮቱ ለአምላክነ ወኢየሱስ ክርስቶስ እግዚእነ ፥ ዘበኃይለ መለኮቱ ወሀበ ለነ ኲሎ ምግባረ ፥ ዘይወስድ ኀበ ሕይወት ወጽድቅ ፤ ውእቱ ዘጸውአነ ውስተ ስብሐቲሁ ወውስተ ሠናይቱ። በመለኮቱ ኃይል (በአምላካዊ ሥልጣኑ) ለሕይወትና ለመልካም አምልኮ የምንሻውን ነገር ሁሉ የሰጠን ፥ (ለምጻሞችን አንጹ፣ አጋንንትን አውጡ፣ብሎ ገቢረ ተአምራትን የሰጠን)፥ እርሱንም በማወቅ በክብሩና በበጎነቱ የጠራን እርሱ ነው። (ይኸውም፦ ወደ ጌትነቱ ፥ወደ በጎነቱ ፥ ከሃሊነቱንና አምጻኤ ዓለማትነቱን ወደ ማወቅ ፥ አንድነቱንና ሦስትነቱን ማለትም ምሥጢረ ሥላሴን ወደ ማወቅ ፥ ከእመቤታችን ከነፍሷ ነፍስ ከሥጋዋም ሥጋ ነስቶ በተዋሕዶ ሰው መሆኑን ማለትም ምሥጢረ ሥጋዌን ወደ ማወቅ የጠራን የመረጠንም እርሱ ነው)።» ብሏል። ፪ኛ ጴጥ ፩፥፪-፫። በዚህም መለኮት የሚለው አምላክ ተብሎ ተተርጉሟል።
፩፥፭፦ ክብር፤
            ክብር፦ በቁሙ ሲተረጐም፦ ልዕልና ፥ልቆ መገኘት፥ ብልጫ፥ሹመት፥ሽልማት፥ታላቅነት፥ኀይል ፥ ብዕል ፥ብዙ ገንዘብ ማለት ነው። ይኽንንም በተመለከተ፦ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፦ «ውእቱ ዘጸውዐነ ውስተ ስብሐቲሁ ወውስተ ሠናይቱ። እኛን አስቀድሞ ወደ ጌትነቱ ፥ወደ በጎነቱ የጠራበት ነው።» ካለ በኋላ፦ «በዘቦቱ ነሐዩ ፥ ወነዐቢ፥ወንከብር፥በተስፋሁ እንተ ጸገወነ፤ ከመ በእንተ ዝንቱ ትኲኑ ሱቱፋነ ለመለኮተ ዚአሁ። በእርሱ በማመን ጸንተን በምንኖርበት ገንዘብ ፥ እርሱ በሰጠን ተስፋ፥ በዚህ የክብሩ ወራሾች ትሆኑ ዘንድ፤ » ብሏል። ፪ኛ ጴጥ ፩፥፬። በዚህ ጥቅስ ግዕዙ መለኮት ያለውን አማርኛው ክብር ብሎ ተርጉሞታል።
፩፥፮፦ ስም፤
            ስም፦ በቁሙ ሲተረጐም፦ ከባሕርይ ከግብር የሚወጣ፤ ቦታነትና አካልነት፥ህላዌና ሕይወት ያላቸውን ማናቸውም ኹሉ ፤ በየክፍሉና በየአካሉ፤ በየራስ ቅሉ ፤ በየአይነቱና በየመልኩ በየነገዱ፤ በየዘሩና በየአባቱ በየዘመዱ ተለይቶ የሚጠራበት፤የሚታወቅበት ነው። እግዚአብሔርም እንደ እግዚአብሔርነቱ የሚጠራበት አምላካዊ ስም አለው። ይኽንንም በተመለከተ፦ «መለኮትሰ ስም ዘአልቦ ብዕድና፤ መለኮት መለያየት የሌለበት ስም ነው፤» ይላል። ቅዱስ ቄርሎስ፦ መለኰት የሦስቱ መጠሪያ ስም ነው ብሏል።
፪፦ አባ ሕርያቆስ ስለ መለኰት፤
            አባ ሕርያቆስ፦ እመቤታችንን፦ ቅድስት ድንግል ማርያምን ባመሰገነበት ምስጋና በቅዳሴ ማርያም ላይ ስለ መለኰት በሰፊው ተናግሯል። እመቤታችንም ማኅደረ መለኰት ሆና መመረጧን አድንቋል። «መጠንና መመርመር የሌለበት እሳተ መለኮት በሆድሽ አደረ፤ በምድራዊ እሳት እንመስለው ዘንድ አይገባም፥ ለእሳትስ መጠን አለው ፥ ልክም አለው፤ መለኮት ግን ይህን ያህላል ፥ ይህንንም ይመስላል ፥ ሊባል