13

.

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው::" የማቴዎስ ወንጌል 7: 4

"እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅናወተት ግዙ።" ትንቢተ ኢሳይያስ 55 : 1

Friday, October 21, 2011

ነገረ ቅዱሳን ክፍል 6


በዜማና በድርሰታቸው ሊቅ የተሰኙ ሊቃውንት
ሀ. ሊቁ ቅዱስ ያሬድ
v  ያሬድ ማለት ሙራድ ማለት ነው። ትውልዱ አክሱም ነው። የሌዋውያን ዘር ነው። አባቱ አዳም ሲባል ካህን ነበር፤ እናቱ ታውክልያ ትባላለች። በ505 ዓ.ም ተወለደ። ለትምህርት ሲደርስ ይስሐቅ ለሚባል መምህር ሰጡት ከእርሱ ፊደልን አጥንቶ መዝሙረ ዳዊት ሊማር ለእናቱ ወንድም (ለአጎቱ) ለመምህር ጌድዮን ሰጡት። 7 ዓመት አንዲት ቀለም ማጥናት አልቻለም። ቢገስጹት ሸሽቶ ሄዶ ከዛፍ ጥላ ቢያርፍ ትል ከዛፍ 6 ጊዜ ወድቃ በ7ኛው ስትወጣ አይቶ እኔስ ብተጋ ትምህርቴ ይገለጽልኝ የለምን ብሎ ሄዶ በአንድ ቀን ብሉይና ሐዲስን ጨርሷል።
v  ጌታችንም ከገነት 3 አእዋፍ ልኮለት በተመስጦ ስብሐተ መላእክትን ሰምቶ “ሃሌሉያ ለአብ፤ ሃሌሉያ ለወልድ፤ ሃሌሉያ ወለመንፈስቅዱስ” በማለት በዜማ ምስጋናን አቅርቧል። ይህንን ድርሰቱን ከአርያም የሰማሁት ነው ሲል “አርያም” ብሎታል። አእዋፍ ፀሐይ እንዳያቃጥለው ብለው በክንፋቸው ይጋርዱት ነበር።
v  ንጉሥ አጼ ገብረመስቀል ከፍቅር የተነሳ ከቤተመንግስታቸው ያኖሩት ነበርና አንድ ቀን ከፊታቸው ቆሞ ስብሐተ እግዚአብሔርን ሲያሰማቸው በተመስጦ ሆነው ሳይታወቃቸው ጦራቸው እግሩን ወጋው እርሱ ግን አልተሰማውም ነበር። እርሳቸውም ደንግጠው የደምህን ዋጋ ወርቅ ልስጥህ ሲሉት አልሻም ወደገዳም እንድሄድ አሰናብቱኝ ብሎ ግድ ስላለ ገዳም ሄዶ በታቦተ ጽዮን ላይ እጁን ዘርግቶ “አንቀጸ ብርሃንን” ንባብና ዜማውን ተናግሯል። በዚህ ጊዜ አንድ ክንድ ያህል ከመሬት ከፍ ብሏል።
v  5 ታላላቅ የዜማ መጻሕፍትን ደርሷል። እነርሱም ድጓ፣ ጾመ ድጓ፣ ምዕራፍ ዝማሬና መዋስዕት ናቸው። 5ቱ ጸዋትወ ዜማ በመባል ይታወቃሉ።
v  ደቀመዛሙርቱን አስከትሎ ተከዜን ተሻግሮ ከሰሜን ገዳማት በአንዱ በጾምናበጸሎት ተወስኖ ቃልኪዳንን ተቀብሎ ብሄረ ህያዋን ሄዷል።
v  የቅዳሴ ማርያም፣ ውዳሴ ማርያምን ከሰኞ እስከ ቅዳሜ በአራራይ የእሑድን በእዝል ዜማ አድርሷል። ቅኔን የጀመረውም እርሱ ነው።
v  ዜማው 3 ዓይነት ሲሆን ግእዝ፣ እዝል እና አራራይ ናቸው። ግእዝ የአብ፣ እዝል የወልድ፣ አራራይ የመንፈስቅዱስ ምሳሌ ነው።
ለ. ሊቁ ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
v  ከ1358 እስከ 1417 ዓ.ም ድረስ የነበረ ቅዱስ አባት ሲሆን ከቅዱስ ያሬድ ቀጥሎ ከተነሱ የያሬድ ደቀመዛሙርት 8ኛ ደቀመዝሙር ናቸው። እኚህ አባት የጸዋትወ ዜማ ሊቅ ከመሆናቸውም ሌላ ተደናቂነትን ያተረፉ ከ40 በላይ የነገረ - ሃይማኖት መጻሕፍት ጽፈው ለቤተክርስቲያን አስረክበዋል። የ15ኛው ክፍለ ዘመን ሐዋርያ ሲሆኑ ቤተክርስቲያን የምትገለገልባቸውን ሰዓታትና አርጋኖን ደርሰዋል። “ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ” በመባል ይጠራሉ ይህም በነገረ ሃይማኖት ትምህርት የበቁ አባት ስለመሆናቸው ነው።

