ታሕሳስ 23 ፡ ዕረፍቱ
ለዳዊት ንጉሠ እስራኤል
ዳዊት ማለት ኅሩይ ማለት ነው። አንድም ልበ
አምላክ ማለት ነው። (ሐዋ. 13፡22)
ትውልዱ
ከነገደ ይሁዳ ነው። አባቱ እሴይ እናቱ ሁብሊ ይባላሉ። ሁብሊ መልከ መልካም ሴት ነበረች። ከጎረቤታቸው ያለ ጎልማሳ መልኳን እያየ
በሐጸ ዝሙት ተነደፈ። እሴይ የእሷም ፈቃድ እንደሆነ አውቆ መንገድ እሄዳለሁ ብሎ ስንቁን ይዞ ወጣ። የሄደ መስሎ ከዚያው ውሎ ሲመሽ
በልብሱ ተሸፋፍኖ ድምጹን ለውጦ ያንን ሰው መስሎ ገብቶ ከእርሷ ጋር አድሮ ጎህ ሳይቀድ ወጥቶ ሄደ። ዳዊት በዚህ ዕለት ተጸንሷል።
“እነሆ፥ በዓመፃ ተፀነስሁ፥ እናቴም በኃጢአት ወለደችኝ።” (መዝ. 50፡5) ማለቱ ስለዚህ ነው። ተወልዶ ጉልበቱ ከጸና በኋላ የአባቱን
በጎች ሲጠብቅ አድጓል። ንጉሥ ሳኦል ከጌታ ፈቃድ በወጣ ጊዜ እግዚአብሔር ሳሙኤልን ቅብዐ መንግስሥት እነዲቀባው አደረገ። (1.ሳሙ.16፡1-13)
ከዚህ በኋላ በረድኤተ እግዚአብሔር ጎልያድን በአንድ ጠጠር ገደለ። ግዳይ ጥሎ ሲመለስ ሴቶች “ሳኦል ሺህ ገደለ ዳዊት እልፍ ገደለ”
እያሉ እየዘፈኑ ተቀበሉት። ቅንዐት አድሮበት ነገር ግን አስቀድሞ ምሎለት ነበርና የመቶ ፍልስጤማውያንን ሸለፈት ተቀብሎ ልጁ ሜልኮልን
ዳረለት። አንድ ቀን ሊገድሉት ሲማከሩ ሜልኮል ሰምታ ሽሽ አለችው። ሳዖልም ሶስት ሺህ ሠራዊት ይዞ ተከተለው፤ ከሠራዊቱ ተለይቶ
ሰውነቱን ለመፈተሽ ዳዊት ካለበት ዋሻ ውስጥ ገባ። ጨለማ ነበርና ሰው መኖሩን አላወቀም። አቢሳ ዳዊትን ጠላትህን አሳልፎ ሰጥቶሀልና
ልውደቅበት አለ። ተው ኦሪት “ኢታውርድ እዴከ ላዕለ መሲሁ ለእግዚአብሔር” ትላለችና አይሆንም አለው። እርሱ የልብሱን ዘርፍ በሰይፉ
ቀዶ ያዘ። ሲወጣ ተከትሎ ወጥቶ “ንጉሥ ሆይ ዳዊት ቢያገኝህ አይምርህም የሚሉህን ለምን ትሰማለህ እነሆ ዛሬ አሳልፎ ሰጥቶኝ ነበር።
ነገር ግን የልብስህን ዘርፍ ከመቅደዴ በቀር ምንም ምን እንዳላደረግሁህ አንተ ታውቃለህ” ብሎ ቅዳጁን አሳየው። ሳኦል “ዳዊት ወልድየ
ቃልከ ማኅዘኒ” እያለ አለቀሰ በነገሠም ጊዜ ለልጆቹ እንዲራራላቸው ቃል አስገብቶት ወደ ቤተ.መንግሥቱ መለሰው። ዳዊት ግን በረሀ
በረሀውን ሲዞር ቆይቷል።
በሐቅለ-ፋራን
ሳለ ናባል የሚባል ባለጸጋ ድግስ ደግሶ በጎቹን አሸልቶ ሲያበላ ሲያጠጣ ብላቶኖቹ “ምሳ ላክልኝ ብለህ ላክበት” አሉት። “ተው አይሆንም
ያለ እንደሆነ እጣላዋለሁ” አለችው። “ይህን ያህል ጊዜ አንዲት ጠቦት እንኳ ሳትነካ ከብቶቹን ጠብቀህለት እምቦ ይላልን ላክበት