አይቻልም። ለመለኮት እንደ ፀሐይና ጨረቃ ክበብ ፥እንደ ሰውም መጠን ያለው አይደለም ፥ ድንቅ ነው እንጂ፤ የሰው ሕሊና የመላእክትም አእምሮ በማይደርስበት በአርያሙ የሚኖር ነው እንጂ፤ ለመለኮት ወርድና ቁመት ፥ ላይና ታች ፥ ቀኝና ግራ ያለው አይደለም ፥ ግዛቱ (ጌትነቱ) በአገሩ ሁሉ ነው እንጂ፤ ለመለኮት በላይ ጠፈር በታችም መሠረት ያለው አይደለም ፥ ጠፈሩ እርሱ መሠረቱም እርሱ ነው እንጂ፤ ለመለኮት ከምድር ከውስጧ የሆነውን ያነሣ ዘንድ ፥ ማጎንበስ ራስንም ዝቅ ማድረግ ያለበት አይደለም ፥ለጴጥሮስ እንዳሳየው ሁሉ በእጁ የተያዘ ነው እንጂ፤» ብሏል።
            ታሪክ፦ የነቢያት አለቃ ሙሴ፦ እግዚአብሔርን፦ «አትተኛምን?» ብሎ ቢጠይቀው፦ «አዎ አልተኛም፤» ብሎታል። ቅዱስ ጴጥሮስም ፦ እንደ ሙሴ ቢጠይቀው፦ በዕንቊ ጽዋ ውኃ መልቶ ሰጠው። ገና ሳይጠጣ ወዲያው እንቅልፍ እንቅልፍ ብሎት ሲያንጎላጅ ከእጁ ወድቆ ተሰበረ፤ ሲነቃም፦ ውኃው ፈስሶ ፥ ጽዋው ተደፍቶ አገኘውና ደነገጠ። ጌታም፦ «እኔ፦ ይህን ዓለም የያዝኩት በመካከል እጄ (በእጄ መዳፍ ) ነው ፥ በመሆኑም በእኔ እንቅልፍ ካለብኝ ፦ ዓለሙ እንዲህ ያልፍ የለምን?» ብሎታል። ዳግመኛም « ይኽንን ዓለም እንደምን እንደያዝከው አሳየኝ፤» ቢለው፦ ዓለሙን በመሐል እጁ ይዞ ፥ እርሱን ደግሞ በመካከል አድርጐ አሳይቶታል።
            አባ ሕርያቆስ የመለኮትን ነገር ይበልጥ በማብራራት፦ «ለመለኮት በሚታይ ገንዘብ ፥ በሚወሰንም ገንዘብ ፥ ደረትና ፊት ፥ የኋላም ጀርባ ያለው አይደለም ፥ በነደ እሳት የተሸፈነ ነው እንጂ፤ ነደ እሳት ግን እርሱ ነው፥ መለኮትስ ንጹሕና ጹሩይ ብሩህም ነው፤» ብሏል። ቁ ፵፯-፶፫።
፫፦ ጽርሐ አርያም፤
            ጽርሐ አርያም፦ የእግዚአብሔር ማደሪያ ናት። ትርጉሙም፦ በሰማይ ያለ አዳራሽ ፥ ታላቅ ቤት ፥ ማለት ነው። ጌታ በተወለደ ጊዜ፦ ቅዱሳን መላእክት፦ «ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ፥ ሰላምም በምድር ፥ ለሰው ልጅም በጎ ፈቃድ ሆነ ፤» እያሉ ዘምረዋል። ሉቃ ፪፥፲፬። ይህም በሰማይ ባለ ማደሪያህ የምትመሰገን መለኮት ነህ፥ ሲሉት ነው።ጌታችንም በምትጸልዩበት ጊዜ ፦ በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፥ በሉ፤» ብሎናል። ማቴ ፮፥፰። በኦሪት ደግሞ፦ «ከቅዱስ ማደሪያህ ከሰማይ ጐብኝ ፥ ሕዝብህንም እስራኤልን ለአባቶቻችን እንደማልህላቸው የሰጠኸንንም ወተትና ማር የምታፈሰውን አገር ባርክ፤» የሚል ተጽፏል።ዘዳ ፳፮፥፲፭። ከዚህም ለላ በመጽሐፈ ነህምያ ላይ፦ «የሰማዮች ሰማይ፤» የተባለችው ጽርሐ አርያም ናት። ነህ ፱፥፮። ንጉሡ ሰሎሞንም ቤተ መቅደሱን ሠርቶ ከጨረሰ ፥ ታቦቱንም ካስገባ በኋላ፦ ወደ እግዚአብሔር የጸለየው። «በማደሪያህ በሰማይ ስማ፥ሰምተህም ይቅር በል፤» እያለ ነው። እግዚአብሔርም፦ «በሰማይ ሆኜ እሰማለሁ፤» ብሎታል። ፪ኛ ዜና ፮፥፲፪-፵፪ ፣ ፯፥፲፩-፲፰።