ሐ. ቅዱሳን ሊቃነ ጳጳሳት
v  ጳጳስ የሚለው ቃል በግሪክ “ኤጲስ ቆጶስ” ማለት ሲሆን መሰረታዊ ትርጉሙ ጠባቂ፣ ተቆጣጣሪ ማለት ነው።
v  የካህናትና የምዕመናን፣ የሰማያውያንና የምድራውያን አንድነት የሆነችውን ቤተክርስቲያን በሃይማኖት መርተዋል። ከቤተክርስቲያን ጠላቶች ከአህዛብና ከመናፍቃን ጋር ታግለዋል፤ በአጠቃላይ ጳጳሳቱ፣ መነኮሳቱ፣ ቀሳውስቱ፣ ዲያቆናቱ፣ ምዕመናኑ በቤተክርስቲያኗ ላይ የመጣው ፈተና ሁሉ ፈትኗቸው ድል ነስተዋል።
v  በኢትዮጵያ ሊቃነ ጳጳሳት ይሾሙ የነበረው ከእስክንድርያ (ግብጽ) ነበር። ነገር ግን ከአባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን (ፍሬምናጦስ) በኋላ ኢትዮጵያውያን ሊቃነ ጳጳሳት (ፓትርያርክ) መሾም ተጀምሯል። ኢትዮጵያ የፓትርያርክነት መዓረግ በራሷማግኘት ከቻለች ሃምሳ ዓመት ሆኗታል።

ጥቅስ፡
V  በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፥ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ።” ሐዋ. 20፤28-30
V  ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሕዝቤን ስለሚጠብቁ እረኞች እንዲህ ይላል። በጎቼን በትናችኋል አባርራችኋቸውማል አልጐበኛችኋቸውምም እነሆ፥ የሥራችሁን ክፋት እጐበኝባችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። ት.ኤር.23፡2
V  ጠቦቶቼን ጠብቅ አለው። ሦስተኛ ጊዜ። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን? አለው። ሦስተኛ። ትወደኛለህን? ስላለው ጴጥሮስ አዘነና። ጌታ ሆይ፥ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ኢየሱስም፦ በጎቼን አሰማራ። ዮሐ. 21፡17

እነዚህም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት እንደሚከተሉት ይሆናሉ፤
1.    አባ ሠላማ ከሳቴ ብርሃን (ፍሬምናጦስ)
v  አባታቸው ምናጦስ እናታቸው ማርያም ሠናይት ይባላሉ። ሕዳር 26 ቀን በ222 ዓ.ም በግሪክ ጢሮስ በተባለ ቦታ ተወለዱ። በ330 ዓ.ም አብርሃና አጽብሃ የተባሉ ኢትዮጵያውያን ነገሥታትን አስተምረው አጥምቀዋል። በ331 ዓ.ም በእለተ እሑድ በግንቦት 16 ቀን ጵጵስናን ከቅዱስ አትናቴዎስ ተሹመው ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል።
v  በነሐሴ 26 ቀን በ150 ዓመታቸው በ352 ዓ.ም አርፈዋል።
   
2.   ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ቀዳማዊ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
v  ሐምሌ 18 ቀን 1940 ዓ.ም ሲመተ ጵጵስና፤ ጥር 6 ቀን 1943 ዓ.ም ሲመተ ሊቀ ጵጵስና ከተቀበሉ በኋላ ሰኔ 21 ቀን 1951 ዓ.ም ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቄርሎስ ግብጻዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሆነው ተሹመዋል።

3.   ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
v  ከ1943 እስከ 1963 ዓ.ም የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ እንደራሴ ሆነው አገልግለዋል። ግንቦት 1 ቀን 1963 ዓ.ም ሁለተኛው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ሆነው ተሹመዋል።

4.   ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
v  ሐምሌ 11 ቀን 1968 ዓ.ም መዓርገ ጵጵስና ተቀብለዋል። በዚህ ዓመት ነሐሴ 23 ቀን 1968 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ሣልሳዊ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ሆነው ተሹመዋል።

5.   ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
v  ጥር 13 ቀን 1971 ዓ.ም በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት አንብሮተ እድ ማዕረገ ጵጵስና አግኝተዋል። ነሐሴ 29 ቀን 1980 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ሆነው ተሹመው ለ3 ዓመት ያህል በፓትርያርክነት አገልግለዋል።
6.   ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
v  መስከረም 16 ቀን 1963 ዓ.ም በብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ አንብሮተ እድ ሲመተ ጵጵስና ተቀበሉ። ሐምሌ 5 ቀን 1984 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አምስተኛ ፓትርያርክ ሆነው ተሹመዋል።

