13

.

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው::" የማቴዎስ ወንጌል 7: 4

"እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅናወተት ግዙ።" ትንቢተ ኢሳይያስ 55 : 1

Friday, October 21, 2011

ነገረ ቅዱሳን ክፍል 5


ቅዱሳን ሰማዕታት
ሰማዕት ማለት ምስክር ማለት ሲሆን በሃይማኖት ምክንያት የተገደለ፣ መከራ የደረሰበት ሰማዕት ይባላል። (ሐዋ.22፡20) የመጀመሪያዎቹ የሐዲስ ኪዳን ሰማዕታት ሐዋርያትና አርድዕት ናቸው።
ቅዱሳን ሰማዕታት የሚባሉት “እግዚአብሔርን ካዱ ለጣዖት ስገዱ” ሲባሉ “እግዚአብሔርን አንክድም ለጣዖት አንሰግድም” በማለት በአላውያን ነገሥታት ፊት ቀርበው ሳያፍሩና ሳይፈሩ ስለጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የባህርይ አምላክነት የመሰከሩ ናቸው። በዚህም ምክንያት ተዘርዝሮ የማያልቅ የመከራ ዓይነት ተቀብለው ለፈጣሪያቸው ክብር ሲሉ ደማቸውን ያፈሰሱ፣ አጥንታቸውን የከሰከሱ፣ ሕይወታቸውን ያጡ ናቸው።
በእሳት ተቃጥለዋል፣ በውኃ ተቀቅለዋል፣ በሰይፍ ተመትረዋል፣ በመጋዝ ተተርትረዋል፣ በመንኩራኩር ተፈጭተዋል (መንኩራኩር የሚባለው በዘመነ ሰማዕታት የነበረ ዘመናዊ የወፍጮ መሳሪያ ነው።)፣ እንደከብት ቆዳቸው ተገፏል፣ ወደጥልቅ ባህር ተጥለዋል። በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ ከሃይማኖታቸው አላፈገለጉም፤ እንደውም “እኔ በእርሱ አምላክ አመልካለሁ” እንዲሉ አድርገዋቸዋል።
ዘመነ ሰማዕታት የሚባለው በአርማንያ 40 ዘመን ሲሆን ብዙ ቅዱሳን ሰማዕትነትን ተቀብለውበታል። ከኢትዮጵያም 1600 ክርስቲያኖች በቀን “ይህ ሰማዕትነት አያምልጠን” በማለት ሄደው ተሰውተዋል። በዘመኑ የነበሩት አረማውያን ነገሥተ ዲዮቅልጥያኖስ፣ መክስምያኖስ፣ ድርጣድስ፣ እለእስክንድሮስ፣ በኡልያኖስ፣ በፋርማህ እጅ የተሰዉ ነበሩ።
ጥቅስ፡
·         ማቴ.10፡28 “ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ።”
·         ዕብ.11፡34 – 38 “የአንበሶችን አፍ ዘጉ፥ የእሳትን ኃይል አጠፉ፥ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፥ ከድካማቸው በረቱ፥ በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ፥ የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ።ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ፤በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፥ ተፈተኑ፥ በመጋዝ ተሰነጠቁ፥ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፥ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ።”
ከቅዱሳን ሰማዕታት ውስጥ ጥቂቶቹ፡
ሀ. ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ
v  እስጢፋኖስ ማለት ፋና ማለት ነው። (ሐዋ.6፡15” በሸንጎም የተቀመጡት ሁሉ ትኵር ብለው ሲመለከቱት እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ፊቱን አዩት።”)አባቱ ስምዖን እናቱ ማርያም ሰና ይባሉ። ሀገሩ እስራኤል (እስራኤላዊ) ሲሆን ጥር 1 ቀን ተወለደ።
v  ? አባቱ ከገማልያል ሲባል ንጹህ የሚሆን የገላምያል ልጅ እስጢፋኖስ ግን ህግን ጠብቆ ህዝቡን እያስተማረ በክርስቶስ ሃይማኖት ጥሪ ስለአቀረበ አይሁድ በኢየሩሳሉም በድንጋይ ወግረው ገደሉት እርሱም መከራውን ሁሉ በትእግስት በመቀበሉ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በአባቱ ቀኝ በሰማያዊክብሩ በአምላካዊ ጌትነቱ እንዳለ ለማየት የበቃ ሆነ። (ተዓምረ ኢየሱስ ተዓምር 113፡9-17)
