13

.

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው::" የማቴዎስ ወንጌል 7: 4

"እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅናወተት ግዙ።" ትንቢተ ኢሳይያስ 55 : 1

Tuesday, September 6, 2011

ኢትዮጵያ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአሥራት አገር ናት፡፡

  
             ሊቃውንትም ነቢያት የተነበዩትን ትንቢት የቆጠሩትን ሱባዔ መሠረት በማድረግ ቅድስት ድንግል ማርያም በኪደተ እግሯ ኢትዮጵያን መባረኳን ያስተምራሉ፡፡ «ነቢዩ ዕንባቆም የኢትዮጵያ ድኳኖች ሲጨነቁ ዐየሁ፤» ዕንባ. 3፡7 ብሎ የተናገረው ቃለ ትንቢት እመቤታችን የኢትዮጵያን አውራጃዎች ለመባረኳ ማስረጃ መሆኑን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይተረጉማሉ፤ ያመሠጥራሉ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ኢትዮጵያን ለእናቱ አሥራት አድርጐ በመሥጠቱ በእርሷ በኩል ለሰው ልጆች ሁሉ የሚሆን የነገረ ድኅነት ምሥጢር በመከናወኑ ኢትዮጵያውያን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የተለየ ፍቅር አለን፡፡ የአብነት /የቆሎ/ ተማሪዎች በትምህርት ዓለም ከአንዱ ወደሌላው እየተዘዋወሩ /የአብነት/ ትምህርት ሲማሩ በእንተ ስማ ለማርያም፤ ስለማርያም እያሉ፡፡ የእመቤታችን ስም ስንቅ ምግብ ሆኗቸው ይጠቀሙበታል፡፡ ግሼን ደብረ ከርቤ የልጇ ግማደ መስቀል ከከተመበት አምባም የሚጓዙ ምእመናን «አንድ እፍኝ ሽምብራ አልያዝኩም ከቤቴ ስሟ ስንቅ ነው የእመቤቴ» እያሉ በፍቅሯ ተማርከው ግብር ሰፍረው ዕጣን ቋጥረው ሱባዔ እየገቡ ይማፀኗታል፡፡ እርሷም ከልጇ ዘንድ ባገኘችው የመወደድ ሞገስ ምልጃቸውን በመቀበል ጸሎታችውን በማሣረግ የእናትነት ሥራ ሥትሠራላቸው ኖራለች፡፡ ዛሬም እየሠራች ነው፡፡ እመቤታችን ከልጇ ያገኘችውን /የተቀበለችውን ቃል ኪዳን መሠረት በማድረግ በዐራቱ ማእዘን «ሰዓሊ ለነ ቅድስት፤ ቅድስት ሆይ ለምኝልን» የማይላት የለም፡፡ በፍቅሯ ተደስተው በአማላጅነቷ ተማምነው «የእመቤቴ ፍቅሯ እንደ ሰማይ ክዋክብት፣ እንደምድር አሸዋ በዝቶልኝ፣ እንደ ልብስ ለብሼው፣ እንደምግብ ተመግቤው» እያሉ ተማጽነው ልመናቸው ሠምሮ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊው፣ ቅዱስ ያሬድ ዘኢትዮጵያና አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ያዘጋጁላትን፣ አባ ጽጌ ድንግል የደረሱላትን የምስጋና መጻሕፍት በመድገም እመቤታችን ዘወትር መማጸን የቀደምት ኢትዮጵያውያንም የዛሬዎች ገዳማውያንና ምእመናን ዕለታዊ ግብር ነው፡፡

ጌታችን ለቀደሙት ቅዱሳን ሐዋርያት እመቤታችን አማላጅ እና እናት ሆኗ እንድታገለግል በገቢርም በነቢብም ከአደራ ቃል ጋር አስረክቧል፡፡ በገቢር በቃና ዘገሊላ የሰውን ችግር ፈጥና የምትረዳ ርኅርኅሪት እናት አማላጅ መሆኗን አሳይቷል፡፡ «ለዚሁም የወይን ጠጅ አልቆባቸዋል» ብላ ያቀረበችው ቃለ ምልጃ ምስክር ነው፡፡ እናት ሆኗ እንድታጽናናቸው በቅዱስ ዮሐንስ በኩል ከእግረ መስቀሉ ስር ሰባቱን አጽራሐ መስቀል ሲያስተጋባ ቅዱስ ዮሐንስን ጠርቶ «እኖኋት እናትህ፤ ድንግል ማርያምን ጠርቶ እነሆ ልጅሽ» ዮሐ. 19፡26፡፡ በማለት እመቤታችን የእናት ሥራ ለሁሉም ቅዱሳን ሐዋርያት እንድትሠራላቸው ምእመናንም ልጅ እንዲሆኗት በማያሻማ ቃሉ ተናግሯል፡፡
ቅዱሳን ሐዋርያት እመቤታችንን በእናትነት ከተረከቧት ጊዜ ጀምረው ልጇ በዕርገት በአካለ ሥጋ ሲለይ እንደ ልጅ አገልግለዋታል፡፡ በቤታቸው አኑረዋታል፤ ብትሠወርባቸው ፈልገዋታል፡፡ ብትርቃቸው ናፍቀዋታል፡፡ እርሷም ሲጠሯት ታደምጣቸዋለች፣ ሲፈልጓት ትገኝላቸዋለች፡፡ ይኸውም የሆነው ልጇ በአዳምና በልጆቿ ኃጢአት ምክንያት የፈረደውን ለራሱም ያላስቀረውን ሥጋዊ ሞት እናቱ ብትቀምስ በእናትነት የተረከቧት ቅዱሳን ሐዋርያት መካነ ዕረፍት ለይተው በንጹሕ በፍታ ከፍነው በጌቴ ሰማኒ እንደቀበሯት ስለ እመቤታችን የተጻፉ መጻሕፍት በዝርዝር ያስረዳሉ፡፡
የእመቤታችን ሥጋዊ ዕረፍት «ከመ ትንሣኤ ወልዳ» እንደ ልጇ ትንሣኤ ነውና ሙስና መቃብር ሳያገኛት ከሦስት ቀናት ሥጋዊ ዕረፍት በኋላ ከሞት ተነሥታ ወደ ሰማይ ስታርግ በዕለተ ቀብሯ ያልተገኘው ቅዱስ ቶማስ ደመና ጠቅሶ በደመና ሰረገላ ሲመጣ ዕርገቷን ይረዳል፡፡ እማኝ ደግሞ የተከፈነችበትን በፍታ /ጨርቅ/ ይቀበላታል፡፡ ለቅዱስ ቶማስ የተገለጠው የዕረፍቷ ምሥጢር ሌሎች ቅዱሳን ሐዋርያት እንዲገለጥላቸው ቢማጸኑ እመቤታችን ዳግም ተገልጻላቸው፡፡ ትንሣኤዋን ለማየት በቅተዋል፡፡
እነዚህ በቅድስናቸው የተመሠከረላቸው ቅዱሳን እመቤታችንን በሁለት ሱባዔ ማግኘታቸውን መሠረት በማድረግ በቤተ ክርስቲያናችን ከነሐሴ 1-16 በየዓመቱ አንደሚጾም ይታወቃል፡፡ ይህ እመቤታችንን የምንማጸንበት ጾመ ፍልሰታ ቤተ ክርስቲያናችን መፍትሄ የምትፈልግባቸውን ጉዳዮች ለእመቤታችን የምታቀርብበት ሰዓት ነው ብለን እናምናለን፡፡