ክፍል ሁለት
ቅዱሳት መካናት

እግዚአብሔር አምላካችን በመዝሙር፣ በቅዳሴ፣ በማኅሌት ይገለገልባቸው ዘንድ የመረጣቸው ቦታዎች ቅዱሳን ናቸው። አንድም ከቦታዎች ሁሉ ለይቶ እግዚአብሔር ታላላቅ የቸርነት ስራውን የሰራባቸው ቦታዎች ቅዱሳን መካናት ይባላሉ። እነዚህን ቅዱሳን ቦታዎች የመረጠ፣ ያከበረና የቀደሰ ራሱ እግዚአብሔር ነውና በእግዚአብሔር ክብር የተሞሉ እና የከበሩ ናቸው።
ጥቅስ፡
v  የእግዚአብሔርም ሠራዊት አለቃ ኢያሱን። አንተ የቆምህበት ስፍራ የተቀደሰ ነውና ጫማህን ከእግርህ አውልቅ አለው። መ. ኢያሱ 5፡15
v  እግዚአብሔር እርሱ ይመለከት ዘንድ እንደ መጣ ባየ ጊዜ እግዚአብሔር ከቍጥቋጦው ውስጥ እርሱን ጠርቶ። ሙሴ፥ ሙሴ ሆይ አለ። እርሱም፦ እነሆኝ አለ። ወደዚህ አትቅረብ አንተ የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች መሬት ናትና ጫማህን ከእግርህ አውጣ አለው። ዘጸ.3፡4-5
v  እኛም በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህን ድምፅ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን። 2ጴጥ.1፡18
v  ሰሎሞንም ጸሎቱን በፈጸመ ጊዜ እሳት ከሰማይ ወርዶ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕቱን በላ የእግዚአብሔርም ክብር ቤቱን ሞላ።የእግዚአብሔርም ክብር የእግዚአብሔርን ቤት ሞልቶት ነበርና ካህናቱ ወደ እግዚአብሔር ቤት መግባት አልቻሉም።… አሁንም በዚህ ስፍራ ለሚጸለይ ጸሎት ዓይኖቼ ይገለጣሉ፥ ጆሮቼም ያደምጣሉ።አሁንም ስሜ ለዘላለም በዚያ ይኖር ዘንድ ይህን ቤት መርጫለሁ ቀድሻለሁም ዓይኖቼና ልቤም ዘወትር በዚያ ይሆናሉ። 2ዜና.7፡1-15
v  ቤተ መቅደስህ ቅዱስ ነው በጽድቅም ድንቅ ነው። መዝ.64(65)፡5
v  በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት፥ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው። 1ኛ ጢሞ.3፡15
ቅዱሳን መካናትን በ2 ክፍል ከፍለን እንደሚከተለው እንመለከታለን፡
ሀ. እግዚአብሔር አምላካችን ታላላቅ ስራዎችን የሰራባቸው ቦታዎች
1.    ቤተልሔም
v  ቤተልሔም ማለት የእንጀራ ቤት ማለት ነው። በያዕቆብ ዘመን ኤፍራታ በመባል ይጠራ ነበር።
v  ከኢየሩሳሌም ወደ ደቡብ 9 ኪ.ሜ ርቆ የሚገኝ ከተማ ነው።
v  የዳዊት ከተማ ነበር። (ዳዊትም የዚያ የኤፍራታዊው ሰው ልጅ ነበረ ያም ሰው ከቤተ ልሔም ይሁዳ ስሙም እሴይ ነበረ ስምንትም ልጆች ነበሩት በሳኦልም ዘመን በዕድሜ አርጅቶ ሸምግሎም ነበር። 1ሳሙ. 17፡12፣ “ዮሴፍም ደግሞ ከዳዊት ቤትና ወገን ስለ ነበረ ከገሊላ ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ ቤተ ልሔም ወደምትባል ወደ ዳዊት ከተማ ወደ ይሁዳ፥ ፀንሳ ከነበረች ከእጮኛው ከማርያም ጋር ይጻፍ ዘንድ ወጣ።” ሉቃ.2፡4-5)
v  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚወለድባት በነቢዩ ሚክያስ የተተነበየበት በኋላም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ታላቅ ቦታ (መካን) ነው። “አንቺም ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፥ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ፥ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል።” ት.ሚክ.5፡2፣ “ኢየሱስም በይሁዳ ቤተ ልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሰብአ ሰገል። የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና እያሉ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።”ማቴ.2፡1)
v  በቤተልሔም ሰብዓ ሰገል ወርቅ፣ እጣን፣ ከርቤ የገበሩበት፤ መላእክትና ሰው በአንድነት እግዚአብሔርን ያመሰገኑበት፤ መላእክት ክንፋቸውን ከሰማይ እስከ ምድር ጥልቀት ድረስ ዘርግተው ጠላት እስኪሸበር ድረስ ታላቅ የነገረ ሥጋዌ መጀመሪያ መገለጫ የሆነ ታላቅ ቦታ ነው።
v  ዛሬ ከ30 ሺህ በላይ ህዝብ ሲኖርባት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደባት ቦታ ላይ ቤተክርስቲያን ታንጾባት ክብሩን እንደተጠበቀ ይገኛል።