v  ሕዝቡን ያገለግሉ ዘንድ 7 ዲያቆናት በሐዋርያት ከተመረጡት ውስጥ አንዱ ሲሆን ሕዝቡን ከማገልገል በተጨማሪ ከእነርሱ ጋር በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ስብከተ ወንጌል ተሰማርቶ ህዝቡን ሁሉ ወደ ክርስትና ሃይማኖት ለመሳብ ይፋጠን ነበር።
v  ቅዱስ እስጢፋኖስ የዲያቆናት ሁሉ አለቃ ሲሆን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ተከትሎ መከራ የተቀበለና ከሐዋርያት ቀድሞ በሰማዕትነት ያረፈ ሰማዕት ነው፤ ስለዚህም ቀዳሜ ሰማዕት ይባላል።
v  ከ72ቱ አርድእት አንዱ ሲሆን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ መነሳቱን ያስተማረ አባት ነው።
v  ከየጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ ከመሆኑ በፊት ከሁለቱ የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ደቀመዛሙርት ውስጥ አንዱ ነበር። ዮሐንስ መጥምቅም ወደ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “የሚመጣው አንተ ነህን? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” (ማቴ.11፡1-11) በማለት ከላካቸው አንዱ እስጢፋኖስ ነበር።
v  እስጢፋኖስ በጥር 1 ቀን በሰማዕትነት ባረፈ ጊዜ ሐዋርያት ሥጋውን በንጹሐን አባቶች በአብርሃም፣ በይስሐቅና በያዕቆብ መቃብር ቀበሩት።
v  ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተማረው “ጌታ ሆይ፥ ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ።” ሐዋ.7፡60 በማለት የአምላካችንን ቃል በቃል የደገመ አባት ነው።
ለ. ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ
v  በጥር 20 ቀን በ277 ዓ.ም ተወለደ። ሀገሩ ፍልስጤም ሲሆን ልዩ ስሟ ልዳ ይባላል። ጊዮርጊስ ማለት ኮከብ፣ ብሩህ፣ ሐረገወይን፣ ፀሐይ ማለት ነው። አባቱ ዘሮንቶስ (አንስጣስዮስ) ይባላል ከልዳ መኳንንት ተሹሞ ይኖር ነበር፤ እናቱ ቴዎብስታ (አቅሌስያ) ትባላለች። ማርታና እስያ የሚባሉ እህቶች ነበሩት። 10 ዓመት ሲሞላው አባቱ ስለሞተ ሌላ ደግ ክርስቲያናዊ መስፍን ከቤቱ ወስዶ አሳደገው። በጦር ኃይልም አሠለጠነው። 20 ዓመት ሲሞላው የ15 ዓመት ልጅ ሊያጋቡት ሲሉ እግዚአብሔር የመስፍኑን ነፍስ ወስደ፤ ቅዱስ ዮርጊስም ወደ ቤሩት ሄደ።
v  በቤሩት ደራጎን ን ያመልኩና ሴት ልጃቸውን ይገብሩለት ነበርና በኃይለ መስቀል ድል ነስቶት ህዝቡን ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር አስገብቷቸዋል።
v  ወደፋርስ ቢመለስ ዱድያኖስ ሰባ ነገሥታት ሰብስቦ ሰባ ጣዖታት አቁሞ ሲሰግድ ሲያሰግድ ቢያገኛቸው ለሃይማኖቱ ቀናዒ ነውና ከቤተመንግስቱ ገብቶ “እኔ ክርስቲያን ነኝ በኢየሱስ ክርስቶስ አምናለሁ” አለው። እርሱም ማንነቱን ከተረዳ በኋላ  “አንተማ የኛ ነህ በ10 አህጉር ላይ እሾምሃለሁ የኔን አምላክ አጵሎንን አምልክ” አለው። ቅዱስ ጊዮርጊስም “ሹመት ሽልማትህ ለአንተ ይሁን እኔ አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስን አልክድም” አለ። በዚህ ጊዜ እጅግ ተናዶ መከራን አጸናበት እርሱ ግን “ይህን ከሀዲ እስካሳፍረው ድረስ ነፍሴን አትውሰድ” በማለት እግዚአብሔርን የለመነና እንደጸሎቱ የተደረገለት። በእምነቱም ጽናት የሰው ልጅ ሊሸከም የማይችለውን መከራ የተቀበለ ቅዱስ አባት ነው። ከእነዚህም መከራዎች ውስጥ፡
1.      በእንጨት አስቀቅሎ ሥጋውን በመቃን አስፈተተው
2.     ረጃጅም ችንካሮች ያሉበት የብረት ጫማ አጫምቶት ሂድ አለው። ቅዱስ ሚካኤልን ልኮለት ፈውሶታል።
3.     በሰባ (70) ችንካር አስቸንክሮ በእሳት አስተኩሶ አናቱን በመዶሻ አስቀጥቅጦ በሆዱ ላይ የደንጊያ ምሰሶ አሳስሮ እንዲያንከባልሉት አደረገ።
4.     ሥጋውን በመጋዝ አስተልትሎ ጨው ነስንሶበት ሥጋው ተቆራርጦ ወደቀ። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈቀ ሌሊት በእጁ ዳስሶ “ገና 6 ዓመት ለስሜ ትጋደላለህ፣ 3 ጊዜ ትሞታለህ፣ በ4ኛው ታርፋለህ።” አለው።
5.     ዱድያኖስ ደንግጦ “የሚያሸንፍልኝ ቢኖር ወርቅ እሰጠዋለሁ” ቢል አትናስዮስ የተባለ መሰርይ ከንጉሱ ላምን በጆሮዋ ሲያንሾካሹክባት ለሁለት ተሰንጥቃ ገድሏት ፈቃድን ተቀበለ። ሆድ በጥብጦ አንጀት ቆራርጦ የሚገድል መርዝ ቀምሞ አስማተ ሰይጣን ደግሞ ሰጠው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን ስመ እግዚአብሔርን ጠርቶ ቢጠጣው እንደ ጨረቃ ደምቆ  እንደ አበባ አሸብርቆ ተገኝቷል። ጠንቋዩም ማረኝ ብሎት ከመሬት ውሃን አፍልቆ ወደ ጌታችን ቢያመለክት ሐዋርያው ቶማስን በመንፈስ መጥቶ አጥምቆት በሰማዕትነት አርፏል።
6.     በመንኮራኩር አስፈጭቶ ከትልቅ ጉድጓድ ጥሎት ደንጊያ ዘግቶበት አትሞበት ሄዷል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  የተፈጨውን ሥጋ በእጁ ዳስሶ መንፈሱን መልሶ አንስቶታል፤ ተመልሶም “አምላኬ ከሞት አዳነኝ” ብሏቸዋል።
7.     በብረት አልጋ አስቸንክሮ ከበታቹ እሳት አንድዶበታል። እሳቱም ደሙ ሲንጠባጠብ ጠፍቷል።
8.     ዱድያኖስ “ኢየሱስ አምላክ መሆኑን አሳየኝ” ቢለው የለመለሙትን ዕፅ አድርቆ፣ የደረቁትን አለምልሞ፣ ከሞቱ 430 ዓመት የሆናቸውን ሙታንን አስነስሰቶ አሳይቶታል። ነገር ግን ልቡ ክፉ ነውና በረሀብና በጽም ይሙት ብሎ ምንም ከሌላት መበለት ቤት አሳስሮታል። እርሷም የሚቀመስ ስትፈልግ ቤቷን በእህል አትረፍርፎ የታሰረበት ግንድ አፍርቶ ልጇ ጆሮው የማይሰማ ነበርና ፈውሶላት መበለቲቷን ከነልጆቿ አጥምቆ ቅዱስ ሚካኤል ከእስራቱ ፈትቶት ተመልሷል።
9.     ዳግም በመንኩራኩር ፈጭታችሁ ደብረ ይድራስ ወስዳችሁ ዝሩት ብሎ አስፈጭቶ ሥጋውን ቢዘሩት ሥጋው ያረፈበት ሳር፣ ቅጠሉ፣ ደንጊያው፣ እንጨቱ  ሁሉ “ጊዮርጊስ ቅዱሱ ለእግዚአብሔር፣ ጊዮርጊስ ሰማዕቱ ለእግዚአብሔር፣” እያሉ አመስግነዋል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለሦስተኛ ጊዜ ከሞት አስነስቶታል። ሔዶም “አምላኬ ከሞት አዳነኝ” አላቸው። ጭፍሮቹ ደንግጸው ከእግሩ ስር ወደቁ። ከመሬት ውሃ አመንጭቶ ቅዱስ ዮሐንስ አጥምቋቸዋል።
10.    “ንጉሡ ልሹምህ ለአጵሎን ስገድ” ብሎ ቢለምነው እሺ ብሎ ገብቶ ሲጸልይ የንጉሱ ሚስት እለእስክንድርያ “ምን እያልክ ነው?” ብትለው አስተምሯት አሳምኗታል። ሲነጋ ንጉሱ በአዋጅ ህዝብን አሰብስቦ “ጊዮርጊስ ለጣዖቴ ሊሰግድ ነው’ ብሎ በተሰበሰበ ህዝብ መካከል አንድን ብላቴና (የመበለቷን ልጅ) “የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ ጊዮርጊስ ይጠራሃል” በል ብሎ ወደጣዖቱ ቢልከው ጣዖቱ ላይ ያደረው ሰይጣን እየጮኸ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለበት ቦታ መጣ፤ አምላክ አለመሆኑን አናዞት መሬት ተከፍታ እንድትውጠው አደረገ። ብዙ ሰዎች ይህንን ተዓምር አይተው አመኑ። ንጉሱን ሚስቱ እንዲመለስ ብትነግረው በአደባባይ አሰቅሎ አሰይፏት ሞታለች ደሟን ጥምቀት አድርጎላት ሰማዕት ሆናለች።
11.     በመጨረሻም በሰይፍ እንዲመተር አስደረገ። ቅዱስ ጊዮርጊስም ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃልኪዳን ተገብቶለት በ27 ዓመቱ በሚያዝያ 23 ቀን በ9፡00 ሰዓት ሰማዕት ሆኗል። አንገቱ ሲቆረጥ ውሃ፣ ደም እና ወተት ወጥቷል።
ሐ. ሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ
v  ሀገሯ አርማንያ ሲሆን አርማንያ በዘመነ ሰማዕታት ብዙ ቅዱሳን የተሰዉባት ሀገር ነበረች። በጥር 6 ቀን ሐሙስ ዕለት ተወለደች። አባቷ ቴዎድሮስ እናቷ አትናስያ ይባላሉ። በዘመነ ሰማዕታት በንጉስ ዲዮቅልጥያኖስ ጊዜ የነበረች ቅድስት ስትሆን አባቷ እንደ ካህኑ ዘካርያስ የሆነ ካህን ነበር።
v  ብሉይን ከሐዲስ ጠንቅቃ የተማረች ስትሆን በምንኩስና ንጽህ ጠብቃ በገዳ በጾም በጸሎት ተወስና የነበረች ቅድስት ናት።
v  ዲዮቅልጥያኖስ በባሪያዎቹ አማካይነት ከመነኮሳት መካከል በስዕል ተስላ የቅድስት አርሴማን ስዕል ተመልክቶ ድርጣድስን እንዲያመጡለት አድርጎ ንግሥት እንድትሆን ግድ ቢላት “የክርስቶስ ሙሽራ” መሆንን እንጂ የዚህን ዓለም ተድላ ደስታ እንደማትሻ ብትነግረው ግንቦት 11 ቀን 27 ከሚሆኑ መነኮሳትን አብሯት አሳስሮ ሳለ ከሰማይ የህይወት መጠጥ ያዘ ጽዋ ወርዶላታል።
v  ሰኔ 17 ቀን 9 በሰማዕትነት በሞት ያለፉትን ቅዱሳን ከሞት አስነስታቸዋለች።
v  በእስር ቤት ሳለች ዓይኗን አስወጥቶ ጣለው፤ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተገልጻ አጽናናቻት። ወደ አናብስት ዘንድ ከ27ቱ መነኮሳት ጋር አናብስቶቹ ግን ከእግሯ ስር ወድቀው ሰገዱላት።
v  በአርሴማ ጸሎት እና ሐዘን ድርጣድስ ከግፉ ብዛት የተነሳ እንደ ናቡከደነጾር እሪያነት (አሳማነት) ተለውጦ አምኜአለሁ በማለት ምህረትን ለመነ። በተዓምራትም ሊቁ ቅዱስ ጎርጎርዮስ አዳነው። (ጎርጎርዮስ ዘአርማንያ የቅድስት አርሴማ ወንድም ነው።)
v  ወታደሮቹ ከቅዱስ አርሴማ ጋር የነበሩትን መነኮሳት በሰይፍ አንገታቸውን ይቆርጡ ዘንድ ወሰዷቸው። የእግርግሪት አስረው በሰይፍ አንድ በአንድ ራሳቸውን ተራ በተራ መተሯቸው። አርሴማ ቅድስትም መነኮሳቱ የክብር አክሊልን ሲቀበሉ እየተመለከተች የእርሷን የሰማዕትነት ጊዜ ትናፍቅ ነበር።  የእርሷ ተራ በደረሰ ጊዜ ቅድስት አርሴማን ከአንገቷ በላይ የብርሃን ሰረገላን ይመልከቱ ነበር። ድርጣድስም የበለጠ መከራ እንድትቀበል ወዶ ጡቶቿን አስቆርጦ አንገቷ አስመትሮ በመስከረም 29 ቀን ሰማዕትነትን ተቀበለች። ከአንገቷም ደም፣ ማር፣ ውሃ፣ወተት ወጣ።
v  በዚህ በዘመነ ሰማዕታት ጊዜ ከኢትዮጵያ በቀን ከ1600 በላይ ቅዱሳን መነኮሳት የሰማዕትነት ክብር እንዳይቀርብን በማለት ወደ አርማንያ በመሄድ ሰማዕትነትን ይቀበሉ ነበር።
እንዲሁም፡
V  ሊቀካህኑ ዘካርያስ (የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ አባት)
V  ቅዱስ መርቆርዮስ
V  ሕፃኑ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ
V  ጊጋር ጥቂቶቹ ናቸው።
1.    ቅዱሳን ጻድቃን
ጻድቃን ማለት በሕግ የጸና ፣ እንደ ሕገ እግዚአብሔር የሚኖር እውነተኛ አካሄዳቸው ከእግዚአብሔር ፊት ያደረጉ እንደ ህግም ኖሩ ማለት ነው።
ቅዱሳን ጻድቃን የሚባሉት መላ ዘመናቸውን ከጣዕመ ዓለምና ከተድላ ዓለም ተለይተው ቤት ልስራ ዘር ልዝራ ሳይሉ ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው አስገዝተው በጾም በጸሎት በስግደት በምናኔ ጸንተው የኖሩ ናቸው። አኗኗራቸውም ድምፀ አራዊትን፣ ጸብዐ አጋንንትን ግርማ ሌሊትን ሳይሳቀቁ ዳዋ ጥሰው ድንጋይ ተንተርሰው ጤዛ ልሰው ነው።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አብነት አድርገው ጌታችን 40 መዓልትና 40 ሌሊት ከቆመ ሳይቀመጥ፣ ከዘረጋ ሳያጥፍ የፈጸመውን ስራ አብነት አድርገው ንጽሕና፣ በድንግልና፣ በብህትውና የኖሩ መነኮሳትና ባህታውያን ቅዱሳን ጻድቃን ይባላሉ።
ጥቅስ፡
v  እርሱ ጻድቅ እንደሆነ ጽድቅን የሚያደርግ ሁሉ ጻድቅ ነው። 1.ዮሐ.3፡7
v  ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል። ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም። ማቴ. 10፡41-42
v  ዓይኑን ከጻድቃን ላይ አያርቅም ለዘላለምም ከነገሥታት ጋር በዙፋን ላይ ያስቀምጣቸዋል፥ እነርሱም ከፍ ከፍ ይላሉ። ኢዮ.36፡7
v  እግዚአብሔር የጻድቃንን መንገድ ያውቃልና፥ የክፉዎች መንገድ ግን ትጠፋለች። መዝ.1፡6
v  የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮቹም ወደ ጩኸታቸው ናቸውና። … ጻድቃን ጮኹ፥ እግዚአብሔርም ሰማቸው ከመከራቸውም ሁሉ አዳናቸው።… የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው፥ እግዚአብሔርም ከሁሉ ያድናቸዋል።መዝ. 34፡15 – 19
v  ኃጢአተኞችን ክፋት ይገድላቸዋል ጻድቃንንም የሚጠሉ ይጸጸታሉ። መዝ.34፡21
v  ይህች የእግዚአብሔር ደጅ ናት ወደ እርስዋ ጻድቃን ይገባሉ። መዝ.118፡20
v  እግዚአብሔር የወደቁትን ያነሣል እግዚአብሔር ዕውሮችን ጥበበኞች ያደርጋቸዋል እግዚአብሔር ጻድቃንን ይወድዳል። መዝ.146፡8

 
ከእነዚህም ቅዱሳን ጻድቃን ውስጥ፡
ሀ. መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ
v  ዮሐንስ ማለት ፍሥሐ ወሐሴት ማለት ነው። አባቱ ካህኑ ዘካርያስ እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ይባላሉ። በቅዱስ ገብርኤል ብሥራት የተወለደ፣ ትንቢት የተነገረለት አባት ነው።(ሉቃ.1፡13፣ ኢሳ.40፡3-5) በ2 ዓመቱ ከመንፈቅ ሄሮድስ እንዳይገድለው ዚፋት (ዊፋት) ወደሚባል በረሃ እናቱ ይዛው ተሰዳ እናቱ በበረሃ ስታርፍ ቶራ የምትባል እንስሳ እያጠባችው አድጓል።
v  የግመል ጠጉር ለብሶ ፣ የበረሃ ማርና አንቦጣ እየተመገበ፣ 30 ዓመት ሲሞላው “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” እያለ የንስሐ ጥምቀትን ያጠምቅ ነበር።
v  ስለጌታችን እየመሰከረ መለኮትን ያጠመቀ፣ ንጉሥ ሄሮድስን የወንድሙ የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን ማግባት እንደሌለበት የገሰጸ፣ በጌታችን አንደበት “እውነት እላችኋለሁ፥ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም” ማቴ.11፡11 ተብሎ የተመሰከረለት ህይወቱን በብህትውና የኖረ ቅዱስ አባት ነው።
v  መስከረም 2 ቀን በ31 ዓ.ም በሄሮድያዳ ክፉ ምክር አንገቱ ቢሰየፍም 15 ዓመት አንገቱ ብቻ ዞራ ስታስተምር ከቆየች በኋላ በሚያዝያ 15 ቀን አርፋለች።

ለ. ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ
v  አባቷ ደረሲና (ዳረሳኒ) እናቷ እሌኒ ይባላሉ። ትውልድ ሀገሯ ሸዋ ቡልጋ ስሙ ጉዩ ከተባለው መንደር ነው። በ14 ዓመቷ ሰምረ ጊዮርጊስ የተባለውን ደገኛ ክርስቲያን አግብታ 12 ልጆችን ወልዳለች። የመጨረሻ ልጇንና ገረዷን ይዛ ደብረሊባኖስ ገዳም ገባች። ከአቡነ ተክለሐይማኖት ጋር ዝምድና ያላት የአንድ አያት ልጆች ናቸው።
v  በጸሎት ላይ ሳለችም የ3 ዓመት ልጇን ልታጠባ ስትል መልአክ እንዳትቸገር ታህሳስ 12 ቀን ነጥቆ ብሔረ ብጹዓን አስገባውና ዳግማዊ ቂርቆስ እንደተባለ ነገራት።
v  ይህች እናት ግንቦት 12 ቀን ሳጥናኤልን ታረቅና ምድር ይዳን ብላ የለመነች እና ሲዖል ድረስ ገብታ በጸጉርዋ እና በመላ ሰውነቷ ብዙ ነፍሳትን ይዛ የወጣች ትልቅ የምናኔ እናት ናት።
v  ጣዖት ያመልክ የነበረውን አሳምና የመለሰችና ያስጠመቀች፣ በደብረሊባኖስ 7 ዓመት በጣና ባህር ሄዳከባህሩ ላይ ቆማ 7 ዓመት፣ በሰውነቷ ውስጥ አሣ እስኪመላለስ የጸለየች ቅድስት እናት ናት።
v  በ 375 ዓመቷ በነሐሴ 24 ቀን አረፈች።
ሐ. ርዕሰ መነኮሳት ወገዳማት ቅዱስ እንጦንስ