ግድ የለህም አሉት።” እንኪያስ ሔዳችሁ ንገሩት አለ። ሄደው ቢነግሩት “የማነው ዳዊት” ብሎ አልሰጥም አለ። ዳዊት ይህን ሲሰማ
ተቆጥቶ ሊጣላው ተነሳ። ሚስቱ አቤግያ ይህን ሰምታ 5 በግ አሳርዳ አሠርታ፣ 5ቱን አሰናድታ የበለስ የወይን ጥፍጥፍ 500 እንጀራ፣
12 ጭነት ዱቄት አሲዛ ሄደች። ዳዊት ከመንገድ አገኛትና “ባልሽን ልታድኚው መጣሽን?” ብሎ ያመጣችውን ተቀብሏት ተመለሰ።
ናባል
ማታ ሰክሮ ነበርና አቤግያ ሳትነግረው አደረች። ሲነጋ ትናንት ዳዊት ሊጣላህ መጥቶ ነበር አለችው። ዳዊት ብሎ ደነገጠ። ልቡን አጥቶ
ሰንብቶ በ10ኛው ቀን መልአኩ ቀስፎታል። እመቤታችንና ጌታችን ከአብራኩ አሉና። እሷን ግን ኀዘኗን ከጨረሰች በኋላ ዳዊት ሚስት
አድርጓታል። (1 ሳሙ. ም 25)
ከዚህ
በኋላ ሳኦል ፍልስጤማውያን በጠላትነት ተነሱበት። ገጠማቸው። ከጠላቶቹ አንዱ ቀስቱን መርዝ ቀብቶ ጎኑን መታው፤ እንደ እሳት አቃጠለው።
ሎሌውን ጠርቶ “ገደልነው እንዳይሉ አንተ ጨርሰኝ” አለው። “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ ባሪያህ ካንተ ጋር እሞታለሁ እንጂ እገድልሃለውን?”
ብሎ እምቢ አለው። የገዛ ሠይፉን ከምድር ተክሎ ወደቀበት። ሌሎቹም እርሱን አይተው በገዛ ሠይፋቸው እየተወጉ ሞቱ። ዳዊት የርሱንና
የልጁ የዮናታንን ሞት ሲሰማ አዘነ። ግጥም እየገጠመ አለቀሰላቸው።
ከሳዖል
ሞት በኋላ ዳዊት መንግሥቱን አጽንቶ ጽዮንን አቅንቶ ተቀመጠ። ታቦተ.ጽዮንንም በዕልልታ በሆታ ወደከተማው አስገባ። የሳኦል ልጅ
ሜልኮል ዳዊትን በታቦተ.ጽዮን ፊት ሲዘምር አይታ በልቧ ናቀችው። ሲገባ ልትቀበለው ወጥታ “የእስራኤል ንጉሥ በባሪያዎቹ ቆነጃጅት
ፊት ዕርቃኑን በመግለጹ ምን ይከብር?” ብላ በአሽሙር ዘለፈችው። በዚህ ቢያዝንባት መካን ሆና ሞታለች። “ኢወለደት ሜልኮል እስከ
አመ.ሞተት፤ ሜልኮል እስከምትሞት ድረስ ልጅ አልወለደችም ነበር” እንዲል። (2 ሳሙ. ም.6)
በዘመኑ
የነበረ ነቢይ ነቢዩ ናታን ነው። ሊጠይቀው መጥቶ ሳለ አዝኖ አየው። “ምን ሆነህ ታዝናለህ?” አለው። “እኔ በጽድ በዝግባ በተሠራ ቤት ተቀምጬ ታቦተ ጽዮን በድንኳን ስትኖር ምነው
አላዝን?” አለ። “ጠላት ጠፍቶልሀል፤ መንግሥትህም ጸንቶልሀል አታንጽምን?” አለው። “ያስ
ቢሆን ያለፈቃደ.እግዚአብሔር ይሆናልን?” አለ። ሁለቱም ቀኖና ገቡ። የቤተመቅደስ ነገር ለናታን ተገልጾለት “አኮ አንተ