 2.   የሲና ተራራ
v  የሲና ተራራ ከግብጽ ሀገር በስተምሥራቅ እና ከእስራኤል በስተደቡብ ይገኛል።
v  አሰርቱ ቃላት (ሕገ ኦሪት) የተሰጠው በዚህ ቅደሱ ተራራ ላይ ሲሆን ሙሴ 40 መዓልትና ሌሊት ከእግዚአብሔር ጋር ቃል በቃል እየተነጋገረ ቆይቶበታል። (ዘጸ.19፡20)
v  የኮሬብ ተራራ በመባልም ይጠራል። (ዘጸ. 3፡1 “ሙሴም የዮቶርን የአማቱን የምድያምን ካህን በጎች ይጠብቅ ነበር ወደ ምድረ በዳ ዳርቻም በጎቹን ነዳ፥ ወደ እግዚአብሔርም ተራራ ወደ ኮሬብ መጣ።”፣ ዘዳ.4፡9-10 “እግዚአብሔር፦ ሕዝቡን ወደ እኔ ሰብስብ፥ በምድርም በሕይወት በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ እኔን መፍራት ይማሩ ዘንድ፥ ልጆቻቸውንም ያስተምሩ ዘንድ ቃሌን አሰማቸዋለሁ ብሎ በተናገረኝ ጊዜ፥ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት በኮሬብ በቆምህበት ቀን ዓይኖችህ ያዩትን ነገር እንዳትረሳ፥ በሕይወትህም ዘመን ሁሉ ከልብህ እንዳይወድቅ ተጠንቀቅ፥ ነፍስህንም በትጋት ጠብቅ ለልጆችህም ለልጅ ልጆችህም አስታውቀው።”)
v  ቦታው በእግዚአብሔር እንደተቀደሰና ለእግዚአብሔር የተለየ ስፍራ መሆኑን እግዚአብሔር ለሙሴ ነግሮታል።

