13

.

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው::" የማቴዎስ ወንጌል 7: 4

"እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅናወተት ግዙ።" ትንቢተ ኢሳይያስ 55 : 1

Saturday, December 3, 2011

በወርሐ ሕዳር የሚከበሩ በዓላት


ከቤተክርስቲያናችን አዋልድ መጻሕፍት ውስጥ በጥራዙ ትልቅ የሆነና በቤተክርስቲያን በዓመቱ ውስጥ የሚታሰቡትን እንዲሁም የሚከበሩትን በዓላት የሚያሳውቅ መጽሐፍ መጽሐፈ ስንክሳር ይባላል። ከዚህ ታላቅ መጽሐፍ ውስጥ በወርሐ ሕዳር ከሚከበሩ በዓላት ውስጥ የሚከተሉትን አቅርበንላችኋል። መልካም ንባብ!
ሕዳር 6 ቁስቋም
ጊዜው በ5 ዓ.ም ሲሆን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ከዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር አረማዊው ሔሮድስ ጌታችንን ሊገድለው በመፈለጉ በመልአኩ አሳሳቢነትና መሪነት ወደ ግብጽ ተሰዳለች። ምንም እንኳን ሔሮድስ 144000 ሕጻናትን የፈጀ ቢሆንም ሰው የሆነው አምላክ አምላክ ሲሆን ሰው የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስን ግን አላገኘውም ነበር። እርሱ ግን   ሁሉን ማድረግ የሚችል አምላክን ይዛ ሳለ ለምክንያት ተሰደደች። 3ዓመት ከመንፈቅ ያህል በስደት ከቆየች በኋላ (ራእ.12፡1-6) ሄሮድስ ከክፋቱ የማይመለስ ቢሆን መልአኩ ሰይፈ መዓቱን መዞ ታይቶት ተልቶ ቆስሎ ሞቷል። ከዚህ በኋላ ዮሴፍን የሕጻኑን “የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት ሞተዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑን እናቱንም ይዘህ ወደ እስራኤል አገር ሂድ ( ማቴ.2፡20) ብሎት ከምድረ ግብጽ ወጥተው በረሀ በረሀውን ተጉዘው በዚህ ዕለት ደብረ ቁስቋም ገብተዋል።
ሕዳር 7 የቅዱስ ጊዮርጊስ በዓል
ጊዜው በ4ኛው ምዕተ ዓመት ሲሆን በዚህች እለት በዓል መሰራቱ ስለ ሁለት ነገር ነው፤ አንደኛው በሕይወተ ሥጋ ሳለ ንጉሡ ዱድያኖስ በረሀብ ይሙት ብሎ የምትልሰው የምትቀምሰው ከሌላት መበለት ቤት አስገብቶ ከምሰሶው ቢያስረው ምሰሶውን አለምልሞ ቤቷን በበረከት መልቶ ለልጅዋም ዕውረ ዓይን ጽቡሰ እግር ነበረና ፈውሶላታል። ሁለተኛው ቅዳሴ ቤቱ የተከበረበት ዕለት ነው። የተሰራውም በአባት በእናቱ ቦታ ላይ ነው። ሥጋውንም ብላቴኖቹ ወደእዚያ አፍልሰውት ሕሙማንን ሲፈውስ ሙታንን ሲያነሳ ይኖር ነበር። ዲዮቅልጥያኖስ ሰይጣናዊ ቅንዓት አድሮበት አውህዮስን አጥፋ ብሎ ላከው። ቢሄድ ምዕመናን ለስዕሉ መብራት አብርተው ሲሳለሙት አገኘ። መብራቱን በሰይፉ ቆረጠው። ሳይታወቀው ስባሪው ከራሱ ላይ ወድቆ አቃጠለው። ሰውነቱ እንደሰነበተ አስክሬን ሸተተ። ሠራዊቱ በመርከብ ተሳፍረው ይዘውት ሲመለሱ ማዕከለ ባህር ሲደርሱ ሞተ። ከባህሩ ጥለውት ሄደዋል።
