በመሪጌታ አዲስ መሀሪ
የ “ቅኔ” ማለት ምን ማለት ነው›
ቅኔ የሚለው ኃይለ ቃል መገኛው “ቀነየ” ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ገዛ ማለት ነው፡፡ በግስ ርባታ “ወ”ን እና “የ”ን መድረሻ ያደረገ ማንኛውም የግስ ዓይነት ደጊመ ቃል ካልኖረው በስተቀር ጎርዶ ወይም ሳይጎርድ ይነገራል፡፡ ለምሳሌ፡ “ቅኔ” የሚለው ቃል የተገኘው ቀነየ ከሚለው የግስ መድረሻ ፊደል “የ”ን ጎርዶ የተነገረ መሆኑን ከቃሉ ላይ መረዳት ይቻላል፡፡ “ቅኔ” የሚለው ቃል በተለያዩ የመስኩ ሊቃውንት ፤ መምህራን የተለያየ ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ “ቅኔ”ን አንዳንዶች “ሰርዋድ” ሲሉት አንዳንዶች ደግሞ ጥሬ ዘር ይሉታል፤ ይህም የአረባብ ዘዴውን በተመለከተ ሲሆን የቃሉ ትርጉም ደግሞ ግዛት፤ አገዛዝ የሚል አንድምታ ይኖረዋል፡፡
የቅኔ ባህርይ
ቅኔ፡ ሰፊና ለምርምር ፈጠን የሚያደርግ፤ ለግኝትና ለድርሰት ብቁ የሚሆን ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው ነው፡፡ የቅኔ መዋቅራዊ ይዘት ከእብራይስጥ፤ ከግሪክና ከዐረብኛ ቋንቋዎች ጋር ከፍተኛ ዝምድና እና ትስስር አለው፡፡ ለዚህም ከግእዝ ቋንቋ ውስጥ ወስደን በንጽጽር መልክ እናያለን፡፡ “ርሑቅ” ይላል የቃሉ ትርጉም “እሩቅ” ማለት ሲሆን በእብራይስጥ ደግሞ “ርሖቅ” ሲል ይደመጣል ትርጉሙም ከግእዙ ጋር ተመሳሳይ ስለሆነ “እሩቅ” የሚል ሆኖ እናገኘዋልን፡፡ ግእዝ በአጠቃላይ ከእብራይስጥ፤ ከግሪክ እና ከዐረብኛ ቋንቋዎች ከፊደል መመሳሰል ጀምሮ እስከ ቋንቋው መዋቅራዊ ሥርዓት ድረስ እጅግ በጣም የተቀራረበ ስልት እና ትርጉም ይታይበታል፡፡ ቅኔ ማህበራዊ ጠቀሜታው የላቀ ነው፤ የረዘመውንና የተንዛዛውን አሳጥሮ የሚፈለገውን መልእክት ለማስተላለፍ ይጠቅማል፡፡
በአንድ ማኅበረ ሰብእ ውስጥ ቋንቋ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ ከተለያዩ ሰዎች ጋር የባህር ልውውጥ ለማድረግና ለመገበያየት በሰፊው ያገለግላል፡፡ ለምሳሌ፡ እንግሊዘኛን ብንወስድ የዓለማችን መገናኛ እና መግባቢያ በመሆኑ ብዙሃን የሚሆነው የዓለማችን ሕዝብ በመጠኑም ቢሆን ይናገረዋል፡፡ በዓለማችን ላይ የሚሰሩት ሞባይልን ጨምሮ የተለያዩ ማሽኖች በብዛት የሚሰሩት የዚህን ቋንቋ ተናጋሪ ህዝብ ታሳቢ በማድረግና ማዕከል በማድረግ ነው፡፡ ይህ ሲባል ሌላ ቋንቋ አያስፈልግም ለማለት አይደለም፡፡ በዓለማችን ላይ በሺህ የሚቆጠሩ ቋንቋዎች አሉ፡፡ ኢትዮጵያን ብንወስድ ከ80 በላይ ቋንቋዎች አሏት፡፡ እኚህም ቋንቋዎች ብርቅዬና የማይጠገቡ ልዩ ስጦታዎቻችን ናቸው፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ ከሚገኙት ቋንቋዎች ውስጥ የግእዝ ጥንታዊ ብሄራዊና ታሪካዊ ቋንቋ በመሆኑ እንዴት ማሳደግና በብዙሃኑ ዘንድ እንደቀድሞው አገልግሎቱን ይስጥ ጥያቄያችን ሊሆን ይገባል ይህ ቋንቋ የ80 ሚሊየን የኢትዮጵያ ህዝብ ሀብት ነውና፡፡ ቅኔ የሚለው ብሂልም የተገኘው የኢትዮጵያ የመጀመሪያ ቋንቋ ከሆነው የግእዝ ቋንቋ ነው፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ ታሪካውያን ቦታዎች የግእዝን ማንነት ከፍ አድርገው ይናገራሉ፡፡ የቱሪስት መስህብ በመሆን የዓለምን ሕዝብ ቀልብ በቁጥጥር ስር ያደረጉ ከድንጋይ ተፈልፍለው የታነጹ አብያተክርስቲያናት እና ሐውልቶች በሙሉ መግባቢያቸው የግእዝ ቋንቋ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
የዘመናችን ወጣት ሆይ በፍልፍል ዋሻዎችና ገዳማት ውስጥ ለጥበብና ለምርምር ሊሆኑ የሚችሉ እና ድብቅ የጥበብ ምንጭነት ያላቸው የብራና መጻሕፍት የሚዳስሳቸው አጥተው ወርቃቸውንና ጠገራ ብራቸውን የቀበሩበትን ቦታ ሳይጠቁሙን በሞት ዋዜማ ላይ ይገኛሉና ንቃ ብለን የውርስ ባለቤት መሆን ይኖርብናል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ወራሽ የሌላቸው ተብለው ባዕድ ለመውረስ ቅድመ ዝግጅቱን እያጠናቀቀ መሆኑን መግለጥ እንሻለን፡፡ ለምሳሌ፡ የተለያዩ ጠቃሚነታቸው የላቀ አያሌ በብራና የተጻፉ የምርምር መጻሕፍት እንደ በእንግሊዝና ጀርመን የመሳሰሉት ሀገራት እየተወሰዱ ለእነርሱ አዲስ ግኝት እና ምርምር ፍንጭ ሆነዋቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሥርዓተ አምልኮውን የሚፈጽመው በግእዝ ቋንቋ መሆኑን ለጸሎት የምንጠቀምባቸው መጻሕፍት ዋቢ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ለምሳሌ፡ መዝሙረ ዳዊት፤ ድጓ፤ ጾመ ድጓ፤ መጽሐፈ ቅዳሴ፤ ጸዋትውና ምዕራፍ የተሰኙት ጥቂቶቹ የሥርዓተ አምልኮቱ መፈጸሚያ መጸሕፍት ናቸው፡፡
በመሆኑም በቤተክርስቲያናችን አጠቃላይ ቁልፍ ሚና የሚጫወተው የ”ቅኔ” ትምህርት ነው፡፡ ስለሆነም ያለዘርና ሃይማኖት ልዩነት ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ ቢኖር ቅኔን ከነ ግእዝ ቋንቋ ጠንቅቆ ሊያጠኑት እና ሊመሩበት ይገባል እንላለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔርምንጭ፡ ፍኖተ - ብርሃን መጽሔት በቦ/መ/ብ/ቅ/እግዚብሔር አብ ቤ/ክ ሰ/ት/ቤት የታሕሳስ/2003 ዓ.ም እትም
No comments:
Post a Comment