ዘትነድቅ ሊተ ቤተ፤ አንተ አይደለህም የምትሠራልኝ ከአብራክህ የተከፈለ ልጅህ ይሠራልኛል” ብሎታል። (2 ሳሙ. 7፡1-17) ለርሱ
ግን የበለጠ የሥጋዌ ነገር ተገልጾለት “ናሁ ሰማዕናሁ በኤፍራታ” ብሏል። (መዝ 131፡6)
ኢዮአብና
አቢሳ ጠላት ለመመለስ ታቦተ ጽዮንን አሲዘው ሠራዊት አስከትለው ወደ አራቦት ዘመቱ። እሱ ከከተማ ቀርቶ ነበር። በሰገነቱ ሲመላለስ
ቤርሳቤህን በአፀደ ወይን ውስጥ ስትጠጣጠብ አይቷት ፍቅረ ዝሙት አደረበት። “የማን ሚስት ናት” አለ። “የኦርዮ” አሉት። ኦርዮ
ዘምቶ ነበር። “ኢትሑር ብእሲተ.ብእሲ” (ዘጸ.20፡14-17) ያለውን ተላልፎ አስጠርቶ ደረሰባት፤ጸነሰች። ጽንስ ያሳስታልኛል ብሎ
ኦርዮን አስጠርቶ ስለጦሩ ሁኔታ ከጠየቀው በኋላ “ወደቤትህ ሂድ” አለው። እሱ ግን ድንኳን አስተክሎ ከዘበኞቹ ጋር አደረ። “አልመጣም”
ብላ ላከችበት። የሚያሰክር መጠጥ አጠጥቶ “ወደቤትህ ግባ” አለው። “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ ታቦተ.ጽዮን አእላፈ እስራኤል ዋዕየ.ፀሐዩን
ቁረ.ሌሊቱን ታግሠው በሜዳ ሲሆኑ እኔ ቤቴ ገብቼ ተድላ ደስታ አደርግ ዘንድ ይገባልን?” ብሎ እምቢ አለ። በማግሥቱ “ኦርዮን ፊት
መሪ አድርጉት ጦሩ ሲበረታ ትታችሁት ሽሹ እሱ በዚያ ይሙት” የሚል ጽፎ አትሞ “ለኢዮአብ ስጠው” ብሎ ሰጠው። የዋህ ነውና የሞቱን
ደብዳቤ ይዞ ሄዶ ሰጠው። ኢዮአብ እንደታዘዘው ኦርዮን ከፊት አሳልፈው ጦሩ ሲበረታ ተጠቃቅሰው ወደኋላ ሸሹ። እርሱ መለስ ብሎ “ምንተ
ኮንክሙ አእላፈ እስራኤል፡ ምን ሆናችሁ?” ቢላቸው ጠላቶቹ ደርሰው ልብ ራሱን ብለው ገድለውታል።
ጌታ
ለናታን ገለፀለት። ናታን ከል ለብሶ ከል ጠምጥሞ ጦር ይዞ ሄደ። ዳዊት “ነቢየ እግዚአብሔር አመጣጥህ በደኅና ነውን?” አለው።
“የምነግርህ አለኝ” አለው። “መቶ በጎች ያሉት ሰው ነበር። ከአንዲት በግ ሌላ ምንም ምን የሌለው ጎረቤት ነበረው። መንገድ ሲሄድ
አደራ ሰጥቶት ሄደ ያ ሰው እንግዳ ቢመጣበት መቶ በጎቹን አስቀምጦ የሱን አንዲት በግ አርዶ እንግዳውን ሸኘበት። እሱንም ለሰው
እንዳይነግርብኝ ብሎ ገደለው። በዚህ እግዚአብሔር አዝኗል” አለው። “ይህን የሚያደርግ በከተማዬ ካለ ሞት ይገባዋል” አለ። “ኦ
ንጉሥ ፈታሕከ በርእስከ አኮኑ አንተ ገባሪሁ ለዝ ኩሉ፤ ይህን ሁሉ ያደረግህ አንተ ነህ በራስህ ፈረድህ ባለጸጋ የተባልህ አንተ