የሆነውን ነገር ቢነግሩት ሠራዊቱን አስከትሎ ሄደ። ከዓውደምህረት መንበሩን ዘርግቶ በትዕቢት ተቀምጦ ሳለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከቅዱስ ሚካኤል ጋር መጥቶ ከነመንበሩ ገልብጦታል። በመንበሩ እጀታዎች የነበሩ ሁለት ዘንጎች ዓይኖቹን አውጥተውት ታውሮ ሠራዊቱም ትተውት ሄደዋል። እርሱም ከነዳያን ጋር እየለመነ በኃሳር ሞቷል።
ሕዳር 12 በዓሉ ለቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት
ጊዜው በ1528 ዓ.ዓ ገደማ ሲሆን ቅዱስ ሚካኤል እስራኤልን ከምድረ ግብጽ እየመራ ማውጣቱን በማዘከር ነው። በያዕቆብ ልጅ በዮሴፍ ምክንያት እስራኤላውያን ወደ ግብጽ ከወረዱ በኋላ ዮሴፍን የማያውቅ ፈርዖን ነግሶ አገዛዙን አጸናባቸው፤ ፍርድ አጓደለባቸው እስራኤላውያንም ለ430 ዘመናት በስቃይ ኖሩ። እግዚአብሔርም የራሔልን እንባና ልቅሶ ምክንያት አድርጎ ሙሴን አስነስቶ ቅዱስ ሚካኤልን ልኮ በ10 መቅሰፍት 11ኛ ስጥመተ ባህር እስራኤልን ከባርነት አውጥቷቸዋል።
ሕዳር 13 ሲመተ መላእከት
ሕዳር 16 ጾመ ነቢያት
ጾመ ነቢያት ጾመ ድኅነት ይባላል። ጾመ ነቢያት መባሉ ነቢያት በግዝረታቸው በመስዋዕታቸው መዳን የማይቻላቸው ቢሆን ለአዳም በሰጠው ተስፋ ከሰማያት ወርዶ ከድንግል ተወልዶ በሕማሙ በሞቱ ያድነን ብለው በየዘመናቸው ግብር ገብተው ቀኖና ይዘው አንስእ ኃይለከ ፈኑ እዴከ ብለዋል፤ ጌታም የተናገረውን የማያስቀር ነውና አምስት ቀን ተኩል (አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን) 2ጴጥ. 3፡8 ሲፈጸም ከሰማያት ወርዶ ከድንግል ተወልዶ እንደሰው አድጎ በ33 ዓመቱ በዕለተ ዓርብ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ በከበረ ደሙ ፈሳሽነት በዓለመ ሥጋ በዓለመ ነፍስ ያሉትን አድኗልና ነው።  ጾመ ድኅነት መባሉም መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ ጠፍቶ ድኅነት የተገኘበት ስለሆነ ነው። ይህ ጾም ከበዓለ ልደት አስቀድሞ ያሉትን ስድስት ሳምንታትን እንጾማለን።
ሕዳር 21 ጽዮን
እግዚአብሔር አምላካችን እስራኤላውያንን ከፈርዖን ቀንበር በተዓምራት ካወጣቸው በኋላ ሙሴ በሲና ተራራ 40 ቀንና ሌሊት ቆይቶ በእግዚአብሔር እጅ የተቀረጹ ሁለት ጽላቶችን
