13

.

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው::" የማቴዎስ ወንጌል 7: 4

"እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅናወተት ግዙ።" ትንቢተ ኢሳይያስ 55 : 1

Friday, November 25, 2011

የአባ ዮሐንስ ኀፂር ሕይወት -ክፍል 2


ዮሐንስ ኀፂር ቤተሰቦቹ ያወጡለት ስም ኮሎቦስ የሚል ነው፡፡ በሀገራቸው ቋንቋ አጭር፣ ድንክ ማለት ነው፡፡ በገዳመ አስቄጥስ በተጋድሎ ጸንተው ክብር ካገኙ ቅዱሳን መካከል አንዱና በግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ታላቅ ክብር ያለው አባት ነው፡፡ ቤተክርስቲያናችንም ከምትዘክራቸው ቅዱሳን መካከል አንዱ ነው፡፡ /ነሐሴ 29/ ፍልስተ አጽሙን ቤተክርስቲያን ታከብራለች፡፡ 
አባ ዮሐንስ ኀፂር በላይኛው ግብኝ “ቴባን” በምትባል መንደር በ339 ዓ.ም. ገደማ ተወለደ፡፡ ምንም እንኳን ቤተሰቦቹ የተትረፈረፈ ምድራዊ ሀብት ባይኖራቸውም ትዳራቸው በፍቅርና በፈሪሃ እግዚአብሔር ያጌጠ ነበር፡፡ ገና ለጋ ሕፃን  ሳለ የዘወትር ምኞቱ መንኩሶ መኖር ነበር፡፡ ውሎ ሲያድር በልቡና ያሰበውን እውን ያደርግ ዘንድ መንፈሰ እግዚአብሔር አነሣሣው፡፡ መላ ዘመኑን በሥርዓተ አበው በተጋድሎ ሊፈጽም ራቅ ወዳለ በረሃማ ገዳም ሄደ፡፡ ይህችውም ገዳመ አስቄጥስ ናት፡፡

ዮሐንስ በፍጹም  ትኅትና ወደ ገዳሙ አበምኔት ወደ አባ ባሞይ ቀርቦ የዘወትር ምኞቱን ነገራቸው፡፡ ልጅነቱን ተመልክተው /አሥራ ስምንት ዓመቱ ነበር/ በወቅቱ ከባድና አስቸጋሪ የሆነውን የምንኩስና ሕይወት ለዚያውም በገዳም አስቄጥስ ሊቋቋም እንደማይችል ፤ የገዳሙ መነኮሳት ሁሉ ብዙ ደክመው ራሳቸውን ከመመገባቸውም በላይ በጾምና በስግደት ብዙ ተጋድሎ እንደሚያደርጉ፣ /ለመኝታቸው/ የሰሌን ምንጣፍ እንኳን ስለሌላቸው ከበረሃው አሸዋ ላይ እንደሚተኙ ካስረዱት በኋላ ወደ አገሩ ተመልሶ ትዳር ይዞ በንጽሕና  በቅድስና ይኖር ዘንድ መከሩት፡፡ ከመጀመሪያውኑ በፈቃደ እግዚአብሔር መጥቷልና አባቴ ሆይ በትእዛዝህ ሁሉ እየተመራሁ ያዘዝከኝን እየፈጸምኩ እኖር ዘንድ መጥታቸለሁ፡፡ ልጅነቴን ዓይተህ እንዳትመልሰኝ በእግዚአብሔር ስም እለምንሃለሁ፡፡ ደግሞም አንተ ብትቀበለኝ እግዚአብሔር መልካሙን ሁሉ እንደሚያደርግልኝ አምናለሁ” ሲል አበምኔቱን ለመነው፡፡

አባ ባሞይ ነገሩ ቢከብደው ስለ ዮሐንስ የሚያደርገውን ይገልጥለት ዘንድ ወደ እግዚአብሔር አመለከተ፡፡ በዚያችም ሌሊተ ከእግዚአብሔር የተላከ መልአክ ተገልጦ “ዮሐንስ ለእግዚአብሔር የተመረጠ ዕቃ ነው፡፡ በመሆኑም እንድትቀበለው እግዚአብሔር አዝዞሃል” ሲል አስረዳው፡፡ በዚህ መሠረት ጊዜው ሲደርስ የገዳሙ መነኮሳት ተሰብስበው ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት ጾመው ጸልየው ሥርዓተ ምንኩስናውን ፈጸሙለት፡፡
ምንም እንኳን በዘመኑ በገዳሙ ያለው ሥርዓት የተጠናከረ ባይሆንም ዮሐንስ ብዙ ምግባር ትሩፋትን ያለሃኬት ይፈጽም ጀመር፡፡ ሃሳብን ከሚከፋፍል፣ ልቡናን ለምኞት ከሚጋብዝ ንግግርና ከሌሎች ጋር ጊዜን በጨዋታ ማባከንን ከራሱ አራቀ፡፡ እንደወጣኒ ሳይሆን በፍጹማን አምሳል ረሃብና ጥሙን እየታገሰ በትሕርምት፣ በጾም፣ በጸሎት፣ በሰጊድ ጸና ፡፡ ከመምህሩ ከአባ ባሞይ የተማራቸውን አጽንዖ በዓትን፣ ማስተዋልን፣ ጸጥታና መረጋጋትን፣ በመከራ መጽናትን፣ ትሕትናን፣ ታዛዥነትን ገንዘብ አደረገ፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ባሞይ ዮሐንስን ይመክረው ዘንድ ተነሣ፡፡ ብዙ ምክር ከሰጠውም በኋላ ከእርሱ ጋረ ማደር እንደሌለበት ነገረው፡፡ በዚህ መሠረት ዮሐንስ ለሰባት ቀናት ወደ መምህሩ በኣት ሳይገባ በውጪ ለዚያውም ከገዳሙ ክልል ውጭ ቆመ፡፡ ይህም ሳያንሰው አባ ባሞይ ዕለት ዕለት እየሄደ ትዕግሥትን እንዲማር በዱላ ይመታው ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆንበት ዮሐንስ እየሰገደ “አባቴ ሆይ ይቅር በለኝ” በማለት  ይለምነው ነበር፡፡ በሰባተኛው ቀን አባ ባሞይ ወደቤተክርስቲያን ሲሄድ ስድስት መላእክት ስድስት አክሊል ይዘው በዮሐንስ ራስ ሲያቀዳጁ አየ፡፡ በዚህ ተገርሞ ዮሐንስን ወደ በኣቱ መለሰው፡፡
ታዛዥነትና ተዘክሮተ እግዚአብሔር አባ ዮሐንስ ከሚታወቅባቸው መልካም ምግባራት መካከል የሚጠቀሱለት ናቸው፡፡ አንደ ቀን አባ ባሞይ ዮሐንስ ኀፂርን የደረቀ እንጨት ተክሎ ለምልማ እስክታፈራ ድርስ ውኃ እንዲያጠጣት አዘዘው፡፡ ያለማንጎራጎር በትኅትና ሆኖ አሥራ ሁለት ምዕራፍ ያህል ከሚርቅ ቦታ በቀን ሁለት ጊዜ ውኃ እያመላለሰ ያጠጣው ጀመር፡፡ በሦስተኛው ዓመት ያቺ በትር ለምልማ፣ አብባ ያማረ ፍሬ አፈራች፡፡ አባ ባሞይ በዮሐንስ ታዛዥነት እጅግ ተደሰተ፡፡ ፍሬውን ለቅሞ ለገዳሙ መነኮሳት እንካችሁ ይህ የታዛዥነት ፍሬ ነው እያለ ሰጣቸው፡፡ መነኮሳቱም ይህን ተአምር ባዩ ጊዜ አደነቁ፡፡ ለቅን ታዛዥ ሰው ይህ ጸጋ የሰጠ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡ በ402 ኛ.ም. በግብፅ ይኖር የነበረው ፓስቱሚያ /postumian/  በገዳሙ የአትክልተ ሥፍራ የአባ ዮሐንንስ እንጨት ለምልማና ብዙ ቅርንጫፎች አውጥታ ማየቱን መስክሯል፡፡
ዮሐንስ በልቡናው ዘወትር እግዚአብሔርን ያስብ ነበር፡፡ ከማሰብ ለአፍታ ያህል እንኳን አያቋርጥም፡፡ በዚህም በዙሪያው ያሉትን፣ በእጅ የሚሠራውን እስከመርሳት ደርሶ ነገረ እግዚአብሔርን በማሰብ ልቡናው ይመሰጥ ነበር ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም አርምሞን /ጸጥታን/ ገንዘብ በማድረግም ይታወቃል፡፡ የአርምሞን ጠቃሚነት አስመልክቶም ልጄ ሆይ መጥፎ ሃሳብ በአእምሮህ ተመላልሶ ልቡናህን መሳት ደረጃ ብትደርስም ዝም በል፣ አታጉረምርም በማለት ይመክር ነበር፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥ የበለጠ አፍአዊና ውሳጣዊ ዝምታ የሚገባ መሆኑን አስመልክቶም በቤተክርስቲያንም ውስጥ ቅዱሳት ምሥጢራት የሚፈጸሙበተ ቦታ መሆኑን ተገንዝበን ከምንጊዜውም በላይ ጸጥታንና አርምሞን እንያዝ ብሎ አስተምሯል፡፡
አባ ዮሐንስ ኀፂር ራስን የመግዛት ጥቅምን በሚመለከትም “አንድ መነኩሴ ከፍጹምነት ደረጃ መድረስ የሚችለው መላ ሕዋሳቱን ጠብቆ በልቡናው ተዘክሮተ እግዚአብሔርን ሲይዝ ነው” ብሏል፡፡ ከዚህ እምነቱ የተነሣም ስለጊዜያዊ ደስታ ማሰብና ማውራትን ይጠላ ነበር፡፡ በዚህም ፈንታ አፍአዊና ውሳጣዊ ሕዋሳትን የሚገባ መሆኑን በመግለጥ ያስተምር ነበር፡፡ የዚህም ምክንያት “ሰው አብዝቶ ሕዋሳቱን በገዛ ቁጥር በልቡናው የሚመላለሱ ምክንያቶች ከውስጡ እየጠፉ ይሄዳሉ፡፡ ይህም ልቡናን ሰላማዊና የተረጋጋ ያደርጋል” በማለት ያስረዳል፡፡
አባ ዮሐንስ ይህን በመሰለ መንፈሳዊ ተጋድሎ በርትቶ ሳለ አበምኔቱ አባ ባሞይ ለአሥራ ስምንት ዓመታት በደዌ ዘእሴት ክፉኛ ተይዘው ነበርና፡፡ እርሳቸውን ያስታምም ነበር፡፡ በስተመጨረሻም አባ ባሞይ ሊሞቱ ሲሉ የገዳሙን መነኮሳት አስጠርተው “አባ ዮሐንስን አክብሩት፣ ታዘዙለት፣ እርሱ በምድር የሚኖር መልአክ ነው እንጂ ሰው አይደለም” በማለት ክብሩ ከሰማያውያን መላእክት ደረጃ መድረሱን መሰከሩለት፡፡
በእንዲህ ዓይነት ተጋድሎ ጸንቶ ሳለ በአካባቢው የሚገኙ አረማውያን መነኮሳቱን ሊያርዱ፣ ሊያቃጥሉ መጡ፡፡ ዮሐንስም ወደ አባ እንጦንስ ገዳም ወደ ቁልዝም ሄደ፡፡ መሄዱም ሞትን ፈርቶ ለመሸሽ አልነበረም፡፡ ነገር ግን በአረማዊው ወንድሙ እጅ ሞቶ እርሱን በመግደላቸው ለዘላለም ሞት እንዳይዳረጉ በማዘን ነበር፡፡ በቁልዝም ገዳምም ዋሻ አዘጋጅቶ በብሕትውና ተጋድሎውን ተያያዘው፡፡
በአንድ ወቅትም የገዳሙ ምርት በመሰብሰብ ላይ ሳሉ አልታዘዝ ብሎ መነኮሳቱን ያስቸገረ አንድ መነኩሴ ይመክረው ዘንድ ለአባ ዮሐንስ አቀረቡለት፡፡ እርሱም አልታዘዝም ያለውን ይቅር በለኝ እያለ ጀመር፡፡ ላመት ሙሉ ጥቂት ጨው ብቻ ያላት ቁራሽ ደረቅ ዳቤ እየበላ አልታዘዝ ስላለው መነኩሴ አለቀሰ፡፡ ጌታ ሆይ ፍጥረትህን ሳላውቅ አናድጄዋለሁ፡፡ አሁንም አንተ ይቅር በለኝ በማለት ብዙ ጸለየ፡፡ በዚህ ጸሎቱም በደለኛውን ወደ ታዛዥነት መለሰው፡፡
አባ ዮሐንስ በጸሎቱ በለቅሶው ወደ እግዚአብሔር ከመለሳቸው ኃጥአን መካከል አትናስያ አንዷ ናት፡፡የአትናሲያን ታሪክ በሚቀጥለው እንመለከተዋለን ፡፡በዚህ ዓይነት ኃጥአንን ከእግዚአብሔር እያስታረቀ በአካባቢው ያትን ጎሳዎእ እያጠመቀ በቅድስና ዘመኑን ፈጸመ፡፡ በዘመኑ ፍጻሜም ደቀ መዛሙርቱ ቀርበው የመጨረሻ ምክሩን እንዲሰጣቸው ለመኑት፡፡ ብዙ ከመከራቸው በኋላ “. . .የራሴን ሥራዊ ፍላጎት በፍጹም አልከተልም፡፡ በራሴ ያልሠራሁትንም ሥራ ሌሎች ይሠሩ ዘንድ በፍጹም አልመክርም” በማለት አካፈላቸው፡፡ ብዙ ቃል ኪዳን ተቀብሎ በክብር ባረፈባት ዕለት ቅዱሳን መላእክት በመዝሙር በይባቤ ክብርት ነፍሱን ወደ ገነት አሳረጓት፡፡

የአባ ዮሐንስ ኀፂር ረድኤት በረከት አይለየን፡፡ 

No comments:

Post a Comment