ክፍል 4
ቅዱሳት መጻሕፍት
የጽሕፈት አጀማመር የጽሑፍን ጥበብ ለሰው ልጆች የገለጸው እግዚአብሔር አምላካችን ሲሆን መጀመሪያ ለሔኖክ በጸፍጸፈ ሰማይ ላይ ጽፎ አሳይቶታልና ቅዱሳት መጻሕፍት መጻፍ የጀመሩት ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር ኩፋሌ 5፡22-24 “… ከዚያ በኋላ ስሙን ሔኖክ አለው እርሱ አስቀድሞ በዚህ ዓለም ከተፈጠሩ ሰዎች ይልቅ መጽሐፍንና ትምህርትን ጥበብንም ተማረ። ሰዎች ሁሉ በየወራቸው እንደ ሥርዓታቸው የዘመኑን ጊዜ ያውቁ ዘንድ እንደ ወራቸው ሥርዓት የሰማይን ምልክት በመጽሐፍ ጻፈ። እርሱ አስቀድሞ ምስክርን ጻፈ።”ይላል ስለዚህም የመጀመሪያውን መጽሐፍ ሔኖክ ጻፈ።
በዘመናችን የተለያየ ይዘትና ዓላማ ያላቸው መጻሕፍት ይገኛሉ። እነዚህም መጻሕፍት በ3 ወገን እንመልከት፤
1. ቅዱሳት መጻሕፍት፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ እንጻፈለት “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።” 2 ጢሞ.3፡16-17 እንዳለ በእግዚአብሔር መንፈስ የተጻፉ ሁሉ ቅዱሳት መጻሕፍት ይባላሉ። ቅዱሳት መጻሕፍት በዓለማችን ላይ ካሉት ዓለማውያት መጻሕፍት በእጅጉን የሚለዩ የመጻሕፍት ዓይነቶች ሲሆኑ በግብረ መንፈስቅዱስ የተጻፉ በመሆናቸው ክብራቸውና ቅድስናቸው ልዩ ነው።
2. ርኩሳት መጻሕፍት፡ ክህደትን፣ ጥርጥርን፣ ኑፋቄን የሚያስተምሩ እና የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ተለይቶ በአምልኮተ ጣዖት፣ በገቢረ ኃጢአት እንዲኖር የሚያደርጉ መጻሕፍት ናቸው።
3. ምኑናት መጻሕፍት (ዓለማውያት መጻሕፍት)፡ እነዚህ መጻሕፍት ለመንፈሳዊ ሕይወት ጥቅም የሌላቸው ሲሆኑ እንደ ልብወለድ፣ የስነ-አእምሮ መጻሕፍት፣ የታሪክ መጻሕፍት ወ.ዘ.ተ ናቸው።
ቅዱሳት መጻሕፍት የምንላቸው፡
1. መጽሐፍ ቅዱስ እና
2. አዋልድ መጻሕፍት ሲሆኑ በዝርዝር እንደሚከተለው እንመለከታለን።
1. መጽሐፍ ቅዱስ
v የሁለት ቃላት ጥምረት ሲሆን ፡
o መጽሐፍ ማለት በአንድ ጥራዝ ተጠቃሎ የተሰበሰበ ጽሑፍ ሲሆን
o ቅዱስ ማለት በዕብራይስጥ ክድስ፣ በሱርስት ካዲህ፣ በግእዝና በዓረብኛ ቅዱስ ካለው ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም የተለየ፣ የከበረ ማለት ነው። ስለዚህም በቁም ትርጉሙ መጽሐፍ ቅዱስ ማለት የተለየ፣ የከበረ መጽሐፍ ማለት ነው።
v መጽሐፍ ቅዱስ የተለየና የከበረ (ቅዱስ) የተባለበት ምክንያት፡
o አስገኝው እግዚአብሔር ቅዱስ ነውና፤ (ዘሌ.19፡2 “ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ እንዲህ በላቸው፦ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ።”)
o ቅዱሳን ሰዎች የጻፉት በመሆኑና በመንፈስቅዱስ ገላጭነት ካልሆነ በቀር ማንም መተርጎምና መረዳት አይችልም። (2ጴጥ. 1፡ 20-21 “ይህን በመጀመሪያ እወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም፤ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።”)
