13

.

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው::" የማቴዎስ ወንጌል 7: 4

"እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅናወተት ግዙ።" ትንቢተ ኢሳይያስ 55 : 1

Friday, October 21, 2011

“የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፣ ያድናቸውማል” [መዝ 33፥7]


እግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፣ ያድናቸውማል” [መዝ 337]

በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት ሐምሌ 19 የቅዱስ ገብርኤል አመታዊ በአል ነው፡፡ ይህ ቀን ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ቅድስት እየሉጣንና ልጇን ቅዱስ ቂርቆስን ከሞት አደጋ እንደታደገበት የሚታሰብበት ዕለት ነው፡፡ የሐምሌ 19 ስንክሳርና የሐምሌ ወር ድርሳነ ገብርኤል እንዲህ ተርከውታል፡፡

በዘመነ ሰማእታት ከሐድያን ነገሥታትና መኳንንት በክርስቲያኖች ላይ መከራ አጽንተውባቸው ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ብዙዎች ሰማእትነትን ሲቀበሉ የተቀሩት አገር ጥለው ተሰደዱ፡፡ እየሉጣም የሦስት ዓመት ህፃን የነበረውን ቅዱስ ቂርቆስን ይዛ ሸሸች በዚያም የሸሸችውን መኮንን አገኘችው ሰዎችም ነገር ሰሩባት ወደእርሷ አስቀረባት እና ስለ አምልኮ ጠየቃት እርሷም መኮንን ሆይ ዕድሜው ሦስት አመት የሆነው ህፃን አለ አማልክቶችህን ማምለክ መልካም እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ያስረዳን ዘንድ እሱን ጠይቅ አለችው፡፡

ህፃኑም ወዳለበት ጭፍራውን ልኮ ወደእርሱ አስመጣው ህፃኑም ፊቱ ብሩህና ደስተኛ እንደሆነ አየውና አንተ ደስተኛ ህፃን ሆይ እንዴት ነህ አለው፡፡ ህፃኑም መልሶ አዎ ለኔ ተጠብቆልኛል ላንተ ግን ሐዘንና ለቅሶ ጥርስ ማፋጨትም ነው፡፡ መጻሐፍ ለዝንጉዎች ተድላ ደስታ የላቸውም ብሏል እና አለው፡፡ እግዚአብሔር ኃይልና ንግግርን ሰጥቶታልና ብዙ ተናገረ በዚያም ያሉትን እስካስደነገጣቸው ድረስ ንጉሱን መኳንንቱንና ጣኦታቱን ረገማቸው፡፡ ከብርታቱም የተነሳ አደነቁ፡፡ መኮንኑም በአፈረ ጊዜ በያይነቱ በሆነ ስቃይ ታላላቆች የማይችሉትን ታላቅና አስጨናቂ የሆነ ስቃይን አሰቃየው እናቱንም ከእርሱ ጋር አሰቃያት፡፡ እግዚአብሔር ያለ ምንም ጉዳት ያነሳቸው ነበር፡፡ ብዙዎች አህዛብም ይኸንን አይተው አደነቁ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምነው በሰማእትነት ሞቱ፡፡ የሰማእትነትንም አክሊል ተቀበሉ፡፡

በህፃኑም ላይ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ አደረበት፡፡ ታላላቅ ድንቆችና ተአምራቶችንም አደረገ ብዙዎች በሽተኞችንም አዳናቸው፡፡

