13

.

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው::" የማቴዎስ ወንጌል 7: 4

"እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅናወተት ግዙ።" ትንቢተ ኢሳይያስ 55 : 1

Monday, September 19, 2011

ነገረ ማርያም ክፍል፦ ፰

መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው


«ወላዲተ ቃል፤»
  እግዚአብሔር ተወለደ፤

ካለፈው የቀጠለ፦

፬፦ ቃል ሥጋ የሆነው ፦ ያለ ሚጠት ነው፤
          ሚጠት፦ ማለት፦ መመለስ ማለት ነው። ይኽውም እንደ ማየ ግብፅ ፥ እንደ በትረ ሙሴ ነው። «ሙሴና አሮንም እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው እንዲሁ አደረጉ፤ አሮንም በትሩን አነሣ፤ በፈርዖንና በሹሞቹ ፊት የወንዙን ውኃ መታ፤ የወንዙም ውኃ ሁሉ ተለወጦ ደም ሆነ።» ይላል። ዘዳ ፯፥፳። የግብፅ ወንዞች ደም የሆኑት ውኃነታቸውን ሙሉ በሙሉ ለቅቀው ነው። በመጨረሻም ደምነታቸውን ትተው ወደ ውኃነታቸው ተመልሰዋል። ባይመለሱ ኖሮ እስከዛሬም የግብጽ ወንዞች ደም ሆነው በቀሩ ነበር። ሚጠት ማለት እንዲህ ነው።
          እግዚአብሔርም ሙሴን፦ «ይህ በእጅህ ያለው ምንድን ነው?» አለው። እርሱም «በትር ነው፤» አለ። «ወደ መሬትም ጣለው፤ አለው፤ እባብም ሆነ፤ ሙሴም ከእርሱ ሸሸ። እግዚአብሔርም ሙሴን፦ «እጅህን ዘርግተህ ጅራቱን ያዝ፤» አለው፤ ሙሴም እጁን ዘርግቶ ፥ ጅራቱን ይዞ ፥ አነሣው፤ በእጁም ላይ በትር ሆነ።የሙሴ በትር እባብ የሆነችው እንጨትነቷን ለቅቃ ነው። በዚያው አልቀረችም ፥ ተመልሳ በትር ሆናለች። ዘፀ ፫፥፪። እንግዲህ ቃል ሥጋ ሲሆን፦ አምላክነቱን ለቅቆ ሰው የሆነ ፥ ተመልሶም ሰውነቱን ለቅቆ አምላክ የሆነ አይደለም። ቅዱስ ቄርሎስ፦ «ክርስቶስን በፊት ሰው ሆኖ ኋላ ተመልሶ አምላክ ሆነ አንለውም፤ ቃል ጥንቱን አምላክ ነበረ እንጂ፤ እርሱ አንዱ፦ ሰው የሆነ አምላክ እንደሆነ እናውቅ ዘንድ፤» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፸፪፥፭)
፭፦ ቃል ሥጋ የሆነው፦ ያለ ውላጤ ነው፤
          ውላጤ ማለት መለወጥ ማለት ነው። ይህም እንደ ብእሲተ ሎጥ እና እንደ ማየ ቃና ነው። ቅዱሳን መላእክት፦ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል፦ ሎጥን፦ «ተነሣ፤ ሚስትህንና ከዚህ ያሉትን ሁለቱን ሴቶች ልጆችህን ውሰድ፤ አንተም በከተማይቱ ሰዎች ኃጢአት እንዳትጠፋ፤» ብለውት ከከተማይቱ እያቻኮሉ አውጥተውታል። ከዚህም በኋላ፦ ራስህን አድን፤ ወደ ኋላ አትይ ፥ በዚህም ዙሪያ ሁሉ አትቁም ፥ እንዳትጠፋም ወደ ተራራው ሸሽተህ አምልጥ።» ብለውታል። ዘፍ ፲፱ ፥፲፪-፳፰። የሎጥ ሚስት ግን ቅዱሳን መላእክት የሠሩላቸውን ሥርዓት አቃልላ በዚያ ሥፍራ ቆመች ፥ ወደ ኋላዋም አየች። በዚህም ምክንያት ሙሉ በሙሉ ተለውጣ የጨው ሐውልት ሆና ቀርታለች።