o የቅዱሳን ክቡር ታሪክና ተጋድሎ ስለሚገኝበት
o የዕድሜው ርዝማኔና ዘመን የማይሽረው በመሆኑ (ኢሳ. 40፡8 “ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል፥ የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች”ማቴ.5፡18 “እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ፥ ከሕግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም፥ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ።” ማቴ. 24፡35 “ሰማይና ምድር ያልፋሉ፥ ቃሌ ግን አያልፍም።”)
o ስላለፈውና ስለሚመጣው ነገር በእርግጠኝነት በመናገሩ
o አንባብያኑና ሰሚዓኑን (የሚሰሙትን) ስለሚቀድስና ወደቅድስና ስለሚመራ (ራእ. 22፡7 “የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል የሚጠብቅ ብፁዕ ነው አለኝ።”)
v የመጽሐፍ ቅዱስ ዓላማው ሰዎች የእግዚአብሔርን ባህርይና ፈቃድ በማወቅ ከኃጢአት በመራቅ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጸጋና በረከትን በማግኘት እንዲኖሩ መንገዱን ማሳየትና መምራት ነው። እንዲሁም የሰው ልጅ ያሳለፈውን ታሪክ እና የሚመጣውን (መጻዕያኑን) በማሳወቅ ፍኖተ ቅዱሳንን እንዲከተል መምራትና ማስተማር ነው።
v መጽሐፍ ቅዱስ በሁለት (2) ክፍላት ተከፍሎ ይገኛል፤ የብሉይ ኪደን እና የሐዲስ ኪዳን ክፍላት ናቸው።
v ብሉይ ኪዳን ማለት ያረጀ፣ ያፈጀ ውል ስምምነት ማለት ነው። ብሉይ ኪዳን በመጀመሪያ በዕብራይስጥ ቋንቋ የተጻፈ ሲሆን ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በፊት ያለውን ዘመን ይገልጻል። ስለ ሥነ-ፍጥረት፣ ስለነገረ ድኅነት የተስፋ ቃሎችን፣ ስለሐዲስ ኪዳን የትንቢት ቃሎች፣ ሕገ-እግዚአብሔር ስለመሰጠቱ፣ ስለ ሕዝበ እግዚአብሔር እስራኤላውያን መንፈሳዊና ሥጋዊ ጉዞ፣ ወ.ዘ.ተ ይናገራል።
v በዘመነ በጥሊሞስ (በ284 ዓ.ዓ)የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ከዕብራይስጥ ቋንቋ ወደ ጽርዕ ቋንቋ ተተርጉመዋል። ከዚያም በ4ኛው መ.ክ.ዘ የተነሳው ታላቁ የቤተክርስቲያን አባት አባ ጄሮም ለ40 ዓመታት የዕብራይስጥ፣ የግሪክ ቋንቋዎችን በሚገባ በማጥናት መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ቮልጌት ቋንቋ (ሮማይስጥ) ተርጉሟል።
v በ70ው ሊቃውንት የተተረጎሙት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት አስቀድሞ በቀሳማዊ ምኒልክ ዘመን በ982 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ወደ ኢትዮጵያ እንደገባ ትውፊታዎ ታሪክ አለ። ይህም በሐዋ.ሥራ 8፡26 ላይ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ የኢሳይያስ መጽሐፍን እያነበበ መገኘቱ ኢትዮጵያ ከክርስትና ጊዜ አስቀድሞ ቅዱሳት መጻሕፍትን እንደምትጠቀም ያሳየናል።
