13

.

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው::" የማቴዎስ ወንጌል 7: 4

"እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅናወተት ግዙ።" ትንቢተ ኢሳይያስ 55 : 1

Thursday, September 15, 2011

«ከዚህም በላይ የምታወጣውን ሁሉ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ፤»



          ዲናር፦ የሮሜ መንግሥት የብር ምንዛሪ ሆኖ ያገለገለ ከሁሉ ያነሰ የናስ ሳንቲም ነው መጠኑም አሥራ ስድስት ሳንቲሞች ነበር። በዚያን ዘመን የአንድ ቀን የሠራተኛ ደሞዝ ሆኖ ይከፈል ነበር። ማቴ ፳፥፪። ጌታችንን በንግግር ሊያጠምዱት ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ ወገን የሆኑ ሰዎች ወደ እርሱ ተልከው መጥተው «ለቄሣር ግብር መስጠት ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም? እንስጥን፥ ወይስ አንስጥበማለት ጠይቀውት ነበር። እርሱ ግን ግብዝነታቸውን እና ተንኰላቸውን አውቆ፦ «ለምን ትፈትኑኛላችሁ? አንድ ዲናር አምጥታችሁ አሳዩኝ፤» አላቸው። ባመጡለትም ጊዜ፦ «ይህ፦ መልኩ ጽሕፈቱስ የማን ነው? » አላቸው፤ እነርሱም፦ «የቄሣር ነው፤» አሉት። እርሱም መልሶ፦ «የቄሣርን ለቄሣር ስጡ፤ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አድርጉ፤» አላቸው። ምክንያቱም፦ የንጉሥ የሆነ እንደሆነ፦ ስመ ንጉሥ ይጻፍበታል ሥእለ አንበሳ ይቀረጽበታል፤ የእግዚአብሔር ሲሆን ደግሞ፦ ስመ አምላክ ይጻፍበታል፥ ሥዕለ ኪሩብ ይቀረጽበታል።
፩፥፩፦ «የዘለዓለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ?»
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርቱን ለብቻቸው አድርጎ «እናንተ የምታዩትን የሚያዩ ዓይኖች ብፁዓን ናቸው። ብዙ ነቢያትና ነገሥታት እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ተመኙ አላዩምም፤ እናንተ የምተሰሙትንም ሊሰሙ ተመኙ አልሰሙም።» ካላቸው በኋላ እንደ ሕግ አዋቂ (ሕገ ኦሪትን ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው) ወደ እርሱ መጣ። ሊፈትነውም፦ «መምህር ሆይ የዘለዓለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ? (የማታልፍ ርስት መንግሥተ ሰማያትን የምወርሰው ምን ሠርቼ ነው?) አለው። ጌታችንም፦ «በሕግ የተጻፈው ምንድርነው? እንዴትስ ታነባለህበማለት ጥያቄውን በጥያቄ መልሶለታል። ሕግ አዋቂውም ከኦሪት ዘዳግም ጠቅሶ፦ «እስራኤል ሆይ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው፤ አንተም አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ (አሳብህ) በፍጹም ነፍስህ (ሰውነትህ) በፍጹምም ኃይልህ ውደድ። ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ፤» ይላል ሲል መለሰለት። ዘዳ ፮፥፭። በዚህን ጊዜ ጌታችን፦ «እውነት መለስህ፤ ይህን አድርግ፥ በሕይወትም ትኖራለህ፤» በማለት አዘዘው።
          ይህ ሰው የዕውቀት ባዕለጸጋ የተግባር ደሀ ነው፤ እንዲሁ በዕውቀቱ እየተመጻደቀ የሚኖር ሰው ነው፤ አመጣጡም ውዳሴ ከንቱን ሽቶ እንጂ ሕይወትን ፈልጎ አይደለም። ጌታ ሊቅነቴን ይመሰክርልኛል ብሎ ነው፤ በዚህም እርሱን በተከተለው አምስት ገበያ ሕዝብ ፊት ሞገስን ለማግኘት ነው። ዛሬም አገልግሎታቸው ሁሉ ሊቅ ለመባል ብቻ የሆነባቸው ሰዎች አሉ፤ እነዚህም መንፈሳዊ ዕውቀት እንጂ መንፈሳዊ ሕይወት ፈጽሞ የማይገኝባቸው ናቸው፤ ከዚህም የተነሣ ገንዘብ አድርገው የሚኖሩት፦ሰውን መናቅና እግዚአብሔርን መድፈር ነው። አንደበታቸው ስለ ሕይወት ይናገራል ይተረጉማል ያዜማል፥ ይቀኛል ልባቸው ግን በትዕቢት፣ በግብዝነት የተያዘ ፍጹም ሥጋዊ ነው። ይኽንን በተመለከተ፦ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ «አንተ ግን አይሁዳዊ ብትባል ፥በሕግም ብትደገፍ በእግዚአብሔርም ብትመካ ፈቃዱንም ብታውቅ ከሕግም ተምረህ የሚሻለውን ፈትነህ ብትወድ በሕግም የዕውቀትና የእውነት መልክ ስላለህ የዕውሮች መሪ በጨለማም ላሉ ብርሃን የሰነፎችም አስተማሪ የሕፃናትም መምህር እንደሆንህ በራስህ ብትታመን እንግዲህ አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርምን? አትስረቅ ብለህ የምትሰብክ ትሰርቃለህን? አታመንዝር የምትል ታመነዝራለህን? ጣዖትን የምትጸየፍ ቤተ መቅደስን ትዘርፋለህን? በሕግ የምትመካ ሕግን በመተላለፍ እግዚአብሔርን ታሳፍራለህን? በእናንተ ሰበብ የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባልና ተብሎ እንደ ተጻፈ።» ብሏል። ሮሜ ፪፥፲፯-፳፬።
፩፥፪፦ «ባልንጀራዬ ማነው?
