ባለፈው የዮሐንስ ሐጺርን ታሪክ ስንመለከት የቅድስት አትናስያን ታሪክ እንደማቀርብ ቃል ገብቼ ነበር፡፡ ከዚህ እንደሚከተለው የቅድስት አትናስያ ታሪክ በጣም በአጭሩ የቀረበ ሲሆን ሰፊ የሆነውን የቅድስት አትናስያን ታሪክ በተለያዩ ክፍሎች በመከፋፈል በሌላ ጊዜ የምመለስበት ይሆናል ፡፡
“መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ፡ ዘጠና ዘጠኙን በበረሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሄድ ከእናንተ ማን ነው? ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ይሸከመዋል፣ ወደ ቤትም በመጣ ጊዜ ወዳጆቹንና ጎረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ፡- የጠፋውን በጌን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ ይላቸዋል፡፡ እላችኋለሁ እንዲሁም ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል በማለት ጌታችን ለፈሪሳውያንና ጻፎች የንስሐን ታላቅነት ለማስተማር በምሳሌ ነግሯቸዋል፡፡" ሉቃ. 15፤4-7፡፡
የቅድስት አትናሲያ ታሪክ የንስሐን ታላቅነት ልንማርበት የሚያስችለን ታሪክ ነው ፡፡ ቅድስት አትናሲያ ሚኑፎ /በአረፈችበት ቦታ ስም/ በመባል ትታወቃለች፡፡
ይኽ መልካም ሥራዋ በቤቷ ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ በየቦታው የሚገኙ ገዳማትን ትረዳ ነበር፡፡ ለመነኮሳቱ የሚያስፈልጋቸውን ትልካለች፡፡ ከአንዱ ገዳም ወደ ሌላ ቦታ ለተልዕኮ የሚጓዙትን መነኮሳት በቤቷ ተቀብላ ታስተናግዳለች፡፡ ቤቷ ማረፊያቸው ነበር፡፡ በዚህ መልካም ምግባሯ የአካባቢዋ ሕዝብ ያከብራታል፡፡ በገዳም ያሉ መነኮሳትም ስለበጎ ሥራዋ ይወዷት ነበረ፡፡
አትናሲያ በዚህ ሁኔታ ስትኖር የመልካም ነገር ሁሉ ጠላት የሆነው ሰይጣን ታጥቆ ተነሳ፡፡ ግብራቸው በከፋ ሰዎች ልቡና አድሮ እርስዋ ዘንድ ቀረበ፡፡ እነዚያ ክፉዎች ሰዎች ወደ አትናሲያ እየሄዱ ተቀራረቡ፡፡ በጓደኝነት እየተጠጉ ተለማመዷት፡፡ የዓለምን የተመቸና የተደላደለ ኑሮ አስደሳችነቱን ይነግሯት ጀመር፡፡ በሀብቷ፣ በመልኳ፣ በቁመናዋ የዚችን ዓለም ደስታ የርስዋ ማድረግ እንደምትችል ያጫውቷታል፡፡
በየጊዜው በዙሪያዋ ተሰብስበው የሚነግሯትና የሚያባብሏት ሁሉ የልቡናዋን ሓሳብ እየከፈለው መጣ፡፡ ከመልካም ምግባሯ ይልቅ የዓለሙ ደስታ አጓጓት፡፡ በጎ ሥራዋን ዘነጋችው፡፡ ከዕለት ወደ ዕለት እየተለወጠች ከመልካም ነገር እየራቀች ወደ ኃጢአት ሥራ እየተሳበች መጣች፡፡
የተራቡ ይመገቡበት፣ የተቸገሩ ይረዱበት የነበረ ቤት፣ መነኮሳት ያርፉበትና ይስተናገዱበት የነበረ፣ ለመልካም ተግባር ያገለግል የነበረ ቤት ተለወጠ፡፡ የዝሙት ቤት አደረገችው፡፡ እርሷም በመልኳና በቁመናዋ ወንዶችን እያባበለች በዝሙት ተግባር ተሰማራች፡፡ ኃጢአትን አብዝታ ትፈጽም ጀመር፡፡
ይኽም ሥራዋ ከምትኖርበት አካባቢ አልፎ በሚያውቋት መነኮሳትም ዘንድ ተሰማ፡፡ ወሬው በአስቄጥስ ገዳም ደረሰ፡፡ ገዳመ አስቄጥስ ከዓባይ መጨረሻ ደቡባዊ ምዕራብ አቅጣጫ 65 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ አሁን ዋዲ አልናትሩን በሚባል፣ ከደቡም ምሥራቅ ወደ ሰሜን ምዕራብ 30 ኪሎ ሜትር ያህል በተዘረጋው ሸለቆ ውስጥ፣ በሊቢያ በረሃ አካባቢ የሚገኝ ገዳም ነው፡፡
የአትናሲያን ነገር በገዳሙ የሚኖሩት አረጋውያን ቅዱሳን እንደሰሙ ስለእርሷ እጅግ አዘኑ፡፡ መልካም ሥራዋን ያውቁ ስለነበረ ዝም ብለው ሊተዋት አልፈቀዱም፡፡ ተመካከሩ፡፡ ከአለችበት ድረስ መክሮና አስተምሮ የሚመልሳት እንደሚያስፈልግ ተገንዝበዋል፡፡ ሆኖም የአስቄጥስን ገዳም በረሃ አቋርጦ አትናሲያ ዘንድ መሄድ አለበት፡፡ ለዚህም የሚሆን ትሁትና ታዛዥ ሰው ያስፈልጋል፡፡ እናም በታዛዥነቱ የሚታወቀውን አባ ዮሐንስ ሐጺርን መረጡት፡፡
አባ ዮሐንስ ሐጺር ታሪኩን ባለፈው እንደተመለከትነው ወላጆቹ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያደረባቸው በእምነት የጸኑ በመልካም ምግባር የጠነከሩ ነበሩ፡፡ አባ ዮሐንስ ከወላጆቹና ከአንድ ወንድሙ ተለያይቶ ወደ ገዳም የገባውም ገና በልጅነቱ ነው፡፡ባለፈው እንደገለጽነው የገዳሙ አበምኔት ወድቆ ያገኘውን ደረቅ እንጨት አንስቶ “ ይኽንን ደረቅ እንጨት ወስደህ ትከለው፡፡ ሳታቋርጥም ውሃ አጠጣው” ብሎ አዘዘው፡፡ አባ ዮሐንስ የደረቀ እንጨት አይጸድቅም ብሎ አልተናገረም፡፡ “እሺ” ብሎ በትህትና ታዘዘ፡፡ ደረቁን እንጨት ተክሎ ከ18 ኪሎ ሜትር ርቀት በቀን ሁለት ጊዜ ውሃ እያመላለሰ ያጠጣው ነበር፡፡ ሦስት ዓመት ያማቋረጥ ውሃ ሲያጠጣ ቆይቶ የደረቀው እንጨት ለመለመ፡፡ አድጎ ዛፍ ሆኖ ጣፋጭ ፍሬ አፈራ፡፡ አበምኔቱ ከዛፉ ፍሬ ወስዶ ወደ ታላላቆቹ መነኮሳት ዘንድ ይዞት ሄደ፤ “ እንካችሁ የታዛዥነትን ፍሬ ብሉ” ብሎ ሰጣቸው፡፡ ይኸው በአባ ዮሐንስ ሐጺር ቅን ታዛዥነት ያደገ ዛፍ ዛሬም በገዳሙ ይገኛል፡፡
እነዚያም የገዳሙ አረጋውያን መነኮሳት አባ ዮሐንስ ሐጺርን ጠርተው ስለ አትናሲያ ነገሩት፡፡ ወደ እርሷ ሄዶ ነፍሷን ያድን ዘንደ ለመኑት፡፡ አባ ዮሐንስም ትእዛዛቸውን ተቀበለ፡፡ በጸሎታቸው እንዲረዱት አሳስቦ አስቸጋሪውን የበረሃ ጉዞ ሊያያዘው ተነሳ፡፡ ከረጅሙ የበረሃ ጉዞ በኋላ አትናሲያ ወዳለችበት ቦታ ደረሰ፡፡ ከቤቷም ሄዶ እንግዳ ተቀባይዋን “ ለእመቤትሽ ስለ እኔ ንገሪ” በማለት እንድታገናኘው ጠየቃት፡፡ እንግዳ ተቀባይዋም ወደ እመቤቷ ሄዳ የእንግዳውን መልእክት ነገረች፡፡ አትናሲያ መልእክቱን በሰማች ጊዜ እንደ ለመዱት “እንግዶቿ” ለረከሰ ሥራ ፈልገዋት የመጡ መሰላት፡፡ በመኝታ ክፍሏ ውስጥ እንደሆነች ተዘገጃጀች፡፡ ተኳኩላ አጊጣ በአልጋዋ ላይ ሆና እንግዳውን አስጠራችው፡፡
አባ ዮሐንስ እየጸለየ ይጠብቃል፡፡ “በሞት ጥላ ውስጥ ብሄድም እንኳን ክፉን አልፈራም አንተ ከእኔ ጋር ነህና” እያለም ይዘምር ነበር፡፡ የአትናሲያ ጥሪ ደርሶት እንግዳ ተቀባዩዋ እየመራችው ወደ መኝታ ቤቷ ገባ፡፡ አየችው፡፡ ጠበቀችው፡፡ የዛሬው እንግዳዋ ከዚህ በፊት እንደምታስተናግዳቸው የለመደቻቸው እንግዶች ዓይነት አይደለም፡፡ አስተያየቱም አኳኋኑም የተለየ ነው፡፡ አባበለችው፡፡ በአልጋዋ ላይ ከአጠገቧ እንዲቀመጥ ጋበዘችው፡፡ አባ ዮሐንስ ከጎኗ ተቀመጠ፡፡ ጠበቀች፡፡ እንግዳዋ በዝምታ ቆየ ከዚያም ራሱን ዘንበል አድርጎ ያለቅስ ጀመር፡፡ አትናሲያ በእንግዳዋ አኳኋን ተገርማ “ለምን ታለቅሳለህ ? ” ስትል ጠየቀችው፡፡ ቀና አለና በአትኩሮት አያት፡፡ አስተያየቱ ንጹሕና የአባትነት አስተያየት ነው፡፡ ለተጎዳ ለተጨነቀ፣ በችግር ላይ ላለ ልጅ የሚያዝን፣ ከልብ የሚያስብ አባታዊ አስተያየት፡፡
“አትናሲያ ሰይጣናት በላይሽ ሲጫወቱ አየኋቸው” መልሷን አልጠበቀም “ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስን ለምን አሳዘንሽው የቀድሞ በጎ ሥራሽን ትተሽ ወደ ጥፋት ሥራ ተመልሰሻልና አላት፡፡
አትናሲያ የተናገራትን ቃል ስትሰማ ደነገጠች፡፡ የቀደመ ስሜቷን አኳኋና ወዲያው ተለወጠ፡፡ ተንቀጠቀጠች፡፡ በዚያች አፍታ ራሷን ወደ ውስጧ አየች፡፡ መረመረች፡፡ በኃጢአት ያለፈ ሕይወቷ አንድ በአንድ ታያት በእጅጉ መበደሏ ጥፋቷ ታሰባት ባለፈ ውድቀትዋ ሁሉ ተጸጸተች፡፡ በሰራችው ሥራ አዘነች እናም እያለቀሰች “ምን ይሻለኛል?” በማለት ጠየቀችው፡፡ አባ ዮሐንስ ኀጺርም የእግዚአብሔርን መሐሪነትና ቸርነት ነገራት፡፡ በርጋታ እየመከረ ካስተማራት በኋላ “ንስሐ ግቢ” አላት፡፡ የኃጢአቷን ብዛት የበደሏን ታላቅነት ስታስበው “እግዚአብሔር ይቀበለኛልን ? ” ስትል ጠየቀችው፡፡ እርሱም “አዎን” በማለት የእግዚአብሔር ይቅር ባይነት አስረዳት፡፡
ከዚያ በኋላ አትናሲያ ተረጋጋች፡፡ በቃ ሕይወቷ በኃጢአት እንደአደፈ መቆየት የለበትም፡፡ ወሰነች፡፡ ከአለችበት ድረስ የመጣላትን የእግዚአብሔርን ቸርነት ማሳለፍና ማጣት የለባትም፡፡ ከአባ ዮሐንስ ምክር በኋላ ዓለም ኃላፊ መሆኑን ተገንዝባ ዘለዓለማዊውን ሕይወት መርጣለችና አላቅማማችም፡፡ ቤት ንብረቷን ለማሰብ ወደኋላ አላለችም፡፡ “ወደምትሔድበት ከአንተ ጋር ውሰደኝ” ስትል ለመነችው፡፡ እሱም “ነይ ተከተይኝ” አላት፡፡
ወርቅና አልማዝ ጌጦችን አልፈለገችም፡፡ ልብሶቿን አልመረጠችም፡፡ ከገንዘቧ ምንም ምን አልያዘችም፡፡ ያን ጊዜውኑ ፈጥና ተነስታ አባ ዮሐንስን ተከተለችው፡፡
ቀኑን ሙሉ ሲጓዙ ውለው በመሸ ጊዜ ለማደር ወደ ጫካ ውስጥ ገቡ፡፡ በዚያም ለእርሷ መኝታ የሚሆን ቦታ አዘጋጅቶ “እስኪነጋ በዚህ አረፍ ብለሽ ተኚ፡፡ እኔም ወደዚያ እሆናለሁ” አላት፡፡ ይህንንም ብሎ ከእርሷ ራቅ ብሎ ተገለለና እየጸለየ ብቻውን ተቀመጠ፡፡
አባ ዮሐንስ በሌሊቱ እኩሌታ ለጸሎት በተነሣ ጊዜ ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርስ የብርሃን ምሰሶ ተተክሎ አየ፡፡ የእግዚአብሔርም መላእክት የከበረች ነፍስዋን ተሸክመው ሲወጡ በአድናቆት ተመለከተ፡፡ በነጋም ጊዜ ወደ አትናሲያ ሄደ፤ ዐርፋም አገኛት፡፡ እጅግም አዘነ፡፡ ስለእርሷም ይገልጥለት ዘንድ እየሰገደ ወደ እግዚአብሔር ለመነ፡፡ ወደ እርሱም “ከቤቷ በወጣች ጊዜ እግዚአብሔር ንስሐዋን ተቀብሎ ኃጢአትሽ ተሠረየልሽ ብሏታል” የሚል ቃል መጣ፡፡ አባ ዮሐንስ ይኽን እንደሰማ የአትናሲያን ነፍስ መዳን ተረድቶና በሐሴት ተሞልቶ ወደ ገዳመ አስቄጥስ ሄዶ ለአረጋውያን የሆነውን ሁሉ ነገራቸው፡፡ ቅዱሳን አባቶች እርሱ እንዳያት ሁሉ እነርሱም ማየታቸውን ነገሩት፡፡ በአንድነት ሆነው የኃጢአተኛን ወደ ንስሐ መመለሱን እንጂ ሞቱን የማይሻ እግዚአብሔር አመሰኑት፡፡
የቅዱሳን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር የተመሰነ ይሁን፡፡
ለእኛም ዕድሜ ለንስሐ ዘመን ለፍስሐ ያድለን ፡፡
No comments:
Post a Comment