መስፍኑም በውስጡ ሰም፣ ጨው፣ ባሩድ፣ ሙጫ፣ የዶሮ ማር፣ እርሳስ፣ ብረት፣ ቅንጭብ፣ ቁልቋል ጨምራችሁ ታላቅ የብረት ጋን አንጡልኝ ብሎ ጭፍሮቹን አዘዛቸው፡፡ ጭፍሮቹም እንዳዘዛቸው ካአደረጉ በኋላ ያዘዝከንን ሁሉ ፈጽመን እሳቱ ነዶ ፈልቷል፡፡ ድምፁ እንደነጐድጓድ ይጮኸል ወላፈኑም እንደጸሐይ ነጸብራቅ በሩቁ ይጋረፋል፡፡ የፍላቱም ኃይል 14 ክንድ ያኽል ከፍታ ወደ ላይ ይዘላል፡፡ እንግዲህ በውስጡ የሚጣሉትን እዘዝ አሉት በዚህ ጊዜ ህፃን ቂርቆስና እናቱ እየሉጣ ክርስቶስ ሥም ስለሚያምኑ አስረዋቸው ነበርና ከፍላቱ ሊጨምሯቸው ከእስር ቤት አወጧቸው፡፡ በዚያም ፍላቱ ወደላይ በሚዘል ብረት ጋን ውስጥ ለመጨመር ሲወስዷቸው የነዚህን ቅዱሳን አሟሟት ያዩ ዘንድ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲሰበሰቡ አዘዛቸው፡፡ በዚህን ጊዜ ቅድስት እየሉጣ የፍላቱን ጩኸት በሰማችና ባየች ጊዜ ተሸበረች፡፡ ተዘጋጅቶላት ከነበረው ክብር ልታፈገፍግ ሞከረች፡፡ ልጇ ቅዱስ ቂርቆስ ግን እናት ሆይ ከዚህ የብረት ጋን ግርማ የተነሳ አትፍሪ ድንጋጼም አይደርብሽ አናንያንና አዛርያን ሚሳኤልንም እግዚአብሔር ከእቶነ እሳት እንዳወጣቸው ሁሉ እኛንም ከዚህ ከብረት ጋን ሊያወጣን ችሎታ ያለው መሆኑን አትጠራጠሪ፡፡ እናት ሆይ ከዚህ ከሚያልፈው ዓለም ጭንቅና መከራ ለመዳን ስትይ በማያልፈው ዘላለማዊ እሳት ለመቀጣት ትመርጫለሽን ይኽስ አይሆንም ይቅርብሽ፡፡ በአሁኑ ጊዜ እግዚአብሔር በመካከላችን አለና ይረዳናል፡፡ እናት ሆይ ሶስናን ከእደ ረበናት /መምህደራነ አይሁድ/ ዳንኤልን ከአፈ አናብስት ያዳነ እርሱ እኛንም ከጋን ፍላት ያወጣናል፡፡ ይልቁንም እግዚአብሔር በዚህ የብረት ጋን ውስጥ ግዳጃችንን ልንፈጽም ፈቅዶ ከሆነ ኢዮብ ንብረቱንና ገንዘቡን ልጆቹንና ሚስቱን በመጨረሻም የተፈጥሮ አካሉን ባሳጣው ጊዜ እግዚአብሔር አመሰግነዋለሁ እግዚአብሐር ሰጠ እግዚአብሔር ነሳ እግዚአብሔር እንደወደደ አደረገ  ከማለት በስተቀር ምንም የተናገረው ነገር እንደሌለ ሁሉ እኛም የሱን ዓላማ በመከተል ይኽንን መከራ ልንታገስ ይገባናል፡፡ ነገር ግን እናቱ በዚህ ምክር ልትጽናና ባለመቻሏ ቅዱስ ቂርቆስ ዐይኑን ወደ ሰማይ አቅንቶ አቤቱ አምላክ ሆይ ይችን ባሪያህን ከርስትህ የምትለያት ከሆነ ከባለሟልነትህ መጽሐፍ ፋቀኝ፤ አቤቱ አዝመራውን አቃጥለህ ፍሬውን ልትባርክ ትወዳለህን ይኽን እንዳታደርግ ግን ቸርነትህ ትከለክልኸለች፡፡ አቤቱ እንጨቱን ቆርጣችሁ አንድዱት ቅጠሉን ግን ጠብቁት ብለኽ ልታዝ መለኮታዊ ባሕሪህ አይደለም፡፡ ነገር ግን እንጨቱንም ቅጠሉንም በአንድ ጠብቁት ብለኽ ታዝዛለኽ እንጂ፡፡ እንግዲህ በዚህ ምክንያት ይኽንን ያየ ሁሉ ማዳን የሚችል አምላክ ቢኖራቸውስ ኖሮ ከእሳት ባልሸሹም ነበር ብሎ አይጠራጠር፡፡ አቤቱ ዲያብሎስም ከባለስልጣኑ ይልቅ እኔ በረታሁ ቅዱሳኖቹንም ድል ነሳኋቸው ብሎ እንዳይመካ ከመንጋውም አንድ በግ ቀማው በማለት እንዳይደነፋ ለእናቴ ጽኑ የሆነ ኃይለ መንፈስ ቅዱስን ስጣት ብሎ በጸለየ ጊዜ ዲያብሎስ ከእየሉጣ አጠገብ ብን ብሎ ጠፋ፡፡ ከዚህ በኋላ ቅድስት እናቱ በሰማያዊ መንግሥት አባት የሆንከኝ ልጄ ሆይ ጌታኽ ኃይልን ሰጥቶኛልና የሚጠብቀንን ገድላችንን ፈጽመን ድል እናድርግ እነሆ በብረት ጋን ውስጥ የሚነደውን እሳት በማይበት ጊዜ በለምለም /በምንጭ/ ላይ እንደሚወርድ ጠል ሆኖ አይቸዋለሁና አለችው፡፡ እኒኽም ቅዱሳን ይኽንን በሚነጋገሩበት ጊዜ በውስጡ አንገትን የሚቆለምም ልብንም የሚያቀልጥ ሆድን የሚሰነጥቅ ሥርን የሚበጣጥስ መሳሪያ ካለበት የብረት ጋን ውስጥ ጨመራቸው፡፡ ከዚህ በኋላ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ከሰማይ ወረደና የብረቱን ጋን እሳት አጠፋው፡፡ ከቅዱሳኑም አንዳቸውንም ሳያቃጥላቸው የብረቱ ጋር ማቃጠሉና መፍላቱ ጸጥ አለ፡፡ ወንድሞቻችን ሆይ እንግዲህ በጭንቃቸው ጊዜ ገድላቸውን እስኪፈጽሙ ድረስ ይህ መልአክ ከሰማእታትና ከጻድቃን ጐን እንደማይለይ እወቁ ለኃጥአንም ኃጢአታቸውን ይቅር ይላቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ይጸልይላቸዋል፡፡ እኛም የዚህ የሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል በአሉን እያከበርን አማላጅና ወዳጅ እናድርገው፡፡ በዚህም በሚመጣውም ዓለም ሊረዳን ይችላልና፡፡