          መንፈሳዊም ሆነ ሥጋዊ ዕውቀት በትህትና የሚያገለግሉበት እንጂ የሚመኩበት የሚመጻደቁበት አይደለም። እነ አርዮስ እነ ንስጥሮስ በመንፈሳዊ ዕውቀታቸው ሲፈላሰፉ ሲመጻደቁ ጠፉበት እንጂ አልዳኑበትም። ሥጋዊውም የዕውቀት ሰው ከተራ ጠመንጃ እስከ ኒዩክለር ድረስ የሠራው የፈለሰፈው ረቂቅ መሣሪያ መጥፊያው እንጂ መዳኛው አይደለም። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ ተብሎ ተጽፎአልና። ጥበበኛ የት አለ? ጻፊስ የት አለ? የዚች ዓለም መርማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚህችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገምን? በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአልና።» ያለው ለዚህ ነው። ፩ኛ ቆሮ ፩፥፲፱-፳፩። 
          የሕገ ኦሪቱ ሊቅ፦ ምን ማድረግ እንዳለበት መጽድቂያውን ጌታችን በነገረው ጊዜ፦ እርሱ ግን ራሱን ሊያጸድቅ ወድዶ፦ «ባልንጀራዬ ማን ነውአለ። «የሚመስለኝ የሚተካከለኝ ማነውማለቱ ነው። ራሱን ከጉልላቱ ላይ ያስቀመጠ ሰው በመሆኑ የትዕቢት ንግግር ነው። ትዕቢት ደግሞ ዲያቢሎስ የተያዘበት አሸክላ ነው ኢሳ ፲፬፥፲፪። ቅዱስ ያዕቆብ እንደተናገረው፦ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ያዕ ፬፥፮። ጠቢቡ ሰሎሞንም፦ «ሰውን ትዕቢቱ ያዋርደዋል፤» ብሏል። ምሳ ፳፱፥፳፫።
፩፥፫፦ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ፤
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ በሊቅነቱ ብቻ ተመክቶና ተመጻድቆ፦ «ባልንጀራዬ ማነውያለውን ሰው ያስተማረው በምሳሌ ነው። ምሳሌውም፦ «አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ይወርድ ነበር፤ ሽፍቶችም አገኙት፤ ደበደቡት አቈሰሉት ፥ልብሱንም ገፍፈው በሕይወትና በሞት መካከል ጥለውት ሄዱ። አንድ ካህንም በዚያች መንገድ ሲወርድ ድንገት አገኘው፤ አይቶም አልፎት ሄደ። እንዲሁም አንድ ሌዋዊ በዚያ ቦታ አገኘውና አይቶ እንደፊተኛው አልፎት ሄደ። አንድ ሳምራዊ ግን በዚያች መንገድ ሲሄድ አገኘው፤ አይቶም አዘነለት። ወደ እርሱም ቀረበ፤ ቊስሉንም አጋጥሞ አሰረለት፤ በቊስሉ ላይም ወይንና ዘይት ጨመረለት፤ በአህያውም ላይ አስቀምጦ እንዲፈውሰው የእንግዶችን ቤት ወደ ሚጠብቀው ወሰደው፤ የሚድንበትንም ዐሰበ፤ በማግስቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለእንግዳ ቤት ጠባቂው ሰጠውና፦ በዚህ አስታምልኝ፤ ከዚህ የሚበልጥ ለእርሱ የምታወጣው ቢኖር እኔ በተመለስሁ ጊዜ እከፍልሃለሁ፥ አለው። እንግዲህ ሽፍቶች ለደበደቡት ሰው ከእነዚህ ከሦስቱ ባልንጀራ የሚሆነው ማንኛው ይመስልሃል? ሲል ጠየቀው እርሱም፦ ምሕረት ያደረገለት ነዋ አለው፤ ጌታችን ኢየሱስም፦ እንኪያስ አንተም ሂድና እንዲሁ አድርግ አለው።»የሚል ነው። ሉቃ ፲፩፥፳፱-፴፯።
          ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ መውረድ ማለት፦ ከፍ ካለ ሥፍራ ወደ ዝቅተኛው ሥፍራ መውረድ ማለት ነው። ትርጉሙም፦ ከብሮ መዋረድን ፥ተሹሞ መሻርን ፥አግኝቶ ማጣትን ያመለክታል። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፦ «ገዢዎችን ከዙፋናቸው አዋርዷል፤ . . .  ባለጠጎችንም ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል፤» ያላችው እንዲህ ዓይነቱን ነው። ሉቃ ፩፥፶፪ መዝ ፻፵፮፥፮።
፩፥፬፦ ኢያሪኮ፤
          ኢያሪኮ፦ ከጨው ባሕር በስተሰሜን አሥራ አምስት .. ከኢየሩሳሌም ደግሞ ሃያ አምስት ኪሜ ርቆ የሚገኝ ከተማ ነው። ኢያሪኮ ማለት፦ የጨረቃ ከተማ ማለት ነው፥ ይኸውም በኢያሪኮ የኖሩ የጥንት ሰዎች ጨረቃን ስላመለኩ ነው። በኢያሪኮ ዙሪያ ብዙ የውኃ ምንጮች ስላሉ ከጥንት ጀምሮ ሰዎች በዚያ መኖር ጀምረዋል። ዘዳ ፴፬፥፫። የፊተኛዋን ከተማ በታቦቱ ላይ በተገለጠ ኃይለ እግዚአብሔር ኢያሱ ወልደ  ነዌ አፍርሶታል። ኢያ ፮፥፩። አኪኤል የተባለው የቤቴል ሰው ደግሞ እንደገና ሠርቶታል። ፩ኛ ነገ ፲፮፥፴፬። በኢያሪኮ ብዙ የኦሪት ካህናት ነበሩ፤ ሉቃ ፲፥፴፩። በአዲስ ኪዳን ጌታችን የበርጤሜዎስን ዓይን ያበራው በኢያሪኮ ነው፤ ማር ፲፥፵፮። ዘኬዎስንም የጎበኘው በዚሁ ከተማ ነው። ሉቃ ፲፱፥፩። ይህንን ከተማ ሮማውያን 67 .. አፍርሰውታል። ኢያሪኮ ሁለት መቶ ሃምሣ ሜትር ከባሕሩ ጠለል ዝቅ ስለሚል ከዓለም ከተሞች ሁሉ ዝቅተኛ ነው።
፩፥፭፦ ኢየሩሳሌም
          ኢየሩሳሌም፦ ማለት፦ የሰላም ከተማ ማለት ነው፤ የዮርዳኖስ ወንዝ ወደ ጨው ባሕር ከሚገባበት በምዕራብ ሠላሳ .. ከታላቁ ባሕር ደግሞ ሃምሣ .. ርቃ በተራራማ ሀገር የምትገኝ ከተማ ናት። ከባሕር ወለልም ሰባት መቶ ሃምሣ ሜትር ገደማ ከፍ ትላለች። ጥንታዊ ስሟ ሳሌም ነበር፥ ቀጥሎም፦ ኢያቡስ ፆፌል ጽዮን ተብላለች፤ ዘፍ ፲፬፥፲፰ ኢያ ፲፭፥፷፫ ፲፰፥፲፮፤ ፪ኛ ዜና ፳፯፥፫፤ ፴፫፥፲፬፤ መዝ ፻፴፮፥፩። ቅድስት ከተማ ተብላም ተጠርታለች፤ ነህ ፲፩፥፩። ንጉሥ ዳዊት ኢየሩሳሌምን ከኢያቡሳውያን ከወሰዳት በኋላ የእስራኤል ሁሉ በተለይም የይሁዳ ዋና ከተማና መስገጃ አደረጋት ፪ኛ ሳሙ ፭፥፮-፲።
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ «ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ፤ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮአል። ወራት ይመጣብሻልና ጠላቶችሽም ቅጥር ይቀጥሩብሻል ይከቡሻልም በየበኲሉም ያስጨንቁሻል፤ አንቺንም በአንቺም ውስጥ የሚኖሩትን ልጆችሽኝ ወደ ታች ይጥላሉ በአንቺ ውስጥም ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉም የመጐብኘትሽን ዘመን አላወቅሽምና።» እያለ አልቅሶላታል። ሉቃ ፲፱፥፵፮። የዓለምን መጨረሻ ምልክቶች በተናገረበት አንቀጽም፦ «ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ።» በማለት ተናግሯል። ሉቃ ፳፩፥፳። ሥጋውን በመቁረስ፥ ደሙን በማፍሰስ፥ ነፍሱንም አሳልፎ በመስጠት ድኅነተ ዓለምን የፈጸመው በዚያ ነው። ይኽንንም ነቢዩ ዳዊት፦ «እግዚአብሔር ግን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፥ በምድርም መካከል መድኃኒትን አደረገ።» በማለት ተናግሯል። መዝ ፸፫፥፲፪። ነቢዩ ዳዊት ማዕከለ ምድር ያለው ኢየሩሳሌምን ነው። «ኢየሩሳሌም ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ። ባላስብሽ፥ ምላሴ በጉሮሮዬ ይጣበቅ፤ ከደስታዬ ሁሉ በላይ ኢየሩሳሌምን ባልወድድ።» ያለበት ጊዜም አለ። መዝ ፻፴፮፥፭።
          ኢየሩሳሌም፦ ሕገ ኦሪትም ሕገ ወንጌልም የሚሠራባት ድኅነተ ምእመናንም የሚፈጸምባት በመሆኗ ነቢያት ሁሉ ትንቢት የተናገሩት ለርሷ በርሷ ነው። ቅዱሳን ሐዋርያትም የሰበኩት ለርሷ በርሷ ነው። ኢየሩሳሌም የትንቢት መድረሻ፥የድኅነት መፈጸሚያና የስብከት መነሻ ከመሆኗም በላይ ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያምና ለገነት ለመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ናት።