3.   ቤተክርስቲያን
v  አቅሌስያ የሚለው የግሪክን ቃል ሰብዓ አጊንት (ሰባው ሊቃውንት) ቤተክርስቲያን ብለው ተርጉመውታል፤ በግሪክ ችግር በተፈጠረ ጊዜ አረጋውያን ጉባኤ ሰርተው ችግሩን ይፈቱበታል፣ ሰላምን ያወርዱበታል፤ በቤተክርስቲያንም የጥል ግርግዳ ይፈርስበታል፤ እውነተኛው ሰላም ይገኝበታል፣ ሰውና እግዚአብሔር ይገናኝበታል።
v  ቤተክርስቲያን በምሥጢር ሲተረጎም ፡
1.    ቤተክርስቲያን ማለት የክርስቲያን ቤት፣ የክርስቲያን መሰብሰቢያ፣የክርስቲያን መገናኛ ቤት ማለት ነው።
V  ይህ ማለት ክርስቲያኖች በመሰብሰብ የሚጸልዩበት፣ ክቡር ሥጋውን ቅዱስ ደሙን የሚቀበሉበት፣ የሚሰግዱበትና አምልኮተ እግዚአብሔርን የሚፈጽሙበት ቦታና የአምልኮ ቤት ነው። ቤተክርስቲያን ቤተ-ጸሎት ናት። (ኢሳ.56፡7 “ሉቃ.19፡46 “እርሱም፦ ቤቴ የጸሎት ቤት ይሆናል ተብሎ ተጽፎአል፤ እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት አላቸው።”፣ወደ ተቀደሰ ተራራዬ አመጣቸዋለሁ፥ በጸሎቴም ቤት ደስ አሰኛቸዋለሁ ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የሚሆን የጸሎት ቤት ይባላልና የሚቃጠለውን መሥዋዕታቸውንና ሌላ መሥዋዕታቸውን በመሠዊያዬ ላይ እቀበላለሁ።”፣ ማር.11፡17 “ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ የተጻፈ አይደለምን? እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት አላቸው።”)
V  የመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን የማርቆስ እናት ማርያም ቤት ስትሆን በኋላ ማኅበረ ክርስቲያኑ እየሰፋ በመሄዱ በፊልጵስዮስ በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፈቃድ ተሰርታለች።
2.   ቤተክርስቲያን ማለት ማኅበረ ክርስቲያን፤ የክርስቲያኖች ህብረት ማለት ነው።
v  ከሊቅ እስከ ደቂቅ ድረስ በመሰብሰብ ቃለ እግዚአብሔርን፣ ለመማር፣ ለጸሎት፣ ስብሐተ እግዚአብሔርን ለማድረስ፣ ሁለትም ሦስትም ሆነው የሚሰበሰቡበት ህብረት ቤተክርስቲያን ይባላል።
(ማቴ.18፡20 “ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና።”፣ ሉቃ. 24፡13-34 የኤማሁስ መንገደኞች ዮሴፍና ቀለዮጳም ስለ ነገረ ድኅነት ሲነጋገሩ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመካከላቸው ተገኝቷል።፤ሐዋ.8፡3 “ሳውል ግን ቤተ ክርስቲያንን ያፈርስ ነበር፤ ወደ ሁሉም ቤት እየገባ ወንዶችንም ሴቶችንም እየጐተተ ወደ ወኅኒ አሳልፎ ይሰጥ ነበር።”፣ ሐዋ.11፡22 “ወሬውም በኢየሩሳሌም ባለችው ቤተ ክርስቲያን ስለ እነርሱ ተሰማ፥ በርናባስንም ወደ አንጾኪያ ላኩት፤”፣ ሐዋ.15፡4 “ወደ ኢየሩሳሌምም በደረሱ ጊዜ ቤተ ክርስቲያንና ሐዋርያት ሽማግሌዎችም ተቀበሉአቸው፥ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ያደረገውን ሁሉ አወሩ።”)
3.   ቤተክርስቲያን ማለት የክርስቲያን ወገን ማለት ነው።
v  የክርስቲያን ወገን የሆነ የሚጠራበት ስም ቤተክርስቲያን የሚለው ነው። ለምሳሌ፡ ቤተ እስራኤል፣ ቤተ ያዕቆብ፣ ቤተ አሮን ሲል የእስራኤል ወገን፣ የያዕቆብ ወገን፣ የአሮን ወገን ማለት ነው። (ማቴ.16፡18 “እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም።”፣ መዝ. 117(118)፡3 “ቸር እንደ ሆነ፥ ምሕረቱ ለዘላለም እንደ ሆነች የአሮን ቤት አሁን ይንገሩ።”፣ መዝ.113(114)፡1 “እስራኤል ከግብጽ፥ የያዕቆብም ቤት ከእንግዳ ሕዝብ በወጣ ጊዜ፥”፣ ሐዋ.18፡22 “ወደ ቂሣርያም በደረሰ ጊዜ ወጥቶ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምታ ከሰጠ በኋላ ወደ አንጾኪያ ወረደ።”፣ )
4.   ቤተክርስቲያን ማለት የክርስቲያን ሰውነት ማለት ነው።
