13

.

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው::" የማቴዎስ ወንጌል 7: 4

"እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅናወተት ግዙ።" ትንቢተ ኢሳይያስ 55 : 1

Wednesday, August 31, 2011

ቅዱስ ፓሊካርፕ

በአልታዬ ገበየሁ
የልጅነት ሕይወት

ምንም እንኳን የልጅነት ሕይወቱ በደንብ ባይታወቅም እንደ ሲ.ፒ ኤስ ክላርክ ገለጻ አንዲት ደግ ሴት በራእይ ቤቷን እንደሚያስተዳድርላት ስለተገለፀላት በባሪያነት እንደገዛችውና ካደገ በኋላም በንብረቷ ላይ እንደሾመችው፣ ለአንድ አንድ ጉዳዮችም ከሀገር ወደ ሀገር ስትዘዋወር ንብረቷን ለተቸገሩ ሰዎች እንዳከፈፋለ፣ ወደ ሀገሯ ስትመለስም ሌላኛው ባሪያዋ፣ ፖሊካርፐስ ያደረገውን በመንገድ ላይ እንደነገራት፣ ቤቷ ስትደርስ ግን ንብረቷ በሙሉ እንደነበረ ሆኖ በማግኘቷ ወሬውን ያወራትን ባሪያ ስለ ጥፋቱ ልትቀጣው ስትል በቅዱስ ፓሊካርፕ ምልጃ ይቅር እንደተባለ የሚገልጽ ሐተታ ይገኛል።

በራእይ 2፡8 ላይ “በሰምርኔስም ወዳለው ወደ ቤተክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ . . .” የተባለለት መልእክተኛ ቅዱስ ፓሊካርፕ እንደሆነ ብዙ አባቶች ይስማሙበታል።

ቅዱስ ፓሊካርፕ ጳጳስ ከሆነ በኋላ ስለ ማንነቱ በመጥቀስ የገለጹ ምንጮች፡
>የቅዱስ አግናጢዮስ መልእክት
>የራሱ የቅዱስ ፓሊካርፕ መልእክት ወደ ፊልጵስዮስ ሰዎች
>የቅዱስ ሄሬኔዎስ ስብስቦች
የቅዱስ ፓሊካርፕን ገድል የሚተርከው የሰርምኔሳውያን መልእክቶች ናቸው።

የቅዱስ አግናጢዮስ መልእክቶች ከሚባሉት 7ቱ መልእክቶች አራቱ የተጻፉት በሰርምኔስ እያለ ነበር። ከእነዚህ ሁለቱ የማግኔዚያና የኤፌሶን መልእክቶቹ ውስጥ ስለ ቅዱስ ፓሊካርፕ የሚናገሩ መልእክቶች ይገኛሉ። 7ኛው መልእክቱ ደግሞ የተጻፈው ለቅዱስ ፓሊካርፕ ነው። በዚህ ለእሱ በጻፈው መልእክት ውስጥ መግቢያው ላይ ለፓሊካርፕ ያለውን አመለካከት አጉልቶ በሚያሳይ መልኩ “አንተን ለማየት ያበቃኝን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ” በማለት ይናገራል።

ቅዱስ ሄሬኔዎስ ስለ ቅዱስ ፓሊካርፕ ሲገልጽ እርሱ የቀደመውንና የአሁኑን የሚያገናኝ ድልድይ እንደሆነ አድርጎ ሲሆን እርሱንም (ቅዱስ ፓሊካርፕን) በአራት የተለያዩ ቦታዎች ላይ ጠቅሶታል። እነዚህም፡
=>ቅዱስ ፓሊካርፕ ከፓፒያስ ጋር ስላለው ግንኙነት ሲጠቅስ ሁለቱም በአንድ ወቅት የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ተማሪዎች እንደሆኑ ይገልጽልናል። (Against Heresies Book.33 verse 4)

=>የሮማ ካህን ለነበረውና በኋላ ወደ መናፍቅነት ለተቀየረው ለመናፍቁ ፍሎረንስ በጻፈው የተቃውሞ መልእክቱ ቅዱስ ፓሊካርፕን ከልጅነቱ ጀምሮ እንደሚያውቀውና ያስተምር የነበረው ትምህርት ሁሉ አሁን ከተማራቸው በበለጠ በደንብ እንደሚያስታውሳቸው እየገለጸ የተናገረበት (Eusebius, Church History Book 5.20 verse 4-6 )

=>ለ ጳጳስ (ፓፕ) ቪክቶር በጻፈው መልእክት ቅዱስ ፓሊካርፕ ሮምን እንደጎበኘ፤ ይህም የሆነው በወቅቱ የፋሲካ በዓል አከባበር ላይ የተነሳውን ውዝግብ ለመፍታት እንደነበረ የገለጸበት ነው። (Church History Book 5.24 verse 16)

=>በሮማ ቤተክርስቲያን ላይ በጻፈው መልእክቱ ቅዱስ ፓሊካርፕ ያለፈውንና (የሐዋርያትን ዘመን) የአሁኑን ዘመን የሚያገናኝ አባት መሆኑን የገለጠ ሲሆን መነሻውም የሮማ አብያተክርስቲያናት የሐዋርያት የመጨረሻ አድርገው የሚናገሩት ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ ሰማዕትነት የተቀበሉበትን ዘመን 67 ዓ.ምን ሲሆን የሐዋርያን አበው መጨረሻ ብለው የሚጠሩት ደግሞ ቅዱስ ቀሌምንጦስ ዘሮምን ነው። በእሲያ አብያተ ክርስቲያናት የሐዋርያት ዘመን የሚባለው እስከ ቅዱስ ዮሐንስ ከዚህ ዓለም መለየት 100 ዓ.ም ሲዘልቅ የሐዋርያን አበው ደግሞ እስከ ቅዱስ ፓሊካርፕ ሰማዕትነት 155 ዓ.ም ድረስ ያለው እንደሆነ ይታመናል። ይሁን እንጂ በሮማ ቤተክርስቲያን የሐዋርያትን ትምህርት እስከ መጨረሻ የተማሩት አበው በእኛ ዘንድ ነበሩ የቤተክርስቲያን አስተዳደር ስልጣንም (Apostolic Succession) በእኛ በኩል ያለው ነው ትክክል ብለው ለሚሉት የተቃዉሞ መልእክት የጻፈበትና እሱ ራሱ የሐዋርያት ተማሪ የነበረውን ቅዱስ ፓሊካርፕን በዓይኑ እንዳየውና እሱም (ቅዱስ ፓሊካርፕ ከሐዋርያት የሰማውን እንዳስተማራቸው ከሱ ሰማው ያለውን በመረጃ እየጠቀሰ የጻፈበት መልእክት ነው። (Against Heresies (Book III, Chapter 3 verse 4)

የቅዱስ ፓሊካርፕን ገድል የሚተርከው የሰርምኔሳውያን መልእክት
የቅዱስ ፓሊካርፕ ሰማዕትነት
የቅዱስ ፓሊካርፕ የሰማዕትነት ገድል ጸሐፊ የሰርምኔስ ቤተክርስቲያን ስትሆን የተጻፈውም ለፊሎሜሊየም ቤተክርስቲያንና ለተቀሩት የአለም አብያተክርስቲያናት በሙሉ ነው ፤ ታሪኩም እንደዚህ ይነበባል።

በወቅቱ ክርስቲያኖች ከፍተኛ ሰማዕትነትን የሚቀበሉበት ወቅት ነበር። ኢ-አማናዊያኑም ለዚህ ሁሉ ተጠያቂ ያደረጉት ቅዱስ ፓሊካርፕን ነበር። ለዚህም እርሱን በመግደል የክርስቲያኖችን ታሪክ ለመዝጋት ስላሰቡ እርሱን ካለበት ፈልገው የሚያመጡ ወታደሮች አዘዙ። ወዳጆቹም ይህንን ሲሰሙ ከከተማ አውጥተው በገጠር ወዳለች ወደ አንድ የእርሻ ቤት እንዲሸሸግ አደረጉት። እርሱም በዚህች ቤት ጊዜውን በጸሎት ያሳልፍ ጀመር። በሦስተኛው ቀን በሰመመን የተኛበት ትራስ ሲቃጠል ራእይ አየ። አብረውት ላሉትም “በሕይወት ወደ እሳት በመጣል ሰማዕትነትን እቀበላለሁ” አላቸው። ፈላጊዎቹም ተከታትለው ያለበትን ሲያውቁ ከዛ እልፍ ብሎ ወደ ሌላ ቤት ሔደ። ባጡትም ጊዜ በዛ የነበሩ ሁለት ሰዎችን እያሰቃዩ ያለበትን እንዲናገሩ ይጠይቋቸው ጀመር፤ አንዱ አገልጋይም በመጨረሻ ያለበትን ተናገረ። ሄሮድ የሚባለው አዛዥም ወታደሮቹን ወደዛ ላከ። ምንም አሁንም ማምለጥ ቢችልም እስቲ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንይ በማለት ዓርብ ቀን ተያዘ። ወጥቶም ፈላጊዎቹን በሞቀ ሰላምታና በፍቅር ተቀበላቸው። ከእነርሱም “ይህን የተከበረን ሰው ለመያዝ ነው ይህን ያህል ድካም የተደረገው?” ያሉ ነበሩ። የሚበላና የሚጠጣ እንዲያቀርቡላቸው ካደረገ በኋላ ለአንዲት ሰዓት ታገሱኝ ብሎ ብቻውን ሊጸልይ ዘወር አለ። የእግዚአብሔርንም ጸጋ ተሞልቶ ለሁለት ሰዓት ሳያቋርጥ ፀለየ። ሊይዙት ከመጡትም ውስጥ ይህን የተከበረ ሽማግሌና የእግዚአብሔርን ሰው ተቃውመው ሊይዙት በመምጣታቸው ተጸጽተው ንሰሐ ገቡ። ጸሎቱንም ሲጨርስ በቅርብም በሩቅም ያሉትን፣ የጎበኙትን፣ የሚታየውንም የማይታየውንም፣ ስለዚህ ዓለምና ስለ አንዲቷ ቤተክርስቲያን ጸሎት አደረገ። በመጨረሻም በአህያ አስቀምጠው ወደ ከተማ ወሰዱት።

ሔሮድና የሔሮድ አባት ኒካቴስ በሰረገላቸው ይዘውት እየተጓዙ “ቄሳርን ጌታ ማለትና ለአማልክቱ መስዋዕት ማቅረብ ምን ጉዳት አለው? እንዲህ አድርገህ ራስህን ብታድን ምናለበት?” እያሉ ሊያግባቡት ሞከሩ፤ እርሱም ምንም ሳይመልስ ዝም አላቸው። አብዝተው ሲጨቀጭቁትም “እንደምትሉኝ አላደርግም” አላቸው። እነርሱም እንዳማይሆንላቸው ሲያውቁ በብዙ እየሰደቡ እየበረረ ከሚሄድ ሰረገላቸው ላይ የሰማንያ ስድስት ዓመቱን አዛውንት ወርውረው ጣሉት፤በዚህም እግሩ ተሰበረ።

ወደ ስታዲየምም ሲገባ “ፓሊካርፕ ሆይ በርታ! ማንነትህንም አሳይ!” የሚል ድምፅ ተሰማ። ይህንን ድምፅም አብረውት ያሉት ሁሉ ሰሙ። ማን እንደተናገረ ግን አላወቁም። ብዙ ሕዝብም ቅዱስ ፓሊካርፕ ማን እንደሆነ ለማየት ይረባረቡ ነበር። በዛም “እባክህ በዚህ ዕድሜህ ራስህን አታዋርድ” እያሉ እንደ ባህላቸው ሊያግባቡት ሞከሩ። በመቀጠል “በቄሳር ማል ኢኣማንያን ይጥፉ (ክርስቲያኖችን ኢ-አማንያን ብለው ያምኑ ስለነበር)” በል አሉት። እርሱም ወደ ሕዝቡ ዞሮ “ ኢ-አማንያን ይጥፉ” አለ። እነርሱም ደስ ብሏቸው “በል በቄሳር ማል፤ ክርስቶስንም ስደበው” አሉት። እርሱም “”ሰማንያ ስድስት ዓመት ሙሉ አገልግዬዋለሁ፣ አንዳች ክፉ ነገርም አልደረሰብኝም ታዲያ ያዳነኝን፣ ንጉሤን እንዴት አድርጌ እሰድበዋለሁ?” አላቸው። አገረ ገዢውም ተስፋ ባለ መቁረጥ “እባክህ በቄሳር ማል” አለው። ቅዱሱ አባታችንም “እኔ ክርስቲያን ነኝ፤ የክርስቲያን አስተምህሮ ደግሞ ምን እንደሆነ ለማዋቅ ከፈለጋችሁ ትሰሙ ዘንድ አንዲት ቀን ስጡኝ” አላቸው። አገረ ገዢውም “ሀሳብህን ቀይር አለበለዚያ ለአውሬዎች እጥልሃለው” አለው። ቅዱስ ፓሊካርፕም “እባክህ ፍጠን መጥፎውን በመልካም እንጂ መልካሙን በመጥፎ ልንለውጥ አልተማርንም” አለው። አገረ ገዢውም “አውሬዎችን ካልፈራህ ወደ እሳት እንድትጣል አደርግሃለው” አለው ። ቅዱስ ፓሊካርፕም “ለሰዓታት በርቶ በሚጠፋ እሳት ታስፈራራኛለህን? እግዚአብሔርን ለሚክዱ በፍርድ ቀን ዘለዓለም የማይጠፋ እሳት እንዳለ አስተውለሃል? ለምን ትዘገያለህ በል የፈቀድከውን አድርግ” አለው።

በስተመጨረሻ ሕዝቡ በታላቅ ድምፅ “ይህ የእስያውያን (የምስራቅ አብያተክርስቲያናት) መምህር፣ የክርስቲያኖች አባት፣ አማልክቶቻችንን የሚንቅ፣ ብዙዎችን አማልክቶቻችንን እንዳያመልኩ፣ እንዳይሰውላቸው የሚያስተምር ለአውሬዎች ይጣል” በማለት ጮኹ። አንደ ወዳጁና እንደ ጓደኛው (ቅዱስ አግናጢዮስ) ለአውሬዎች ሊጥሉት ከተዘጋጁ በኋላ ከአውሬ ጋር የሚታገሉትን የሚመለከቱ ተመልካቾች ስለሌሉ አስቀድሞ እርሱ ራሱ በራእይ እንዳየው በእሳት ይጣል ዘንድ ተፈረደበት።

እርሱን ለማቃጠል ይረዳ ዘንድም እንጨት ከሚገባው በላይ በፍጥነት ሰበሰቡ። ለዚህም አይሁድ በሚደንቅ ሁኔታ ተባበሯቸው። ልብሱንም፣ ጫማውንም አወለቀ። በአከባቢው ያሉ ክርስቲያኖችም ሰውነቱን ለመንካት ተጋፉ። በመጨረሻ እሳቱ ሲያቃጥለው እንዳይሸሽ በሚስማር ከእንጨት ጋር ሊቸነክሩት ፈለጉ። እርሱ ግን “እንደዚሁ በእሳት እንድቃጠል ተውኝ፤ ጥንካሬን የሰጠኝ ከእሳትም እንዳልወጣ ይረዳኛል” አላቸው። እነርሱም በሚስማር መምታቱን ትተው እጁን ወደ ኋላ አሰሩት። እርሱም ለመስዋዕት ተመርጦ እንደቀረበ አውራ በግ ራሱን ለመስዋዕትነት አቀረበ ፤ እንዲህ በማለትም ጸለየ፦

“ሁሉን ቻይ የሆንከው፣ የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ፣ የቅዱሳንና የመላእክት ሁሉ ፈጣሪ፤ አንተን ያወቅንበት የተወዳጁና የቅዱሱ ልጅህ የኢየሱስ ክርስቶስ አባት ሆይ በዚህች ቀንና ሰዓት ስለ አንተ ሰማዕትነትን ከተቀበሉት ጋር፣ ክርስቶስ ከተቀበለው ጽዋ ጋር፣ ሕያው ለሚሆን ለማይበሰብስና ለዘለዓለም የነፍስና የሥጋ ትንሣኤ ስላበቃኸኝ አመሰግንሃለሁ። . . .” ይህንን ብሎ ሲጨርስ እሳቱን ለኮሱት። ይሁን እንጂ እሳቱ ምንም ጉዳት አላደረሰበትም ፤ ይልቅስ በወቅቱ የሚያስደስት መዓዛ ያለው ሽታ ከእሳቱ ይወጣ ነበር። እነርሱም በጦር እንዲወጋ አደረጉ። በዚህም እሳቱን እስኪያጠፋ ድረስ ብዙ ደም ፈሰሰው። በወቅቱ ክርስቲያኖቹ ሥጋውን ለመውሰድ ቢፈልጉም “ሥጋውን ይዘው ክርስትናን ያስፋፉበታል” በሚል እንዳይወስዱ ተከለከሉ፤ ከዛም በእሳት አቃጠሉት። ክርስቲያኖችም አጥንቶቹን እና አመዱን ወስደው አስቀመጡት። እግዚአብሔር በፈቀደ ሰዓትም በዚህ ሰማዕት አጽም ዙሪያ በመሰባሰብ በደስታ በዓሉን ይዘክራሉ፣ ያስባሉ።

የሰማዕትነቱ ቀን
አንድ አንድ ምንጮች ዕለተ ዕረፍቱን ቅዳሜ የካቲት 23 ቀን 155/156 ዓ.ም በ8፡00 ሰዓት እንደሆነ ሲገልጹ በስንክሳራችን ግን በየካቲት 29 167 ይታሰባል።

የቅዱስ ፓሊካርፕ መልእክት ወደ ፊልጵስዮስ ሰዎች
ቅዱስ ፓሊካርፕ ይህንን መልእክት የጻፈው ቅዱስ አግናጢዮስ የፊልጵስዮስ ሰዎችን ጎብኝቶ ከሄደ በኋላ ነው። የጻፈበት ምክንያትም የሚያጽናና እና የሚያበረታታ ምክር ጻፍልን፤ እንዲሁም በእጅህ የሚገኙ የቅዱስ አግናጢዮስ መልእክቶች ካሉ ላክልን ብለው በጻፉለት መሠረት ነው። ከመልእክቱም በከፊል እነሆ፦

1. “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የማያምኑትን እግዚአብሔር የልጁን ደም ከእነርሱ ይፈልጋል። ልጁን ከሙታን ያስነሣ እኛንም ያስነሣናል። ፍቃዱን እንፈጽም፣ ትእዛዙንም እናክብር እርሱ የሚወደውንም እንውደድ። ከርኵሰት ራቁ፣ ለምድራዊ ሀብትም አትጓጉ፣ ገንዘብን አትውደዱ፣ ክፉ አትናገሩ፣ በሐሰት አትመስክሩ፣ በክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፣ አትፍረዱ፣ ይቅርታንና ምሕረትን አድርጉ” እያለ ጌታችን በማቴ 5 ላይ ያስተማራቸውን ስድስቱን ቃላተ ወንጌልን እየጠቀሰ ይመክራቸዋል። 2

2. ስለ ቅድስና የምጽፍላችሁ ራሴን እንደ አንዱ ቆጥሬ አይደለም ፤ ጻፍልን ስላላችሁኝ ነው እንጂ። እኔም ሆንኩ ማናችንም የተባረከው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ደረሰበት ጥበብ አልደረስንም። እሱ በመካከላችሁ በነበረበት ጊዜ ስለ እውነት ቃል አስተማራችሁ። ከእናንተ ሲለይ መልእክት ጻፈላችሁ። አስተውላችሁ ካጠናችሁት ወደ ተስፋ የሚያደርሳችሁ፣ በእምነት የሚያሳድጋችሁ፣ ለእግዚአብሔርና ለጎረቤቶቻችሁ ፍቅር እንዲኖራችሁ የሚያደርግ ነው። 3

