13

.

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው::" የማቴዎስ ወንጌል 7: 4

"እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅናወተት ግዙ።" ትንቢተ ኢሳይያስ 55 : 1

Friday, January 18, 2013

ምሥጢረ ጥምቀት



በመምህር ፍቅረማርያም ባዘዘው
የቦሌ መ/ብ/ቅ/እግዚአብሔር አብ ቤ/ክ የመጽሐፍ መምህር
ጥምቀት
ጥምቀት ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ከዘጠኙ አበይት በዓላት መካከል ሲሆን፤ ይህ የጥምቀት ስርዓት የሚካሄደው በመዝፈቅ ነው፡፡ ይህም፤
V  ጥምቀት ዳግመኛ ተወልደን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የምንገባበት ምሥጢር ነው፡፡ ዮሐ.3፤5
V  በጥምቀት ኃጢአት ይሰረያል ሐዋ. 2፤8
V  መንጻትና መቀደስም በጥምቀት ነው፡፡ 1ኛ ጴጥ. 3፤21
የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት
ይህ ጥምቀት የሰው ልጆች የዕዳ ደብዳቤ የተደመሰሰበት ጥምቀት ነው፡፡ ይህ ማለት ሰይጣን በአዳምና በሔዋን አገዛዝ አጽንቶባቸው በነበረ ሰዓት እኛ የአንተ ባርያ ነን በማለት “አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ፤ ሔዋን አመቱ ለዲያብሎስ” የሚል የዕዳ ደብዳቤ አንዱ በዮርዳኖስ አንደኛው ደግሞ በሲዖል ጥሎት ነበር፤ በዮርዳኖስ ያለው በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ተደምሷል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል “ወደምሰሰ ለነ መጽሐፈ ዕዳነ በሥርያቱ እምዕደውነ” ቆላስይስ 2፤14 ይህም ማለት የዕዳ ደብዳቤያችንን ከባላንጋራችን ከዲያብሎስ አጠፋልን (ደመሰሰልን) ማለት ነው፡፡ ይህ  የዕዳ ደብዳቤ የባርነት ደብዳቤ ነበር፡፡ ጌታችን በዮርዳኖስ ሲጠመቅ እንደሰውነቱ ረግጦ፤ እንደአምላክነቱ አቅልጦ አጥፍቶልናል፡፡ ቅዱስ ኤፍሬምም “ወሰጠጠ መጽሐፈ ዕዳዎሙ ለአዳም ወለሔዋን፤ የአዳምንና የሔዋንን የዕዳ ደብዳቤ ደመሰሰላቸው”” ነው የሚለው የሰኞ ውዳሴ ማርያም፡፡ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ለእርሱ የሚጠቅመው ሆኖ ሳይሆን መጠመቁ ለእኛ ክብር ነው፡፡
ትንቢተ ሕዝቅኤል 36፤25 “ጥሩ ውሀንም እረጫችኋለሁ እናንተም ትጠራላችሁ፤ ከርኩሰታችሁም ሁሉ ከጣዖቶቻችሁም ሁሉ አጠራችኋለሁ፡፡” አለ፤ ይህም የሚያስተምረን በጥምቀት የነጻን የተቀደስን እኛ መሆናችንን ነው፡፡ የጌታችን ጥምቀትን ስናስብ የተቀደስንበትና የነጻንበት የዕዳ ደብዳቤያችን የተደመሰሰበት መሆኑን ነው፡፡
ጥምቀቱን በውሀ ያደረገበት ምክንያት
ውሀ ድሀ፤ ባለፀጋ ሳይል በሁሉም የሚገኝ በመሆኑ እንዲሁም ውሀ ብንጠጣው ሕይወት የሚሆን፤ ታጥበን የምንነጻበት …ወዘተ በመሆኑ ጌታም የመጣ ለሁሉም ሰው እንዲሁም ድሀ ባለጸጋ ሳይል ሁሉንም የሚያፈቅር አባት መሆኑን ለማስተማር ነው፡፡
ጥምቀቱን በዮርዳኖስ ስለምን አደረገው
1.  ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የአዳምና የሔዋን የዕዳ ደብዳቤ አንዱ በዮርዳኖስ ስለነበር ያን ለመደምሰስ ነው፡፡
2.  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ እንደሚጠመቅ ትንቢት ተነግሮ ነበር፡፡                                          መዝ. 113፤3-6
3.  በዮርዳኖስ ንህማን ከለምጹ የተፈወሰበት ነው፡፡ 2ኛ. ነገ.5፤8- ፍጻሜ
4.  አባታችን ኢዮብ የተፈወሰበት ነው፡፡

ጌታችን በ30 ዓመቱ ለምን ተጠመቀ
ብዙ ጊዜ ሰዎች የሚከራከሩበት በመሆኑ ነው፤ ይህም አንዳንዶቹ “ጌታ የተጠመቀ በ30 ዓመቱ ነውና እኛም እንደ እርሱ በ30 ዓመት መጠመቅ አለብን” ይላሉ፡፡ ይህ ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ  ጋር እኩል ነኝ እንደማለት ነውና አቅምን ማወቅ ጥሩ ነው፡፡ አዳምና ሔዋንም የወደቁት እንደ አምላካቸው እንሆናለን ብለው ነበር፡፡ “ጌታችን ለምን በሰላሳ ዓመቱ ተጠመቀ” ተብሎ ይጠየቃል እንጂ “እኔም እንደእርሱ በሰላሳ ዓመት መጠመቅ አለብኝ” ሊሆን አይችልም፤ ይህንን የምትሉ ወንድሞችና እህቶች ካላችሁ ስህተት ነውና ተመለሱ እንላለን፡፡ ጥቂት ቆይታችሁ ደግሞ እንደጌታ እንሰቀላለን እንደምትሉ ፍርሃቱ አለን፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰላሳ ዓመቱ መጠመቁ ምሥጢሩ ግን እንዲህ ነው፤ አዳም ሲፈጠር የ30 ዓመት ጎልማሳ ሆኖ ነበር፤ ይህ የ30 ዓመት ጎልማሳ አዳም ልጅነቱን አስወግዶ፤ ክብሩንም አጣ፡፡ ስለዚህ የአዳም ልጅነት የሚመለስለት ጌታችን በ30 ዓመቱ ሲጠመቅ በመሆኑ ነው፡፡ ክርስቶስን “ሁለተኛ አዳም” ያልነውም የመጀመሪያው አዳም ያጣውን በረከት በሁለተኛው አዳም በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወትን በማግኘቱ ነው፡፤ ስለአዳም ልጅነት ነው በ30 ዓመቱ የተጠመቀ እንጂ እናንተም በሰላሳ ዓመታችሁ ተጠመቁ እያለን አልነበረም፡፡
የእኛ ጥምቀት በ40 እና በ80 ቀን መሆኑ
1.  ሔዋን በተፈጠረች በ80 ቀን፤ አዳም ከተፈጠረ በ40 ቀን ነበር ገነት የገቡት፡፡ ይህም በተወለድን ወንዶች በ40 ቀን፤ ሴቶች በ80 ቀን ወደ ቤተመቅደስ መግባት እንዳለብን ነው የሚያስተምረን፡፡ (መ.ኩፋሌ 4፤9-11፤ መ.ዘሌዋውያን 12፤1-5፤ ሉቃ. 2፤21-24)
2.  ሕፃናት በብሉይ ኪዳን ሲገረዙ ክብርን ያገኙ ነበር፤ ፀጋውን ለይቷቸው አያውቅም፡፡ (ዘፍ.17፤11) ለምሳሌ
·         ነቢዩ ኤርምያስ የተቀደሰው በእናቱ ማኅጸን ነበር፡፡ (ት.ኤር. 1፤5)፤
·         መጥምቁ ዮሐንስ በእናቱ ማኅጸን በመንፈስቅዱስ ተመልቶ ነበር፡፡ (ሉቃ. 1፤15)
·         ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያስተምርበትም ሰዓት ሕፃናትን ባርኳቸዋል፤ ይህም ሕፃናት በዕድሜያቸው ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ የሚከለክላቸው አለመሆኑን ያሳያል፡፡ (ማቴ. 19፤13-15፤ ማር. 1፤13-15)
·         ቅዱስ ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 1፤16 ላይ የእስጢፋኖስን ቤተሰቦች በሙሉ እንዳጠመቀ ይናገራል፡፡ ቤተሰብ ሲል ደግሞ ከሕፃን እስከ ሽማግሌ ድረስ ያለው መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ስለዚህ “ሰላሳ ዓመት ሲሞላኝ ነው መጠመቅ ያለብኝ” የሚል ሰው ከመጽሐፍቅዱስ ጋር ገና ግንኙነት ያላደረገ ወይንም መጽሐፍቅዱስ ምን እንደሚል ያልተገነዘበ ሰው ነው፡፡
