13

.

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው::" የማቴዎስ ወንጌል 7: 4

"እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅናወተት ግዙ።" ትንቢተ ኢሳይያስ 55 : 1

Wednesday, September 14, 2011

ንሰሐ ግቡ ከኃጢአታችሁም ተመለሱ… ሕዝ. 14፡6



         ንስሐ ምንድን ነው?
      ንስሐ ነሰሐ ከሚል የግዕዝ ግስ የወጣ ቃል ነው፡፡ የቃሉ ፍቺ ሐዘን፣ ጸጸት፣ ቁጭት፣ ምላሽ፣ መቀጮ፣ ቅጣት፣ ቀኖና፣ የኃጢአት ካሳ ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ መልኩ ንስሐ  በሰዎች ሕይወት ውስጥ ደግሞ የሚከተሉትን ፍችዎች ይዞ እናገኘዋለን፡፡
ሀ. ንስሐ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው
      ከእግዚአብሔር መለየት ኃጢአት ነውና ንስሐ የሚገባ ሰው ከሠራው ኃጢአት በሙሉ ልቡ ይመለሳል፡፡ የበደለውን ፈጣሪውን ስለበደሉ ይቅርታ ይጠይቃል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በነቢያት አድሮ ሕዝቡ ከኃጢአት ንስሐ እንዲገቡ እና ወደ እርሱ እንዲመለሱ ተናግሯል፡፡ ‹‹ከአባቶቻችሁ ዘመን ጀምሮ ከሥርዓቴ ፈቀቅ ብላችኋል እርሷንም አልጠበቃችሁም ወደ እኔ ተመለሱ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ›› ሚል. 3፥7 በማለት ጥሪውን አስተላልፏል፡፡ በመጽሐፈ ምሳሌም ‹‹ኃጢአቱን የሚሰውር አይለማም የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል›› በማለት ተጽፈዋል፡፡ ምሳ. 28፥13 በሉቃስ ወንጌል ላይ የምናገኘው አባካኙ ልጅ ኃጢአቱ በመረረውና በጸጸተው ጊዜ ወደ ልቡ ሲመለስ ወደ አባቱ ለመምጣት ወሰነ አባቱም በሐሴት ተቀበለው ሊቃ.15፥18 እውነተኛ ንስሐም ሰዎች በበደልና ኃጢአት ምክንያት ወደ አጡት ሥፍራ ለመመለስ የሚኖራቸው ናፍቆትና የሚወስኑት ውሳኔ ነው፡፡
ለ. ንስሐ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ነው፡፡
      ኃጢአት ከእግዚአብሔር ጋር መጣላት ነውና ስለዚህ ነገር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማለድ ስለ ክርስቶስ መልእክተኞች ነን ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን እንለምናችኋለን›› 2ቆሮ. 5፥20 በማለት ተናግሯል፡፡ ንስሐ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ብቻም ሳይሆን የእግዚአብሔር በሰዎች ልቦና ውስጥ ማደርም ነው፡፡ ሰው ኃጢአትን ከእርሱ ካላስወገደ የእግዚአብሔር ማደሪያ መሆን ስለማይቻል ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ማለት የእግዚአብሔር ማደሪያ ለመሆን መዘጋጀት ማለት ነው 2ቆሮ. 6፥19
ሐ. ንስሐ የአእምሮ መታደስ ነው፡፡
      ኃጢአት የአእምሮ መበላሸት ነውና ኃጢአትን የሚያመላልስ አእምሮ የተበላሸ ነው፡፡  በኃጢአት እድፍ ንጽሕናውን ያጣው አእምሮ የሚታደሰው ኃጢአትን ማመላለስ የተወ እንደሆነ ነው፡፡ ይህም በንስሐ ነው፡፡ ይህን ሲገልጥ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹በልባችሁ መታደስ ተለወጡ›› ሮሜ. 12፥2 በማለት ተናግሯል፡፡
            አንዴት ንስሐ ይገባል?
     1.  ከራስ ጋር መሆን፡- ንስሐ መግባት የራስን ፈቃድ ይጠይቃል ሰው ንስሐ ለመግባት ፈቃዱ፤፤ የራሱ ነው የእግዚአብሔር ፍቃድ ሰው ንስሐ እንዲገባ ነው፡፡ ስለዚህ ነው ‹‹እግዚአብሔር ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደማወቅ ሊደርሱ ይወዳል›› በማለት ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረው፡፡ 1ጢሞ. 2፥4
ከራሳችን ጋር የሆንን እንደሆነ ድካማችንንና ኃጢአታችንን ለእግዚአብሔር መናገር አይከብደንም መዝ. 50፥1-17 ለእግዚአብሔር የነገርነውን ኃጢአት ለመምህረ ንሰሐችን መናገር አያሳፍርም ይህም ጸሎተ ንስሐ ከተደረገልን በኋላ ስጋውን ደሙን ለመቀበል የተዘጋጀን ያደርገናል፡፡
2. ምክንያትንና ለራስ ይቅርታ ማድረግን ማስወገድ
በንስሐ ሕይወት ለመኖር የምንሻ ከሆነ ለወደቅንበት ኃጢአት ምክንያት መደርደርና ለራሳችን ይቅርታን ለመስጠት መሞከር የለብንም፡፡ በዚህ አይነት ለኃጢአቱ ምክንያት እየደረደረ የሚጽናና ሰው ኃጢአትን እየለመደ ወደ ባሰ አዘቅት ከመውደቅ በቀር ንስሐ ለመግባት አይችልም ምንም ምክንያት ቢደረድር ኃጢአት ምንም ጊዜ ኃጢአት ነውና ለሰራነው ኃጢአት የተለያዩ ምክንያቶችን ለማበጀት ራሳችንን እያጽናናን ነጻ ለመሆን መጣር የለብንም አዳምና ሔዋን ባቀረቡት ምክንያት ከቅጣት አልዳኑም፡፡ አዳም ስላቀረበው ምክንያት ‹‹የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና ከእርሱ እንዳትበላ ካልኩህ ዛፍ በልተሃልና . . . ›› በማለት ለኃጢአቱ የሚገባውን ቅጣት ሰጠው እንጂ አልተወውም ዘፍ. 3፥17 ጌታው እንዲያተርፍበት አንድ መክሊት የሰጠው ሰው ጌታው በመጣና በጠየቀው ጊዜ ላለመነገዱና ላለማትረፉ ምክንያት ከመስጠት ወደ ኋላ አላለም፡፡ ይሁን እንጂ ጌታው ያቀረበውን ምክንያት አልተቀበለውም ወደ እሳት እንዲጣል አዘዘ እንጂ ማቴ. 25፥24
በእግዚአብሔር ዘንድ ለኃጢአት ምክንያት መደርደር መልካም አይደለም፡፡ ከዚህም ይልቅ በደልን ማመንና በኃጢአት ላይ መናዘዝ እግዚአብሔርን ያስደስተዋል ስርየትም ያስገኛል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ከመ/ር ዳኛቸው ግርማ ዘኆኅተብርሃን

No comments:

Post a Comment