13

.

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው::" የማቴዎስ ወንጌል 7: 4

"እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅናወተት ግዙ።" ትንቢተ ኢሳይያስ 55 : 1

Tuesday, November 29, 2011

የቅዱስ ያሬድ ዜማ


የቅዱስ ያሬድ ዜማ
በመምህር አዲስ መሃሪ
የቦሌ መንበረ ብርሃን ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤ/ክ የቅኔ መምህር

ዜማ ማለት ቃናው መልካም የሆነ፣ ለጆሮ የሚጣፍጥና አእምሮን የሚመስጥ ነው፡፡ ስለዝማሬ (ዜማ) በኢትዮጵያ ከመናገራችን በፊት ዝማሬ በዓለም ላይ ምን ይመስል ነበር የሚለውን መዳሰሱ አስፈላጊ ነው፡፡ ዝማሬ በኦሪት በነአሮንና ሙሴ ዘመን በሌዋውያኑ በኩል ይፈፀም ነበር፡፡ ቅዱስ ዳዊትም መዘምራኑን በቀንና በለሊት መድቦ ያሰራቸው እንደነበር በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሶ እናገኘዋለን፡፡ 1ዜና መዋዕል ምዕ.15-16
ሦስቱ ዋንኛ የዜማ መደቦች
1ኛ--አራራይ
2ኛ--ግእዝ
3ኛ--ዕዝል ናቸው
እያንዳንዳቸው የሚዜሙበት  የራሳቸው የሆኑ ወራቶች አሉ፡፡
           1ኛ--አራራይ፤ በአቢይ ጾምና በጾመ ማርያም ከግእዝ ዜማ ጋር እየተቀላቀለ ይዜማል ለምሳሌ በቅዳሴ ማርያም ላይ ያለው ‹‹ሠራዊተ መላእክቲሁ ለመድኃኔአለም››  የሚለው የአራራይ ዜማ የሚዜምባቸው ወቅቶች በክረምት ከሰኔ 25 እስከ መስከረም 25፤ከህዳር ዘመነ አስተምህሮ እስከ ዘመነ ስብከትና በአቢይ ጾም አልፎ አልፎ ከግእዝ ዜማ ጋር እየተቀላቀለ ይባላል፡፡
           2ኛ---ግዕዝ፤ ጠንካራና ጎርነን ያለ ድምፀ-ዜማ ሲሆን የሚባልባቸው ወራቶችም ዐቢይ ጾም፣ ጾመ-ፍልሰታ፣ ዘመነ አስተምህሮ ናቸው ፡፡ሰፋ ያለውን የዝማሬ ቦታ የሚይዘው የግእዝ ዜማ ቢሆንም አራራይም ከላይ እንደተጠቀሰው ከግእዝ ጋር ጣልቃ እየገባ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ለምሳሌ --በደብረዘይት የሚዘመረው ዝማሬ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው አካባቢ በግእዝ ዜማ ተቀላቅሎበት ይገኛል፡፡
          3ኛ---እዝል፤ከአመት እስከ አመት የሚባል ወይም የሚዘመር ቢሆንም ከዘመነ ስብከት -እስከ አቢይ ጾም መግቢያ ፤ከትንሳኤ -እስከ ጰራቅሊጦስ ወይም በዓለ-ሃምሳ መጨረሻ ከመስከረም 25 -ህዳር 6 ድረስ ያሉት ወራቶች ልዩ የእዝል ቅዳሴ ፤የእዝል ድጓና የእዝል ዜማ በአብዛኛው የሚሰማባቸው ወቅቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሦስቱ የዜማ ዓይነቶች የሥላሴን አንድነትና ሦስትነት የሚያበስሩ ናቸው፡፡ ሦስቱም የዝማሬ ዓይነቶች እያንዳንዳቸው በአራት ይመደባሉ፡፡
                           1ኛ--የደስታ ጊዜ ዝማሬ (ዜማ) መዝ፤94-13
                           2ኛ-የሃዘን ጊዜ ዝማሬ (ዜማ) መዝ፤101-1-10
                           3ኛ--የጸሎት ጊዜ ዝማሬ (ዜማ) መዝ፤50-1-14
                           4ኛ-የአምልኮት ጊዜ ዝማሬ (ዜማ) መዝ፤65-1-5
ብለን በሦስት ከፋፍለን ማየት ይቻላል ፡፡ሦስቱም የዜማ ዓይነቶች ህሊናዊ እርካታን የሚሰጡ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህን ሦስቱን የዝማሬ ዓይነቶች እንደ የድምጽ መሳሪያ ተጫዋች ልበወለዳዊ ስም ሲሰጧቸው ይስተዋላል፡፡ በሙዚቀኞች አሰያየም ፤አንቺ ሆየ፤ትዝታ ፤ባቲ ተብለው እንዲጠሩ ተጽእኖ መፍጠራቸው ግልጽ ነው፡፡ ስለሆነም እነዚህ ጊዜያዊ የስምምነት ስያሜዎች አራራይ፤እዝል፤እና ግእዝ በሚባሉት የቅዱስ ያሬድ የዜማ ስልቶች እንዲሰየሙ ሁሉም የእውነተኛው ዜማችን ባለታሪክ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያድርግ እንላለን፡፡
   
 የአዘማመሩ ሥርዓት
የአዘማመሩ ሥረአትና ቋንቋው ማንኛውም ዓለም አቀፍ ሰው ሊዘምር ይችላል ፡፡ዝማሬ የቋንቋ ገደብ ሳይደረግበት ይዘመራል፡፡ ነገር ግን የአዘማመር ሥርዓቱም የድምጽ አወጣጥ ዘዴው መረን የለቀቀ ሊሆን አይገባም፡፡ በአጭሩ ለዛና ለከት የሌለው የጭፈራ ዜማ (ድምጽ) በእጅጉ መለየት ይኖርበታል፡፡ ማንም ሰው በሚችለውና በሚያውቀው ቋንቋመዘመር እንዳይቻል የሚያስገድደው የለም የዜማ ቀመሩና የኖታው የይዘቱ፤የጽፋቱ፤የቁርጡ፤የጭረቱ፤የአንብሩና የድርሱ ባጠቃላይ የዜማ ድምጽ አወጣጡ ሥርአተ መንፈሳዊ ገጽታውን የለቀቀና ትርጉም የለሽ ሊሆን አይገባም፡፡ አንድ ዜማ በማንኛውም ቋንቋ ይዘመር እንጂ መንፈሳዊ ቅኝትን  ማእከል ያላደረገ ከሆነና ሰዎችን እያፈናጠጠ ወደ ጭፈራ ገጸ ምድር የሚወስድ ከሆነ በመዝሙር ስም የተሰየመው (የዝማሬ ስም) ተሠርዞ ዘፈን በሚል ስም መጠራት ይኖርበታል፡፡
ያሬዳዊ ዜማ ከላይ በጠቀስናቸው ሦስቱ የዝማሬ አይነቶች ስር የሚካተት ሆኖ ዜማው የሚያተኩርባቸው ቃላቶች ደግሞ ሀለወተ እግዚአብሔርን፤ ነገረ መለኮትን፤ ምስጢረ ስላሴን፤ ምስጢረ ሥጋዌን፤ ሞተ ቅዱሳንን ና ተፈጥሮተ ዓለምን የሚያስቃኙ ናቸው፡፡  
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!
Source: "FENOTE BERHAN HIDAR - TAHISAS " PREPARED BY BOLE MENBERE BERHAN HOLYFATHER CHURCH SUNDAY SCHOOL

No comments:

Post a Comment