1. ቅዱሳት ዕለታት
እግዚአብሔር ሥራዎችን የሰራባቸው ዕለታት የተቀደሱ ናቸው። “ለተዓምራቱ መታሰቢያን አደረገ” መዝ.110፡4 እንዲል ይህም እግዚአብሔር ድንቅ ስራ ያደረገበትን ቀን፣ በእለቱ ያደረገልንን ድንቅ ስራ እያሰብን የእግዚአብሔር ከሃሊነቱን፣ ገናናነቱን፣ ቸርነቱን እንድናስተውል እንድንዘክር ነው። እነዚህ ቅዱሳን ዕለታት በዓላት በመባልም ይጠራሉ።
ቅዱሳት ዕለታት በሁለት ከፍለን እንመለከታለን፡
1. እግዚአብሔር እራሱ ድንቅ ስራን የሰራባቸው ዕለታት፡
እነዚህ ዕለታት እግዚአብሔር አምላካችን በቀጥታ ታላላቅ ስራዎችን የሰራባቸው ዕለታት ሲሆኑ ቅዱስና ክቡር ዕለታት ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ 9ኙ ዓበይት በአላት እግዚእ እና 9ኙ ንዑሳን በአላተ እግዚእ ናቸው።
v 9ኙ ዓበይት በአላት እግዚእ
1. ብስራት
2. ልደቱ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ
3. ጥምቀት
4. ደብረታቦር
5. ሆሳዕና
6. ስቅለት
7. ትንሣኤ
8. ዕርገት
9. ጰራቅሊጦስ ናቸው።
v 9ኙ ንዑሳን በአላተ እግዚእ
1. መስቀል
2. ስብከት
3. ብርሃን
4. ኖላዊ ሄር
5. ግዝረት
6. ልደተ ስምኦን
7. ቃና ዘገሊላ
8. ደብረ ዘይት
9. መጋቢት መስቀል ናቸው።
v ሰንበት
· ዘፍ.2፡3 “እግዚአብሔርም ሰባተኛውን ቀን ባረከው ቀደሰውም እግዚአብሔር ሊያደርገው ከፈጠረው ሥራ ሁሉ በእርሱ ዐርፎአልና።”
· ዘኁ.15፡32 “የእስራኤልም ልጆች በምድረ በዳ ሳሉ አንድ ሰው በሰንበት ቀን እንጨት ሲለቅም አገኙ። እንጨትም ሲለቅም ያገኙት ሰዎች ወደ ሙሴና ወደ አሮን ወደ ማኅበሩም ሁሉ አመጡት። ያደርጉበትም ዘንድ የሚገባው አልተገለጠምና በግዞት አስቀመጡት።”
· ራእይ 1፡10 “በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ፥ በኋላዬም የመለከትን ድምፅ የሚመስል ትላቅ ድምፅ ሰማሁ፥”
2. እግዚአብሔር በወዳጆቹ ቅዱሳን ላይ አድሮ ድንቅ ስራን የሰራባቸው ዕለታት
v በአላተ እግዝእትነ ማርያም
· የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአላት 33 ሲሆኑ ከእነዚህም ውስጥ፡
o ግንቦት 1 ቀን፡ ልደታ ለማርያም፡ በሊባኖስ ተራራ የተወለደችበት
o ታህሳስ 3 ቀን በአታ ለማርያም፡ ወደ ቤተመቅደስ የገባችበት
o የካቲት 16 ቀን ኪዳነምህረት፡ የምህረት መሐላ የተቀበለችበት
o ግንቦት 21 – 25 አስተርዕዮ፡ በግብጽ የተገለጸችበት
o ነሐሴ 16 ፍልሰታ፡ ክቡር ሥጋዋ ከምድር ወደገነት፣ ከገነት ወደ ምድር የፈለሰበት ዕለታት ቅዱሳት ዕለታት ናቸው።
· በአላተ ቅዱሳን መላእክት
o ህዳር 12 ቅዱስ ሚካኤል እስራኤላውያንን በአምደ ደመና እየመራ ከግብጽ ያወጣበት
o ህዳር 13 ሲመተ ቅዱሳን መላእክት፡ ቅዱሳን መላእክት የተሾሙበት
o ሰኔ 12 ባህራንን እና አፎምያን ቅዱስ ሚካኤል ያዳነበት እለት
o ጳጉሜ 3 ቅዱስ ሩፋኤል የጦቢትን ዓይን ያበራበት
o መጋቢት 29 ብስራተ ገበርኤል
o ታህሳስ 19 በአሉ ለቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት ጥቂቶቹ ናቸው።
· በአላተ ቅዱሳን አበው
o መጋቢት 29 አቡነ ገብረመንፈስቅዱስ የተጸነሱበት እና ታህሳስ 19 የተወለዱበት በአል ነው። እንዲሁም በመጋቢት 29 ቀን አቡነ ገብረመንፈስቅዱስ በመብረቅ ላይ ሆነው ቁጥራቸው ሰባ ሺህ እልፍ ከአንድ ሺህ የሚሆኑ አጋንንትን ሰባቱን ሊቃነ መላእክት ይዘው በእሳት ሰይፍ መትረው በመብረቅ አጭደው ያጠፉበት ቅዱስ ዕለት ነው። እንዲሁም የአቡነ ገብረመንፈስቅዱስን በረከት ለመቀበል አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ፣ አባ አንበስ ዘአዘሎና አባ ብንያም ዘላእላይ ግብጽ ሆነው ወደ ምድረ ከብድ በመጡበት ጊዜ አባታችን ስለተሰወሩባቸው ለሰባት ቀን ሱባኤ ገብተው ቢጸልይዩ የሚያስፈሩ አንበሶች 3ቱ ቅዱሳን ወዳሉበት መጥተው አንበሶቻቸውን በሉባቸው። ቅዱሳኑም ፈጽመው ደንግጠው ሳሉ አባታችን አቡነ ገብረመንፈስቅዱስ በመጡ ጊዜ የሆነውን ቢነግሯቸው አንበሶቻቸውን አውግዘው የበሉትን አስተፍተው በኃይለ መንፈስቅዱስ ከሞት አስነስተው ሰጥቷቸዋል።
o ሕዳር 23 ነብዩ አብድዩ ያረፈበት
o ጥቅምት 20 ዕረፍቱ ለሆሴዕ ነቢይ
o መስከረም 6 ዕረፍቱ ለኢሣይያስ ነቢይ
o ጥር 6 ዕርገቱ ለኤልያስ ቴስብያዊና ዕረፍቱ ለኖኅ ጻድቅ
o ግንቦት 11 ዕረፍቱ ለአቡነ ሐራድንግል
o ጥር 11 ልደቱ ለአቡነ ሐራድንግል ጥቂቶቹ ናቸው።
ጥቅስ፡
· ማቴ. 10፡41 - 42 “ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፥ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል። ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም።”
· ዮሐ. 13፡20 “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ማናቸውን የምልከውን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።”
· ማር.9፡41 “የክርስቶስ ስለ ሆናችሁ በስሜ ጽዋ ውኃ የሚያጠጣችሁ ሁሉ፥ ዋጋው እንዳይጠፋበት እውነት እላችኋለሁ።”
· መዝ.112፡6 “ለዘላለም አይናወጥም የጻድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል።”
· መዝ.116፡15 “የቅዱሳኑ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው።”
ይቆየን...
የቦ/መ/ብ/ቅ/እግዚአብሔር አብ ቤ/ክ ሰ/ት/ቤት
No comments:
Post a Comment