ደኃ የተባለ ኦርዮ ነው። መቶ በጎች የተባሉ አሥሩ ዕቁባቶችህ ናቸው። አንዲት በግ የተባለች ቤርሳቤህ ናት። እንግዳ የተባለ ፈቃደ
ሥጋ ነው። ፈቃደ ሥጋህ ቢነሳብህ 10ሩ ዕቁባቶችህን አስቀምጠህ ከቤርሳቤህ ደረስህ። ኦርዮንንም አስገደልከው። በዚህ እግዚአብሔር አዝኗል” አለው። ልዋል ልደር ሳይል ዕለቱን
ጉድጓድ አስምሶ ማቅ ለብሶ ሱባኤ ያዘ።
ጥንቱን
መርጦታልና ጸሎቱን ሰማው። ነቢዩ ናታን መጥቶ “በነፍስህ ምሬሀለሁ ብሎሀል። በሥጋህ ግን ኃጢአት ያለፍዳ አይነጻምና ለሦስት ወር
ልጅህ መንግሥትህን ይነጥቅሀል፤ ዕቁባቶችን ይቀማሀል” አለው። “ይህ እንዲሆን በምን አውቃለሁ” አለ። “የሚወለደው ሕፃን ይሞታል እሷን አግባት ወንድ ልጅ ትወልድልሀለች
ስሙን ሰሎሞን ትለዋለህ” አለው። ቀን ከሌት አብዝቶ ያለቅስ ነበርና ከዕንባው ብዛት መሬቱ ርሶ ሠርዶ አብቅሎ ሰውነቱን ተብትቦ
ይዞት ነበር። ብላቴኖቹ ቆርጠው አወጡት።
ከዚህ
በኋላ ሕፃኑ ተወልዶ ታመመ። “እኔን በነፍሴ እንደማረኝ ሕፃኑንም በሥጋው ይማረው” ብሎ ማቅ ለብሶ አመድ ነስንሶ ያለቅስ ጀመር።
ሕፃኑ ሞተ ፤ ከወደቀበት ተነስቶ ተጣጥቦ ልብሰ መንግሥቱን ለብሶ ማዕድ ቀረበ። ከምሳ መልስ “ታመመ ስንልህ ማዘንህ ሞተ ስንልህ
እንዲህ ማድረግህ ስለምንድር ነው?” አሉት። “ይገብዕኑ ማይድኅረ ተክዕወ ፤ ውኃ ከፈሰሰ ይታፈሳልን? እንዲሁ ወደርሱ እንሄዳለን
እንጅ እሱ ወደኛ አይመጣም” ብሏቸዋል።
ጌታ
የተናገረው አይቀርምና ፍዳን ሊቀበል ሰይጣን የበኵር ልጁ አምኖንን በእኅቱ በትዕማር ፍቅር እንዲያድርበት አደረገ። ኢዮናዳብ የሚባል
የአጎቱ ልጅ ሰውነቱ ከስቶ ፊቱ ገርጥቶ ቢያየው “አንተ የንጉሥ ልጅ ሆነህ ምን ያከሳሀል?” አለው። “ፈርቼ እንጂ እኅቴ ትዕማርን
ወድጃታለሁ” አለው። “ታመምሁ ብለህ ተኛና አባትህ ሊጠይቅህ መጥቶ ልጄ ብላ ሲልህ በትዕማር እጅ ቢሆን ኖሮ ሁለት ሦስት እንጎቻ
በበላሁ ነበር በለው ያዝልሀል” አለው። እንደመከረው አደረገ ዳዊትም ትዕማርን አስጠርቶ እንድታሰናዳለት አዘዛት። “እኅቴ አንቺን
ብዬ እንጂ እህል የሚያቀርብልኝማ መቼ አጣሁ” ብሎ ያዛት። “ወንድሜ ይህን አታድርገው እኔን የተናቀች የተጠላች ታደርገኛለህ አንተም
ከሰነፎች እንደ አንዱ ትቆጠራለህ” አለቸው። በግድ አስነወራት። ወዐብየ ጽልዕ እንተጸልዓ ድኅረ እምቀዳሚ ፍቅር ዘአፍቀራ ይላል