v  ክርስቲያኖች የክርስቶስ ማደሪያዎች ስለሆኑ ቤተክርስቲያን የሚለው የክርስቶስ ማደሪያ የሆኑ ክርስቲያኖች ፣ የክርስቲያኖች ሰውነት ማለት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን?” 1ቆሮ.3፡16 እንዳለ።
v  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ።” ዮሐ. 6፡56 እንዳለ የአማንያን ሰውነት የክርስቶስ ቤት ነው።
5.   የቤተክርስቲያን አባቶችም ቤተክርስቲያን ይባለሉ።
V  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአምላካዊ ቃሉ “ወንድምህም ቢበድልህ፥ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው። ቢሰማህ፥ ወንድምህን ገንዘብ አደረግኸው፤ባይሰማህ ግን፥ በሁለት ወይም በሦስት ምስክር አፍ ነገር ሁሉ እንዲጸና፥ ዳግመኛ አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ፤እነርሱንም ባይሰማ፥ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት፤ ደግሞም ቤተ ክርስቲያንን ባይሰማት፥ እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ።” ማቴ. 18፡15-17 ስለዚህም ቤተክርስቲያን ያለው የቤተክርስቲያን የበላይ አባቶችን (ጳጳሳትን) ነው።
የሕንፃ ቤተክርስቲያን አሰራር ምሥጢር
ቤተክርስቲያን የሚሰራው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ደም የነጠበበት ቦታ ላይ ሲሆን በፈቃደ እግዚአብሔር ካልሆነ በቀር መስራት አይቻልም። ቅዱስ ዳዊት የእግዚአብሔርን ቤት ለመስራት እጅግ ቢፈልግም እግዚአብሔር ግን ቤቱን እንዲሰራለት የመረጠው ልጁ ሰሎሞንን ነበር። (እርሱም፦ ልጅ ይሆነኝ ዘንድ መርጬዋለሁና፥ እኔም አባት እሆነዋለሁና ልጅህ ሰሎሞን ቤቴንና አደባባዮቼን ይሠራል። 1ዜና.28፡6) ፈቃደ እግዚአብሔር የሆነበት ቦታ ላይ ቤተክርስቲያንን ለመትከል መጀመሪያ ኤጲስ ቆጶስ ሊፈቅድ ይገባል። (ፍትሐ ነገሥት. አንቀጽ 1፡3)
ከታላቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ መነሳት በኋላ የክርስትና ሃይማኖት በነጻነት ለማስተማር፤ አገልግሎቱን በነጻነት ለመፈጸም ይቻል ዘንድ አዋጅ ተነገረ። ስለዚህም ክርስቲያን ሁሉ በየቦታው እንደኑሯቸው ደረጃ መጠነኛም ታላላቅም ሕንፃ ቤተክርስቲያን ይሰሩ ጀመር። በዚህም መልክ የሥርዓተ አምልኮ ቤቶች ይሰሩ እንጂ ራሳቸውን የቻሉ የሕንፃ ዲዛይን (ፕላን) አልያዙም ነበር። በጊዜው ትላልቅና ግሩም ድንቅ የሚያሰኙ አብያተ ክርስቲያናት ትልቅነታቸውና ውበታቸው ይነገርላቸው እንጂ የሮማውያንን ታላላቅ ህንፃዎች እና ቤተመንግሥት በመሳሰሉ መልክ ይሰሯቸው ነበር።
ከጊዜ ወደጊዜ ግን ቤተክርስቲያን የራሷ የሆነ አሰራር፣ መልክ መያዝ ግድ ስለሆነና ከሌላው የተለየ ቤተክርስቲያን መስራት ጀመሩ። እነዚህም የቤተክርስቲያን አሰራር የሚባሉት፤ ቫስሊክ (ሞላላ)፣ ቪዛንቲን ፣ ጎቲክ (በመስቀል አምሳል የሚሰራ)፣ ባሮኪያ (ከመስቀል አምሳል ውጭ የሆነ ፕላን) ዓይነት ሲሆኑ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ግን የሯሷ የሆነ የቤተክርስቲያን አሰራር አላት። እነዚህም፡
ሀ. ቫስሊክ (ሞላላ፣ ሰቀላማ) ቅርጽ ቤተክርስቲያን
V  ቫስሊክ ማለት እንደ ብሉይ ኪዳን ቤተመቅደስ (ምኩራብ) ቅርጽ ሰቀላ ወይም ሞላላ ቅርጽ ነው። የዚህ ዓይነት ቤተክርስቲያን ቅርጽ የተወረሰው ከሰሎሞን ቤተመቅደስና ኋላም በዘመነ ክርስትና ታላቁ ቆስጠንጢኖስ እና እናቱ ንግሥት እሌኒ በኢየሩሳሌምና በቤተልሔም ከአሰሯቸው አብያተ ክርስቲያናት ቅርጽ ነው። ይህ የሰቀላ ቅርጽ ቤተክርስቲያን በመጋረጃ ወይም በአእማድ እንጂ በግንብ የተከፋፈለ አይደለም። የቅኔ ማኅሌት፣ የመቅደስና ዋናው መንበሩ ያለበት ቦታ (ቅድስተ ቅዱሳን) የተለየ ነው።
V  የሰቀላ ቤተክርስቲያን ጉልላቱ አንድ ብቻ አይደለም። ሦስትም፣ አራትም ከዚያም በላይ ሊሆን ይችላል።

