በስመአብ ወወልድ
ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
ከታሕሳስ 21 –
27 ኖላዊ ይባላል።
ኖላዊ ማለት
ጠባቂ ማለት ነው። ኖላዊም የተባለ ጌታችን ቅዱስ እግዚአብሔር ነው።
“ኖላዊሆሙ ለእስራኤል አጽምዕ፡ የእስራኤል ጠባቂ ሆይ፥ አድምጥ”
(መዝ. 80፡1፤ ሕዝ. 34፡1-20) ጠባቂም ቢባል መንጋውን የሚነዳ፤ ሽፍታ በጎቹን የሚነጥቅ ተኩላ ሲመጣበት የሚሸሽ አይደለም።
ስለበጎቹ ነፍሱን የሚሰጥ ቸር ጠባቂ ነው እንጂ “አነ ውእቱ ኖላዊ ኄር ይሜጡ ነፍሶ ቤዛ አባግዒሁ፡ መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም
እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል።” (ዮሐ. 10፡11)
ታሕሳስ 22 ብስራተ
ገብርኤል
እመቤታችን
ቅድስት ድንግል ማርያም የብጽዓት ልጅ ናት። ሦስት ዓመት ሲሆናት አባት እናቷ ለካህናት ሰጥተዋት ካህናትም በቤተመቅደስ ከመካነ
ደናግል አስገብተዋት 12 ዓመት በቅዱስ ፋኑኤል አማካይነት ኅብስት ሠማያዊ፤ ጽዋዕ ሰማያዊ እየመጣላት ያን እየተመገበች መላእክት
እየጎበኟት ኖራለች። አሥራ አምስት ዓመት ሲሆናት አይሁድ ለምቀኝነት አያርፉምና ሊቀ ካህናቱ ዘካርያስን “ይህች ብላቴና ቆነጀች
እሷን ሲሉ ጎረምሶች ቤተመቅደሳችንን እንዳያረክሱብን ትውጣልን” አሉት። ገብቶ እንደምን
ትሆኚ ቢላት “አኮኑ አንተ አቡየ ወአንተ እምየ ዘሀሎከ እምታሕተ
እግዚአብሔር፡ ከእግዚአብሔር በታች ያለህ አባቴም እናቴም አንተ ነህ አንተ ወደ እግዚአብሔር አመልክትልኝ እንጂ እኔ ምን አውቃለሁ?” አለችው። ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክት “ከነገደ ይሁዳ ሚስቶቻቸው የሞቱባቸውን
አስቆጥረህ በትራቸውን ሰብስበህ በቀዳማይ ሰዓተ.ሌሊት ከቤተመቅደስ አግብተህ በቀዳማይ ሰዓተ መዓልት አውጣው ምልክት አሳይሀለሁ”
አለው። 1985 በትር ሰበሰበ፤ ከዚህ በኋላ በቀዳማይ ሰዓተ ሌሊት ከቤተመቅደስ አግብቶ በቀዳማይ ሰዓተ መዓልት ቢያወጣው በዮሴፍ
በትር ላይ ‘ኦ ዮሴፍ ዕቀባ ለማርያም ፍህርትከ፤ ጠብቃት” የሚል ጽሑፍ ተቀርጾ ተገኝቷል። ዕጣም ቢጣጣሉ ለዮሴፍ ደረሰችው። ርግብም
መጥታ በራሱ ላይ አረፈችበት። ነገር ሁሉ በሦስት ምስክር ይጸናልና ዮሴፍ ይጠብቃት ብለው ሰጥተውታል። ዘመኑ የችግር ዘመን ነበርና
ለንግድ ሄደ። እመቤታችንም ባጭር ታጥቃ ማድጋዋን ነጥቃ ውኃ ልትቀዳ ሄደች። ቀድታ ስትነሳ የተጠማ ውሻ እያለከለከ መጣ። በዚያ
የነበሩ ሴቶች ሲያባርሩት እመቤታችን “ምነው ይህስ ፍጠር አይደለምን?
አያሳዝናችሁምን?” አለቻቸው። አንቺ አለባበስሽም የሥራ ፈት ይመስላል አንቺ አጠጪው አሏት። በወርቅ ጫማዋ አድርጋ አጠጥታዋለች።
ሴቶቹ ደንቋቸው ማድጋሽን አጎደልሽው ቀድቼ እንዳልመስ እንዳትይም ጉድጓዱ ጥልቅ ነው መቅጃም የለሽ አሏት። “አኮ ማይ ዘይወጽእ እምታሕቱ አላ እምላዕሉ፡ ውኃ የሚገኝ ከወደላይ ነው
እንጂ ከታች ነውን ፍጥረቱን ያጠጣ ጌታ ይሞላልኛል” አለቻቸው። በተአምራት መልቶላታል። “በዚህ ዘመን አምላክ ከድንግል ይወለዳል
ይላሉ ካንቺ ይሆን” ብለው ዘበቱባት። ወዲያው ከወደኋላዋ ቅዱስ ገብርኤል መጥቶ “ትጸንሲ” አላት። ዞር ብትል አጣችው። “አባቴ
አዳምን እናቴ ሔዋንን ያሳተ ጠላት ይሆናል” ብላ ዝም ብላ ሄደች። ከቤት ደርሳ ማድጋዋን ስታስቀምጥ ዳግመኛ “ትጸንሲ” አላት። “ይህ
ነገር ደጋገመኝ እንዲህ ያለውን ነገር ቤተመቅደስ ሄደው ሊረዱት ይገባል” ብላ ወደ ቤተመቅደስ ሄዳ በወርቅ ወንበሯ ተቀምጣ
ከደናግለ እስራኤል ጋር የተካፈለችውን ወርቅና ሐር እያስማማች ስትፈትል ቅዱስ ገብርኤል ተገልጾ “ተፈስሒ ፍሥሕት ኦ ምልእተ ጸ ጋ ፡ ጸጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ”
አላት። “እንደምን ያለ ሰላምታ ነው” ብላ አሰበች።
“ኢትፍርሂ ማርያም እስመ ረከብኪ ሞገሰ በኀበ እግዚአብሔር፡ በእግዚአብሔር
ዘንድ ባለሟልነትን አግኝተሻልና አትፍሪ እነሆ ትጸንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ ስሙንም አማኑኤል ትይዋለሽ እግዚአብሔር አምላክም
የአባቱ የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም” አላት። “ምድር ያለ ዘር ፍሬ፤ ድንግልም ያለ ወንድ ልጅ ማስገኘት ትችላለችን? እንዲህ ያለውን የምስራች ከማን አገኘኸው? እፎኑ
ይከውነኒ እንዘኢየአምር ብእሴ፤ ወንድ ስለማላውቅ እንደምን ይሆንልኛል?” አለችው። “መንፈስቅዱስ ይመጽእ ላዕሌኪ ወኃይለ ልዑል ይጼልለኪ፤ መንፈስቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል የልዑል ኃይልም ይጋርድሻል”
ብሎ የተቀመጠችበትን የወንበሩን እጀታ አለምልሞ “ይህን ማን
አደረገው” አላት። “እግዚአብሔር ነው” አለችው። “ይህንንም የሚያደርግ እግዚአብሔር ነው፤ እስመ አልቦ ነገር ዘይሰዓኖ ለእግዚአብሔር፤
ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና ኤልሳቤጥ እንኳን ከጸነሰች ይህ ስድስተኛ ወር ነው” አላት። “ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ፤ እንደቃልህ ይሁንልኝ ይደረግልኝ” አለችው።
ይህን ቃሏን ምክንያት አድርጎ ዋህድ ወልደ እግዚአብሔር በማኅፀኗ አደረ።
ይህ
የተደረገው መጋቢት 29 ቀን ነው። በዚህ እለት እንዲከበር
ያደረገው ግን የጥልጥልያው ኤጲስቆጰስ ቅዱስ ደቅስዮስ ነው።
ይህስ እንደምን ነው ቢሉ እመቤታችንን በፍጹም ልቡ ይወዳት ነበር። ከመውደዱም የተነሳ ብዕር ቀርጾ፤ ቀለም በጽብጾ፤ ብራና ዳምጾ
ተአምራቷን ይጽፍ ነበር። “እንደወደድከኝ ወድጄሃለሁ፤ እንዳከበርከኝ
አክብሬሃለሁ ተአምራቴን በመጻፍህም ዋጋህ ብዙ ነው” አለችው። ደስ አለው። ከዚህ የበለጠ ምን ሠርቼ ላክብራት አለ። ይህን
ሲያወጣ ሲያወርድ ጌታ ይህን በዓል እንዲያስብ አደረገው። መልአኩ ያበሰራት መጋቢት 29ን በጾም ምክንያት በሚገባ አያከብሩትም ነበረና
ከበዓለ ልደቱ ሰባት ቀን አስቀድሞ በታኅሳስ 22 ቀን ሕዝቡን ሰብስቦ በታላቅ ሥርዓት አከበረው። እመቤታችንም ተገልጻ “ደቅስዮስ ሆይ ዛሬ ይህን በዓል በማክበርህ ተአምራቴንም በመጻፍህ ይህን
ሰጥቼሃለሁ ካንተ ሌላ የሚለብሰውን የሚቀመጥበትን እበቀለዋለሁ” ብላ በሰው እጅ ያልተሠራ መንበርና የከበረ አጽፍ አውርሳዋለች።
እርሱ
ካረፈ በኋላ ሌላ ደቅስዮስ ተሾመ። “እርሱ የለበሰውን አጽፍ አምጡልኝ ልልበሰው መንበሩንም አምጡልኝ ልቀመጥበት” አለ። “እርሱ
በገድሉ በትሩፋቱ ከእመቤታችን ያገኘው ነው አንተም በትሩፋትህ አግኝ” ቢሉት “እኔ ከእርሱ በምን አንሳለሁ እርሱም ኤጲስ ቆጶስ
እኔም ኤጲስቆጶስ እርሱም ደቅስዮስ እኔም ደቅስዮስ” ብሎ የግድ አላቸው። እመቤታችንም ተአምሯን ታሳየን ብለው ከዕቃ ቤት አውጥተው
ሰጡት። ልብሱን ለብሶ በመንበሩ ሲቀመጥ የታዘዘ መልአክ መጥቶ ከነመንበሩ ገልብጦት ሞቷል።
የእመቤታችን
የቅድስተ ቅዱሣን የንጽሕተ ንጹሐን ድንግል ማርያም እናትነት፣ ረድኤት፣ በረከት እና አማላጅነት በሁላችን ላይ አድሮ ይኑር። አሜን!
ምንጭ፡-
መዝገበ - ታሪክ
የቦሌ
መንበረ ብርሃን ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤ/ክ ሰ/ት/ቤት
ወርሐ
ታሕሳስ/2005 ዓ.ም
www.holyfathersundayschool.blogspot.com
No comments:
Post a Comment