ዳግመኛም መስፍኑ ሐሳቡ ሳይሳካለት ስለቀረ 14 የሾሉና የጋሉ የብረት ችንካሮች አምጥተው ሰባቱን በእናቱ በኢዮልጣ አካል ሰባቱን በራሱ በቂርቆስ አካል ማለት ሁለቱን በጆሮዎቹ ሁለቱን በዐይኖቹ ሁለቱን በአፍንጫዎቹ አንዱን በልቡ ይቸነክራቸው ዘንድ ጭፍሮቹን አዘዘ፡፡ ዳግመኛም የህፃኑን የእራስ ቆዳ ገፈው እሳት ውስጥ ይጨምሩ ዘንድ አዘዘ፡፡ አሁንም መልአኩ መጥቶ ይህንን መከራ ከእርሱ አራቀለት፡፡ ቀጥሎም በመቃን ውስጥ ጨምረው በገመድ እንዲገትቱት አዘዘ፡፡ በዚህም ጊዜ መልአኩ አዳነው፡፡ ሕዝቡም ይህንን ሁሉ ተአምር ባዩ ጊዜእግዚአብሔር አመሰገኑት ቅዱስ ገብርኤልንም አከበሩት፡፡  
ቅዱስ ቂርቆስና ቅድስት እየሉጣ ብዙ መከራ ከተቀበሉ ጥር 15 በሰይፍ ተመትተው ስማትነትን ተቀብለዋል።

የሊቀ መላእክት የቅዱስ ገብራኤል   ቅዱስ ቂርቆስና የእናቱ የቅድስት እየሉጣ ተራዳኢነት ጸሎት አይለየን።

No comments:

Post a Comment