13

.

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው::" የማቴዎስ ወንጌል 7: 4

"እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅናወተት ግዙ።" ትንቢተ ኢሳይያስ 55 : 1

Friday, October 21, 2011

ነገረ ቅዱሳን ክፍል 1




“ነገረ - ቅዱሳን”
እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ።
ኦ.ዘሌ.11፡45


በቦሌ መንበረ ብርሃን ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን
ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት ክፍል
የዓውደ - ርዕይ ዝግጅት

አዘጋጆች፡
ተስፋሚካኤል አበራ
ወንድወሰን ስለሺ   .



ሰኔ 22 ቀን 2003 ዓ.ም

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
የቦሌ መ/ብ/ቅ/እግዚአብሔር አብ ቤ/ክ ሰ/ት/ቤት
በዓውደ - ርዕይ የነገረ ቅዱሳን ዓምድ
ክፍል 1 ቅድስና
የቅድስና ትርጉም
ቅዱስ የሚለው ቃል በዕብራይስጥ ቅዳሽ፣ በሱርስት ቃዲህ፣ በዐረብኛና በግዕዝ ቅዱስ ይላል። ትርጓሜውም፤
1.      አመሠገነ
2.     ለየ፣መረጠ፣አከበረ
3.     መለወጥ፣ ለውጥ (ከክፋት ወደ መልካምነት የመለወጥ እድገት ዘፀ. 26፤33-35፣ ዘፀ.30፤6፣ ዕብ.9፤21) ማለት ነው።
ስለዚህም ቅዱስ የሚለው ቃል ለብዙ ሲነገር “ቅዱሳን” ወይም “ቅዱሳት” ይሆናል።
ጥቅስ፡
·         ሥጋም ሁሉ የተቀደሰውን ስሙን ይባርክ። መዝ.144፤21
·         ከማኅጸን ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ። ት.ኤር. 1፤4
·         .
የቅድስና ዓይነት
ሁለት ዓይነት ቅድስና አለ፤
1.    የባህርይ ቅድስና፡
ቅድስና የባህርይ ገንዘብነቱ ለእግዚአብሔር ብቻ ነው። የእግዚአብሔር ባህርይ ስንል በሐዋርያት ሃይማኖት ውሳኔ እንደተገለጠው ለእግዚአብሔር ባህርይ ጥንተ ምክንያት የለውም። ግን የማይታወቅ ባህርይ በፍጥረቱ ተገልጧል። (ሮሜ 1፤20 “የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና)። ባህርይ ክብር ተብሎ ይተረጎማል (2ጴጥ. 1፤4 ስለ ክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት አምልጣችሁ ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች በተስፋ ቃል እንድትሆኑ፥ በእነዚያ ክብርና በጎነት የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋን ሰጠን።) ከዚህም ሌላ ግብርን ያሳያል እግዚአብሔር ቅድመ ዓለም በአንድነትና በሦስትነት ያለ፤ ባህርዩ ባህርዩን እያመሰገነው ምስጋናው ያልተቋረጠ ክብሩ ያልጎደለ አምላክ ነው። ይህም እግዚአብሔር በባህርዩ፤
v  ቅዱስ ነው (ት. ኢሳ. 6፤3 “አንዱም ለአንዱ። ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያለ ይጮኽ ነበር።”)
v  ቸርና ለጋስ ነው። (መዝ.33፡5 “ጽድቅንና ፍርድን ይወድዳል የእግዚአብሔር ቸርነት ምድርን ሞላች።” ሮሜ.2፡4” ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን?”)
v  ፍቅር ነው። (1ዮሐ.4፡8” ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፥ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና።”)
v  መንፈስ ነው። (ዮሐ.4፡24 “እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል።”)
v  ብርሃን ነው። (1ዮሐ.1፡5” እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም የምትል ይህች ናት።”)
v  በራሱ ንጹህ ነው። (ት.ዕንባቆም1፡13” ዓይኖችህ ክፉ እንዳያዩ ንጹሐን ናቸው፥ ጠማምነትንም ትመለከት ዘንድ አትችልም)
v  እውነት ነው፣ ታማኝ ነው። (ዮሐ.14፡6” ኢየሱስም፦ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።” ዘኁ.23፡19” ሐሰትን ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አይደለም፥ ይጸጸትም ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም። እርሱ ያለውን አያደርገውምን? የተናገረውንስ አይፈጽመውምን?” 2ጢሞ.2፡13 “ባናምነው፥ እርሱ የታመነ ሆኖ ይኖራል፤ ራሱን ሊክድ አይችልምና።”)
v  ባለሙሉ ባለሥልጣን ነው። (ሮሜ.9፡15 “የምምረውን ሁሉ እምረዋለሁ ለምራራለትም ሁሉ እራራለታለሁ ይላልና።”)
v  አልፋና ኦሜጋ ነው። (ራእይ 21፡6 “አልፋና ዖሜጋ፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ።”)
v  ኤልሻዳይ ነው። (ዘፍ.17፡1 “እኔ ኤልሻዳይ ነኝ በፊቴ ተመላለስ፥ ፍጹምም ሁን”)
ጥቂቶቹ የእግዚአብሔር ባህርያት ናቸው።
ስለዚህ የአምላካችን የልዑል እግዚአብሔር መጠሪያ ስሙ “ቅዱስ” ነው። (ሉቃ. 1፡49 “ብርቱ የሆነ እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራ አድርጎአልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው።”)
ጥቅስ፡
·         እንደ እግዚአብሔር ቅዱስ የለምና እንደ አምላካችን ጻድቅ የለምና ከአንተ በቀር ቅዱስ የለም። (1ሳሙ.2፡2)
·         ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የነበረውና ያለ የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ እያሉ ቀንና ሌሊት አያርፉም። ራእ.4፡8
·         እንግዲህ እተካከለው ዘንድ በማን መሰላችሁኝ ይላል ቅዱሱ። ኢሳ.40፡25
·         አምላካችን እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ አድርጉት ቅዱስ ነውና ወደ እግሩ መረገጫ ስገዱ። መዝ. 98፡5
·         ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ ስራህ ታላቅና ድንቅ ነው፤ አንተ ብቻ ቅዱስ ነህ። ራእ.15፤4
·         እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝ። ዘሌ. 19፡2

2.   የጸጋ ቅድስና
ጸጋ በግሪክ ቃል “ካሪስ” ሲሆን ሞገስ፣ ፍቅር፣ ምህረትና ቸርነት በሚል ይተረጎማል። አንድም ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ስጦታ ማለት ነው። (ሮሜ.12፡6 “እንደ ተሰጠንም ጸጋ ልዩ ልዩ ስጦታ አለን” ኤፌ.3፡8-9 “ፍለጋ የሌለውን የክርስቶስን ባለ ጠግነት ለአሕዛብ እሰብክ ዘንድ፥ ሁሉንም በፈጠረው በእግዚአብሔር ከዘላለም የተሰወረው የምሥጢር ሥርዓት ምን እንደሆነ ለሁሉ እገልጥ ዘንድ ይህ ጸጋ ከቅዱሳን ሁሉ ይልቅ ለማንስ ለኔ ተሰጠ፤”) እንዲል። ይህም በበጎነት፣ ያለብድራትና ያለዋጋ የሚደረግ ስጦታ ማለት ነው። በመሆኑም ማናቸውም ከእግዚአብሔር የሚገኝ ሀብት ሁሉ ጸጋ ይባላል። መጽሐፍ ቅዱስ በጎነት፣ ቸርነት፣ ምህረት፣ ስጦታ እያለ የሚገልጸው ለእግዚአብሔር የባህርይ ገንዘቡ ስለሆነውና ከእግዚአብሔር ለሰው ልጆች ስለሚሰጠው ጸጋ ነው። (መዝ.15(16)፡1 “እግዚአብሔርን፦ አንተ ጌታዬ ነህ አልሁ ከአንተ በቀር በጎነት የለኝም።” መዝ.33(34)፡5 “ጽድቅንና ፍርድን ይወድዳል የእግዚአብሔር ቸርነት ምድርን ሞላች።”)
እግዚአብሔር ጻድቅና ቅዱስ እንደሆነ የእርሱን ፈለግ ተከትለው በቅድስና ህይወት የተጓዙ ቅዱሳን ይባላሉ። ይህም ከባህርይ ቅድስና (ከእግዚአብሔር ዘንድ) ለፍጥረቱ የተሰጠ ሲሆን እርሱ “ቅዱስ” እንደሆነ እነርሱም “ቅዱሳን” ይባላሉ። በአጠቃላይ ለእግዚአብሔር የተለየ ሁሉ “ቅዱስ” ነው።
ጥቅስ፡
·         እርሱ ጻድቅ እንደሆነ ጽድቅን የሚያደርግ ጻድቅ ነው። 1ዮሐ. 3፡7
·         በእውነት የተቀደሱ እንደሆኑ እኔ እራሴን ስለእነርሱ እቀድሳለሁ። ዮሐ 17፡19 (የሰው ልጅ ቅዱስ ይሆን ዘንድ ራሱን የተቀደሰ መስዋዕት አድርጎ ሥጋውን ቆርሶና ደሙን አፍስሶ ቅድስናን ለሰው ልጅ እንደሰጠ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተናገረ።)
·         እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ። ዘሌ11፡45
·         እኔ እግዚአብሔር ቅዱስ ነኝና፥ ለእኔም ትሆኑ ዘንድ ከአሕዛብ ለይቻችኋለሁና ቅዱሳን ትሆኑልኛላችሁ። ዘሌ.20፡26
·         ዳሩ ግን። እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ። 1ጴጥ. 1፡15-16

የጸጋ ቅድስና የተሰጣቸው ፍጥረታት
1.    ቅዱሳን መላእክት
መላእክት የሚለው ቃል ለአከ ከሚለው የግዕዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ላከ ማለት ነው፤ በብዙ ሲተረጎም መልእክተኞች ማለት ነው። ስራቸው ከእግዚአብሔር ወደ ሰው፤ ከሰው ወደ እግዚአብሔር መላላክ ስለሆነ ነው። መላእክት ተፈጥሯቸው “እምሀበ አልቦ ሀበቦ፡ ካልተፈጠረ ነገር የተገኙ ናቸው፤ ከአምላካዊ ብርሃን የተገኙ ሲሆን ግብራቸውን ወይም ስራቸውን ሲገልጽ “መላእክቱን መንፈስ የሚያደርግ፥ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል።መዝ.103(104)፡4”በማለት ሲገልጽ “ከእሳት ከነፋስ ፈጠራቸው እርሱ እንደሆነ ስላወቁ እነሳቸው በተዋረደ ልቡና ፈጣሪያቸውን ያመሰግኑታልና ከትዕዛዙም አይወጡም።መ. መቃብያን 13፡15” ይላል አክሲማሮስ አለበለዚያ ከተፈጠረ የተፈጠሩ ቢሆን ኖሮ እንደእኛ ሟች በሆኑ ነበር።
ቁጥራቸው የብዙ ብዙ ሲሆን ምግብና መጠጣቸው፤ እረፍትና ደስታቸው የእግዚአብሔርን ስም በመጥራት በማመስገን ስብሐተ እግዚአብሔርን ማድረስ ነው።
ጥቅስ፡
·         ዙፋኖቹም እስኪዘረጉ ድረስ አየሁ በዘመናት የሸመገለውም ተቀመጠ፤ ልብሱም እንደበረዶ ነጭ የራሱም ጸጉር እንደጥሩር ነበር። ዙፋኑም የእሳት ነበልባል ነበር መንኮራኩሮቹም የሚነድ እሳት ነበሩ፣ የእሳትም ፈሳሽ ከፊቱ ይፈልቅና ይወጣ ነበር ሺህ ጊዜ ሺህ ያገለግሉት ነበር፥ እልፍ አእላፋትም በፊቱ ቆመው ነበር ፍርድም ሆነ፥ መጻሕፍትም ተገለጡ። ት.ዳን. 7፡8-9
·         አየሁም፥ በዙፋኑም በእንስሶቹም በሽማግሌዎቹም ዙሪያ የብዙ መላእክትን ድምፅ ሰማሁ፤ ቍጥራቸውም አእላፋት ጊዜ አእላፋትና ሺህ ጊዜ ሺህ ነበር፥ ራእይ 5፡11
·         እነሆ ከዚህች በለስ ፍሬ ልፈልግ ሦስት ዓመት መጣሁ ምንም አላገኘሁም ቁረጣት ስለምን መሬቱን ታጎሳቁላለች አለው እርሱ ግን መለሰ ጌታ ሆይ ዜሪያዋን እስክኮተኩትላትና ፋንድያ እስካፈስላት ድረስ ደግሞ በዚህች ዓመት ተዋት ወደፊት ብታፈራ ደህና ነው አለዚያ ግን ትቆርጣታለህ። ሉቃ.13፡6 በማለት መልአኩ በበለስ ለተመሰለው የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ፊት እንዳማለደ ይገልጻል።
ሊቃነ መላእክት የሚባሉት
ሊቃነ መላእክት
የነገዱ ስም
ሀገራቸው
ኪሩብ
ኪሩቤል

ሱራፊ
ሱራፌል

ቅዱስ ሚካኤል
ኃይላት
ኢዮር
ቅዱስ ገብርኤል
አርባብ
ራማ
ቅዱስ ሩፋኤል
መናብርት
ራማ
ቅዱስ ሱርኤል
ሥልጣናት
ራማ
ቅዱስ ሰዳክያል
መኳንንት
ኤረር
ቅዱስ ሰላትኤል
ሊቃናት
ኤረር
ቅዱስ አናንኤል
መላእክት
ኤረር
  
የመላእከት ሥልጣናቸውና ክብራቸው፡
1.    ኃይላቸው፡ ቅዱሳን መላእክት የተሠጣቸው ሥልጣንና ኃይል ታላቅ ነው።
v  ት.ዳን.10፡5-9 “አካሉም እንደ ቢረሌ ይመስል ነበር፥ ፊቱም እንደ መብረቅ ምስያ ነበረ፥ ዓይኖቹም እንደሚንበለበል ፋና፥ ክንዶቹና እግሮቹም እንደ ጋለ ናስ፥ የቃሉም ድምፅ እንደ ብዙ ሕዝብ ድምፅ ነበረ።እኔም ዳንኤል ብቻዬን ራእዩን አየሁ፥ ከእኔ ጋር የነበሩ ሰዎች ግን ራእዩን አላዩም ነገር ግን ጽኑ መንቀጥቀጥ ወደቀባቸው፥ ሊሸሸጉም ሸሹ።… የቃሉንም ድምፅ ሰማሁ የቃሉንም ድምፅ በሰማሁ ጊዜ ደንግጬ በምድር ላይ በግምባሬ ተደፋሁ።”
v  ማቴ.28፡1-4 “እነሆም፥ የጌታ መልአክ ከሰማይ ስለ ወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ቀርቦም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ። መልኩም እንደ መብረቅ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበረ። ጠባቆቹም እርሱን ከመፍራት የተነሣ ተናወጡ እንደ ሞቱም ሆኑ።”
2.   በፍርድ ቀን ተሳትፎ አላቸው።
v  ማቴ.13፡39-43 “እንክርዳዱም የክፉው ልጆች ናቸው፥ የዘራውም ጠላት ዲያብሎስ ነው፤ መከሩም የዓለም መጨረሻ ነው፥ አጫጆችም መላእክት ናቸው። እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል፥ በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል። የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፥ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ፥ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።”
v  ማቴ.25፡31 “የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፥ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል”
v  ማቴ.24፡31 “መላእክቱንም ከታላቅ መለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፥ ከሰማያትም ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ ነፋሳት ለእርሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ።”
v  1 ተሰ. 4፡16 “ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፥ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ፤”
3.   ተዓምራትን ያደርጋሉ።
v  መሳ.13፡19 “ማኑሄም የፍየሉን ጠቦትና የእህሉን ቍርባን ወስዶ በድንጋይ ላይ ለእግዚአብሔር አቀረበው። መልአኩም ተአምራት አደረገ፥ ማኑሄና ሚስቱም ይመለከቱ ነበር። ነበልባሉም ከመሠዊያው ላይ ወደ ሰማይ በወጣ ጊዜ የእግዚአብሔርም መልአክ በመሠዊያው ነበልባል ውስጥ ዐረገ ማኑሄና ሚስቱም ተመለከቱ፥ በምድርም በግምባራቸው ተደፉ።”
v  ሐዋ.12፡6-15 “እነሆም፥ የጌታ መልአክ ቀረበ በቤትም ውስጥ ብርሃን በራ፤ ጴጥሮስንም ጎድኑን መትቶ አነቃውና። ፈጥነህ ተነሣ አለው። ሰንሰለቶቹም ከእጁ ወደቁ።”
4.   አመጸኞችን ይቀጣሉ
v  ዘፍ.19፡11 “ሁለቱም ሰዎች እጃቸውን ዘርግተው ሎጥን ወደ እነርሱ ዘንድ ወደ ቤት አገቡት መዝጊያውንም ዘጉት። በቤቱ ደጃፍ የነበሩትንም ሰዎች ከታናሻቸው ጀምሮ እስከ ታለቃቸው ድረስ አሳወሩአቸው ደጃፉንም ለማግኘት ሲፈልጉ ደከሙ።”
v  2ነገ.19፡35 “በዚያችም ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ ወጣ፥ ከአሦራውያንም ሰፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ገደለ ማለዳም በተነሡ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሁሉ በድኖች ነበሩ።”
v  ሐዋ.12፡20-23 “ከጢሮስና ከሲዶና ሰዎችም ጋር ተጣልቶ ነበር፤ በአንድ ልብ ሆነውም ወደ እርሱ መጡ፥ የንጉሥንም ቢትወደድ ብላስጦስን እሺ አሰኝተው ዕርቅ ለመኑ፥ አገራቸው ከንጉሥ አገር ምግብ ያገኝ ነበረና። በተቀጠረ ቀንም ሄሮድስ ልብሰ መንግሥቱን ለብሶ በዙፋን ተቀመጠ እነርሱንም ተናገራቸው፤ ሕዝቡም። የእግዚአብሔር ድምፅ ነው የሰውም አይደለም ብለው ጮኹ። ለእግዚአብሔርም ክብር ስላልሰጠ ያን ጊዜ የጌታ መልአክ መታው በትልም ተበልቶ ሞተ።”
5.   የጸጋ ጌትነት አላቸው
v  መ.ኢያሱ 5፡14 “እርሱም፦ አይደለሁም፤ እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ሆኜ አሁን መጥቼአለሁ አለ። ኢያሱም ወደ ምድር በግምባሩ ተደፍቶ ሰገደና። ጌታዬ ለባሪያው የሚነግረው ምንድር ነው? አለው።”
v  ዘፍ.19፡2 “ሁለቱም መላእክት በመሸ ጊዜ ወደ ሰዶም ገቡ ሎጥም በሰዶም በር ተቀምጦ ነበር። ሎጥም ባያቸው ጊዜ ሊቀበላቸው ተነሣ ፊቱንም ደፍቶ ወደ ምድር ሰገደ፥ አላቸውም፦ጌቶቼ ሆይ፥ ወደ ባሪያችሁ ቤት አቅኑ፥ ከዚያም እደሩ፥ እግራችሁንም ታጠቡ ነገ ማልዳችሁም መንገዳችሁን ትሄዳላችሁ። እነርሱም፦ በአደባባዩ እናድራለን እንጂ፥ አይሆንም አሉት።”
v  ት.ዳን.10፡16-20 “እነሆም፥ የሰው ልጅ የሚመስል ከንፈሬን ዳሰሰኝ የዚያን ጊዜም አፌን ከፍቼ ተናገርሁ በፊቴም ቆሞ የነበረውን፦ ጌታዬ ሆይ፥ ከራእዩ የተነሣ ሕመሜ መጣብኝ፥ ኃይልም አጣሁ። ይህ የጌታዬ ባሪያ ከዚህ ከጌታዬ ጋር ይናገር ዘንድ እንዴት ይችላል? አሁንም ኃይል አጣሁ፥ እስትንፋስም አልቀረልኝም አልሁት።”

 ይቆየን...

No comments:

Post a Comment