በማን ስም እንጠመቃለን
“በስመ ሥላሴ” በማቴዎስ ወንጌል ም.28፤19-20 “ወደ ዓለም ሂዱ ፍጥረትን ሁሉ አስተምሩ በአብ በወልድ በመንፈስቅዱስ ስም አጥምቋቸው” ይላል፡፡ አንድ አንድ ሰዎች በሐዋርያት ሥራ በምዕራፍ 2 ላይ ያለውን በመያዝ “ሐዋርያት ያጠምቁ የነበር በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው እንጂ በሥላሴ ስም አይደለም፤ ስለዚህ እኛም መጠመቅ ያለብን በኢየሱስ ስም ነው” ይላሉ፡፡ ይህ ግን ስህተት ነው፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ አጥምቁ ብሎ የላካቸው በአብ በወልድ በመንፈስቅዱስ ስም ነው፡፡ እነርሱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እያጠመቁ አብ እና መንፈስቅዱስን ዘንግተዋቸው አይደለም፡፡ ነገር ግን፤
1.  የዮሐንስ ወንጌል ም.14፤8 “እኔን ያየ አብን አይቷል፤…. እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን” ብሎ ተናግሮ ነበር፡፡ እነርሱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሲያጠምቁ አንድነታቸውንና ሦስትነታቸውን ጠንቅቀው ስለአወቁ እንጂ ጠፍቷቸው አይደለም፡፡
2.  የኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አብ ልጅ እንደሆነ ራሱ ቅዱስ ጴጥሮስ መስክሮ ነበር፡፡ (ማቴ. 16፤17)
ስለዚህ በወቅቱ አወዛጋቢ እና መፍትሔ ጠፍቶለት የነበር ችግር የእግዚአብሔር ሰው የመሆኑ ምሥጢር ነበር፡፡ ታዲያ ሐዋርያት በሥራቸው ሁሉ ስለኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት እንዲሁም አዳኝነት መመስከር ስለነበረባቸው ብዙ ጊዜ የኢየሱስ ክርስቶስን ስም ይጠሩ ነበር፤ ዛሬ ሁሉ አማኝ ነው፤ በማን ስም መጠመቅ እንዳለበት ያውቃል፡፡ ስለኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት ያልገባው ሰው ብቻ ነው ስለእርሱ አምላክነት አስተምረህ የምታጠምቀው፡፡
የነገረ መለኮት ሊቃውንት “There is no baptism without Holy Spirit” ይላሉ ይህም ማለት በጥምቀት አብ ወልድ መንፈስቅዱስ ከሌሉበት፤ የእነርሱ ስም ካልተጠራ ያ ጥምቀት “ጥምቀት” አይባልም በውሀ ተነክሮ እንደመውጣት ያህል ነው ይላል፡፡ በዮርዳኖስ አብ በደመና “የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት” ሲል መንፈስቅዱስ በአምሳለ ርግብ ሲወርድ መታየቱ ሰው በሥላሴ ስም መጠመቅ እንዳለበት የተገለፀ ምሥጢር ነው፡፡ ለዚህ ነው የነገረ መለኮት ሊቃውንት “In the river Jordan is revealed the mysteries of Holy Trinity – that mean without Holy Trinity no baptism.” (The scholars of Theology) ያሉት፡፡
በኦሪት ዘፍጥረት ምዕ. 1፤2 “የእግዚአብሔር መንፈስ በውሀ ላይ ሰፍፎ ነበር” ይላል፡፡ ይህ ማለት ውሀን የሚያጠራ ለሰው ሁሉ ተስማሚ እንዲሆን የሚያደርግ መንፈስቅዱስ መሆኑን የሚገልጽ ሲሆን በተጨማሪ ግን ምሥጢራዊ ትርጉም ነው፡፡ ቅዱስ ጄሮም እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፤
“The symbol of Baptism. It is mystical meaning “the Spirit was stirring above the waters” already at that time baptism was being flourish ad owed. It caused not,  be true baptism, to be sure, without the Spirit.” (St. Jerom) “በውሀ ላይ ሰፍፎ የነበረው መንፈስ የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ ይህም ምሥጢራዊ ትርጉም ያለው ነው፤ ያለ መንፈስቅዱስ ጥምቀታችን እውነት አይሆንም” ነው የሚለው፡፡
የትርጓሜ መጻሕፍት መምህራንም የጥምቀት ምሳሌ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ “ውሀ በልብ የሚሳቡትን፤ በእግር የሚሽከረከሩትን ፤ በክንፍ የሚበሩትን አስገኝቶ ነበር፡፡ ይህም ማንኛውም ሰው በጥምቀት የሚወለደው ልደት ነው፤ ከሥጋ የተወለደው የሰው ልጅ በመንፈስ ሲወለድ ረቂቅ ምሥጢር ይገለጽለታል” ይላሉ፡፡ “በብዙ አቅጣጫ መንቀሳቀስ ይችላል፤ ሰማያዊ ፀጋ እንዲሁም ምድራዊ ፀጋ ይበዛለታል” ይላሉ፡፡ ስለዚህ ጥር 11 ቀንን ስናስብ ብሔራዊ ባህላችን ነው፤ ዓለም ሁሉ በጉጉት የሚጠብቀው በዓል ነው፡፡ በየዓመቱ ስናከብረው ሁልጊዜ በየዓመቱ እያጠመቅን አይደለም፤ አንዳንዶች “ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ በየዓመቱ ታጠምቃለች” ይላሉ፤ ጥምቀት አንዲት መሆኗን የምትመሰክር ሃይማኖት መሆኗን ሁሉም ያውቀዋል፡፡ (ኤፌ. 4፤4) ይህ ግን ክርስቶስ ለእኛ ሲል መጠመቁን ከገሊላ ወደ ይሁዳ (ዮርዳኖስ) ሄዶ መጠመቁን ለማመልከት አባቶቻችን ታቦታትን ከክብር መንበሩ ወደ ጥምቀተ ባሕር ይዘው በመሄድ የጌታን ትህትና እያስተማሩ እንጂ ሁልጊዜ ማጥመቃቸው አይደለም፡፡
ስለጥምቀት ያላችሁን ጥያቄ በሙሉ ለዝግጅት ክፍሉ በመላክ ለጥያቄዎቻችሁ ተገቢውን ሰፋ ባለ መልኩ ለመመለስ እንደሚቻል ለማሳወቅ እንወዳለን፡፤
የሰላም በዓል ያድርግልን፡፡
 ወስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment