13

.

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው::" የማቴዎስ ወንጌል 7: 4

"እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅናወተት ግዙ።" ትንቢተ ኢሳይያስ 55 : 1

Tuesday, November 29, 2011

ትምህርተ - ሃይማኖት


በመምህር ፍቅረ ማርያም ባዘዘው
የቦ/መ/ብ/ቅ/እግዚአብሔር አብ ቤ/ክ የመጽሐፍ መምህር
ሃይማኖት አምነ - አመነ ከሚል የግእዝ ቃል የተገኘ ወይም የወጣ ሲሆን ትርጓሜውም ማመንና መታመን ማለት ነው፤፤ማመን ሲባል የማይታየውንና እንዲሁም የማይመረመረውን በርቀት ወይም በረቂቅነት ያለውን ይደረጋል ብሎ መቀበል ሲሆን መታመን ማለት ይሆናል ፤ ይደረጋል ብሎ በእምነት የተቀበሉትን እንዲሆን ፤እንዲደረግ ተግባራዊ ምላሽ መስጠት ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ሃይማኖት  - አጥንተን ወይም መርምረን በራሳችን አቅም ወይም ችሎታ የምንጠቀምበት የምንደርስበት ሳይሆን በእምነት የምንቀበለው ነው፡፡ በእርግጥ ሰው በተፈጥሮ እውቀቱ በፍኖተ አእምሮ በእግረ ልቡና አምላኩን ወደ ማወቅ ሊደርስ ይችላል ለዚህም አብርሃምን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ለዚህ ነገር ያበቃው ግን አጥንቶ ሳይሆን መጀመሪያ እምነቱን መግለፁን ያሳየናል፡፡
ስለዚህ በሰፋትና በጥልቀት ወደ ትምህርተ ሃይማኖት ከመግባታችን በፊት ከእውቀትና ከማመን መቅደም የሚገባውን ነገር ቅድሚያ በይፋ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ ይህም የብዙ ሰዎች ጥያቄ በመሆኑና፡፡ እንዲሁም እውቀትን ከእምነት በፊት ሲጠቀሙበት ስለሚስተዋሉ ነው፡፡ ነገር ግን መቅደም የሚገባውን ነገር አስካላስቀደምን ድረስ ሃይማኖት የሚለውን ነገር መረዳት ስለማይቻል ነው፡፡ በመሆኑም ከእውቀትና ከማመን ማን ይቀድማል ቢባል መልሳችን ምን ይሆን? እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አስተምሮ የሚቀድመው ማመን ነው፡፡ እንዲህ ይላል እግዚአብሔር ለአብርሃም ሲገለጥለት የማይታይ አምላክ እንደሆነ እንጂ ስሙ እግዚአብሔር እንደሆነ አልገለጠለትም ለነቢዩ ሙሴ በተናገረው ቃል መረዳት እንችላለን፡፡ ዘጸ.6፤23 እንዲህ ይላል ‹‹እግዚአብሔርም ሙሴን ተናገረው አለውም እኔ እግዚአብሔር ነኝ ለአብረሃም ለይስሐቅም ለያዕቆብም ሁሉን እንደሚችል አምላክ ተገለጥሁ፡፡ ነገርግን ስሜ እግዚአብሔር አልታወቀላቸውም ነበር፡፡››
በመሆኑም ሃይማኖት ተቀብለው (አምነው) የሚያውቁት እንጂ አውቀው የሚቀበሉትና የሚያምኑት አይደለም፡፡ ዮሐ1፤13 ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ስልጣንን ሰጣቸው እነርሱም ከእግዚብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ አልተወለዱም፡፡ ከተቀበሉት ካመኑበት በኋላ ሁሉንም የማወቅ ስልጣን ከእግዚአብሔር ይሰጣል መጀመሪያ ከሥጋና ከደም የተወለዱ ቢሆኑ ኖሮ ግን ወደ ማመን ባልቀረቡም ነበር፡፡ ከእግዚአብሔር የተወለዱ በሙሉ ቅድሚያ ወደማመን ይቀርባሉ፡፡ ዮሐ.6፤69 ‹‹ቅዱስ ጴጥሮስም እኛስ አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ እንደሆንክ አምነናል አውቀናልም›› ያስቀደመው እውቀት ሳይሆን እምነትን ነው ኤፌ.4፤13 ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረውን መመልከት ይቻላል፡፡ ‹‹ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት›› በማለት ቅድሚያ የሰጠው እምነትን እንጂ እውቀትን አይደለም ማንኛውም እምነት አለኝ የሚል ሰው ሁሉ ቅድሚያ እምነት ከሌለው እውቀቱ የትም አያደርስውም ብዙ አዋቂዎች አሉ መጽሐፍ ቅዱስን በሙሉ ከዳር እስከዳር ያነበቡ ያ እውቀታቸው ግን ለትችት ዳረጋቸው እንጂ ለእምነት አላበቃቸውም የእነአብርሃም ሕይወት እንዲሁም የሐዋርያት ትምህርት ለእኛ በቂያችን ነው፡፡ እግዚአብሔር በእምነት እንድንጓዝ ይርዳን፡፡
ይቆየን!!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment