1. ቅዱሳን ሰዎች
እግዚአብሔር ሰውን ከምድር አፈር አበጀው። ይህም ሰው ሥጋና ነፍስ (መንፈስ) ነው፤ ይህም ማለት ከ4ቱ ባህርያተ ሥጋና ከ3ቱ ባህርያተ ነፍስ መገኘቱን ሲያጠይቅ ነው። ይህንንም አብነት አድርገው ሰው የሚለው በግዕዙ “ሰብዐ” ትርጉሙ “ሰባት” ማለት ሲሆን ከአፈጣጠሩ ተነስቶ ሰው ይለዋል። አንድም ሰው ማለት ፍጹም ማለት ነው ለምን ቢሉ በዕብራይስጥ “ሰባት” ቁጥር ፍጹም ነውና። አንድም “ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር”(ዘፍ.1፡26) እንዳለ ሰው በአርዓያ ሥላሴ የተፈጠረ እግዚአብሔርን በባህርዩ የሚመስል መልካም ፍጥረት ወን። ሰው አስቀድሞ ህይወት ካለው እንስሳ ሳይሆን ግዑዝ ከሆነ ከአፈር መፈጠሩን መጽሐፍቅዱስ ይነግረናል።(ዘፍ.2፡7፣ 3፡19)
ሰው ሲፈጠር ቅዱስ፣ ጻድቅ፣ ሕያው ሆኖ ተፈጥሮ ነበር፤ በዚህም ምድር ፍጥረታት ገዢ፣ አምላክ ዘበጸጋ እንዲሆን እግዚአብሔር አድርጎት ነበር። በዚህም የአዳም የጸጋ አምላክነት እግዚአብሔር “አምላከ አማልእክት፡ የጸጋ አምላክ የሆነው አምላክ የሆንክ” ተብሎ ተመስግኗል፤ ተወድሷል። (መዝ.50፡1 “የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር ተናገረ፥ ከፀሓይም መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ምድርን ጠራት።”)
ስለዚህ የመጀመሪያው ሰው አዳም ከተፈጠረባት ዕለት አንስቶ በገነት በጽድቅ፣ በቅድስናና በህያውነት በእግዚአብሔር ፊት እንደተመላለሰ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ነገር ግን አዳም የተሰጠውን ትእዛዝ በማፍረስ (ዘፍ.2፡17) የሞት ሞትን ሞተ፣ እንግዳና መጻተኛ ሆነ፣ ተሰደደ.ተራቆተ በአጠቃላይ ጸጋውንና ክብሩን ቅድስናውን አጣ። ስለዚህም የሰው ልጅ የሰው ልጅ ህይወት በምድር ላይ ሁለት መልክእ ያለው ሆነ፡ የቅድስና ሕይወትና የርኩሰት ሕይወት ናቸው።
1. የርኩሰት ሕይወት (የኃጢአት ሕይወት)፡
ኃጢአት ትርጉሙ ስህተት፣ ክፋት፣ህግን መተላለፍ፣አመጻ፣ በጎ ማድረግን አውቆ አለመስራት፣ በእምነት መሰረት አለመኖር፣ ወደ እግዚአብሔር ክብር አለመብቃት ማለት ነው። (ሮሜ.3፡11፣12፡23፣14፡23፣ 1ዮሐ.3፡4፣ ራእ. 2፡10)
የሰው ልጅ የኃጢአት ህይወት ፡
ሀ. የውርስ (የዘር) ኃጢአት
ይህ ኃጢአት በአዳም ስህተት ምክንያት የሰው ዘር ሁሉ ኃጢአተኛ ሆኖ ነበር። ይህንን ኃጢአት መጽሐፍቅዱስ ሲያስረዳ፡
· ሮሜ.5፡12-18 “ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፥ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ፤”
· ኢዮብ.15፡14-16 “ንጹሕ ይሆን ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ጻድቅስ ይሆን ዘንድ ከሴት የተወለደ ምንድር ነው? እነሆ፥ በቅዱሳኑ ስንኳ አይታመንም ሰማያትም በፊቱ ንጹሐን አይደሉም።”
· ኢዮብ 25፡4-6 “ሰውስ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ይሆን ዘንድ፥ ከሴትስ የተወለደ ንጹሕ ይሆን ዘንድ እንዴት ይችላል? እነሆ፥ ጨረቃ እንኳ ብሩህ አይደለም፥ ከዋክብትም በፊቱ ንጹሐን አይደሉም። ይልቁንስ ብስብስ የሆነ ሰው፥ ትልም የሆነ የሰው ልጅ ምንኛ ያንስ!”
· መዝ.14፡2-3 “የሚያስተውል እግዚአብሔርንም የሚፈልግ እንዳለ ያይ ዘንድ እግዚአብሔር ከሰማይ የሰው ልጆችን ተመለከተ። ሁሉ ዐመፁ በአንድነትም ረከሱ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም አንድም ስንኳ የለም።”
ለ. የፈቃድ ኃጢአት፡
ከአዳም ዘር የወጡ ሰዎች ምንም እንኳን በዘር ኃጢአት ውስጥ ቢኖሩም ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ባለማስገዛት በህይወታቸው በፈቃደ ሥጋቸው በመመራት በጽድቅ መንገድ ፈንታ የኃጢአትን መንገድ፣ በአምልኮተ እግዚአብሔር ፈንታ አምልኮተ ጣዖትን መርጠው በኃጢአት የወደቁ ሰዎች ነበሩ።
ጥቅስ፡
· መዝ. 49፡12 “ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ አያውቅም እንደሚጠፉ እንስሶች መሰለ።”
· ት.ኢሳ.53፡6 “እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ።”
2. የቅድስና ሕይወት (ቅዱሳን ሰዎች)
v እግዚአብሔር በረድኤቱ ያደረባቸው
v ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ እግዚአብሔር ያስገዙ
v ከጥርጥርና ከክህደት ራሳቸውን የጠበቁ
v በተቀደሰ አኗኗር እግዚአብሔርን የመሰሉ
v በምሥጋና፣ በገድል፣ በትሩፋት ህይወታቸውን የመሩትን ቅዱሳን ሰዎች እንላቸዋለን።
በመሆኑም እግዚአብሔር ልጁን መልክእ እንዲመስሉ ወስኖ የጠራቸው፣ የመረጣቸው፣ ያጸደቃቸውና ያከበራቸው ሰዎች ቅዱሳን ሰዎች ናቸው።
ጥቅስ፡
· ማቴ.22፡14 “የተጠሩ ብዙዎች፥ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና።”
· 1ቆሮ.12፡27 “እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ። እግዚአብሔርም በቤተ ክርስቲያን አንዳንዶቹን አስቀድሞ ሐዋርያትን፥ ሁለተኛም ነቢያትን፥ ሦስተኛም አስተማሪዎችን፥ ቀጥሎም ተአምራት ማድረግን፥ ቀጥሎም የመፈወስን ስጦታ፥ እርዳታንም፥ አገዛዝንም፥ የልዩ ልዩ ዓይነት ልሳኖችንም አድርጎአል።”
እነዚህ ቅዱሳን ሰዎችን በ6 ክፍል ከፍለን እንደሚከተለው እንመለከታለን፡
1. ቅዱሳን ቀደምት አበው
እነዚህ ቅዱሳን በህገ ልቡናና በህገ ኦሪት በመመራት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኙና እግዚአብሔርም “አካሄዳቸው መልካም እንደሆነ” የመሰከረላቸው አባቶች ናቸው። ከእነዚህም ቅዱሳን ውስጥ፡
ሀ. ሔኖክ ወልደ ያሬድ
· የአዳም 7ኛ ትውልድ ነው።
· አባቱ ያሬድ እናቱ ባለካ ይባላሉ።
· ሐምሌ 25 ቀን ተወለደ፤ 165 ዓመት ከኖረ በኋላ ከአድኔ ማቱሳላን ወለደ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ።
· 6 ዓመት ከምግብ ተከልክሎ በእግረ ገነት በጾም ጸሎት ተወስኖ የኖረ፣ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገ መናኝ ቅዱስ አባት ነው።
· በጥር 26 ቀን በ365 ዓመቱ ወደ ብሄረ ሕያዋን አርጓል።
ለ.ኖኅ ወልደ ላሜህ
· አባቱ ላሜኅ እናቱ ቤቴናስ ይባላሉ።
· በሚያዝያ 6 ቀን ተወለደ፤ ሲወለድ ፊቱ እንደ ጸሃይ የሚያበራ ሰውነቱ እንደ እንቁ ነጭ የሆነ ዓይኑን በገለጠ ጊዜ ቤቱ ሁሉ ያበራ ነበር፤ ከእናቱም እጅ በተነሳ ጊዜ ስብሐተ እግዚአብሔርን ያደረሰ ከማኅጸን ጀምሮ የተመረጠ አባት ነበር። (ሔኖክ 41፤17-20)
· ኖኅ ማለት ደስታ፣ ዕረፍት፣ አዳኝ፣ ጎህ፣ ታማኝ ማለት ነው።
· 500 ዓመት ሲሆነው ከአምዛራ ሴም፣ ካምንና ያፌትን ወለደ። (ኩፋ. 6፤7፡ ዘፍ.5፤32)
· ለሊቀመልአኩ በሱርያል አማካይነት ምድርን በንፍር ውሃ እንደምትጠፋ ተነግሮት መርከብ ሰርቷል፤ ሕዝቡንም አስተምሯል።
· ከራሱ ጋር 8 ሰዎችን እንስሳትን ይዞ ባለ 3 ክፍሏ መርከብ ውስጥ አስገብቷል፤ በግንቦት 27 ቀን ከተነገረው በ93 ዓመት የንፍር ውሃ 40 ቀንና ሌሊት ዘነበ። ኖኅም ከእግዚአብሔር ቃልኪዳንን የተቀበለ አባት ሲሆን ይህም በቀስተደመና ተገልጦለታል።
· አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ በ950 ዓመቱ በጥር 6 ቀን አርፏል።
ሐ. አብርሃም ወልደ ታራ
· አብርሃም ማለት አበብዙሃን (የብዙዎች አባት) ማለት ሲሆን አባቱ ታራ እናቱ እድና ይባላሉ እናቱ ስሙን በእናቱ አባት (በአያቱ) ስም አብራም አለችው ታላቅ አባት ማለት ነው።
· እግዚአብሔርን ተመራምሮ ያገኘ ሥላሴን በአንድንትና በሦስትነት የተመለከተ፣ የተቀበለ ከጣዖት አምላኪ ቤተሰቡ ተለይቶ ለእግዚአብሔር ፍቅር ራሱን የለየ ልጁን ለእግዚአብሔር ሲል ለመስዋዕት ያቀረበ ታላቅ አባት ነው።
· የአዳም 21ኛ ትውልድ ሲሆን አባቱ ሚስት ባገባ በ71ኛው ዓመት በነሐሴ 29 ቀን ተወለደ።
· አባትና እናቱ የጣዖት ፍቅር ቢኖርባቸውም እርሱ ግን፡
o በሥነ-ፍጥረት ተመራምሮ አምላኩን ያገኘ
o በእግዚአብሔር ጥሪ ከወገኖቹ ተለይቶ ሚስቱ ሦራ ትባል የነበረችውን ሣራን፣ የጎቱን ልጅ ሎጥን፣ ይዞ ከካራን ወደ ከነዓን የወጣ፤
o መልከጼዴቅን በእግዚአብሔር ትእዛዝ ያገኘው፤
o በእንግዳ ተቀባይነቱ የታወቀ የተመሰከረለትና በሐምሌ 7 ቀን ሥላሴን በእንግድነት ከቤቱ የተቡለትና በእርጅናው ዘመን ይስሐቅን እንደሚወልድ ተስፋ ተሰጥቶት የተፈጸመለት፤
o ንጉስ አቤሜሌክን በጸሎቱ ያስማረ
o ስለ ሰዶምና ገሞራ በእግዚአብሔር ፊት የቆመ
o እግዚአብሔር “ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፥ እነዚህንም ምድሮች ሁሉ ለዘርህ እሰጣለሁ የምድርም አህዛብ ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ” ዘፍ. 26፤4 በማለት ተስፋ የተሰጠው አባት ነው።
o አብርሃም ልጁ ይስሐቅን ለእርብቃ የባቱኤል ልጅ አጋብቶ በሀብቱና በንብረቱ አሰልጥኖ በ175 ዓመቱ ነሐሴ 29 ቀን አርፏል። (ዘፍ. 25፡5-11)
o አብርሃም በአጸደ ነፍስም እያለ ህዝቡ መምህራነ ቤተክርስቲያንን በመስማት ከኋለኛው ሞት እንዲድኑ ያስተማረና በምልጃው ያልተለየን አባት ነው። (ሉቃ. 16፡19 -31)
መ. ሙሴ ወልደ አንበረም
· አባቱ አንበረም እናቱ ዮካብድ ይባላሉ። በነሐሴ 13 ቀን እሑድ 3844 ዓ.ዓ ተወለደ።
· ነገዱ ከሌዊ ወገን ሲሆን የፈርዖን ልጅ ከባህር ከውሀ አውጥቸዋለሁ ስትል ሙሴ አለችው።
· 40 ዓመት ሲሞላው የአማቱን የዮቶርን በጎች ሲጠብቅ በኮሬብ ተራራ መስከረም 8 ቀን ነበልባል ከሀመልማል ተስማስቶ ተመልክቶ እግዚአብሔርም በዚያ ተገልጾለት በፈርዖን ላይ አምላክ አድርጎት ወንድሙ አሮንን ደግሞ ነብይ አድርጎለት በ10 መቅሰፍት በ11ኛ ስጥመተ ባህር (በባህር ውስጥ መስጠም) 85 ሺህ የፈርዖን ሠራዊትንና ፈርዖንን በባህር በማስጠም እስራኤላውያን ፍጹም ነጻነትን እንዲያገኙ ያደረገ ታላቅ አባት ነው።
· 40 ዘመን እስራኤላውያንን በምድረ በዳ የመራ፤ መናን ከሰማይ ያወረደና ይከተላቸው ከነበረው ዓለት ላይ ውሃን ያፈለቀ፤ ከመቅሰፍት ይድኑ ዘንድ የነሀስ እባብን የሰቀለ፣ 570 ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል በቃል የተነጋገረና በግንባሩ ላይ ብርሃን የተሳለበት፤ ለህዝበ እስራኤል በእግዚአብሔር ፊት የቆመ ታላቅ አባት ነው።
· በሚያዝያ 8 ቀን 40 መዓልትና ሌሊት ቆይቶ ሕገ ኦሪትን (ጽላትን) የተቀበለ እና ጣዖትን የደመሰሰ ቅዱስ ነው።
· ማርና ወተት የምታፈልቀውን የተስፋይቱን ምድር ከነዓንን በሩቅ ተሳልሞ ሥርዓትን የሰራልን አባት ነው።
· በ120 ዓመቱ በሞአብ ተራራ በቤተ ፊጎር በእለተ አርብ የካቲት 17 ቀን በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤልና በሌላ መልአክ የተቀበረ ታላቅ አባት ነው።
ሠ. ኢያሱ ወልደ ነዌ
· ኢያሱ ማለት መድኃኒት እና እግዚአብሔር አዳኝ ነው ማለት ነው፤ የመጀመሪያ ስሙ አውሴን ሲባል ኢያሱ ብሎ የጠራው ሙሴ ነው። (ዘኁ.13፡16)
· ትውልዱ ከነገደ ኤፍሬም ሲሆን በመስከረም 4 ቀን ተወለደ፤ አባቱ ነዌ ይባላል።
· ኢያሱ ከሙሴ ሕግ አንዷንም አልጣለም ነበር፤ ስለዚህም ኢያሱ ነቢይም መስፍንም ካህንም ነበር።
· እግዚአብሔር ከሙሴ ጋር እንደነበረ ከኢያሱም ጋር እንዳለ ያነጋገረው፤ ያጽናናው (ኢያ. 1፡5-7)በገባዖን ፀሐይን በጸሎት ያቆመ፤ እስራኤላውያንን በዮርዳኖስ ባህር በደረቅ ያሻገረ፤ በድምጽ የኢያሪኮ ግንብን ያፈረሰ፤ አሕዛብን ድል ነስቶ ርስት ያከፋፈለ፤ “የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ። እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን።” (ኢያ. 24፡15) በማለት እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ የሙሴን ህግ በኤባል ተራራ ላይ ለሕዝቡ ያነበበ፡ በሕዝቡና በእግዚአብሔር ፊት ምስክር ይሆን ዘንድ 3 ገጻት ያሉት ደንጊያ ሐውልት በሴሎ በደብተራ ኦሪት አጠገብ የተከለና ቃልኪዳን ያስገባ ታላቅ አባት ነው።
· በተወለደ በ110 ዓመቱ በኤፍሬም ሀገር ያረፈ ታላቅ አባት ነው።
ይቆይን...
የቦ/መ/ብ/ቅ/እግዚአብሔር አብ ቤ/ክ ሰ/ት/ቤት
No comments:
Post a Comment