ለ. ክብ ቅርጽ ቤተክርስቲያን (ቤተ ንጉሥ ቅርጽ)
V  በኢትዮጵያ የነበሩ ነገሥታት ቤተመንግሥታቸውን በክብ ቅርጽ ይሰሩ ነበርና ቤተክርስቲያንንም ሲያንጹ በክብ መልክ አድርገው ስለነበር ቤተንጉሥም ይባላል።
V  ከአጼ ምኒልክ 2ኛ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ልዩ ልዩ ክብ ዓይነት ቤተክርስቲያን መሰራት ተጀመረ። ይህም 4 ማዕዘን፣ 6 ማዕዘን፣ 8 ማዕዘን  ዓይነት ናቸው።
V  ክብ ቤተክርስቲያን 3ቱ ክፍላት (ቅኔ ማኅሌት፣ ቅድስት፣ መቅደስ) የሚለያዩት በግንብ ሲሆን 3 ሲኖሩት እንደ ቤተክርስቲያኗ ስፋት መስኮቶች ይኖሩታል።
V  ክብ ቤተክርስቲያን 1 ጉልላት ብቻ ይኖረዋል።
V  ቅድስተ ቅዱሳኑ (መቅደሱ) 3 በሮች በምዕራብ፣ በሰሜንና በደቡብ ሲኖረው በምስራቅ በኩል ግን መስኮት ብቻ ይኖረዋል። ይህም ሰሎሞን ቤተመቅደሱን ከሰራ በኋላ ዘግቶት የኖረ በመሆኑ ዛሬ ድረስ በቤተክርስቲያናችን የሰሎሞን በር በመባል ይታወቃል። ቅኔ ማኅሌቱና ቅድስቱም በ3ቱ በሮች ይኖራቸዋል። ይህም የ3ቱ ጾታዎች (ወንድ፣ ሴት፣ ካህን) መግቢያና መውጫ ናቸው።
ሐ. ዋሻ ቤተክርስቲያን
V  መግቢያው በር ብዙ ጊዜ 1 ብቻ ነው። ጉልላት የለውም፤ ከአናቱ ላይ መስቀል ይደረግበታል።
V  ቅዱስ ላሊበላ (ላልይበላ) ከሰራቸው አብያተ ክርስቲያናት አብዛኞቹ ዋሻ ቤተክርስቲያን ናቸው።
V  3 ቱም ክፍላት በመጋረጃ ይከፈላሉ።
V  በዘመነ ሰማዕታት ጊዜ አባቶች በዋሻ ሲሸሸጉ፣ ንዋያተ ቅድሳትን ሲሸሽጉ ፈልፍለው የሚሰሩት ዋሻ ሲሆን በብዛት በዚህ ዘመን እንደተፈለፈሉ ይታመናል።
የቤተክርስቲያን 3ቱ ክፍላት አገልግሎት፤
1.    ቅኔ ማኅሌት
v  ወደ ቤተክርስቲያኑ ሲገቡ የመጀመሪያው ክፍል ሲሆን ስያሜው ከግብሩ የተወረሰ ነው። ይህም ሥርዓተ ማኅሌት ይደርስበታልና ነው።
v  በቅኔ ማኅሌቱ በሰሜናዊ ምስራቅ በኩል ቀሳውስትና ዲያቆናት በመንፈቀ ሌሊት በነግህ ሰዓታት ይቆሙበታል፣ ኪዳን ያደርሱበታል፣ በጥንተ ቤተክርስቲያን ሥርዓት ሥርዓተ ጥምቀት ይፈጸምበት ነበር። ለጥምቀተ ክርስትና እና ለቁርባን ያልበቁ በትምህርት፣ በንሰሐ ገና የሚፈተኑ አዲስ አማንያን (ንዑሰ ክርስቲያን) ዲያቆኑ “ጻዑ ንዑሰ ክርስቲያን፡ የክርስቲያን ታናናሾች ውጡ” እስከሚል ድረስ በዚያ ይቆያሉ፣ ምዕመናንም የሚያስቀድሱበት ክፍል ነው።
v  መዘምራን የሚዘምሩበት  በቅኔ ማኅሌት ቆመው የሚያስቀድሱት ንፍቅ ዲያቆናት፣ አናጉንስጢስ፣ መዘምራን ናቸው። (ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 9)
v  በቅኔ ማኅሌቱ በሌብ (ደቡብ ምስራቅ) በኩል የሚገኘው ቦታ የሴቶች መቆሚያ ሲሆን የወንዶችና የሴቶች በመጋረጃ ይለያል።
v  ክፍሉ በምስራቅ በካህናት መግቢያ፣ በሰሜን የወንዶች መግቢያ፣ በደቡብ የሴቶች መግቢያ 3 በሮች አሉት።
2.   ቅድስት
v  ስያሜው ከብሉይ ኪዳን ስያሜ ጋር ተመሳሳይ ነው። የቤተክርስቲያኗ ማዕከላዊ ክፍል ሲሆን (በተለይ በክብ አብያተ ክርስቲያናት አሰራር) በስተምዕራብ በኩል ቆመው የሚያስቀድሱት ቆሞሳት፣ ቀሳውስትና ዲያቆናት ናቸው። በስተ ሰሜን በኩል መነኮሳትና የሚቆርቡ ወንዶች ምዕመናን፣ በስተደቡብ በኩል ደናግል መነኮሳያት፣ የካህናት እና የዲያቆናት ሚስቶች እና የሚቆርቡ ምዕመናት ቆመው ያስቀድሱበታል። በዚህ ክፍል ቆመው ላስቀደሱ ምዕመናን ሥርዓተ ቁርባን ይፈጸማል።
v  ከሥርዓተ ጥምቀትና ከሥርዓተ ንስሐ በቀር የሌሎች ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን ሥርዓተ ጸሎት የሚፈጸመው በዚሁ ክፍል ነው። ከእነዚህም ጸሎቶች ውስጥ፡ የምሥጢረ ክህነት ጸሎት፣ የምሥጢረ ተክሊልና የምሥጢረ ቀንዲል ጸሎት የሚጸለይበት ክፍል ነው።
v  ቅድስቱ በምሥራቅ፣ በምዕራብ፣ በሰሜን እና በደቡብ አራት በሮች ይኖሩታል።
3.   መቅደስ (ቅድስተ ቅዱሳን)
v  ስያሜው ከብሉይ ኪዳን ቤተመቅደስ የተወረሰ ነው። በዚህ ክፍል ውስጥ ምሥጢረ ቁርባን፣ ሥርዓተ ቁርባን ይፈጸምበታል።
v  መንበረ ታቦቱ ሌሎችም የቤተመቅደስ አገልግሎት የሚሰጡ ንዋያተ ቅድሳት ይገኙበታል።
v  በዚህ ክፍል ውስጥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት ያስቀድሱበታል እንዲሁም መግባት የሚችሉት ካህናትና ዲያቆናት ብቻ ናቸው።
v  መቅደስ 3 ክፍላት ሲኖሩት በምዕራብ፣ በሰሜንና በደቡብ ሲሆን ለእያንዳንዱ በር መንጦላዕት (መጋረጃ ) አለው።
በዚህ እግዚአብሔር በሚመለክበት፣ ሥርዓተ አምልኮት በሚፈጸምበት የእግዚአብሔር ቤት (ቤተክርስቲያን) ዙሪያ አገልግሎት የሚሰጡ ቤቶች ይሰራሉ። እነዚህም፡
1.      ቤተልሔም፡- በቤተክርስቲያኗ በምሥራቅ በኩል የሚሰራ ሲሆን ዲያቆናቱ ለመስዋዕት የሚሆነውን ኅብስትና ወይን የሚያዘጋጁበት ነው። ስያሜውን ያገኘው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተወለደባት ስፍራ “ቤተልሔም ዘይሁዳ” ምሳሌ ነው።
2.     የግብር ቤት፡- ለመስዋዕት የሚቀርበው (መገበሪያ) የሚሰየምበት፤ በቤተክርስቲያኑ ቅጽረ ግቢ የሚሰራ ቤት ነው። (ስንዴው መገበሪያ ይባላልና መገበሪያውን አሰናድቶ ማቅረቡ መሰየም ይባላል። ይህ የመስዋዕቱ አቀራረብ ቋንቋ ነው።)
3.     ዕቃ ቤት፡- ይህ የቤተክርስቲያናችን ንዋያተ ቅድሳት የሚቀመጡበት ቤት ነው። (ሕዝ.44፤19፡ ፍት. ነገ. 12)
4.     የማጥመቂያ ቤት፡- ይህ ሥርዓተ ጥምቀት የሚፈጸምበት (የማጥመቂያ) ቤት ነው።
5.     ደጀ ሰላም፡- የሙታን በድን የሚያርፍበት እና ጸሎተ ፍትሐት የሚፈጸምበት ቤት ነው።
ከላይ የተገለጹት ቤቶች አብረው ከቤተክርስቲያኗ ጋር የሚሰሩ መሰረታዊ ቤቶች ናቸው። በተጨማሪም እንደቤተክርስቲያኗ አቅም የሚከተሉት ቤቶች ሊሰሩ ይችላሉ።
6.     የሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት
7.     የሰንበት ትምህርት ቤቶች
8.     የስብከተ ወንጌል አዳራሽ
9.     የእንግዶችና የካህናት ማረፊያ ቤቶች
10.    የመንፈሳዊ ትምህርት ቤቶችና ተግባረ ዕድ መማሪያ ክፍሎች
11.     ቤተ መጻሕፍት
12.    የንዋያተ ቅድሳት፣ የጧፍና ዕጣን መሸጫ ቤቶች ናቸው።
5ቱ እህት አብያተ ክርስቲያናት
በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነትና ሥርዓት አንድ የሆኑ፤ በሥርዓተ አምልኮት፣ በትምህርተ ሃይማኖት፣ በዶግማና ቀኖና ቤተክርስቲያን አንድ የሆኑ 5 ሃገራት ሲኖሩ እነዚህም፡-
1.      የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን (ኢትዮጵያ)
v  በ34 ዓ.ም በባኮስ (የንግሥት ህንደኬ ጃንደረባ) ፊልጶስ አስተምሮ፣ አጥምቆት ኢትዮጵያም ከብሉይ ኪዳን አምልኮተ እግዚአብሔር ወደ ሐዲስ ኪዳን የክርስትና እምነት ተሸጋግራለች።
2.     የግብጽ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን (ግብጽ)
v  በወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ ተሰብከው በእምነታቸውና በሥራቸው የተመሰከረላቸው ኦርቶዶክሳውያን ምዕመናንን አፍርታለች።
3.     የአርመን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን (አርመን)

4.     የሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን (ሕንድ)
5.     የሶርያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን (ሶርያ)

ይቆየን...
የቦ/መ/ብ/ቅ/እግዚአብሔር አብ ቤ/ክ ሰ/ት/ቤት



No comments:

Post a Comment