13

.

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው::" የማቴዎስ ወንጌል 7: 4

"እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅናወተት ግዙ።" ትንቢተ ኢሳይያስ 55 : 1

Monday, October 17, 2011

ቃና ዘገሊላቃና ዘገሊላ

በመምህር ፍቅረ ማርያም ባዘዘው
የቦ/መ/ብ/ቅ/እግዚአብሔር አብ ቤ/ክ የመጽሐፍ መምህር


ቃና ዘገሊላ
ይህ በዓል ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ከዘጠኙ ንዑሳን በዓላት መካከል አንዱ ሲሆን ይህም ጥር 12 ቀን ይውላል፡፡ በዓሉ መከበር የነበረበት የካቲት 23 ነበር፤ ነገር ግን የካቲት ላይ ጾም ስለሚሆን “የውሀን በዓል ከውሀ ጋር” ሲሉ ሊቃውንት ናቸው ጥር 12 ያደረጉት፡፡
የዮሐንስ ወንጌል ም.2፤1 “በሦስተኛው ቀን በገሊላ አውራጃ በቃና ሰርግ ነበር” ይላል፡፡ ከዚህ በኋላ በተራ ቀደም ያስቀድማሉ “የኢየሱስ እናት በዚያ ነበረች፤ ኢየሱስደቀመዛሙርቱ” ይላል፡፡ከዚህ ላይ የምንረዳው መጀመሪያ እመቤታችን ድንግል ማርያም አስቀድማ በሰርጉ ውስጥ መኖሯን ነው፡፡ እናት ከተጠራ በኋላ ነው ልጅ የሚጠራና ከዚያም ኢየሱስ ክርስቶስ፤ ከመምህር ጋር ደቀመዝሙር ይጠራልና ከእርሱም ጋር ደቀመዛሙርቱ ተጠሩ፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር በወቅቱ ወይን ባለቀ ጊዜ እመቤታችን ድንግል ማርያም ወይን የላቸውም ያለችው፡፡ እርሱም “ከአንቺ ጋር ምን አለኝ፤ ጊዜዬ ገና አልደረሰምና” አላት፡፡
ወደምሥጢሩ ስንገባ፤1.  ሦስተኛ ቀን ምንድን ነው
1.  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀ ጥር 11 ቀን ነው፡፡ ወዲያውኑ እንደተጠመቀ ሳይውል ገዳመ ቆሮንቶስ ሄደ፤ 40 ቀንና 40 ሌሊት ጾመ፤ ጾሙ የካቲት 20 ቀን ይፈጸምና የካቲት 23 ቀን “በሦስተኛው ቀን ሰርግ ነበር” ይላል፡፡
2.  ሦስተኛ ቀን የሚለው
·         የመጀመሪያ ቀን የሚባለው ዘመነ አበው ፤ አዳም፤ እነአብርሃም፤ ይስሐቅ አበው የነበሩበት ዘመን ሲሆን፤
·         ሁለተኛ ቀን የሚባለው ዘመነ ኦሩት ነው፤ እነሙሴ የነበሩበት ዘመን ሲሆን
·         ሦስተኛ ቀን የተባለው ዘመነ ሐዲስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የሆነበት ዘመን ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር ሰርግ የሆነው፡፡

2.  “እመቤታችን አስቀድማ ነበር” ሲል ደግሞ እመቤታችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በሥጋዊ እድገቱ እንደምትቀድመው ነው፡፡ እንኳን የእርሱ እናት ትቅርና ዮሐንስ መጥምቁም በ6 ወር ይቀድመው ነበር፡፡ እንግዲህ እናትን ሳያውቁ ልጅን ቢጠይቁ ያስቸግራል፡፡ አስቀድማ የነበረችውን ከኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ከመሆን በፊት አብራን የኖረችውን ድንግል ማርያምን ሳናውቅ ኢየሱስ ብንል ትርፉ ድካም ብቻ እንጂ አይሳካም፡፡ ዛሬም ቢሆን “ኢየሱስ” ከማለት በፊት አስቀድመን እርሷን አማልጅን እንበላት፡፡ ነገረ ድኅነትን ስናስብ በህሊናችን አስቀድመን እርሷን መሳል አለብን፤ ነገረ ማርያም የምሥጢረ ሥጋዌ መቅድም (መጀመሪያ)፤ የነገረ ድኅነት መሠረት ነውና፡፡ ጌታችን ተወለደ፤ ተሰደደ፤ አስተማረ፤ ተሰቀለ፤ ሞተ፤ ተነሳ፤ አረገ፤ ዳግም ይመጣል ሲባል በድንግል ማር ያም ሥጋ ነው፡፡ በነገራችን ሁሉ እርሷን ማስቀደም እንዳለብን ነው የምንረዳው፡፡
3.  ወይኑ ባለቀ ጊዜ “ወይን የላቸውም” አለች፡፡ የወይኑን ማለቅ ለእመቤታችን ማን ነገራትሙሽራው ወይስ ከሰርገኞቹ መካከል አንዱለዚህ ምንም አይነት መልስ እንደማይሰጥ ግልጽ ነው፡፡ ድንግል ማርያም ግን እራሷ ነበር ያወቀችው፤ ነቢይት ናትና፡፡ ስለሆነው እንዲሁም ስለሚሆነው ታውቃለች፤ ቅዱስ ዘካርያስና ቅድስት ኤልሳቤጥ ካመሰገኗት በኋላ “ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብጽዕት ይሉኛል” ማለቷ ወደፊት ስለሚመጣው ትውልድ ነበር የተናገረችው፤ ይህ  ነቢይነቷን የሚገልጽ ነው፡፡ (ሉቃ. 1፤48-49)  ኢሳይያስ በትንቢቱ በምዕራፍ 8፤1 “ወደ ነቢይቱ ሄድኩ ጸንሳም ነበር” የሚላት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ነው፡፡
በ2ኛ ነገ. 6፤8 በሶርያ የነበረው ንጉሥ በኢየሩሳሌም ያለውን ንጉሥ ሊወጋ (ሊገድል) በፈለገ ጊዜ በእልፍኝ ሆኖ የሚመክረውን ምክር ነቢዩ ኤልሳዕ ኢየሩሳሌም ሆኖ ይመለከትና ያውቅ ነበር፤ ኢየሩሳሌም ሆኖ በሶርያ የሚደረገውን እያየ ነበር፡፡ ስለዚህም የኢየሩሳሌሙን ንጉሥ “ከቤትህ እንዳትወጣ ሶርያውያን ሊገድሉህ ይፈልጋሉ” እያለ ይመክረው ነበር፡፡ ምን አይነት ጸጋ እንደሆነ አስቡት፤ ኢየሩሳሌም ሆኖ በሶርያ የሚደረገውን ነገር ማወቅ፡፡ ታዲያ በዘመነ ብሉይ የነበሩ ነቢያት እንዲህ የርቀቱን ነገር የሚያውቁ ከሆነ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የዶኪማስን የቤት ችግር፤ የወይን ማለቅ ብታውቅ ብትረዳ ምን ይደንቅየመለኮት እናትም እንዴት ጸጋው ይበዛላትእንደ እመቤታችንስ ጸጋው የበዛለት በዘመነ ብሉይ ማን ነበር “ጸጋን የተመላሽ ድንግል ሆይ ደስ ይበልሽ” የተባለች ድንግል ማርያም አይደለችምንእግዚአብሔር ዓይነ ልቡናችንን ያብራልን፡፡