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ በወንጌል፦ ኢየሩሳሌምን፦ «የታላቁ ንጉሥ ከተማ ብሏታል።» ማቴ ፭፥፴፭። ይኸውም፥ ለጊዜው፦ ምድሪቱን ሲሆን ለፍጻሜው እመቤታችንን አንድም ገነት መንግሥተ ሰማያትን ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ግን በነፃነት የምትኖር ናት እርስዋም እናታችን ናት።» ብሏል። ገላ ፭፥፳፭። በዕብራውያን መልእክቱም ላይ፦ «ነገር ግን ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም በደስታም ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት በሰማያትም ወደተጻፉ ወደ በኲራት ማኅበር የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ እግዚአብሔር ፍጹማንም ወደሆኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል፤» ብሏል። ዕብ ፲፪፥፳፪-፳፬። በራእይ ዮሐንስ ላይ ደግሞ፦ «ድል የነሣው በአምላኬ መቅደስ ዓምድ እንዲሆን አደርገዋለሁ ወደፊትም ከዚያ ከቶ አይወጣም፤ የአምላኬ ስምና የአምላኬ ከተማ ስም ማለት ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን አዲሲቱን ኢየሩሳሌምን አዲሱንም ስሜን በእርሱ ላይ እጽፋለሁ፤» የሚል አለ። ራእ ፫፥፲፪። በተጨማሪም፦ «አዲስ ሰማይና አዲስ ምድርንም አየሁ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፥ ባሕርም ወደፊት የለም። ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለባልዋ እንደተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ፤» የሚል ተጽፏል። ራእ ፳፩፥፩-፪።   
፩፥፮፦ በወንበዴዎች እጅ መውደቅ፤
          ከፍ ብላ ከምትገኘው ከኢየሩሳሌም በጣም ዝቅተኛ ወደሆነው ሥፍራ ወደ ኢያሪኮ የወረደው ሰው የአዳም ምሳሌ ነው። ይኸውም ከልዕልና ወደ ትህትና መውረዱን፥ ከመታዘዝ ወደ አለመታዘዝ መጓዙን የሚያመለክት ነው። ወንበዴ የተባለው ደግሞ፦ ከማዕረጉ የተዋረደ ከሥልጣኑ የተሻረ ዲያቢሎስ ነው። የቀደመ ሰው አዳም፦ የነቢይነት የንጉሥነት የካህንነት የጸጋ አምላክነት(ገዢነት) መንፈሳዊ ሀብት ተስጥቶት በክብር ፣በልዕልና በገነት ይኖር ነበር። በዚህ ዓይነት በፍጹምነት ለሰባት ዓመታት ከኖረ በኋላ ወንበዴዎች የተባሉ አጋንንት አግኝተውት አስተው ልጅነቱን አስወስደውበታል። መርገመ ሥጋ መርገም ነፍስ ወድቆበት በነፍስም በሥጋም እንዲቆስል አድርገውታል። በዚህም በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስ በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ገሃነም ተጨምሮ እንዲፈረድበት ሆኗል። ልብስን እንደመገፈፍ ጸጋውን ሁሉ ተገፍፏል ከማዕረጉ ተዋርዶ፥ ከሥልጣኑ ተሽሮ ከገነት ተባርሮ ወደ ምድረ ፋይድ ተጥሏል።
፩፥፯፦ አንድ ካህን አይቶት ገለል ብሎ አለፈ፤
«መልከ ጼዴቅ፤»
          አንድ ካህን የተባለው መልከጼዲቅ ነው፤ መልከጼዴቅን ለክህነት መርጦ በማይመረመር ግብር የሾመው እግዚአብሔር ነው፤ እነ አሮን በተሾሙበት ሥርዓት፦ ተቀብቶ መሥዋዕት ተሠውቶ የከበረ ልብስ ለብሶ፥ የተሾመ አይደለም። ከሰው ወገን ከእገሌ ተቀብቶ የተሾመ ነው አይባልም፤ ከእርሱም በኋላ ሹመት ለእገሌ ተላልፏል አይባልም።
          የመልከ ጼዴቅ ክህነቱ በኖኅና በሴም ዘንድ ይታወቅ ነበር ይኸውም ምሥጢሩን እግዚአብሔር ስለገለጠላቸው ነው። ሴምም ከወገኖቹ ማንም ሳያውቅ ዓፅመ አዳምን ሊያስጠብቀው መልከ ጼዴቅን ወደ ጎልጎታ ይዞት ሄዷል። መልከ ጼዴቅም በእጁ ደም እንዳይፈስስ ተጠብቆ በንጹሕ ስንዴና ወይን በተዘጋጀ መሥዋዕት እያስታኰተ በብሕትውና በድንግልና ኖሯል። በታዘዘው መሠረት ፀጉሩን ተላጭቶ፥ ጥፍሩንም ተቆርጦ አያውቅም ኑሮውም በዓት አጽንቶ በዋሻ ነበር።
          መልአከ እግዚአብሔር እየረዳውም ከሰው ወገን ለማንም ሳይገለጥ እስከ አብርሃም ዘመን ቆይቷል። አብርሃም፦ አምላክ፦ ከእርሱ ወገን ሰው ሆኖ ከሚወለድበት ዘመን ደርሶ ለማየት ይፈልግ ነበር። እግዚአብሔር ግን «ከዚያ ዘመን አትደርስም ዮርዳኖስን ተሻግረህ ምሳሌዬን ታያለህ፤» ብሎታል። እንደተባለውም፦ ዮርዳኖስን ተሻግሮ መልኬ ጼዴቅን አግኝቶ ከሁሉ አሥራት አውጥቶ ሰጥቶታል መልኬ ጼዴቅ ደግሞ ለሥጋ ወደሙ ምሳሌ የሆነውን ኅብስት በመሶበ ወርቅ ወይንኑም በጽዋ አድርጐ ሰጥቶታል። ዘፍ ፲፬፥፲፯። በዚህም ጌታን እንዳየ ተደርጎ ተቆጥሮለታል። ይኽንንም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል፦ «አባታችሁ አብርሃም የእኔን ቀኔን ያይ ዘንድ ተመኘ፤ አይቶም ደስ አለው።» በማለት መስክሮለታል። ዮሐ ፰፥፶፮። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በዕብራውያን መልእክቱ፦ ለእግዚአብሔር ልጅ ለኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ሆኖ እንደኖረ በዝርዝር ጽፎለታል። ዕብ ፯፥፩-፫።
          እንግዲህ፦ ጌታችን በምሳሌው፦ በወንበዴዎች እጅ የቈሰለውን ሰው፦ «አንድ ካህን አይቶት ገለል ብሎ አለፈ፤» ማለቱ፦ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ሆኖ የኖረው ካህኑ መልከጼዴቅ የሠዋው የስንዴና የወይን መሥዋዕት፦ ለቊስለኛው ለአዳም ምንም እንዳልጠቀመው ለመግለጥ ነው።
፩፥፰፦ አንድ ሌዋዊ አይቶት አለፈ፤
          ሌዊ፦ ከያዕቆብ አሥራ ሁለት ወንዶች ለጆች መካከል ሦስተኛው ነው። ዘፍ ፳፱፥፴፬። እኅቱን ዲናን ከአሕዘብ ወገን አንዱ ከክብር ባሳነሳት ጊዜ የሴኬምን ሰዎች ተበቅሏቸዋል፤ ይኽንንም ያደረገው ከወንድሙ ከስምዖን ጋር ነው። አባታቸው ያዕቆብ ግን፦ «በዚች ሀገር በሚኖሩ በከነዓናውያንና በፌርዛውያን ሰዎች የተጠላሁ ታደርጉኝ ዘንድ እኔን አስጨነቃችሁኝ፤ እኔ በቊጥር ጥቂት ነኝ፤ እነርሱ በእኔ ላይ ይሰበሰቡና ይመቱኛል። እኔም ከወገኔ ጋር እጠፋለሁ።» ብሎ አልተደሰተባቸውም። እነርሱም፦ «በጋለሞታ እንደሚደረግ በእኅታችን ያድርግባትንአሉ። ዘፍ ፴፬፥፩-፴፩።
          ያዕቆብ፦ በግብፅ ምድር በነበሩበት ጊዜ በኋለኛው ዘመን የሚያገኛቸውን ሁሉ ዘርዝሮ ለልጆቹ ነግሯቸዋል። ከዚህም መካከል፦ «ስምዖን እና ሌዊ ወንድማማቾች ናቸው ሰይፎቻቸው የዓመፃ መሣሪያ ናቸው። (ብዙ ደም አፍስሰዋል) በምክራቸው ነፍሴ አትግባ፤ (ሰውነቴ በበረከት አትገናኛቸውም) በቊጣቸው ሰውን ገድለዋልና፥ (ተቈጥተው የሴኬምን ሰዎች አጥፍተዋልና) በገዛ ፈቃዳቸውም የሀገርን ሥር ቈርጠዋልና። (ከአባታቸው አልተማከሩም ፈቃዱን አልጠየቁም) ቊጣቸው ርጉም ይሁን፤ ጽኑ ነበርና፤ ኲርፍታቸውም ብርቱ ነበርና፤ በያዕቆብ እከፋፍላቸዋለሁ፤ በእስራኤልም እበትናቸዋለሁ።» የሚል አለ። ዘፍ ፵፱፥፭-፯።
          ሌዊ ከእስራኤል ነገዶች የአንዱ አባት ነው ሌዋውያን ይባላሉ፤ ዘፍ ፵፮፥፲፩። በሙሴ ዘመን የሌዊ ልጆች የሙሴን ትእዛዝ አክብረው፥ ፍቅረ ጣዖት ያደረባቸውን ሳይራሩ በማጥፋታቸው፦ «ዛሬ በረከትን እንዲያወርድላችሁ ከእናንተ እያንዳንዱ ከልጁና ፥ከወንድሙ የተነሣ እግዚአብሔርን ደስ አሰኛችሁት፤» ተብለዋል። ዘጸ ፪፥፩ ፮፥፲፮-፳፯። ክህነት የተሰጠው ለሌዊ ነገድ በመሆኑ አሮንና ልጆቹ ተቀብተው ተሹመዋል። ዘጸ ፳፰፥፩። ሌዋዊያን በጠቅላላ ለእግዚአብሔር አገልግሎት በመለየታቸውም ሥራቸውና አገልግሎታቸው በኦሪት ዘሌዋውያን ተገልጦአል። ሙሴ፦ ለመጨረሻ ጊዜ ሕዝቡን ሲባርክ ስለ ሌዊ፦ «ለሌዊ ቃሉን በመከራም ለፈተኑት በክርክር ውኃም ለሰደቡት ለእውነተኛው ሰው ጽድቁን መልስ። እናቱንና አባቱን አላየኋችሁም ላለ ወንድሞቹንም ላላወቀ ልጆቹንም ላላስተዋለ፤ ቃልህን ለጠበቀ በቃል ኪዳንህም ለተማጠነ። ፍርድህን ለያዕቆብ ሕግህንም ለእስራኤል ያስተምራሉ፤ በማዕጠንትህ ዕጣንን፥ በመሠዊያህም የሚቃጠል መሥዋዕትን ሁሌጊዜ ያቀርባሉ። አቤቱ ኃይሉን ባርክ፤ የእጁንም ሥራ ተቀበል፤ በሚቃወሙት ጠላቶቹ ላይ መከራን አውርድ፤ የሚጠሉትም አይነሡ፤» ብሏል። ዘዳ ፴፫፥፰-፲፩።
          ሌዋውያን በከነዓን የርስት ድርሻ ሳይሆን አርባ አምስት ከተሞች ተሰጥተዋቸዋል፤ እንደ ርስት ሆኖ የተሰጣቸው የእሥራኤል ልጆች የሚያወጡትን አሥራት ነበር። ይኽንንም ያደረገው እግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔር አሮንን፦ «በምድራቸው ርስት አትወርስም፤ በመካከላቸውም ድርሻ አይሆንልህም፤ በእስራኤል ልጆች መካከል ድርሻህና ርስትህ እኔ ነኝ፤ ለሌዊም ልጆች እነሆ፥ በምስክሩ ድንኳን አገልግሎት ስለሚያገለግሉ የእስራኤልን ልጆች ዐሥራት ርስት አድርጌ ሰጥቻቸዋለሁ።» ብሎታል። ዘኁ ፲፰፥፳-፳፩ ኢያ ፳፩፥፩-፵፭።
          ሌዋውያን ካህናት፦ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት አምስት ዓይነት መሥዋዕቶችን ሲያቀርቡ ኖረዋል። እነርሱም፦ የሚቃጠል መሥዋዕት የእህል ቊርባን የደኅንነት መሥዋዕት የኃጢአት መሥዋዕትና የበደል መሥዋዕት ናቸው። ዘሌዋውያን ከምዕራፍ -፭። በዚህም ምክንያት፦ የአያሌ እንስሳት ደም ፈስሷል። እንግዲህ፦ «አንድ ሌዋዊ ወንበዴዎች ያቆሰሉትን ሰው አይቶት ገለል ብሎ አለፈ፤» ማለት፦ ሌዋውያን ካህናት ሲሠዉት የኖሩት መሥዋዕት የፈሰሰው ሁሉ የእንስሳት ደም ወንበዴዎች የተባሉ አጋንንት በነፍስም በሥጋም ላቆሰሉት አዳም አልጠቀመውም አልረባውም አላዳነውም ማለት ነው። ይኽንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ «የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን እንዲያስወግድ የማይቻል ነውና። . . .  መሥዋዕትንና መባን በሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕትንም ስለኃጢአትም የሚሠዋ መሥዋዕትን አልወደድህም፥ በእርሱም ደስ አላለህም። . . . ሊቀ ካህናትም ሁሉ ዕለት ዕለት እያገለገለ ኃጢአትን ሊያስወግዱ ከቶ የማይችሉትን እነዚያን መሥዋዕቶች ብዙ ጊዜ እያቀረበ ቆሞአል።፤» ብሏል። ዕብ ፲፥፬-፲፩። በመሆኑም ከሊቀ ካህናቱ ከአሮን ጀምሮ እስከ ሊቀ ካህናት ሐና እና ቀያፋ ድረስ የተሠዋው መሥዋዕት ከአዳም ኃጢአት ዓለምን ማዳን አልቻለም። እነርሱ ራሳቸውም አልዳኑም።
፩፥፱፦ ደጉ ሳምራዊ፤
          ሳምራውያን፦ በሰማርያ የኖሩ ህዝብ ናቸው። ሰማርያ ከኢየሩሳሌም በስተሰሜን ስድሣ አምስት .. ርቆ የሚገኝ ከተማ ነው። የእስራኤል ንጉሥ ዘንበሪ ተራራውን ገዝቶ ከተማ ሠርቶበት መናገሻም መስገጃም አድርጎታል። ፩ኛ ነገ ፲፮፥፳፬-፴፪። የሰሜኑ መንግሥት አንዳንድ ጊዜ ሰማርያ እየተባለ ይጠራ ነበር። ፩ኛ ነገ ፲፫፥፴፪ አሞ ፫፥፱። በአዲስ ኪዳን ዘመን በገሊላና በይሁዳ መካከል ያለው ሀገር ሰማርያ ይባል ነበር። ዮሐ ፬፥፬ የሐዋ ፩፥፰
          የአሦር ነገሥታት ስልምናሶርና ሳርጎን ሰማርያን ከያዙ በኋላ ዋና ዋና የተባሉ ሰዎችን ማርከው ወስደው ነበር። በእነርሱም ምትክ ብዙ ሰዎችን ከልዩ ልዩ አገር አምጥተው አስፍረዋል። እንዲህም ማድረጋቸው ለሃይማኖትና ለሀገር የሚቆረቆር ሰው እንዳይኖር ነው። ቀስ በቀስ በመጀመሪያ፦ ሥርዓታቸውን ባሕላቸውን ታሪካቸውን ቀጥሎም ሃይማኖታቸውን ለማጥፋት ነው። የመጡትም ሰዎች ከአይሁድ ጋር እየተጋቡ ተዋለዱ። በሂደትም ፈሪሃ እግዚአብሔር እየጠፋ፥ የድፍረት ኃጢአት እየሰፋ ሄደ። በዚህም ምክንያት የአንበሳ መንጋ ታዘዘባቸው እነርሱም መዓቱን በምሕረት እንዲመልስላቸው እግዚአብሔርን ማምለክ ፈለጉ፤ በዚህን ጊዜ የሙሴን ሕግ የሚያስተምራቸው ካህን ተላከላቸው። 2 ነገ ፲፯፥፳፬-፴፫።
          አይሁድ ከባቢሎን ምርኮ ሲመለሱ ሳምራውያን አብረው የፈረሰውን ቤተ መቅደስ ለመሥራት ቀርበው ነበር። ዘሩባቤል ግን ጥንታውያን የእሥራኤል ዘር ባለመሆናቸው አልተቀበላቸውም። ዕዝ ፬፥፩-፬። ነህምያም ከእስራኤል አስወጥቷቸዋል። ነህ ፲፫፥፬-፱። ሳምራውያን በገሪዛን ተራራ የራሳቸውን ቤተ መቅደስ የሠሩት ከዚህ በኋላ ነው። ሳምራዊቷ ሴት ኢየሱስ ክርስቶስን፦ «አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ፤ እናንተ ግን ይሰግዱበት ዘንድ የሚገባው ሥፍራ በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ» ያለችው ለዚህ ነው። ዮሐ ፬፥፳።
          አይሁድ ከሳምራውያን ጋር አይገናኙም ነበር ከእጃቸው ተቀብለው መብላትንም ሆነ መጠጣትን እንደ ርኲሰት ይቆጥሩት ነበር። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰማርያዋን ሴት፦ «ውኃ አጠጪኝ፤» ባላት ጊዜ፦ «አንተ አይሁዳዊ ስትሆን እኔም ሳምራዊት ስሆን እንዴት ከእኔ ዘንድ ውኃ ትለምናለህ? » ያለችው በዚያ ልማድ መሠረት ነው። ዮሐ ፬፥፯። ሳምራዊ መባልም እንደ ንቀት ነበር ለእርሱ ለጌታችን ክብር ምስጋና ይግባውና፦ አይሁድ ኢየሱስ ክርስቶስን «አንተ ሳምራዊ እንደሆንህ ጋኔንም እንዳለብህ (ሎቱ ስብሐት) መናገራችን በሚገባ አይደለምን ያሉት ለዚህ ነው። ዮሐ ፰፥፵፰። ሳምራውያን ሕገ ኦሪትን እንጂ ትንቢተ ነቢያትን አይቀበሉም ነበር።
          ደጉ ሳምራዊ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው። ሳምራዊ ማለት ሀገር ጠባቂ ማለት ነው፥ እየሱስ ክርስቶስም እረኛችን ጠባቂያችን ነው፤ ዮሐ ፲፥፲፩ ፣፩ኛ ጴጥ ፪፥፳፬። ሀገር ጠባቂ ሀገርን የሚጠብቀው ራሱን ለሞት አሳልፎ በመስጠት ነው፥ እየሱስ ክርስቶስም እኛን በነፍስም በሥጋም የጠበቀን ራሱን ለመስቀል ሞት አሳልፎ ሰጥቶ ነው፤ የሳምራዊ ትውልዱ ከሕዝብ (ከእስራኤል) እና ከአሕዛብ ነው፥ የኢየሱስ ክርስቶስም ትውልዱ ከሕዝብም ከአሕዘብም ነው።
          ደጉ ሳምራዊ ቊስለኛውን በሩቅ አይቶ አዘነለት ፥ቀርቦም በቊስሉ ላይ ወይንና ዘይት አፈሰሰለት፤ ወይኑ፦ የቊስለኛውን ደም እንዲያቆምለት እንዲያደርቅለት ነው። ቊስል ቶሎ የሚደርቀው ከላይ ነው፥ ወዲያውም እየተሰነጣጠቀ ያሰቃያል፤ ለዚህም መከላከያ እንዲያለሰልስለት ዘይቱን አፍስሶለታል። ጌታችንም በሩቅ ማለትም በሰማይ መንበሩ ተቀምጦ ቊስለኛውን አዳም በዓይነ ምሕረቱ አየው ገጸ ምሕረቱን መለሰለት፤ ቀረበውም። (ባሕርዩን ባሕርይ አደረገ የባሕርዩ መመኪያ ከሆነች ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ ያንን ተዋሕዶ ሰው ኹኖ ተወለደ) ወይን እንደማፍሰስ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ ሥጋውን ቆረሰለት ደሙን አፈሰሰለት። ጌታችን የጸሎተ ሐሙስ ዕለት ወይኑን በጽዋ አድርጎ፦ «ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው፤» ያለው ለዚህ ነው። ማቴ ፳፮፥፳፯።
          እንደ ዘይት ደግሞ የመንፈሰ ቅዱስን ጸጋ ሰጥቶታል። ይኽንን በተመለከተ ቅዱስ ዳዊት፦ «ወይን (የክርስቶስ ደሙ) የሰውን ልብ ደስ ያሰኛል፥ ዘይትም ፊትን ያበራል (መንፈስ ቅዱስ ሰውን ብሩኅ መልአክ ያስመስለዋል) እህልም (የክርስቶስ ስንዴ ሥጋው) የሰውን ጉልበት (ነፍስን) ያጠናክራል።» ብሏል። መዝ ፻፫፥፲፭። ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስም፦ «እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋልና ሁሉንም ታውቃላችሁ።» ያለው ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ነው።
          ደጉ ሳምራዊ ከአህያው ወረዶ ቊስለኛውን ማስቀመጡ የሚያመለክተው፦ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ መንበሩ መውረዱንና የአዳምን ሥጋ በዕርገት በሰማይ መንበሩ ማስቀመጡን ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «በኢየሱስ ክርስቶስ በሰማያዊ ሥፍራ ከእርሱ ጋር አስቀምጠን፤» ያለው ይኽንን ምሥጢር ይዞ ነው። ኤፌ ፪፥፯። ምክንያቱም በተዋሕዶ አምላክ የሆነ ሥጋ በሰማይ የእሳት መንበር ተቀምጧልና። ቅዱስ እስጢፋኖስ በመከራው ጊዜ ሰማይ ተከፍቶለት(ምሥጢር ተገልጦለት) ፊት ለፊት አይቷል። የሐዋ ፯፥፶፭።
          ደጉ ሳምራዊ፦ ያከመውን ቊስለኛ ለእንግዶች ቤት ጠባቂ ማስረከቡ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ ፈሳሽነት ያከማቸውን ምእመናን ለመምህራን የማስረከቡ ምሳሌ ነው። ቅዱስ ጴጥሮስን፦ «ግልገሎቼን አሰማራ ጠቦቶቼን ጠብቅ በጎቼን አሰማራ፤» ያለው ለዚህ ነው። ዮሐ ፳፩፥፲፭። ሁለት ዲናሮች ደግሞ የሁለቱ ማለትም የብሉይ ኪዳንና የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ምሳሌዎች ናቸው። የሰው ሕይወቱ የሚጠበቀው በእነዚህ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ «የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣፅ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።» ያለው ለዚህ ነው። ፪ኛ ጢሞ ፫፥፲፮። በኤፌሶን መልእክቱም ላይ «በሐዋርያት (በአዲስ ኪዳን) እና በነቢያት (በብሉይ ኪዳን) መሠረት ላይ ታንጻችኋል የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።» ብሏል። ኤፌ ፪፥፳።
          እግዚአብሔር፦ ነቢዩ ሕዝቅኤልን፦ «የሰው ልጅ ሆይ! ያገኘኸውን ብላ፤ ይህን መጽሐፍ ብላ፤ ሄደህም ለእስራኤል ልጆች ተናገር።» ያለው ቅዱሳት መጻሕፍትን ነው። እርሱም፦ «የሰው ልጅ ሆይ! አፍህ ይብላ፤ በምሰጥህም በዚህ መጽሐፍ ሆድህን ሙላ አለኝ። እኔም በላሁት፤ በአፌም ውስጥ እንደ ማር ጣፈጠ፤» ብሏል። ሕዝ ፫፥፩-፬። በመሆኑም፦ በሁለት ዲናር የተመሰሉ ቅዱሳት መጻሕፍት ምግበ ነፍስ ናቸው። ቅዱስ ዳዊትም፦ «ቃልህ ለጉሮሮዬ ጣፋጭ ነው፤ ከማርና ከወለላ ይልቅ ጣፈጠኝ።» ብሏል። መዝ ፻፲፰፥፻፫።
          ደጉ ሳምራዊ የእንግዳ ቤት ጠባቂውን፦ «ከሁለት ዲናር በላይ ብታወጣ እኔ በተመለስኩ ጊዜ እከፍልሃለሁ፤» አለው እንጂ፥ «ዋጋ የለህም፤» አላለውም። ይህም የሚያመለክተው፦ መምህራን የተሰጣቸውን፦ ሁለት ዲናር (ብሉይ ኪዳንን እና አዲስ ኪዳንን) ይዘው የምእመናንን ሕይወት ለመጠበቅ ሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍትን ቢጽፉ፥ ጌታ ሲመጣ የድካማቸውን ዋጋ እንደሚከፍላቸው ነው። ቅዱሳን ሊቃውንት፦ መጽሐፍ ቅዱስን ለማብራራት ንባቡን በመተርጐም ምሥጢሩን በማራቀቅ አያሌ መጻሕፍትን ጽፈዋል። እነዚህም አዋልድ መጻሕፍት ይባላሉ። የቅዱሳት መጻሕፍት ልጆች ማለት ነው። የገድል የድርሳን እና የተአምር መጻሕፍት ቊጥርም ከአዋልድ መጻሕፍት ነው። እነርሱም የእግዚአብሔር ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል እንዴት እንደፈጸሙ፥ መንፈሳዊ ሕይወታቸውን የሚያሳይ ነው። መጻፍ ማጻፍም መስማት ማሰማትም ዋጋ አለው።
          እንግዲህ በተሰጡን ሁለት ዲናሮች ሥራ እንድንሠራ ሌሎችንም ቅዱሳት መጻሕፍት በመጻፍና በማጻፍ እንድንመክርና እንድንመክር የተሰጠንን አደራ እንድንጠብቅ በዚህ ዓለም ተዋርደን ምእመናን የሚከብሩትን ግብር ይዘን እንድንገኝ የሚያዝን ልቡና እንዲሰጠን የምናቆስል ሳይሆን የቆሰሉትን የምናክም እንዲያደርገን፥ የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን አሜን።

SOURCE: www.betedejene.org

No comments:

Post a Comment