በውስጣቸው እስራኤላውያን እንዲመሩባቸው 10ቱ ትእዛዛት የተጻፉባቸውን ጽላት ይዞ ሲመጣ እስራኤላውያን አምልኮተ እግዚአብሔርን ትተው፤ ውለታውን ረስተው በጣዖት አምልኮት ቢያገኛቸው ከካህን እጅ መስቀል እንዲወድቅ ደንግጾ ጽላቱ ከእጁ ወድቆ ጣዖቱን ደምስሶታል። እግዚአብሔርም እንደቀደሙት ዓይነት ሁለት ጽላት ቀርጾ እንዲያመጣ ባዘዘው መሰረት ጽላቱን እግዚአብሔር ባዘዘው መሰረት ሰርቶ አቅርቧል፤ እግዚአብሔርም አሠርቱን ትዕዛዛት ጽፎበታል። ይህም የሆነው ለምሥጢር ነው የቀደመው ጽላት የአዳም ምሳሌ ሲሆን የመጀመሪያው ሰው አዳም በታላቅ ክብር ተፈጥሮ ሳለ ክብሩን ሕገ እግዚአብሔርን በመጣስ ወድቋል፤ ከክብር ቦታው ተሰዷል። ሁለተኛው ጽላት ምሳሌ ከሰው ወገን የሆነች በእግዚአብሔር የተመረጠች፤ ምክንያተ ድኅነት የሆነችው ቅድስት ድንግል ማርያም ስትሆን የተጻፈው ቃል የቀዳማዊው ቃል ሦስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ የሆነው የጌታችን የመድኃኒታችን ምሳሌ ነው። (ዮሐ. 1፡1-3) ታቦተ ጽዮን 40 ዘመናት መናን ከደመና ውሐን ከጭንጫ እያፈለቀ በሠናይ መግቦት ምድረ ርስት አግብቷቸዋል፣ እግዚአብሔር በጽላቱ ላይ ያነጋግራቸው የልባቸውንም መሻት ይፈጽምላቸው ነበር።
ታቦተ ጽዮን በአፍኒንና ፊንሐስ በኃጢአት በካህኑ ኤሊ ቸልተኝነት ምክንያት ተማርካ በፍልስጤማውያን እጅ ከተማረከች በኋላ ፍልስጤማውያን አዛጦን ወስደው በቤተ ጣዖታቸው ከዳጎን ጋር አስቀመጧት። በማግስቱ ሊያጥኑለት ሊሰውለት ቢገቡ ዳጎን በታቦተ ጽዮን ፊት በግምባሩ ወድቆ አገኙት። ከቦታው መልሰውት ሄዱ። በሌላው ቀን ሲመለሱ እጅ እግሩ ተቆራርጦ ደረቱ ለብቻው ቀርቶ አገኙ ፤ ሰዎቹም በእባጭ ተመቱ። መቅሰፍቱ ቢጸናባቸው ወደጌት ወሰዷት። የጌት ሰዎችም እንዲሁ በመቅሰፍት ተመቱ። ወደ አስቀሎና ቢወስዷት “ልታስፈጁን ነው ወደ ሀገሯ መልሱልን” ብለው ጮሁ። ከሰባት ወር በኋላ  ወደ ሀገሯ ትመለስ ብለው ቀንበር ባልተጫነባቸው በሚያጠቡ ላሞች በሚሳብ አዲስ ጋሪ አድርገው የበደል መስዋዕት እንዲሆን በአምስቱ ከተሞቻቸው አምሳል አምስት የወርቅ አይጦች አድርገው ሰደዷት። ላሞቹ ወደ ግራ ወደ ቀኝ ሳይሉ ከኢያሱ እርሻ ደርሰው ቆመዋል። ታቦተ ጽዮንን ከሐውልተ ስምዕ አኑረው ሠረገላውን ፈልጠው ላሞቹን አርደው መስዋዕት አቀረቡ። ነገር ግን ሕዝቡ ታቦተ ጽዮንን በድፍረት በማየታቸው 5 ሺህ ያህሉ ተቀስፈዋል። ወስደውም በአሚናዳብ ቤት አድርገዋት ልጁ አልዓዛር 20 ዓመት አገልግሏታል።
 እግዚአብሔር ከበዓላቱ በረከትን ያድለን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
 ምንጭ፡ ፍኖተ - ብርሃን መጽሔት በቦ/መ/ብ/ቅ/እግዚአብሔር አብ ቤ/ክ ሰ/ት/ቤት የሚዘጋጅ የወርሐ ሕዳር - ታሕሳስ /2004 ዕትም

No comments:

Post a Comment