በዲ/ን ቴዎድሮስ ጌታቸው
የቦ/መ/ብ/ቅ/እግዚአብሔር አብ ቤ/ክ ም/ስብከተ ወንጌል ኃላፊ
የቦ/መ/ብ/ቅ/እግዚአብሔር አብ ቤ/ክ ም/ስብከተ ወንጌል ኃላፊ
ወደ ሴት አትመልከት በልብህም አታመንዝር፡፡ ማቴ. 5፤28
ይህ ወደ ሴት በመመልከት በልቡና የሚያድረው ፍትወተ ሥጋ ኃጢአት መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ ሴትን ማየት ሳይሆን ባዩአት ጊዜ ለፈቃደ ሥጋ መመኘትን ነው፤ እግዚአብሔር የማይፈቅደው ለዚህም ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል “ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርሷ ጋር አመንዝሯል፡፡” በማለት የተናገረው፤ “አይቶ የማይሰናከል ዓይን” የተባለውን ፍትወተ ተራክቦን አውጥቶ መጣልና መንግሥተ ሰማያትን ገንዘብ ማድረግ በማየት የሚመጣ ምኞትን በመፈጸም በገሃነም ከመጣል እጅጉን ይሻላል፤ ይበልጣልም፡፡ ማቴ. 5፤28
አንዳንድ ጊዜ ሰዎች የሚያነሱት ጥያቄ አለ፤ ጥያቄውም በእምነት ውስጥ ያሉትንም የሚጨምር ነው፤ ይኸውም ዓይን የተፈጠረው ለማየት ነው፤ ስለዚህ ማየት እንዴት ኃጢአት ሊሆን ይችላል› ይላሉ፡፡ ነገር ግን ሊስተዋል የሚገባው አንድ ነገር አለ፤ ጌታችንም በወንጌል ሲያስተምር ወደሴት ያየ ብቻ አላለም፤ ይህ ማለት ማየት ብቻውን ኃጢአት አይደለም ማለት ነው፡፡ ነገር ግን የተመኛት ቢኖር “ያን ጊዜ በልቡ አመነዘረ” ነው ያለው፡፡ ይህ ማለት አንድ ወንድ አንዲ ሴትን ተመልክቶ በልቡ ከርሷ ጋር በዝሙት ለመውደቅ መመኘቱ ነው ትልቁ ኃጢአት ምክንያቱም ያ ሰው በልቡ ያለውን የዝሙት ስሜት ለመፈጸም የተመቻቸ ሁኔታ ስለሌለ እንጂ በልቡ ያንን ክፉ ኃጢአት ፈጽሞታልና ነው፡፡ በቅዱ መጽሐፍም ላይ ምኞት የሚያመጣውን ኃጢአትና በደል እንማራለን፡፡ አዳምና ሔዋን ዕፀበለስ የማይጠቅማቸው እደሆነ በአምላካቸው ቢነገራቸውም እነርሱ ግን ለመብላት ጎመጁ፤ ተመኙ፤ ነው የሚለን፤ ነገር ግን ይ ክፉ ምኞታቸው የሞትን ሞትን አመጣባቸው፡፡ ዘፍ. 3፤1-24
ታላቁ አባታችን ቅዱ ዳዊት በእግዚአብሔር እንደ ልቤ የተባለው አባት በሕይወቱ ዘመን እግዚአብሔርን የበደለበትና ያሳዘነበትን ኃጢአት የፈፀመው ከክፉ የሥጋ ምኞት የተነሳ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ 2 ሳሙ.11፤1-26 ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብም እግዚአብሔር ማንንም በክፉ እንደማይፈትን ነገር ግን ሰው በሥጋዊ ምኞት ሲጓዝና ሲታለል እንደሚፈተን አስተምሯል፡፡ ያዕ. 1፤12-15
ስለዚህ ዓይን ሁሉን ይመለከታል ወደ ልቡና መዝገብ የሚልከው ግን ቀልቡ ያረፈበትን ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ወንድ ሴትን፤ ሴትም ወንድን በክፉ የኃጢአት ምኞት መመልከት አይገባም፤ በልቡናም ለዝሙትና ለሥጋ ፈቃድ ማሰብ ታላቅ በደል ነው፡፡ የሀሳብ ፍጻሜው ተግባር ነው፤ የሥጋ ምኞት ኃጢአትን ይወልዳል፡፡ የኃጢአት ክፍያው ደግሞ ሞት ነው፡፡ ያዕ. 1፤15 ስለዚህም በማየት (በመመኘት) መዘዝ ከሚመጣ ውድቀት ለመዳን ይህን ሕገ ወንጌል በሚገባ መረዳትና ዓይነ ሥጋን ብቻ ሳይሆን ዓይነ ልቡናንም መቆጣጠር ያስፈልጋል፡፡ በተለይ በወጣትነት ዘመን ላለን ሁሉ ትልቁ ፆር ይህ ዓይነቱ ነውና ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት በመሸሽ ሰውነታችንን ለቅድስናና እግዚአብሔርን ደስ ለሚያሰኝበት ሕይወት እንድናዘጋጅ ቸሩ አምላካችን ይርዳን፡፡
ይቆየን
No comments:
Post a Comment