ኢትዮጵያ የእመቤታችን አሥራት አገር ስትሆን እመቤታችን ለኢትዮጵያውያን እናት መሆኗ እየተነገረ ለምን በፈተና ውስጥ አለፍን? ልጇ በአሥራት ኢትዮጵያን የሰጠባት ሀገር አባቶች ማስፈራሪያ ሲደርስባቸው መንፈሳዊነት /ኀይለ መንሳዊ/ ተዘንግቶ ሥጋዊ ጥበብ በቤተ ክርስቲያን መድረክ ሲታይ ምን ይባላል? «እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋት ርኩሰት በተቀደሰችው ሥፍራ ቆሞ ስታዩ አንባቢው ያስተውል በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራራዎች ይሽሹ» ማቴ. 24፡15፡፡ የተባለው ቀን ደርሶ ይሆንን?
ቤተ ክርስቲያን ለረጅም ዓመታት ለገጠማት ችግር መፍትሔ እመቤታችን እጅ ላይ አለ ብለን እናምናለን፡፡ እመቤታችን ብትሠወርባቸው አባቶች ሱባዔ ገብተው እንዳገኟት የፍቅር እናት ናትና ፍቅር አንድነት እንድትሰጠን እርሷን መማጸን፤ የዶኪማስን ጓዳ እንደሞላች የጐደለውን እንድትሞላ ውዳሴዋን እየደገሙ ድንግልን መማጸን ያስፈልጋል፡፡

በውዳሴ ማርያም፣ በጸሎተ ማርያም የሚመካ በጉልበቱ አይመካም፡፡ ጊዜ ረዳኝ ብሎ በወገኖቹ ላይ ግፍ አይፈጽምም፡፡ ስለዚህ በዚህ በወርኀ ጾም እመቤታችን ምልጃዋ ከአገራችን፣ ከቤተ ክርስቲያናችን ጋር እንዲሆን በሱባዔ እንማጸናት፡፡
በጾመ ፍልሰታ ከሊሂቅ እስከ ደቂቅ በማስቀደስ፣ በጾምና በጸሎት ሁለቱን ሳምንታት እንደሚያሳልፉት ይታወቃል፡፡ በሱባዔው የቤተ ክርስቲያናችን ችግሮች የሚወገድበት ምእመናን በበረከት የሚጐበኙበት ቅድስና የሚሰፍንበት መንፈሳዊነት ትልቅ ከበሬታ የሚገኝበት ጾም እንዲሆን ሁሉም ምእመን መትጋት አለበት፡፡

ሁለቱ ሳምንታት በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ዘወትር እየተገኘን ምሕላ የምናደርስበት፣ የተጣላነውን ይቅር ለእግዚአብሔር፣ የበደልነውን የምንክስበት ጾም መሆን አለበት፡፡ ቀናቱን እየቆጠርን እስከተወሰነው ሰዓት ብቻ መጾም ብቻ በሕይወታችን መሠረታዊ ለውጥ አያመጣም፡፡ እመቤታችን የአገራችን አሥራት የሁላችን እናት በመሆኗ የእናትነት ሥራ እንድትሠራልን በሚገባ ልንማጸናት ይገባል እንጂ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ሱባዔ ብለን ውዳሴ ማርያም በደገመ አፋችን ሰው የምናማ በሰው ሕይወት ገብተን የምንፈተፍት ከሆነ እመቤታችንን አናውቃትም፡ እመቤታችንም አታውቀንም፡፡ ስለዚህ ጾመ ፍልሰታን እስኪ ሁላችን ኢትዮጵያውያን የተዋሕዶ ልጆች ድንግልን በአንድ ድምፅ እንጥራት፡፡
የእመቤታችንን ጾመ ፍልሰታ፤ እንደ ብርሃን ተስፋ በማድረግ በተለይም ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚተጉ አባቶች እና ምእመናን ለተሰደዱ፣ ለተራቡ፣ በፈተና ውስጥ ለሚገኙ ይማጸኑ እንላለን፡፡ ውዳሴ ማርያሙ፤ ሰዓታቱ ጨለማን ተገን አድርጐ ከሚቃጣ ማስፈራሪያ እና ዛቻ ድርብ ኀይል አለው፤ እስኪ ለቅድስና፣ ለንጽሕና ለመንፈሳዊነት ቅድሚያ እንስጥና የእግዚአብሔርን ብድራት እንጠብቅ፡፡ ጾመ ፍልሰታ መንፈሳዊነት፣ እውነት፣ ቅድስና የጠራ አሠራር፣ በቤተ ክርስቲያን የሚሰፍንበት እንዲሆን እንመኛለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Source: Kidane-Mihrt.org by G/M

No comments:

Post a Comment