“ክቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅድመ እግዚአብሔር፤ የጻድቅ ሰው ሞት
በእግዚአብሔር ፊት የተከበረ ነው፡፡”
በጥር 12 ቀን ዕረፍቱ ለቴዎድሮስ ሰማዕት
ሀገሩ አንጾኪያ (ከሮም
ምስራቅ በኩል የሚገኝ) ሲሆን አባቱ ሲድራኮስ እናቱ በጥይቃ ይባላሉ፡፡ በዘመኑ ዲዮቅልጥያኖስ ለአጵሎንና ለአርዳሜስ ለተባሉት ጣዖታቱ
ያልሰገደ ቤቱ ይበረበራል፤ በሠይፍ ይቀላል፤ ሥጋው ለእሳት ይሰጣል ብሎ አዋጅ ያወጀበት ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ
ቡናብሴ በሚባል ወንዝ አካባቢ ሳለ በህልሙ የወርቅ መሰላል ከምድር
እስከ ሰማይ ተተክላ በላይዋ ዙፋን ተዘርግቶባት በዙፋኑ ላይ ንጉሥ ተቀምጦበት በግራ በቀኙ መላእክት ከበው ሲያመሰግኑት ወዲያውም
ከመላእክቱ አንዱ ከወንዙ ቢነክረው እንደእርሱ እሳታዊ ሲሆን ጌታም ስለስሜ ትሞታለህ ከእኚህ እንደ አንዱ ትሆናለህ ሲለው ጓደኞቹ
ለውድዮስና በኒቃሮስም መልአኩ ነክሯቸው እንደእርሱ ሲሆኑ አየ፡፡ በሰማዕትነት ሙቱ ሲለን ነው ብሎ ከሠራዊቱ የፈሩትን አሰናብቶ
የተከተሉትን ከወንዙ አስጠም ለውድዮስንና በኒቃሮስን አስከትሎ ሄደ፡፡ ዲዮቅልጥያኖስም ለአጵሎም ስገድለት አለው፡፡ “አንተ አላዋቂ
ጠበብቶችህ ደንጊያ ፀርበው እንጨት አለዝበው ለሠሩት ጣዖት ስገድ ትላለህን› አልሰግድም” አለ፡፡
ተከታዮቹን በሰይፍ አስመታቸው፤እርሱን ግን አሰቀለው፡፡ ሥጋው እንደወንፉት ተበሳሳ፤ ደሙም እንደ ውኃ ፈሰሰ፡፡ ከሥቃዩ እንዲያጽናናው
ቅዱስ ሚካኤልን ላከለት፤ ኋላ ግን ራሱ ጌታ ተገልጾለት “ስለምስፍናህ፤ ስለድንግልናህ፤ ስለተጋድሎህ ሦስት አክሊላት አቀዳጅሀለሁ፡፡
በስምህ ጥርኝ ውኃ እስከማጠጣት ድረስ መልካም ያደረገውን ሁሉ ምሬልሀለሁ፤ በጦር በእስር በመከራ በሥቃይ ሆኖ በስምህ የተማፀነውን
ሁሉ ኃይል ጽንዕ እሆነዋለሁ” ብሎ ተስፋውን ነግሮት ነፍሱን ከሥጋው ለይቶ በስብሐተ መላእክት አሳርጎታል፡፡
የቴዎድሮስ ሰማዕት ረድዔትና
በረከቱ ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡ አሜን፡፡
ጥር 15 ቀን ዕረፍቱ ለሰማዕቱ ቂርቆስ
ቅዱስ ቂርቆስና ቅድስት
ኢየሉጣ በእግዚአብሔር ቸርነት በቅዱስ ገብርኤል ረዳትነት በእሳት ከመቃጠል፤ በንፍር ውሀ ከመለብለብ ከዳኑ በኋላ እለእስክንድሮስ
መከራውን ፈርተው ይመለሳሉ ብሎ እያሰረ፤ በችንካር እየቸነከረ ሲያሰቃያቸው ቆየ፡፡ የማይሆንለት ቢሆን እጅ እግራቸውን አስሮ ከዝግ
ቤት አስቀመጣቸው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የመከራቸውን ጽናት የትዕግሥታቸውን ብዛት አይቶ ከመከራው ሊያሳርፋቸው
ሽቶ በመንፈቀ ሌሊት ተገልጾ “ሰላም ላንተ ይሁን፤ የመከራህን ጽናት የትዕግሥትህን ብዛት አይቼ ላሳርፍህ መጣሁ” አለው፡፡ “በሕፃንነቴ
ይህን ያህል ተጋድዬ የምትሰጠኝ ምንድን ነው›” አለው፡፡ “በልብህ ያለውን ሁሉ እሰጥሀለሁ” አለው፡፡ “እንኪያስ
በስሜ ቤተክርስቲያን ከታነጸበት፤ ማየ ጸሎት ከተረጨበት ቦታ ሁሉ ረሀብ ቸነፈር የሰው በሽታ የከብት እልቂት፤ የእኅል የውሀ ጥፋት
አይሁን” አለ፡፡ “ይሁንልህ” አለው፡፡ “ሥጋዬም በምድር አይቀበር” አለ፡፡ “እውነት እልሀለሁ ከመንበረ መንግሥቴ፤ ከማርያም እናቴ
ከዮሐንስ መጥምቅም በቀር በመንግሥተ ሰማያት የሚበልጥህ የለም ሥጋህም እንዳይፈርስ በኤልያስ ሠረገላ አኖርልሀለሁ” ብሎ ተስፋውን
ነግሮታል፡፡
ሲነጋ እለእስክንድሮስ
ከመካነ ምኩናኑ ተቀምጦ ካለበት አስጠርቶ “የተመለስከው መመለስ አለን” አለው፡፡ ሰይፍ ጃግራውን ጠርቶ ንሳ ውደቅበት አለው፤ በሰይፍ
መታው፤ ጌታም ነፍሱን በመካነ ዕረፍት ሥጋውንም ነጥቆ በሠረገላ ኤልያስ አኑሮታል፡፡ እናቱ ቅድስት ኢየሉጣንም በማግሥቱ በሰይፍ
አስመትቷታት በሰማዕትነት አርፋለች፡፡
የሰማዕቱ ሕፃን ቂርቆስ
እና የእናቱ ቅድስት ኢየሉጣ ረድዔትና በረከት ይደርብን፡፡ አሜን፡፡
ጥር 21 ቀን ዕረፍታ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል
ወላዲተ አምላክ
ማርያም ማለት
·
ልዕልት
ማለት ነው፡፡ሮም ራማ አርያም ማለት ልዑል ማለት እንደሆነ እሷም መትሕተ-ፈጣሪ መልዕልተ ፍጡራን ናትና፡፡
·
እግዝእተ
ብዙኃን ማለት ነው፡፡
·
ጸጋ
ወሀብት ማለት ነው፡፡ ለጊዜው ለአባትና ለእናቷ ፍጻሜው ግን ለሰው ሁሉ ጸጋ ሆና ተሰጥታለችና፡፡
·
ፍጽምት
ማለት ነው፡፡ ለጊዜው መልክ ከደምግባት ፍጻሜው ግን ንጽሐ ሥጋ ከንጽሐ ነፍስ፤ ድንጋሌ ሥጋ ከድንጋሌ ነፍስ አስተባብራ ይዛ ተገኝታለችና፡፡
·
መርሕ
ለመንግሥተ ሰማያት ማለት ነው፡፡ ምእመናንን መርታ መንግሥተ ሰማያት ታገባለችና፡፡
·
በዓለመ
ሥጋ በዓለመ ነፍስ ካሉት ሁሉ የከበረች የገነነች ማለት ነው፡፡ ማር በምድር ካሉት መባልዕት (የሚበሉ ሁሉ) ያም በገነት ካሉ ዕፅዋዕት/ፍሬያት/
ሁሉ የከበሩ የጣፈጡ እንደሆኑ፡፡
·
ማ
- ማኅደረ መለኮት
ር
- ርግብየ ይቤላ
ያ
- ያንቀዓዱ ኀቤኪ ኩሉ ፍጥረት
ም - ምስአል ወምስጋድ ማለት ነው፡፡
የዕረፍቷ ነገር እንደምን ነው› ቢሉ ስድሳ አራት ዓመት በዚህ ዓለም ኖራ ጥር 21 እሑድ ቀቀን ጌታ እልፍ
አእላፍ መላእክቱን አስከትሎ መጥቶ “እናቴ ሆይ ከዚህ ዓለም ድካም ላሳርፍሽ መጣሁ” አላት፡፡”ልጄ ሰማይና ምድር የማይወስኑህን
ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማኅፀኔ ተሸክሜ፤ በድንግልና ወልጄህ እሞታለሁን›” አለችው፡፡ በሲኦል የሚሰቃዩ ነፍሳትን አሳይቶ “እናቴ ሆይ ሞትሽ ለኚህ ቤዛ
ይሆናቸዋል” አላት፡፡ “እኚህን ከማርክልኝስ ይሁን” አለችው፡፡ ቅድስት ሥጋዋን ከክብርት ነፍሷ ለይቶ በቃለ አቅርንት በዝማሬ መላእክት
አሳረጋት፡፡ ደቀ መዛሙርቱንም ከያሉበት በደመና ጠቅሶ ካለችበት አድርሶ “እመቤታችሁን ቅበሩ” አላቸው፡፡ ባጎበር አድርገው ይዘዋት
ወደ ጌቴ ሴማኒ ሲወስዷት አይሁድ አይተው “ልጅዋን ተነሣ፤ ዐረገ
እያሉ ሲያውኩን ይኖራሉ፤ አሁን ደግሞ እሷን ተነሳች ዐረገች እያሉ ሊያውኩን አይደለምን› ኑ ሥጋዋን እናቃጥለው፡፡” ብለው ተነሱ፡፡ ከመካከላቸው
አንዱ ታውፋንያ ዘሎ ያልጋውን ሸንኮር ያዘ፤ የታዘዘ መልአክ መጥቶ ሁለት እጁን በሰይፍ ቀጣው፡፡ “በድያለሁ ማረኝ” ብሎ ቢማፀናት
ራሷን ዘንበል አድርጋ ቅዱስ ጴጥሮስን “እንደነበረ አድርግለት” አለችው፤ ቢመልሰው ድኖለታል፡፡ ከዚህ በኋላ ዮሐንስን ጨምሮ ከመካከላቸው
ነጥቆ ገነት በዕፀ ሕይወት ሥር አኑሯታል፡፡ ኋላም በሐዋርያት ሱባዔ በነሐሴ 14 ቀን ክቡር ሥጋዋ ተመልሶላቸው ቀብረዋት በነሐሴ
16 ቀን እንደ ልጇ ባለ ትንሣኤ አርጋለች፡፡ የእመቤታችን የወላዲተ አምላክ ቅድስት ደንግል ማርያም እናትነቷ፤ ፍቅሯ፤ በረከቷ
እና ምልጇዋ ከሁላችን ጋር ለዘለዓለም ይኑር፡፡ አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
No comments:
Post a Comment