3. የገንዘብ ፍቅር የኃጢአት ሥር ነው። ወደዚች ምድር ስንመጣ ምንም ይዘን እንዳልመጣን ስንሔድም ምንም ይዘን አንሔድም። የጽድቅን ጥሩር እንታጠቅ። መጀመሪያ እኛ ለራሳችን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ማክበርን እንማር። በመቀጠል ሚስቶቻችሁ በተሰጣቸው እምነት እንዲሔዱ፣ በንጹህ ፍቅርና በእውነት ባሎቻቸውን እንዲወዱ፣ ሁሉንም ሰው በእኩል ዓይን እንዲመለከቱ፣ ልጆቻውን እግዚአብሔርን ማወቅንና መፍራትን እንዲያስተምሩ አስተምሯቸው። መበለቶችን አዘውትረው መጸለይና ክብራቸውን መጠበቅን አስተምሯቸው። ስም ከማጥፋት፣ ክፉ ከመናገር፣ በሐሰት ከመመስከር ራቁ። እንዲሁም ምንም ዓይነት ምክንያት፣ ሰበብ ወይም የልብ ምሥጢር ከእግዚአብሔር እንደማይሰወር እወቁ። 4

4. ለዲያቆናት፡ የእግዚአብሔርና የክርስቶስ አገልጋይ እንጂ የሰው ስላልሆናችሁ በቅድስናው ፊት ነውር የሌለባችሁ ሁኑ። መንታ ምላስ፣ ስም ማጥፋት፣ የገንዘብ ፍቅር ከእናንተ ይራቅ። ለወጣቶች፡ በሁሉ ነገር ነውር የሌለባቸሁ ይሁኑ፣ በተለይ ንጽህናቸውን ለመጠበቅ ይጠንቀቁ። እንደ ሙሽራ ራሳቸውን ከክፉ ነገር ሁሉ ይጠብቁ። በዚህ ነው ከዚህ ዓለም የዝሙት ወጥመድ የሚያመልጡት። ይህ የመንፈስ ጠላት ነው። ዝሙት፣ መሽቀርቀር እና ርኵሰት የእግዚአብሔርን መንግሥት አያስወርስም። ደናግላንም ነውር የለሽና፣ ንጹሀን መሆን አለባቸው። እግዚአብሔር እንደማይዘበትበት በማወቅ ትእዛዙን በማክበር እንኑር። ታጋሽ፣ ርህሩህ፣ ጠንካራ ሰራተኛ፣ በክርስቶስ እውነት የምንጓዝ እንሁን። በዚህ ዓለም እሱን ካስደሰትነው፣ የሚቀጥለው ዓለምም ወራሾች እንሆናለን። ቃል እንደገባልንም ከሙታን ያስነሳናል፤ በእርሱ ካመንንና እንደሚገባው ሆነን ከኖርን ከእርሱጋርም ገዢዎች እንሆናለን። 5

5. ካህናት ሩህሩሆች፣ መሐሪዎች፣ የሚቅበዘበዙትን የሚመልሱ፣ በሽተኞችን የሚጎበኙ፣ መበለቶችን፣ ወላጅ አልባዎችን፣ ድሆችን የማይተዉ ነገር ግን በእግዚአብሔር ዘንድም በሰው ዘንድም የሚያስፈልጋቸውን የሚያቀርቡላቸው ይሁኑ . . . ። 6

6. ማንም ክርስቶስ በሥጋ እንደተወለደ የማያምን የክርስቶስ ጠላት ነው። የመስቀሉን ነገር የማይመሰክር እርሱ ዲያብሎስ ነው። ማንም የክርስቶስን ድንቅ ስራ ለራሱ ፈቃድ በመቀየር ትንሣኤ ሙታን የለም የሚል፣ ፍርድ የለም የሚል እርሱ የሰይጣን የበኩር ልጅ ነው። ስለዚህ የእነዚህን ከንቱ አስተምህሮ በመተው ከመጀመሪያው ለእኛ ወደተሰጠን ቃል እንመለስ ፤ በጾምና በጸሎትም እንጠብቀው። . . . 7

7. መታዘዝንና የቅድስናን ስራ እንድትሰሩ አሳስባችኋለው። በዓይናችሁ ያያችሁትን የተከበረውን የአግናጢዮስን፣ የዞሲመስን፣ የሩፈስን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ከእናንተ ጋር ያሉትን እያያችሁ እንዲሁም ቅዱስ ጳውሎስና ሌሎች ሐዋርያት ይህችን ዓለም እንደማትገባ አውቀው በእምነትና በቅድስና እንጂ በከንቱ እንዳልደከሙ ፣ አሁንም አብረውት ከተሰቃዩት ከጌታ ጋር የሚገባቸው ቦታ ላይ እንዳሉ እያሰባችሁ የትዕግስትንም ነገር ተለማመዱ። 9

8. መልካም ስታደርጉ አታበላልጡ። ምጽዋት ከሞት ትታደጋለች። 10

9. በአንድ ወቅት በእናንተ መካከል ካህን ስለነለበረው ስለ ቫለንስ በጣም አዝናለሁ። እርሱ ካህን የነበረ ቢሆንም በቤተክርስቲያን የተሰጠው ቦታ ምን ያህል ትልቅ እንደሆነ አልተረዳም። . . . ስለ ጌታ ፍርድ የማያውቅ ማን አለ? ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረው ፣ ቅዱሳን በዓለም እንደሚፈርዱ አታውቁምን? ወንድሞች ሆይ ስለ ቫለንስ እና ስለ ባለቤቱ በጣም አዝናለሁ። ጌታም እንደ ጣላት ሳይቆጥረው ለንሰሐ ያበቃው ዘንድ እመኛለሁ። እናንተም እንደ ተቸገሩና እንደ ጠፉ አባሎቻችሁ በመቁጠር ወደእናንተ በመመለስ ሙሉ ትሆኑ ዘንድ ስለእርሱ ልትጸልዩ ይገባል። 11

10. ቅዱስ አግናጢዮስ የእናንተን መልእክት ሰው ካገኘው እንድልክላችሁ እንደጻፈልኝ፣ እናንተም ማንም ወደ ሶርያ ቢወጣ ደብዳቤያችንን ይዞልን ይመለስ በማለት እንደጻፋችሁልኝ እኔም ሁነኛ ሰው ካገኘሁ የፍላጎታችሁን አደርጋለሁ። ቅዱስ አግናጢዮስ ለእኛ የጻፈውን መልእክትና ባጠቃለይ በእኛ ዘንድ የሚገኙ መልእክታቱን እንደጠየቃችሁን ከዚህ መልእክት ጋር አያይዘን ልከንላቸኋል። ከእነርሱም እንደምታተርፉ እናምናለን። ስለ እምነትና ስለ ትዕግስት እንዲሁም በጌታ ዘንድ ንጹህ የሚያደርጓችሁን ነገሮች ታገኙባቸዋላችሁ። ቅዱስ አግናጢየስንና አብረውት የነበሩትን እያከበራችሁ እንደ ሆነ በማወቃችን ደስ ብሎናል። 13

ይህ የቅዱስ ፓሊካርፕ መልእክት ምን ያህል በሐዲስ ኪዳን ቃላት የበለጸገ እንደሆነ ስንረዳ ዛሬ ዛሬ መጽሐፍ ቅዱስ ተበርዟል የሚሉትም ሆኑ ሌሎች ቅዱሳን መጻሕፍትን አንቀበልም የሚሉት ምንኛ ሞኝ እንደሆኑ እንረዳለን። ከዚህ ባሻገር ቅዱስ ፓሊካርፕ በዚህ መልእክቱ የሚነግረን ምክሮች በጣም የሚደንቁና ትክክለኛ ክርስቲያኖች እንድንሆን ምን ያህል እንደሚረዱን ሳንገነዘብ አንቀርም። በመጨረሻም ቅዱስ ፓሊካርፕ በዚህ በሽምግልናው ዘመን ሰማዕትነትን ለመቀበል የነበረው ቁርጠኛነት ክርስትና ምን ያህል ዋጋ የሚከፈልባት እንደሆነች እና ያለ ተጋድሎ የእግዚአብሔርን መንግሥት ማሰብ እንደማይገባን፣ የቅዱሳኑን ፈለግ መከተል እንደሚገባን እና እነርሱ ያለ ምክንያት ለነፍሳቸው እንዳልራሩ እንድናስተውል ይረዳናል።
የቅዱስ ፓሊካርፕ ጸሎቱና በረከቱ በእኛ ይደርብን ለዘለዓለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment