13

.

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው::" የማቴዎስ ወንጌል 7: 4

"እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅናወተት ግዙ።" ትንቢተ ኢሳይያስ 55 : 1

Friday, November 18, 2011

“ማር ይስሐቅ”


በክንፈ ሚካኤል
በአብ ስም አምነን አብን ወላዲ ብለን፤ በወልድ ስም አምነን ወልድን ተወላዲ ብለን፤ በመንፈስቅዱስ ስም አምነን መንፈስቅዱስን ሠራጺ ብለን፤ ምንም ለአጠይቆ አካላት ሦስት ስላልን በባሕርይ፣ በህልውና አንድ አምላክ ብለን አምነን ንዑድ ክቡር የሚሆን የአባታችን የማር ይስሐቅን ነገር የሚናገር መጽሐፍን እናስተዋውቃለን።


ይህን መጽሐፍ ማር ይስሐቅ ተናግሮታል። የማር ይስሐቅ ብሔረ ነገዱ ሀገረ ሙላዱ ሶርያ ነው። መጽሐፍ የተማረበት ምሥጢር ያገመረበት ቂሳርያ ነው። ቂሳርያ ለምን ሄደ ቢሉ ከኤፍሬም ዘንድ። የኤፍሬም ሀገሩ ሶርያ አይደለምን ቢሉ ለዚህስ ምክንያት አለው፤ አርዮስ ሎቱ ስብሐት ወልድ ፍጡር በባሕርየ መለኮቱ አለ፤ ንጉሡ ቆስጠንጢኖስ ጉባኤ በኒቅያ ይሁን ብሎ አዋጅ ነገረ። በዚህ ምክንያት ሦስት መቶ አሥራ ስምንት ሊቃውንት ተሰበሰቡ። ከኒህ አንዱ ያዕቆብ ዘንጽቢን ሲሆን ቅዱስ ኤፍሬምም የያዕቆብ ዘንጽቢን ደቀ መዝሙር ነው። ከጉባኤው ሲሄድ አስከትሎት ሄዷል። አርዮስን ረተው ለይተው ሲመለሱ ቂሳርያ አደሩ። በዚያን ሌሊት ራእይ ያያል። ዓምደ ብርሃን ተተክሎ ጨለማውን ሲያርቀው አየ። ማን እንደሆነ ግለጽልኝ ብሎ ቢያለመክት ባስልዮስ ዘቂሳርያ መሆኑን ገለጸለት። የእርሱን ነገር ስለምን ገለጸለት ቢሉ በቦታ ቢለይ በማዕረግ እንዳልተለየ ለማጠየቅ ነው። በዓምድ መታየቱ ስለ ምንድን ነው ቢሉ ዓምድ ቤትን ያጸናል እርሱም የምእመናንን ልቡና ያጸናልና ነው። ብርሃኑ ጨለማውን እንዲያርቅ እርሱም ከምእመናን ልቡና ክህደትንና ድንቁርናን ያርቃልና ለምክንያት ዓምደ ብርሃኑ ታየው። ለጊዜው ልቅር ብሎ አሰበ፤ ኋላ ግን እንኳን መምህር ሌላውን ቢሆን ያወጡትን ከቦታው አግብቶ መሄድ ይገባልና መምህሩ ያዕቆብ ዘንጽቢን ከቦታው አግብቶ ተመልሷል። መመለሱም ስለሦስት ነገር ነው፤ በዓይነ ነፍስ ያዩትን በዓይነ ሥጋ ማየት ይገባልና። ዳግመኛ ከእንደዚህ ያለ ሰው ቢጫወቱ ጸጋ ክብር ይገኛልና፤ ሦስተኛ የመንፈስቅዱስ ይሆን ወይስ ሰይጣን በምትሃት ተጫውቶብኝ ነው ብሎ ተመለሰ። ስለተመለሰ እንዳየው ሁኖ አላገኘውም። ኩፋር ለብሶ፣ ኩፋር ጠምጥሞ፣ ገበታው የወርቅ፣ ወንጌል በወርቅ አትሮንስ አዘርግቶ፣ ጉባኤ ሰርቶ ሲያስተምር አገኘው። “ወተኀዘበ ልቡ ለኤፍሬም” እንዲል ልቡናው ተጠራጠረበት። “እስመ ውስተ ምይንት ነፍስ ኢተኀድር ጥበብ ወውስተ ሥጋ ዘቅኑይ ለኃጢአት ኢየኀድር መንፈስ” ይላል፡ በውኑ በእንደዚህ ያለ ሰው ጸጋ እግዚአብሔር ታድራለእን በምኑናን በትሑታን ታድራለች እንጂ አለ። በኋላ ግን አራት ነገር አይቶ ተረዳ፤ መጀመሪያ ካፉ ነጸብራቀ እሳት እየወጣ ሕዝቡን ሲዋሃዳቸው ያያል። ሁለተኛ ርግብ በራሱ ላይ ተቀምጣበት ተመለከተ። ሦስተኛ ተሐዋስያን ከልብሱ ላይ ሲያርፉ እሳት እንደገባ ጅማት እርር ኩምትር እያሉ እንደ ቆሎ ሲረግፉ ያያል። አራተኛ ሰርሖተ ሕዝብ ካደረገ በኋላ “ኤፍሬምን ጥሩልኝ” ብሎ በስሙ አስጠራው። እርሱም “አስቀድሞ ካየሁት አሁን የሰማሁት ይብለጥ ስሜን አያውቅ ሀገሬን አይጠይቅ” ብሎ አደነቀ። በመጣም ጊዜ ባስተርጓሚ ሲጫወቱ “ቋንቋህ ይገለጽልኝ ዘንድ ጸልይልኝ” አለው። ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክት የባስልዮስ ቋንቋ ጽርዕ ነበር፤ የኤፍሬም ቋንቋ ሱርስት ነበርና ለባስልዮስ ተገልጾላቸው ሲጫወቱ አድረዋል። አሰናብተኝ ልሂድ ቢለው “መች ልትሄድ መጥተሃል” ብሎ ሕዝባዊ ነበር ቢሉ ዲቁና፤ ዲያቆን ነበር ቢሉ ቅስና ሹሞት ባጠገቡ የሚያስተምር ሆኗል። በዚህ ጊዜ ማር ይስሐቅ ተወለደ። ለትምህርት ሲደርስ አባት እናቱ ከኤፍሬም ዘንድ ሰደዱት ስለምን ቢሉ አጎቱ ነውና ተግቶ ነቅቶ ያስተምረዋል ብለው አንድም ሕጻን ከእናት ከአባቱ ካልተለየ አይማርም ብለው እንዲማር አንድም የተማረ ግብረ ገብ ነበርና ወደ እርሱ ዘንድ ሰደዱት። ማር ይስሐቅም ብሉይንና ሐዲስን ተማረ፣ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን አጸና። ከዚህ በኋላ እናትና አባቱ የካህን ሙያ እንደተማረ የጨዋ ሙያ ይማርልን ስደድልን አሉት፤ ሲሔድ ሕሊና ሥጋዊ ሕሊና መንፈሳዊ ሰውነቱን እንደ ሜዳ አድርገው ይራወጹበት ጀመረ። ሕሊና ሥጋዊ የካህን ሙያ ተምሬ በላይ እንደሆንሁ የጨዋ ሙያ ተምሬ በላይ እሆናለሁ ማለት ነው፤ ይህስ ትዕቢት ነው ብሎ በሕግ ጸንቼ ሥጋውን ደሙን ተቀብዬ ገንዘቤን መጽውቼ እኖራለሁ ማለት ነው። ሕሊና መንፈሳዊ ዓለም እንደ ጥላ ያልፋል እንደ አበባ ይረግፋል ብሎ መተው ነው። አንድም አንድ ወገን በሕሊና ሥጋዊ ቆሞ ለሕሊና መንፈሳዊ አጋዥ  ሆኖ ከዚህ ደርሼ ልምጣ ብሎ ዱር ለዱር ሄዶ ከአባ እብሎይ ገዳም ገባ። 25 ዓመት ገዳሙን እያገለገለ ዓይነ ምድር እየማሰ ቆየ። አባ እብሎይ ሲያርፉ እርሱን ባየሁበት ቦታ ማንን አያለሁ ብሎ አናብስት፣ አናምርት፣ አክይስት፣ አቃርብት ካሉበት ልምላሜ ዕጽ ነቅዐ ማይ ከሌለበት ሄደ ከዚያ ተገልጾለት ማር ይስሐቅን በጽርዕ ቋንቋ ጽፎታል።
ማር ይስሐቅን ከጽርዕ ወደ ዓረብ የሚመልሰው ጠፍቶ ለብዙ ጊዜያት ቆየ። በኋላም ኒክፋር የሚባል ሊቀ ጳጳስ ስምዖን ሚካኤል የሚባሉ ኤጲስ ቆጶሳት ረብ (ጥቅም) እንዳለበት አውቀው የሚመልስላቸው አጥተው ይኖሩ ነበርና ከብዙ ጥረት በኋላ አንድ ግብር የገባ የተማረ ቋንቋ የሚያውቅ ዲያቆን ተገኝቶ እርሱ ተርጉሞላቸዋል። ወደ ሀገረ ኢትዮጵያ መቼ መጣ ቢሉ ፊልክስዮስ በአጼ ድልነዓድ (ሠይፈ አርአድም) ጊዜ ሲገባ ማር ይስሐቅ ወደ ግዕዝ የተተረጎመበት ጊዜ ባይታወቅም በሰሊክ ዘደብረ ሊባኖስ የተድባበ ማርያም መነኩሴ በአጼ ገላውዴዎስ ጊዜ ተርጉሞታል የሚል ታሪክ አለ።
መጽሐፈ መነኮሳት የሚባሉት ሦስት መጻሕፍት ሲሆኑ እነዚህም ፊልክስዮስ፣ ማር ይስሐቅና አረጋዊ መንፈሳዊ ሲሆኑ፤ ፊልክስዮስ የቅዱሳን መነኮሳትን ታሪካቸውን ይናገራል፣ ዓረጋዊ መንፈሳዊ ጸጋቸውን ማዕርጋቸውን፣ ማር ይስሐቅ ጾራቸውን፣ ግብራቸውን ይናገራል።
ከዚህ ታላቅ መጽሐፍ ውስጥ አንዱን አንቀጽ እነሆ፡-
አንቀጽ 13፡ ገጽ 148
ዝልፋ ወትረ ለነፍስከ ኦ እኁ
ወንድሜ ሰውነትህን ዘወትር ዝለፋት
ወበላ ናሁ በጽሐ ተኃልፎትኪ እምሥጋ
ከሥጋ የምትለዪበት የምታልፊበት ጊዜ ደርሷል በላት።
ለምንት ትትፌሥሒ በዘአንቲ ሀለውኪ ዮም ቦቱ ወተኀድጊዮ
ትትፌሥሒ በዘሀለውኪ ብለህ ግጠም ባለሽበት ኋላ ጥለሽው በምትሄጅ ሥራ ዛሬ ለምን ደስ ይልሻል
ዘትዴለዊ ለርእየቱ ኅዳጦ ዘመነ
እርሱን በማየት ጥቂት ዘመን ተድላ ደስታ የምታደርጊበት
ወተኃጥኢዮ እስከ ለዓለም
ኋላ ብዙ ዘመን በምታጭው
አጽምዒ ኀበ ዘቅድሜኪ
ርእዪ ሲል ነው የቀደመ ሥራሺን ዕወቂ
ወሐልዪ ዘገበርኪ ምንት ውእቱ
የሠራሽው ሥራ ምንም እንደሆነ አስቢ አለ። ጽድቅም እንደሆነ ኃጢአትም እንደሆነ ማለት ነው።
ወምስለ መኑ አኀለፍኪ መዋዕለ ሕይወትኪ
ያለ ዘመንሽን ከማን ጋራ ፈጸምሽው። ከጌታ ጋራ ነው ከሰይጣን ጋራ
አው መኑ ዘይትቄከፍ ጻማ ምግባርኪ
ደክመሽ የሠራሽውን የሚቀበልሽ ማነው። ጌታ ነው ወይስ ሰይጣን ነው
ወለመኑ ዘአስተፍሣሕኪዮ በተጋድሎትኪ
በትሩፋትሽ ማንን ደስ አሰኘሽ። ጌታን ነው ወይስ ሰይጣንን ነው
ከመ ይጻዕ ለቀበላኪ በጊዜ ፀዓትኪ
በጊዜ ሞትሽ ሊዋሃድሽ የሚመጣው ማን ነው
ወመኑ ውእቱ ዘተሐሥየ በሑረትኪ ከመ ታዕርፊ ውስተ መርሶሁ
በመንግሥተ ሰማይ አርፈሽ ትኖሩ ዘንድ በስራሽ ደስ ያለው ማን ነው። ሰይጣን አለመሆኑ በዚህ ይታወቃል። ሰይታን በመንግስተሰማይ ስንኳን ሌላ ሊያሳርፍበት እሱ ሊያርፍበት ቦታ የለውምና።
ወበእንተ ምንት ፃመውኪ ወተመንደብኪ
ለማን ብለሽ ደከምሽ ለማን ብለሽ መከራ ተቀበልሽ’ ለመንግስተ ሰማይ ብለሽ ነው ወይስ ለገሃነም ብለሽ ነው።
ወምንት ክዋኔሁ ከመ ትርብሒዮ በፍሥሐ
ደስ ብሎሽ ታገኚው ዘንድ አኳሆኑስ ምንድን ነው።
ወአይኑ ዕፀ ሕይወት ዘአጥረይኪ በዓለም ዘይመጽእ ከመ ይትቀበልኪ በጊዜ ፀአትኪ።
ነፍስሽ ከሥጋሽ በተለየች ጊዜ በመንግሥተ ሰማይ ይዋሃድሽ ዘንድ ገንዘብ ያደረግሽው ምንድን ነው። አንድም ገንዘብ ያደረግሽው ምግባር ምንድን ነው።
ወበአይ ገራህት ተዓስቡኪ (ማቴ. 20፡1-8)
በማናቸው እርሻ ሊያውሉሽ ተቃጸሩሽ ማለት በማናቸው ማዕርግ ተቃጸሩሽ በባለሠላሳው ነው በባለስልሳው ነው ወይስ በባለመቶው ነው።
ወመኑ ውእቱ ዘተከሀልኪ ላዕለ አግብዖ ሀስብ ኀቤኪ በጊዜ ዕርበታ ለፀሐየ ተፈልጦትኪ (ማቴ. 1፡ 8)
ነፍስሽ ከስጋሽ የምትለይበት ፀሐይ ዕድሜሽ በገባ ጊዜ ዋጋሽን እሰጥሻለሁ ያለሽ ማነው ጌታን ነው ዲያብሎስን ነው። ጌታ ቢሆን ክብር ይሰጣታልና ዲያብሎስ ቢሉ ፍዳ ያመጣባታልና እንዲህ አለ።
ኦ ነፍስ ሕቲ ርእስኪ
ነፍስ ሆይ ሰውነትሽን መርምሪ።
ወነጽሪ በአይ ምድር ይከውን መክፈልትኪ
እጻሽ በማናቸው ቦታ እንደሆነ እወቂ አለ። መንግስተ ሰማይም እንደሆነ ገሃነምም እንደሆነ እወቂ።
ወለእለ ይትአገሱ ኃዘናተ ወትካዛተ ወፃዕቃተ
ጭንቅ ጭንቅ ለሚሆን መከራውን ለሚታገሱ
ወዘዘዚአሁ ሥቃጣተ
ልዩ ልዩ የሚሆን ሥቃይ ለሚታገሡ ሰዎች የሚሰጥ ክብር
ይኩነነ ለኩልነ አስተርእዮታቲከ
ለሁላችን የሚደረግ ምሥጢር የሚገለጽባት
ኀርክቦ ድልዋነ ሎቱ
ክብሩን በቅተን እናገኘው ዘንድ። አንድምይርከብነ ድልዋነ ጸጋው የበቃን ሆነን ያገኘን ዘንድ
በጸጋሁ ለመድኃኒነ
በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቸርነት
ወበአፍቅሮቱ ሰብአ
ሰውን በመውደዱ
ይእዜኒ
ዛሬ ባለው ዓለም
ወበዓለም ዘይመጽእ
በሚመጣው ዓለም
ወእስከ ለዓለመ ዓለማት
በማይፈጸመው ዓለም ሰውን በመውደዱ አሜን። በእውነት።

ውድ አንባብያን ሕይወቶን እንዲያቀኑ፣ በሃይማኖት እንዲጸኑ “ማር ይስሐቅን” አንብቡ እንላለን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ፤ ወለወላዲቱ ድንግል፤ ወለመስቀሉ ክቡር
 ምንጭ፡ ፍኖተ - ብርሃን መጽሔት በቦሌ መ/ብ/ቅ/እግዚአብሔር አብ ቤ/ክ ሰ/ት/ቤት የሚዘጋጅ

No comments:

Post a Comment