          በአዲስ ኪዳን ደግሞ፦ በቃና ዘገሊላ ሠርግ ነበረ፤ በዚህ ሠርግ ላይ፦ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና የጌታ ደቀመዛሙርት ነበሩ። እናትን ጠርቶ ልጅን ፥ ወይም ልጅን ጠርተው እናትን፤ መምህርን ጠርተው ደቀመዛሙርትን ፥ ወይም ደቀመዛሙርትን ጠርተው መምህርን ማስቀረት ስለማይገባ ሁሉም ተጠርተዋል። ወደ ሠርጉ የተጠሩ እድምተኞች ብዙዎች ስለነበሩ ፥ የወይን ጠጁ አልቆ ሠራተኞቹ ተጨነቁ። ከሰው ወገን የሰው ችግር ፈጥኖ የሚገባት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሳይነግሯት አውቃላቸው አማለደቻቸው። ጌታም በስድስቱ የድንጋይ ጋኖች ያስሞላውን ውኃ በተአምር ወደ ወይን ጠጅነት ለወጠው። ዮሐ ፪፥፩-፲፩። ውኃው ሙሉ በሙሉ ተለውጦ የወይን ጠጅ ሆኗል። ውላጤ ማለት እንዲህ ነው። «ቃል ሥጋ ሆነ፤» ማለት ግን፦ አምላክነቱን ለቅቆ ፥ ተለውጦ፥ ሰው ሆነ፤ ማለት አይደለም። ምክንያቱም ቃል እግዚአብሔር ነውና፤ ዮሐ ፩፥፪። እግዚአብሔር ደግሞ አይለወጥም። ይኽንንም፦ «እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም፤» በማለት ነግሮናል። ሚል ፫፥፮። ደግሞም ቃል ሥጋ የሆነው በመለወጥ ቢሆን ኖሮ፦ ጌታችን፦ ሰው ከሆነ በኋላ፦ «እኔና አብ አንድ ነን፤» አይልም ነበር። ዮሐ ፩፥፴። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ በመስቀል ላይ የፈሰሰውን ደም፦ «የእግዚአብሔር ደም፤» አይለውም ነበር። የሐዋ ፳፥፳፰። ከዚህም ሌላ አምላክ ወደዚህ ዓለም የመጣበትን የማዳን ዓላማ መርሳት አይገባም። ለመሆኑ ጌታችን ዓለምን ለማዳን ተለወጦ ሰው መሆን ለምን አስፈለገው? በሰማይ ዙፋን እንደተቀመጠ፦ በአንድ ነቢይ ወይም በአንድ ሐዋርያ ደም ዓለምን አያድንም ነበር? ቅዱስ ቄርሎስ፦ «ቃል ሰው ሲሆን ከነበረበት ባህርዩ አልተለወጠም ፥ በእኛ ባሕርይ ቢገለጥም ፦ ቃል አስቀድሞ በነበረበት ባሕርዩ ጸንቶ ኖረ፤» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፸፪ ፥፬) ። ዳግመኛም፦ «የማይታየው ሳይለወጥ ሰው ሆነ፤ ከቀደሙ አበው፦ አስቀድሞ የነበረ እርሱ በሥጋ ተወለደ፤» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፸፪ ፥ ፲፭)። ሦስተኛም፦ «የእግዚአብሔር ቃል ሥጋን ወደ መሆን ፥ ሥጋም መለኮትን ወደ መሆን ተለወጠ አንልም ፤ የእግዚአብሔር ቃል አይናወጥም ፥ አይለወጥምና፤» ብሏል። (ሃይ ፡ አበው ፸፬፥፵) ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙም፦ «ሁሉን የፈጠረ ነው ፤ ሰው ከመሆኑ አስቀድሞ ፥ ሰውም ሆኖ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከተወለደ በኋላ እግዚአብሔር ቃል ነውና፤ እርሱ መቸም መች አንድ ነው ፤ የመለኮቱ ባሕርይ አልተለወጠም፤» ብሏል። (ሃይ ፡ ፷፥፲፯)። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ደግሞ፦  «ዳግመኛ ድንግልናዋ እንዳልተለወጠ፦ ጽኑዕ መለኮቱ ከባሕርዩ አልተለወጠም፤ አምላክ ለሦስትነት እንደሚገባ ተወለደ፤» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፷፯ ፥፯)። ቅዱስ ኤፍሬምም በሐሙስ ውዳሴ ማርያም ላይ፦ «እምድኅረ ወለደቶ ድንግልናሃ ተረክበ ፥ ወመለኮቱ ኢተወለጠ ኮነ ወልደ ዕጓለ እመሕያው፤ «እርሱንም ከወለደችው በኋላ ማኅተመ ድንግልናዋ አልተለወጠም ፥ ሰውም ቢሆን ባሕርየ መለኮቱ አልተለወጠም፤» ብሏል።
፮፦ ቃል ሥጋ የሆነው ያለ ቱሳሔ ነው፤
          ቱሳሔ ማለት፦ ቅልቅል ፥ የተቀላቀለ ማለት ነው። ይኸውም እንደ ማር እና እንደ ውኃ ፥ እንደ ወተት እና እንደ ቡና ነው። ማር እና ውኃ ቢቀላቀሉ፦ ስም ማዕከላዊ ፥መልክ ማዕከላዊ ፥ ጣዕመ ማዕከላዊ ፥ ይገኝባቸዋል። ስም ማዕከላዊ የሚባለው፦ የዕለቱ ብርዝ ፥ የሰነበተው ጠጅ ይባላል እንጂ ከቀደሙት ስሞች በአንዱ ወኃ ወይም ማር ተብለው  አይጠሩም። መልክ ማዕከላዊ የሚባለው፦ ብርዙ ወይም ጠጁ፦ እንደ ማር አይነጣም ፥ ወይም እንደ ውኃ አይጠቁርም ፥ ማዕከላዊ መልክ ይይዛል። ጣዕም ማዕከላዊ የሚባለው ደግሞ፦ እንደ ማር ሳይከብድ ፥ እንደ ውኃም ሳይቀል መካከለኛ ጣዕም ይኖረዋል። ወተት እና ቡናም ሲቀላቀሉ እንዲሁ ናቸው። እንደ ወተት ያልነጣ ፥ እንደ ቡናም ያልጠቆረ ማዕከላዊ መልክ ያመጣሉ፤ ጣዕማቸውም ከሁለቱም ወስዶ ማዕከላዊ ይሆናል፤ ስማቸውም፦ በማዕከላዊ ስም፦ «ማኪያቶ» ቢባል እንጂ በቀደመ ስም ቡና ወይም ወተት ተብለው አይጠሩም።
          ቃል ሥጋ የሆነው እንዲህ አይደለም፤ እንዲህ ቢሆን ኖሮ፦ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክም ፥ የሰው ልጅም ተብሎ አይጠራም ነበር። ነገር ግን ሰው ከሆነ በኋላ «የሰው ልጅ፤» ተብሎ ተጠርቷል። ማቴ ፲፮፥፲፫። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ደግሞ፦ «የእግዚአብሔር ልጅ (የአብ ልጅ ወልድ) እንደመጣ ፥ እውነተኛም የሆነውን እግዚአብሔርን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደሰጠን እናውቃለን፤ . . .  እርሱም እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው፤» ብሎታል። ፩ኛ ዮሐ ፭፥፳። ይኽንን በተመለከተ፦ ቅዱስ ቄርሎስ፦ «መለኮትና ትስብእት እርስ በርሳቸው ሳይቀላቀሉ፦ መለየት በሌለበት ተዋሕዶ ፈጽመው አንድ ሆኑ፤» ብሏል። (ሃይ ፡ አበው ፸፫ ፥፴)።