4.   “ከአንቺ ጋር ምን አለኝ” ያላትስ ምን ማለቱ ነበርወግጅልኝ፤ ሂጂልኝ ማለቱ ሳይሆን “ያልሽኝን እንዳልፈጽምልሽ ምን የሚከለክለኝ ነገር አለ” ሲል ነው፡፡ “እናትና አባትህን አክብር፤ ለእናትና ለአባትህ ታዘዝ” ያለ አምላክ እናቱን ሂጂልኝ፤ ወግጅልኝ አላት ሲባል አያሳፍርምይህማ እንዳይሆን ለእናቱ እየታዘዘ አደገ ወንጌል ይል የለምን፡፡ (ሉቃ. 2፤51) “ጊዜዬ ገና አልደረሰም” ያለው ወይኑ ከእንስራው በደንብ ካለቀ በኋላ ውሀ ሞልተው የጌታን ተአምር እዲታይ ለማድረግ ነው፡፡ ምክንያቱም ወይኑ በደንብ ሳያልቅ ከዚያው ላይ ቢሞላው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ተአምር አይታወቅም፤ ረድኤት አሳደረበት ይባላል አንጂ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወይኑ ሁሉ ካለቀ በኋላ ግን ውሀ ተሞልቶ ወይን ሲሆን ተአምሩ ይታወቃል፤ ይገለጻል፡፡ ለዚህም ነው “ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያውን ተአምር በቃና አደረገ” የሚል፡፡( ሌላም ሰፊ ምሥጢር ቢኖርም ለዚህ እትም ግን ይህን አቅርበናል፡፡)
የሰርገኛው ቤት ብቻ አይደለም፤ ወይን የጎደለበት ሁላችንም ወይን የለንም የሕይወት እንሥራችን ጎደሎ ነው፡፡ ይህ እንስራ (ጋን) የሚሞላው በእመብርሀን አማካኝነት ነው፡፡ እርሷ ከሌለችበት በፍጹም ሊሞላ አይችልም በመሆኑም ለሁሉም ሰው ለማስገንዘብ የምንወደው በቅድሚያ ጸጋ የበዛበት እመቤት መያዝ እንዳለብን፤ ለምን እግዚአብሔር ከእርሷ ጋር ነውና፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነውና ብሏታል እርሷን ከያዝን እግዚአብሔርን እንይዘዋለን፤ ያለእርሷ እንሥራችን አይሞላም ለዘመናት ደክመናል ነገር ግን እንስራችን ባዶ ነው፡፡ “እመቤቴ ከቤቴ ግቢ፤ ቤቴ ባዶ ነው” እንበላት፤ ትመጣለች ያን ጊዜ ቤታችን ይሞላል፡፡ የፍቅር ወይን፤ የቸርነት ወይን፤ የሰላም ወይን፤ የመተማመን ወይን በቤታችን ጎድሎብናል፡፡ 

ስለዚህ እመቤታችን በምልጃዋ ትሙላልን፤ ፍቅሯን ታሳድርብን፡፡ አሜን፡፡


ምንጭ፡ ፍኖተ - ብርሃን መጽሔት የቦ/መ/ብ/ቅ/እግዚአብሔር አብ ቤ/ክ ሰ/ት/ቤት ጥር/2003 እትም

No comments:

Post a Comment