ፊት ከወደዳት መውደድ ይልቅ ኋላ የጠላት መጥላት ፀና። ውጪልኝ አላት። “ከቀደመው የአሁኑ ክፋትህ ይከፋል ተወኝ” አለችው። ብላቴናውን
ጠርቶ አስወጥቶ እንዲዘጋባት አደረገ። የለበሰችውንም ባለህብር ልብስ ቀዳ አመድ ነስንሳ እያለቀሰች ስትሄድ ወንድሟ አቤሴሎም አገኛት።
አምኖን መሆኑን አውቆ “ወንድምሽ ነውና አትግለጪበት” ብሎ አጽናንቶ ዳዊት በከተማ ያሠራው ቤት ነበር ከዚያ አስቀመጣት።
ከሁለት
ዓመት በኋላ አቤሴሎም ድግስ ደግሶ ዳዊትን ጠራው። “አስቀድመህ ብትነግረኝ መልካም ነበረ አሁን ግን እኔ ስመጣ መኳንንቱ፣ መሳፍንቱ ወይዛዝርቱ ስለሚከተሉኝ ይበዛብሃል አይሆንም” አለው። “ያም ባይሆን ታላቅ
ወንድሜ አምኖን ይገኝልኝ” አለ። ይሂድልህ አለው። ከዚህ በኋላ አምኖን በልቶ ሲጠግብ፤ ጠጥቶ ሲሰክር አቤሴሎም ብላቴኖቹን አዝዞ
አስገደለው እርሱ ወደናቱ ሀገር ጌድሶር ሸሸ።
ዳዊት ለልጁ ለአምኖን አለቀሰለት። ከሁለት ዓመት በኋላ አምኖንን እየረሳ አቤሴሎምን እያስታወሰ ሄደ። ቢትወደዱ ኢዮአብ ይህን አውቆ አንዲት ቴቁሄያዊት ልኮ አስታረቀው። አቤሴሎም ከአባቱ ጋር ከታረቀ በኋላ በሠረገላ ሆኖ እስራኤልን “ምን ዳኛ አለና ይፈርድላችኋል? እኔማ ይህችን መንግሥት ጥቂት ጊዜ ባገኛት ቀን በፀሐይ ሌት በመብራት ፈርጄ ኢየሩሳሌምን አቀናት ነበር” ሲል ሰንብቶ ዳዊትን ለምኖ ሥርዓተ መንግሥት አስወጥቶ ሁለት መቶ መኳንንት ይዞ አቤሴሎም በኬብሮን ነገሠ እያለ ነጋሪት አስጎሠመ።
ዳዊት
ይህን ሰምቶ “ኑ ከኢየሩሳሌም እንሽሽ” አለ። ኢዮአብና አቢሳ እንዋጋለን አሉ። “ጌታ ልጅህ መንግሥትህን ይነጥቅሀል እዋጋለሁ አትበል
ብሎኛል አይሆንም” ብሎ ተራ ልብስ ለብሶ ተራ ጫማ ተጫምቶ ከከተማው ወጥቶ ሦስት ወራት በጫካ ሲያዝን ኖሯል። ከሦስት ወር በኋላ
አቤሴሎም ሲዋጋ ሞተ። ዳዊት ወደ ቤተመንግሥቱ ቢመለስ አሥሩ ዕቁባቶቹን ልጁ አርክሷቸው ተገኘ። እስከ ፍጻሜ ዘመኑ ሳይደርስባቸው
ቀርቷል። ከዚህም በኋላ ብዙ ጊዜ ቆይቶ “እስመ እምፍሬ ከርስከ አነብር ዲበ መንበርከ” ያለው ቃል ተፈጽሞለት ልጁ ሰሎሞንን በዙፋኑ
አስቀምጦ በነገሠ በ40 ዘመኑ በዚህች ዕለት ዐረፈ። (1 ነገ 2፡12-14)
የልበ አምላክ የቅዱስ
ዳዊት በረከቱ በሁላችን ላይ ይደር። አሜን!!
ምንጭ፡-
መዝገበ - ታሪክ
የቦሌ
መንበረ ብርሃን ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤ/ክ ሰ/ት/ቤት
ወርሐ
ታሕሳስ/2005 ዓ.ም
No comments:
Post a Comment