፯፦ ቃል ሥጋ የሆነው ያለ ትድምርት ነው፤
          ትድምርት ማለት፦ መደረብ ፥ መደመር ማለት ነው። ይህም እንደ ልብስ ፥ እንደ እንጀራ ነው። ልብስ ቢደርቡት ይደረባል ፥ ቢነጥሉት ይነጠላል፤ እንጀራም ቢደርቡት ይደረባል ፥ ቢነጥሉት ይነጠላል። ቃል ሥጋ የሆነው እንዲህ፦ በመደረብ ወይም በመደመር አይደለም። መለኮት፦ ከሥጋ ተጠግቶ ፥ ወይም ተደርቦ፥ የኖረ፦ በኋላም ተለይቶ የሄደ አይደለም። ቅዱስ ቄርሎስ ፦ «ሥጋንም ለእርሱ ብቻ ገንዘብ አደረገ፤ ልብስ ከአካል እንዲለይ መለኮትን ከትስብእት አንለየውም፤ በተዋሕዶ ጸንቶ ይኖራል እንጂ፤ እግዚአብሔር እንደሆነ የእግዚአብሔርም ልጅ እንደሆነ አውቀነዋል።» ብሏል። (ሃይ ፡ አበው ፸፪፥፴)። በተጨማሪም፦ «መለኮትና ትስብእት አንዱ ከአንዱ ጋር በኅብረት የሚኖሩ አይደለም፤ አንዱ በአንዱ አላደረም፤ መለኮትና ትስብእት በባሕርይም በአካልም አንድ ናቸው እንጂ። ሰው የሆነ እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ በዚህ አንቀጽ ከሥጋ ጋር መዋሓዱን የምናገርለት፤ መለኮትን በመዋሓድም አምላክ የሆነው ሰው ነው፤» በማለት ተናግሯል። (ሃይ፡ አበው ፷፩ ፥ ፳፩) ፡
፰፦ ቃል ሥጋ የሆነው ያለ ቡዓዴ ነው ፤
       ቡዓዴ ማለት፦ መለየት ፥ አለያየት ፥ ልዩነት ፥ ማለት ነው። ለምሳሌ፦ ሁለት የተለያዩ ነገሮችን ፦ (ብረትንና እንጨትን)፦ በብሎን ማያያዝ ፥ መልሶም መለያየት ይቻላል። የቃል ሥጋ መሆን እንዲህ አይደለም። የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳስ አባ ዮሐንስ፦ «ይህም ወልድ ዋሕድ ፥ እግዚአብሔር ቃልን ፦ ከወለደችው ከእመቤታችን ከንጽሕት ከቅድስት ድንግል ማርያም የተገኘ ነው፤ ግድ ሰው ሁን ፥ ያለው ሳይኖር፦ ከእርሷ በፈቃዱ ሥጋን ነሣ፤ ለመለኮት ለትስብእት እንደሚገባ ያለመከፈል፦ (በተዋሕዶ) የአምላክነትን ፥ የሰውነትን ሥራ ሠራ፤ እንደ ሰው አነጋገር ይናገራል፤ አምላክ እንደመሆኑ ሙት ያስነሣል፤ ድውይ ይፈውሳል፤ መከራም ይቀበላል፤ ነገር ግን፦ ከማይነገርና ከማይመረመር ተዋሕዶ በኋላ፦ አምላካዊነት ባሕርይ ፥ ከሰብአዊት ባሕርይ ተለይታ አይደለም፤ አነጋገሩን ፥ ሥራውን ፥ መከራውን ፥ ይህ፦ ለመለኮት ይገባል፤ ይህ፦ ለትስብእት ይገባል ፥ እያልን በየራሳቸው አንለይ፤ አንድ ባሕርይ ፥ አንድ አካል ፥ አንድ ገጽ በመሆን (በተዋሕዶ) ሠራው እንበል እንጂ፤» ብሏል። (ሃይ ፡ አበው ፻፲፫ ፥፲፬)።
፱፦ ቃል ሥጋ የሆነው በኅድረት አይደለም፤
          ከላይ እንደገለጥነው፦ ቅዱስ ዮሐንስ፦ አስቀድሞ ፦ «ሆነ፤» ያለው፦ «አደረ፤» የሚለውን ይዘው ኅድረት እንዳይሉበት ነው። «ኅድረት፤» ማለት፦ ማደር ማለት ነው። ይኸውም፦ እንደ ውኃና ማድጋ ፥ እንደ ዳዊትና ማኅደር ፥ እንደ ሰይፍና ሰገባ ነው። እነዚህ አንደኛው አካል በሌለኛው አካል እንደሚቀመጡ፦ (ኀዳሪና ማኅደር) ፦ እንደሆኑ ፥ መለኰትም ፦ ሥጋን ማኅደር አድርጎ የተቀመጠ አይደለም። ይኽንን በተመለከተ፦ ቅዱስ ቄርሎስ፦ «እርሱ አንድ ወልድ አንድ ጌታ ነው፤ ቃል በዕሩቅ ብእሲ አላደረም ፥ በክብሩም አላስተካከለውም፤ ብዙ ሰዎች በድንቊርና አስበው እንደተናገሩት በኅድረት የልጅነትን ክብርና አምላክነትንም አልሰጠውም ፤ ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ፥ ከእግዚአብሔር የተገኘ የእግዚአብሔር ቃል፦ እርሱ ነፍስን ሥጋን ተዋሕዶ ሰው ሆነ እንጂ።» ብሏል። (ሃይ ፡አበው ፸፪ ፥ ፲፩)። ዳግመኛም፦ «እግዚአብሔር ቃልስ ዓለምን ሳይፈጥር አስቀድሞ የነበረ ነው፤ የተዋሓደውን ሥጋም ከሰው ባሕርይ ፈጠረው፤ ከተዋሕዶ በኋላ ለክርስቶስ ሁለት ባሕርያት አሉት ብሎ የተናገረ ከእነርሱ (ከአባቶቻችን) አንድ ሰው እንኳ አለን? ወይስ በእግዚአብሔር ፈቃድ በድንግል ማኅፀን ፍጹም ሕፃን ተፈጠረ ፥ ከዚህ በኋላ ከማርያም በተገኘው በዚያ ሕፃን እግዚአብሔር ቃል አደረበት ብሎ የተናገረ አለን? ወይስ ከተዋሕዶ በኋላ ለአንድ ክርስቶስ ሁለት ባሕርያት አሉት ተብሎ ሊነገር በውኑ ይገባልን?» ብሏል። (ሃይ ፡ አበው ፸፭ ፥፲፩)።
ተጨማሪ ማስረጃ ከሊቃውንት፤
          ቅዱስ አቡሊድስ፦ «ፈጣሪ እርሱ በሰው ያደረ አይደለም፤ በነቢያት በሐዋርያት አድሮ ሥራ የሠራ፦ ፍጹም አምላክ በሥጋ ተገለጠ እንጂ። ሰውም ቢሆን በመለኮቱ ፍጹም ነው፤ . . . ከአብ ዘንድ ብቻውን የተወለደ ፥ ከድንግልም አንድ ብቻውን የተወለደ እርሱ አንድ ነው እንጂ። በተዋሕዶ ሰው የሆነ የባሕርይ አምላክ ነው።» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፴፱ ፥፲፩)። ዳግመኛም፦ «መቀላቀል ፥ ይህንንም የመሰለ ሌላ ነገር የለበትም እንላለን፤ ተዋሕዶው እውነተኛ ስለሆነ ተቀላቀለ ማለት አይስማማውምና። የእግዚአብሔር ልጅ ወልድ ዋሕድ ነፍስን ሥጋን ነሥቶ ሰው ሆነ ባልን ጊዜም፦ ስለዚህም ነገር ቢሆን እነዚያ( መናፍቃን) እንደሚያምኑ መቀላቀል የለበትም፤ የቃል ባሕርይ የሥጋን ባሕርይ ወደ መሆን ፥የሥጋ ባሕርይም የቃልን ባሕርይ ወደ መሆን አልተለወጠም፤ ሁለቱ ባሕርያት ያለመለወጥ ያለመቀላቀል ጸንተው ይኖራሉ እንጂ።» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፵፭ ፥፭)።
          ቅዱስ ፊልክስ፦ «ክርስቶስ በሐዲስ ግብር (በኅድረት በውላጤ) አልመሰለንም፤ በማይመረመር ተዋሕዶ ባሕርያችንን ባሕርይ አድርጎ ነው እንጂ። ብሏል። ቅዱስ ጎርጎርዮስም፦ «የእግዚአብሔር ቃል፦ ድንግል ማርያም በወለደችው ሰው እንዳደረ የሚናገሩትን፦ እኔ ልበ ሰፊ በመሆን፦ የትስብእትና የመለኮት ሁለቱ ባሕርያት በተዋሕዶ አንድ የሆኑ አይደለምን? ብዬ እጠይቃቸዋለሁ፤ በአካል ፍጹም የሚሆን የቃል ባሕርይ፦ የምታውቅና የምትናገር ነፍስ ያለችውም የሥጋን ባሕርይ ተዋሕዷልና ፥ በሥጋም ከድንግል ተወልዷልና። ሰው ሆኖ የታየ እርሱም በፍጡራን ልቡና ከመመርመር የራቀ ነው፤ ከመለኮትና ከትስብእት ከሁለቱ ባሕርያት ድንቅ በሚያሰኝ ምሥጢር አንድ ክርስቶስ ሆነ፤ ቅን ልቡና ያላቸው ሰዎች ግን አግዚአብሔር በሰው እንዳደረ አይናገሩም ፥ ተዋሕዶ አዲስ ሥራ ነውና ፥ ድንቅ ምሥጢርም ነውና። . . .  እኛ ግን እግዚአብሔር ቃልን ከነፍስ ከሥጋ አንለየውም፤ ከዓለም ሁሉ አስቀድሞ የነበረ፦ ቀዳማዊ ወልድ ዋሕድ መዋሓዱን እናምናለን እንጂ፤ በመዋሓዱም ከሥጋው ጋር አልተቀላቀለም፤ እኛን ለማዳን ነፍስ ልቡና ያለው ሥጋን ከእኛ ባሕርይ ነሥቶ ተዋሐደ እንጂ።» ብሏል።(ሃይ፡ አበው ፷፮፥፪ ፣፲፮)።
          ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፦ «ነገር ግን እውነተኛ የእግዚአብሔር ልጅ አንድ እንደሆነ ብንናገር ፥ ወዲህም ከእኛ ባሕርይ የተገኘ ሥጋ ያለመለየት በማይመረመር ተዋሕዶ ከቃል ጋር አንድ መሆኑን እኛ እናውቃለን፤ ሥጋ የመለኮትን ባሕርይ እንዳልለወጠ ፥ መለኮትም እንዲሁ የሥጋን ባሕርይ አልለወጠም፤ እርሱ ወልድ በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነው፤» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፷፯ ፥፴፩)። ቅዱስ አትናቴዎስም፦ «እርሱ ሰው የሆነ አምላክ ነው፤ ስለዚህም መለኮት ሥጋን ወደ መሆን ፥ ሥጋም መለኮትን ወደ መሆን አይለወጥም፤ እርሱ ከመለወጥ ከመለዋወጥ ሁሉ የራቀ ነው፤ ከተዋሕዶ በኋላ ግን ፈጽሞ መለየት የለበትም፤ ሰው የሆነ ቃል፦ አንድ አካል ፥አንድ ባሕርይ መሆኑ እውነተኛ ተዋሕዶው የጸና ነው፤ እግዚአብሔር ያደረባቸው አበው እንዳስተማሩን፤» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፻፮፥፲፫)። ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ደግሞ፦ «አድሮ እንደተናገረባቸው እንደ ነቢያት ሁሉ አይደለም፥ ፍጹም ሰው ሆነ እንጂ። ቃል ሥጋ ሆነ፤ አልተለወጠም ፤ መለኮቱን ሰው ወደ መሆን አልለወጠውም ፤ ከመለኮት ጋር ጽኑዕ አንድነቱን በተዋሕዶ አደረገ እንጂ።» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፶፯ ፥፳፰)።
 
ቃል ሥጋ የሆነው በተዋሕዶ ነው፤

Source: http://www.facebook.com/groups/180759695294706/doc/183920384978637/

No comments:

Post a Comment