            ጽርሐ አርያም ከሰባቱ ሰማያት አንዷ ናት። ቅዱስ ዳዊት፦ «ወበቃለ እግዚአብሔር  ጸንአ ሰማያት ፥ በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ጸኑ፤ » እንዳለ፦ ባለማለፍ ጸንተው ፥ ለዘለዓለም የሚኖሩ ሰማያት ሰባት ናቸው። መዝ ፴፪፥፮። እነዚህም፦ መንበረ መንግሥት ፣ ጽርሐ አርያም፣ ሰማይ ውዱድ ፣ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ፣ ኢዮር ፣ ራማና ኤረር ናቸው።
            በሠለስቱ ምዕት ቅዳሴ፦ ጽርሐ አርያምን በተመለከተ፦ «መንበሩ በእሳት ክሉል ፥ ወማኅደሩ በማይ ጥፉር ፥ ወዲበ ተድባበ ቤቱ ኅንባበ ማይ ዘኢይትከዐው። ዙፋኑ በእሳት የተከበበ ነው ፥ ማደሪያውም በውኃ የተታታ ነው ፥ በቤቱም ዙሪያ ላይ የማይፈስ የውኃ መርገፍ አለ።» የሚል ተጽፏል። በማደሪያው ውስጥ ስላለው ነገር ሲያብራራም፦ «ከዙፋኑም ብልጭልጭታ ይወጣል ፥ ውስጡ እንደ ጋለ እሳት ነው፤ በውስጡ እንደ ክረምት ቀስተ ደመና ያለ ደገኛ ብርሃን አለ ፥ ዙሪያውም መብረቅ ነው። ከዚያም መንበር አጠገብ አራቱ እንስሳ (ገጸ ሰብእ ፣ ገጸ ላህም ፣ ገጸ ንስር ፣ ገጸ አንበሳ) ኅብሩ እንደ በረድ ነጭ የሆነ ሰፊ መንበር በራሳቸው እንደ ተሸከሙ ሆነው አሉ። በዚህ መንበር ዙሪያ ሃያ አራት ካህናተ ሰማይ (ሱራፌል) አሉ ፥ በፊታቸውም የበጉን ሥዕል ፥ ደም የተረጨች ልብስ ፥ የታተመ መጽሐፍም ያያሉ። ይህንንም መንበር በዞሩ ቁጥር ለዚያ ለበጉ ሥዕልና በደም ለታለለች ለዚያች ልብስ ለታተመው መጽሐፍም ሦስት ጊዜ ይሰግዳሉ። በአዳራሹም ድንኳን የምሥጋና ጢስ ይመላል ፥ከዚያም መንበር በታች ጐዳናው ሁለት የሆነ የብርሃን እና የነፋስ ባሕር ይፈልቃል፤ የአማልክት አምላክ በዚያ አለ ፥ የአጋዕዝትም (የጌቶች) ጌታ በዚያ አለ። በውጭ ይኖራል ፥ በውስጥም ይገኛል ፤ ያገኙት ዘንድ አይሄዱም ፥ በፈለጉት ጊዜም አይታጣም ፥ በያዙት ጊዜ አይዳሰስም ፥ ከሕሊና ልዩ ነውና።» የሚል ተጽፏል። ቁ ፶፫-፶፰።
            ቅዱስ አትናቴዎስም በቅዳሴው፦ «እንዳንተ ዙፋኑን በእሳት የጋረደ ማነው? በልብሱ የውኃ ሥዕል ያደረገ ማነው? ተራራዎችንስ እንዳንተ በሚዛን የመዘናቸው ፥ የባሕርንስ ውኃ በእፍኙ የሚሰፍር ማነው? እንዳንተ አዳራሹን (ማደሪያውን) በውኃ የሚታታ ፥ ዙሪያውንስ በእሳት የሠራ ማነው? በላይ ያለው የውኃ ጠፈር በጥበብህ ወደ እሳት ግድግዳ አይወርድም። በታች ያለው የውኃ ግድግዳም በአኗኗርህ በላይ ወዳለው ወደ ውኃው ጠፈር አይወጣም።» ብሏል። ቁ ፻፲፰። ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ደግሞ፦ «ሁሉ ከእርሱ ነው ፥ ሁሉም ስለ እርሱ ነው ፥ሁሉም የርሱ ነው ፥ ሰማይ በርሱ ነው ፥ ከሰማያት በላይ ያለ ሰማይም የርሱ ነው ፥የአርያም ሰፋት የክብሩ ዙፋን ነው ፥ የምድርም ስፋት የእግሩ መመላለሻ ናት። ፀሐይ የርሱ ነው ፥ ጨረቃም ከርሱ ነው ፥ ከዋክብትም የእጁ ሥራ ናቸው፤ ደመናትም መልእክተኞቹ ነፋሳትም ሠረገላዎቹ ናቸው ፥ እሳትም የቤቱ ግድግዳ ነው። የቤቱ ጠፈር ውኃ ነው፥ የዙሪያውም ጸፍጸፍ የበረድ ሰሌዳ ነው ፥ድንኳኖቹ ብርሃናት ናቸው። የመሠወሪያ መጋረጃውም የብርሃን መብረቅ ነው ፥ መመላለሻውም በአየር ነው» ብሏል። ቁ ፴፮ -፴፫። ( ጠፈር ማለት በቁሙ ሰማይ ማለት ነው ፥የቤትም ክዳን ወይም ጣራ ጠፈር ይባላል። ይኽንን በተመለከተ « እግዚአብሔርም፦ በውኃው መካከል ጠፈር ይሁን ፤ በውኃና በውኃ መካከል ማለትም፦ በሐኖስና በውቅያኖስ መካከል ይለይ፥ አለ፤ እንዲህም ሆነ። እግዚአብሔርም ጠፈርን አደረገ፤ ከጠፈር በላይና ከጠፈር በታች ያሉትንም ውኆች ለየ። እግዚአብሔር ያን ጠፈር ሰማይ ብሎ ጠራው።» የሚል ተጽፏል። ዘፍ ፩፥፮-፰። የቤትን ጣራ በተመለከተ ደግሞ፦ «ኦ እግዚእየ ኢየሱስ ክርስቶስ ፥አኮ ዘይደልወኒ ትባእ ታሕተ ጠፈረ ቤትየ ርኲስት ፤ አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ርኲስት ከሆነች ከቤቴ ጣራ በታች ትገባ ዘንድ የሚገባኝ አይደለም፤ » የሚል አለ። ሉቃ ፯፥፮። መታታት ማለትም፦ መሥራት ፥መጐንጐን ፥ ማክረር ፥ መግመድ ፥ መሸረብ ማለት ነው።)
            ነቢዩ ሕዝቅኤል፦ ሰባቱ ሰማያት ተከፍተውለት(ምሥጢር ተገልጦለት) የእግዚአብሔርን ራእይ አይቷል። በማየቱም መንበሩን ስለሚሸከሙ ኪሩቤል መልካቸውን ጭምር ተናግሯል። «የፊታቸው አምሳያ እንደ ሰው ፊት . . . . እንደ አንበሳ ፊት . . . . እንደ ላም ፊት . . . .እንደ ንስር ፊት . . . . ነበራቸው፤» ብሏል። እሳታውያንና በፊትም በጀርባም ባለ ብዙ ዓይኖች መሆናቸውን ከተናገረ በኋላ፦ «ከእንስሶች (ከኪሩቤል) ራስ በላይ የሚያስፈራ በረዶ የሚመስል የጠፈር አምሳያ በራሳቸው ላይ ተዘርግቶ ነበር። ከጠፈሩም በታች ክንፎቻቸው እርስ በርሳቸው ተቃንተው ነበር፤ ለእያንዳንዱም ገላውን የሚከድኑ ሁለት ሁለት ክንፎች ነበሩት። ሲሄዱም የክንፎቻቸው ድምፅ እንደ ብዙ ውኃ ድምፅ ፥እንደ ሁሉን የሚችል አምላክ ድምፅ ፥ እንደ ታላቅም ሠራዊት ድምፅ ፥ ሆኖ ሰማሁ፤ ሲቆሙም ክንፎቻቸውን ዝቅ ያደርጉ ነበር። በራሳቸውም ላይ ካለው ጠፈር በላይ ድምፅ ተሰማ፤ ሲቆሙም ክንፎቻቸውን ዝቅ ያደርጉ ነበር።» በማለት የተገለጠለትን ሰማያዊ ምሥጢር በዝርዝር አስቀምጧል። በመጨረሻም፦ «በራሳቸውም በላይ ካለው ጠፈር በላይ የሰንፔር ድንጋይ የሚመስል የዙፋን አምሳያ ነበረ፤ በዙፋኑም አምሳያ ላይ እንደ ሰው መልክ አምሳያ ነበረ። ከወገቡም አምሳያ ወደ ላይ የሚብለጨለጭ የወርቅ ምስያ አየሁ ፥ በዙሪያውም ፀዳል ነበረ። በዝናብ ቀን በደመና ውስጥ እንደ ቀስተ ደመና አምሳያ ፥ እንዲሁ በዙሪያው ያለ ፀዳል አምሳያ ነበረ። የእግዚአብሔር ክብር ምሳሌ መልክ ይህ ነበረ። ባየሁም ጊዜ በግምባሬ ተደፋሁ ፥ የሚናገርንም ድምፅ ሰማሁ፤» ብሏል። ሕዝ ፩፥፩-፳፫። ነቢዩ ኢሳይያስም እግዚአብሔርን በታላቅ ንጉሠ ነገሥት አምሳል ፥በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ ፥ ሱራፌልም ፦ «ቅዱስ ፥ቅዱስ ፥ቅዱስ » እያሉ እግዚአብሔርን በሰማይ ባለው ማደሪያው ሲያመሰግኑት አይቷል። ኢሳ ፮፥፩-፬። በሐዲስ ኪዳን ደግሞ፦ ቅዱስ ዮሐንስ፦ ኪሩቤልንም ፥ ሱራፌልንም በራእይ አይቷል። ራእ ፬፥፮-፲፩።
፬፦ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፤
            ቅዱስ ያሬድ፦ በአንቀጸ ብርሃን ድርሰቱ፦ እመቤታችንን፦ «ቅድስት ሆይ! ብፅዕት ነሽ ፦ የተመሰገንሽና የተባረክሽ ነሽ፥ የከበርሽና ከፍ ከፍ ያልሽ ነሽ ፥ የብርሃን መውጫ የሕይወት መሰላል ነሽ። አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ድንግል ማርያም ሆይ! ከተለዩ የተለየሽ የመለኮት ማደሪያ ነሽ። » እያለ ካመሰገናት በኋላ ፦ «ከፍጥረት ሁሉ ይልቅ የተከበርሽ ሆይ! አብ የወደደሽ ፥ ወልድ ያደረብሽ ፥ መንፈስ ቅዱስ ያረፈብሽ ተባልሽ። በምድር ላይ ከፍተኛ አርያምን የሆንሽ ፥ ከሰማያት በላይ ያለ የአርያም የልዑል ሥፍራ ምትክ አንቺ ነሽ፤» ብሏታል።
            በሰማይ ባለ በእግዚአብሔር ማደሪያ ሰባት የእሳት መጋረጃዎች ያሉት የእሳት ዙፋን አለ። እግዚአብሔር ወልድ ፥ አካላዊ ቃል ከሰማይ ወርዶ የእመቤታችንን ማኅፀን እንደ እሳት ዙፋን አድርጎ ተቀምጦባታል። ሰባቱን የሥጋና የነፍስ ባሕርያቷንም እንደ ሰባቱ የእሳት መጋረጃ አድርጓቸዋል። አራቱ የሥጋ ባሕርያት ፦ መሬት ፥እሳት ፥ ነፋስና ውኃ ሲሆኑ፦ ሦስቱ የነፍስ ባሕርያት ደግሞ፦ ለባዊነት (ማሰብ) ፥ነባቢነት(መናገር)፥ ሕያውነት (ዘለዓለማዊነት) ናቸው። የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆነችው ሰማይ፦ በተቀሩት ስድስት ሰማያት ታጥራ ተከብራ እንደምትኖር፦ እመቤታችንም ፩ኛ፦ በንጽሐ ሥጋ ፤ ፪ኛ፦ በንጽሐ ነፍስ ፤ ፫ኛ፦ በንጽሐ ልቡና ፤ ፬ኛ፦ በድንጋሌ ሥጋ፤ ፭ኛ፦ በድንጋሌ ነፍስ፤ ፮ኛ፦ በድንጋሌ ልቡና፤ ታጥራ ፥ታፍራ፥ተከብራ፥ትኖራለች።
            ቅዱስ ኤፍሬም፦ በውዳሴ ማርያም ድርሰቱ፦ እመቤታችንን፦ «ከቅዱሳን ክብር የማርያም ክብር ይበልጣል፤ የአብን ቃል ለመቀበል በተገባ ተገኝታለችና። መላእክት የሚፈሩትን  ፥ ትጉሆች በሰማያት የሚያመሰግኑትን ድንግል ማርያም በማኅፀንዋ ተሸከመችው። ይህች ከኪሩቤል ከሱራፌልም ትበልጣለች ፥ ከሦስቱ አካል ለአንዱ ማደሪያ ሆናለችና።» ብሏል። ምክንያቱም ኪሩቤል ቢሸከሙ መንበሩን ነው ፥ ሱራፌልም ቢያጥኑ መንበሩን ነው። እርሷ ግን በማኅፀኗ የተሸከመችው በእሳቱ መንበር ላይ የሚቀመጠውን እሳተ መለኰት ነው።
            ቅዱስ ዳዊት፦« እግዚአብሔር ጽዮንን መርጧታልና ፥ ማደሪያው ትሆነው ዘንድ ወድዶአታልና ፥ ይህች ለዘለዓለም ማረፊያዬ ናት፤ መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ አለ።» በማለት እመቤታችን ለማኅደረ መለኮትነት እንደተመረጠች አስቀድሞ በትንቢት ተናግሮላታል። መዝ ፻፴፩ ፥፲፫። ከዚህም ሌላ፦ «የአማልክት አምላክ በጽዮን ይታያል፤» በማለት እርሷን ዙፋን አድርጐ እንደሚገለጥም ተናግሯል። መዝ ፹፫ ፥ ፯። በሰማይ ያለ የእግዚአብሔር ዙፋን በውስጥ በአፍአ እሳት እንደሆነ ፦ እመቤታችንም፦ በውስጥ በአፍአ (በነፍስም ፥ በሥጋም)፦ እሳት ምሳሌው በሆነ በመንፈስ ቅዱስ የተከበበች ፥ የታጠረች ናት። «እንደ እሳት የተከፋፈሉ የእሳት ላንቃዎችም ታዩአቸው፤ በሁሉም ላይ ተቀመጡባቸው። ሁሉም መንፈስ ቅዱስን ተሞሉ፤» ይላል። የሐዋ ፪፥፫።
            የአሥራ አምስት ዓመት ብላቴና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ማኅደረ መለኮት ሆና መገኘቷ ፥ ቃላት የማይገልጡት ከመነገር በላይ ነው። ቅዱስ ኤፍሬም ፦ በውዳሴ ማርያም ድርሰቱ፦ « የአብ ቃል እናቱ ንጽሕት ድንግል ሆይ! ስለአንቺ የሚነገረውን ነገር መናገር የሚቻለው ምን አንደበት ነው፤ ኪሩቤል ለሚሸከሙት ንጉሥ፦ ዙፋኑ (ማደሪያው) ሆንሽ፤» ያለው ለዚህ ነው። አባ ሕርያቆስም፦ በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ፦ «ድንግል ሆይ! እሳተ መለኮት በሆድሽ ባደረ ጊዜ፦ ፊ ቱ እሳት ፥ ልብሱ እሳት ፥ቀሚሱ እሳት ነው እንደምን አላቃጠለሽም፤ ሰባት የእሳት ነበልባል መጋረጃ በሆድሽ ውስጥ ወዴት ተጋረደ? ወዴትስ ተዘረጋ? ከጐንሽ በቀኝ ነውን? ከጐንሽ በግራ ነውን? ትንሽ አካል ስትሆኝ። የሚያንጸባርቅ ነደ እሳት የሚከበው ኪሩቤል የተሸከሙት ዙፋን በሆድሽ ውስጥ ወዴት ተዘጋጀ? ወዴትስ ተተከለ? ታናሽ ሙሽራ ስትሆኝ።» እያለ ከሰማያዊው ማደሪያ ጋር እያነጻጸረ አድንቋል። ምክንያቱም እርሷ የእሳቱንም ዙፋን ፥ የእሳቱንም መጋረጃዎች ሆና ተገኝታለችና።

Source : http://www.facebook.com/groups/180759695294706/doc/183919981645344/

No comments:

Post a Comment