13

.

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው::" የማቴዎስ ወንጌል 7: 4

"እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅናወተት ግዙ።" ትንቢተ ኢሳይያስ 55 : 1

Thursday, September 15, 2011

የቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያዊ ሥራ

የመጀመሪያው የቅዱስ ጳውሎስ ጉዞ

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ ከተመለሰ በኋላ በልዑል እግዚአብሔር ጥሪ (የሐዋ. 13.1-3) በአሕዛብ ሀገር ወንጌልን ለመስበክ ከበርናባስ ጋር ወጡ፡፡ በዚህ ጉዞቸው በጠቅላላ ወደ 2000 ኪ.ሜ የሚደርስ መንገድ በእግር ተጉዟል፡፡ ይህም ጉዞ የተከናወነው በ46 ዓ.ም አካባቢ ነው፡፡ የተሸፈኑትም ሀገሮች ሲሊንውቂያ፣ ቆጵሮስ፣ ስልማና፣ ጳፋ፣ ጰርጌን፣ ገላትያ፣ ጵስድያ፣ ኢቆንዮን፣ ሊቃኦንያ፣ ልስጥራ፣ ደርቤን፣ ጵንፍልያ፣ አታልያ እና አንጾኪያ ናቸው፡፡




ሁለተኛ የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስ ጉዞ
ቅዱስ ጳውሎስ እና ማርቆስ 
ሁለተኛው ጉዞ የተከናወው በ50 ዓ.ም ገደማ ነው፡፡ በመጀመሪያው ጉዞ ማርቆስ አብሮ ተጉዞ ነበር፡፡ ነገር ግን ጵንፍልያ ከተማ ሲደርስ እናቱ ስለናፈቀችው መመለስ በመፈለጉ በርናባስ ወደ ኢየሩሳሌም ይዞት መጣ፡፡ ስለዚህም በሁለተኛው ጉዞው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲላስን ይዞ ወደ ኪልቋያ ሶርያ ሲጓዝ በርናባስ ደግሞ ማርቆስን አስከትሎ ወደ ቆጵሮስ ሄደ፡፡ በዚህ ጉዞው ቅዱስ ጳውሎስ እስከ ግሪክ ደርሶአል፡፡ የተጓዘባቸውና ያስተማረባቸው ከተሞችም፡- ደርብያ፣ ልስጥራ፣ ፍርግያ፣ ገላትያ፣ ሚስያ፣ ጢሮአዳ፣ ሳሞትራቄ፣ ናፒሊ፣ ፊልጵስዩስ፣ ተሰሎንቄ፣ በርያ፣ አቴና፣ ቆሮን፣ ቶስ፣ አንክራኦስ፣ ኤፌሶን፣ ቂሳርያ፣ ኢየሩሳሌም እና አንጾኪያ ናቸው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመንፈስ ልጁ ጢሞቴዎስን ያገኘው በዚሁ ጉዞው በልስጥራ ከተማ ነው፡
 ሦስተኛው የቅዱስ ጳውሎስ ጉዞ
     ይህ ጉዞ የተከናወነው በ54 ዓ.ም ሲሆን የተሸፈኑትም ሀገሮች የሚከተሉት ናቸው፡፡
ገላትያ፣ ፍርግያ፣ ኤፌሶን፣ መቄዶንያ፣ ፊልጵስዩስ፣ ቆሮንቶስ፣ ጢሮአዳ፣ አሶን፣ ሚሊጢኒን፣ አንጠቀከስዩ፣ ትሮጊሊዩም፣ መስጡ፣ ቆስ፣ ሩድ፣ ጳጥራ፣ ጢሮስ፣ ጵቶልማይስ፣ ቂሳርያ፣ ኢየሩሳሌም፡፡

ክርስቲያኖች የሰበሰበውን ዕርዳታ ለኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያኖች በመያዝ ሦስተኛውን ጉዞ አጠናቅቆ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡ ነገር ግን ኢየሩሳሌም የገባበት ጊዜ የፋሲካ በዓል ስለነበር ከልዩ ልዩ ሀገሮች የተሰበሰቡ አይሁድ በከተማዋ ነበሩ፡፡ እነዚህ በዝርወት የሚኖሩ አይሁድ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን በየሀገራቸው በትምህርቱ የተነሣ ሲቃወሙት የነበሩ ናቸው፡፡

እኒህ አይሁድ ቅዱስ ጳውሎስን በኢየሩሳሌም ሲያዩት ታላቅ ተቃውሞ አነሡበት፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ተቃውሞአቸውን ለመግታት እንደ አይሁድ ሕግ በቤተ መቅደስ የመንጻት ሥርዓት መፈጸም ጀመረ፡፡ ነገር ግን ከኤፌሶን የተከተለውን ጥሮፊሞስን ወደ መቅደስ ያስገባው ስለመሰላቸው ተቃውሞአቸው በረታ፡፡ የሐዋ. 22.29፡፡ ከተማውንም አወኩት፤ ይህ ነበር ቅዱስ ጳውሎስን በ58 ዓ.ም ለሮም እሥር የዳረገው፡፡
 ከብዙ መከራና ስቃይ በኋላ ታሥሮ ሮም ገባ፡፡ በዚያም በቁም እሥር ሆኖ ለሁለት ዓመታት ያህል ወንጌል ሰበከ፡፡ የሁለቱን ዓመት የቁም እሥር እንደጨረሰ ወደ ኔሮን ፍርድ ቤት ቀረበ፡፡ ይህም በ60ዎቹ ዓ.ም ነው፡፡ በፍርድ ቤቱ በተደረገው ምርመራ የሮሜን ሕግ የሚቃወም ምንም ወንጀል ስላልተገኘበት በነፃ ተለቀቀ ::

የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስ ጉዞዎች


አራተኛው የቅዱስ ጳውሎስ ጉዞ
ከዚህ በኋላ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አራተኛውንና የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ያልመዘገበውን ጉዞውን ያደረገው፡፡ ይህ ጉዞው በመታሠሩ አዝነው ተክዘው የነበሩ ክርስቲያኖችን ለማጽናናት የጀመራቸውን ሥራዎች ፍጻሜ ለማየት የተደረገ ጉዞ ነው፡፡ በዚህም ጉዞው ኢየሩሳሌምን፣ ኤፌሶንን፣ ሎዶቅያን፣ መቄዶንያን፣ ቀርጤስን፣ ጢሮአዳን፣ ድልማጥያን፣ እልዋሪቆን፣ ኒቆጵልዮን፣ ብረንዲስን፣ ጐብኝቷል፡፡ በዚህ የመጨረሻ የስብከት ጉዞው ለአራት ዓመታት ያህል ቆይቷል፡፡
ሰማዕትነት
በመጨረሻ በ64 ዓ.ም ኔሮን በጥጋቡ የሮማ ከተማ ስትቃጠል ምን እንደምትመስል ማየት እፈልጋለሁ ብሎ አቃጠላት፡፡ የሮም ሕዝብ በከተማው መቃጠል በማዘኑና በማመፁ ነገሩን ሁሉ በክርስቲያኖች ላይ አሳበበ፡፡ በዚህም የተነሣ ክርስቲያን የተባለ ሁሉ መሰደድ፣ መሠየፍ፣ መታረድ፣ ዕጣ ፈንታው ሆነ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በኒቆጵልዮን ከተማ ሲያስተምር በ65 ዓ.ም ተይዞ ወደ ወኅኒ ገባ፡፡ ለሁለት ዓመት ከስድስት ወር በጨለማ ቤት ታሥሮ ከቆየ በኋላ በ74 ዓመት ዕድሜው በሮማ ከተማ በኦስትያ መንገድ አንገቱን ተሠይፎ በ67 ዓ.ም ሐምሌ አምስት ቀን በሰማዕትነት ዐረፈ፡፡

በአጠቃላይ 
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ :-


ዕውቀትን ከትህትና ደርቦ የያዘ ነበር፡- ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በኢየሩሳሌም በሚገኘው በታላቁ የአይሁድ ትምህርት ቤት በሊቁ በገማልያል እግር ሥር ብሉይ ኪዳንን የተማረ ነበር፡፡ በኋላም ትምህርተ ክርስትናን ከሐዋርያት አግኝቷል፡፡ ይህን ሁሉ ዕውቀት ይዞ ሁል ጊዜ ኑሮው የትህትና ነበር፡፡ እኔ ጭንጋፍ ነኝ እስከማለትም ደርሶ ነበር፡፡ (1ቆሮ. 15.8)

ትጉህና ታታሪ ነበረ፡- ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስለ42 ዓመታት ያህል በሐዋርያነት አገልግሎአል፡፡ እስከ እስጳኝ ድረስ ሄዶም አስተምሯል፡፡ በባሕር እና በእግር፣ ተመላልሷል፡፡ በ12ቱም ሐዋርያት ሀገረ ስብከት እየገባ ወንድሞቹን አግዞአቸዋል፡፡

ትዕሥተኛ ነበረ፡- ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በላከው ቀዳማዊ መልእክቱ እንደገለጠው (11.25-33) ብዙ ፈተናዎችን አልፏል፡፡ ሁለት ጊዜ ታሥሯል ተደብድቧል፣ በረሃብ ተገርፏል ይህ ሁሉ ቢሆንም በኑሮው ደስተኛ ነበር፡፡ በሮሜ ታሥሮ እያለ ለፊልጵስዩስ ሰዎች መልእክት ስጽፍ በደስታ የተሞላ ነበረ፡፡ በመጀመሪያ ጉዞው ያልተቀበሉትን ከተሞች በሁለተኛው አልያም በሦስተኛ ጉዞው ጎብኛቸው እንጂ እምቢ አሉኝ ብሎ ተስፋ አልቆረጠም፡፡

ጥበበኛ ነበረ፡- ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን የቤተ ክርስቲያን አበው (መዶሻ) ይሉታል፡፡ መዶሻ ማዕድናቱን ቀጥቅጦ አንደ ያደርጋቸዋል፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በትምህርቱ ሕዝብንና አሕዛብን አንድ ያደረገ ሐዋርያ ነው፡፡ በ50 ዓ.ም አካባቢ ወደ ኢየሩሳሌም ሲወጣ ቲቶንና በርናባስን አስከትሎ ነበር፡፡ ቲቶን ከአሕዛብ ወገን በርናባስን ደግሞ ከአይሁድ፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ሰውን እንዴት መቅረብ እንደሚቻል የሚያውቅ ሰው ነበረ፡- ከተራ ሰዎች እስከ ነገሥታት ቤተሰቦች በፍቅር እየሳበ ክርስቲያን አድርጓቸዋል፡፡ በመልእክቱ መጨረሻ የቤተክርስቲያን ልጆች በስማቸው እየጠራ ሰላምታ ማቅረብ የዘወትር ልማዱ ነበረ፡፡ ይህም ሁሉም በልቡ እንደታተሙ ያውቁ ዘንድ ነው፡፡

ጸሐፊ ነበር፡- ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በቃል ያለ ይረሳል በጽሑፍ ያለ ይወረሳል ነውና ያስተማራቸውን ክርስቲያኖች እንዲሁ አይተዋቸውም፡፡ ለሃይማኖታቸው ማጽኛ ለመንፈሳዊ ሕይወታቸው መመሪያ የሚሆኑ መልእክታትን ጽፎላቸዋል፡፡ አብዛኛዎቹ መልእክታት በእሥር ቤት ውስጥ ነው፡፡ ለመጓዝ የሚያስችለው አመቺ ጊዜ ሲያገኝ በአካል፣ በቃል፣ ያስተምራቸዋል፡፡ ሲታሠር መንቀሳቀስ ሲከለከል ደግሞ ጣቶቹ ብዕር ይጨብጣሉ፡፡ መልእክቶቹ በየሀገረ ስብከቱ ይላካሉ፡፡

ሥራ ወዳድ ነበር፡- ቅዱስ ጳውሎስ ሌት ተቀን ለስብከተ ወንጌል ቢባክንም ለምእመናን እንዳይከብድባቸው ድንኳን እየሰፋ የዕለት ጉርሱን የዓመት ልብሱን ያገኝ ነበር፡፡ የሐዋ. 18.3፣4 ለዚህም ነው ‹ሊሠራ የማይወድ ቢኖር አይብላ› እያለ ያስተምር የነበረው፡፡ 2ተሰ.3.10፡፡

የምሥራቅ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት ከመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ሲተላለፍ የኖረውን ትውፊት በማሰባሰብ ስለ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ተክለ ሰውነት እንዲህ ይላሉ፡፡
ጭንቅላቱ ትልቅ ሲሆን ራሰ በራ ነበር፡፡ የሁለቱም ቅንድቦቹ ጠጉር የተጋጠው፣ ዓይኖቹ ሰማያዊ ቀለም ያላቸው ሲሆኑ ዘወትር ብሩሃን ነበሩ፡፡ አፍንጫው ትልቅና ቀጥ ብሎ የወረደ ጽሕሙና ሪዙም ረጃጅም ናቸው፡፡ አንገቱ አጠር ያለ ሆኖ ትከሻው ክብና ጐባባ እግሮቹ ደግሞ ከጉልበቱ ላይ የተቃረቡ ናቸው፡፡ ቁመቱ አጠር ያለ ደንዳና ሰው (ከድንክ የረዘመ) እንደነበር ይነገርለታል፡፡


ዋቢ፡-
·        መጽሐፍ ቅዱስ
·        ዜና ሐዋርያት
·        ቤተክርስቲያንህን ዕወቅ
·         ትንሳኤ መጽሔት

No comments:

Post a Comment