13

.

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው::" የማቴዎስ ወንጌል 7: 4

"እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅናወተት ግዙ።" ትንቢተ ኢሳይያስ 55 : 1

Monday, November 21, 2011

ውዳሴ ከንቱ

ውዳሴ ከንቱ የሚለው ቃል የማይረባ የማይጠቅም  ውዳሴ የሚል ትርጓሜ ያለውሲሆን  ውዳሴ  ብጡል (የተናቀ፤ተርታ) ውዳሴ ተብሎም ይጠራል፡፡የቃሉ ትርጉም  በዚህ መልኩ የሚፈታ  ይሁን እንጂየማይጠቅምከመሆን አልፎ  ሰውን ሊጎዳ የሚችል ነገር በመሆኑ  የቤተክርስቲያናችን መጻሕፍት  አጥብቀን   ልንሸሸው እንዲሚገባ ያስተምራሉ፡፡
         ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግሩ ስር   ተቀምጣ ቃላት ታዳምጥ የነበረችውን የማርታ እህት  ማርያምንማርያምስ የማይቀሟትን  በጎ ዕድል መረጠችሉቃ10÷42  ብሎ ያመሰገነበትን  ቃል አበው ሲተረጉሙመማር ውዳሴ ከንቱ  የለውም “  አላውቅም  ማለት ነውና፡፡  ስለዚህም  አጋንንት  የማይቀሟትን (ዋጋዋን ) የማያስቀሩባትን መማርን መረጠች ማለት ነው ብለው መተርጎማቸው ‹‹ውዳሴከንቱ›› የሰውን የልፋት ዋጋ  በምድራዊ  ክብር  የሚያስቀር  ከንቱ ነገር መሆኑን ያስረዳል፡፡  አበው ከውዳሴ ከንቱ  እንድንጠበቅ ማስተማራቸው  የመልካም ስራችን  ዋጋ  ሰዎች  በሚያቀርቡልን የምስጋና ስጦታ ምክንያት በምድር  እንዳይቀርብን በማሰብ ነው፡፡ በወንጌልም ጌታ  ከሰዎች ምስጋና  በመሻት መልካም  ሥራቸውን  በሰው  ፊት ስላደረጉ ፈሪሳውያን  ሲናገር  “እሙንቱሰ ነሥኡ እሴቶሙእነዚህስ  ዋጋቸውን  ተቀብለዋልማቴ6÷2  በማለት ከሰው የተቀበሉት ምስጋና  ሰማያዊ  ዋጋቸውን እንዳሳጣቸው አስተምሯል፡፡
     እንዲህ ስንል ግን በሰው የተመሰገነ ሁሉ ውዳሴ ከንቱ  ሆኖበታል   ያልተመሰገነ ደግሞ አልሆነበትም  ማለትም  አይደለም፡፡  በልቦናው   የመመስገን መሻት  ኖሮት  መልካም ሥራ  የሠራ  ነገር ግን   በለስ ያልቀናው  ያልተመሰገነ ሰው ሊሰርቅ ሄዶ አጥር ፀንቶበት፣  ውሻ ጮሆበት፣ጠባቂ ነቅቶበት  የተመለሰ ሰውን  ይመስላል፡፡   መሻቱ  በልቦናው  ስላለ ሰዎች  ባያመሰግኑትም  ቅሉ ለመመስገን  በመሻት አስቀድሞ  ወድቋልና  ከሰው ውዳሴ  ሳይፈልግ  የሠራ ሰውም  ሰው  ቢያመሰግነው  እንኳ አይሻውምና  በውዳሴ  ከንቱወደቀ አያሰኝም፡፡  ይህም ውዳሴ ከንቱ ኃይል አግኝቶ ሰውንየ ሚጥለው  የተዘጋጀ ልቦና ሲኖረው መሆኑን  እንገነዘባለን፡፡
    ውዳሴ ከንቱ  በሦስት ዓይነት  መንገድ ሲቀርብ እንደ  አቀራረቡና አቀባበሉም ሰዎችን ሊጎዳ ይችላል፡፡
.  ሰዎች ስለ እኛ
  ውዳሴ ከሰዎች ለእኛ በሚቀርብበት ወቅት  የሚያመሰግነን ሰው ማን ነው? ምስጋናውስ ለእኛ የሚገባን  ነውን? የሚሉትን ጥያቄዎች  ራሳችንን  መጠየቅ ከጉዳት  ይጠብቀናል፡፡ የሚያመሰግነን  ሰው ማነው? የሚለውን ማሰባችን  ተወዳጅነትን  ለማትረፍና በአፀፋ ለማመስገን  ከሚመጡ ሰዎች  ሲጠብቀን ምስጋናው ለእኔ ይገባልን? የሚለውን ማሰብ ደግሞ ምስጋናውን ይገባናል ብሎ ከመቀበል ይጠብቀናል፡፡ በወንጌል ጌታችንቸር መምህር ሆይብሎ የቀረበው ሰው  መመስገንንና  ተወዳጅነትን ለማትረፍ  ሲሉ ምስጋና   ከሚያቀርቡ ሰዎች የሚመደብ ነው፡፡ (ማር 10÷17) ምስጋናንለእኔ የሚገባ ነውን?” ብሎ መርምሮ መቀበልን የተማርነው ከቅዱሳን እናቶቻችንና ከቅዱሳን አባቶቻችን ነው፡፡
   ክብር ይግባትና በሚገባት ግብር የተመሰገነች እመቤታችንእፎኑ ከመ ዝኑ እንጋ አምኃ ይትአምኁ - እንዲህ ያለውን ሰላምታ እንዴት ይቀበሉታል?” ሉቃ 1÷29 ማለቷ ቅዱሳን በሚገባቸው ገንዘብ ቢመሰገኑ እንኳ (በትህትና) አይገባንም እንደሚሉ የሚያስረዳ ነው፡፡
     በትንሣኤ ዘጉባኤምተርቤ አብልታችሁኛልና፣ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና ….” ተብለው የሚመሰገኑ ቅዱሳንመቼ ተርበህ አበላንህ?መቼ ተጠምተህ አጠጣንህ?.....” ሲሉ ሠርተው እንዳልሰሩ ሆነው በትህትና እንዲመልሱ ተጽፏል፡፡ ማቴ 25÷44
አቡነ ተክለሃማኖትም ከብዙ ትሩፋትና ተጋድሎ በኋላአሌ ሊተ ወይ ሊተ ለዘኢገበርኩ ምንተ - ወዮ ለኔ ምንም ላልሠራሁትእያሉ ምርር ብለው ማልቀሳቸውን ገድላቸው ዘግቦታል፡፡
እኛም ምንም እንኳ ከእነርሱ መዐርገ ትህትና ደርሰን አይገባንም ማለት ባንችል በብሩህ ፊት ሆነን ውዳሴን እያጣጣሙ ከመቀበል መለየት ይገባናል፡፡ይልቁንም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ እንዳሉት በምንመሰገንበት ወቅት የከፉ ኃጢአቶቻችንን እያሰብን ራሳችንን መገሰፅ ይገባናል፡፡
. እኛ ስለ ሰዎች 
ምስጋና ከእኛ ስለ ሰዎች በሚቀርብበት ወቅትም ልናስተውላቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ፡፡በእርግጥ ሰዎችን ማመስገንና እንዲመሰገኑ መፈለግ ከክርስቲያኖች  የሚጠበቅ የበጎ ምግባር መገለጫ  ነው፡፡
እንደ ዲያቢሎስ መመስገን ብቻ እንጂ ሰውን ማመስገንና ማበረታታት የማይፈልጉ ሰዎች አሉና፡፡ ነገር ግን የምስጋናውን ልክ የምናልፍ ከሆነ ለተመስጋኙ ጥቅም ከመሆን ይልቅ ፈተና የምንሆንበት ዕድል የሰፋ ነው፡፡በውዳሴ ከንቱ የወደቀ ከሆነም መሰናክል የሆንነው እኛ በመሆናችን እንቀጣለን፡፡ ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ቢኖር የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ከጥልቅ ቢጣል ይሻለው ነበርተብሎ ተጽፏልና፡፡ ማቴ 18÷6 ስለዚህም መመስገን የሚገባውን ሰው መለየትና መመስገን በሚገባው ልክ ማመስገን ከእኛ የሚጠበቅ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ደግሞምከጠላት መሳም የወዳጅ ንክሻ ይሻላልተብሎ እንደ ተፃፈ ለሰዎች ከሚቀርብላቸው ምስጋና ይልቅ ወቀሳና ምክር ለመሻሻል ይጠቅማቸዋልና ማመስገን ብቻ ሣይሆን መውቀስና መምከር ተገቢ ነው፡፡ጌታችን የአይሁድ መምህር የሆነ ኒቆዲሞስንአንተ የአይሁድ መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን?” ብሎ አለማወቁን ገስፆ መምህርነቱን አመስግኖ እንደ ተናገረው ዮሐ. 3÷10 ፡፡
. እኛ ስለ እኛ
 ውዳሴ ከንቱ ሰዎች እኛን በሚያመሰግኑበት ወቅት ባለን አቀባበል ወይም እኛ ለሰዎች በምናቀርበው ምስጋና ልክ ብቻየ ሚመዘን አይደለም፡፡እኛ ስለ ራሳችን ባለን አስተያየትና በምናቀርበው ምስጋናም ጭምር እንጂ፡፡ በእርግጥ ለራስ ጥሩ አመለካከት መያዝና ራስን ማበረታታት ተገቢ ነው፡፡ይህ ሁኔታ ልክ ከሌለው ግን ለራሳችን ብቻ የምናዜም በውይይት መሃል እኛ ብቻ መነሳት የምንፈልግ ከእኛ ይልቅ ሌላ ሰው ቢነሣ ቅር የሚለን ገፍተንም ስለራሳችን ጥሩነት የምናወራ እንሆናለን፡፡ በቅዱስ መጽሐፍየሌላ ሰው አፍ ያመስግንህተብሎ መጻፉ ሰው በራሱ አንደበት መመስገን እንደሌለበት የሚያስረዳ ነው፡፡በወንጌልም የታዘዙትን ሁሉ በፈፀሙ ጊዜ አገልጋዮች ምን ማለት እንዳለባቸው የተቀመጠላቸው ትዕዛዝ  “የማንጠቅም ባሪያዎች ነን በሉ”  የሚል ነው ሉቃ. 1710 ፡፡ ይህም ሰው ከልክ አልፎ ለራሱ ቦታ እንዳይሰጥና በውዳሴ ከንቱ  እንዳይወድቅ ለመጠበቅ  የታዘዘ ነው፡፡ ርዕሳችን  ውዳሴ ከንቱ በመሆኑ  በማይጠቅም  ውዳሴ ላይ ብቻ አተኮርን  እንጂ የሚገቡና  የሚጠቀቅሙ የታዘዙም  ምስጋናዎች አሉ፡፡የማይጠቅም ውዳሴየሚለውን ርዕስ  በራሱ  የሚጠቅም ውዳሴ መኖሩን  የሚጠቁም  ነው፡፡
የሚጠቅም ውዳሴ (ውዳሴ ዘይረብሕ)
    ቅድስት ቤተክርስቲያናችን መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት በማድረግ ጎጂነቱን አውቃ የከለከለችው ከንቱ ምስጋና እንዳለ ሁሉ ተገቢ ነው ይጠቅማል ብላ የፈቀደችው ያዘዘችውም የምስጋና ዓይነት አለ፡፡ ይህ የምስጋና አይነት የተለየ ስያሜ  ባይኖረውም  ከውጤቱ በመነሳት ውዳሴ ዘይረብሕ (የሚረባ-ረብ ያለው ውዳሴ)፣ ውዳሴ ዘይበቊዕ (የሚጠቅም ውዳሴ) ልንለው እንችላለን፡፡
    ለአምላካችን እግዚአብሔር፤ለቅዱሳን፤ በሥራቸው ሊመሰገኑ ለሚገባቸው ቅን ሰዎች፤ አንዳንዴም በምስጋና ልናበረታቸው ለሚገቡ ድኩማን የሚደረጉ ምስጋናዎች ከዚህ ዓይነቱ ምስጋና ውስጥ የሚመደቡ ናቸው፡፡
     ለእግዚአብሔርና ለቅዱሳን የሚቀርቡ ምስጋናዎች አመስጋኙን ብቻ ሲጠቅሙ የቀሩት ደግሞ የሚጠቅሙበት ጎዳና ቢለያይም አመስጋኙንም ተመስጋኙንም የሚጠቅሙ ናቸው፡፡ ምስጋና አመስጋኙን ብቻ ሊጠቅም እንደሚችል የሚያሳይ በቅዳሴ ማርያም ላይ “ዘንተ ቅዳሴ ዘይቄድስ ካህን አኮ ማርያምሃ ዘይቄድስ አላ ውእቱ ይትቄደስ - ይህን ቅዳሴ የሚቀድስ ካህን ማርያምን የሚቀድሳት አይደለም ራሱ ይቀደሳል እንጂ” የሚል ንባብ ይገኛል፡፡ ከጥቅማቸው ከፍታ አንፃር ካየነው ደግሞ ለእግዚአብሔርና ለቅዱሳን የሚቀርብ ምሥጋና ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ራሱን የቻለ ሰፊ ሐሳብ በመሆኑም በዚህ ጽሑፍ የምንዳስሰው አይሆንም፡፡ ይልቁን ከሰዎች ጋር ባለን ማኅበራዊ ሕይወት ስለሚያጋጥሙንና ጥንቃቄ ስለሚፈልጉ ምስጋናዎች በጥቂቱ እንመለከታለን፡፡
       መልካም ለሚሠሩና ቅን ለሆኑ ሠዎች ምስጋና እንደሚገባቸው በቅዱስ ዳዊት የመዝሙር መጽሐፍ “ወለራትዓን ይደልዎሙ ክብር - ለቅኖችም ምስጋና ይገባቸዋል  መዝ 33:1 ተብሎ የተጻፈ ሲሆን ልጁ ሰሎሞን ደግሞ መልካም ስለምትሠራ ልባም ሴት በጻፈበት የምሳሌ ክፍል  ልጆችዋ ይነሣሉ ምስጋናዋንም ይናገራሉ ባልዋ ደግሞ እንዲህ ብሎ ያመሰግናታል።መልካም ያደረጉ ብዙ ሴቶች አሉ አንቺ ግን ከሁሉ ትበልጫለሽ። ውበት ሐሰት ነው ደም ግባትም ከንቱ ነው እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን እርስዋ ትመሰገናለች። ከእጅዋ ፍሬ ስጡአት ሥራዎችዋም በሸንጎ ያመስግኑአት።”  ምሳ 31:28 በማለት ጽፏል፡፡ ከእነዚህ ጥቅሶች መልካም ለሚሠሩ ሁሉ ምስጋና የሚገባ መሆኑን ብንረዳም ጎን ለጎን ልናደርጋቸው የሚገቡ በቂ ጥንቃቄዎችም አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል፡-
፩- በመጠንና በተገባ ነገር ማመስገን
ምስጋናው ያልተመጠነና የተጋነነ ከሆነ በአንድ በኩል ተመስጋኙ በደንብ አንዲሠራ ከማድረግ ይልቅ በምስጋናው እየተደሰተ ተዘናግቶ እንዲኖር የሚያደርገው ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ በውዳሴ ከንቱ እንዲወድቅ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ አመስጋኙም ለውድቀት ምክንያት በመሆኑ ከመቀጣት አይድንም፡፡
፪-ከጕሕሉት(ከሽንገላ) እና ከውሸት የፀዳ መሆን
ብዙ ሰዎች ዘመን የወለደውን ንጉስ የወደደውን ተከትለው በልባቸው ባያምኑበት እንኳ መስሎ ለማደር ብለው ሰዎችን ያመሰግናሉ፡፡ ተመስጋኙ ይህ ከልብ ነው፣ ይህ አይደለም ብሎ መለየት ባይችልም ልብና ኲላሊትን የሚመረምር አምላክ ይፈርድብኛል ብለን “በአፉሆሙ ይድህሩ ወበልቦሙ ይረግሙ - በአፋቸው ይመርቃሉ በልባቸውም ይረግማሉ፡፡” መዝ 62:4 ከተባሉት እንዳንቆጠር መጠንቀቅ ይገባናል፡፡
፫ ምስጋናን ሱስ እስኪሆን አለማስለመድ
      ምስጋና ከተለመደ እንደሌሎቹ ልማዶች ሱስ ሊሆን ይችላል፡፡ አበው “ኀዲገ ልማድ ፅኑዕ ውእቱ - ልማድን መተው ከባድ ነው” እንዳሉ በውዳሴ ሱስ የተጠመደ ሰውም ከዚህ ልማድ መውጣት ሊከብደው ሲቀር ቅር ሊሰኝ አልፎም ለምን አልተመሰገንኩም ብሎ ሊቆጣ ይችላል፡፡ ሰው እንዲህ ካለ ክፉና አስተቺ ልማድ ውስጥ እንዲገባ ምክንያት መሆን ከባድ ፍርድ ያለበት በመሆኑ ሱስ እስኪሆንበት በነጋ ጠባ ሰውን ከማመስገን መጠበቅ ተገቢ ነው፡፡
      በቅዱሳት መጻሕፍት መልካም ለሚሠሩና ቅን ለሆኑ ሰዎች ብቻ ሳይሆን ምስጋናው ለማይገባቸውና የእነርሱ ባልሆነ ነገር ሰዎችን ማመስገን ጠቃሚ ሆኖ የሚገኝበት ጊዜ እንዳለም ተጽፏል፡፡ በሥጋዊ ትምህርት ጎበዝ ያልሆነውን ተማሪ ጎበዝ በማለት ተነሳሽነቱ እንዲጨምርና እንዲሻሻል ማድረግ እንደሚቻል በመንፈሳዊ ሕይወቱ ያልበረታን ሰውንም በማመስገን ማበርታት እንዲሁ ይጠቅማል፡፡ ይህን በተመለከተ በመጽሐፈ መነኮሳት ላይ “ወድሶ ለሰብእ በዘኢኮነ ሎቱ ወድሶ ለሰብእ በዘኢኮነ ድልወቱ እስመ ወድሶ ለሰብእ ይወስክ ኃይለ - ሰውን የእርሱ ባልሆነና ባልተገባው ነገር አመስግነው ምስጋና ለሰው ኃይልን ይጨምራልና” ተብሎ ተጽፏል፡፡
     ከላይ ስለተገለጡት ተገቢ ምክንያቶች ማመስገን በዚህ ጽሑፍ ተነግረው የማያልቁ እጅግ ብዙ ጥቅሞች አሉት፡፡ “ብፁዕ ሕዝብ ዘየአምር የብቦ - እልልታን (ምስጋናን) የሚያውቅ ሕዝብ ምስጉን ነው፡፡” መዝ 89:15 ተብሎ እንደተጻፈ ሰዎችን ለማመስገን መነሳት በራሱ የሚያስመሰግን ደግ ተግባር ነው፡፡ ቁጣው የራቀ ምሕረቱ የበዛ አምላክ “በወንድሙላይየሚቆጣሁሉፍርድይገባዋል” ማቴ 5:22
       
      ብሎ ካስተማረን ወንድሙን ያመሰገነ ምን ይነት ሽልማት ይገባው ይሆን? “ዘይፀርፍ ላዕለ እኁኁ ዘረፈኬ ላዕለ እግዚአብሔር ልዑል - በወንድሙ ላይ የተሳደበ በእግዚአብሔር ላይ ተሳደበ” ተብሎ ከተጻፈ ወንድሙን ያመሰገነ ምን ይነት ክብር ይጠብቀው ይሆን?
Source: http://www.bahiran.org

No comments:

Post a Comment