v  ሀገሩ ግብጽ ሲሆን የተወለደበት ስፍራ ቅማ ትባላለች። አባቱ አብዳል መሲህ አዚዝ እናቱ ኡኸት አዚላ ይባላሉ። የባለጸጋ ልጅ ሲሆን በጥር 22 ቀን በ251 ዓ.ም ተወለደ። በ40 ዓመቱ በቅዱስ ሚካኤል እጅ መነኮሰ።
v  የመጀመሪያው መናኝ መነኩሴ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ቆብ ማድረግን ያመጣ የሥርዓተ ምንኩስና አባት ነው። ቅናተ ዮሐንስን፣ አስኬማ መላእክትን የተቀበለው በመልአኩ በቅዱስ ሚካኤል እጅ ነው። (በድንግልና ህይወት መኖርን ኤልያስ ቴስብያዊው ሲያመጣ፣ በበረሃ ገመድ ታጥቆ ብህትውናን ዮሐንስ መጥምቅ ሲያመጣ፣ ቅንአተ ዮሐንስን አስኬማ መላእክትን ኩርዓተ ርዕሱ አክሊለ ሶክን (ቆብን) እንጦንስ አምጥቶታል።
v  በገዳም 99 ዓመት ኖሮ በ 120 ዓመቱ  አርፏል።
መ. ጻድቁ አባ መቃርስ
v  አባቱ አብርሃም እናቱ ሣራ ይባላሉ። የተወለደው በመስከረም 14 ቀን ሲሆን ሀገሩ ግብጽ ነው። በግብጽ ደቡብ መኑፍ በተባለው ቦታ ልዩ ስሙ ሳስዶር ተወለደ። ያመነኮሰው የመጀመሪያው መነኩሴ በኩረ መነኮሳት የተባለው እንጦንስ ነው።
v  ይህ አባት ቆርቦ ከሰው ሳይነጋገር አፉን ሳይከፍት እጁን ከአፉ ላይ እንደያዘ 60 ዓመት ቆይቷል። ሲሄድም በደመና ተጭኖ አንዳንድ ጊዜም በነፋስ ላይ ይሄድ ነበር።
v  በጥቅምት 28 ቀን ጣዖት አምላኪዎች ረግጠው ተጭነውት በሰማዕትነት አርፏል።
 
እንዲሁም ፡
V  አባ ጳጉሚስ፣
V  አባ አጋቶን
V  ጻድቁ አቡነ ተክለሐይማኖት
1.   ቅዱሳን ሊቃውንት
ቅዱሳት መጻሕፍትን በእግዚአብሔር መንፈስቅዱስ ገላጭነት በመተርጎም ምዕመናንን በሃይማኖት ያጸኑ ቅዱሳን ሊቃውንት ናቸው። መናፍቃን የተሳሳተ ትምህርት ይዘው ሲነሱም መጽሐፍ አልበው፣ ኃይለቃል ስበው ተከራክረው የረቱ ናቸው።
ሃይማኖት እንዳይጠፋ፤ ትምህርተ ቤተክርስቲያን እንዳይፋለስ ሌት ከቀን በማስተማር ብዙ ደቀመዛሙርትን ያፈሩ ብዙ መጻሕፍትን የጻፉ ናቸው። ይህንን ሁሉ ሲያደርጉ እሳቱም፣ ስለቱም፣ እስራቱም፣ ግርፋቱም አልቀረላቸውም።
ዘመነ ሊቃውንት በክርስቶስ የተነገረውና በሐዋርያት የተሰበከው ቃለ ወንጌልም ሆነ የድኅነተ ዓለም ተግባር አፈጻጸም በስፋትና በጥልቀት የተመሰከረበት፤ የነገረ ሃይማኖት ቀኖና በዓለም አቀፍ ጉባኤ የተደነገገበት እና ሥርዓተ ቤተክርስቲያን አንድ ዓይነት መልክና ቅርጽ እንዲኖረው የተደረገበት የቤተክርስቲያን ወርቃማ ዘመን ነው። በተቃራኒውም የመናፍቃን መፍለቂያ ዘመንም ነበር። በዘመኑ የነበሩ ሊቃውንት ቅዱስ አትናቴዎስ (295-375)፣ እለእስክንድሮስ (312 – 328)፣ ቅዱስ ቄርሎስ (375 – 444)፣ ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሳርያ (370 – 379)፣ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ (329 – 389)፣ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ (370 – 395)፣ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ዘእስክንድርያ (444 – 454)፣ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ (347 – 407) የነበሩት ታላላቅ ሊቃውንት መናፍቃንን ደትተው ቤተክርስቲያናችንን መሰረቷን ሳትለቅ አቆይተውልናል። ከእነዚህም ውስጥ ጥቂቶቹን እንመልከት፤
ሀ. ዮሐንስ አፈወርቅ (347 – 407 ዓ.ም)
v  አባቱ አስፋኒዶስ ሴክንደ እናቱ አትናስያ እንቡሳ ይባላሉ። በመስከረም 9 ቀን በ321 ዓ.ም ተወለደ። ሀገሩ ግሪክ ሲሆን እናቱ በጥበብ መንፈሳዊ እንዲያድግ በአቴና አስገባችው። ሁሉንም ተምሮ ከአደገ በኋላ ቅዱስ ባስልዮስ ከነበረበት ገዳም ገባ። መጽሐፈ “አቅራቤ አኮቴት ዮሐንስ ቀዳማዊ ሊቀ ማኅቶተ ብርሃን ለቤተክርስቲያን” ይለዋል
v  ያመነኮሰው የአንጾኪያው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፊላታዎስ ሲሆን እርሱ ሲያርፍ በምትኩ ዮሐንስ አፈወርቅ በ397 ዓ.ም ሊቀጳጳስ ሆኖ የተሾመ የጊዜው ንጉስ አርቃድስን ያስተማረ፣ ከመንበሩ ላይ ያለችው ስዕለ እግዝእትነ ማርያም “ዮሐንስ አፈውርቅ” 3 ጊዜ በልሣነ ሰብእ የተናገረችለት፣ መልአክ ህፃን ሊቀስፍ ሲወርድ በግዝት 10 ዓመት ያቆየው ታላቅ አባት ነው።
v  “እሰግድ ለኪ፣ እሰግድ ለኪ፣ እሰግድ ለኪ …” የሚለውን በተዓምረ ማርያም ላይ የተጻፈውን የደረሰ፣ በስሙ የሚጠራውን ቅዳሴ ስለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መከራ፣ ሕማም፣ ሞት፣ “አልቅሱለት፣ ውደዱት…” የሚለውን ነገረ መለኮት ያለበትን 8 ዓይነት የሆነውን ቅዳሴ የደረሰ ሊቅ አባት ነው።
v  በግንቦት 12 ቀን በ86 ዓመቱ በአጥራክያ ደሴት በ407 ዓ.ም “ተፋቀሩ ደቂቅየ፤ ልጆቼ ተዋደዱ” እያለ አርፏል።
ለ. ሊቁ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ዘደሴተ ጋግራ
v  በመስከረም 7 ቀን ተወለደ። ቁጥሩም ከ25 ሊቃውንት (ሊቃነጳጳሳት) ውስጥ ሲሆን ዲዮስቆሮስ ማለት ለባሴ መስቀል ማለት ነው። (መከራን የሚቀበል ማለት ነው።)
v  በእርሱ ዘመን ጉባኤ ኬልቄዶን ከካቶሊካውያኑ ጳጳስ በአባ ሊዮን በ457 ዓ.ም የተደረገ ጉባኤ ሲሆን ከጉባኤ ኒቂያ እስከ ቁስጥንጥንያ ድረስ 58 ዓመት ነው። ከጉባኤ ኤፌሶን እስከ ጉባኤ ኬልቄዶን ድረስ 21 ዓመት ይሆናል። በዚህ ጊዜ እርሱና ዮሐንስ አፈወርቅ ተገኝተው ነበር። ቅዱስ ዲዮስቆሮስ በ433 ዓ.ም ተሾመና 14 ዓመት በሹመት ቆይቶ በኋላም በ516 ዓ.ም ዳግም ሾመውታው።
v  በጉባኤ ኬልቄዶን ብዛታቸው 636 የሆኑ ሊቃውንት ነን ባዮች የካቶሊክ ስብስቦች በጉባኤው ላይ 7 የመንፈስ ወንድሞቹን ይዞ ሊዮን ካቶሊኩን ሲከራከር ንጉሡ መርቅያን ሊዮንን ደግፎ ነበርና ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ሊዮንን ተከራክሮ ረታው፤ ሊዮንንም አወገዘው። እነርሱ ግን መርታት ባይችሉ ይዘው ጽሕሙን ነጭተው፣ ጥርሱን አውልቀው አሰቃዩት። እርሱም ለደቀመዛሙርቶች “ነዋ ፍሬ ሃይማኖት፤                    ” ብሎ ቢልክላቸው ጥርሱን መብራት እያደረጉ  ይጠቀሙበት ነበር።
v  ብዙ መከራን አድርሰውበት በንግስቷ ብርክልያም ሳይቀር እንዲክድ ሊያስማሙት ቢጥሩም ጸንቶ በእምነቱ በመገኘቱ ከ7ቱ የመንፈስ ወንድሞቹ ጋር መከራን አጽንተውበት በደሴተ ጋግራ እንዲሞት ብለው አግዘውት በግንቦት 7 (በዕለተ ልደቱ) በ60 ዓመቱ አርፏል። 5 ዓይነት መጻሕፍትና በስሙ የሚጠራ ቅዳሴ “ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ” በግዞቱ ሳለ ደርሷል።
ሐ. ሊቁ ቅዱስ አትናቴዎስ
v  አባቱ ሐኪም እናቱ ማርያም ይባላሉ። ወላጆቹ አረማውያን ነበሩ። በመስከረም 20 ቀን በ299 ዓ.ም ተወለደ። ትውልድ ሀገሩ በእስክንድርያ ጡፍ ዳር ነው። አትናቴዎስ ማለት በአለ ነቅዕ፣ አቢይ፣ ንጹህ ውሃ፣ ብርሃነ ዓለም ማለት ነው። በወጣትነት ዘመኑ ወደ አባ እንጦንስ ዘንድ ሄዶ ከእርሱ ጋር በበረሃ መንኖ የቆየ አባት ነው።
v  በዘመኑ የተነሳ አርዮስን በኑፋቄው እለእስክንድሮስ ሲያወግዘው አልቀበልም ብሎ ለቆስጠንጢኖስ ቢከሰው ቆስጠንጢኖስም ጉባኤ ይሰራ ብሎ በ325 ዓ.ም በኒቂያ ከመስከረም 21 - ሕዳር 9 ቀን በጥቁር ባህር አጠገብ በምትገኝው ደሱት በኒቂያ ሊቃውንት አርዮስን አውግዘው ሲለዩት አፈ ጉባኤው አትናቴዎስ ነበር።
v  ከእለእስክንድሮስ ቀጥሎ ለእስክንድርያ ቤተክርስቲያን 20ኛ ፓትርያርክ በመሆን መርቶ (ከ328 – 374 ዓ.ም) 46 ዘመናትን በሹመቱ ቆይቷል።
v  በራሱ ስም በተሰየመው ቅዳሴ ላይ ስለሰንበት፣ ስለበአላት፣ ስለሹማምንት፣ ስለምጽዋት፣ ስለክረምት አስፋፍቶ ጽፏል። ነገር ግን ከሐዲ ንጉስ የአርዮስ ወዳጅ ከሹመቱ አስነስቶ 7 ዓመት አሳደደው። በሀገሩም የአርዮስ ትምህርት ይሰጥ ጀመር። አትናቴዎስ ግን “ቢያከራክሩኝ እከራከራለሁ፤ ከገደለኝም በደስታ በሰማዕትነት እሞታለሁ” በማለት ተመለከ። ከሐዲ ንጉሱም ወደ ባህር ጣለው መልአኩ ግን ጠበቀው።
v  በሉቃስ ወንጌል ላይ “ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል?” ሉቃ.1፡34 የሚለውን በመንፈስቅዱስ ምሥጢር አብራርቶ በሃይማኖተ አበው ላይ የገለጸ፣ ጸሎተ ሃይማኖትን ያረቀቀ፣ አርዮስን የረታ፣ ለኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ለመጀመሪያ ጊዜ የሾመ ታላቅ ሊቅ ነው።
v  በ47 ዓመቱ በደሴተ ጋግራ በ75 ዓመቱ በ374 ዓ.ም በግንቦት 7 ቀን አርፏል።
መ. ሊቁ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮት
v  እናቱ ማርያም ትባላለች። ሀገሩ ቂሳርያ ነው። በ325 ዓ.ም ክርስትናን ተቀበለ። ነባቤ መለኮት ዘእንዚናዙ ይለዋል። በደራሲነቱ 24ቱ ምድራውያን መላእክት ከተባሉት ቅዱሳን ውስጥ አንዱ ነው። የቤተክርስቲያን ኮከብና ሐዋርያ እየተባለ በሃይማኖተ አበው ይጠራል።
v  ከሐዲው መቅዶንዮስ ከተሰደደ በኋላ በየካቲት 1 ቀን የተሾመ፤ ስለጌታችን አንድነትና ሦስትነት፤ አዳኝነት በጠቅላላው ስለነገረ መለኮት በሚገባ የተናገረ አባት ነው። (ሃይ.አበው ምዕ.8. በገጽ 210) በነገረ መለኮት መምህርነቱ ዳግማዊ ዮሐንስ ነባቤ መለኮት ተብሎ ተሰየመ። እንዲሁም ከተሾመ በኋላ መናፍቃንን አወገዘ። 33 ዓመት በሹመት ቆየ።
v  የአርመንን ኦርቶዶክስ ያቀና ታላቅ አባት ሲሆን መንበረ ሊቀጵጵስናውን የኖህ መርከብ ካረፈችበት የአራራት ተራራ ላይ አሰርቶ የኖረ ጻድቅ ነው። ይህ ሊቅ አባት በጥር 30 ቀን አርፏል።
ሰ. ሊቁ ባስልዮስ ዘቂሳርያ
v  ሀገሩ ቂሳርያ ሲሆን የጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ትልቅ ወንድም ነው። ባስልዮስ ማለት መብራት፣ ንጉሠ እግዚአብሔር ማለት ነው። 4 ወንድሞች ነበሩት ጴጥሮስ፣ መካርዮስ፣ ጎርጎርዮስ እና መካሪና ይባላሉ።
v  ሊቁ ባስልዮስ በተከራካሪነቱ ጥበበኛው ባስልዮስ የሚል ስም ነበረው። በልሳነ አረብና ግእዝ ሱርስት አንግልጠር ይሰብክ ነበር። በዚህም በስብከቱ ጊዜ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ እመቤታችን በላከችው መሰረት ባስልዮስ በጽርዕ፤ ቅዱስ ኤፍሬም በሱርስት ቋንቋ የአንዱ ለአንዱ ተገልጾለት ተነጋግረዋል። ሲያስተምር ቃለ እግዚአብሔር በእሳት ላንቃ ሆኖ በሰሚአኑ (በሚማሩት ምዕመናን) ራስ ላይ ሲያርፍ ቅዱስ ኤፍሬም ተመልክቷል። ከ10ቱ ማዕረጋትም ከዊነ እሳት (እሳት የመሆን) ደረጃ ላይ በመድረሱ ነፍሳት ከመጎናጸፊያው ላይ እየተኮማተሩ ሲወድቁም ተመልክቷል።
v  ቁጥሩ ከ318ቱ ሊቃውንት ውስጥ ሲሆን በኋላም የ33 ሊቃውንት መሪ ሆኗል። ከምድር እስከ ሰማይ የተተከለን ዓምደ ብርሃን ተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ አርዮስን አውግዞ ለይቶ ሲመለስ ተመልክቶ በጸሎት የማን እንደሆነ ሲጠይቅ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባስልዮስ እንደሆነ የተነገረለት አባት ነው።
v  8 ዓይነት ድርሰቶችን ደርሷል። በዚህም ውስጥ ስለ ነገረ መለኮት፣ ስለ ደጋጎችና ስለመናፍቃን ምላሽ ጽፏል። (ሃይ. አበው. ገጽ 419) በስሙ የተጠራ ቅዳሴም አለው፤ ድርሳነ ባስልዮስ፣ ተረፈ ባስልዮስ ዜና ባስልዮስ የተባሉ በስሙ የተጠሩ መጻሕፍት አሉ።
v  ሀብተ ትንቢትም ተሰጥቶታልና በጥር 25 ቀን ከወንድሙ ጋር ሲጸልዪ ከሐዲው በኩልያኖስ ሊገድላቸው እንደመጣ አይቶ በሰማዕቱ ቅዱስ መርቆሬዎስ ስዕል ሄደው ቢሰግዱ ስዕሉ በገዘፈ ሥጋ ሆኖ በጦር ገድሎላቸዋል።
v  ሊቁ በተወለደ በ99 ዓመቱ በጥር 6 ቀን አርፏል።
  ይቆየን...
የቦ/መ/ብ/ቅ/እግዚአብሔር አብ ቤ/ክ ሰ/ት/ቤት

No comments:

Post a Comment