v ቅዱሳት መጻሕፍትን መሰብሰብ የተጀመረው የመጀመሪያው መጽሐፍ ከተጻፈበት ጊዜ ጀምሮ መሆኑ ግልጥ ነው። ሆኖም ብዛታቸውንና ዓይነታቸውን ለይቶ ለማወቅ ሲባል በተለይ በሐዲስ ኪዳን ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። ከዚህም ሌላ በ325 ዓ.ም በኒቂያ በተካሄደው ጉባኤ ላይ እውነተኛ ቅዱሳት መጻሕፍት ለመሰብሰብ በተወሰነው መሰረት ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ በ367ዓ.ም በ39ኛው መልእክቱ ላይ የቅዱሳት መጻሕፍትን ቁጥር እና ዓይነት አስታውቋል። ከዚህ ጉባኤ በኋላ ቅዱሳት መጻሕፍት በአንድ መጠረዝ እንደተጀመረ ይነገራል። የሁሉም ቅዱሳት መጻሕትን መድብል (ጥራዝ) በአንድነት “መጽሐፍ ቅዱስ” ተብሎ ይጠራል። ይህም መጽሐፍ የ81 (ሰማንያ ወአሐዱ) መጻሕፍት መድብል ሲሆን ብዛቱም በ318ቱ ሊቃውንት የተወሰነ ነው። (ፍትሐ. ነገ. አንቀጽ 2) የብሉይ ኪዳን መጻሐፍት 46 ሲሆኑ የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት 35 ናቸው።
የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የሕግ፣ የታሪክ፣ የጥበብ(የቅኔ፣ የመዝሙር) እና የትንቢት ተብለው ሲከፈሉ የሐዲስ ኪዳን የወንጌል፣ የታሪክ፣ የትምህርት እና የትንቢት ተብለው ይከፈላሉ።2. አዋልድ መጻሕፍት
አዋልድ መጻሕፍት መሰረታቸውና አባታቸው መጽሐፍቅዱስ በመሆኑ ባህርያቸውም በአብዛኛው የሚወርሱት ከመጽሐፍቅዱስ ነው። አዋልድ የተባሉ መጻሕፍት በዓይነት፣ በዓይነታቸው ተመድበው ሲቆጠሩ ድርሳን፣ ተዓምር፣ ገድል፣ መጽሐፈ ታሪክ ይባላሉ። ሆኖም ዋና ዋናዎቹን ለምሳሌ ያህል እንደሚከተለው እንጠቅሳለን። ወንጌልን የሚመስለው ተአምረ ኢየሱስ፣ ግብረ ሐዋርያትን የሚመስለው ተአምረ ማርያም፣ ራእየ ዮሐንስን የሚመስለው ራእየ ማርያም፣ ኦሪት ዘዳግምን የሚመስለው ዜና አይሁድን፣ መዝሙረ ዳዊትን የሚመስለው መጽሐፈ ቅዳሴ፣ ድርሳነ ማኅየዊ፣ ድርሳነ ሚካኤል፣ መጽሐፈ መነኮሳት፣ ገድለ ጊዮርጊስ፣ ገድለ ተክለሃይማኖት፣ የሰሎሞንን ጥበብ የሚመስለው የሰማየ ሰማያትን፣… ወ.ዘ.ተ. ጥንታዊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከሰማንያ አሐዱ ቅዱሳት መጻሕፍት መሰረተ ሐሳብ የወጡ አዋልድ መጻሕፍት የሏትም፣ ወደፊትም አይኖራትም። ሁሉም አዋልድ መጻሕፍቶቿ ከመጽሐፍቅዱስ ሃሳብ ጋር አንድ የሆኑ፣ ከመጽሐፍቅዱስ የተወለዱ መጻሕፍት ናቸው።
የአዋልድ መጻሕፍት ጥቅም
አዋልድ መጻሕፍት ለሰው ልጆች የዕለት ተዕለት ኑሮና ሥነ-ምግባር እንዲሁም መሠረተ ሃይማኖት እጅግ ከፍተኛ ጥቅም አላቸው። እነዚህም መጻሕፍት፡
1. ከቅዱሳት መጻሕፍት ንባቡ ያጠረውን አስረዝመው
2. ከቅዱሳት መጻሕፍት እንደ ኀይለቃል በንባብ ተቃጥቶ ሳይሟላ የቀረውን አሟልተው
3. በቅዱሳት መጻሕፍት የተመሰለውን ምሳሌ ተርጉመው
4. በቅዱሳት መጻሕፍት የተጠቀሰውን ጥቅስ በበለጠ አብራርተው
5. ብሉያትንና ሐዲሳትን አስማምተው፣ ምስጢሩ የረቀቀውን አጉልተው፣ መሰረቱን ሳይለቅ ለሰው እንደሚረዳው እንደሚገባው ለመተርጎም የሃይማኖትን ምስጢር፣ የስነምግባርን(ትሩፋትን) ነገር መማሪያ እና ማስተማሪያ፣ መመከሪያ፣መምከሪያ በመሆን ከፍተኛ ጥቅም አላቸው።
አዋለድ መጻሕፍትን የሚጽፏቸው ቅዱሳን ጻድቃን፣ ሰማዕታት፣ ሊቃውንት (መምህራን) ናቸው።
የአዋልድ መጻሕፍት ዓይነት
በቤተክርስቲያናችን የሚገኙ አዋልድ መጻሕፍት ዓይነቶች ዋና ዋናዎቹ እንደሚከተለው ናቸው።
1. የትርጓሜ መጻሕፍት
የቅዱሳት (የቀኖናውያት) መጻሕፍትን ምስጢር የሚያስረዱና የሚተነትኑ ናቸው።
2. የመናፍቃን ምላሽ ላይ የተጻፉ ልዩ ልዩ መጻሕፍት
በተለያየ ዘመን የተነሱ መናፍቃን ለሚያነሷቸው የተሳሳቱ አስተሳሰቦችና እምነቶች መልስ ለመስጠት በየዘመኑ የተነሱ አባቶች የጿፏቸው መጻሕፍት ናቸው።
3. የጸሎት መጻሕፍት
በግልና በማኅበር ለጸሎት የሚያገለግሉትን መጻሕፍት ናቸው። እነዚህም መጽሐፈ ክርስትና፣ ውዳሴ ማርያም፣ ወ.ዘ.ተ
4. የሥርዓት መጻሕፍት
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተለያየ ቦታና ዘመን በርካታ ሥርዓቶች ተገልጸዋል። ከህብረተሰቡ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማዛመድ ዘርዘር ያሉ የአሰራር፣ የአኗኗር … ሥርዓቶችን የሚገልጹ መጻሕፍት ናቸው።
5. የተዓምራት መጻሕፍት
እግዚአብሔር በቅዱሳን ላይ እያደረ የሚሰራቸው ተዓምራት በርካቶች ናቸው። በመጽሐፍቅዱስ ውስጥ እግዚአብሔር ራሱ በቀጥታ ያደረጋቸው በወዳጆቹ ሰዎች አማካይነት ያደረጋቸው ብዙ ተዓምራት ተመዝግበዋል። እንደዚህ ሁሉ በተለያዩ ጊዜያት እና ቦታዎች ተዓምራት የተደረገባቸውን (እግዚአብሔር ድንቅ ስራን የሰራባቸው) የተዘገበባቸው መጻሕፍት ናቸው።
6. የገድላት መጻሕፍት
ገድል ትግል፣ ፈተና፣ ውጊያ፣ ሰልፍ፣ ድልና አክሊል እስኪገኝ ድረስ የሚደክሙት ድካም፣ የሚሰሩት ስራ፣ የሚቀበሉት መከራ፣ መንፈሳዊ ዜና፣ ታሪክ፣ የቅዱሳን መከራና ጸጋ፣ እንዲሁም ተጋድሏቸውን የሚናገር መጽሐፍ ነው።
የአንድን ሰማዕት ወይም ጻድቅ ስራና ተጋድሎ ዘርዘር ባለ ሁኔታ የያዘ መጽሐፍ ሲሆን የክርስቶስ አገልጋዮች ከክፉ ሰዎችና ከአጋንንት ጋር ያደረጉትን ተጋድሎ የሚገልጹ መጻሕፍት ናቸው። ጻድቁ ከመነሻው እስከ ፍጻሜው ያሳለፈውን ሕይወት የደረሰበት ፈተናና በገድል እንደተቀጠቀጠ በመጨረሻም ይህን ዓለም ድል አድርጎ ወደ ፈጣሪው የመሄዱን ነገር ያስረዳል።
በቤተክርስቲያናችን የሚገኙ አዋልድ መጻሕፍት
የመጽሐፉ ስም | ደራሲው | ማዕረግ/ ሀገር | የመጽሐፉ ይዘት |
ማር ይስሐቅ | ቅዱስ ማር ይስሐቅ | መነኮስ/ ሶርያ | ሥጋዊ ፈተናን ስለማሸነፍ |
ፊልክስዮስ | ቅ/ፊልክስዮስ | ኤጲስ ቆጶስ/ ሶርያ | ስለስጋዊ ፈተና አሸናፊዎች |
አረጋዊ መንፈሳዊ | ቅ/አረጋዊ | መነኮስ/ግብጽ | ስጋዊ ፈተናን በማሸነፍ የሚገኝ ክብር |
ድጓ | ቅ/ያሬድ | ካህን/ ኢትዮጵያ | በበዓላት የሚደርስ የዜማ መጽሐፍ |
ጾመ ድጓ | >> | >> | በዐቢይ ጾም የሚዘመር የዜማ መጽሐፍ |
ምዕራፍ | >> | >> | በወርኃ ጾም የሚደርስ የዜማ መጽሐፍ |
ዝማሬ | >> | >> | ከቅዳሴ በኋላ የሚዘመር የዜማ መጽሐፍ |
መጽሐፈ አንቀጸ ብርሃን | >> | >> | የእመቤታችን የምስጋና መጽሐፍ |
መጽሐፈ ቄዴር | ቅ/ፊልጶስ | >> | በንስሐ ጊዜ የሚጸለይ |
መጽሐፈ ብርሃን | ቅ/ዘርዐ ያዕቆብ | >> | ስለሥርዓተ ቤ/ክ፣ ነገረ ሃይማኖት የሚናገር መጽሐፍ። |
መጽሐፈ ሰዐታት | ቅ/ጊዮርጊስ | መነኮስ/ኢትዮጵያ | በቤተክርስቲያን ሌሊት በዜማ የሚጸለይ መጽሐፍ |
መጽሐፈ አርጋኖን | ቅዱስ ጊዮርጊስ | መነኮስ/ኢትዮጵያ | የእመቤታችንን ምስጋና የሚያትት መጽሐፍ |
መጽሐፈ አቡሻኽር | ቅ/አቡሻኽር | መነኮስ/ግብጽ | ስለዘመናት አቆጣጠር |
ድርሳነ ማርያም | ቅ/ሚናስ | ኤጲስቆጶስ/ኢትዮጵያ | ስለወላዲተ አምላክ አማላጅነትና ተዓምራት የሚያትት መጽሐፍ |
ድርሳነ ሚካኤል | ቅ/ማቴዎስ | ፓትርያርክ/ግብጽ | ስለቅዱስ ሚካኤል አማላጅነትና ተዓምራት የሚያትት |
ድርሳነ ባስልዮስ | ቅ/ባስልዮስ | ፓትርያርክ/ ቂሳርያ | ስለነገረ መላእክት የሚያስረዳ |
ገድለ ተክለሃይማኖት | ቅ/ዮሐንስ | እጨጌ/ኢትዮጵያ | ስለጻድቁ ተክለሃይማኖት ተጋድሎ፣ አማላጅነት እና ተዓምራት የሚያትት |
ውዳሴ ማርያም | ቅዱስ ኤፍሬም | ካህን/ ሶርያ | ስለእመቤታችን ምስጋና የሚያትት መጽሐፍ |
ቅዳሴ ማርያም | ቅ/ሕርያቆስ | ኤጲስ ቆጶስ/ግብጽ | የቅዳሴ መጽሐፍ |
ተዓምረ ማርያም | ቅ/ደቅስዮስ | ኤጲስ ቆጶስ/ ግብጽ | ስለእመቤታችን ተራዳኢነት የሚናገር |
ራእየ ማርያም | ቅ/ዮሐንስ | ወንጌላዊ/እስራኤል | ስለእመቤታችን ተራዳኢነትና አማላጅነት የሚናገር |
መልክዓ ማርያም | ቅ/ዘርዐ ያዕቆብ | ካህን/ኢትዮጵያዊ | የእመቤታችንን ምስጋና የሚናገር የመልክ ድርሰት |
መልክኣ ኢየሱስ | ቅ/ዓምደ ሐዋርያት | መነኮስ/ኢትዮጵያዊ | የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የማዳን ሥራና ምስጋና የሚናገር |
መልክዓ ሥላሴ | ቅ/ስብሐት ለአብ | መነኮስ/ኢትዮጵያ | የቅድስት ሥላሴን ምስጋና የሚያቀርብ መጽሐፍ |
ባሕረ ሀሳብ | ቅ/ድሜጥሮስ | ፓትርያርቅ/ግብጽ | የበአላትና የአጽዋማት ዘመን መቁጠሪያ መጽሐፍ |
አክሲማሮስ | ቅ/ኤጲፋንዮስ | ኤጲስቆጶስ/ቆጵሮስ | የሥነፍጥረት ጥንተ ታሪክ የሚያስረዳ መጽሐፍ |
ሥርዐተ ቤተክርስቲያን | ቅ/ዮሐንስ አፈወርቅ | ፓትርያርክ/ሶርያ | ስለቤ/ክ ሥርዓት የሚያስረዳ መጽሐፍ |
አዕማደ ምሥጢር | ቅ/ዮሐንስ አፈወርቅ | ፓትርያርክ/ ሶርያ | ስለአምስቱ አዕማደ ምሥጠር የሚናገር መጽሐፍ |
ዮሐንስ አፈወርቅ ድርሳንና ተግሳጽ | ቅ/ዮሐንስ አፈወርቅ | >> | የነገረ ሃይማኖት እና የሥነምግባር መጽሐፍ |
BETAM DES BILOGNAL,BEWNET!!!! BEZI MEHON LENE AYNETU BETAM MELKAM NEW!!
ReplyDelete